የትንቢተ ሕዝቅኤል መግቢያ

የትንቢት መጻሕፍትን በምናጠናበት ጊዜ ኃጢአት በእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም በአንድ አገር ሕዝብ ላይ እንዴት ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድን ወይም የሥነ ሥርዓት ቅጣትን እንደሚያስከትል በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ይህ የሥነ ሥርዓት ቅጣት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በሚደርስበት ጊዜ ሕዝቡ ከሚከተሉት ሁለት ምላሾች አንዱን መስጠታቸው የማይቀር ነው፡- አንድም ከእግዚአብሔር የሥነ ሥርዓት ቅጣት ተምረው ከኃጢአታቸው በንስሐ በመመለስ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ይኖራሉ አልያም ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች ባለመሆን፥ እግዚአብሔር ትክክል እንዳልሆነ በማጕረምረምና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ማደግን በማቆም በእምቢተኝነታቸው ይቀጥላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሕይወትህ እግዚአብሔር ቀጥቶህ ንስሐ ለመግባትና በመንፈሳዊ ሕይወትህ ለማደግ ፈቃደኛ ያልሆንክበትን ጊዜ ጥቀስ። ለ) እግዚአብሔር በሕይወትህ ቀጥቶህ ፈጥነህ ንስሐ በመግባትህ፥ ከቅጣቱ መንፈሳዊ ዕድገት ያገኘህበትን ጊዜ ጥቀስ። ሐ) እግዚአብሔር በሚቀጣቸው ጊዜ ለመለወጥ ፈቃደኞች ያልሆኑ ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያንህ ወይም ከሌሎች እምነት ተከታዮች በመጥቀስ መግለጫ አቅርብ። መ) ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚሆኑባቸው በርካታ ጊዜያት እንኳ ንስሐ ለመግባት እጅግ የሚዘገዩት ለምን ይመስልሃል?

ሕዝቅኤል የኖረው እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ በፈረደበት ጊዜ ነበር። ሕዝቅኤል እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበር። ነገር ግን ብዙዎቹ እግዚአብሔርን የማያከብሩና ኃጢአትን የሚያዘወትሩ ስለነበሩ፥ ሕዝቅኤልም ከእነርሱ ጋር መከራ ተቀበለ። የእግዚአብሔር ፍርድ የተገለጠው ደረጃ በደረጃ ነበር። በመጀመሪያ፥ ጥቂት የኢየሩሳሌም መሪዎች በ605 ዓ.ዓ. ተማርከው ሄዱ። አይሁድ ግን ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች አልነበሩም። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ታዋቂ ዜጎች በ597 ዓ.ዓ. ተማርከው እንዲሄዱ አደረገ፤ ዳሩ ግን አሁንም በምርኮ የተወሰዱትም ሆኑ በኢየሩሳሌም የቀሩት መንገዳቸውን አልቀየሩም። በመጨረሻ፥ በ586 ዓ.ዓ. እግዚአብሔር ከተማዋ እንድትጠፋና አብዛኛው ሕዝብ እንዲማረክ አደረገ። ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ፈቃደኞች ከመሆናቸው በፊት ረጅም ዓመታትን በምርኮ አሳለፉ።

ያለፉት ሁለት ትምህርቶች እንደሚያሳዩን በኢየሩሳሌም ለቀሩት አይሁድ የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብሉ የሚያመጣው ዋናው ነቢይ ኤርምያስ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ባቢሎን ተማርከው ለሄዱ አይሁድ የእግዚአብሔርን መልእክት የሚያስተላልፈው ነቢይ ሕዝቅኤል ነበር። ሕዝቅኤል በምርኮ ላይ የነበረ ነቢይ ቢሆንም፥ አብዛኛው መልእክቱ ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁድን የሚመለከት ነበር። ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ ግን ሕዝቅኤል ወደ መሢሑ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻ ታላቅ መንግሥት በማመልከት፥ በምርኮ የነበሩትን አይሁዳውያን ማጽናናት ፈለገ። 

የትንቢተ ሕዝቅኤል ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 1፡3 አንብብ። ሀ) የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን ነው? ለ) የሕዝቅኤል ሙያ ምን ነበር? ሐ) ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር ጥሪ ሲደርሰው የት ነበር? መ) ስለ ሕዝቅኤል ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ግል ሕይወቱ የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር።

ትንቢተ ሕዝቅኤል የተሰየመው በጸሐፊው በሕዝቅኤል ስም ነው። ሕዝቅኤል የተወለደው በይሁዳ ምድር ሲሆን ዘመኑም ከ622-621 ዓ.ዓ. ነበር። የሕዝቅኤል አባትና እናት ከሌዊ ነገድ የሆኑ የአሮን ዝርያዎች ነበሩ። ስለዚህ ሕዝቅኤል በኢየሩሳሌም ባደገበት ጊዜ አባቱና ሌሎች ዘመዶቹ በቤተ መቅደስ አካባቢ ሲያገለግሉ ሳይመለከት አልቀረም። ሕዝቅኤል ሲወለድ እግዚአብሔርን ይፈራ የነበረው ንጉሥ ኢዮስያስ በይሁዳ መንፈሳዊ ተሐድሶ በማካሄድ ላይ ነበር። የሕዝቅኤል ቤተሰብ ታማኝ የሆኑ የእግዚአብሔር ተከታዮችና የንጉሥ ኢዮስያስ አማካሪዎችም ሳይሆኑ አልቀሩም። ሕዝቅኤል በኢዮስያስ ዘመን በነቢይነት ያገለግል ስለነበረው ስለ ኤርምያስ እንደሰማ ጥርጥር የለውም። የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ንጉሥ ኢዮስያስ ሞተና ሕዝቅኤል የሕዝቡን ፈጣን መንፈሳዊ ውድቀት ተመለከተ። የ16 ወይም የ17 ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜ ዳንኤልና ሌሎች አይሁዳውያን ተማርከው የሄዱበትን የመጀመሪያውን ጒዞ ተመልክቷል።

ሕዝቅኤል የ25 ዓመት ሳለ፥ ኮቦር ወንዝ አጠገብ ወደምትገኝ ቴል-አቢብ ወደተባለች የባቢሎን ምድር ተማርኮ ሄደ። ይህም ብዙ አይሁድ ተማርከው የሄዱበት ስፍራ ነበር። ስፍራው በባቢሎን አጠገብ የሚገኝ ሲሆን፥ የኮቦር ወንዝ ባቢሎናውያን ከኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የገነቡት መስኖ አካል ሳይሆን አይቀርም። ሕዝቅኤል በ597 ዓ.ዓ. በተፈጸመው ሁለተኛ ዙር ምርኮኛ ሰው ነበር። በዚህ ምርኮ ከይሁዳ ወደ ባቢሎን የተጓዙት ሰዎች ብዛት 10000 ያህል ነበር። በዚህ ጊዜ ሕዝቅኤል ከቤተ መቅደሱ፥ ከቤተሰቡና ከሚወዳት ኢየሩሳሌም ተለየ።

ሕዝቅኤል ከካህን ቤተሰብ የተገኘ ከመሆኑም ሌላ፥ ነቢይም ነበር። የነቢይነት አገልግሉት ጥሪውን የተቀበለው ከኢየሩሳሌም መደምሰስ 6 ዓመታት ቀደም ብሎ በ593 ዓ.ዓ. ነበር። ሕዝቅኤል በቅርብ የሚፈጸመውን የኢየሩሳሌምን ጥፋት ተንብዮ ስለነበር መልእክቱ ከኤርምያስ መልእክት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ሕዝቅኤል ከተነበያቸው ትንቢቶቹ የመጨረሻው በ571 ዓ.ዓ. የተነበየው ነበር። ሕዝቅኤል የንጉሥ ዮአኪንን ከወኅኒ መለቀቅ ስላልገለጸ ከ562 ዓ.ዓ. በፊት ሳይሞት አልቀረም።

ሕዝቅኤል በኢየሩሳሌም ቀርቶ ቢሆን ኖሮ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግል ካህን ይሆን ነበር። ሕዝቅኤል በምርኮ ምድር እንደ አይሁድ የሃይማኖት መሪ ይታይ ነበር። እንዲሁም በምርኮ ምድር ለነበሩ ሰዎች ነቢይ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር ተመርጦ ነበር። ሚስት ያገባ ቢሆንም፥ በኢየሩሳሌም ላይ ከበባ በተጀመረ ጊዜ ሚስቱ ሞተችበት (ሕዝቅኤል 24፡18)። ሕዝቅኤል ለ22 ዓመታት አገልግሏል፤ አገልግሎቱም በሁለት ዐበይት ክፍለ ጊዜያት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፤ 

1. ከ593-586 ዓ.ዓ.፡- (ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት) ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም እስከምትወድቅና ትንቢቶቹ እስከሚፈጸሙ ድረስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ፈጥኖ ስለሚመጣው ጥፋት ሰብኳል።

2. ከ586-571 ዓ.ዓ. (ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ) ሕዝቅኤል ስለ አይሁድ ሕዝብ መመለስና ስለ ቤተ መቅደሱ እንደገና መሠራት ተነበየ።

ሕዝቅኤል ደፋር የሆነ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ ነበር። እንደ ኤርምያስ ስደት ባይገጥመውም እንኳ በምርኮ የነበሩ አይሁድ መሳለቅና ተቃውሞ ገጥሞታል። እግዚአብሔር ከማንኛውም ነቢይ ይልቅ የምርኮውን እውነታ በአካል እንዲገልጥ አድርጎታል። ልክ ዛሬ በድራማ ወይም ተውኔት እንደምናደርገው ትንቢቶቹን በምሳሌያዊ አደራረግ እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን እንዲያሳይ ጠይቆት ነበር። ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር መልእክት ለሕዝቡ በግልጽና በትክክል እንዲደርስ በማለት ሞኝ ለመምሰልና የግል ምቾቱን ለመተው ፍጹም ፈቃደኛ ነበር።

ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለገለው ኤርምያስና ዳንኤል ያገለግሉ በነበሩበት ዘመን ነው። ኤርምያስ የኖረውና ያገለገለው በኢየሩሳለም፥ በኋላም በግብፅ፥ ዳንኤል ደግሞ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሲሆን ሕዝቅኤል ያገለገለው ግን ከባቢሎን ከተማ ውጭ በምርኮኞች ወመካከል ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading