ብዙ ጊዜ ከመገንባት ይልቅ የሚቀለው ማፍረሱ ነው። የሐሰት ትምህርቶች በጥቂት ሳምንታት ወይም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊገቡና የብዙ ሰዎችን ሕይወት በቀላሉ ሊያጠፉ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሐሰት ትምህርት ወይም በመለያየት ከፈረሰች በኋላ እንደገና እርስዋን መገንባት ብዙ ዓመታትንና እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ይጠይቃል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቲያኖች ሕይወት ሊጠፋ የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የፈረሰውን ነገር የሚገነቡባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያንህ የፈረሰችበትና እንደገና የተሠራችበት ሁኔታ ካለ ምሳሌዎችን ዘርዝር።
መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የፈረሰው ነገር እንዴት እንደተገነባ የሚናገሩ ናቸው። ከመጽሐፈ ዕዝራ በፊት በነበሩ የታሪክ መጻሕፍት እንደተገለጸው፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ዓመፅና ኃጢአት ምክንያት፥ ባቢሎናውያን የኢየሩሳሌምን ከተማና የክብር ደመናው እንዲቀመጥበት ያዘዘውን ቤተ መቅደስ እንዲያጠፉ መፍቀዱን ተመልክተናል። አብዛኛዎቹ የይሁዳ ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት በምርኮ ተወሰዱ። በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዴት ተመልሰው ለመቋቋምና ቤተ መቅዱሱን እንደገና መሥራት እንደጀመሩ እናያለን። የአይሁድ ሕዝብ ቅሬታዎች ከምርኮ ወደ ይሁዳ ተመለሱ። ቤተ መቅደሱ፥ በመጨረሞም የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ተሠሩ። ከሁሉ በላይ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት መሥራት ነበር። ይህም ቤተ መቅደሱንና ቅጥሮቹን ከመሥራት እጅግ የከበደና ረጅም ጊዜ የወሰደ ነበር።
እስካሁን ድረስ የተመለከትናቸው የታሪክ መጻሕፍት፥ አይሁድ ወደ ምርኮ ከመሄዳቸው በፊት በነበራቸው ታሪክ ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ። እነዚህም ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ዜና መዋዕል ያሉት ናቸው። አይሁድ ከምድራቸው ተግዘው ወደ ምርኮ ከሄዱ በኋላ ስላለው ታሪከ የሚናገሩ ሦስት መጻሕፍት አሉ። እነዚህ ሦስት የመጨረሻ መጻሕፍት ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር ናቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ ዕዝራ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ከዚያም በዚህ ስፍራ ስለ መጽሐፈ ዕዝራ የተጠቀሱ ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)