ሚክያስ 1-7

የውይይት ጥያቄ፥ ሚክያስ 1-7 አንብብ። ሀ) ሚክያስ ሕዝቡን የከሰሰባቸውን ኃጢአቶች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ምን ዓይነት ፍርድ እንደሚያመጣ ተናገረ? ሐ) ዛሬ ሊያጽናኑን የሚችሉትንና ወደ ፊት ስለሚመጣው ንጉሥና መንግሥት የተነገሩትን ትንቢቶች ዘርዝር።

እግዚአብሔር ጻድቅና ቅዱስ አምላክ ነው። ስለዚህ ኃጢአትን በተለይም ደግሞ በሕዝቡ መካከል ያለውን ኃጢአት መቅጣት አለበት፤ ይቀጣልም። ብዙ ጊዜ ሰይጣን ሕዝቡን እግዚአብሔር የሚገደው ለመሥዋዕት ሥነ-ሥርዓት፥ ለአምልኮ ጸሎት፥ ለመዝሙር፥ ለስብከትና ለመሳሰሉት ነው በማለት ያስታቸዋል። በዚህ ምክንያት እነርሱ ይህንን እስካደረጉ ድረስ፥ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝና የሚባርካቸው ይመስላቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በቀላሉ ባዶና ምንም ዋጋ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ኃጢአት፥ መለያየት፥ የሥነ-ምግባር ድቀት፥ ጠብ፥ ጥላቻ ቅንዓትና ትዕቢት ወይም ሌላ ዓይነት ኃጢአት ካለ እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ አይሰኝም፡፡ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሕይወት ችግር እንዲመጣ ያደርጋል። ሕዝቡን ወደ ራሱ ለመመለስ የስደት ሞት ሳይቀር ሊያመጣ ይችላል። ከሥርዓተ አምልኮ በላቀ ሁኔታ እግዚአብሔር በሁሉም ሕይወታችን ክፍል አግባብ ባለው መንገድ እንድንመላለስ ይፈልጋል። ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር በምንሰጥበትና ለእርሱ በምንታዘዝበት ጊዜ፥ አምልኮአችን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆንና እርሱም ክብሩንና ኃይሉን ያሳየናል።

የውይይት ጥያቄ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በእሑድ የእርሱን በሚያመልኩበት ጊዜ በሚያደርጉት ድርጊት ብቻ ሳይሆን፥ በአጠቃላይ ስለ ሕይወታቸው የሚገደው መሆኑን የሚዘነጉት ለምንድን ነው? አንተም ሆንህ ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን እውነቶች ማስታወሳችሁ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

1. ሚክያስ በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 1)

ጻድቅ የሆነው አስፈሪው ዳኛ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ለመፍረድ ከሰማይ ሲወርድ ይታያል። ሰማርያና ኢየሩሳሌም ስለ ኃጢአታቸው ተጠያቂዎች ናቸው። ሰማርያ ፈጽማ ልትጠፋ፥ ኢየሩሳሌምም ልትቀጣ ነበር። ስለዚህም፥ ሚክያስ ይህን ትንቢት በተቀበለ ጊዜ በኃዘን ተሞልቶ ነበር። አንድ ወዳጁ ወይም አፍቃሪው የሞተበት ሰው በሚያዝንበት መንገድ ያለቅስና በባዶ እግሩ ዕርቃኑን ይመላለስ ነበር። 

2. ሚክያስ በይሁዳ መሪዎች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 2-3) 

እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ለመፍረድ የተነሣው ለምን ነበር? በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል በነበረው ኃጢአትና የፍትሕ መዛባት ምክንያት ነበር። ሀብታሞች፣ ጎረቤቶቻቸውንና ድሆችን በማታለል ገንዘባቸውን ይቀሙአቸው ነበር። ሕዝቡ ኃጢአታቸውን ተገንዝበው በንስሐ እንዳይመለሱ የሐሰት ማጽናኛ ቃሎችን ይተነብዩ ነበር። የሚያገለግሉት የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ በማስተማር፣ ሕዝቡ ንስሐ ሲገቡ ለማየት በመናፈቅ ሳይሆን፥ ለገንዘብ ሲሉ ነበር። መሪዎቹ ጉቦ በመቀበልና ኃይላቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ሀብትን ይሰበሰቡ፥ ለድሆች የሚገባውንም ነገር ይነጥቁ ነበር። ሰዎች እነዚህን መሰሎቹ ድርጊቶች በእግዚአብሔር ፊት መልካም እንደሆኑ ቢያስቡም የእግዚአብሔር ፍርድ ግን በደጅ ነበር። 

3. ሚክያስ ስለ ጽዮን መመለስ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 4-5)

በይሁዳ መንግሥት ከነበረው ክፋት ጋር ሲነጻጸር በመጨረሻው ዘመን በእግዚአብሔር የሚመሠረት ሌላ መንግሥት እንደሚመጣ ተናገረ። እርሱና የእግዚአብሔር ጻድቅ ሕዝብ የሆነው ቅሬታ የዚህ መንግሥት አካል ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ሕዝብ በተለወጠ ልብ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። ጦርነትና ክፋት ይወገዳል። ሰዎች በሰላም ይኖራሉ። አሕዛብ ሳይቀሩ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚፈርድ ቢሆንም እንኳ አንድ ቀን እንደ ዳዊት ያለ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመራ ንጉሥ እንደሚመጣ ተናገረ። በእግዚአብሔር ኃይልና ብርታት ይመጣል፤ ዳሩ ግን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ርኅሩኅ እረኛ ይሆናል። 

4. ሚክያስ ስለ ይሁዳ ክፋትና ስለሚመጣባት ፍርድ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 6-7፡6) 

እግዚአብሔር ተራሮችንና ኮረብቶችን በምስክርነት በመጥራት በይሁዳ ላይ ክሱን ያቀርባል። እግዚአብሔር ለእነርሱ በቸርነት የተገለጠ ቢሆንም፥ አይሁድ ግን ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁ። የእግዚአብሔርን ሕግጋት ባሕርያት ሊለውጡ በማይችሉ ውጫዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች ለወጡ። የጣዖት አምልኮን ለእግዚአብሔር ከሚቀርብ አምልኮ ጋር ቀላቀሉ። ክፋትን በመቃወም የሚናገሩ መልካም ሰዎች እየተገደሉ ከምድሪቱ ይወገዱ ጀመር። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ በእነርሱ ላይ ይመጣል። ፍርድ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው። ፍርዱ በሚፈጸምበት ጊዜ ታማኝ የሆኑት የእግዚአብሔር ሕዝቦች «እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አምላኬም ይሰማኛል» (ሚክያስ 7፡7) የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። 

5. የእስራኤል ቅሬታዎች በወደፊቱ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚቀበሉት ይቅርታ ሚክያስ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 7፡7-20) 

ይሁዳ በእግዚአብሔር ፍርድ ምክንያት የሚደርስባት ጥፋት ዘላለማዊ አልነበረም። አንድ ቀን እንደገና በምሕረቱ ሊጎበኛት እግዚአብሔር ቀን ቀጥሮ ነበር። እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሠራውን ሥራ የምድር አሕዛብ በመደነቅና በአክብሮት ይመለከቱታል። ኢየሩሳሌም እንደገና ትሠራለች። እውነተኛ ይቅርታና ተሐድሶም ይሆናል። ሚክያስ ስለዚህ ነገር እርግጠኛ የሆነው ለምን ነበር? እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ስላደረገና ለቃል ኪዳኑም ታማኝ ስለሆነ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ሚክያስ የተማርካቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ የተወሰኑ ቡድኖች ለማስተማር ዐቅድ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/LtXaXqvQgQcabDnu7

1 thought on “ሚክያስ 1-7”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading