ከኤፌ 5፡18-20 በመንፈስ ቅዱስ ስላ መሞላት ምን ልንመለከት እንችላለን?

1. ትእዛዝ ነው። በመንፈስ ቅዱስ መሞላት እንዳለብን ተነግሮናል። ይህ ሁለት ነገሮችን ያመለክታል። በመጀመሪያ ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ ምርግ እንዳለን ነው። በመንፈስ ቅዱስ እንሞላ ዘንድ በእግዚአብሔር ጋር ለመሥራት እንችላለን። ወይም በመንፈስ ቅዱስ ከመሞላት የሚያግደንን ኦኗኗር መኖር እንችላለን። ሁለተኛ በዚህ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ተሳታፊዎች መሆናችንን ያመለክታል። እግዚአብሔር የማንሳተፍበትን ነገር እንድናደርግ አያዘንም። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ እንሞላ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ለመሥራት የምንችልበት መንገድ አለ። የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዕቅድ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ከግለሰቡ ፈቃድ ጋር የሚሄድ እንዲሆን አድርጐታል። መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን እንዲሞላና እንዲጠቀምብን ማድረግ ወይም በከፊልም ቢሆን ይህ እንዳይሆን መከላከል እንችላለን። 

2. በተደጋጋሚ የሚፈጸም ተግባር ነው። በግሪክ ቋንቋ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ትእዛዝ የአሁን ጊዜን በሚያመለክት ግሥ ነው የተጻፈው። ይህ ማለት በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላታችን ሁልጊዜ እርግጠኞች መሆን አለብን ማለት ነው። ይህ ማለት በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ፥ በሆነ ምክንያት ደግሞ ይህን ሙላት ልናጣና እንደገና መሞላት ሊያስፈልገን ይችላል ማለት ነው። ይህ እውነት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተመልክቷል። የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት በበዓለ ኀምሣ ቀን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ነበር (የሐዋ. 2፡4)። ቆይቶ ጴጥሮስ በካህናት ጉባኤ የፍርድ ወንበር ፊት በቀረበ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላ ተጽፏል (የሐዋ. 4፡31)። 

3. የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በጣም በተላመደ ነገር ግን ኃይል በሞላበት መንገድ ተገልጧል። በግሪኩ ቋንቋ ኤፌ. 5፡18-21 ያለው ቃል አንድ ዐረፍተ ነገር ነው። አንድ ትእዛዝ ማላትም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ» የሚለውን ይዟል። ይህ አንዱ ትእዛዝ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት ምልክት የሚሆኑ አራት ቅድመ-ሁኔታዎችን ያስከትላል። እነርሱም መናገር (ቁጥር 19)፥ መዝሙር (ቁጥር 19)፥ ምስጋና ማቅረብ (ቁጥር 20) እና ለሌሎች መገዛት (ቁጥር 2) ናቸው። 

በመንፈስ ቅዱስ በምንሞላበት ጊዜ መሞላታችን የሚረጋገጠው እንዴት ነው? በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ክአስደናቂ ድርጊቶች ጋር እንደሚያያዝ እናስብ ይሆናል። ምናልባት የሆነ ታላቅ ተአምር ወይም ልዕለ-ተፈጥሮአዊ ምልክቶች እንደሚያጅቡት እናስብ ይሆናል። ጳውሎስ በእነዚህ ጥቅሶች የሚናገረው ነገር ይህን አይደለም። የመንፈስ ቅዱስ መሞላት በሁለት ዋና መንገዶች ራሱን ይገልጻል። በመጀመሪያ፥ አመላለካችን ይቀየራል። ልባችን በመዝሙርና በምስጋና ይጥለቀለቃል። 

በሁለተኛ ደረጃ ፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላታችን ከሌሎች ጋር ያላንን ግንኙነት ይቀይራል። ተፈጥሮአችን የሆነውን የለለታምነታችንን ዝንባሌ ቀይረን በትሕትና ዝቅ ብለን ለሌሎች እራሳችንን እንድናስገዛ ያስችለናል። በዕድሜ የገፉ ለወጣቶች ፍላጐት እንደዚህም ወጣቶች በዕድሜ የገፉ ሰዎች ፍላጐት ይገዛሉ። ወንዶች ለሴቶች ሴቶችም ላወንዶች አመለካከት ይገዛሉ። ባሎች ለሚስቶች፥ ሚስቶች ደግሞ ለባሎች ይገዛሉ። ሀብታሞች ለድሆች፥ የተማሩት ላልተማሩት ወዘተ… ይገዛሉ። ሰዎች እግዚአብሔር በሰውዩው ሕይወት ኃይለኛ ነገር እየሠራ እንደሆነ ለማየት እስከሚገደዱ ድረስ ግንኙነቶች ይቀየራሉ። 

ጥያቄ፡- ሀ) በመንፈስ ቅዱስ ስለ መሞላት ይህ የተመለከትነው መረዳት እኛ ብዙ ጊዜ ካለን አመለካከት የተለየ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) መንፈስ ቅቶስ ለእግዚአብሔር ክብር የሆነውን ነገር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያደርግ ዘንድ ሥርዓት የሞላበት አምልኮና መልካም ግንኙነቶች ከሁሉ በላይ አስፈላጊ ነገሮች የሚሆኑት ለምንድን ነው? 

የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ከሕይወታችን የሚቋረጥበት ተቀዳሚ ምክንያት የራሳችንን ሕይወት ኃጢአት በሞላበት መንገድ ልንቆጣጠር በምንሞክርበት ጊዜ ነው። የራሳችንን ሕይወት ልንቆጣጠር በምንወስንበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ እኛን መቆጣጠሩን ያቆማል። ነገር ግን ንስሐ በምንገባበትና እግዚአብሔር ሕይወታችንን በሙላት እንዲቆጣጠር በምንጠይቅበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ እንደገና ይሞላናል። 

በክርስቲያኖች ሕይወት ብዙ ጊዜ ከደኅንነታቸው በኋላ ቀውስ የተፈጠረባቸው ወቅቶች ይኖራሉ። ውስጣዊ የሆነ ጥልቅ ሕይወታቸውን ለመቆጣጠር የሚካሄድ ትግል አለ። መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ዙፋን ላይ በመቀመጥ የምንፈልገውን፥ የምናደርገውንና የምንናገረውን ሁሉ ላመቆጣጠር ይፈልጋል። በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ግን የኖርነው እራሳችንን በመቆጣጠር ነው። ስለዚህ ታላቅ ጦርነት ይካሄዳል። በመጨረሻ ይህ ራስ ወዳድ የሆነው መንፈሳችን ይሰበራል። ለእግዚአብሔር ቁጥጥር እራሳችንን እሳልፈን እንሰጣለን። ትልቁ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በሕይወታችን ታላቅ ለውጥ ይከናወናል። ታላቅ ደስታና ሰላም ይሆናል። አገልግሎታችን ኃይልን ይቀዳጃል። ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ጉዞ ጣፋጭና በጥብቅ ቁርኝት የሚካሄድ ይሆናል። ሕይወታችንን ለመቆጣጠር የሚደረጉ እነስተኛ ውጊያዎች ይኖራሉ። ለኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን እራሳችንን የምናስገዛበትና እግዚአብሔር በላያችን ላይ እንዳይሠለጥን የምናደርግባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ወይም ቁጥጥር በዚያ ነጥብ ላይ ይጠፋል። ነገር ግን ለመንፈስ ቅዱስ ድምፅ ንቁ የመሆን ልምምድ በሕይወታችን ስለሚኖር ወዲያውኑ ወደ ጸጋ ዙፋኑ ፊት በመቅረብና ይቅርታን በመጠየቅ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ወደ መኖሩ እንመለሳለን። ከዚያም እንደገና በመንፈስ ቅዱስ እንሞላና በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንደገና እንቀጥላለን። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በሰው ሕይወት ውስጥ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ የበላይነት አግኝቶ ይቆጣጣር ዘንድ ወሳኙን ጦርነት ማካሄድ ነው። ከዚያም በክርስቲያን ሕይወት ዘመን ሁሉ የሕይወቱን እያንዳንዱን ክፍል የበለጠ በበላይነት ይቆጣጠር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ትናንሽ ጦርነቶችን ያካሄዳል። በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ ማለት ሕይወታችን ለዘላቄታው በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን መፍቀድን እንደሚያካትት እናያለን። 

ጥያቄ፡- ሀ) ስለ ራስህ ሕይወት አስብ። የእግዚአብሔር መንፈስ ሕይወትህን እንዳይቆጣጠር የታገልክባቸው ጊዜያት በእርግጥ ነበሩን? ያንን ልምምድህን ግላጽ። ለ) እንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ልምምድ ካልነበረህ መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ቀደም እንደሞላብህ እሁንም ሕይወትህን እያገዘ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለህ? ሐ) መንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ በሥልጣን እንዲገዛህ ያልፈቀድክባቸውን የሕይወትህን ክፍሎች እንዲያሳይህ በጸሎት ትጠይቀው ዘንድ አሁን ጊዜ ውሰድ። ስለ እነዚያ ሁኔታዎች ንስሐ ግባ። መንፈስ ቅዱስ እንደ አዲስ እንዲሞላህና ኢየሱስን እንድትመስል እንዲረዳህ ጸልይ። 

እንግዲያውስ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ትርጉሙ ምንድን ነው? በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ክርስቲያን ሕይወቱን ለመንፈስ ቅዱስ በማስገዛት በባሕርይና በተግባር የበለጠ ኢየሱስን እየመሰላ እንዲሄድ መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱን እንዲሠራ የሚፈቅድበት ተደጋጋሚ ልምምድ ነው።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.