የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች

የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ

ትንቢተ ዕንባቆም እግዚአብሔር በባቢሎናውያን አማካይነት በይሁዳ ላይ ስለሚያመጣው ቅጣት የሚተነብይ ቢሆንም፥ ዓላማው የእግዚአብሔርን ቅንና ትክክለኛ ፍርድ መመርመር ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የእግዚአብሔርን መንገድ ለሕዝቡ እንደሚገልጡ የጥበብ መጻሕፍት ዓይነት ነው።

ትንቢተ ዕንባቆም ከመጽሐፈ ኢዮብ የሚመሳሰልም የሚለያይም ነው። የመጽሐፈ ኢዮብ ዋና የፍልስፍና ጥያቄ «ጻድቅ መከራን በሚቀበልበት ጊዜ የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ አለን?» የሚል ነው። በዚያ ስፍራ የተሰጠው መልስ፥ ሰይጣን ጻድቃንን እንዲፈትን እግዚአብሔር ይፈቅዳል የሚል ነበር። ጻድቃን የተከበረውን የእግዚአብሔር ኃይልና ከእግዚአብሔር ጋር ሲወዳደሩ የቱን ያህል ኢምንት እንደሆኑ በማስታወስ በፈተናቸው በእግዚአብሔር መታመን አለባቸው።

በትንቢተ ዕንባቆም ውስጥ ሁለት የፍልስፍና ጥያቄዎች ተመልሰዋል፡-

1. «ሕዝቦችና መንግሥታት በክፋት ሲሞሉና ክፉ ሰዎች ሲበለጽጉ የእግዚአብሔር ቅንና ትክክለኛ ፍርድ አለን?» እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ፡- እርሱ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ይፈርዳል። ይሁዳ ቅጣት የሚፈጸምባት በባቢሎን ነው የሚል ነበር። 

2. «ጻድቁ እግዚአብሔር ከይሁዳ ይልቅ ክፉና ጠማማ የሆነውን ሕዝብ እንዴት ለቅጣት መሣሪያ አድርጎ ይመርጣል?» 

እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ ሁለት ክፍሎች አሉት፡-

ሀ. እግዚአብሔር ታላቅና ኃይለኛ ነው። ሰው ስለ እግዚአብሔር የአሠራር መንገዶች የመጠየቅ መብት የለውም። ይልቁንም ጻድቅ ግራ በተጋባና እርግጠኛ ባልሆነበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እንኳ መጠበቅ አለበት። ጻድቅ ሰው የእግዚአብሔርን መንገዶች ምንነት በማይረዳበት ጊዜም እንኳ የታማኝነትና የጽናት ሕይወቱን ይጠብቃል።

ለ. እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በራሱ ጊዜ ለመቅጣት ሌሎችን ይጠቀማል። እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት በባቢሎን መንግሥትና ሕዝብ ከተጠቀመ በኋላ በተራቸው ይቀጣቸዋል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመቅጣት የተጠቀመበት ሰው ወይም መንግሥት መልካም ነው ማለት አይደለም። በእግዚአብሔር እጅ እንዳሉ መሣሪያዎች ናቸው። ስለዚህ ከተጠቀመባቸው በኋላ ሊጥላቸው ወይም እንደየአስፈላጊነቱ እነርሱን ደግሞ ሊቀጣቸው ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ማወቅና መጠቀም የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) በዚህ ዘመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ዘወትር የሚጠይቁባቸውን ነገሮች ዝርዝር። ሐ) እነዚህ እውነቶች እንዴት ይረዷቸዋል?

ዕንባቆም ተገቢውን ትምህርት እንዳገኘ ከመጨረሻ ጸሎቱ እንረዳለን። ባይረዳውም እንኳ የእግዚአብሔርን መንገድ ተቀብሏል። የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ፍርድ መጠራጠሩን አቁሞ ነበር። በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር ክፉዎችን እንደሚቀጣና ጻድቃንን እንደሚባርክ በሰጠው ዋስትና ላይ አርፎ ነበር። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን መቼና እንዴት መቅጣት እንዳለበት መወሰን የዕንባቆምም ሆነ የእኛ ኃላፊነት አይደለም። የዕንባቆምም ጸሎት ሊመጣ ካለው መዓት አንጻር የተጸለየ አስደናቂ የእምነት ጸሎት ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በሚፈርድበት ጊዜ ምሕረቱን ከቶ እንደማይረሳ ጸለየ። በተጨማሪ በእጁ የሚገኘው ማንኛውም ሥጋዊ በረከት ሁሉ ቢወሰድ እንኳ፥ በእግዚአብሔር ብርታት ላይ መደገፉንና በእርሱም መታመኑን ለመቀጠል መወሰኑን ገለጸ። 

የትንቢተ ዕንባቆም ዋና ዋና ትምህርቶች

1. እግዚአብሔር ክፉዎችን በኃጢአታቸው ምክንያት ይቀጣቸዋል። ብዙውን ጊዜ ግን ክፉዎች በኃጢአታቸው የማይቀጡ ይመስላል። እንዲያውም በኃጢአታቸው ምክንያት ሲበለጽጉና ሲከናወንላቸው ስለሚታዩ በኃጢአታቸው የተባረኩ ይመስላሉ። ክፉዎችና ኃጢአተኞች ሲሳካላቸው፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ አብዛኛዎቹ መከራ ይቀበላሉ። ይህም ለመበልጸግ ሲሉ ኃጢአተኞች የሚጠቀሙባቸውን መንገዶች ክርስቲያኖችም እንዲጠቀሙበት ይገፋፋቸዋል። ይህን ሲያደርጉ ግን እግዚአብሔር ክፉዎችን እንደሚቀጣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ዘንግተዋል ማለት ነው። ቅጣቱ እኛ በምንፈልገው ፍጥነትና መንገድ ቢይሆንም፥ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚቀጣ ቃል ይገባል። ስለዚህ ኃጢአተኞች አሁን ስላልተቀጡ እኛም ብንሆን አንቀጣም ብለን በማሰብ፥ እንደ እነርሱ ለመሆን መፈተንና ለፈተናው መንገድ መክፈት የለብንም። የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ ብዙ ጊዜ ቢዘገይም መፈጸሙ ግን የማይቀር ነው። የይሁዳና የአሦር መንግሥታት እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከመፍረዱ በፊት ለብዙ ዘመናት ቆይተዋል። ባቢሎናውያን ግን በእግዚአብሔር ሳይቀጡ የቆዩት ለ70 ዓመታት ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ የማያምኑ ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው ባለመቀጣታቸው ምክንያት እነርሱም እንደማይቀጡ በማሰብ፥ በኃጢአት የሚወድቁት እንዴት እንደሆነ ግለጽ። ለ) ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ የዘነጉት ነገር ምንድን ነው? የዕንባቆም ትምህርት ማስጠንቀቂያ ሊሆናቸው የሚችለው እንዴት ነው?

2. ክፉዎችና ኃጢአተኞች ሲበለጽጉ ወይም ጻድቃን መከራ ሲቀበሉ፥ በታማኝነት ጸንቶ መኖር የጻድቃን ኃላፊነት ነው። እጅግ ታዋቂ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ ዕንባቆም 2፡4 ነው። ይህም በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሰውን የሚያጸድቀው በሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት መሆኑን ለመገልጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናያለን (ሮሜ 1፡ 17፥ ገላትያ፤ 3፡11፤ ዕብራውያን 10፡38)። ይሁን እንጂ በትንቢተ ዕንባቆም የተሰጠው ትኩረት በጣም የተለየ ነው። ዕንባቆም የእግዚአብሔር ምርጦች የሆኑት ጻድቃን በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ፥ በእግዚአብሔር መታመን እንዳለባቸው ያስተምራል። ክፋትና ኃጢአት ሲስፋፉ፥ ምን ክፉዎች ከመቀጣት ይልቅ እየበለጸጉ የሄዱ ሲመስሉ፥ ጻድቃን ሊያስታውሱት የሚገባው የተጠሩት በእግዚአብሔር ፊት የጽድቅና የቅድስና ሕይወት ለመኖር እንደ ሆነ ነው። ስለሆነም የቅድስና አካሄዳቸውን መጠበቅ አለባቸው። እግዚአብሔር አንድ ቀን ኃጢአተኞችንና ጠማሞችን እንደሚቀጣ ማስታወስ አለባቸው። ይህ ቅጣት በምድር እያሉ ሊደርስባቸው ወይም ላይደርስባቸው ቢችልም በመጨረሻው ዘመን ግን የማይቀር ነው። ደግሞም ጻድቃን አንዳችም ነገር ሳያጠፉ መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅ አለባቸው። እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት ባቢሎንን በተጠቀመ ጊዜ በይሁዳ በርካታ ጻድቃን ሰዎች ነበሩ፤ ዕንባቆም፥ ኤርምያስ፥ ሶፎንያስና ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ። ቅጣቱ በሚፈጸምበት ጊዜ መከራቸውን ያዩ ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ለእነርሱ ቀላል ነበር። «ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኜ እያለሁ መከራን ከተቀበልሁ፥ በእርሱ ላይ ያለኝን እምነት እክዳለሁ» ብሎ ማሰብ ቀላል ነበር። ዳሩ ግን ዕንባቆም የሚያስተምረን እምነታችን በእግዚአብሔር እንጂ በዙሪያችን ባሉ ሁኔታዎች ላይ መመሥረት እንደሌለበት ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ለመታመን ፈቃደኞች የሚሆኑት ገንዘብ እስካገኙ፥ ፈውስ እስከተሰጣቸውና የተለያዩ ሥጋዊ በረከቶችን እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ በእግዚአብሔር ካመንን ሁልጊዜ ባለጸጎች እንሆናለን ወይም ከበሽታችን እንፈወሳለን በማለት የሐሰት ትምህርት የሚያስተምሩ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸው ነው። ኢዮብ ከፍ ያለ ሥቃይ ቢደርስበትም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን እምነቱን ጠብቋል። ዕንባቆም ደግሞ መንጋውንና የእርሻ ፍሬውን ሁሉ በማጣት፥ ረሃብ ምናልባትም ሞት እንደሚያጋጥመው ቢያውቅም እንኳ እምነቱ በእግዚአብሔር ላይ ነበር። ሐሤት የሚያደርገው በእግዚአብሔር ላይ እንጂ በሁኔታዎች ላይ አልነበረም። በሁኔታዎቹ ሁሉ ውስጥ ማለፍ እንዲችል ደግሞ እግዚአብሔር ኃይሉን ያድስለት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ሰው እውነተኛ እምነት ካለው ሀብታም ይሆናል ወይም አይታመምም እያሉ ሲያስተምሩ ሰምተሃልን? ለዚህ ትምህርት የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? ለ) ትንቢተ ዕንባቆምን በመጠቀም መልስ የምትሰጣቸው እንዴት ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እስከባረካቸው ድረስ ብቻ በእርሱ እያመኑ፥ መከራ ወይም ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ ግን የሚክዱት ለምንድን ነው? መ) «ጻድቅ በእምነት ይኖራል» የሚለው ትምህርት ክርስቲያኖች ሊያስታውሱት የሚገባ እጅግ ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

3. እግዚአብሔር መንግሥታትን ስለ ክፉ ድርጊታቸው ይቀጣቸዋል። ከትንቢተ ዕንባቆም በግልጽ እንደምንመለከተው፥ እግዚአብሔር መልካምም ሆነ ክፉ መንግሥታትን ላደረጉት ነገር ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል። እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ተጠያቂ አድርጎ ነበር። ኃጢአታቸው እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰ ጊዜ ፍርዱን አመጣባቸው። እግዚአብሔር ስለ ክፋታቸው በአሦርና በባቢሎንም ላይ ፈርዷል። ማንኛውም ሰው ሆነ ሕዝብ ወይም መንግሥት ከእግዚአብሔር ፍርድ ማምለጥ አይችልም። ግለሰቦችም ሆኑ ሕዝቦች በብሔራዊ ደረጃ ለሚያደርጉት ድርጊት ተጠያቂዎች ናቸው። እግዚአብሔር ለእኛም ሆነ ለመንግሥታት የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በዚህ ነፃ ምርጫችን ስለምንወስደው እርምጃ ሁሉ ግን እግዚአብሔር ይጠይቀናል። ልንቆጣጠር የምንችለው ምርጫችንን እንጂ ምርጣችን የሚያስከትላቸውን ነገሮች ወይም ውጤቶች አይደለም። የምርጫችን ውጤቶች በእግዚአብሔር እጅ ናቸው። መልካም ነገሮችን ከመረጥን (ከዘራን) መልካም ነገሮችን እናጭዳለን። ክፉ ነገሮችን ከመረጥን (ከዘራን) የክፉ ምርጫዎቻችንን ውጤቶች እናጭዳለን (ምሳሌ 11፡18፤ 22፡8፤ ገላትያ 6፡7-8)። በመጨረሻ ሁላችንም በሚፈርድብን በእግዚአብሔር ፊት እንቆማለን፤ እርሱም እንደየድርጊታችን ዋጋችንን ይሰጠናል ወይም ይቀጣናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህን የመጨረሻ ትምህርት ማስታወስ ለእኛ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ሰዎች ስለሚያደርጉአቸው ምርጫዎች ሁሉ እግዚአብሔር ተጠያቂዎች እንደሚያደርጋቸው ቢያስታውሱ የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላ ምርጫ የሚያደርጉት እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ ዕንባቆም 1-3 አንብብ። ሀ) ዕንባቆም የጠየቃቸው ሁለት ጥያቄዎች ምን ነበሩ? ለ) እግዚአብሔር የዕንባቆምን ጥያቄዎች የመለሰው እንዴት ነበር? ሐ) የዕንባቆም ጸሎት ዛሬ እኛም ብንጸልየው መልካም የሚሆንው እንዴት ነው?

1. ዕንባቆም ለእግዚአብሔር ያቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር በይሁዳ የሚገኘውን ክፋት ያልቀጣው ለምንድን ነው? (ዕንባቆም 1፡1-4)። 

በይሁዳ ሕዝብ መካከል ይኖር የነበረውን ዕንባቆምን፥ የሕዝቡ መንፈሳዊ ሁኔታ እጅግ አሳስቦት ነበር። የሥነ-ምግባርና የማኅበራዊ ክፋቶች ጉዳይ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የሚታዘዙት ሰዎች እጅግ ጥቂት መሆናቸው አሳስቦት ነበር። ስለዚህ ዕንባቆም የይሁዳን ኃጢአት ለመቅጣት ለምን እንደማይፈርድ እግዚአብሔርን ጠየቀው። ሆኖም ዕንባቆም በኋላ በእስራኤል የደረሰው ዓይነት ከፍተኛ ጥፋት እንዲመጣ አይፈልግም ነበር። እግዚአብሔር ክፋትን በመጠኑ በመቅጣት፥ ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡ እንዲያደርግ ይፈልግ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዕንባቆምን የተሰማው ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃልን? መልስህን አብራራ። ለ) ክርስቲያኖች በሌሎች ክርስቲያኖች ሕይወት ወይም በአገራቸው ውስጥ ስለሚፈጸመው ክፋት መቆርቆር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ሐ) በዙሪያቸው ስለሚፈጸመው ኃጢአት የክርስቲያኖች ግዴለሽ መሆን የምን ምልክት ነው? መ) በዙሪያችሁ ያለው ኃጢአት አንተን ወይም ቤተ ክርስቲያንህን ምን ያህል እያሳሰባችሁ ነው? ስለ እርሱስ ምን እያደረጋችሁ ነው? 

2. የእግዚአብሔር የመጀመሪያ መልስ፡- እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት ባቢሎናውያንን ይልካል (ዕንባቆም 1፡5-11)። 

3. ዕንባቆም እግዚአብሔርን የጠየቀው ሁለተኛ ጥያቄ፡- ጻድቅና ትክክለኛ ፍርድ ሰጭ የሆነው እግዚአብሔር የይሁዳን ኃጢአት ከእርሷ ይበልጥ ኃጢአተኞች በሆኑት በባቢሎናውያን አማካይነት እንዴት ይቀጣል? (ዕንባቆም 1፡12-2፡1)።

ብዙዎቻችን ሰዎችን መልካም ወይም ክፉ በሚል ክፍል መመደብ እንወዳለን። ብዙም ጊዜ አንዳንዶች ከሌሉች የተሻሉ ወይም የባሱ ናቸው የሚል እምነት በአእምሮአችን ይቀረፃል። ስለዚህ እግዚአብሔር አንዱ ከሌላው የባሰ ስለሆነ የባሰውን ከተሻለው በላቀ ሁኔታ መቅጣት አለበት ብለን እናስባለን። ዕንባቆም ተመሳሳይ አሳብ ነበረው። አይሁድ ፍርድ እንደሚገባቸው ተገንዝቦ ነበር። እግዚአብሔር አይሁድን የሚቀጣው ከእነርሱ በባሱት በባቢሎናውያን አማካይነት እንደሆነ በተገነዘበ ጊዜ ግን ግራ ተጋባ። ቅዱሱ ዳኛ እግዚአብሔር ጥፋተኞች የነበሩትን አይሁድን ከእነርሱ እጅግ የባሱ ጥፋተኞች በነበሩት ባቢሎናውያን አማካይነት እንዴት ይቀጣል? በጥፋታቸው እጅግ የባሱትንስ እንዴት አይቀጣም? ብሎ ተናገረ።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም ክርስቲያኖች ዕንባቆም የጠየቃቸውን ዓይነት ጥያቄዎች የሚጠይቁባቸው ሁኔታዎች ምን ምን እንደሆኑ አብራራ።

4. የእግዚአብሔር ሁለተኛ መልስ፡- 

ሀ. ጻድቅ በእምነት ይኖራል (ዕንባቆም 2፡2-5)።

እግዚአብሔር ያደረገውን ነገር ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ሞክሮ አያውቅም። እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ትክክለኛነቱን ለማንም ማረጋገጥ አያስፈልገውም፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ በሚመለከት ማንም ጥያቄ ሊያነሣ አይችልም። ስለዚህ ማንም ስለ ሥራው ጥያቄ ሲያነሣ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ጥያቄውን የሚመልሰው በተዘዋዋሪ መንገድ ነበር። ዕንባቆም ስለ እግዚአብሔር የአሠራር መንገዶች በጠየቀ ጊዜ በመጀመሪያ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ነገረው። ይህም ጻድቅ በክፉ ጊዜያትም ያልፋል የሚል ነው። በእግዚአብሔር ዓላማዎች በምንገረምበት ጊዜ እግዚአብሔር ባይቆጣም እንኳ አንድን ነገር ለምን እንዳደረገ በመጠየቅ እርሱን የመፈታተን መብት የለንም። ጻድቅ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ፥ በአደጋ ውስጥ፥ ወይም በክፉና ጠማማ ነገሮች ውስጥ ሲሆን ዘወትር ዓይኖቹን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ ይጠበቅበታል። እምነቱን በእግዚአብሔርና ባሕርያቱ ላይ ማድረግ ዘወትር ከእርሱ የሚጠበቅ ነው። ለእግዚአብሔር መኖር የተሻለ ጥቅም የማያስገኝ በሚመስልበት ጊዜ እንኳ በታማኝነትና በጽናት ለመኖር መወሰን አለበት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዕንባቆም 2፡4 ክርስቲያን ሊመማር ከሚገባቸው እጅግ አስፈላጊ መንፈሳዊ ትምህርቶች አንዱ የሆነው በምን መንገድ ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ያሉ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወይም እምነታቸውን ለመተው በሚፈተኑበት ጊዜ ይህን ትምህርት እንዴት ልታስተምራቸው ትችላለህ? 

ለ. ባቢሎናውያን ይቀጣሉ (ዕንባቆም 2፡6-20)።

እግዚአብሔር ዕንባቆም ለጠየቃቸው ጥያቄዎች የተሟላ ምላሽ ባይሰጠውም እንኳ ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ እንደሚቀርብ ያስታውሰዋል። እግዚአብሔር አይሁድን ለመቅጣት ባቢሎናውያንን የተጠቀመ ሲሆንም እንኳ በባቢሎናውያን ላይ አይፈርድም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር አንድን ሰው ተጠቀመበት ማለት ደገፈው ማለት አይደለም። አንድ ቀን የእግዚአብሔር ፍርድ ባቢሎናውያንንም ያፋጥጣቸዋል። ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍርድ የሚጀምረው ከቤቱ ስለሆነ (1ኛ ጴጥሮስ 4፡17)። በመጀመሪያ አይሁድን ቀጥሎ ደግሞ ባቢሎናውያንን ለመቅጣት ወሰነ። እርግጠኛ ልንሆንበት የሚገባው አንዱ ነገር እግዚአብሔር በሰው ሁሉ ላይ እንደሚፈርድና ክፉና ጠማማ የሆኑ ሰዎች ደግሞ በእግዚአብሔር እንደሚቀጡ ነው። 

5. የዕንባቆም ጸሎት፡- ፍርድን በምታመጣበት ጊዜ ምሕረትህን አስብ (ዕንባቆም 3፡1-19)። 

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ውብ መዝሙራት ወይም ጸሎቶች አንዱ ዕንባቆም 3 ነው። ዕንባቆም ከእግዚአብሔር ጋር በተወያየበት ጊዜ ብዙ ነገሮችን ተምሯል። ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት ተምሯል። በሕዝቡ ላይ ፍርድን በሚያመጣበት ጊዜ ምሕረትን እንዲያስብ እግዚአብሔርን ጠየቀ። በተጨማሪም ያሉት ነገሮች በሙሉ ቢወሰዱበትም እንኳ ለእግዚአብሔር በታማኝነት እንደሚቆይ አረጋገጠ። ደስታው በእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ሰዎች ብዙ ጊዜ ደስ በሚሰኙበት ነገር እንደማይሆን አረጋገጠ። የእምነት ዋስትናው በእግዚአብሔር ላይ እንጂ ከእግዚአብሔር በሚሰጡ በረከቶች ላይ አልነበረም። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ እግዚአብሔር ኃይሉን እንደሚያድስና በታማኝነት እንዲቆይ እንደሚረዳው ያውቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዕንባቆም 3ን ደግመህ አንብብ። ሀ) ይህ ጸሎት ዛሬም ለምናደርገው ጸሎት በጣም ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ለ) ከዚህ ጸሎት ስለ እግዚአብሔር ምን እንማራለን? ሐ) እምነታችን እግዚአብሔር በሚሰጠን ሥጋዊ በረከቶች ላይ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ላይ ብቻ መሆን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? መ) ከትንቢተ ዕንባቆም የተማርሃቸው አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/NgUhcTggAyyRk5R28

1 thought on “የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች”

  1. በትምህርቱና በሰጣችሁኝ ማብራሪያ እጅግ ተጠቅሜበታለሁ፣ ተምሬበታለሁ፣ ተባርኬበታለሁ።
    እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ !!!

Leave a Reply to Netsanet MiftahCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading