ምሳሌ 10-31

ምሳሌ 10-20

ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን፥ እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ እንደሆነ ብዙ ጊዜ እንናገራለን። እንደዚያም እያልን (እንዘምራለን፤ ችግሩ ግን ብዙ ጊዜ ይህ እውነት በሕይወታችን ውስጥ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ያለመቻሉ ነው። እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉስ ከሆነ፥ የሕይወታችን ንጉሥ ጭምር መሆን አለበት። ኢየሱስ የጌቶች ጌታ ከሆነ የሕይወታችንም ጌታ መሆን አለበት። ይህ እውነት በሕይወታችን ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ካላሳደረ፥ እግዚአብሔር ንጉሥ ነው፤ ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት አንዳችም ጥቅም የለውም። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር የሕይወትህ ንጉሥ መሆኑን ተረድተህ ሁልጊዜ ብትኖር ሕይወትህ የሚለወጥባቸውን መንገዶች ዘርዝር፡፡ ለ) ብዙ ክርስቲያኖች በአኗኗራቸው ይህን እውነት የሚያሳዩባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

በእውነት እግዚአብሔር ንጉሣችንና ጌታችን ከሆነ፥ በእርሱ ቁጥጥር ሥር የማይውል የሕይወታችን ክፍል አይኖርም። እያንዳንዱ የሕይወታችን ክፍል፥ አስተሳሰባችን፥ አኗኗራችን፥ ከድሆች ጋር ያለን ግንኙነት፥ አበላላችንና አጠጣጣችን ሁሉ በወንጌል አዎንታዊ ተጽዕኖ ሥር ይውላል። መጽሐፈ ምሳሌ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን በአጫጭር አባባሎች በመግለጥ እንዴት እግዚአብሔር የሕይወታችን ጌታ እንደሚሆን ያስረዳል። መጽሐፈ ምሳሌ የማይዳስሰው የሕይወት ክፍል የለም። አምልኮአችን እንዴት መሆን እንዳለበት ብቻ ሳይሆን፥ በሕይወታችን ሁሉ ፈሪሀ-እግዚአብሔር በሞላበት ጥበብ እንዴት እንደምንኖር ያስተምረናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 10-20 አንብብ። ሀ) እነዚህ ምሳሌዎች ቀጥለው ስለተዘረዘሩት ነገሮች ምን እንደሚያስተምሩ ዘርዝር፡- 

1. ስለ መብላትና መጠጣት። 

2. ከጉረቤቶቻችንና ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት 

3. አንደበታችንን በሚገባ ስለ መጠቀም፥ 

4. ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግ እንዴት እንደምንችል፥ 

5. እንደ አሠሪና ሠራተኛ ሆንን ስለ መሥራት፥ 

6. ስለ አመራር፥ 

7. ስለ ሀብት ሊኖረን ስለሚገባ አመለካከት፥ 

8. ከድሆች ጋር ስላለን ግንኙነት፥ 

9. ለጋብቻ የምንመርጠው የትዳር ጓደኛ ዓይነት፥ 

10. እንዴት ጥበበኞች እንደምንሆን፥ 

11. መልካም መዳጅ ምን ዓይነት እንደሆነ፥ 

12. ልጆችን በጌታ መንገድ ስለ ማሳደግ። 

ለ) ክርስቲያኖች እነዚህን መመሪያዎች ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ሐ) እነዚህን መመሪያዎች ለቤተ ክርስቲያንህ አባሎች እንዴት ታስተምራቸዋለህ? 

እውነቶቹ ግልጽ ስለሆኑ፥ ለዚህ ክፍል ምንም ማብራሪያ አያሻውም። ማስታወሻ፡- አንዳንዶቹ ምሳሌዎች በሕይወት ውስጥ ምን እንደሚሆን የሚናገሩትን ያህል ምን ማድረግ እንዳለብን አይናገሩም። ለምሳሌ ያህል በመጽሐፈ ምሳሌ 19፡7 «ድሀን ሰው ወንድሞቹ ሁሉ ይጣሉታል» የሚል ቃል እናነባለን። መሆን ያለበት ግን እንደዚህ አይደለም። ድሆችን መርዳት እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምረናል። የሚነግረን ድሆች ብዙ ጊዜ ስለሚደርስባቸው ነገር ነው እንድንንቅና እንድንተው የሚያበረታታን አይደለም። መጽሐፈ ምሳሌ በሕይወት ውስጥ መደረግ ያለበትን ነገር ሳይሆን የሕይወትን ዝንባሌ ያንጸባርቅልናል። በምሳሌ የተገለጡ ነገሮች በሁሉም ሁኔታ ውስጥ እውነት ላይሆኑ ይችላሉ።

ምሳሌ 21-31 

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 31፡10-31 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ስለ መልካም ሚስት የገለጹዋቸውን ባሕርያት ዘርዝር። ለ) ብዙ ሰዎች ከመልካም ሚስት ወይም ባል የሚፈልጉት ምንድን ነው? ባል ወይም ሚስት በሚመርጡበት ጊዜ አስፈላጊው ነገር ምንድን ነው? ሐ) ይህ በምሳሌ 31 ሴትን መልካም ሚስት ከሚያደርገው ባሕርይ ጋር የሚያወዳደረው እንዴት ነው? መ) ሚስትን በመምረጥ ረገድ እጅግ አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች ይህ ምዕራፍ ምን ያስተምረናል? 

በሕይወት ውስጥ በሁለተኛነት ደረጃ የምናደርገው ከፍተኛ ውሳኔ ማንን እንደምናገባ የምንወስነው ነው። ክርስቲያን ስለ ፍቺ ለማሰብ አይችልም፤ ስለዚህ ለማግባት ከምንወስነው ተቃራኒ ፆታ ጋር የምናደርገው ቃል ኪዳን የዕድሜ ልክ ነው። በመሆኑም ስለ ትዳር ጓደኛችን ለመወሰን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሆኖም ግን የተቀረው ዓለምና እንዲሁም ብዙ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ ጥሩ መሠረት የሌላቸው መሆኑ የሚያሳዝን ነገር ነው። ለምርጫቸው ብዙ ጊዜ ሦስት መመዘኛዎችን ይጠቀማሉ፡፡ 

1. በሰዎች አመለካከት መልከ መልካም ነውን (ናትን)? 

2. ሀብትና እውቀት አለውን (አላትን)? 

3. እርሱ ወይም እርሷ ከትክክለኛ ቤተሰብ የተገኙ ናቸውን? ወላጆቻቸው ወንጌላውያን ወይም የታወቁ ናቸውን? ወይስ ባሪያዎች፥ ወይም ሸክላ ሠሪዎችና ብረት ቀጥቃጮች ናቸው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድ በእነዚህ መመዘኛዎች የሚጠቀሙት ምን ያህል ክርስቲያኖች እንደሆኑ ግለጽ። ለ) እነዚህ መመዘኛዎች፥ የትዳር ጓደኛ የሚመርጥ ክርስቲያን ይጠቀምባቸው ዘንድ ትክክል ያልሆኑት ለምንድን ነው? 

መጽሐፈ ምሳሌ ስለ ትዳር ጓደኛ አመራረጥ ፍንጭ ይሰጠናል። ግልጽ የሆነውን ማብራሪያ የምናገኘው በምዕራፍ 31 ከተጠቀሰችው መልካም ሴት ነው። በእነዚህ ቍጥሮች በደም ግባትና በውበት ላይ ተመሥርተን እንዳንመርጥ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል (ምሳሌ 31:30)፡፡ በመሠረቱ አንዲትን ሴት መልካም ሚስት የሚያደርጓትን ነገሮች ብዙ ጊዜ ወንዶች የማይቀበሉኣቸው ናቸው። እነዚህ ቍጥሮች ለአንዲት ሴት ትልቅ ክብርና ሞገስ እንዲሁም በኅብረተሰቡ መካከል ከሁሉ የላቀ ስፍራ ስላሚያስገኝላት ባሕርያት ይናገራሉ። በምሳሌ 31 ስለ መልካም ሚስት የተጠቀሱ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡- 

1. መልካም ባሕርይና ከበሬታ ያላት ናት (ምሳሌ 31፡10፡ 25)። 

2. በምታደርገው ነገር ሁሉ እምነት የሚጣልባት ስለሆነች የባልዋ ልብ ይታመንባታል (ምሳሌ 31፡11)። 

3. ለባልዋና ለልጆችዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለማቅረብ ትጉ ናት። 

4. ጐበዝና ጠንካራ ስለሆነች በራስ አነሣሽነት ወደ ገበያ በመሄድ ትገዛለች ትሸጣለች። በባሏ ሥር ብቻ የምትተዳደር ባሪያ አይደለችም። ይልቁንም ቤተሰቧን ትንከባከባለች (ምሳሌ 31፡27)። 

5. ፈሪሀ-እግዚአብሔር የሞላባት፥ ጥበብ ያላትና ለሌሎች እውነተኛ ጥበብ የምታስተምር ናት። 

6. እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ናት። 

7. በባሏ የተመሰገነች ናት። 

በዚህ ዘመን ብዙ ሴቶች አይከበሩም፤ በባሎቻቸው ቍጥጥር ሥር ናቸው። በሥራ ቦታ፣ በቤትና በትምህርት ቤት በራሳቸው አነሣሽነት እንዲንቀሳቀሱ አይፈቀድላቸውም። በመጽሐፈ ምሳሌ ከተጠቀሰችው መልካም ሴት ሥዕላዊ ሁኔታ በጣም ለየት ያለ ነው። በመጽሐፈ ምሳሌ የተጠቀሰችው ሴት ፈሪሀ- እግዚአብሔር የሞላበት ባሕርይና ከፍተኛ የአእምሮ እውቀት ያላት፥ በሥራዋ ንግድን ለማካሄድ የምትችል፥ የቤተሰቧንና የሌሎችን ፍላጎት ለማሟላት በትጋት የምትሰራ ናት፡፡ እንዲያውም ለሌሎች ጥበብን የምታስተምር ሴት ናት (ምሳሌ 31፡10፤ 8፡11)። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በእጅጉ የምታስደስትህ የትዳር ጓደኛ ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ እንዲህ ዓይነቷን ሴት ፈልግ። ሴቷ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ወንድ ትፈልግ። መልካም የትዳር ጓደኛ፡ ውበት፥ ሀብት፥ ወይም ከመልካም ቤተሰብ የመገኘትን መመዘኛ ማሟላት እንዳለበት በሚናገረው የዓለማዊ ጥበብ ወጥመድ ተሰናክላችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። 

የውይይት ጥያቄ፥ በቤተ ክርስቲያንህ ለሚገኙ ወጣቶች ጥሩ የትዳር ጓደኛን ስለ መምረጥ እንዴት ታስተምራቸዋለህ? 

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 21-31 አንብብ። ሀ) እነዚህ ምሳሌዎች ስለሚከተሉት ነገሮች ምን እንደሚያስተምሩ ጥቀስ፡- 

1. ስለ መብላትና ስለ መጠጣት፥ 

2. ከጐረቤቶቻችንና ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት፥ 

3. አንደበታችንን በሚገባ ስለ መጠቀም፥ 

4. ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት፥ 

5. ሥራን እንደ አሠሪና ሠራተኛ ሆኖ ስለ መሥራት፥ 

6. ስለ አመራር፥ 

7. ሀብትን በሚመለከት ስለሚታይ ዝንባሌ፥ 

8. ከድሆች ጋር ስላለን ግንኙነት፥ 

9. ለጋብቻ የምንመርጠው የትዳር ጓደኛ ዓይነት፥ 

10. ጥበበኞች ስለ መሆን፥ 

11. መልካም ወዳጅ ምን ዓይነት እንደሆነ፥ 

12. ልጆችን በጌታ መንገድ ስለ ማሳደግ። 

ለ) ለክርስቲያኖች እነዚህን መመሪያዎች ማወቅ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ለቤተ ክርስቲያንህ አባሎች እነዚህን መመሪያዎች እንዴት ታስተምራቸዋለህ? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.