የትንቢት ስጦታ ምንድን ነው?

ዛሬ የትንቢት ስጦታ በሚያካትታቸው ነገሮች ላይ በርካታ የተለያዩ እመለካከቶች አሉ። አንዳንዶች ትንቢት የእግዚአብሔርን ቃል ወስዶ በግልጽ ለማስተማርና ለሚሰሙት ሰዎች ሕይወት ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ሰማዛመድ ለማመልከት መቻል ነው ይላሉ። እግዚአብሔር በቃሉ ይናገራል እንጂ ቀጥተኛ መገለጥ መስጠቱን አቁሟል ይላሉ። በእነርሱ አመለካከት ምን መስማት እንዳለባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በአጠቃላይ መልኩ ለሰዎች መናገር የመንፈስ ቅዱስ ሚና ነው። ይሁንና፥ ስለ ትንቢት ይህን ጠባብ አመለካከት የምንቀበልበት ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለንም። 

ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሆኑ መንገዶች ቀን መልእክቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጋር በማይቃረንበት ሁኔታ ይናገራል ይላሉ። የአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ ዛሬም ለክርስቲያኖች የሚሠራ እንደሆነ ይቀበላሉ። በትንቢት መንፈሳዊ ስጦታና በነቢያት እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች ያለውን ፈቃድ ለየት ባሉ ቃሎች አማካኝነት ይናገራል ይላሉ። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ማቴ. 16፡17፤ ማቴ. 11፡27 1ኛ ቆሮ. 2፡10፤ ኤፌ. 1፡17። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች መሠረትነት «መግለጥ። ወይም «መገለጥ» ለሚለው ቃል ስላሉት የተለያዩ ዓይነት ትርጉሞች ምን መረዳት እንችላለን? ለ) በእነዚህ ጥቅሶች «መገለጥ» የሚለው ቃል የትንቢት አካል መሆኑን ብዙ ጊዜ በማንረዳበት ሁኔታ አገልግሎት ላይ የዋለው እንዴት ነው? ሐ) እነዚህ ጥቅሶች የትንቢት ስጦታ ሊያካትታቸው ስለሚችላቸው ነገሮች መረዳትን እንዴት ሊሰጡን ይችላሉ? 

ትንቢት እንዲኖር መገለጥ የግድ ያስፈልጋል። ነቢይ የሚለው ቃል ፍቺ እግዚአብሔር የገለጠለትን ለሰዎች የሚያስተላልፍ ማለት ነው። ነገር ግን መገለጥ በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል የግድ በድንቃ ድንቅ መንገዶች ብቻ አይደለም የሚመጣው። 

1. መገለጥ እግዚአብሔር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሰውዬው በማይረዳበት ሁኔታ እንኳ የሚያስቀምጠው ነገር ነው። በማቴ. 16፡17 ጴጥሮስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ከተናገረ በኋላ ኢየሱስ “ለጴጥሮስ ሲናገር «ይህን የገለጠልህ በሰማያት ያለው አባቴ ነው» አለው። ጴጥሮስ ራእይ አላየም ወይም ድምፅ አልሰማም። ይልቁኑ በቅጽበት አእምሮአዊ መረዳቱ ተቀይሮ ኢየሱስ ማን መሆኑን በክፊልም ቢሆን እንኳ ተረዳ። በከፊል ልንል የተገደድንበት ምክንያት ጴጥሮስ ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሔድ ለመከላክል በሞከረ ጊዜ ኢየሱስ ይህንን ከሰይጣን ከራሱ የመጣ ፈተና ነው በማለቱ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ትንሣኤ በፊት ኢየሱስ ማን መሆኑንና በመሢሕነቱ የነበረውን ሚና አልተረዱም ነበር። 

2. ኢየሱስ መሆኑን ተረድቶ በእርሱ የሚያምን ሰው ይህን የሚያደርገው እግዚአብሔር እውነትን ስለሚገልጥለት ነው። ኢየሱስ ሰው በእርሱ የሚያምነው አብ ወልድን ብቻ ሊገልጥለት እንደሆነ መናገሩ ተጠቅሷል (ማቴ. 11፡27)። እምነት እውን ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበቡን ለሰው መግላጥ አለበት (1ኛ ቆሮ. 2፡10)። 

3. በመንፈሳዊ መረዳት የማደግ ችሎታ እውን የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ እውነትን ስለሚገልጥ ብቻ ነው (ኤፌ. 1፡17)። 

4 እግዚአብሔር ፈቃዱን በተፈጥሮአዊ ነገሮች ይገልጻል። ለምሳሌ የምትጠልቅ ፀሐይን በሚመለከትበት ጊዜ እግዚአብሔር ኃያልነቱንና ብርታቱን ለሰው ሊጎልጽ ይችላል። 

5. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እራሱን ፈጽሞ በተለየ ልዕለ-ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ይገልጣል። ራእዮችን፥ ድምፁን፥ ወዘተ… በመጠቀም በቀጥታ ለአንድ ሰው ሊናገርና ፈቃዱን ሊገልጽ ይችላል። ጳውሎስ ከቲቶ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ የተናገረው እግዚአብሔር በሰጠው ልዩ መገለጥ ምክንያት ነበር (ገላ. 2፡1-2)። 

ጳውሎስ ትንቢት በመገለጥ ይመጣል ሲል ልዩ የሆኑ ሕልሞች፤ የሚሰሙ ድምፆች ወይም ልዩ ድንቀኛ መልእክት ለቤተ ክርስቲያን የግድ ይሰጥ ማለቱ እንዳልነበረ እነዚህ ምሳሌዎች ያሳዩናል። ጸጥ ባለ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ የክርስትና ሕይወትን ጥልቅ ነገርና ይኸው ጉዳይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ሰው እንዲረዳው ማድረጉን ጳውሎስ ማካተት ይችል ነበር። እንደዚህ ዓይነት መገለጦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል አልነበሩም። ምክንያቱም መገለጡን የሚቀበሉት ሰዎች በትክክል ላይረዱት ስለሚችሉ ነበር። የአንድ ሰው ትንቢት መመዘንና አስፈላጊ ከሆነም መታረም የነበረበት ለዚህ ነው። የቤርያ ሰዎች የጳውሎስን መልእክት እንኳ በጊዜው በእጃቸው ከነበሩት ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ለማወዳደር አመዛዝነውታል (የሐዋ. 17፡1)። 

ስለዚህ በአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ ምን ነበር? ትንቢት አንድ ሰው በማንኛውም ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አማካይነት የሚያመጣው የእግዚአብሔርን ሕዝቦች የሚያንጽና የሚያበረታታ መልእክት ነበር። ብዙ ጊዜ እነዚህ መልእክቶች በድንገት ወደ አንድ ሰው የሚመጡና መልእክቶቹን የተቀበለው ሰው ለሌሎች የሚያካፍላቸው ነበሩ።

የብሉይ ኪዳን ትንቢትና የአዲስ ኪዳን ትንቢት የሚለያዩት እንዴት ነው? 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ትንቢቶች ማለትም ኤር. 44፡1፤ 29፤ 48፡1፤ ከሐዋ. 11፡28፤ 21፡4 ና 21፡10-14 ጋር አወዳድር። ሀ) እነዚህ ትንቢቶች ተመሳሳይ የሆኑት በምን መንገድ ነው? ለ) የሚለያዩትስ በምን መንገድ ነው? 

በብሉይ ኪዳን ሁለት ዓይነት ነቢያት ነበሩ። የመጀመሪያዎቹ የሚጽፉ ነቢያት ናቸው። እነዚህ እግዚአብሔር መገለጡን የሰጣቸው ብቻ ሳይሆን በኋላ ትንቢታቸውን በሚጽፉበት ጊዜ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዲወጣው እግዚአብሔር የተቆጣጠራቸው ናቸው። መልእክታቸውን በጽሑፍ ያልተው ወይም የማይጽፉ ነቢያትም ነበሩ። ኤልሳዕ፥ ኤልያስ፥ ናታንና ሌሎች በስም ያልተጠቀሱ የነቢያት ልጆች (2ኛ ነገ 2፡3) የእንደዚህ ዓይነት ነቢያት ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ የሁላተኛዎቹ ዓይነት ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚናገሩ የታወቀ ቢሆንም ትንቢታቸው ስላልተጻፈ በጽሑፍ መልእክታቸውን የተው ነቢያትን ያህል ለመላእክታቸው ዘላቂነት ያለው ዋጋ አልተሰጠም። 

በአዲስ ኪዳንም እዚህ ሁለት ዓይነት ነቢያት ይታያሉ። የመጀመሪያዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያውቁና የተረዱትን ፈቃዱን በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ እግዚአብሔር ያደረጋቸው ሲሆን ጽሑፋቸውም አዲስ ኪዳን ሆኗል። ይህ ተግባር በተቀዳሚነት የተከናወነው ከሐዋርያት በአንዳንዶቹ (ጴጥሮስና ዮሐንስ) እና በተመረጡ ሌሎች ጥቂት ደቀ መዛሙርት (ይሁዳ፣ ማርቆስ) ነው። ሐዋርያት የጻፉት በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ሥልጣን ያለው አልነበረም። ብዙ ሊቃውንት እንደሚያምኑት ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሌላ መልእክት የጻፈ ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ቃል ተጠብቆ ይቆይ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አላደረገም (2ኛ ቆሮ.2፡1-10)። በሁለተኛ ደረጃ፥ የትንቢት ስጦታ ያላቸውና መገለጥን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሉ ነገር ግን በጽሑፍ ያላስቀሩ ነቢያት አሉ። እነዚህኞቹ የተናገሩትን ቃል እግዚአብሔር እንደ ጸሐፊ ነቢያት መልእክቶች አልጠበቀውም። 

አንዳንድ ሊቃውንት የአዲስ ኪዳን ነቢያት ሚናና የብሉይ ኪዳን ነቢያት ሚና የተለያየ እንደሆነ ያምናሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያለአንዳች ስሕተት ያወጁት የብሉይ ኪዳን ነቢያት አገልግሎት በሐዋርያትም እንደተከናወነ ያምናሉ። የአዲስ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር መገለጥን የተቀበሉበት መንገድ (ራእይና ውስጣዊ ድምፅ) ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ጋር ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ለነበሩ ነቢያት እንደተደረገው ቃል በቃል የእግዚአብሔር ቃል አይደለም። መጻሕፍቱን የጻፉት ሰዎች በራሳቸው ቃል በመጠቀም እግዚአብሔር በልባቸው ያደረገውን መልእክት በራሳቸው አሳብ ተናገሩት። ስለዚህ የአዲስ ኪዳን ነቢያት ቃል የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ያህል ሥልጣን የለውም። 

ወደ አዲስ ኪዳን ስንመለከትና ትንቢቶች እንዴት እንደተሰጡ ስናስብ ከብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በርካታ ልዩነቶች እንዳሉአቸው እናያለን። 

በመጀመሪያ፥ ትንቢተቹ በብሉይ ኪዳን የተሰጡበትን ሁኔታ በአዲስ ኪዳን ከተሰጡበት ጋር ስናወዳድር አንዳንድ ልዩነቶች እናያለን። በዘዲ 18፡18-22 ነቢዩ በጌታ ስም እንደተናገረ እናነባለን። ይህን ዓይነቱን ልምምድ በትንቢት መጻሕፍቶች በግልጽ እንመለከታለን። እያንዳንዱ ነቢይ «የእግዚአብሔር ቃል መጣልኝ» ብሎ ለመናገር እጅግ ይጠነቀቅ ነበር። ከዚያም ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ ነቢዩ ራሱ መናገሩን ያቆምና እግዚአብሔር እራሱ እንደሚናገር የሚያመለክተውን እኔ የሚለው ተውላጠ ስም ሊጠቀም እግዚአብሔር መናገሩን ይጀምራል። ነቢዩ እግዚአብሔር መልእክቱን የሚያስተላልፍበት መሣሪያ ብቻ ይሆናል። እግዚአብሔር የነቢዩን ድምፅ ብቻ በመጠቀም ለሕዝቡ የመናገሩ ያህል ነው። በአዲስ ኪዳን ነቢያት «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» የሚል የአነጋገር ዘይቤ ሲጠቀሙ ፈጽሞ እንመለከትም። ይህን ሲያደርጉ ኖሮ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር በነበራቸው ዓይነት ሥልጣን እንደተናገሩ ራሳቸውን መቁጠራቸውን የሚያመላክት ይሆን ነበር። ይልቁኑ ትንቢተቻቸው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሆነ ግላትም ትክክለኛነቱ በጣም ዝቅተኛ እሳብ ነው። ስለሆነም ሰማይጽፉ ወይም መልእክታቸውን በጽሑፍ በማያልቀሩ ነቢያት መልእክታቸውን በሚያስተላልፉበት ወቅት እግዚአብሔር እንደሚናገር «እኔ» የሚለውን ተውላጠ ስም የተጠቀሙበት ጊዜ የለም። በብሉይ ኪዳን ነቢያትና የትንቢት ስጦታዎች ባላቸው ሰዎች መካከል የብቃት ልዩነት ስላለ በዚህ ዘመን ያሉ ነቢያት «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወይም እግዚአብሔርን ወክላው «እኔ ፡ ወይም «ሕዝቤ ሆይ» እያሉ የብሉይ ኪዳን ቀመርን ተጠቅሞ መናገር ለሕተት ነው። እነዚህን አባባሎች መጠቀም ቃሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ትክክል ናቸው ማለት ሊሆን ይህ ደግሞ እጅግ አደገኛ አዝማሚያ ነው። 

በሁለተኛ ደረጃ፥ አንዳንድ የአዲስ ኪዳን ነቢያት ሌሎች ሊተላላፉአቸው የሚችሉ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። ለምሳሌ በሐዋ. 21 ላይ አጋቦስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም እስር እንደሚጠብቀው ከተናገረ በኋላ ሌሎች ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ሊከላከሉት ሞክረዋል። ጳውሎስ በአጋቦስ በኩል የመጣለትን ትንቢት እንዳይታዘዝ በነፃነት እንደ ማበረታታት ያህል ነበር ድርጊታቸው። ጳውሎስ እንዳይሄድ የሚከላከል ትንቢትን (የሐዋ. 2፡4) ካቀረቡለት ውትወታ ይልቅ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ መንፈስ እየነገረው እንደሆነ የተሰማው ግንዛቤ አመዘነበት። ከዚህ በተቃራኒ በብሉይ ኪዳን ቀን ሕዝቡ አንድ ሰው የእግዚአብሔር ነቢይ መሆኑን አምነው አንዴ ከተቀበሉት እርሱን አለመታዘዝ እግዚአብሔርን እንዳለመታዘዝ ስለሆነ የመታዘዝ ሥነ ምግባራዊ ግዴታ ነበረባቸው። 

(ማስታወሻ፡- ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም በሚወለድበት ጊዜ ድርጊቱ የተፈጸመበት ሁኔታ ትንቢቱ ከተነገረበት ሁኔታ የተላያ ነበር። በሐዋ. 21፡11 ላይ የተሰጠው ትንቢት አይሁድ ጳውሎስን እንደሚያስሩት የሚናገር ነበር። ነገር ግን በአይሁድ ቅስቀሳም ቢሆን ጳውሎስን ወደ እስር የወሰዱት ሮማውያን ነበሩ። ደግሞ አይሁድ የፈለጉት እንዲገደል እንጂ እንዲታሰር አልነበረም። ይህ ትንቢት በብሉይ ኪዳን ከተነገሩ ትንቢቶች ጋር ሲወዳደር መዛነፎች ይታዩበታል።) 

ሦስተኛ፥ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ በተደጋጋሚ ትንቢት አለን የሚሉትን እንድንፈትንና እንድንመዝን ተነግሮናል። ይህ የሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰው የሚናገረውን መልእክት ከእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ማሰብ እንደሌለባት ነው። ይልቁኑ ሁልጊዜም ቢሆን ምን ያህሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነና እንዳልሆነ የተነገረውን መልእክት መመርመርና መመዘን ያስፈልጋል። «መመዘን» የሚለው ቃል (1ኛ ቆሮ. 14፡29) መልካም የሆነ (የእግዚአብሔር) ወይም ክፉ የሆነ (ከሰይጣን) ማላት ብቻ አይደለም። የተነገረው መልእክት ከጥራት አንጻር የተደባለቀ ስለሆነ እውነትን ለማውጣት ማብጠርጠር እንደሚያስፈልግ የሚያመለክት ነው። 

ከተነገረው መልእክት ውስጥ የተወሰነው መልካም ሊሆንና የቀረው ደግሞ ክፉ ሊሆን ይችላል። መልእክቱ የተደባለቀ ሆኖ ለመቅረብ የመቻሉ ነገር የሚጠበቅና የተለመደ ይመስላል። በብሉይ ኪዳን ትንቢቶች የተደበላለቀ ጥራት ሊኖራቸው እንደሚችል የሚያመለክት ነገር የለም ከእግዚአብሔር የመጣ መልእክት ከሆነ ሙሉ በሙሉ ትክክል ይሆናል ከእግዚአብሔር ካልሆነ ግን ሰውዬው ሐሰተኛ ነቢይ ነው። 

አራተኛ፥ በብሉይ ኪዳን ነቢይ ነኝ ብሉ እግዚአብሔርን ወክሎ የሚናገር ሰው መልእክቱ እውነት ባይሆንና የተናገረው ትንቢት ባይፈጸም ሐሰተኛ ነቢይ ተብሎ ይገደል ነበር። በአዲስ ኪዳን ግን እንደዚህ ዓይነት ሥጋት አንመለከትም። መልእክታቸው ሙሉ በሙሉ ትክክል ያልሆኑ ሰዎች ቢገኙ ምን መደረግ እንዳለባቸው የሚያመለክት አንዳችም ነገር የለም። 

አምስተኛ፥ ጳውሎስ ነቢያት ነን የሚሉ ሰዎች ሥልጣን ከእርሱ የሐዋርያነት ሥልጣን ሥር መሆኑን አመልክቷል (1ኛ ቆሮ. 14፡32-38)። ሐዋርያ የሆነን ሰው አለመታዘዝ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ነቢይ ካላመታዘዝ እኩል ይታይ ነበር (1ኛ ቆሮ. 4፡21፤ 2ኛ ቆሮ. 10፡1 13፡1 10)። የአዲስ ኪዳን ነቢይን ስላላመታዘዝ የተሰጠ እንደዚህ ዓይነት ማስጠንቀቂያ ቀን የለም። 

ስድስተኛ፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የእውነትን ምንነት የሚገልጹና እውነትን የሚጠብቁ ሐዋርያት በነበሩበት ጊዜ፥ ነቢያት እነርሱን እንደሚተኩአቸው የተባለ ምንጭ ነገር የለም። በጊዜው ተነሥተው ከነበሩት የሐሰት ትምህርቶች ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቁ እነርሱ እንደሆኑ የተናገሩበት ጊዜ አልነበረም። የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሊጠቃለል በቀረበበትና ሐዋርያት እየሞቱ በነበረበት ወቅት የተጻፉ መጻሕፍት ትኩረት አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ከመቀበል ይልቅ «እምነትን በመጠበቅ ወይም በመከላከል› ላይ ነበር (2ኛ ጢሞ. 1፡14፥ ይሁዳ 3)። 

ሰባተኛ፥ በአዲስ ኪዳን ነቢያት በቤተ ክርስቲያን የተለየ ታላቅ ክብር ተሰጥቷቸው አያውቅም። 1ኛ ቆሮ. 12፡14 ባለው ትምህርታችን የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በልሳናት መናገርን ሲያማርጡ ጳውሎስ ግን ትንቢት ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት እንደሞከረ ተመልክተናል። የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ነቢያትን እንዳይንቁ ተነግሮአቸዋል (1ኛ ተሰ 5፡20)። 

እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱን ነቢያት በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበራቸውን ዓይነት ሚና መጫወት ሐዋርያት በሞቱ ጊዜ እንዳበቃ ወይም የአዲስ ኪዳን ነቢያት ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ጋር በእኩልነት የታዩበት ወቅት ፈጽሞ እንዳልነበረ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) በአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ሥልጣን የሌለው ከሆነ ዛሬም ቢሆን ከእግዚአብሔር የሆነ መልእክት እንዳላቸው የሚናገሩትን እንዴት እንደምንመለከት ይህ ምን ያሳየናል? ለ) ሰዎች ከእግዚአብሔር የሆነ መልእክትን የሚያመጡባቸውን ሁኔታዎች ግላጽ። መልእክታቸው ተቀባይነት ያገኘው እንዴት ነበር? ሐ) በዚህ መንገድ የሚመጡ መልእክቶችን ሰዎች ያዩአቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል እኩይ ክብደትና ዋጋ ሰጥተው ነበር? ሐ) ትንቢቶች መመዘን ካለባቸው አንድ ሰማር ከእግዚአብሔር የሆነ መልእክት አለኝ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ሲል የአን ቤተ ክርስቲያን መሪ ሚና ምን መሆን አለበት? 

አንዳንድ ሊቃውንት ከላይ ለጠቀስነው አባባል ምላሽ የሚሰጡት በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሁለት ዓይነት ናቸው በማለት ነው። መልእክቶቻቸውን በጽሑፍ የሚያስቀሩ ነቢያት በጽሑፍ ከማያልቀሩት የተላዩ ነበሩ። መልእክታቸውን በጽሑፍ ላስቀሩ ነቢያት አንዳችም ስሕተት እንዳይሠሩ እግዚአብሔር ጠብቆአቸዋል። አዲስ ኪዳን ተጽፎ እንዳለ እንደዚህ ዓይነት የነቢያት መልእክቶች ከስሕተት መጠበቃቸውና የነበራቸው ሥልጣን ተፈጸመ። በጽሑፍ የሚያስቀሩ ነቢያት ግን በዚህ መልክ ፈጽ መልእክት ያያዙ አልነበሩም። ከእግዚአብሔር የተቀበሉት መገለጥ ትክክል ቢሆንም እንኳ የሚያመጡት መልእክት አግባብ ላለሆነ አተረጓጐምና, ለተሳሳተ አጠቃቀም የተመቻቸ ነበር። ዛሬ የትንቢት መልእክቶችን ማየት ; ያለብን በዚህ መንገድ ነው ይላሉ። ከእግዚአብሔር የሚሰጥ መገላጥ ሁልጊዜ ትክክል ቢሆንም መልእክቱን የተቀበለው ነቢይ የሚተረጉምበትና በተግባር ላይ የሚያውልበት መንገድ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልን በተሳሳተ መንገድ የምንተረጉመውን ያህል ስሕተት ሊሆን ይችላል።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: