የመጽሐፈ ምሳሌ ዓላማ እና በመጽሐፈ ምሳሌ ያሉ ዐበይት ትምሕርቶች

የመጽሐፈ ምሳሌ ዓላማ 

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 1፡2-7 አንብብ። መጽሐፈ ምሳሌ የተጻፈበትን የተለያየ ምክንያት ዘርዝር። 

መጽሐፈ ምሳሌ ሰዎች በተለይም በወጣትነት ዘመናቸው በአኗኗራቸው ጥበበኞች እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል መጽሐፍ ነው። የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊዎች ትኩረት ሰዎች ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ እንዲያውቁና ፍሬያማ ሕይወት መኖር እንዲችሉ ለማድረግ ነበር። በመጽሐፈ ምሳሌ መግቢያ ላይ እንደተመለከትነው (1፡1-7) ምሳሌዎቹ የሚከተሉትን ተጨባጭ ትምህርቶች ያስተላልፋሉ፡- 

– ሰው ጥበብ፥ ማስተዋልና እውቀት እንዲያገኝ፥ 

– ሰው ትክክለኛ፥ ፍትሐዊና፥ መልካም ነገርን እንዲያደርግ፥ 

– ሰው የተለያዩ ምሳሌዎችን፥ ምሳሌያዊ አነጋገሮችንና እንቆቅልሾችን እንዲረዳ፥ 

– ጥበበኞች በጥበባቸው ላይ ተጨማሪ ጥበብ እንዲያገኙ ለመርዳት፥ 

– ሰው ሥርዓት በተሞላበት ሕይወት እንዲኖር ለማስቻል፥ 

– ሰው የጥበብ መጀመሪያ የሆነውን «እግዚአብሔርን መፍራት» እንዲማር ለመርዳት። 

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 2፡1-9 አንብብ። ሀ) ጥበብ የሚያስገኛቸውን አንዳንድ ጥቅሞች ዘርዝር። ለ) ፈሪሀ እግዚአብሔር የተሞላበትን ጥበብ በሙሉ ኃይላችን የመፈለግ አስፈላጊነት ምንድን ነው? 

የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች መጽሐፈ ምሳሌ በርካታ ጥቅሞችን ይዘረዝራል፡- 

– ጥበበኛ ሰው እግዚአብሔርን መፍራት የሚያውቅና ስለ እግዚአብሔር እውቀት ያለው ነው። (ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ግንኙነት ኖሮት፥ ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት የሚመላለስ ነው)። 

– እግዚአብሔር ለጥበበኛ ሰው ጥበብን ጨምሮ ይሰጠዋል፤ ከሚጐዳው ነገርም ይጠብቀዋል። 

–  ጥበበኛ ሰው በጽድቅ፥ በቅን ፍርድና ሰዎችን በእኩልነት ይመለከታል። 

– ጥበበኛ ሰው ከእግዚአብሔርና ከሰው ዘንድ ሞገስን ያገኛል (3፡4)። 

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ልብ በልና በቃልህ አጥና፡- ምሳሌ 9፡10፤ ምሳሌ 3፡5-6። እነዚህ ጥቅሶች በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚገኙ አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ አሳጥረው የሚያቀርቡት እንዴት ነው? 

በመጽሐፈ ምሳሌ ያሉ ዐበይት ትምህርቶች 

መጽሐፈ ምሳሌ የሕይወትን ክፍሎች በሙሉ ስለሚመለከት ቁልፍ የሆኑ ትምህርቶቹን ሁሉ ማሳጠር አስቸጋሪ ነው፤ ይሁን እንጂ መጽሐፉን በምናነብበት ጊዜ የሚከተሉትን ትምህርቶች ያለ ማቋረጥ ተደጋግመው እናገኛለን፤ ስለዚህ የመጽሐፉ ዐበይት ትምህርቶች ይሆናሉ፡- 

1. እግዚአብሔርን መፍራት፡- እግዚአብሔርን መፍራት ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት እግዚኣብሔርን እንደ አስጨናቂና አስደንጋጭ ቆጥሮ መንቀጥቀጥ ማለት ነውን? አይደለም። ይልቁንም እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በእግዚአብሔር ፊት በአምልኮና ራስን በማስገዛት መኖር ማለት ነው። ይህ አመለካከት ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ትክክለኛ ግንኙነትና ትእዛዛቱን ሁሉ መፈጻምን የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በትክክለኛ አካሄድና አመለካከት እንኖራለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሕይወትህ «እግዚአብሔርን መፍራት» እንዳለብን ያንጸባርቃሉ ብለህ የምታምናቸውን ለየት ያሉ ጥቂት ምሳሌዎችን ስጥ። አንተም ሆንክ ሌሎች ሰዎች የምታደርጓቸውና በሕይወት ውስጥ «እግዚአብሔርን መፍራት» እንደሌለ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ስጥ። 

መጽሐፈ ምሳሌ ጥበበኛ ለመሆን ሁለት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ያስተምራል። በመጀመሪያ፥ ሕይወታችን ለእግዚአብሔር ፍላጎት የሚገዛ መሆኑን የሚያሳይ ተገቢ የሆነ ግንኙነት ያስፈልጋል። ሕይወታችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር በምናስገዛበት ጊዜ እርሱ ጥበብን ይሰጠናል። ስለዚህ ጥበብ ለሚያውቁትና ለእርሱ ክብር ለሚኖሩ ሰዎች እግዚአብሔር የሚሰጠው ስጦታ ነው። ሁለተኛ፥ ጥበብ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ስንሰጠውና አጥብቀን ስንፈልገው ብቻ የምናገኘው ነገር ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ጥበበኞች እንዲያደርገን በብርቱ መሻት ያስፈልጋል። 

2. እግዚአብሔር ጻድቃንን ይባርካል፤ ክፉዎችን ይቀጣል። ሌሎች የግጥም መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት፥ መጽሐፈ ምሳሌም ሰዎች ሊመርጧቸው ስለሚችሉ ሁለት የተለያዩ መንገዶች ብዙ ነገሮችን ይናገራል። አንደኛ፥ ወደ በረከት የሚመራ፥ እግዚአብሔርን የመታዘዝ፥ የጽድቅ መንገድ አለ። ሁለተኛ፥ ወደ ቅጣት የሚመራ፥ የኃጢኣተኝነትና ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ መንገድ አለ። 

መጽሐፈ ምሳሌ በሕይወታችን ውስጥ በረከት ይሆን ዘንድ መጠበቅ የሚገባን ሁለት ግንኙነቶች እንዳሉ ይናገራል። የመጀመሪያው፥ ሕይወታችን ያለማቋረጥ ልንኖረው የሚያስፈልግ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ቀጥተኛ ግንኙነት ሲሆን ሁለተኛ፥ በትይዩ አብረውን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በትክክለኛ፥ በቅንነትና ተገቢ የሆነ ድርጊት በመፈጸም የሚኖረን ግንኙነት ነው። 

ደግሞም ምሳሌዎችን ስንተረጕም ለእግዚአብሔር በምንታዘዝበ ወይም በማንታዘዝበት ጊዜ ምን እንደሚደርስብን በማስገንዘብ የሰውን ሕልውና በጥንቃቄ በማጥናት ላይ የተመሠረቱ አጠቃላይ መመሪያዎች መሆናቸውን ማስተዋል አስፈላጊ ነው። ሆኖም ግን ሁልጊዜ ተፈጻሚ የሚሆኑ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች አይደሉም። በመጽሐፈ ኢዮብ እንደተመለከትነው፥ በጽድቅ የመኖር ሕይወት ብዙ ጊዜ በረከትን የሚያስገኝ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ብዙ መከራና ሥቃይን ሊያስከትል ይችላል። 

3. ጥበበኞች ለመሆን አንደበታችንን መግታት መማር አለብን። በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ በአንደበታችን እንዴት እንደምንጠቀምና ያልተገራ አንደበት ስለሚያመጣቸው ክፉ ነገሮች፥ ብዙ ተጽፎአል። እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ሰባት ነገሮች መካከል ሦስቱ ያልተገራ አንደበት ውጤቶች ናቸው (ምሳሌ 6፡16-19 ተመልከት)። የሰው አንደበት አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ከፍተኛ ኃይል ያለው ነው። የሕይወትና የሞት (ምሳሌ 18፡21) ወይም የማቍሰልና የመፈወስ ኃይል አለው (ምሳሌ 12፡18፤ ምሳሌ 15፡14)። ንግግራችን ትርጕም ያለው እንዲሆን ለማድረግ ከትክክለኛ ድርጊት መነሣት አለበት (ምሳሌ 14፡23፤ ምሳሌ 24፡12)። ብዙ ጊዜ የምንናገራቸው ቃላት ባሕርያችንን ይገልጻሉ። እግዚአብሔርን የምንፈራ ሰዎች ከሆንን ቃላችን ቅን (ምሳሌ 16፡13)፣ ልዝብ (ምሳሌ 15፡1) እንዲሁም በትክክለኛ ጊዜ የሚነገር መሆን አለበት (ምሳሌ 15፡23)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ያዕቆብ 3ን አንብብ። ሀ) እነዚህ ቍጥሮች አንደበታችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ምን ያስተምሩናል? ለ) አንደበታችንን ካልገራን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች ምን አይነት ናቸው? ሐ) የምንናገራቸውን ነገሮች ለመቈጣጠር ልናደርጋቸው የምንችል ነገሮች ምንድን ናቸው? 

4. በእግዚአብሔር አመለካከት ጥበበኞች የሆኑ ሰዎች ትክክለኛ የትዳር ጓደኛ ስለሚመርጡ በፍትወተ ሥጋ ሃጢአት አይወድቁም፡፡ መጽሐፍ ምሳሌ የትዳር ጓደኛን በጥንቃቄ ስለ መምረጥ አስፈላጊነትና በፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ስለ መውደቅ አደገኛነት ይናገራል። አብዛኛዎቹ ምሳሌዎች ስለ ዝሙትና ፍትወተ ሥጋ ኃጢአት አደገኛነት ይናገራሉ። በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ ከምናገኛቸው ከሚከተሉት ትምህርቶች አንዳንዶቹን አስተውል፡- 

– ጥበብ እግዚአብሔር በሰጠን የትዳር ጓደኞቻችን ደስ እንድንሰኝ የሚያደርግ ነው። መልካም የትዳር ጓደኛ የመረጠ ሰው ከፍተኛ ደስታን ያገኛል (ምሳሌ 5፡15-23፤ 18፡22)። የትዳር ጓደኛን እንደ ቍንጅና ባለ ውጫዊ ገጽታ ሳይሆን፥ ውስጣዊ በሆነ የባሕርይ ብቃት በጥንቃቄ መምረጥ ያስፈልጋል (ምሳሌ 31፡ 10-31)። 

– ብዙ ጊዜ ሰውን ወደ ፍትወተ ሥጋ ኃጢአት የሚመሩት ዓይኖቹና አፉ ስለሆኑ በጥብቅ ሊገሩ ያስፈልጋል (ምሳሌ 5፡1-6፤ 7፡21-23)። 

– አመንዝራነት ወደ ቅንዓትና ሞት ይመራል (ምሳሌ 6፡20-35)። 

– የፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ወደ ሰዎች ቀስ በቀስ የሚመጣና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰውን በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ የሚችል ነው (ምሳሌ 23፡26-28)። 

– ለፍትወተ ሥጋ ኃጢአት አሳማኝ ምክንያት መስጠት እጅግ ቀላል ነው፤ እርሱም ወደ ልብ ክሕደት ይመራል (ምሳሌ 7፡10-23፤ 30፡20)። 

በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የሚገኙ ቊልፍ ቃላትና ሐረጎች 

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከትና የእያንዳንዳቸውን ፍቺ በአጭሩ ጻፍ፡- ጥበብ፥ ሰነፍ፥ ቀላል፥ ፌዘኛ፥ ታካች 

1. ጥበብ፡- ቀደም ሲል ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለበትን ጥበብ ከዓለማዊ ጥበብ ጋር በማነጻጸር ተመልክተናል። እውነተኛ ጥበብ ከእግዚአብሔር የሚመጣ ለእግዚአብሔርና ለሥልጣኑ መገዛትን የሚጠይቅ ነው። ጥበብን ስንፈልገው እየጨመረ ይሄዳል፤ ግቡም እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ በመኖር በይበልጥ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ እውቀት፥ ግንዛቤ፥ የመለየት ችሎታና ማስተዋል ሁሉ ከጥበብ ጋር የተያያዙ ናቸው፤ ትኩረታቸውም የተጨበጠ እውነትን በማወቅ ሳይሆን፥ እውነትን በሕይወት በመለማመድ ላይ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) እውነትን ከማወቅ ይልቅ በምናውቀው እውነት መኖር የበለጠ ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ትክክለኛ የሆነውን ነገር ከማወቅ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ማድረግ ወይም መሆን የበለጠ [አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መልስህን አብራራ። 

2. ሰነፎች፡- በመጽሐፈ ምሳሌ ሰነፎች ወይም ሞኞች በእውቀት ሰነፎች የሆኑ አይደሉም፤ ይልቁንም ሰነፍ ለክርክርና ለውይይት ፈቃደኛ ያልሆነና ጥበብን የማይፈልግ ሰው ነው። ለእውነት የጠለቀ ኣክብሮት የሌለው፥ ጥበብንና ምክርን የማይቀበል ነው። ሰነፍ በኃጢኣት የሚቀልድና እግዚአብሔርን የማይሰማ ነው (ምሳሌ 1፡7፤ 14፡9)። 

3. ፌዘኛ፡- ሰው እንዲገሥጸው የማይፈልግ፥ በጥበብ የማያድግ እያወቀ በሌሎች ሰዎች ላይ ችግር የሚፈጥር ነው (ምሳሌ 9፡7፣ 8፤ 14፡6፤ 21፡24፤ 22፡10)። 

4. ታካች፡- ታካች እጅግ ደካማና ሰነፍ ሰው ነው። አንድን ነገር አይጀምርም፤ ከጀመረ ደግሞ አይፈጽመውም። ለነገሮች ሁሉ ምክንያትን ይሰጣል። የሚሰጣቸው ምክንያቶች ደግሞ ለራሱ በቂ እንደሆኑ አድርጎ ያምንባቸዋል። ስንፍናውም ወደ ድህነት ይመራዋል (ምሳሌ 6፡6፥ 9፤ 13፡4፤ 19፡24፤ 20፡4፤ 24፡30)። 

5. ወዳጅ፡- መጽሐፈ ምሳሌ ይህንን «ወዳጅ» የሚለውን ቃል የሚጠቀመው አንዳንድ ጊዜ ለጐረቤት ቢሆንም፥ ልዩ ስለሆነ ጓደኛም ይናገራል። ወዳጅ ከቤተሰብ ዝምድና የላቀ ኅብረት ያለው ነው። በችግር ጊዜ ድጋፍ የሚሆን፥ ከንጹሕ ልብ የሚተች፥ ተግሣጽና መልካም ምክርን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ነው (ምሳሌ 17፡17፤ 18፡24፤ 22፡11፤ 27፡6፥ 9-10)። 

የውይይት ጥያቄ፥ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የሚገኙትን አምስት ቁልፍ ቃላት የሚመለከቱ ምሳሌዎችን ከሕይወትህ ጥቀስ፡፡ 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ የተመሠረቱ ስብከቶች ጥቂት የሆኑት ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ሰዎች በኃጢአት ከመውደቅና ሕይወታቸውን ከማበላሸት ይድኑ ዘንድ መጽሐፈ ምሳሌን መረዳት እንዴት ይረዳቸዋል? ሐ) ምእመናን ጥበበኞች ይሆኑ ዘንድ ለመርዳት ቤተ ክርስቲያንህ የመጽሐፈ ምሳሌን እውነት በበለጠ ለማስተማር ምን ማድረግ ትችላለች?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: