የታሪክ መጻሕፍት

መጽሐፈ ኢያሱ፡- መጽሐፈ ኢየሱ በጠላት ላይ ስለሚገኝ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ርስታቸው አድርጎ ሊሰጣቸው ቃል ኪዳን ገብቶላቸው ነበር፤ ነገር ግን በከነዓን ድል መነሣት የነበረባቸው በርካታ ጠላቶች ነበሩ። መጽሐፈ ኢያሱ ሕዝቡ ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉና የተስፋይቱን ምድር እንዲወርሱ እግዚአብሔር እንዴት እንደረዳቸው ይገልጻል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ክርስቲያን ሊያሸንፋቸው ወይም ድል ሊያደርጋቸው የሚገባው ጠላቶች እነማን ናቸው? (ኤፌሶን 6፡12 ተመልከት)። ለ) እነዚህን ጠላቶች ልናሸንፍ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

መጽሐፈ መሳፍንት፡- መጽሐፈ መሳፍንት የእግዚአብሔርን ሕዝብ አለመታዘዝ የሚያሳይ አሳዛኝ ታሪክ ነው። ይህ መጽሐፍ «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳፍንት 17፡6) በሚለው ቃል ሊጠቃለል ይችላል። እግዚአብሔር መንገዳቸውን የለቀቁ ልጆቹን በጠላቶቻቸው እንዲሸነፉና በባርነት ቀንበር እንዲወድቁ በማድረግ፥ የሥነ-ሥርዓት ቅጣትን እንዴት እንደቀጣቸው የሚያሳይ ታሪክ ነው፤ ነገር ግን መሳፍንትን በመጠቀም እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው የባርነት ቀንበር እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው የሚናገርም ታሪክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ አንታዘዝም በምንልባቸው ጊዜያት እግዚአብሔር አንዳንዴ እንድንሸነፍ የሚፈቅደው እንዴት ነው?

መጽሐፈ ሩት፡- በዘመነ መሳፍንት የተፈጸመው የሩት ታሪክ ከፍተኛ የክፋት ሥራ በሞላበት ሁኔታ ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የሚኖሩ ሰዎች እንደሚገኙ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። ሩት የተባለችው ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት እግዚአብሔርን በመከተልዋ የታላቁ የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት አያት የመሆን ሽልማት እንዳገኘች የሚናገር ታሪክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ አብዛኛው ሕዝብ እግዚአብሔርን መከተል በተወበት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኞች መሆን ያለብን እንዴት ነው?

1ኛ ሳሙኤል (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ)፡- መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስራኤል በአንድ ንጉሥ ሥር እስከቆየችበት፥ እስከተባበረው የእስራኤል መንግሥት ድረስ ያለውን የሽግግር ወቅት ታሪክ የሚሸፍን ነው። የመጨረሻው መስፍን የነበረው የሳሙኤልና የመጀመሪያው ንጉሥ የነበረው የሳኦልን ታሪክ የሚናገር ነው። የመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ አብዛኛው ክፍል ሳኦልን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ይነግሥ ዘንድ ከተመረጠውና የመልካም ንጉሥ የላቀ ምሳሌ ከሆነው ከዳዊት ጋር ያወዳድረዋል። ሌሎች የእስራኤል ነገሥታት በሙሉ የሚመዘኑት ዳዊትን በመምሰላቸው ወይም ባለመምሰላቸው ነበር። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ የሚጠናቀቀው በሳኦል ሞት ነው።

2ኛ ሳሙኤል (መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ)፡- መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ መጀመሪያ በታላቁ ንጉሥ በዳዊት ላይ የሚያተኩር አንድ መጽሐፍ ነበር። መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ስለ ዳዊት መንገሥ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዳዊት በአሕዛብ ሁሉ ላይ ስላገኛቸው ታላላቅ ድሎችና የእስራኤልን ድንበር ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ እንዳሰፋ ይናገራል። የዳዊት ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በመግባቱ ሲሆን፥ በዚህ ቃል ኪዳን በእስራኤል ላይ ንጉሥ የመሆንን ሥልጣን ለዘሩ ሰጥቶአል። የመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ሁለተኛ ክፍል ግን ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ኃጢአት ያስከተላቸው ውጤቶች የተዘረዘሩበት ነው። ይህ ኃጢአት የቤርሳቤህ ባል የኦርዮንን ሞት አመጣ፤ በድጋሚም ከዳዊትና ከቤርሳቤህ የተወለደውን የመጀመሪያ ልጅ ቀሰፈ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዳዊት ቤት ላይ ችግር በዛ። የዳዊት ሴት ልጅ በግድ ተደፈረች፤ አቤሴሉም ወንድሙን ገደለ፤ ቀጥሉም በአባቱ በዳዊት ላይ ዓመፀ፤ ከዚያም አቤሴሎም ተገደለ። ዳዊት እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ ሰው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 13፡22)። ይህ ማለት እግዚአብሔርን በከፍተኛ ደረጃ የሚወድና በሙሉ ልቡ እርሱን ለመከተል የጣረ ሰው ነበር ማለት ነው እንጂ ዳዊት ፍጹም ነበር ማለት አይደለም።

የውይይት ጥያቄ፥ እንደ እግዚአብሔር ልብ መሆንን በሚመለከት ከዳዊት በሕይወት ውስጥ ከምንማራቸው ትምህርቶች አንዳንዶቹን ዘርዝር። 

1ኛና 2ኛ ነገሥት (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ)፡- እነዚህ ሁለት መጻሕፍት የእስራኤል ነገሥታትን ታሪክ ይናገራሉ። ለእግዚአብሔር ትልቅ ቤተ መቅደስ ስለሠራው ስለ ሰሎሞን ታሪክ ይናገራሉ፤ ነገር ግን የሚያሳዝነው ሰሎሞን ሐሰተኞች አማልክትን ማምለክ ጀመረ። ከሰሎሞን ሞት በኋላ እግዚአብሔር በመፍረዱ መንግሥቱ በሰሜን- እስራኤል፥ በደቡብ-ይሁዳ ተብሎ ለሁለት ተከፈለ፡ እነዚህ መጻሕፍት በሁለቱም መንግሥታት የነበሩትን ነገሥታት ታሪክ እግዚአብሔርን ይወድ ከነበረው ንጉሥ ከዳዊት ጋር በተናጠል በማወዳደር ያጠቃልላሉ። እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ ባለመቀበላቸውና ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሰሜኑ መንግሥት በአሦር፥ የደቡቡ መንግሥት ደግሞ በባቢሎን ስለ መጥፋታቸው ይናገራሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እግዚአብሔርን ስለ መተውና እርሱን ባለመታዘዝ ስለ መኖር የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው?

1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል (መጽሐፍ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕ)፡- እንደ ሳሙኤልና ነገሥት መጻሕፍት፥ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕም አንድ መጽሐፍ ነበሩ። እነዚህ መጻሕፍት የሳሙኤል ካልዕንና የነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ መጽሐፍትን ታሪክ ይደግማሉ። የዳዊትን፥ የሰሎሞንና የይሁዳ ነገሥታትን ታሪክ በድጋሚ የሚናገሩ ናቸው። ይሁን እንጂ የዜና መዋዕል መጽሐፍ ታሪኩን የሚያቀርበው ከሃይማኖታዊ አመለካከት አንጻር ነው። በነገሥታቱ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ያተኩራል። በመልካም ምሳሌነቱ ዋና ተጠቃሽ ለሆነው ለንጉሥ ዳዊት በእስራኤል ስለሰጠው መንፈሳዊ አመራር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአል። በተጨማሪ የሰሎሞን ቤተ መቅደሱን የመገንባቱ ታሪክ ተጽፎአል። ከነገሥታት መጻሕፍት በተቃራኒ የይሁዳ ነገሥታትን ታሪክ እንጂ የእስራኤልን ነገሥታት ታሪክ አይናገርም።

ዕዝራ፡- የዕዝራ መጽሐፍ የሚናገረው ከባቢሎን ምርኮ ስለተመለሱ አይሁዶች ታሪክ ነው። አይሁዶች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ስለወሰዱት እርምጃ ፥ ስለገጠማቸው ተቃውሞና ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ መጠናቀቅ ይናገራል። በተጨማሪ በዕዝራ መሪነት ስለተካሄደው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል።

መጽሐፈ ነህምያ፡- ይህ መጽሐፍ አስቀድሞ ከመጽሐፈ ዕዝራ ጋር በአንድነት ተጠቃልሉ ይገኝ የነበረ ነው። አይሁድ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ስለነበረው ጊዜ ታሪክ መናገሩን ይቀጥላል። የመጽሐፈ ነህምያ ትኩረት በኢየሩሳሌም ቅጥር እንደገና መሠራትና በነህምያ መሪነት በኢየሩሳሌም በተካሄደው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአይሁድ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ፈሪሀ-እግዚአብሔር የተሞላበት አመራር የተጫወተው ሚና ምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃትን ለማበረታታት የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ምን ማድረግ አለባቸው?

መጽሐፈ አስቴር፡- በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ የታሪክ መጻሕፍት የመጨረሻው መጽሐፈ አስቴር ነው። በአቀማመጥ ቅደም ተከተል የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቢሆንም፥ በብሉይ ኪዳን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተፈጸመውን የመጨረሻ ክሥተት የሚናገር አይደለም። ይልቁንም የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው በመጽሐፈ ዕዝራ ታሪክ መካከል ነበር። መጽሐፈ አስቴር አይሁዳውያን በፋርስ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከመደምሰሳቸው በፊት፥ እግዚአብሔር ፡ በአንዲት አይሁዳዊት ሴት በመጠቀም እንዴት እንዳዳናቸው ይናገራል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመጠበቅ ኢምንት በሚመስሉ ድርጊቶች ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ታሪክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ተራ በሚመስል ድርጊት ውስጥ የእግዚአብሔር እጅ ሕይወትህን ለመጠበቅ ሲሠራ ያየኸው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: