የሕይወት እንጀራ

ትንቢተ ሆሴዕ

እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለው ፍቅር (ሆሴዕ 11-14)

የትንቢት መጻሕፍት መልእክቶቻችን እንዴት ሚዛናዊ መሆን እንዳለባቸው የሚያሳዩ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። የትንቢት መጻሕፍት የፍርድና የኃጢአት ብቻ ሳይሆን፥ የተስፋን መልእክት አጣምረው የያዙ ናቸው። ይህ ሚዛናዊ ሁኔታ በትንቢተ ሆሴዕ ውስጥ ይታያል። እግዚአብሔር እስራኤልን እንደሚቀጣ ሲናገር፥ ወደፊት በረከቱን እንደሚመልስላቸውም ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖችን የሚያበረታቱ መልእክቶችን ከመስበክ ይልቅ የሚኮንን መልእክት መስበክ የሚቀልለው ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ለማበረታታት መልእክት ልታቀርብባቸው የምትችል የአሥር ርእሶች ዝርዝርን አዘጋጅ።  የውይይት ጥያቄ፥ ሆሴዕ 11-14 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው ተስፋዎች ምንድን ናቸው? ሆሴዕ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል ያለውን ኅብረት ለመግለጽ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚያነጻጽር ምሳሌ እንዴት እንደተጠቀመ ቀደም ሲል ተመልክተናል። ሆሴዕ ይህንን ፍቅር ለመግለጽ አሁን ሌላ ምሳሌ ይጠቀማል። ይህም አባት (እግዚአብሔር) ለልጁ (ለእስራኤል) ያለው ፍቅር ነው። አዲስ ኪዳንም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለመግለጥ እነዚህን ሁለት ተመሳሳይ ማነጻጸሪያዎች እንደተጠቀመ ስንመለከት እንደነቃለን፤ ለምሳሌ (ዮሐንስ 1፡12)። እግዚአብሔር ልጁን እስራኤልን ስለወደደው አሳደገው። እስራኤል ግን በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀ። እግዚአብሔር ከእርሱ ርቆ ያለውን ልጅ ቢቀጣም፥ ለእስራኤል ያለው ፍቅር ግን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፋው የሚያስችለው አልነበረም። ይልቁንም አንድ ቀን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ ይሰበስባቸዋል። እስራኤላውያን የኃጢአታቸውን ቅጣት ቢሸከሙና በሰይፍ ቢጠፋም እንኳ አንድ ቀን እግዚአብሔር ይህንን ሕዝብ ከሞት ይቤዣል። ካለባቸው በኃጢአት የመንከራተት ዝንባሌ በሽታ እስራኤላውያንን ይፈውሳቸዋል። በአኃጢአታቸው ንስሐ ይገባሉ። እግዚአብሔርም በረከቱን ለእስራኤል ሕዝብ ይመልሳል።  እነዚህ የተስፋ ቃሎች ለእስራኤል ሕዝብ ገና አልተፈጸሙም። ከይሁዳ ሕዝብ የሚለዩበት ነገር ቢኖር ወደ እስራኤል ምድር አለመመለሳቸው ነው። ስለዚህ እነዚህ የተስፋ ቃላት ወደ ፊት ይፈጸማሉ። በዘመናት መጨረሻ ክርስቶስ በምድር ላይ በሚነግሥስበት ጊዜ አይሁድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚመለሱ፥ ከዚያ በኋላ በእግዚአብሔር ላይ በጭራሽ ኃጢአት እንደማያደርጉና እርሱም እንደገና እንደሚባርካቸው የሚመስላቸው ምሁራን በርካታ ናቸው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል ኪዳን ይፈጸማል።  የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በዚህ የመጨረሻ ክፍል የሚገኙና ለአንተ በረከት የሆኑ አንዳንድ መንፈሳዊ እውነቶች ምንድን ናቸው። ለ) እነዚህ ተመሳሳይ እውነቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች በረከት የሚሆኑት እንዴት ነው? ሐ) በቤተ ክርስቲያህ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ትንቢተ ሆሴዕን ለማስተማር ዕቅድ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለው ፍቅር (ሆሴዕ 11-14) Read More »

ሆሴዕ 4-10

ኃጢአት እንደ ተስቦ ነው። የእግዚአብሔርን ሕዝብ በሙሉ እስኪያዳርስ ድረስ በፍጥነት ይስፋፋል። ብዙ ጊዜ ኃጢአት የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት እየቀዘቀዙ በሚሄዱና ኃጢአት ወደ ሕይወታቸው እያደባ እንዲገባ በሚፈቅዱ መሪዎች አማካይነት ሲሆን፥ እነርሱ ደግሞ ሌሉችን ወደ ኃጢአት ይመራሉ። ኃጢአት የሰዎችን የግል ሕይወት መጒዳት ብቻ ሳይሆን፥ ምስክርነታቸውን በማበላሸት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን እውነተኛ አምልኮ ያደናቅፋል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአት በአብያተ ክርስቲያናትና በመንግሥታት ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ ያሳድራል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የኃጢአት ውጤት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሲስፋፋ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የኃጢአትን አካሄድ በመጀመር ጕዞውን ባለመግታት መሪዎች ምን ድርሻ ነበራቸው።  የውይይት ጥያቄ፥ ሆሴዕ 4-10 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን የተከሰሱባቸውን የኃጢአት ዓይነቶች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ተስፋዎች ምን ነበሩ? ሐ) ከዚህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር ምን መማር እንችላለን?  1. እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ያቀረበው ክስ (ሆሴዕ 4) የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን በኃጢአት ወድቀው ነበር። በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት አጕድለው ነበር። እግዚአብሔርን አላወቁትም፥ አላከበሩትምም ነበር (ሆሴዕ 4፡1)። የእውቀት ማነስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያጠፋል (ሆሴዕ 1፡6)። የዚያ ኃጢአት ተጽዕኖ በሕዝቡ መካከል ተስፋፍቶ፥ የሕይወትን የተለያዩ ክፍሎችን ይነካል። ውሸት፥ ነፍሰ ገዳይነት፥ ስርቆትና ማመንዘር በብዙ ተራ ሰዎች ዘንድ የተለመደ ነበር። በመሪዎች፥ በካህናትና በነቢያት ዘንድ ግልጽ የሆነ ኃጢአት ነበር። ምድሪቱን በጣዖት አምልኮ ሞልተዋት ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ምድሪቱ ፍሬ እንዳትሰጥ በማድረግ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ፈረደ። ማስታወሻ፡- በትንቢተ ሆሴዕና በበርካታ ታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት ውስጥ እስራኤል፥ ኤፍሬምና ሰማርያ የሚሉ ስሞች ተፈራርቀው ይገኛሉ። ኤፍሬም የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ትልቁ ነገድ ነበር። ስለዚህ የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት አንዳንድ ጊዜ ኤፍሬም እየተባለ ይጠራ ነበር። ሰማርያ ደግሞ የሰሜኑ መንግሥት ዋና ከተማ ነበረች። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ሰማርያ የሰሜኑን የእስራኤል መንግሥት ታመለክት ነበር።  2. እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የሚያመጣው ፍርድ (ሆሴዕ 5) ከእስራኤል ንጉሥ ጀምሮ እስከ ተራው ሰው ድረስ ኃጢአት ሕዝቡን የሚያጠፋ በሽታ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር እንደሚፈርድባቸው ተናገረ። ያ ፍርድ የጀመረው እግዚአብሔር እነርሱን በተወና ቢጸልዩ እንኳ እንደማይሰማቸው በገለጸ ጊዜ ነበር (ሆሴዕ 5፡6)። ሶርያን በመውጋት እንዲረዳት እስራኤል የጠየቀችው የአሦር መንግሥት መልሶ እስራኤልን ያጠፋል። እንደ እስራኤል ሕዝብ ክፉና ኃጢአተኛ የሆነችው ይሁዳም ይፈረድባታል።  3. ከኃጢአቷ ትመለስ ዘንድ እግዚአብሔር እስራኤልን ለመናት (ሆሴዕ 6-7)  እግዚአብሔር በሆሴዕ አፍ እስራኤል እንዳትጠፋ ንስሐ እንድትገባና ወደ እርሱ እንድትመለስ ለምኗት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው በሚቀርብለት የመሥዋዕት ብዛት ሳይሆን፥ ለሕዝቡ ምሕረትን በማድረግ ነበር። ሕዝቡ በመታዘዝ ራሳቸውን እንዲሰጡትና እንዲያከብሩት ይፈልግ ነበር። እስራኤል ግን አሻፈረኝ በማለት ኃጢአትን መረጠች። እግዚአብሔርን በመጥራት ፋንታ ለእርዳታ ሌሎች አሕዛብን ፈለገች። ስለዚህ እግዚአብሔር ቀጣት።  4. እግዚአብሔር እስራኤልን ለመቅጣት የደነገገው ድንጋጌ ሆሴዕ 8-10)  እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ወይም ኅብረት ውስጥ ልዩ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ሁላችንም ነፃ ምርጫ እንዲኖረን መፍቀዱ ነው። ምንም ነገር እንድናደርግ አያስገድደንም። ልንታዘዘው ወይም ላንታዘዘው የምንችልበትን ምርጫ ይሰጠናል። ለመምረጥ ነፃ ብንሆንም፥ በምርጫችን የምናደርጋቸው ነገሮች የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች ለመወሰን ነጻ አይደለንም። ያንን የሚወስነው እግዚአብሔር ነው። ምርጫችን መታዘዝ ከሆነ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሸልመን ይወስናል። ምርጫችን አለመታዘዝ ከሆነ ደግሞ እንዴት እንደሚቀጣንና ኃጢአት እንዴት እንደሚጐዳን የሚወስን እግዚአብሔር ነው። እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር አለመታዘዝን መረጡ። ለፍተው ዘርተው ለነፋስ አስረከቡ። የምርጫቸው ውጤት በእግዚአብሔር እጅ ነበረ። ስለዚህ ዓውሎ ነፋስ ላከባቸው (ሆሴዕ 8፡7፤ 10፡12-15)። ከተሞቻቸው ተደመሰሱና ወደ አሦር በምርኮ ተወሰዱ። የአምልኮ ስፍራቸውም ተደመሰሰ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከሆሴዕ 1-10 የተማርካቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን መንፈሳዊ ትምህርቶች የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች ሊያውቋቸውና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዷቸው ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ከሆሴዕ 1-10 ልታገኛቸው የምትችል የመልእክት ርእሶችን ምረጥ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ሆሴዕ 4-10 Read More »

ሆሴዕ 1-3

የውይይት ጥያቄ፥ ሆሴዕ 1-3 አንብብ። ሀ) በሆሴዕ 1፡2 እግዚአብሔር ሆሴዕን እንዲያደርግ ያዘዘው ምን ነበር? ለ) የሆሴዕን ልጆች ስሞች ከነትርጕማቸው ግለጥ። ሐ) እግዚአብሔር እስራኤልን የሚቀጣባቸው መንገዶች ምን ነበሩ? መ) ለእስራኤል የተሰጡ የወደፊት ተስፋዎች ምን ምን ነበሩ? ሠ) እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረው ግንኙነት ሆሴዕ ከጎሜር ጋር ከነበረው ግንኙነት የተነጻጸረው እንዴት ነው? 1. የሆሴዕ ጋብቻና ልጆቹ (ሆሴዕ 1) ሆሴዕ መጽሐፉን የሚጀምረው እርሱ በነበረበት ዘመን የነገሡትን የይሁዳ ነገሥታት ስም በመዘርዘር ነው። ሆሴዕ እዚህን ነገሥታት የዘረዘረው እንደ ዓመፀኞቹ የእስራኤል ነገሥታት ሳይሆን በእስራኤል ሁሉ ላይ ሊነግሡ የሚገባቸው ሕጋውያን ነገሥታት ናቸው ብሎ ያምን ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። እግዚአብሔር ሆሴዕን «ጋለሞታ ሴት» እንዲያገባ አዘዘው። ሚስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ግልሙትና የምትወክል ነበረች። ሆሴዕ ተማርን በማግባት ከእርሷ ሦስት ልጆችን ወለደ። ሀ. ኢይዝራኤል፡- በእስራኤል ይገኙ ከነበሩ ዋና ዋና ከተሞች አንዱ ኢይዝራኤል ነበር። ይህ ስም ለእስራኤላውያን ልዩ ትርጒም ነበረው። ምክንያቱም ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የኢዮርብዓምን ሥርወ መንግሥት የመሠረተው ኢዩ ኤልዛቤልን የገደለው በኢይዝራኤል ነበር (2ኛ ነገሥት 9-10)። ይህ ስም የሚያመለክተው የኢዩ ቤት እንደ አክዓብ ቤት እንዴት እንደሚቀጣና የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ እንደሚደመሰስ ነበር። ሆሴዕ ይህን መልእክት በሚናገርበት ጊዜ የዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት በመገባደድ ላይ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ ተገደለና የኢዩ ንጉሣዊ ቤተሰብ ዘር ተደመሰሰ። የሆሴዕ ትንቢትም በዚህ ዓይነት ተፈጸመ። ለ. ሎሩሃማ፡- ሎሩሃማ ማለት ያልተወደደ ወይም ምሕረትና ርኅራኄ ያልተደረገለት ማለት ነው። ይህ ሰም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለውን ርኅራኄና ፍቅር እንደሚያቆምና (ዘጸአት 33፡19) እንደሚቀጣቸው የሚያመለክት ትንቢት ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔር እስራኤልን የሚተወው እስከ መጨረሻ አልነበረም፤ ምክንያቱም አንድ ቀን እርሱ ለእስራኤል ያለውን ፍቅር ለመመለስ ዝግጁ ነበርና (ሆሴዕ 2፡23)።  ሐ. ሉዓሚ፡- ሉዓሚ ማለት ሕዝቤ አይደላችሁምን ማለት ነው። ይህ ስም የሚያመለክተው እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረውን ግንኙነት ማቋረጡን ነበር (ዘጸአት 6፡7፤ ኤርምያስ 7፡23)። የጥበቃና የበረከት ቃል ኪዳን ፈርሶ ነበር። እስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆኗ ወይም እርሱ የእርስዋ ጠባቂ መሆኑ ቀርቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መለያየት ቋሚ አልነበረም። አንድ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን «ሕዝቤ» ብሎ የሚጠራት ቀን ይመጣል (ሆሴዕ 1፡10፤ 2፡1፥ 23)።  2. ስለ እስራኤል የተነገረ ትንቢት (ሆሴዕ 2) እግዚአብሔር ሙሽራው የሆነችውን እስራኤል ስለ ግልሙትናዋ እንደሚቀጣት ተናግሮ ነበር። በግልሙትናዋ ምክንያት እርሷና ልጆችዋ ሊቀጡ የግድ ነበር። ወዳጆችዋ አብረዋት የጋራ ስምምነት ያደረጉ አሕዛብና መሥዋዕት ያቀረበችላቸው አማልክት ነበሩ። እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የነበረውን የበረከት እጅ አነሣ የጣዖት አምልኮዋንም ደመሰሰ። ነገር ግን አንድ ቀን እስራኤል ትነጻለች። እንደ ታማኝ ሚስት ሆና ራስዋን ለእግዚአብሔር ትሰጣለች። እግዚአብሔርም ለዘላለም ይወዳታል። ተስፋ የገባላትን በረከትም ይመልስላታል። የፍርድ እጁንም ያነሣላታል። 3. ሆሴዕ ከሚስቱ ጋር ታረቀ (ሆሴዕ 3) ተሜር ሆሴዕንና ልጆችዋን ትታ ወደ ግልሙትና ተሰማራች። በአመንዝራነቷም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወደቀች። ምን እንደደረሰባት አናውቅም። ምናልባት የሌላ ሰው ባርያ ወይም ዕቁባት ሆና ይሆናል። ወይም በታላቅ ሐፍረት ወደ አባቷ ተመልሳ ይሆናል። ሆሴዕ እንደገና የሙሽርነት ጥሉሽ ከፍሎ ሊወስዳት አስፈልጎት ይሆናል። ወይም በዕዳ ተይዛ ለባርነት በመዳረጓ በገበያ ልትሸጥ የቀረበች ይመስላል። እግዚአብሔር ግን ወደ ገበያ በመሄድ ገንዘቡን እንዲከፍልና እንደገና ለራሱ ሚስት አድርጎ እንዲወስዳት ሆሴዕን አዘዘው። ይህም እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውን ታላቅ ፍቅርና የቅጣት ዓመታት ካለፉ በኋላ እንደገና የራሱ እንደሚያደርጋት የሚያሳይ መግለጥ ነበር። ሆሴዕ 3፡5 የሚያመለክተው እስራኤላውያን ጌታንና ንጉሣቸውን ዳዊትን እንደገና እንደሚፈልጉ ነው። ንጉሣቸው ዳዊት የሚያመለክተው መሢሐዊውን ንጉሥና እግዚአብሔር እንዲያገኙት የሚፈልገውን በረከት የሚያገኙበትን ጊዜ ነው። ይህም በብዙ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዳችን ያደረገውን ነገር የሚገልጽ ነው። እኛ በኃጢአት ባርነት የጠፋን ነበርን። እግዚአብሔር እንዲያድነን የሚያደርግ አንዳችም በጎ ነገር በእኛ ውስጥ አልነበረም። በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ባልተመሠረተው የክርስቶስ ፍቅር ምክንያት ግን ኢየሱስ ለእኛ ሲል በመሞት የኃጢአታችንን ዕዳ ከፍሎ የእግዚአብሔር ልጆችና የራሱ ሙሽራዎች አደረገን። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ ታሪክ ስለ ሆሴዕ ባሕርይ ምን እንማራለን? ለ) ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምን እንማራለን? ሐ) ስለ ኃጢአት ምን እንማራለን? መ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንማራለን? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ሆሴዕ 1-3 Read More »

በትንቢተ ሆሴዕ የሚገኙ ዐበይት የሥነ-መለኮት እውነቶች

1. የእግዚአብሔር ባሕርይ፡- በትንቢተ ሆሴዕ ውስጥ ሦስት ዋና ዋና የእግዚአብሔር ባሕርያትን እንመለከታለን። የመጀመሪያው፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ያለውን ኃጢአት የሚቀጣ ወይም በበደላቸው ላይ የሚፈርድ መሆኑ ነው። ይህም ሕዝቡን በሕይወታቸው ካለው ኃጢአት ለማጥራት ነው። ሁለተኛው፥ የእግዚአብሔር ምሕረት ነው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ነገር ግን ለብዙ ዓመታት ሕዝቡን በተደጋጋሚ በማስጠንቀቅ በትዕግሥት ጠበቃቸው። በፍርድ ጊዜ እንኳ አልጣላቸውም። ሦስተኛ፥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር ጥልቅና ዘላለማዊ ነው። እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ሕዝቡን የሚወድ፥ በሌላ በኩል ኃጢአት ሲሠሩ የሚጠላቸው አይደለም። እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት ሕዝቡን ይቀጣል። ዳሩ ግን ያ ቅጣት ለእነርሱ ያለውን ታላቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው። እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ ወይም ኅብረት ከፈጠረ ለዘላለም ይወዳቸዋል። ኃጢአት ሲያደርጉ እንኳ አይተዋቸውም (ሮሜ 8፡38-39)። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች እነዚህን ሦስት የእግዚአብሔር ባሕርያት ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር እነዚህን ባሕርያት በሕይወትህ ሲገልጥ ያየኸው እንዴት ነው? 2. ምንዝርና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ከባድና ክፉ ስለ መሆኑ፡- ኃጢአት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ቢሆንም፥ ከሌሎች ይልቅ አስከፊ ውጤት የሚያስከትሉ አንዳንድ ኃጢአቶች አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ከተጠቀሱ ኃጢአቶች ዋነኛው የምንዝርና ኃጢአት ሳይሆን አይቀርም። ወንድና ሴት በሚጋቡበት ጊዜ አንዳቸው ለሌላቸው ታማኝ ለመሆን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ይገባሉ። እርስ በርስ ይሰጣጣሉ፤ በወሲብ ግንኙነት አንዳቸው ለሌላቸው ታማኞች እንደሚሆኑ ቃል ይገባሉ። በስሜትና በአካል አንድ ይሆናሉ። እግዚአብሔር ጋብቻን የሠራው በዚህ ዓይነት ነው። ወንዱ ወይም ሴቷ ያንን ቃል ኪዳን በሚያፈርሱበትና ምንዝርና በሚፈጽሙበት ጊዜ አንዳቸው ሌላቸውን መዋሸታቸው ብቻ ሳይሆን በጋብቻው ውስጥ የነበረውን ቃል ኪዳንና አንድነት ያፈርሳሉ፤ ወይም ደግሞ አንድ ጊዜ በጋብቻ ውስጥ የነበረውን አንድነት ያፋልሳሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመልካም ግንኙነት መቀጠል አስቸጋሪ ይሆናል። አንዱ ሌላውን ማመን ይከብደዋል፤ ልጆቻቸው ይሠቃያሉ፤ ጋብቻቸውም ሊፈርስ ይችላል። ቤተ ክርስቲያንንና መንግሥትን ብርቱ የሚያደርገው ጠንካራ ቤተሰብ ይፈርሳል። መልካም ጋብቻ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የሚመሠረቱበት ጥሩ መሠረት ነው። ብዙ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ባሎች ቢያመነዝሩ ምንም እንዳይደለ፥ ሚስቶች ግን ይህን ማድረግ እንደሌለባቸው የሚያቀርቡትን አሳብ መጽሐፍ ቅዱስ አይቀበልም። በእግዚአብሔር ፊት ሁለቱም ታማኞች መሆን አለባቸው። መንፈሳዊ ምንዝርናም በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር ነው። ሁላችንም ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛችን አድርገን በተቀበልን ጊዜ እግዚአብሔርን ብቻ ለማምለክ ቃል ኪዳን ገብተናል ማለት ነው። ከእግዚአብሔርና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ሆነናል። የዚህ ዓለም ነገሮች ለምሳሌ፡- ቍሳዊ ሀብት ወይም ሐሰተኛ አምልኮ ዝንባሌያችንን ከኢየሱስ እንዲያርቀን በምንፈቅድበት ጊዜ መንፈሳዊ ምንዝርና እየፈጸምን ነው ማለት ነው። በእኛና በእግዚአብሐር መካከል ያለው ግልጽ ግንኙነት ይበላሻል። ምስክርነታችን ይበላሻል። የእግዚአብሔርን ስም እናሰድባለን። በቤተሰባችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይደርስባቸዋል። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች በምንዝርና የሚወድቁት ለምንድን ነው? ለ) ይህስ ጋብቻቸውን የሚጐዳው እንዴት ነው? ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ አመንዝራነትን አጥብቆ የሚቃወመው ለምን ይመስልሃል? መ) ሥጋዊና መንፈሳዊ ምንዝርና የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ) ክርስቲያኖች ከሁለቱም ዓይነት ምንዝርና ራሳቸውን እንዴት ሊጠብቁ ይችላሉ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

በትንቢተ ሆሴዕ የሚገኙ ዐበይት የሥነ-መለኮት እውነቶች Read More »

ትንቢተ ሆሴዕን የሚመለከቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

1. የሆሴዕና የጎሜር ጋብቻ የአብዛኛው የትንቢተ ሆሴዕ ታሪክ መሠረት የሆሴዕና የጎሜር ታሪክ መሆኑን ተመልክተናል። ዳሩ ግን ምሁራን ይህንን ታሪክ የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህንን ታሪክ ከሚረዱባቸው መንገዶች መካከል ጥቂቶቹ ቀጥለው ተዘርዝረዋል፡- ሀ. ተምሳሌታዊ አተረጓጐም፡- አንዳንድ ምሁራን ይህ ታሪክ እውነተኛ መሆኑን አያምኑም። ይህ ታሪክ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረውን አመንዝራነት የተሞላበት ግንኙነት የሚያሳይ ለነቢዩ የተሰጠ ራእይ ወይም ምሳሌ ነው ይላሉ። ለ. ቀጥተኛ አተረጓጐም፡- አብዛኛዎቹ ምሁራን ይህ ታሪክ በሆሴዕ ሕይወት በእርግጥ የተፈጸመ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ታሪኩን የሚተረጕሙበት መንገድ ግን ይለያያል። 1. ትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 1ና 3 ሆሴዕ ከጎሜር ጋር ስለፈጸመው ጋብቻ ይናገራሉ። የሁለቱም ምዕራፎች ድርጊቶች በአንድ ጊዜ የተፈጸሙ እንጂ ሁለት የተለያዩ ድርጊቶች አይደሉም። ሆሴዕ 3 እርስዋን ከማግባቱ በፊት ጎሜር ምን ዓይነት ሴት እንደነበረች ተጨማሪ ዝርዝር አሳቦችን ያቀርባል ብለው ያምናሉ። 2. ሆሴዕ ሁለት ሴቶችን አገባ። ሆሴዕ 1 የሚገልጠው ከጎሜር ጋር ስላደረገው ንጹህ ጋብቻ ነው። ሆሴዕ 3 ግን ለሁለተኛ ጊዜ ማንነቷ ካልታወቀ ከአንዲት አመንዝራ ሴት ጋር ስለፈጸመው ጋብቻ የሚገልጥ ነው።  3. ሆሴዕ ጎሜር የተባለች አንዲት ሴት አገባ። የመጀመሪያው ጋብቻ በሆሴዕ 1 ተገልጧል። የጎሜር አመንዝራነት በባርነት መውደቋና ከሆሴዕ ጋር እንደገና መጋባቷ ደግሞ በምዕራፍ 3 ተገልጧል። ይህ አመለካከት ሁለቱን ምዕራፎች በሚመለከት እጅግ በጣም ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤን የሚያስጨብጥና የተለመደ ይመስላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሊቃውንት ሆሴዕ ባገባት ጊዜ ምን ዓይነት ሰው ነበረች? ስለሚለው ጥያቄ የተለያየ አመለካከት አላቸው። ሀ. አንዳንድ ምሁራን ጎሜር ከሆሴዕ ጋር በጋብቻ ስትጣመር ድንግል እንደነበረችና ከተጋቡ በኋላ ግን አመንዝራ እንደሆነች አበክረው ይናገራሉ። ለ. ሌሎች ምሁራን ጎሜር እንደ ብዙሐኑ የእስራኤል ሕዝብ ጣዖታትን የምታመልክ «መንፈሳዊ አመንዝራ» ብቻ ነበረች ብለው ያስባሉ። ሐ. በመጨረሻም፥ ሌሎች ምሁራን ጎሜር ሆሴዕን ከማግባቷ በፊት አመንዝራ ነበረች ይላሉ። አመንዝራ ብትሆንም እንኳ ሆሴዕ እንዲያገባት እግዚአብሔር አዘዘው። በኋላም ሆሴዕ ለእርሷ የነበረውን ታላቅ ፍቅር ትታ ወደ ቀድሞ የምንዝርና ኑሮዋ ተመለሰች። ይህም በእርሷ ላይ ከፍተኛ ችግር አመጣ። ሆሴዕ ከባርነቷ እንደገና በመዋጀት ሚስት አድርጎ ወሰዳት። እነዚህ አመለካከቶች ሁሉ የአተረጓጐም ችግር ቢኖርባቸውም፥ ታሪኩን የምንረዳበት እጅግ የተለመደው መንገድ ግን ይህ የመጨረሻው አመለካከት ነው፤ ከእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ጋርም በሚገባ የሚስማማ ነው። እስራኤላውያን፥ አብርሃም ሳይቀር፥ እግዚአብሔር ሳይጠራቸው በፊት ጣዖት አምላኪዎች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እግዚአብሔር በፍቅሩ መጥቶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ መንፈሳዊ አመንዝራዎች ነበሩ። ከዚያ በኋላ ባለው ታሪካቸው ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ቢያደርጉም እንኳ ለጣዖት መስገዳቸውን ቀጠሉ። ስለዚህ ጎሜር ካገባች በኋላ በምንዝርናዋ እንደቀጠለች እነርሱም መንፈሳዊ አመንዝራዎች ነበሩ (ለምሳሌ ሕዝቅኤል 16 እና 23)።  2. የበአል አምልኮ  እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ እስራኤላውያን ከእርሱ በቀር ሌሎች አማልክትን ላለማምለክ ቃል ገብተው ነበር (ዘጸአት 20፡1-6)። ይሁን እንጂ እስራኤል ለእግዚአብሔር በሚቀርበ አምልኮ ላይ የጣዖታትን አምልኮ ለማከል በተከታታይ ይፈተኑ ነበር። ይህም የተጀመረው እስራኤላውያን በታዘዙት መሠረት ከነዓናውያንን መሉ በሙሉ ባልደመሰሱበት በኢያሱ ጊዜ ነበር። ስለዚህ ከከነዓናውያን ጋር ወዲያውኑ በመጋባት፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮን ለከነዓናውያን አማልክት ከሚቀርብ አምልኮ ጋር አደባለቁ (ለምሳሌ፡- መሳፍንት 2፡11-15)። ከከነዓናውያን ዐበይት አማልክት አንዱ በአል ነበር። ኤልያስ ትግል ያደረገው የበአልን አምልኮ በመቃወም እንደነበር ይታወሳል። የስሙ ትርጉም «ጌታ» ወይም «የምድር ባል» ሲሆን፥ የዝናብና አውሎ ንፋስ አምላክ፥ ደግሞም ምድር ፍሬያማ እንድትሆን የሚያደርግ አምላክ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ሰዎች ልጆችን እንዲወልዱ የሚያደርገውም እርሱ እንደሆነ ይታመን ነበር። በአል ሞት የተባለ ጠላት ነበረው። በአል ኃያልና ብርቱ በሚሆንበት ጊዜ የከነዓን ምድር እጅግ ብዙ ምርትና ሰብል ታገኝ ነበር። ሞት በሚበረታበት ጊዜ ድርቅ ይሆን ነበር። በአል ጠንካራና ብርቱ መሆኑንና የማያቋርጥ ምርታማነት መኖሩን ማረጋገጥ የሰዎቹ ኃላፊነት ነበር። ይህንን የሚያደርጉት በአልን በማምለክ ነበር። ይህ አምልኮ የእንስሳትን፥ የእርሻ ፍሬንና በተለይም የሰውን መሥዋዕትን የመሳሰሉ የተለያዩ ዓይነት መሥዋዕቶችን የሚያጠቃልል ነበር። ይህ አምልኮ የምንዝርና ሥርዓትንም የሚጨምር ነበር። በእያንዳንዱ የተቀደሰ ወይም ከፍተኛ የአምልኮ ስፍራ የወንድና የሴት አመንዝራዎች ይገኙበት ነበር። በአልን ለማምለክ የሚመጡ ሰዎች ከእነዚህ የበአል ወንድና ሴት ካህናት ከሆኑት አመንዝራዎች ጋር ዝሙት መፈጸም ነበረባቸው። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ከማምለክ አኳያ በአልን ከዋና ዋና አማልክት እንደ አንዱ ተቀብለውት ነበር። ከእውነተኛው አምላክ ከእግዚአብሔር ሌላ ሐሰተኛ አምላክ በማምለክ መንፈሳዊ ምንዝርና መፈጸም ብቻ ሳይሆን፥ ከእነዚህ አመንዝራዎች ጋር ዝሙት በማድረጋቸው ሥጋዊ አመንዝራዎችም ሆነው ነበር። ሆሴዕ የበአልን አምልኮ አጥብቆ ይቃወም ነበር (ሆሴዕ 4፡10-12፤ 13፡3-4)። እግዚአብሔር ለእርሱ የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ለሌሎች ጣዖታት በሚቀርብ የሐሰት አምልኮ እንዲረክስ የማይፈልግ መሆኑን ሆሴዕ አሳይቶአል። የተቀየጠ አምልኮ ሐሰተኛ እንጂ እውነተኛ አምልኮ ሊሆን የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። እስራኤላውያን በአል ይሰጠናል ብለው ያሰቡትን ነገር እግዚአብሔር የወሰደባቸው መሆኑን መመልከት የሚያስገርም ነው። እርሻቸው በቂ ፍሬ እንዳይሰጥ አደረገ (ሆሴዕ 8፡7-10)። ቍሳዊ ብልጽግናቸውን (ሆሴዕ 9፡1-4) እና ፍሬያማነታቸውን (ሆሴዕ 9፡10-17)፣ የአምልኮ ስፍራዎችንና ጣዖቶቻቸውን (ሆሴዕ 10፡ 1-6)፥ የጦር ኃይላቸውን (ሆሴዕ 10፡9-15) ሁሉ አጠፉ። እግዚአብሔር ሐሰተኞች አማልክት ክብሩን እንዲሰርቁ አይፈቅድም። ባዶና የማይጠቅሙ መሆናቸውን እንዲያውቁ እነዚህ የሐሰት ሃይማኖቶችና አማልክት እንሰጣለን የሚሉትን ተስፋዎች ሁሉ ይወስዳል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ፥ ሃይማኖትን የመቀያየጥ ተመሳሳይ ዝንባሌ እንመለከታለን። ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን፥ ቍሳዊ ሀብትና ንብረታቸውን በአንድነት ለማምለክ ሲሞክሩ እንመለከታለን። ይህ መንፈሳዊ ምንዝርና ነው (ያዕቆብ 4፡4)። ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሌሉች ደግሞ ወደ አስማተኞች፥ ጠንቋዮች፥ ቃልቻዎች፥ ኮከብ ቈጣሪዎችና ወደ አባቶቻቸው ውቃቢ ወዘተ. ይሄዳሉ። የእግዚአብሔርን አምልኮ ከባህላዊ አምልኮ ጋር ይደባልቃሉ። ይህም ሰይጣንን እንደማምለክ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአሁኑ ጊዜ በርካታ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን አምልኮ ከሌሎች አምልኮ ጋር እንዴት እንደሚቀይጡ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡ እንጂ መንፈሳዊ አመንዝራዎች አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ ትችላለህ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ ሆሴዕን የሚመለከቱ ዋና ዋና ጉዳዮች Read More »

የትንቢተ ሆሴዕ አስተዋጽኦ እና ዋና ዋና አላማዎች

I. የትንቢተ ሆሴዕ አስተዋጽኦ  የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ሆሴዕ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የምታገኘውን በማንበብ እርሱን በሚመለከት የተጠቀሱትን ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝር። ትንቢተ ሆሴዕ በማያሻማ መንገድ በሁለት ክፍሎች ተከፍሏል። ክፍል 1፡- ሆሴዕ 1-3 ስለ ሆሴዕ ቤተሰብ ታሪክ የቀረበ ትረካ ነው። ሆሴዕ ከሚስቱ ከጎሜር ጋር የነበረው ግንኙነት እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረው ግንኙነት ምሳሌ ነበር። የሆሴዕ ልጆች በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ፍርድ አስቀድመው የሚናገሩ ምልክቶች ሆነው ቀርበዋል። ክፍል 2:- ሆሴዕ 4-14 ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጡትን ትንቢቶች የሚያካትት ሲሆን፥ እነዚህም ስለ መጥፋታቸው በመጨረሻም ስለ መመለሳቸው የሚናገሩ ናቸው። የሚከተለውን የትንቢተ ሆሴዕ አስተዋጽኦ መርምር፡- 1. በሆሴዕ ቤተሰብ ታሪክ አማካይነት የተሰጡ ትንቢቶች (ሆሴዕ 1-3)፡ ሀ. በሆሴዕ ልጆች ምክንያት የተሰጠ ትንቢት (ሆሴዕ 1፡1-2፡1)፥  ለ. ሆሴዕ ከአመንዝራይቱ ሚስቱ ከጎሜር ጋር በነበረው ግንኙነት ተምሳሌት የተሰጠ ትንቢት (ሆሴዕ 2፡2-3፡5)።  2. ስለ እስራኤል የተሰጡ ትንቢቶች (ሆሴዕ 4-14)፡- ሀ. የእስራኤልን አለመታመን የሚመለከት (ሆሴዕ 4-6፡3)።  ለ. አሦር በእስራኤል ላይ ስለምትፈጽመው ጥፋት የተነገረ ትንቢት (ሆሴዕ 6፡4-10፡15)፣  ሐ. እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለው ታማኝነትና ፍቅር የእስራኤል መመለስ ማለት ነው (ሆሴዕ 11-14)።  II. የትንቢተ ሆሴዕ ዓላማ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ቃል ኪዳን አድርጎ ነበር። በዚያ ቃል ኪዳን ከተጠቀሱት ነገሮች አንዱ እግዚአብሔር ሕዝቡ በእርሱ ላይ ባላቸው መታመን እንደሚባርካቸው ነበር። ዳሩ ግን በእርሱ ላይ ካመፁና ሐሰተኞች አማልክትን ካመለኩ ደግሞ እንደሚቀጣቸው ተናግሮ ነበር። ይህ ቃል ኪዳን ባልና ሚስት በመጀመሪያ በሚጋቡበት ጊዜ ከሚገቡት ቃል ኪዳን ጋር የሚመሳሰል ነበር። የሁለቱንም ግን ታማኝነት የሚጠይቅ ቃል ኪዳን መሆን ነበረበት። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን በምሳሌነት የእስራኤል ባል ሆኖ የምናየው በዚህ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውን ፍቅር ከሕዝቡ አባቶች ጋር በገባው ቃል ኪዳን በኩል አሳይቷል (ሆሴዕ 12፡2-6)። የእስራኤልን ሕዝብ ገና ከለጋነታቸው ጊዜ ጀምሮ ጠበቃቸው (ሆሴዕ 11፡1-4፤ 12፡9፤ 13፡4)። ከሰሎሞን ሞት በኋላ የእስራኤል መንግሥት ከተከፈለበት ከ931 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከ ሆሴዕ ዘመን 750 ዓ.ዓ. ድረስ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይታገሥ ነበር። ለእርሱ ታማኝ እንዳልሆኑ ይገልጡላቸውና ያስጠነቅቁአቸው ዘንድ በርካታ ነቢያትን በተደጋጋሚ ይልክ ነበር። የእስራኤላውያንን ልብ ለመመለስ ኤልያስን፥ ኤልሳዕን፥ አሞጾንና ሌሎች ነቢያትን ላከላቸው። እነርሱ ግን በንስሐ ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። ይልቁንም በከፊል እግዚአብሔርን፥ በከፊል ደግሞ ሌሎች ጣዖታትን ለማምለክ ፈለጉ። እስራኤል አግብታ በትዳር ላይ እያለች ለባሏ ታማኝ ባለመሆን ከሌሎች ወንዶች እንደምትፈልግ ሴት ነበረች። በመጨረሻ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት አለቀ። የፍርድ ጊዜ መጣ። እግዚአብሔር እስራኤላውያን በንስሐ ይመለሱ ዘንድ የመጨረሻ ዕድል ለመስጠት ሆሴዕን ላከላቸው። አለበለዚያ ወደ ምርኮ በመውሰድ እንደሚቀጣቸው ተናገረ። ትንቢተ ሆሴዕ ታማኝ ላልሆነችው እስራኤል እግዚአብሔር የሰጠው መልእክት ነው። እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ምርኮን በማምጣት ከመቅጣቱ በፊት ያስተላለፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነበር። የማይታዘዙ ከሆነ በምርኮ እንደሚወሰዱ በሲና ተራራ በተደረገው ቃል ኪዳን ላይ እንደ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ተሰጥቶ እንደነበር የሚታወስ ነው (ዘዳግም 28፡64)። የእስራኤልን አለመታመንና ክፋት በሚታይ መንገድ ለመግለጥ፥ እግዚአብሔር የሆሴዕን ቤተሰብ በምሳሌ ተጠቀመበት። የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሚስት እንደሆነችውና ከአሕዛብ ጋር በነበራት ግንኙነት ሌሎች አማልክትን በማምለክ ምንዝርና እንደፈጸመችው እስራኤል እንዲሁም የሆሴዕ ሚስት የነበረችው ጎሜርም ለሆሴዕ ታማኝ አልነበረችም። ሁለቱም አመንዝራዎች ነበሩ። ከዚህ የተነሣ ለተወሰነ ጊዜ ግንኙነቱን ለማቋረጥ ወሰነ። የሆሴዕ የመጀመሪያ ክፍል የተጻፈው እግዚአብሔር ፍቺን እንደሚደግፍ በሚመስል መልኩ ነው። ሆሴዕ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረውን ግንኙነት ማቋረጡን ለማሳየት በአይሁድ ባህላዊ የፍቺ ዘዴ ተጠቀመ (ሆሴዕ 2፡2)። ይህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ክስ እንደመሠረተ ተደርጎ የቀረበ ዓይነት ነው (ሆሴዕ 4፡1፥ 4፥ 15፤ 5፡1፥ 7)። የሆሴዕና የጎሜር ልጆች እግዚአብሔር ከዚያ በኋላ ለእስራኤል ምሕረት እንደማያደርግ፥ ከእንግዲህ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች እንዳይደሉና በኢይዝራኤል እንደሚቀጡ የሚያሳዩ ምሳሌያዊ ስሞች ነበሯቸው። ዳሩ ግን እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የሚፈርደው ፍርድ ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም እንኳ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የሚኖረው መለያየት ዘላቂ አልነበረም። ሆሴዕ ለጎሜር የነበረውን ዘላቂ ፍቅር ከባርነት በመዋጀትና እንደገና በማግባት እንዳሳየ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንደገና የቃል ኪዳን ግንኙነት ያደርጋል። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረው ፍቅር ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ ከቶ አይችልም። እግዚአብሔር አንድ ቀን ወደ እስራኤል ይመልሳቸውና ይፈውሳቸዋል፤ እንዲሁ ይወዳቸዋል (ሆሴዕ 14፡4)። ባለፈው የእስራኤል ታሪክ የታየው የማይለወጠው የእግዚአብሔር ፍቅር ወደፊት ለእነርሱ ላለው ፍቅር ዋስትና ነበር። ሆሴዕ እስራኤል በእግዚአብሔር ላይ የፈጸመችውን ምንዝርና በምሳሌ መልክ ማሳየት ብቻ ሳይሆን፥ ሕዝቡንና መሪዎቹን ስለ መንፈሳዊ አመንዝራነታቸው በቀጥታ ይገሥጻቸዋል። በእግዚአብሔር ላይ ለማመፅ ከአሕዛብ ጋር ቃል ኪዳን አድርገው ነበር። በአልን የመሳሰሉ ባዕድ አማልክትንም ያመልኩ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ አሦር በማስማረክ እነርሱን የሚቀጣበት ጊዜ ደርሶ ነበር (ሆሴዕ 5፡8-9)። 5ኛ ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች ዛሬ መንፈሳዊ ምንዝርና መፈጸም የሚችሉት እንዴት ነው? ለ) ይህ ነገር ሲፈጸም ያየህባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ። ሐ) የቤተ ክርስቲያን አባላት ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው እንዲቆዩ ለማድረግ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምን ሚና መጫወት አለበት? መ) የመንፈሳዊ ምንዝርናን አደገኛነት ለማስተማር ትንቢተ ሆሴዕን እንዴት ልትጠቀምበት የምትችል ይመስልሃል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሆሴዕ አስተዋጽኦ እና ዋና ዋና አላማዎች Read More »

የትንቢተ ሆሴዕ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

ሆሴዕ የኖረበት ዘመን እጅግ አስቸጋሪና ከባድ ነበር። ምንም እንኳ የተወለደው ከሰሎሞን ዘመን በኋላ እስራኤል አይታ የማታውቀው የተትረፈረፈ ብልጽግናና ሰላም በሞላበት ጊዜ ቢሆንም ሆሴዕ ግን የእስራኤልን ጥፋትና ውድቀት መስክሯል። ሆሴዕ ከአሦራውያን ጋር ውጊያ በተካሄደበትና የእስራኤል መንግሥት በተደመሰሰበት ዘመን ኖረ። ከእስራኤል ውድቀት በኋላ ምን እንዳደረገ የምናውቀው ነገር የለም። ከእስራኤል ውድቀት በኋላ የይሁዳ ንጉሥ እስከነበረው እስከ ሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ድረስ እንደኖረ ተገልጾአል። ሆሴዕ በእስራኤል ከተወለዱና መጻፍ ከሚችሉ ጥቂት ነቢያት አንዱ ነበር። በእስራኤል የተወለደና መጻፍ የሚችል ሌላው ነቢይ ዮናስ ነበር። ሆሴዕ በተወለደ ጊዜ ንጉሡ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነበር። ኢዮርብዓም ከኢዩ ወገን የሆነ የነገሥታት ዘር ነበር። በፖለቲካ አንጻር ታላቅ ንጉሥ ነበር። አባቱ ዮአስ እስራኤልን ከሶርያ ጭቆና ነጻ ያወጣ ሰው ነበር። ዳግማዊ ኢዮርብዓም በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት የእስራኤል የነበሩትን ግዛቶች ሁሉ ለማስመለስ ችሏል። እስራኤል በጳለስጢና ምድር ከነበሩ ነገሥታት ሁሉ እጅግ ኃያል ሆነች። ዳግማዊ ኢዮርብዓም ዋና ዋና የንግድ መተላለፊያዎችን ሁሉ ስለተቆጣጠረ እስራኤልን ባለጠጋ መንግሥት አድርጓት ነበር። ትልልቅ ሕንጻዎችን፥ ወታደራዊ መከላከያዎችን ገንብቶ ነበር። የዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት በሰው አመለካከት ለእስራኤል ሕዝብ እጅግ መልካም ጊዜ ነበር። በመንፈሳዊ ረገድ ግን ነገሮች ሁሉ እጅግ ተበላሽተው ነበሩ። እግዚአብሔርን በማምለክ ረገድ በታማኝነት የጸኑ ጥቂት ሰዎች ነበሩ ሕዝቡ በአልን የመሳሰሉ ሐሰተኞች አማልክትን ያመልኩ ነበር። ሃይማኖታዊ መሪዎች በሥነ-ምግባር እጅግ የተበላሹ ነበሩ። ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ ውሸትን የሚያስተምሩ ሐሰተኞች ነቢያት ነበሩ፡፡ ነገሥታቱ ሰካራሞችና የገዛ ሕዝባቸውን የሚያስጨንቁ ነበሩ። የእስራኤል ሕዝብ ነገሮች ሁሉ መልካም የሆነለት ቢመስለውም፥ ሆሴዕ የእስራኤል ሕዝብ ፈጥኖ እንደሚደመሰስና የኢዩ ንጉሣዊ የዘር ሐረግም እንደሚያበቃ ተናገረ። ነቢዩ ትንቢቶቹ ምን ያህል ፈጥነው እንደሚፈጸሙ ምናልባት አልተገነዘበም ይሆናል። ኢዮርብዓም በ753 ዓ.ዓ. ሲሞት፥ መንግሥቱ ፈጥኖ ተፍረከረከ። ስለ መጨረሻዎቹ የእስራኤል ነገሥታት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡- 1. የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ መንገሥ በጀመረ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በሰሎም ተገደለ። ይህም የኢዩ ሥርወ መንግሥት ፍጻሜ ነበር።  2. ሰሎም ለአንድ ወር ገዛና በምናሔም ተገደለ።  3. ምናሔም መንገሥ በጀመረ ጊዜ አገሪቱ ባለጠጋ ነበረች። በ745 ዓ.ዓ. ግን ቴልጌልቴልፌልሶር የአሦርን በትረ መንግሥት በመጨበጥ የአሦርን መንግሥት ወደ ምዕራብ አሰፋ። ይህ የአሦር መንግሥት ታላቁ የዓለም መንግሥት በመሆን ለ100 ዓመታት ገናና ሆኖ ቆየ።  አሦራውያን የንግድ መሥመሮችን ሁሉ እየተቈጣጠሩ በሄዱ ቍጥር እስራኤል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ያሠቃያት ጀመር። አሦራውያን ያሸነፏቸውን ሕዝቦች የሚቆጣጠሩበት አዲስ ዘዴ ማበጀት ጀመሩ። ካሸነፏቸው ሕዝቦች መካከል በከፍተኛ ቊጥር የሚገመቱትን ወደ ሌላ አገር በመውሰድ ያሰፍሯቸው ጀመር። ሌሎች ዝርያዎችን ደግሞ በጦርነት ወደ ያዙአቸው አገሮች ያመጡ ጀመር። በዚህ ዓይነት የተለያዩ ዝርያዎች እንዲቀላቀሉ በማድረግ በአሦር ላይ ማመፅን አስቸጋሪ አደረጉት። በ722 ዓ.ዓ. በእስራኤል ላይ የተፈጸመው ይህ ነበር። ምናሒም የተባለው የእስራኤል ንጉሥ የአሦራውያን ጦር እንዳይወጋው ለአሦር መንግሥት በመገበር የዚህ መንግሥት አገልጋይ ሆነ።  4. ምናሴ ከሞተ በኋላ ልጁ ፋቂስያስ በፋቁሔ እስከተገደለ ድረስ ለሁለት ዓመታት ብቻ ነገሠ።  5. ፋቁሑ የአሦርን መንግሥት አገዛዝ ለማስወገድ ሞከረ። ከሶርያ ጋር በመተባበር አሦርን ለማጥቃት ያልተባበረችውን ይሁዳን ወጉ። ይህም ድርጊት አሦርን እጅግ ስላስቈጣት ሶርያን በማጥቃት በ732 ዓ.ዓ. ፈጽማ አጠፋቻት። ከዚያም ፋቁሑ ተገደለ።  6. የእስራኤል የመጨረሻ ንጉሥ የሆነው የኤላ ልጅ ሆሴዕ በአሶር ቊጥጥር ሥር የሚኖር የአሦር መንግሥት መሣሪያ ነበር። ይሁን እንጂ በ727 ዓ.ዓ. ቴልጌልቴልፌልሶር ሲምት ለማመፅ ወሰነ። አዲሱ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር አምስተኛ እስራኤልን ወጋ። ከሦስት ዓመታት ጦርነት በኋላ የሰማርያ ከተማ ተያዘችና ተደመሰሰች። የእስራኤል መንግሥት በ722 ዓ.ዓ. ተደመሰሰ። አብዛኛው ሕዝብ በመካከለኛው ምሥራቅ ወደሚገኙ የአሕዛብ መንግሥታት በምርኮ ተወሰዱ። አሦራውያን ሌሎች ሕዝቦችን ይኖሩ ዘንድ ወደ እስራኤል አመጡ። እነዚህ አሕዛብ ከእስራኤላውያን ጋር በመጋባት በአዲስ ኪዳን ዘመን ሳምራውያን ተብለው የሚጠሩትን ሕዝቦች አስገኙ። ሆሴዕ የንጉሥ ሕዝቅያስን ስም ስለሚጠቅስ በምርኮ የተወሰደ አይመስልም ለመኖር ወደ ይሁዳ ሳይሄድ አልቀረም። የሚያውቃቸውና የሚወዳቸው በርካታ ሰዎች ግን በምርኮ ሳይወሰዱ አልቀሩም። እግዚአብሔር በእርሱ በኩል የተናገራቸው ትንቢቶች ሲፈጸሙ በማየት ልቡ በኃዘን ሳይሞላ አልቀረም። ሆሴዕን የሚያበረታታው ብቸኛው ነገር ሕዝቡ ከምርኮ እንደሚመለሱ እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል ብቻ ነበር። ሆሴዕ የነበረበት ዘመን ብዙ አለመረጋጋትና ለውጥ የሚታይበት ነበር። እግዚአብሔር የሰጠውን መልእክት በቅድሚያ መንገር ሲጀምር ሕዝቡ በሰላምና በታላቅ ብልጽግና ውስጥ ስለነበሩ አይሰሙትም ነበር። እውነት ጥያቄ፥ ብዙ ጊዜ ሀብታም የሆኑና ምንም ችግር የሌለባቸው ሰዎች ወንጌልን ለመቀበል የሚቸገሩት ወይም ከባድ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው? ሕዝቡ በአሦራውያን ምክንያት አለመረጋጋትና ጭቆና በነበረባቸው ጊዜ እንኳ ሰምተው ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች አልነበሩም። ሆሴዕ ግን ለእግዚአብሔር ባለው ታማኝነት በመጽናት እርሱ የሰጠውን መልእክት በግልጽ ያስተላልፍ ነበር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሆሴዕ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት Read More »

የትንቢተ ሆሴዕ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የብሉይ ኪዳን የትንቢት መጻሕፍትን ሁለት ዐበይት ክፍሎችን ጥቀስ። ለ) በእነዚህ ሁለት ዐበይት ክፍሎች ሥር የሚገኙትን መጻሕፍት ዘርዝር። በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የመጨረሻ ክፍል አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍት የሚገኙ መሆናቸውን ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥናታችን የሚታወስ ነው። እነዚህ የትንቢት መጻሕፍት በሁለት ዋና ክፍሎች የሚከፈሉ ሲሆን፥ የመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት ይባላሉ፤ እነርሱም ኢሳያይስ፥ ኤርምያስ (ሰቆቃወ ኤርምያስን ጨምሮ)፥ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት የተባሉት በመጠናቸውና በያዙዋቸው ትንቢቶች ጥልቀት ምክንያት ነው። በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው አሥራ ሁለቱን የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ መጻሕፍት ነው። እነዚህ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ። የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት የተባሉበት ምክንያት በመጠን አነስተኛና የትንቢተቹ ዝርዝርና ጥልቀት ከሌሎቹ መጻሕፍት ያነሰ በመሆኑ ነው። አይሁድ እነዚህን አሥራ ሁለት መጻሕፍት «አሥራ ሁለቱ ነቢያት» የሚል መጠሪያ በመስጠት እንደ አንድ መጽሐፍ ጠርዘዋቸዋል። የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት በአራት ሊከፈሉ ይችላሉ። ሀ. ለሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት (ሆሴዕ፥ አሞጽ ምናልባትም ኢዩኡል)፥ ለ. ከምርኮ በፊት ለደቡብ የይሁዳ መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት (ሚክያስ፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስና ምናልባት ኢዩኤል)፥  ሐ. በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ፍርድን ያወጁ ነቢያት (ዮናስ፥ አብድዩ፥ ናሆም)፥  መ. ከምርኮ መልስ በኋላ ያገለገሉ ነቢያት (ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ) ናቸው። በእንግሊዝኛውና በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ መካከል የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት የአቀማመጥ ቅደም ተከተልን በሚመለከት ልዩነቶች አሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የአቀማመጥ ቅደም ተከተሉን የወሰደው ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን፥ አማርኛው ደግሞ ከዕብራይስጥ ወደግሪክ ከተተረጐመው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ በመሆኑ ነው። በዚህ ጥናታችን ውስጥ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ቀደም ተከተል መሠረት እነዚህን መጻሕፍት እንመለከታለን። አብዛኛዎቹ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት አቀማመጥ በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አይደለም። መጻሕፍቱ የተጻፉበትን ጊዜ ስለማይገልጹ አንዳንዶቹ መጻሕፍት መቼ እንደተጻፉ ለመናገር ምሁራን በአሳብ ይለያያሉ። በተለይ ትንቢተ አብድዩና ኢዩኤል መቼ እንደተጻፉ መወሰን በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶቹ እነዚህ ሁለት መጻሕፍት ቀደምት የትንቢት መጻሕፍት (ከ840-835 ዓ.ዓ. የተጻፉ) እንደሆኑ ሲናገሩ፥ ሌሎች ግን ትንቢተ አብድዩና ኢዩኤል በ600 ዓ.ዓ. እንደተጻፉ ይገምታሉ። አሁን ባሉበት ቅደም ተከተል መሠረት የሚገኙት ለምን እንደሆነ አናውቅም። አሥራ ሁለቱ የነቢያት መጻሕፍት በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት የሚገኙ ቢሆኑ ኖሮ፥ ቅደም ተከተላቸው የሚከተለው ሊሆን ይችል ነበር፡- ዮናስ፥ አሞጽ፥ ሆሴዕ ሚክያስ (ከ750-700 ዓ.ዓ.) ናሆም፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስ፥ አብድዩ፥ ኢዩኤል (ከ650-586 ዓ.ዓ.) ሐጌ፥ ዘካርያስ፥ ሚልክያስ (ከ520-420 ዓ.ዓ.) በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ብዙ ጊዜ ከማይነበቡና ካልታወቁ መጻሕፍት መካከል ዋናዎቹ አሥራ ሁለቱ የነቢያት መጻሕፍት ናቸው። የእግዚአብሔር ቃል ቢሆኑም እንኳ የሚያነብቡአቸው ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። በእግዚአብሔር ሙሉ ፈቃድ ውስጥ እንድንኖር የሚረዱንና ከሕይወታችን ጋር ልናዛምዳቸው የምንችል በርካታ መንፈሳዊ እውነቶችን ከእነዚህ መጻሕፍት እናገኛለን። የእነዚህን መጻሕፍት መልእክት አንድ ጊዜ ከተረዳን መልእክቱን በማድነቅ፥ የቤተ ክርስቲያናችንን ምእመናን ለማስተማር እንጠቀምበታለን። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ከአንድ ሰው ጋር ኅብረት በማድረግ ሊያድነውና ቢወደውም ከጊዜ በኋላ ሊተወውና በዘላለም ሞት ሊቀጣው ይችላልን? መልስህን አብራራ። ለ) ስለዚህ ጉዳይ ያለህን አመለካከት የሚደግፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ዘርዝር። ትንቢተ ሆሴዕ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላለው ፍቅር የሚናገር መጽሐፍ ነው። ይህም ከሰው ፍቅር የተለየ አስደናቂ ነው። እግዚአብሔር ከኃጢአታቸው ተመልሰው እርሱን ለመታዘዝ ጨርሶ ፈቃደኞች ያልሆኑትን ሕዝቡን እስራኤልን ለመቅጣት የወሰነው በፍቅር ነበር። እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው ከኃጢአታቸው ሊያነጻቸው እንጂ ሊያጠፋቸው አልነበረም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ሙሉ ለሙሉ እንደማያጠፋቸውና እነርሱን መውደዱን እንደማያቋርጥ ነገር ግን በዘመናት ሁሉ ለእነርሱ ያለውን ፍቅር እንደሚጠብቅ በፍቅር ቃል ገባላቸው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመመለስና ለመባረክ ቃል ገብቶ ነበር። እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ያለውን ፍቅር ማቋረጥ የሚችል አንዳችም ኃይል አይኖርም። ይህ እውነት ዛሬ እኛንም የሚመለከት ነው። በፍቅር እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታችን ይቀጣናል። ይህ እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያመለክት በመሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያሳየናል (ዕብራውያን 12፡5-11)። ከእግዚአብሔር ወይም ከፍቅሩ ሊለየን የሚችል አንዳችም ነገር እንደሌለ እግዚአብሔር ቃል ገብቶልናል። (ሮሜ 8፡38-39)። ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ እግዚአብሔር ፍቅሩን ከእኛ አይወስድም። ከእግዚአብሔር ጋር ወዳለ እውነተኛ ኅብረት አንድ ጊዜ ከገባን፥ የእርሱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከሆንን፥ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ስጦታውን ከተቀበልን የእግዚአብሔር ፍቅር ለዘላለም ከእኛ አይወሰድም። ይህ እውነት አንድ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ እንዳልሆነ በሚሰማው ወይም ትልቅ ኃጢአት በሠራ ጊዜ ከፍተኛ ዋስትናና መጽናናት ሊሰጠው ይገባል።  የትንቢተ ሆሴዕ ጸሐፊ  ትንቢተ ሆሴዕ የተጻፈው ሆሴዕ በተባለ ሰው ነው። ሆሴዕ የሚለው የዕብራይስጥ ስም ኢየሱስ የሚለውን ስም (ማቴዎስ 1፡21) ካስገኘው ኢያሱ ከሚለው የዕብራይስጥ ስም (ዘኁልቁ. 13፡16) ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፥ ትርጕሙም ረዲኤት፥ ነፃነት መውጣት ወይም ደኅንነት ማለት ነው። መጽሐፉ ስያሜውን ያገኘው ከጸሐፊው ስም ነው። ስለ ሆሴዕ የምናውቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው። በእስራኤል ተወልዶ ከዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የእስራኤል መንግሥት እስከወደቀበት እስከ 722 ዓ.ዓ. እና እስከ ይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ለእስራኤል ሕዝብ አገልግሏል። የሆሴዕ የነቢይነት አገልግሎት ከ760-715 ዓ.ዓ. ድረስ ሳይዘልቅ አልቀረም። ሆሴዕ ጎሜር የምትባል ሴት አግብቶ፥ ኢይዝራኤል፥ ስሩሃማና ሉዓሚ የተባሉ ሦስት ልጆችን ወልዷል። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ የነቢዩን ሕይወት ለእስራኤል ልጆች ሕያው መልእክት አድርጎ ተጠቅሞበታል። እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቢፈርድም እንኳ የማያልቅ ፍቅር ለእነርሱ እንዳለው ለማስተማር የሆሴዕን ቤተሰብ ታሪክ ተጠቅሞበታል። ትንቢተ ሆሴዕ የተጻፈው ከ760-722 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነበር። ትንቢተ ሆሴዕ የይሁዳን ነገሥታትና ሕዝቅያስን ስለሚጠቅስ (ሆሴዕ 1፡1) ተጽፎ ያለቀው ከእስራኤል ውድቀት በኋላ በይሁዳ ሳይሆን አይቀርም። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሆሴዕ መግቢያ Read More »