የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ብዙ ጊዜ ስለ ነቢይ በምናስብበት ጊዜ ለለ ወደፊቱ ጉዳይ ለመናገር የሚችል እንደሆነ እናስባለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት እግዚአብሔር የወደፊቱን ነገር ለመናገር የተጠቀመባቸው ቢሆኑም ይህ የአገልግሎታቸው አነስተኛው አካል ብቻ ነበር። ትንቢት ሰው ከእግዚአብሔር የሚቀበለው መልእክት ነበር። እግዚአብሔር ፈቃዱን በተለያዩ መንገዶች የሚገልጥበት ነበር። (ይህም በሕልም፥ በራእይ፥ በድምፅ፥ ሊሆን ይችላል።) የተገለጠውንም መልእክት ለሌሎች እንዲያካፍል ለሰው በእግዚአብሔር የሚነገር ነበር። ትንቢተች ወይም መገለጦች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የሚመጡ አይደሉም። ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ መልእክቱን ለሚቀበለው ሰው በቀጥታ የሚመጡ ናቸው። በአዲስ ኪዳን እያንዳንዱ ክርስቲያን የትንቢት ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ የመቀበል መብትና ችሎታ ያለው ይመስላል (የሐዋ. 2፡16-18)። ይህ ክርስቲያኖች ሁሉ ወንጌልን በመስበክና በማስተማር ሥራ መሳተፍ አለባቸው ከሚለው እውነት ጋር ተመሳሳይ ነው። ሆኖም ቀን ክርስቲያኖች ሁሉ ነቢያት አይሆኑም። የእግዚአብሔርን እውነት ያለማቋረጥ በቤተ ክርስቲያን ለማስተላለፍ ስጦታና ችሎታ ላላቸው ሰዎች የተሰጠ ነው።
ነቢይ ከእግዚአብሔር ቃልን በቀጥታ ተቀብሎ ብዙ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰዎች የሚናገር ነው። ይህ መገለጥ ላለ ወደፊቱ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ስለሌላ ሰው ምስጢር የሆነ መልእክት ወይም እግዚአብሔር ሕዝቡ በተቀጻሚ እንዲያደረገው የሚፈልገውን ነገር መግለጥ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ነቢዩ የአንድ ጊዜ መገለጥን የሚያመጣ ሳይሆን እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሆነውን መልእክት ያላማቋረጥ የሚሰጠውና ለሌሎች የሚያስተላለፍ ሰው ነው። ብዙ ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዳንድ መልእክቶች የሚቀበሉ ቢሆኑም ነቢይ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያላማቋረጥ የመግለጥ አገልግሎት አለው።
ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሆነ ስለ ትንቢት ወይም መገለጥ ስናስብ ለለ ሁላት ዋና ዓይነት ትንቢቶች ለይተን መናገር አለብን። አንደኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ሕዝቡ በነቢይ አማካይነት የሚመጡ አንዳንድ ትንቢተች ነበሩ። እግዚአብሔር እነዚህን ትንቢቶች የመጽሐፍ ቅዱሳችን አካል ለመሆን በሚጻፉበት ወቅት ጥንቃቄ አድርጐባቸዋል። እነዚህ ትንቢተች ነቢዩ የእግዚአብሔርን መልእክት በተቀበለበት ግልጽነት ብቻ ሳይሆን መገለጦች በተጻፉባቸው ቃላትም ጭምር መለኮታዊነትን የተላበሱና በእግዚአብሔር ቁጥጥር የተከናወኑ ነበሩ። በሙሉ መተማመን መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት ነው የምንለው ለዚህ ነው። ቃሎቹ እንኳ በእግዚአብሔር የተጠበቁ እስከሚሆኑ ድረስ በመንፈስ ቅዱስ የተጠነቀቀለትና አንዳችም ስሕተት የሌለበት ነው (ማቴ. 5፡7-18)። እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነቱን ትንቢት መስጠት አቁሟል (ራእይ 22፡18-19)። ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት ሥልጣን ያለው መጽሐፍ ተጠናቋል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅ እንድንችል፥ እግዚአብሔር መመዘኛ እንድናደርገው የሚፈልገውን እውነት በሙሉ በስድሳ ስድስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ በተጻፈው መገለጥ አማካኝነት እናገኛለን። የትኛውም የወንጌል አማኝ የሆነ . ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የተቀበላው ትንቢት የመጽሐፍ ቅዱስ ያህል ጥራትና ሥልጣን እንዳለው መናገር አይችልም። የኑፋቄ ትምህርቶች አንዱ ምልክት ሌሎች ጽሑፎችን ሥልጣን ባለው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጣመራቸው ነው። ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ናቸው የሚባሉት ሌሎች ትምህርቶች ሁሉ የሚዳኙበት ብቸኛው መንፈስ ቅዱስ ያረፈበት የእግዚአብሔር ቃል ነው።
ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለሕዝቡ የሚሰጣቸው ሌሎች መገለጦች አሉ። እነዚህ መገለጦች በተለያዩ መልኮች ሊመጡ የሚችሉ ናቸው። ሕልሞችና ራእዮች ሊኖሩ ይችላሉ። በሌላ ጊዜ ደሞ አንድን ነገር የማድረግ ወይም የመናገር ጠንካራ ውስጣዊ ስሜት ይኖራል። ወዲያውኑ ባንረዳውም እንኳ ከጊዜ በኋላ የተናገረን እግዚአብሔር እንደነበር እናውቃለን። ለአንዳንዶች እግዚአብሔር ግልጽ የሆነ ቃል በድምጽ ወይም በውስጣዊ ስሜትን ሰጥቶአቸዋል። ለምሳሌ እግዚአብሔር ምስጢራዊ በሆነ መንገድ የምታገባት ሴት ይህች ናት በማለት እንደተናገራቸው ያውቃሉ። ሌሎችን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል ወደተዘጋጀ ሰው «ሂድና ላዚያ ሰው ስለ እኔ ተናገር» ብሎ እግዚአብሔር ወርቶአቸዋል። እነዚህ መገለጦች በሙሉ ከእግዚአብሔር ናቸው። እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ በትክክል የሚናገሩ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ መገለጦች እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ከሰጣቸው መገለጦች የተለዩ ናቸው። የሚለዩት በሁለት መንገዶች ነው።
1. በእንደዚህ ዓይነት መገለጦችና በመጽሐፍ ቅዱስ መገለጥ መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት በብሉይና በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እግዚአብሔር መልእክቱን መስጠቱ ብቻ ሳይሆን መልእክቱ ወደ ሰዎች የሚደርስበትን ሁኔታ እንኳ በመጠበቅ አንዳች ስሕተት እንዳይኖር እደረገ። ዛሬ እግዚአብሔር የትንቢት ቃሎችን ወይም መገለጦችን ሊሰጥ የሚነገረውን ቃል እይጠብቅም። በሌላ አባባል የመጨረሻው ውጤት ወይም የሚሰጠው መልእክት የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል መላኮታዊነትን የተላበሰ አይደለም።
2. በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጡ መገለጦች ለዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን የተሰጡ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፈው ያሉ በሙሉ በየትኛውም ዘመን በየትኛውም አገር ለሚኖሩ ለየትኛውም የብሔር አባላት የተሰጡ ናቸው። ዛሬ በዚህ ዘመን ላለ አንድ ቀለሰብ ወይም ለአንድ የአማኞች ኅብረት ብቻ የተወሰኑ አይደለም።
ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡
1.ስለ ትንቢት ፣ ነብይነት፣ ራዕይ እና ሕልም ልዩነት አልተረዳሁም
2. በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አካላት ነብይ የለም ከአዲስ ኪዳን በኃላ አያሉ ነዉ :: እውነት ነው ወይ
የተወደድክ ወንድሜ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰላም እልሃለሁ።
እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ለህዝቡ በተለያዩ መንገዶች ይናገራል (ዕብ 1:1-2)። በነብይነት (ትንቢት)፣ በራዕይ እና በሕልም መካከል ያለውን ልዩነት በእግዚአብሔር ቃል መሰረት እንደሚከተለው እንመለከታለን።
1. ነብይነት (ትንቢት)
ነብይነት ወይም ትንቢት መናገር ማለት የእግዚአብሔርን ሃሳብ፣ ፈቃድ እና ቃል በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ለሰዎች ማስተላለፍ ነው። ይህ ስጦታ በዋነኝነት የሚሰራው በንግግር ወይም በቃል በማወጅ ነው። የትንቢት ዋና አላማ ቤተክርስቲያንን ማነጽ፣ ሰዎችን መምከር እና ማጽናናት ነው (1ኛ ቆሮ 14:3)። ትንቢት ከሰው ፈቃድ የመጣ ሳይሆን ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩት ነው (2ኛ ጴጥ 1:21)። ትንቢት ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚነገር ሊሆን ቢችልም፣ በዋናነት ግን የእግዚአብሔርን ልብ፣ ተግሳጽ እና የወቅቱን መልእክት ለህዝቡ ማድረስ ነው።
2. ራዕይ
ራዕይ ማለት አንድ ሰው ነቅቶ እያለ ወይም በመንፈስ ተመስጦ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ዓይኖቹን ከፍቶ የሚያሳየው መለኮታዊ እይታ ወይም ምስል ነው። ራዕይ ብዙውን ጊዜ የሚመጣው ሰውየው በጸሎት ወይም በእግዚአብሔር ህልውና ውስጥ ባለበት ጊዜ ነው። እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር በራእይ እገለጥለታለሁ ብሎ ተናግሯል (ዘኁ 12:6)። ለምሳሌ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በጣሪያ ላይ ሲጸልይ ተርቦ ሳለ ተመስጦ መጣበት እና ሰማይ ተከፍቶ ራዕይን አየ (የሐዋ 10:9-16)። ራዕይ ከትንቢት የሚለየው፣ ትንቢት በዋናነት የሚሰማ እና የሚነገር ቃል ሲሆን፣ ራዕይ ግን የሚታይ መለኮታዊ ትእይንት መሆኑ ነው።
3. ሕልም
ሕልም እግዚአብሔር የሰውን አእምሮ በእንቅልፍ ጊዜ ተጠቅሞ መልእክቱን የሚያስተላልፍበት መንገድ ነው። ሰው ሲተኛ እና ወደ እረፍት ሲገባ፣ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ይናገረዋል። በኋለኛው ዘመን መንፈሴን በስጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፣ ወጣቶቻችሁ ራእይ ያያሉ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ ተብሎ ተጽፏል (ኢዩ 2:28)። እንዲሁም የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶት ማርያምን ለመውሰድ እንዳይፈራ እንደነገረው እናያለን (ማቴ 1:20)። ሕልም ከራዕይ የሚለየው ሰውየው ሙሉ በሙሉ በእንቅልፍ ላይ ሆኖ የሚቀበለው መሆኑ ነው።
ማጠቃለያ እና የጥንቃቄ ቃል
መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በትንቢት፣ በራዕይ እና በሕልም እንደሚናገር እናምናለን። እነዚህ የጸጋ ስጦታዎች ቤተክርስቲያንን ለማነጽ የተሰጡ ናቸው። ነገር ግን፣ ማንኛውም ትንቢት፣ ራዕይም ሆነ ሕልም ከእግዚአብሔር ቃል (ከመጽሐፍ ቅዱስ) ጋር መመዘን አለበት። ትንቢትን አትናቁ ነገር ግን ሁሉን ፈትኑ መልካም የሆነውንም ያዙ ተብሎ ታዟል (1ኛ ተሰ 5:20-21)። የእግዚአብሔር ቃል የመጨረሻው እና ፍጹሙ ሚዛናችን ነው።
ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ!
በአዲስ ኪዳንም ሆነ በዛሬዋ ቤተክርስቲያን የነቢይነት ጸጋም ሆነ የነቢይነት አገልግሎት (ነቢያት) በእርግጠኝነት አሉ።
ይህንንም ከእግዚአብሔር ቃል በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡-
1. የነቢይነት (ትንቢት የመናገር) ጸጋ በአዲስ ኪዳን
በአዲስ ኪዳን ትንቢት የመናገር ጸጋ ለመላው አማኞች የተሰጠ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። ይህ ጸጋ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በተለይም ትንቢት መናገርን አጥብቀን እንድንፈልግ ይመክረናል (1ኛ ቆሮ 14:1)። የዚህ ጸጋ ዋና አላማ ሰዎችን መገሰጽ ወይም መኮነን ሳይሆን፣ ትንቢት የሚናገር ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰዎች ይናገራል (1ኛ ቆሮ 14:3)። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለወደደው በሚያካፍለው መጠን ማንም አማኝ በዚህ ጸጋ ሊያገለግል ይችላል።
2. የነቢይነት አገልግሎት (ነቢያት) በአዲስ ኪዳን
ከጸጋ ስጦታው ባለፈ፣ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን እንዲያንጹ እና ቅዱሳንን ለአገልግሎት ስራ እንዲያዘጋጁ በአዲስ ኪዳን “ነቢያት” ብሎ የጠራቸው እና የሾማቸው አገልጋዮች አሉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጥቷል (ኤፌ 4:11)።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ስናጠና በግልጽ ነቢያት ተብለው የተጠሩ ሰዎችን እናገኛለን፡-
በዚያን ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ እንደወረዱ እና ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንዱ ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ እንዳመለከተ እናነባለን (የሐዋ 11:27-28)።
እንዲሁም ይሁዳና ሲላስ ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው እንዳጸኑአቸው የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል (የሐዋ 15:32)።
በሌላ ስፍራም ለወንጌላዊው ፊልጶስ ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ልጆች እንደነበሩት ተጽፏል (የሐዋ 21:9)።
የብሉይ ኪዳን እና የአዲስ ኪዳን ነቢያት ልዩነት
በአዲስ ኪዳን ነቢያት ቢኖሩም አሰራራቸው ግን ከብሉይ ኪዳን ነቢያት የተለየ መሆኑን በሚገባ መረዳት አለብን። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ቃል (መጽሐፍ ቅዱስ) ገና አልተጻፈም ነበር፤ ስለዚህ ነቢያቱ የእግዚአብሔር ብቸኛ ድምጽ በመሆን መጽሐፍ ቅዱስን ጻፉ። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ተጽፎ አልቋል። ስለዚህ የአዲስ ኪዳን ነቢያት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አዲስ ቃል አይጨምሩም፤ እንዲሁም ከቃሉ ጋር የሚቃረን ትምህርት አያመጡም።
የአዲስ ኪዳን ነቢያት መልእክት ሁልጊዜ ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚስማማ እና በቤተክርስቲያን የሚመዘን መሆን አለበት። ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ፣ ሌሎቹም ይለዩ ብሎ የሚያዘን (1ኛ ቆሮ 14:29)።
ለማጠቃለል፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የነቢይነት ጸጋም ሆነ ነቢያት በቤተክርስቲያን ውስጥ አሉ። አማኞች ይህንን ጸጋ ልንጠማ፣ ልንጸልይበት እና ሁልጊዜም በእግዚአብሔር ቃል ሚዛን እውነተኛነቱን እየመረመርን ልንጠቀምበት ይገባል።
የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ጥልቅ ህብረት ከአንተ ጋር ይሁን!