በቀላል አነጋገር፥ «አስተምህሮ» የሚለው ቃል «ማስተማር» ማለት ነው። ክርስቲያኖችም ብዙ ጊዜ ስለ አስተምህሮ በሚናገሩበት ወቅት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝ በአንድ በተወሰነ ርእሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት ስለሚሰጥ ትምህርት መናገራቸው ነው። በዚህ በትምህርተ መለኮት ማስፋፋት ጥናት መርሐ ግብር ውስጥ የሚጠቀሱ መጻሕፍት አብዛኛዎቹ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያስነብቡ ናቸው። በዚህ አኳኋን መጽሐፍ ቅዱስን መጽሐፍ በመጽሐፍ ማጥናት የመጀመሪያውና በጣም ጠቃሚው መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠናበት መንገድ ነው። የእያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መልእክት አስቀድመን ሳንገነዘብ፥ መላውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፈጽሞ ልንረዳ እንችልም። ሆኖም ግን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ልናጠና የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ መሪ አሳቦችን በመለየትና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ርእሰ ጉዳዮቹ ከሚሰጠው ትምህርት ጋር በማስተያየት ልናጠና እንችላለን። በዚህ አኳኋን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እጅግ በጣም ጠቃሚ መሪ አሳቦችን በምናጠናበት ጊዜ፥ እነዚህን መሪ አሳቦች ከምንኖርበት ዓለም ሁኔታ ጋር አገናዝበን እንዴት እንደምንገልጻቸውና በተግባርም ላይ እንዴት እንደምናውላቸው ለማሰብ ምቹ ሁኔታ እናገኛለን። ይህ የአስተምህሮ (ዶክትሪን) ጥናት ይባላል። አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ርእሰ ጉዳዮችን ጠቅለል አድርጎ ማስተማርና የርእሰ ጉዳዮቹን መልእክቶች ከዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚገናዘብ መልኩ መግለጽ ማለት ነው።