የትንቢተ ሕዝቅኤል ታሪካዊ ሥረ መሠረት

ሕዝቅኤል በተወለደበት ጊዜ ለይሁዳ ሕዝብ ነገሮች ሁሉ አበረታች ይመስሉ ነበር። አገሪቱ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ የሚያመጣውን ቅጣት ካረጋገጠበት ከክፉው ንጉሥ ከምናሴ ግዛት ገና እፎይ ብላ ነበር (2ኛ ነገሥት 21፡9-15፤ 24፡3-4)። ንጉሥ ኢዮስያስ መንፈሳዊ ተሐድሶውን ጀምሮ ስለነበር አገሪቱ እግዚአብሔርን በንጽሕና የምታመልክበት ጊዜ የደረሰ ይመስል ነበር። በዚህ ጊዜ የአሕዛብ መንግሥታት በጣም ደካሞች ስለነበሩ ይሁዳ የአሦር መንግሥት የፈጠረባት አለመረጋጋት ካለፈ በኋላ የሰላም አየር የምትተነፍስበት ጊዜ ነበር።

በ609 ዓ.ዓ. ግን ነገሮች በድንገት ተቀየሩ። ንጉሥ ኢዮስያስ ከግብፃውያን ጋር በተደረገ ጦርነት ተገደለ። ልጁ ኢዮአካዝ ደግሞ ተማርኮ ወደ ግብፅ ሄደ። ኢዮአቄም በትረ ሥልጣኑን ጨበጠ። ኢዮአቄም ክፉ ነበርና ንጉሥ ኢዮስያስ ያካሄደውን መንፈሳዊ ተሐድሶ አበላሸው።

ባቢሎን ወዲያውኑ ኢዮአቄምን አስገበረችው። ዳንኤልና ሌሎችም ተማርከው ሄዱ።

በ598 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን ግብፅን በጦርነት ማሸነፍ በተሳናቸው ጊዜ ንጉሥ ኢዮአቄም በባቢሎናውያን ላይ ለማመፅ ወሰነ። ከባቢሎን ጋር በሚያደርገው ውጊያ ግብጻውያን ይረዱኛል ብሎ አሰበ፡፡ ግብፃውያን ግን አይሁዳውያንን አልረዱም። ስለዚህ በ597 ዓ.ዓ. ንጉሥ ኢዮአቄም ሞተና ንጉሥ ዮአኪን በእርሱ ፈንታ ነገሠ። ዮአኪን ለሦስት ወራት ብቻ ከገዛ በኋላ ከሕዝቅኤል ጋር ተማርኮ ወደ ባቢሎን ተወሰደ። ባቢሎናውያን በንጉሥ ዮአኪን ምትክ ንጉሥ ሴዴቅያስን ሾሙት። በ594 ዓ.ዓ. ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን በመሄድ የጣዖት አምልኮን የሚጨምር አክብሮት ለባቢሎን መሪ አቀረበ። ከአንድ ዓመት በኋላ ሕዝቅኤል ከእግዚአብሔር ጥሪ በመቀበል ኢየሩሳሌም ፈጽማ እንደምትጠፋ ተነበየ። ሴዴቅያስም በባቢሎን ላይ ዓመፀ። የባቢሎን ጦር በታላቅ ቍጣ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነት፥ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የበሽታ መቅሠፍቶችና በኢየሩሳሌም ከተማ የሚበላ ነገር በመጥፋቱ በራብ አለቁ። በመጨረሻ በ586 ዓ.ዓ. ከተማዋ ወደቀች። ከ400 ዓመታት በፊት ሰሎሞን የሠራው ቤተ መቅደስ መቃጠል ብቻ ሳይሆን በድንጋይ ላይ ድንጋይ ሆኖ ፈራረሰ። በከተማዋ ውስጥ የነበሩ ሕንጻዎችና ቅጥሮች ፈራረሱ። ሕዝቡም ተማርከው ሄዱ። በዚህም ከዳዊት የዘር ግንድ የሚመጡ የይሁዳ ነገሥታት ነገር አበቃ።

በ597 ዓ.ዓ. የተማረኩ ሰዎች ከሚወዱት አገራቸው መለየት ሥነ-ልቡናዊ ተጽዕኖ ቢደርስባቸውም፥ ጥሩ ኑሮ ይኖሩ ነበር፡፡ የሚያርሱት መሬት ተሰጥቶአቸው ነበር፡፡ መነገድም ይችሉ ነበር። ትልቁ ችግራቸው በባቢሎን ተረጋግተው እንዳይኖሩ ይልቁኑ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ እንዲዘጋጁ ሐሰተኞች ነቢያት ያመጡላቸው የነበረው የሐሰት መልእክት ነበር፡፡ እነዚህ ነቢያት ባቢሎን ፈጥና እንደምትወድቅ ይናገሩ ነበር። ኤርምያስና ሕዝቅኤል እነዚህን ሐሰተኞች ነቢያት በመዋጋት ምርኮው ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል ስለሆነ ተረጋግተው እንዲኖሩ ለሕዝቡ መግለጥ ነበረባቸው። ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰችና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች አይሁዳውያን ተማርከው ከሄዱ በኋላ፥ እግዚአብሔር አሁንም ቢሆን ለእነርሱ ዕቅድ እንዳለው በመግለጥ ሕዝቅኤል እንዲያበረታታቸው ፈለገ። ከምርኮ እንደሚመለሱ፥ ከተማይቱና ቤተ መቅደሱ እንደገና እንደሚሠሩ አሕዛብም እንደሚፈረድባቸው ነገራቸው። 

ስለ ትንቢተ ሕዝቅኤል መጽሐፍ 

በጥንታውያን አይሁድ ዘንድ የትንቢተ ሕዝቅኤል መጽሐፍ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ወዲያውኑ ተቀባይነትን አላገኘም ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ሕዝቅኤል በመሢሑ ጊዜ ስለሚሆን የመሥዋዕት አቀራረብ ያሳየበት መንገድና በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተገለጸው የመሥዋዕት ሥርዓት ፈጽሞ የተለየ ስለነበር ነው። ይሁን እንጂ የመጽሐፉን ታላቅነትና ለሕዝቅኤል የተሰጠውን የእግዚአብሔር ቃል የያዘ መሆኑን ለመካድ አልቻሉም። እንዲያውም ሕዝቅኤል 49 ጊዜ ያህል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ እንደመጣ ተናግሯል። በመጨረሻም አይሁድ መጽሐፉ የቅዱሳት መጻሕፍት አካል መሆኑን በመቀበል፥ ይህ የመሥዋዕት አቀራረብ ልዩነት ከሙሴ ሕግ ጋር የሚጣጣመው መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

ትንቢተ ሕዝቅኤል ከኤርምያስ የሚለየው በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት በመጻፉ ነው። ከብሉይ ኪዳን የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ይልቅ ትከክለኛ በሆነ የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት የተጻፈ መጽሐፍ ትንቢተ ሕዝቅኤል ነው። ከሕዝቅኤል መልእክቶች መካከል አሥራ ሦስቱ ንጉሥ ዮአኪን የተማረከበትን ቀን ወርና ዓመት የሚጠቅሱ ናቸው። ሕዝቅኤል የነቢይነት ጥሪውን የተቀበለው በሐምሌ 593 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ የመጨረሻ መልእክቱን የተናገረው ደግሞ በሚያዝያ 571 ዓ.ዓ. ነበር።

የሕዝቅኤል ትንቢቶች የተነገሩባቸውን ጊዜያት የሚያሳየውን የሚከተለውን ሠንጠረዥ ተመልከት፡-

1. ስለ ሰረገላ ያየው የእግዚአብሔር ራእይ ሕዝ. 1፡1-3 ሰኔ 593 ዓ.ዓ. ራእይ 

2. ሕዝቅኤል ጠባቂ ለመሆን ተጠራ ሕዝ. 3፡16 ሰኔ 593 ዓ.ዓ. 

3. ስለ ቤተ መቅደስ ያየው ራእይ ሕዝ. 8፡1 መስከረም 592 ዓ.ዓ. 

4. ለሽማግሌዎች የተነገረ መልእክት ሕዝ. 20፡1 ነሐሴ 591 ዓ.ዓ. 

5. የኢየሩሳሌም ለሁለተኛ ጊዜ መያዝ ሕዝ. 24፡1 ጥር. 588 ዓ.ዓ.

6. በጢሮስ ላይ የሚመጣ ፍርድ ሕዝ. 26፡1 ሚያዝያ 587 ዓ.ዓ. 

7. በግብፅ ላይ የሚመጣ ፍርድ ሕዝ. 29፡1 ጥር 587 ዓ.ዓ. 

8. በግብፅ ላይ የሚመጣ ፍርድ ሕዝ. 29፡17 ሚያዝያ 571 ዓ.ዓ. 

9. በግብፅ ላይ የሚመጣ ፍርድ ሕዝ. 30፡20 ሚያዝያ 587 ዓ.ዓ. 

10. በግብፅ ላይ የሚመጣ ፍርድ ሕዝ. 31፡1 ሰኔ 587 ዓ.ዓ. ‘ 

11. ስለ ፈርዖን (የግብፅ ንጉሥ) ሕዝ. 32፡1 መጋቢት 585 ዓ.ዓ. የቀረበ ሙሾ 

12. ስለ ግብፅ የቀረበ ሙሾ ሕዝ. 32፡17 ሚያዝያ 586 ዓ.ዓ. 

13. የኢየሩሳሌም ውድቀት ሕዝ. 33፡21 ጥር 586 ዓ.ዓ. 

14. ስለ አዲሱ ቤተ መቅደስ የተገለጠ ራእይ ሕዝ. 40፡1 ሚያዝያ 573 ዓ.ዓ. 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading