የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በሰው ድነት (ደኅንነት) ውስጥ፤ ክፍል 3

በኤፌ. 1፡3–14 ጳውሎስ እግዚአብሔር በሰማያዊ ስፍራ ባለ መንፈሳዊ በረከት ሁሉ ክርስቲያኖችን ስለባረከን ያመሰግናል። ባለፉት ሁለት ቀናት ትምህርት በዳንንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በርካታ በረከቶችን ሕይወትን የሚለውጡ በረከተችን፥ ተአምራዊ በረከቶችን እንደሰጠን እይተናል። ስለሆነም እግዚአብሔር እንድናመሰግነው መፈለጉ የሚያስገርም አይሆንም። ወደ ክርስቶስ በእምነት ስተመለስንበት ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ስለሰጠን በረከቶች በሙሉ አብረን እግዚአብሔርን ከማመስገን ሌላ ምንም ማለት አንችልም። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ። 2ኛ ቆሮ. 1፡22፤ 5፡5፤ ኤፌ. 1፡13፤ 4፡30፤ ዮሐ 1፡12፤ ሮሜ 8፡13-17፤ ገላ. 4፡5-7፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡13። ሀ) አንድ ሰው ገና በሚድንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያን በሆነው ሰው ውስጥ ስለሚሠራቸው ሥራዎች እነዚህ ጥቅሶች የሚሰጡትን እውነቶች ዘርዝር። ለህ እያንዳንዱ በረከት ስለያዛቸው ነገሮች አጭር መግለጫ ጻፍ። 

1. የመንፈስ ቅዱስ ማኅተምና መያዣ (2ኛ ቆሮ. 1፡22፤ 5፡5፤ ኤፌ. 1፡13፤ 4፡30)። በጥንት ጊዜና ዛሬም በኢትዮጵያ ማኅተም በጣም ጠቃሚ ምልክት ነው። የባለቤትነት ምልክት ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፥ አንድ ሰው በአንድ ነገር ላይ ማኅተም ሊያደርግ የዚያ ነገር ባለቤት መሆኑን ያሳያል። (መጻሕፍት ላይ ስማችንን ስንጽፍ የእኛ መሆናቸውን እንደምናመለክተው ዓይነት ማለት ነው።) ደግሞም አንድ ድርጅት ለመንግሥት ወይም ለሌላ ድርጅት በሚልከው ማንኛውም ኦፊሴላዊ ደብዳቤ ላይ እንደሚጠቀምበት ሁሉ፥ ማኅተም የሕጋዊ ሰነዶችን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነው። ደብዳቤው ሳይከፈት እንዲደርስ በፓስታው እፍ ማኅተም እንደምናሳርፍ ሁሉ፥ አንድ ሰነድ ያልተለወጠና ሕጋዊ ስለመሆኑ ማኅተም በምልክትነት ያገለግላል። መያዣ ደግሞ የመጨረሻው ክፍያ በሚካሄድበት ጊዜ ሙሉ ባለቤትነት ላይ እንደሚደረስ ዋስትና የሚሰጥ ነገር ነው። 

በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ማኅተም እንደሆነ ወይም በአማኙ ላይ ማኅተም የሚያደርግ እንደሆነ ተነግሮናል። ማኅተም የሚደረግበት አማኙ ነው። ማኅተም አድራጊው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በመጠቀም በሆነ መንገድ እያንዳንዱን ልጁን ያትምበታል። በእግዚአብሔር ማኅተም የሚደረግበት ማን ነው? በአዲስ ኪዳን ውስጥ ክርስቲያኖች ማኅተም እንደተደረገባቸው በተጻፈባቸው ቦታዎች ሁሉ ማኅተሙ የተደረገባቸው ክርስቲያኖች በሙሉ ናቸው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ብቻ ማኅተም እንደተደረገባቸው የሚያመለክት ነገር የለም። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንኳ ያ ሁሉ ችግር በቤተ ክርስቲያናቸው እያላ በእግዚአብሔር እንደታተሙ ተጽፎአል። በተጨማሪ ክርስቲያን ይታተምበት ዘንድ እንዲያደርገው የተጠየቀው አንዳችም ትእዛዝ የለም። ለምሣሌ፡- ይታተም ዘንድ መጸለይ የለበትም። ስለዚህ አንድ ሰው በኢየሱስ በሚያምንበት ወቅት ወዲያውኑ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያትመው ማሰብ እንችላለን። መንፈስ ቅዱስ በተጨማሪ አሁን በከፊል ሐሴት ለምናደርግባቸውና ወደ መንግሥተ ሰማያት ስንደርስ በሙላት የእኛ ስለሚሆኑት በረከቶች የሚያረጋግጥልን መያዣችን በመሆንም ይሠራል። 

አዲስ ኪዳን በመንፈስ ቅዱላ ታትመናል፤ እርሱ ዋስትናችን ነው፤ ሊል ምን ማለቱ ነው? በዚህ የመንፈስ ቅዱስ ተግባር ውስጥ ሦስት ድርጊቶች የተጠቃለሉ ይመስላል። 

በመጀመሪያ፥ የባለቤትነት አሳብ አለበት። ማኅተሙ የእግዚአብሔር መሆናችን ማረጋገጥ ነው። 

በሁለተኛ ደረጃ ፥ የሥልጣን አሳብ አለው። እንድ ማኅተም ያለው ደብዳቤ ማኅተም ያደረገበትን አካል ሥልጣን የያዘ እንደሆነ፥ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ማኅተም በእኛ ላይ መኖሩ የንጉሥ ልጆች ከመሆናችን የተነሣ የእግዚአብሔር ሥልጣን እንዳለን የሚያሳይ ምልክት ነው። 

በሦስተኛ ደረጃ ፥ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች በሙሉ እንደምንቀበል ማኅተሙ ዋስትና ነው። የእግዚአብሔር ንብረቶች እንደምንሆን ዋስትና የሚሰጥ ነው። በእግዚአብሔር ተስፋ የተገባልንን በረከቶች በሙሉ በተለይም ደግሞ የዘላለም ድነት (ደኅንነት) ተስፋ እንደምንቀበል የሚያረጋግጥ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚያምኑት ወደ መንግሥተ ሰማይ እስክንደርስ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን ከእውነተኛ እምነት ተሳስተን እንዳንወድቅ እንደሚከልለን የሚያረጋግጥ ዋስትና ነው። እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ማኅተም አንድ ጊዜ ካደረገብን በኋላ ወድቀን ደኅንነታችንን እንድናጣና ከዘላላም ሽልማታችንም እንድንቀር የሚያደርገን እንዳችም ነገር የለም። 

ጥያቄ፡– መንፈስ ቅዱስ የሚያትመን የመሆኑ እውነት ዛሬ እንዴት ሊያበረታታን ይገባል? 

2. መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ የልጅነት መብት ሰጥቶናል (ዮሐ 1፡12፤ ሮሜ 8፡13-17፤ ገላ. 4፡5-7)። ከአዲስ ኪዳን አስደናቂ እውነቶች አንዱ በዳንንበት ወቅት እግዚአብሔር ጠላቶቹ የነበርነውን እኛን ልጆቹ ማድረጉ ነው። ይህ ሂደት ማደጎነት ወይም ልጅነትን መቀናጀት ይባላል። በጥንት ጊዜ ሮማውያንና ግሪኮች ልጅ ያልወለዱ ወላጆች የሌላን ሰው ልጅ ወይም የባሪያን ልጅ እንኳ ሰመውሰድ በሕግ የራሳቸው ልጅ ያደርጉ ነበር። ወደ ቤተሰቡ የተጨመረው የማደጎ ልጅ ወዲያውኑ በሥጋ እንደተወለደ እንደማንኛውም ልጅ ሕጋዊ መብቶችን በሙሉ ያገኛል። 

ምንም ልዩነት አይደረግበትም። እነዚህ ወላጆች በሥጋ የወለዱት ልጅ ቢኖራቸው የመውረስ ሙሉ መብት እንዳለው ሁሉ ይህም ልጅ ይኖረዋል። 

በዳንንበት ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ እኛን ወስዶ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ያስቀምጠናል። የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን የሚገኝ መብት፥ ደረጃ ግዴታዎች በሙሉ ይሰጡናል። ይህ የልጅነት ስፍራችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነቶች ሙሉ በሙሉ ይለውጣል። ክዚህ ቀደም በፍርሃት ከእግዚአብሔር ርቀን እንዳልነበርን አሁን ግን በሙሉ ልብ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን። መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ የእግዚአብሔር ተወዳጅ ልጆች መሆናችንን ያሳስበናል። ትንሽ ልጅ ምድራዊ አባቱን «አባዩ» ብሎ እንደሚጠራ ከእግዚአብሔር ጋር እጅግ በቀረበ መንገድ እንድንነጋገር ያስችለናል። በልጅነታችን በእግዚአብሔር ተስፋ የተገቡልንን ዘላለማዊ በረከቶች በሙሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንደምንወርስ ቃል ገብቶልናል። ነገር ግን ይህ መብት ከግዴታዎች ጋር አብሮ የሚመጣ ነው። እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንገድ በመኖር የቤተሰቡን ስም እንዳናጎድፍ መጠንቀቅ አለብን። ልጅ ወላጆቹን እንደሚታዘዝ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ የመታዘዝ ግዴታ አለብን። 

ጥያቄ፡– እውነተኛ አማኝ ከሆንክ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ። ሀ) እግዚአብሔርን እንደ አባት ብትቆጥርና እንደ ፈጣሪ ብቻ ብትቆጥር ከእርሱ ጋር የሚኖርህ ግንኙነት የሚለወጠው በምን በምን መንገድ እንደሆነ በዝርዝር ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር አባትህን ምን ያህል እንደምትወደው ለመግለጽ ጊዜ ውሰድ። 

3. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት (1ኛ ቆሮ. 12፡13)። ይህን የጥናት መጽሐፍ በጻፈው ሰው አመለካከት መንፈስ ቅዱስ አንድን ሰው የማጥመቅ ሥራው የሚፈጸመው ሰውዬው በዳነ ጊዜ ከመቅጽበት ነው። አዲሱን አማኝ የክርስቶስ አካል በሆነችው ጽንፈ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የመጨመር ተግባር የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። ከየትኛውም ነገድ ይምጣ ምንም ዓይነት ፆታ ይኑረው ምንም ዓይነት ማኅበረሰባዊ አቋም ይኑረው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የዳነውን ሰው ወስዶ በክርስቶስ አካል ውስጥ እኩል ደረጃ ያለው አባል ያደርገዋል። በክርስቲያኖች መካከል ውዝግብ ከሚያስነሡ ጉዳዮች እንዱ ይህ በመሆኑ ወደፊት ባሉ ትምህርቶች በጥልቀት እንመለከተዋለን። 

ጥያቄ፡- ከ 1ኛ እስከ 4ኛ ቀን ያሉ ትምህርቶችን ከልስ። ሠንጠረዥ አብጅ። በመጀመሪያው ክፍል ውስጥ አንድ ሰው ክርስቲያን በሚሆንበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ የሚፈጽማቸውን ተግባራት በሙሉ ዘርዝር። በሁለተኛው ክፍል ይህ በረከት ምን ማለት እንደሆነ አጭር ገለጻ ጻፍ። በሦስተኛው ክፍል ውስጥ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ልጅነትህ ይህ በረከት ለምን ለአንተ ጠቃሚ እንደሆነ ግላጽ። 

አንድ ሰው በሚድንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የሚፈጽማቸውን አገልግሎቶች የዘረዘርን ቢሆንም እንኳ ከእነዚህ አብዛኛዎቹ አገልግሎቶች ተወራራሽ መሆናቸውን ማስታወስ ይገባናል። እንዲያውም አንዳንድ የሥነ መለኮት ሊቃውንት እነዚህ ሁሉ የዘረዘርናቸው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች በጥቅሉ የሚያመለክቱት አንድን ሁኔታ ነው ብለው ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው አንድ ሰው በሚድንበት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር ወልድ ልዩ ስጦታ ይቀበላል ብለው ያምናሉ። ይህ ስጦታ የመንፈስ ቅዱስ በሰው ልብ ውስጥ መኖር ወይም ማደር ነው። የዚህ የመንፈስ ቅዱስ ማደር ወይም መኖር በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል። እነዚህም «የመንፈስ ቅዱስ ተለፋ»፥ «የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ»፥ «የመንፈስ ቅዱስ ዘር»፥ «የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት»፥ በመንፈስ ቅዱላ ልጅ የመሆን ሂደት»፥ ወዘተ… ናቸው። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ግን አንድ ናቸው። ስለዚህ በእነዚህ አገልግሎቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳንፈጥር መጠንቀቅ አለብን። ከሁሉ የሚሻለው አመለካከት ይህ እያንዳንዱ አገልግሎት የአንዱ የመንፈስ ቅዱስ ህልውና የተለያየ ገጽታ መሆኑን መቀበል ነው። 

ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ትምህርት በስተቀር ክርስቲያኖች ሁሉ እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች በአዲሱ አማኝ ሕይወት ውስጥ የሚፈጸሙ እንደሆኑ ይስማማሉ። የሚያሳዝነው ነገር ግን ትኩረት የምናደርገው በአንድ ወይም በሁለት አገልግሎቶች ላይ ብቻ መሆኑ ነው። ሰመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ወይም በተወሰኑ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ላይ ማተኮር በሥነ መለኮት ትምህርታችን ሚዛናዊነትን ያሳጣናል። መንፈስ ቅዱስ ስለሚያከናውናቸው ስጦታዎች እንደ በልሳን መናገር፥ ፈውስ፥ ተአምራትና መገለጥ ያላችሁ እምነት ምንም ይሁን፥ ነገር ግን ከተእምራት ሁሉ የበላይ በሆነው ማለትም የአዲስ ልደት ተአምር ላይ እንድታተኩሩ አበረታታችኋለሁ። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ጠላት የሆነውን ሰው ወስዶ ወደ እግዚአብሔር ልጅነት ሊለውጠው ክማየት የላቀ አስደሳችና ተአምራዊ ድርጊት የላም። ሁላችንም የበለጠውን ትኩረታችንን በዚህ ተአምር ላይ ብናደርግ በሌሎች የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ላይ በክርስቲያኖች መካከል የሚነሡ አለመግባባቶች የደበዘዙ ይሆናሉ። በአብያተ ክርስቲያናት መካከልና በአማኞች መካከል ያለው አንድነት እንደገና ይታደሳል።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.