የፔንታቱክ ክለሣ

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) አምስቱን የፔንታቱክ መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) በየመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ገጸ ባሕርያት ዘርዝር። ሐ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዋና ዓላማ ወይም ትምህርት ዘርዝር፡፡ መ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በአጭሩ ጻፉ።

የመጀመሪያዎቹ አምስቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ፔንታቱክ በመባል በአንድ መጽሐፍ ስም ይጠራሉ። ፔንታቱክ አምስት ንዑሳን-ክፍሎች ያሉት አንድ ትልቅ መጽሐፍ ነው። የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት የሚባለው ሲሆን፥ የሚያተኩረው በነገሮች ጅማሪ ላይ ነው። በመጀመሪያ በዓለም አጀማመር ላይ ያተኩራል። ዋናው ትኩረቱ ግን በእስራኤል ሕዝብ አጀማመር ላይ ነው፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ አባቶች የሆኑትን የአብርሃም፣ የይስሐቅንና የያዕቆብን ታሪክ ይነግረናል። ቀጥሉም የእስራኤል ሕዝብ እንዴት ወደ ግብፅ ምድር እንደመጡ ለመናገር የዮሴፍን ታሪክ ይጠቀማል።

ኦሪት ዘጸአት፡- እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከነበሩበት የግብፅ ባርነት እንዴት በተአምር ነፃ እንዳወጣቸው የሚናገር ታሪክ ነው። የኦሪት ዘጸአት ዋና ትኩረት ግን እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን ወደገባበት ወደ ሲና ተራራ እንዴት እንደመራቸው ነው። ኦሪት ዘጸአት በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ስለተገባው ቃል ኪዳን ይነግረናል። በተጨማሪ እግዚአብሔር ያድርበት ዘንድና እነርሱም በዚያ ያመልኩት ዘንድ እስራኤላውያን የመገናኛውን ድንኳን እንዲሠሩ በሰጠው ትእዛዝ ላይ የተደረገ ትኩረት እንመለከታለን፡፡

ኦሪት ዘሌዋውያን፡- እግዚአብሔር በእርሱ ፊት የተቀደሱ ሕዝብ ሆነው ይኖሩ ዘንድ ለእስራኤል የሰጣቸው ሕግጋት የተመዘገበበት መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው እስራኤላውያን በሲና ተራራ ሰፍረው እያሉ ነው። ትኩረቱም እስራኤላውያን በዙሪያቸው ካሉ አሕዛብ ተለይተው እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መኖር እንደሚገባቸው በማሳየት ላይ ነው።

ኦሪት ዘኁልቁ፡- እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እስከተስፋይቱ ምድር ጫፍ ድረስ እንዴት እንደመራቸውና እነርሱ ግን ባለማመናቸው ወደ ምድሪቱ ለመግባት እንዴት እንዳልቻሉ የሚናገር መጽሐፍ ነው። በዚህም ሳቢያ ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ ለ 40 ዓመታት በምድረ በዳ ተንከራትተዋል። የመጽሐፉ ታሪክ በእግዚአብሔር ላይ የተደረገ ዓመፅ ታሪክ ነው፤ ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በዮርዳኖስ ምሥራቃዊ አካባቢ ያለውን ስፍራ በጦርነት አሸንፈው እንደያዙም ይናገራል። እስራኤላውያን ከከነዓን ምድር ፊት ለፊት ሰፍረው ወደ ምድሪቱ ለመግባት እስከተዘጋጁ ድረስ ያለውን ታሪክ ይነግረናል። ከዚያም እግዚአብሔር ከ400 ዓመታት በፊት ለአብርሃም የገባለት ቃል ኪዳን ይፈጸም ዘንድ ወረራውና ድሉ ይከተላል።

ኦሪት ዘዳግም፡- የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት ተመዝግበው የሚገኙበት መጽሐፍ ነው። ሙሴ ለአዲሱ የእስራኤል ትውልድ እግዚአብሔር በሲና ተራራ የሰጣቸውን ቃል ኪዳን ለማስታወስ ሦስት ዋና ዋና መልእክቶችን ይሰጣል። የእስራኤል ሕዝብም ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል ኪዳን አደሱ። ሙሴ በተጨማሪ ለቃል ኪዳኑ አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ውጤት በመናገር አስጠነቀቃቸው።

የኦሪት ዘዳግም መጨረሻ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የሚቀጥለው ደረጃ ወደሆነው ማለትም የከነዓንን ምድር ወደ መውረር ታሪክ ያመጣናል። ይህ ታሪክ የሚገኘው በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ ሲሆን የሚቀጥለው ጥናታችን እርሱ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በፔንታቱክ ውስጥ በእምነት ምሳሌነታቸው የተጠቀሱትን ዋና ዋና ሰዎች ዘርዝር። ለ) በየትኛው መጽሐፍ እንደሚገኙና ቅደም ተከተላቸውንም ተናገር። ሐ) ከእያንዳንዳቸው ሕይወት የምናገኛቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ጥቀስ። መ) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱን ምረጥና የዚያን ሰው ሕይወት የሚገልጥና ምሳሌነቱን እንዴት ልትከተለው እንደፈለግህ የሚያሳይ አንድ ገጽ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘዳግም 27-34

የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግም 30፡15-18 አንብብ። ሀ) በሰው ፊት የቀረቡ ሁለቱ ምርጫዎች ምንድን ናቸው? ለ) የእነዚህ ምርጫዎች ውጤት በተናጠል ምንድን ነው? ) እነዚህ የምንሰብከው ወንጌል ክፍል የሆኑት እንዴት ነው?

ብዙ ጊዜ ከርስቲያኖች ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ለሚያጋጥማቸው ችግር በአንድ ነገር ላይ ወይም በሌላ ሰው ላይ ያላክካሉ። አንዳንድ ጊዜ በሰይጣን ያመካኛሉ። ሌሎቹ ደግሞ እግዚአብሔርን ይወቅሳሉ። ሰይጣንም ሆነ እግዚአብሔር በምንወስነው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ቢችሉም፥ የመጨረሻ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት መውሰድ ያለብን እኛ ነን። ሰይጣን ከፈቃዳችን ውጭ ኃጢአት እንድንሠራ ሊያስገድደን አይችልም። በሌላም በኩል እግዚአብሐር፥ አንድን መልካም ነገር እንድናደርግ ፈቃዳችንን ጥሶ አያስገድደንም። በመጨረሻ እግዚአብሔር ምርጫውን ለእኛ ሰጥቷል። ሕይወትን ወይም ሞትን፥ በረከትን ወይም መርገምን መምረጥ እንችላለን። ሙሴ ከመሞቱ በፊት እስራኤላውያን ማድረግ ስላለባቸው ትክክለኛ ምርጫ ሊያስታውሳቸው ፈለገ። በእግዚአብሔር የሚሸለሙት ወይም የሚቀጡት ባደረጉት ምርጫ መሠረት እንደሆነ ሊያሳያቸው ወደደ።

እንደ ወንጌል ሁሉ ቃል ኪዳንም ተስፋ የተሰጠበትን በረከትና የቅጣት ማስጠንቀቂያዎችን ይዟል። ወንጌል «የምሥራች» ነው። ከኃጢአታቸው ያድናቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑት ሁሉ የድነት (ደኅንነት) ተስፋ ይዞአል። እንዲሁም ወንጌል «ክፉ ወሬ» ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰጠውን ድነት (ደኅንነት) እንቢ ላሉ ዘላለማዊ ፍርድን ያውጃልና። የወንጌል መልእክተኞች እንደመሆናችን፥ መናገር ያለብን ሰው በማመኑ ምክንያት ስለሚያገኘው በረከት (ቃል ስለ ተገባለት በረከት) ብቻ ሳይሆን፥ ለማያምኑትም ሁሉ ስለተደረገውና ስለሚጠብቃቸው ዘላለማዊ ፍርድም ጭምር ነው። ወንጌል ለሰዎች ሞት ወይም ሕይወት፥ በረከት ወይም የሞት ፍርድ እርግማን ይዞ ይቀርባል። ሰዎች ወንጌልን የበለጠ እንዲወዱት ብለን ርግማኑን ወይም የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት መደበቅ የለብንም። ሙሴ ከመሞቱ በፊት በፊታቸው ያለውን ምርጫ ለሕዝቡ በጥንቃቄ አሳያቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በወንጌል መልእክት ውስጥ የተጠቃለሉትን የበረከት ዓይነቶች ዘርዝር። ለ) በወንጌል መልእክት ውስጥ የተጠቃለሉትን የርግማን ዓይነቶች ወይም ፍርዶች ዘርዝር። ለ) ላልዳኑት ሰዎች ምርጫቸውን ያስተካክሉ ዘንድ ሁለቱንም ነገሮች ማሳየት የሚጠቅመው ለምንድን ነው? መ) ዛሬ ወንጌልን ለአንድ ሰው አካፍል። በመልእክትህ ውስጥ ሁለቱንም ማለትም የወንጌልን በረከትና ርግማንንም አቅርብ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግ። 27-34 አንብብ። ሀ) ሕዝቡ ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሚመጡባቸውን የርግማን ዓይነቶች ዘርዝር? ) ሕዝቡ በመታዘዛቸው ምክንያት የሚያገኙአቸውን የበረከት ዓይነቶች ዘርዝር። ሐ) ኢያሱ አዲሱ መሪ መሆኑን እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዴት አሳያቸው? መ) ከኦሪት ዘዳግም ለራስህ ሕይወትም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙና ሊዛመዱ የሚችሉ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ዘርዝር።

እያንዳንዱ ትውልድ ለእግዚአብሔር መሰጠትና ቃል ኪዳኑን ማደስ አለበት። ከ40 ዓመታት በፊት፥ የመጀመሪያው የእስራኤል ትውልድ በሲና ወይም በኮሬብ ተራራ ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት፥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። አሁን ደግሞ ሕዝቡ ወደ ከነዓን ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሙሴ አዲሱ ትውልድ ቃል ኪዳኑን እንዲያረጋግጥ ሲያደርግ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ደግሞ በሲና ተራራ የሰጠውን ሕግ ሲደግም እንመለከታለን። ከዚያም ወደ ከነዓን ምድር በሚገቡበት ጊዜ ቃል ኪዳኑን እንዴት እንደሚያጸኑ መመሪያ ሲተውላቸው እንመለከታለን። ሙሴ ሕጉን እንዴት በጽላት ላይ መጻፍ እንዳለባቸውና እንዴት በመታሰቢያነት እንደሚያቆሙት እስራኤላውያንን አዘዛቸው። ከዚያም በጌባል ተራራ ሕጉን እንዲያነብቡና በመታዘዝ የሚገኙትን በረከተችና ባለመታዘዝ የሚመጡትን ርግማኖች እንዲደግሙአቸው አዘዘ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሙሴ ይህንን ትእዛዝ ለአይሁድ የሰጠው ለምንድነው ብለህ ታስባለህ? ለ) ቀጣዩን ትውልድ በወንጌል ውስጥ ስለሚገኙት በረከቶችና ርግማኖች እንዴት ማስተማር እንዳለብን ይህ ምን ያስተምረናል?

አብዛኛዎቹ በረከቶች፥ በተለይም ደግሞ ርግማኖች የተሰጡት በትንቢት መልክ ነው። የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በማጥናት ወደ ፊት እየገፋን ስንሄድ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ የነገራቸው በረከቶችና መርገሞች በኃላ እንደ ተፈጸሙ እንመለከታለን። መታዘዝ ሲኖር፥ በረከትም ነበር። ዳሩ ግን እስራኤላውያን ብዙውን ጊዜ ባለ መታዘዝ ተመላልሰዋል። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በኦሪት ዘዳግም ውስጥ የተጠቀሱትን ርግማኖች ለቃል ኪዳኑ ባለመታዘዛቸው ምክንያት በእነርሱ ላይ መፈጸማቸውን የሚናገር ታሪክ ነው ለማለት እንችላለን። የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የተመዘገበባቸውን መጻሕፍት ስታጠና በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ቅጣት በኦሪት ዘዳግም አስቀድሞ ከተነገረው ጋር ማወዳደር በጣም እንደሚጠቅም አስታውስ።

የውይይት ጥያቄ፣ አንዳንዶቹ ርግማኖች በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እንዴት እንደተፈጸሙ መግለጫ ስጥ።

ኦሪት ዘዳግም የሚያበቃው በሙሴ ሞት ታሪክ ነው። እግዚአብሔር አስቀድሞቶ ኢያሱን እንደ ተከታይ መሪ አድርጎ እንዲቀባው ለሙሴ ነግሮት ነበር። ከዚያም ሙሴ ወደ ናባ ተራራ ሄደ። እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ ያለውን የተስፋይቱን ምድር አሳየው። ከዚያም ሙሴ ሞተ። ትውልዶችን ሁሉ ያየን እንደሆነ በእስራኤላውያን ዓይን እንደ ሙሴ ያለ ታላቅ መሪ አልነበረም። ሙሴ በዚህ ስፍራ እንደ «እግዚአብሔር አገልጋይ» እንደ ነቢይና «እንደ» ተአምራት አድራጊ ሆኖ ቀርቧል። እግዚአብሔር ሕግን የሰጠው በእርሱ በኩል ስለሆነ፥ አይሁድ ሙሴን ሕግ ሰጪ አድርገው ይመለከቱታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ከሙሴ ሕይወት ስለ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ አመራር ምን ለመማር እንችላለን? 

በኦሪት ዘዳግም ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ትምህርቶችን ተመልክተናል፤ ለምሣሌ፡-

 1. ሰው ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር ላለው ኅብረት መሠረቱ «ፍቅር» በሚለው ቃል ውስጥ ይገኛል። ፍቅር የሚለው ቃል በኦሪት ዘዳግም ውስጥ 22 ጊዜ ተጠቅሷል። አንድ ሰው እግዚአብሔርን በፍጹም ኃይሉ ከወደደና ባልንጀራውን ከወደደ የቃል ኪዳን ሕግ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ተሟላ ማለት ነው። በኦሪት ዘዳግም የእግዚአብሔር ሰዎች ከሁሉም ነገር በላይ በፍጹም ኃይላቸው እግዚአብሔርን እንዲወዱ ተጠርተዋል።
 2. በኦሪት ዘዳግም ውስጥ የሚገኘው በጣም አስፈላጊ የሆነ ሁለተኛ ዋና ርዕስ «መታዘዝ» ነው። በመጽሐፉ ውስጥ 10 ጊዜ ተጠቅሷል። መታዘዝ የፍቅር ውጤት (ፍሬ) ነው። አንድን ሰው ካልታዘዝነው እንወደዋለን ማለት አንችልም። እንዲሁም ከልብ ሳንታዘዘው እግዚአብሔርን እንወደዋለን ማለት አንችልም። ደግሞም እርስ በርስ የምንጎዳዳበትን ነገር እያደረግን እንዋደዳለን ማለት አንችልም። 
 3. ኦሪት ዘዳግም፥ የ«ሕግጋት» መጽሐፍ ነው። ብዙ ጊዜ ሕግን የጸጋ ተቃራኒ አድርገን እንመለከታለን። አይሁድ ግን የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን የሚያዩት የእግዚአብሔር የጸጋ ምልክት እንደሆነ አድርገው ነው፤ ምክንያቱም እነርሱ የሚኖሩት እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚያመልኩትና እርሱን ደስ የሚያሰኙበትንም መንገድ በማያውቁ አሕዛብ መካከል ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በጸጋው እንዴት እንደሚያመልኩና እንዴት መኖር እንዳለባቸው ለመግለጽ ለአይሁድ ሕግጋትን ሰጣቸው። ለአይሁድ ሕግ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። ከብርና ከወርቅ የሚሻል ከማርም ይልቅ የሚጣፍጥ ነው [መዝ. (119)፡10፤ (119)፡72]። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውን ፍቅር ራሱን በመግለጥና ሕግን በመስጠት አሳየ። ሕጉ በእነርሱ ዘንድ እንደ ሸክም የታየበት ጊዜ ጨርሶ አልነበረም። 

እግዚአብሔር ሕግን በመስጠት ረገድ የነበረው ዓላማ ሰዎች እንዲሁም ዝም ብለው ሥርዓቶችን እንዲታዘዙ ብቻ አልነበረም። ይልቁንም፥ ሰዎች ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር የሚያረጋገጥባቸው መንገዶች ነበሩ። ሰው በእግዚአብሔር ፊት በእውነተኛ የቅድስና ሕይወት እንዲኖር የሚመሩ ነበሩ። እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት እርስ በርስ በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ነበሩ። 

በአዲስ ኪዳን ጳውሎስ ሕግን አልተቃወመም፤ የተቃወመው አይሁድ ደኅንነታቸውን በሕግ ለማግኘት የነበራቸውን የተሳሳተ እምነት ነበር። ጳውሎስ እንዳለው «ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት» (ሮሜ 7፡12)። የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ስሕተት አልነበሩም፤ በተሳሳተ መንገድ ድነት (ደኅንነት) ለማግኘት የሕግጋት አጠቃቀማቸው ግን ስሕተት ነበር። 

ብዙ ክርስቲያኖች ዛሬ አይሁድ የሠሩትን ስሕተት ይደግማሉ። የዳኑት ሕግን በመጠበቅ ይመስላቸዋል፤ ደግሞም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙት በቂ ሕግጋትን በመጠበቅ እንደሆነ ይገምታሉ። ይህ አስተሳሰብ ስሕተት ነው። ይህ በክርስቶስ ወዳለ ነጻነት ሳይሆን፥ ወደ ባርነት የሚመራ ሐሰተኛ ወንጌል ነው። ለሕግ በመታዘዛችን ለእግዚአብሔር ፍቅር እንዳለን እንገልጻለን። 

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች የዳኑት አንዳንድ ድርጊቶችን በመፈጸም እንደሆነ ይመስላቸዋል። እስቲ ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) ሕግጋትን ወደሚጎዳ ነገር እንዴት ልንለውጣቸው እንችላለን?

 1. ሙሴ በኦሪት ዘዳግም ያተኮረበት ሌላ ነገር፡- አምልኮ በአንድ በተቀደሰ ቦታ በውስጠኛ ክፍል ብቻ መደረግ እንዳለበት ነው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ብዙ አማልክት እንደሌሉና በአንድ በተወሰነ ስፍራ ማለትም በመገናኛው ድንኳ የራሱን ሕልውና የገለጠ አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ገልጦላቸዋል፤ ስለዚህ ያንን እውነተኛ አምላክ በአንድ ስፍራ ብቻ ሊያመልኩ ይገባ ነበር። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የነበሩ አይሁዶች የአሕዛብን ልምምድ በመከተል በርካታ የተለያዩ አማልክትን በተለያየ ቦታ ለማምለክ ሊፈተኑ እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። የሚያሳዝነው ግን አይሁድ ይህንን የማስጠንቀቂያ ትእዛዝ ሳይከተሉ ስለቀሩ የጣዖት አምልኮ ለአይሁድ የሁልጊዜ ችግር ሆኖ ቀርቷል።

የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐ. 4፡21-24 አንብብ። ጌታ ኢየሱስ ለእውነተኛ አምልኮ መሠረቱ ምንድን ነው አለ በአንድ በተወሰነ ስፍራ ካማምለክ ጋር ያለውስ ግንኙነት ምንድን ነው?

 1. ሰው ሊታዘዝ ወይም ላይታዘዝ እግዚአብሔር ነጻ ምርጫ ሰጥቶታል። እግዚአብሔር ማንንም አስገድዶ እንዲታዘዝ ወይም እንዳይታዘዝ አያደርግም። ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ስለሆነ፥ የመምረጥ ነጻነት አለው፤ ነገር ግን ምርጫው የሚያስከትለውን ውጤት መከላከል አይችልም። የምርጫውን ውጤት የሚወስነው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ብንመርጥ ሕይወት ሊሰጠን ቃል ገብቶልናል፤ ተገቢውንም ሽልማት ይሰጠናል። አለመታዘዝን ከመረጥን ደግሞ እግዚአብሔር ይቀጣናል። ሰዎች ወይም መንግሥታት እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ ሲመርጡ በራሳቸው ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጣሉ። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ መመሪያዎች አንዱ ነው።
 2. እግዚአብሔር የታሪክ አምላክ ነው። ይህ እውነተኛ ታሪክ በትምህርት ቤት እንደተማርነው ዓይነት አይደለም፤ የድርጊቶች ቅደም ተከተል ብቻ አይደለም። ኦሪት ዘዳግም የሚያስተምረን እግዚአብሔር ታሪክን የሚቆጣጠርና የሚወስን መሆኑን ነው። ታሪክ፥ እግዚአብሔር ዓላማውን በዓለም ላይ ለመፈጸም እንዴት እየሠራ እንዳለ የሚናገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ታሪክን እንዴት እንደተቆጣጠረና ተጽዕኖ እንዳደረገበት እንመለከታለን። እግዚአብሔር በዙሪያችን ያለውን ነገር እንዴት እንደሚቆጣጠር ባይገልጽልንም እንኳ ድርጊቶችን በሙሉ እስካሁን ድረስ እየተቆጣጠረ እንደሆነ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለ፤ ዓላማውንም ተግባራዊ በማድረግ እየፈጸመ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን እውነቶች ልናውቃቸውና ልናስታውሳቸው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ኦሪት ዘዳግም ከአዲስ ኪዳንና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለው ዝምድና፡-

 1. ፔንታቱክ ብለን ከምንጠራቸው ከመጀመሪያዎቹ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት አዲስ ኪዳን ብዙ ጊዜ የሚጠቅሰው ከኦሪት ዘዳግም ነው። ጌታ ኢየሱስ በምድረ በዳ በተፈተነ ጊዜ፥ የሰይጣንን ፈተና ለማሸነፍ ከኦሪት ዘዳግም ውስጥ ጠቅሷል፤ (ማቴ. 4፡4፥7፥10 ተመልከት)። ይህን መጽሐፍ ብዙ ባንጠቀምበትም፥ በአይሁድና በቀደምት ክርስቲያኖች አምልኮ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበረውና ጠቃሚ ሚና የተጫወተ መጽሐፍ ነው።
 2. በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ስለ ክርስቶስ የተነገረ ድብቅ ትንቢት ነበር፤ (ዘዳግ. 18፡15-18 ተመልከት)። ይህ ጥቅስ የሚናገረው፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በተለያዩ ዘመናት ውስጥ የተለያዩ ነቢያትን እንደሚያስነሣ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር የእርሱን መልእክት ለእስራኤል ሕዝብ የሚናገር አንድ ልዩ ነቢይ እንደሚያስነሣ የተነገረም ትንቢት ነው። በአዲስ ኪዳን የነበሩ አይሁድ ይህንን ነቢይ ሲጠብቁ ነበር (ዮሐ. 1፡21፣ 25፣ 45፤ የሐዋ 7፡37 ተመልከት)። ነገር ግን መሢሑና ነቢዩ አንድ ሰው እንደሚሆን አልተገነዘቡም ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መሢሑም ስለ ነቢዩም የተነገረውን ትንቢት ፈጸመው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘዳግም 12-26

ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚገደው ለእርሱ ስላለን አምልኮ ብቻ ነው ይላሉ። በአእምሮአቸው «መንፈሳዊ» የሆነውን ነገር «ሥጋዊ» ከሆነ ነገር ይለያያሉ። እግዚአብሔር ግን ይህንን ልዩነት አላደረገም። እንዲያውም የምናደርጋቸው ነገሮች በሙሉ በእግዚአብሔር ዓይን መንፈሳዊ ናቸው። በ1ኛ ቆሮ.10፡31 ጳውሎስ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ፥ ወይም ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ይላል። ስለዚህ እግዚአብሔር ግድ የሚለው አምልኮአችን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ስላለን ግንኙነትም ነው። ከማያምኑ ጋር ባለንም ግንኙነት ደስ ይለዋል። እግዚአብሔር እንዴት እንደምንሠራና እንደምናስተዳድር ያያል። እግዚአብሔርን የማይመለከተውና መመሪያ ያልሰጠበት አንዳችም የሕይወት ክፍል የለም። በኦሪት ዘዳም፥ ስለ አምልኮና ስለ ሃይማኖታዊ በዓላት የተሰጡ ሕግጋትን እናገኛለን። ስለ ንግድ፣ ጋብቻ፣ ምግብ፣ ከምድር ስለሚገኝ ፍሬ፥ ስለ ቤተሰብ ሕይወት፥ ወደ ጦርነት ስለ መሄድ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስለ መምራት ወዘተ የሚናገሩ ሕግጋትንም እናገኛለን። እኛ ግን ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያከብር ወይም የማያከብር ነገር እናደርጋለን፤ ልዩነቱ የሚመነጨው በውስጣችን ካለው ስሜታችን ነው። አንድ ነገር በእግዚአብሔር ተቀባይነት እንዲያገኝ ከተፈለገ ድርጊት ብቻ ሳይሆን የድርጊቱ ዓላማም ጭምር በእግዚአብሔር ፊት የተስተካከለ መሆን ይኖርበታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ጊዜ የምናደርጋቸውና እግዚአብሔር አያገባውም የምንላቸው የተለመዱ ነገሮችን ዘርዝር። ለ) እነዚህ ነገሮች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት ሊደረጉ እንደሚችሉ መግለጫ ስጥ። ሐ) ለእግዚአብሔር ክብር በማያመጣ መንገድም እንዴት ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ምሳሌዎችን ስጥ። 

የዉይይት ጥያቄ፥ ዘዳግ. 12-26 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር መመሪያ የሚሰጥባቸውን የተለያዩ የሕይወት እንቅስቃሴዎችን ከእነዚህ ትእዛዛት አንዳንዶቹን ዛሬም እንዴት ከሕይወታችን ጋር እንደምናዛምድ ምሳሌ ሰጥ።

እነዚህን ትእዛዛት ለማብራራት ጊዜ አንወስድም። ነገር ግን ያልተረዳሃቸው አንዳንድ ቢኖሩ፥ ዝርዝራቸውን ጻፍና በሳምንታዊው የስብሰባ ወቅት ከቡድን አባላት ጋር ተወያይባቸው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘዳግም 1-11

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በምድራችንም ሆነ በዓለም ላይ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ማወቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ባለፉት 20 ዓመታት የተፈጸመውን የቤተ ክርስቲያንህን ታሪክ በአጭሩ ጻፍ። ሐ) የተፈጸሙት መልካምና ክፉ ነገሮች ምንድን ናቸው? መ) የቤተ ክርስቲያንህን ታሪክ ማወቅ ማድረግ ስለሚገባህ ነገርና መውሰድ ስላለብህ ጥንቃቄ ለማስገንዘብ እንዴት ይረዳሃል?

ታሪክን፥ በተለይም ደግሞ የአብያተ ክርስቲያኖቻችንን ታሪክ ማወቅ ለሁላችንም ቢሆን በጣም ጠቃሚ ነው። ታሪክ ከታላላቅ መምህራኖቻችን አንዱ ነው። ታሪክ በተከታታይ ድርጊቶች ላይ የተመሠረተና የተቀናጀ ነው። እነዚህ ድርጊቶችና ለድርጊቶች መፈጸም ምክንያት የሆኑ ነገሮች መልካም አስተማሪዎች ናቸው። ለምሳሌ በእኛ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ መልካም ነገሮች አሉ፤ ለሌሎች ወንጌልን የመንገር መልካም መንገዶች ታይተዋል፤ እነዚህ ነገሮች ዛሬም ለሌሎች ወንጌልን ለመናገር መመሪያ ሊሆን የሚችሉ መልካም ተግባራት ናቸው፤ ነገር ግን በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት አሳዛኝ የሆኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። የሐሰት ትምህርቶች ተስፋፍተዋል፤ በመሪዎች መካከል ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍሉ ልዩነቶች ወዘተ. ታይተዋል። እነዚህን ነገሮች ልንመረምርና ምክንያታቸውን ልንረዳ፥ እንዳይደገምም ልንጠነቀቅ ወይም ልናሻሽላቸው ይገባል። አንድ ሰው እንደተናገረው፡- ታሪካችንን በተለይም ስሕተታችንን የማናውቅ ከሆነ ስሕተቶቻችንን መደጋገማችን አይቀርም። በየቤተ ክርስቲያኖቻችን የሚፈጸሙ ነገሮችን ሁልጊዜ መመርመር አለብን። መልካም ናቸውን? ለቤተ ክርስቲያንና ለወንጌል መስፋፋት ሥራ ወሳኝ ናቸው? እስካሁን እያደረግን ባለነው ነገር ልናሻሽላቸው የሚገቡ ነገሮች ወይም የምናደርጋቸው ነገሮች በተሻለ መንገድ ለማካሄድ እያደረግን ያለው ጥረት ምንድን ነው? እንዳይጠፉ ወይም እንዳይበላሹ ልንጠነቀቅላቸው የሚገቡ፥ ለቤተ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ምንድን ናቸው? በማለት እየጠየቅን ተገቢውን ነገር ከታሪክ መማር አለብን። ያለፈውን ነገር ብቻ በማውሳት የታሪክ ባሪያዎች መሆን የለብንም፤ ነገር ግን ታሪካችንን ለጊዚያችን በሚስማማ መንገድ ለእግዚአብሔር ከሁሉ የላቀ ክብርን እንዲያመጣ ልንጠቀምበት ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ከቤተ ክርስቲያንህ ነባር አባሎች መካከል ለአንዱ ቃለ መጠይቅ አድርግ። ቁልፍ የሆኑ የቤተ ክርስቲያንህን የቀድሞ ታሪኮች ጻፍ። ለ) የቤተ ክርስቲያናችንን የቀድሞ ታሪክ ማወቅ ለአሁኑ ዘመን የሚጠቅመው እንዴት ነው? ) ቤተ ክርስቲያን አባሎችዋ ታሪኳን እንዲያውቁና እንዲመዘግቡ ምን ማድረግ አለባት? 

አብዛኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል ታሪክ ነው። እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ የሚረዳ ታሪክ ነው። እግዚአብሔር በእነርሱ ወገን ሆኖ ሲሠራ ታላቅ ኃይል ያለው መሆኑን ለእስራኤላውያን የሚያስታውስ ታሪክ ነበር። አባቶቻቸው እንዳደረጉት በኃጢአት እንዳይወድቁ፥ ስለ መንፈሳዊ ውድቀት ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ማስጠንቀቂያም ነው። የአይሁድ ባሕልና ታሪክ ከእኛ የተለየ ቢሆንም፥ እግዚአእብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መመላለስ እንደሚቻል ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መማር እንችላለን።

አይሁድ ታሪክን መረዳት እንዳለባቸው ሙሴ ተገነዘበ፡፡ ስለዚህ ሕጉን ለሚቀጥለው ትውልድ መድገም ከመጀመሩ በፊት፥ የእስራኤል ሕዝብ ከግብፅ ከወጡ በኋላ ስላሳለፉት ነገር አጠር ያለ ታሪክ አቀረበ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዘዳግ.1-11 አንብብ። ሀ) ሙሴ ለእስራኤላውያን ያስታወሳቸውን ዋና ዋና ታሪካዊ ድርጊቶች ዘርዝር፡ ለ) ሙሴ ስለ እግዚአብሔር በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሚያስተምረን ነገር ምንድነው? ሐ) በዚህ ክፍል የቀረቡትን ዋና ዋና ትእዛዛትና ከሕይወታችን ጋር እንዴት እንደሚዛመድም ጥቀስ። በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ስብከት መስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ጥቅሶችና መንፈሳዊ መመሪያዎች ያሉባቸውን ዋና ዋና ክፍሎች ዘርዝር።

ሙሴና የእስራኤል ሕዝብ በተስፋይቱ ምድር ትይዩ በሞዓብ ሜዳማ ስፍራዎች ሰፈሩ። ሙሴ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገቡበትና ወረራ በማካሄድ የሚይዙበት ጊዜ አሁን መሆኑን አውቆ ነበር። ወደ ከነዓን ከመግባታቸው በፊት ግን ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ቃል ኪዳን ለአዲሱ የእስራኤል ትውልድ በማስታወስ ቃል ኪዳኑን እንደገና ሊያጸና ፈለገ። ኦሪት ዘዳግም በዚህ ቃል ኪዳን ሁለተኛው የእስራኤል ትውልድና ከእግዚአብሔር ጋር የተሳሰሩበት ታሪክ የተመዘገበበት መጽሐፍ ነው።

 1. የእስራኤል ታሪክ (ዘዳ.1-3)

ለቃል ኪዳኑ መግቢያ ይሆን ዘንድ ሙሴ ያለፈው 40 ዓመት ታሪካቸውን ለእስራኤል ሕዝብ ያስታውሳቸዋል። እግዚአብሔር ከግብፅ እንዴት እንዳወጣቸው በዓይናቸው ያዩና መመስከር የሚችሉ ሦስት ሰዎች ብቻ አሁን በሕይወት ይገኙ ነበር። እነርሱም ሙሴ፥ ኢያሱና ካሌብ ነበሩ። አዲሱ ትውልድ ያለፈውን ታሪካቸውን የመርሳት አደጋ ያሠጋቸው ነበር፤ ስለዚህ ሕዝቡ በእምነትና በታዛዥነት በእግዚአብሔር ፊት ይመላለሱ ዘንድ፥ ለማበረታታት ሙሴ የ40 ዓመት ታሪካቸውን የሚመለከቱበትን ቁልፍ አሳቦች ይነግራቸዋል።

በኦሪት ዘዳግም ውስጥ የሲና ተራራ ብዙ ጊዜ የኮሬብ ተራራ በመባል ይታወቃል። በዚህ ክፍል የተጠቀሱ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

ሀ. የእስራኤልን ሕዝብ በመምራት ሥራ ውስጥ ያግዙት ዘንድ ሙሴ መሪዎቹን ሾመ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዘዳ.1፡16-18 አንብብ። ሀ) በዚህ ስፍራ የተሰጡት መመሪያዎች ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይከተሉአቸው ዘንድ ጠቃሚነታቸው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን መመሪያዎች የማይጠቀሙባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

ለ. 12ቱ ሰላዮች የተስፋይቱን ምድር አይተው እንዲመለሱ ተልከው ነበር። እስራኤል ግን በእግዚአብሔር መታመንና ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት እምቢ አለች።

ሐ. የእስራኤላውያን በምድረ በዳ መንከራተት፥ 

መ. ሴዎንና ዐግ ዖግ የተባሉት ሁለት የከነዓናውያን ነገሥታት መሸነፍና የእስራኤላውያን ምድሪቱን መከፋፈል። 

 1. እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ መሠረት የሚሆኑ የዋና ዋና ሕግጋት መግቢያ (ዘዳግ.4-11)

በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ስድስት ዋና ዋና ትምህርቶችን ተመልከት፡-

ሀ. ከእግዚአብሔር የሆነ በረከትና እውነተኛ ጥበብ ለእርሱ ፍጹም በመታዘዝ ይገኛሉ። 

ለ. በከነዓን ምድር የተለመደውን የጣዖት አምልኮ እንዳይለማመዱ ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። «እግዚአብሔር የሚባላ እሳት» ስለሆነ ይህ በእስራኤላውያን ላይ ፍርድን ያመጣል። እግዚአብሔር የፍቅርና የጸጋ አምላክ ስለሆነ፥ እንደ ቀላል ቆጥረን ኃጢአት ብናደርግም አይፈርድብንም ብለን ልናስብ አይገባንም።

እግዚአብሔር ሊፈራም ሊወደድም ይገባል። እግዚአብሔር ብቻውን እውነተኛ አምላክ ስለሆኝ፥ እርሱን ብቻ ያመልኩ ዘንድ እስራኤላውያን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር «የሚባላ እሳት» መሆኑን የምንረሳውና ስለ ቅጣት ሳናስብ ቀርተን እርሱን የማንታዘዘው እንዴት ነው?

ሐ. የሕግጋት ሁሉ መሠረት የሆኑት አሥርቱ ትእዛዛት እንደገና መቅረብ። 

መ. ለእግዚአብሔር የመታዘዝ ትክክለኛው ምክንያት ለእርሱ ያለን ፍቅር መሆን አለበት። በሁለንተናቸው እግዚአብሔርን መውደድ ነበረባቸው። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እርስ በርስ መማማርና ልጆቻቸውንም ማስተማር እንዳለባቸው እርግጠኞች መሆን ነበረባቸው። ሙሴ የእግዚአብሔርን በረከት ከተቀበሉና መማማርና በቤቶች መኖር ከጀመሩ በኋላ እግዚአብሔርን እንዳይዘነጉ አስጠንቅቋቸዋል (ዘዳግ. 6፡10-12 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፡- ከስደትና ከችግር ጊዜ ይልቅ በሰላምና በብልጽግና (ዘመን እግዚአብሔርን ማስታወስስ የሚከብደው ለምንድን ነው?

ሠ. ከእግዚአብሔር መንገድ ዞር እንዳያደርጉአቸው በከነዓን ምድር የሚኖሩትን አሕዛብ ሁሉ ማጥፋት ነበረባቸው።

ረ. እውነተኛ ታዛዥነት ሕግን በውጫዊ መንገድ መከተል ብቻ ሳይሆን የልብ መለወጥንም ያካትታል። ሥጋዊ የአካል ክፍላቸውን (ሸለፈታቸውን) ብቻ ሳይሆን፥ ልባቸውንም መግረዝ ነበረባቸው። መታዛዝ የሚጀምረው እግዚአብሔርን ከመፍራት፥ በመንገዱ ለመሄድ ከመወሰን፥ ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ መታዘዝ ከሚመራቸው በልባቸው ከሚኖር ፍቅር ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) ዛሬ ልባችን እንዴት እንደተገረዘና በፍጹም ልባችን እርሱን እንደወደድነው ማሳየት የምንችልበትን ምሳሌዎች ስጥ። ለ) በሁለንተናችን እግዚአብሔርን እንዴት መውደድ እንችላለን? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ ዓላማ 

. በኦሪት ዘዳግም፣ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል በሲና ተራራ ተደርጎ የነበረው የቃል ኪዳን ስምምነት እንደገና ተደገመና ሕጋዊ ሆነ። እንደምታስታውሰው በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ራሱን በገለጠበትና የሲና ተራራ ቃል ኪዳን በሰጠበት ጊዜ የነበሩ በዕድሜ ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በምድረ በዳ አልቀዋል። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ያወጣበትና በዓይናቸው ያዩትን የግል ምስክርነት መስጠት የሚችሉ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሦስት ሰዎች ብቻ ነበሩ። እነርሱም ሙሴ፥ ኢያሱና ካሌብ ነበሩ። አሁን የእነርሱን ስፍራ ለመረከብ አዲስ ትውልድ ተነሥቷል። እነዚህ በሲና ተራራ ቃል ኪዳን ለመስማት በቦታው አልነበሩም! ስለዚህ ወደ ከነዓን ከመግባታቸው በፊት ሙሴ የቃል ኪዳኑን ስምምነት ደገመላቸውና እግዚአብሔር በሲና ተራራ በሰጠው የቃል ኪዳን ስምምነት (ቅድመ ሁኔታዎች) ላይ ተመሥርተ አስፋፋው።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) እያንዳንዱ ትውልድ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ማንነት በሙሉ ሊረዳና ከግል ሕይወቱም ጋር ሊያዛምድ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸው ክርስቲያኖች ስለሆኑ ብቻ እነርሱም ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚያስቡት ለምንድን ነው? ይህ አስተሳሰብ ስሕተተ የሆነው ለምንድን ነው? መ) እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ ወንጌልን በሙላት እንዲረዳና እምነቱን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ግላዊ ግንኙነት እንዲኖረው ለመርዳት ቤተ ክርስቲያንህ ምን ማድረግ ትችላለች?

. ሙሴ አሪት ዘዳግምን የጻፈው፥ የእስራኤል አዲስ ትውልድና የሚቀጥለው ትውልድ ቃል ኪዳን የሚጠይቀውን ቅድመ-ሁኔታ እንዲያሟላ ከልብ ለማደፋፈር ነው፤ ነገር ግን ሳይታሰብ በቃል ኪዳኑ ላይ ውስጣዊ ያልሆነ መታዘዝ እንዲደረግ አልወደደም ነበር። ሙሴ በቃል ኪዳኑ መሠረት ላይ ሁለት ዋና ዋና ትእዛዛት እንደነበሩ አስተውሎ ነበር። የመጀመሪያው፥ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ የመውደድ፥ የማክበርና የመታዘዝ ነገር መኖሩ ነው (ዘዳግ. 6፡4-9፤ 10፡12-13)። ሁለተኛ ደገሞ፥ ባልንጀራን የማክበር፥ ተገቢውን ስፍራ የመስጠትና የመውደድ ትእዛዝ መሆኑ ነው፥(ዘሌ. 19፡18)። እስራኤላውያንና ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ እንደ መሆናቸው መጠን ተገቢውን ዝምድናን ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር ጋር ሕያው የሆነ የመታዘዝ፣ እርስ በርስ የመፈቃቀድ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግ።10፡12-13 በቃልህ አጥና። እግዚአብሔርን መፍራት፥ በመንገዱ መራመድና በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ እርሱን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ባልንጀሮቻችንን በምንወድበት ጊዜ ከትእዛዛቱ አብዛኛውን የምንጠብቀው እንዴት ነው?

. ከዚህ ቀደም እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያደረገው የቃል ኪዳን መሠረት እግዚአብሔር በሁለት ጽላቶች ላይ ጽፎ ለሙሴ የሰጠው አሥርቱ ትእዛዛት እንደነበር ተመልክተናል። አሁንም ደግሞ በኦሪት ዘዳግም እነዚህን አሥር ትእዛዛት ከአይሁዶች አጠቃላይ ሕይወት ጋር ያላቸውን ዝምድና በግልጥ በሚያሳይ መንገድ አስፋፍቶ ያቀርባቸዋል። አንዳንዱ ምሁራን ሙሴ ይህንን መጽሐፍ ያዘጋጀው በአሥርቱ ትእዛዛት ዙሪያ ነው ይላሉ። በዚህ መሠረት ኦሪት ዘዳግምን የሚያብራሩት እንደሚከተለው ነው፡

 1. 1ኛ ትእዛዝ፡- ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። 

ሙሴ ይህንን ትእዛዝ ከኦሪት ዘዳግም 6-11 ባለው ክፍል ውስጥ አብራርቶታል። የእነዚህ ምዕራፎች ትኩረት እግዚአብሔር ፈጣሪ በመሆኑና እስራኤልን ከሌሎች አሕዛብ ለይቶ በመምረጡ ባለው መለኮታዊ ሥልጣን ላይ ነው፤ ስለዚህ እስራኤል ሌሎች አማልክትን ሳይሆን እግዚአብሔርን ልታከብርና እርሱን ብቻ ልታመልክ ይገባት ነበር። ትኩረቱ እግዚአብሔርን በመውደድና በመታዘዝ ላይ ነው። የእስራኤላውያን ተቀዳሚ ምርጫ እግዚአብሔርን ማምለክ ሲሆን እርሱ በሕይወታቸው ሁሉ ላይ የመጨረሻ ባለሥልጣን መሆን ነበረበት።

የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) እግዚአብሔር ከእያንዳንችን ስለሚፈልገው ነገር ከላይ የምናየው የመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ምንን ያመልክተናል? ለ) ይህ በሕይወትህ የታየው እንዴት ነው?

 1. 2ኛ ትእዛዝ፡- የተቀረፀ ምስል ለአንተ አታድርግ (ዘዳ. 12)። 

ይህንን ትእዛዝ በጥሩ ሁኔታ ለመረዳት አማልክቶቻቸውን የሚወክሉ በርካታ የተቀረፀ ምስል ካሉአቸው ከከነዓናውያን ጋር በማነጻጸር ማየት የተሻለ ነው። እስራኤላውያን የከነዓናውያንን ልምድ ከመከተል ይልቅ ከፍተኛ ክብር እንዳለው በማወቅ ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት ነበረባቸው። እውነተኛውን የእግዚአብሔር ባሕርይ በማወቅ እርሱን ሊያከብሩ ይገባ ነበር። እግዚአብሔር መንፈስ ሰለሆነ በሥዕል ወይም በተቀረፀ ምስል ሊሳል አይገባውም፡፡ የዘለዓለማዊዉን አምላካዊ ታላቅነትን ስለማያንጸባር፥ እግዚአብሐርን ግኡዝ በሆነ መንገድ ለመግለጥ መሞከር እርሱን መስደብ ነው። እንደ ከነዓናውያን አማልክት ከእርሱ የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት በጥቃቅን መሥዋዕት የሚሸነገል አይደለም። የአምላኪውን ሰው የግል ፍላጎት ለማርካት የሚጠቅም ሊሆንም አይችልም። ይልቁንም እርሱ ሉዓላዊና ሁሉን የሚችል አምላክ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር አንድን ነገር ለመስጠት ወይም አንድ ነገር እንደሚያደርጉለት ቃል በመግባት ወዘተ. ከእርሱ አንድ ነገር ለማግኘት የመሸንገል ሙከራ የሚያደርጉት እንዴት ነው? ) አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በፍቅር ከማገልገል ይልቅ፣ የግል ጥቅምን ከመፈለግ አንጻር ብቻ የሚያገለግሉት እንዴት ነው? ሐ) አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርn በፍቅር ከማገልገል ይልቅ የበለጠ እርሱ ስለሰጠህ ነገር ብቻ የምታገለግለው እንዴት እንደነበር ምሳሌ ስጥ። መ) ይህ ለሕተት የሆነው ለምንድን ነው?

 1. 3ኛ ትእዛዝ፡- የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ (ዘዳ. 13፡1-14፡21)። 

ይህ ክፍል የሚገልጸው እግዚአብሔርን በሕይወታቸው ሙሉ በተለይ ደግሞ በከንፈሮቻቸው የማክበርና ራሳቸውን አሳልፈው ስለ መስጠት አስፈላጊነት ነው። እስራኤላውያን ስለ እነዚህ ነገሮች እርግጠኞች ለመሆን፡- ሀ) ለእግዚአብሔር ያላቸውን አምልኮ ንጽሕናን መጠበቅ፥ ለ) ኃጢአትን እንደመጥላታቸው፣ በመካከላቸው በሚከሰትበት ጊዜ መፍረድ፥ እንዲሁም ሐ) ንጽሕናቸውን ሊያጓድል የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ በማስወገድ የተቀደሰ ሕይወት መምራት ነበረባቸው።

 1. 4ኛ ትእዛዝ፡- የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ (ዘጻ. 14፡22-16፡17)። 

ይህ ክፍል በእግዚአብሔር ማንነት ምክንያት ለእርሱ በሚገባው ክብር ላይ የሚያተኮር ነው። የእግዚአብሔርን የመፍጠር ሥራ የሚያስታውስ ስለሆነ እግዚአብሔር በሰንበት ቀን ሊመለክ ይገባዋል (ዘዳግ. 20፡11)። በተጨማሪ እርሱ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት እንዴት ነጻ እንዳወጣ ያሳስበናል (ዘዳግ. 5፡15)። እግዚአብሔር የመልካም ነገሮች ሁሉና የእስራኤላውያን ነጻነት ምንጭ ስለሆነ፥ ለእርሱና የእርሱም ቤተሰብ ለሆኑት ሁሉ እግዚአብሔር ከሰጣቸው ነገር በመስጠት ሊያከብሩት ይገባ ነበር። 

 1. 5ኛ ትእዛዝ፡- አባትና እናትህን አክብር (ዘዳግ. 16፡18-18፡22)። 

እንደምታስታውሰው፥ከ1-4 ያሉት ትእዛዛት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት የሚናገሩ ሲሆን፥ ከ5-10 ያሉት ደግሞ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር ስላለው ኅብረት የሚናገሩ ናቸው። እግዚአብሔር ግድ የሚለው አንድ ዓይነት የሥልጣን ተዋረድ ስለሚከተለው ከወላጆቻችን ጋር ስላለን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፥ በተለያየ ሥልጣን ላይ ስላሉት ሁሉ ነው። በብሉይ ኪዳን ዋና ዋና የሆኑ አራት ዓይነት መሪዎች ነበሩ። ነቢያት የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ የማድረስ ኃላፊነት ነበረባቸው። ካህናት የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ለሰዎች የማስተማር ኃላፊነት ነበረባቸው። ነገሥታት በእግዚአብሔር ትእዛዛት ላይ የተመሠረተ የጽድቅ መንግሥት የማዋቀር ኃላፊነት የነበረባቸው ሲሆን፥ መሳፍንት ደግሞ እግዚአብሔርና ነገሥታት ለመሠረቱት የአኗናር ስልት ሕዝቡ መታዘዛቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ነበረባቸው። እነዚህ ሁሉ መሪዎች መሠረታዊ ዓላማና ክብር ሊሰጣቸው የሚያስፈልበት ምክንያት፥ ከወላጆች ጭምር ሕዝቡ በሙሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲማሩና ለእግዚአብሔር እየታዘዙ በመኖር እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ ለማደፋፈር ነበር። 

 1. 6ኛ-8ኛ ትእዛዛት፡፡

6ኛ-8ኛ ትእዛዛት የሚያተኩሩት በሦስት የሕይወት ክፍሎች ላይ ነው፡- ሀ) ሰውን በመግደል ለ) በማመንዘርና ሐ) በመስረቅ። እነዚህ በ 19-24፡7ድረስ ተብራርተው ቀርበዋል። 

ሀ) የእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ስለሆነ መከበርና ከአደጋ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ የአንድን ሰው ሕይወት በግድየለሽነት ማጥፋት ስሕተት ነው። በወንጀሉ ምክንያት መንግሥት በአንድ ሰው ላይ ሞት ቢፈርድ ወይም ጦርነት በማስነሣቱ ምክንያት ቢገደል የተከለከለ አይደለም። 

ለ) ጋብቻ ሕይወትን በአንድነት የመካፈል መሠረት ስለሆነ፥ እስራኤላውያን የጋብቻን ቅድስና በጋብቻ ውስጥ በታማኝነት በመኖር መጠበቅ ይኖርባቸው ነበር። ነገር ግን ይህ አሳብ እርስ በርስ መጎዳዳትን፥ ሰላምን አንድነትን የሚያበላሹ ነገሮች ሁሉ መፈጸም የለባቸውም በሚለው አሳብ ተጠቃሎ እናየዋለን።

ሐ) ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ክብር ያላቸው ፍጥረቶች እንደመሆናቸው መጠን፣ የሰውን ክብር ወይም ዋጋ የሚነካ ማንኛውም ነገር መፈጸም የለበትም። ይህም መስረቅ ማለት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪ በባርነት መልክ ሰውን የመሰል ፍጡር ነጻነቱን መግፈፍ ተገቢ አይደለም። 

 1. 9ኛ ትእዛዝ፡- በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር (ዘዳግ. 24፡8-16)። 

መዋሸት ወይም በሐሰት መመስከር በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ላለው ግንኙነት ሁሉ መሠረት መሆን ያለበትን ነገር ማጥፋት ወይም ማበላሸት ነው። በእውነተኛነት ላይ የሚመሠረተውን መተማመን ያጠፋል። በሰዎች መካከል ያለውን እውነተኛነትና መተማመን የሚያጠፋ ነገር ሁሉ እንዳይደረግ ተከልክሏል። 

 1. 10ኛ ትእዛዝ፡- አትመኝ (ዘዳግ. 24፡17-26፡15)። 

መመኘት ማለት የሌላውን ሰው ንብረት የራስ ለማድረግ መፈለግ ማለት ነው። መመኘት የብዙ ኃጢአቶች መንስዔ ነው። የሌላውን ሰው መብት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ወደ መጠቀም ይመራል። የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን ግን እንደ እግዚአብሔር ሕዝብነታቸው፥ በኅብረታቸው ውስጥ ቅን ፍርድን በመፈለግ፥ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሠራተኞቻቸው፥ እንዲሁም ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔርን በሚያከብር መንገድ ከሌሎች ጋር ግንኙነት ስለ ማድረግ፥ ከእነዚህ አራት የመጨረሻ ነጥቦች ምን መማር እንችላለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘዳግም መግቢያ

በፔንታቱክ መጻሕፍት ጥናታችን፥ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን መሠረታቸው ከሆነው ከአብርሃም ጀምሮ፥ ታላቅ ሕዝብ ወደ መሆን እስከ ደረሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን ነገር ተመልክተናል። እግዚአብሔር በጸጋው ይህንን ታላቅ ሕዝብ በባርነትና በምድረ በዳም እያለ ተጠንቅቆ የመራበትን ኃይሉን መስከረናል። እግዚአብሔር ባመፁበት ሕዝብ ላይ የፈረደባቸው ቢሆንም፥ በምሕረቱ ለሕዝቡ እየተጠነቀቀ እስከ ተስፋይቱ ምድር ጫፍ ድረስ መርቶአቸዋል። ሙሴ የመጨረሻዎቹን ቃሎቹን ለአዲሱ የእስራኤላውያን ትውልድ የተናገረው በዚህ በተስፋይቱ ምድር ጫፍ ላይ ነበር። እነዚህ የመጨረሻዎቹ የሙሴ ቃሎች በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ይገኛሉ። ከዚያም ሙሴ የተስፋይቱን ምድር ከሩቅ አሻግሮ አይተ ሞተ።

የኦሪት ዘዳግም ርዕስ 

በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ፥ ከፔንታቱክ መጻሕፍት መካከል የአምስተኛው መጽሐፍ ርዕስ ኦሪት ዘዳግም ይባላል። ይህ ስም ከሴፕቱዋጀንት የተገኝ ሲሆን ትርጉሙም «ሁለተኛ ሕግ» ወይም «የሕግ ድግግሞሽ» ማለት ነው። ይህ ስም የሚያንፀባርቀው የኦሪት ዘዳግም አብዛኛው ክፍል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በሲና ተራራ የሰጣቸው ሕግ የተደገመበትና ተስፋፍቶ የቀረበበት መሆኑን ነው።

አይሁድ ይህንን መጽሐፍ በኦሪት ዘዳግም መጀመሪያ ቁጥር ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን ቃላት በመውሰድ «ቃሉቹ እነዚህ ናቸው» የሚል ርዕስ ሰጥተውታል።

የኦሪት ዘዳግም ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፥ የኦሪት ዘዳግም ጸሐፊ ማን እነደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። 

በዘመናት ሁሉ አይሁድም ሆኑ ክርስቲያኖች የኦሪት ዘዳግም ጸሐሪ ሙሴ እንደሆነ ይስማሙ ነበር። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን ሰዎች ይህንን በሁለት ምክንያቶች በመጠራጠር ጥያቄ ማንሣት ጀምረዋል። አንደኛ፥ ሙሴ በአንድ በተቀደሰ ስፍራ የማምለክን አስፈላጊነት በሚመለከት ትኩረት ሰጥቶ ይናገራል፤ ይህ ግን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እስከ ንጉሥ ኢዮስያስና ሕዝቅያስ ድረስ በተግባር አልታየም። ሁለተኛ ሙሴ በእስራኤል ንጉሥ ያለ ይመስል፥ ስለ ነገሥታት ይናገራል ስለዚህ ኦሪት ዘዳግም የተጻፈው ነገሥታት እስራኤልን መግዛት ከጀመሩ በኋላ መሆን አለበት ይላሉ።

ሆኖም ግን ኦሪት ዘዳግም እነርሱ እንደሚሉት ቆይቶ የተጻፈ መሆኑን ይህ አያረጋግጥም። ሙሴ በተለያዩ ስፍራዎች የሚደረግ አምልኮ የሚያመጣውን ችግርና እስራኤልም በዙሪያዋ እንዳሉ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ንጉሥ መፈለጓን አስቀድሞ በመገንዘብ ነገሥታቱን በሚመለከት መመሪያ መስጠቱንና በአንድ ስፍራ ማምለክን አስፈላጊነት መናገሩን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ዘዳግም ውስጥ ጸሐፊው ሙሴ እንደሆን የተጠቀሱ ነገሮች አሉ (ዘዳግ. 1፡5፤31፡9፥22፥24)። በቀሩት ቅዱሳት መጻሕፍት የኦሪት ዘዳግም ጸሐፊ ሙሴ መሆኑ ተናግሯል (ለምሳሌ ፡- 1ኛ ነገ. 2፡3፤ 8፡53)። ሆኖም ግን፥ አብዛኛውን የመጽሐፉን ክፍል ሙሴ ነው የጻፈው የሚለው አሳብ እንደተጠበቀው ሆኖ፥ መጽሐፉን ያቀነባበረው ሰው ከሙሴ ሞት በኋላ አንዳንዱን ነገር በመጨመር አጠናክሮት ሊሆን ይችላል (ዘዳ. 1-5፤ምዕራፍ 34)።

ኦሪት ዘዳግም የተጻፈው፥ አይሁድ በምድር በዳ መንከራተታቸው አብቅቶ ወደ ከነዓን ምድር ከመግባታቸው በፊት ነው፤ ይህም በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ መሆኑ ነው። 

የኦሪት ዘዳግም አስተዋጽኦ 

ኦሪት ዘዳግም ሁሉንም ዓይነት ሁኔታ የሚጨምሩ የተለያዩ በርካታ ሕግጋት ያሉት በመሆኑ መጽሐፉን በአስተዋጽኦው ከፋፍሎ ማቅረቡ አስቸጋሪ ነው። ቀላሉ መንገድ ኦሪት ዘዳግምን በሙሴ ሦስት ዋና ዋና ስብከቶች ዙሪያ ማደራጀት ነው።

 1. የሙሴ የመጀመሪያ ስብከት (ዘዳግም 1፡1-4፡43) 
 2. የሙሴ ሁለተኛው ስብከት (ዘዳግ. 4፡44-28፡68) 
 3. የሙሴ ሦስተኛው ስብከት (ዘዳግ. 29-33) 
 4. የሙሴ ሞት (ዘዳግ. 34)

ሆኖም ኦሪት ዘዳግም ሊደራጅ የሚችልበት የመጽሐፉን ባሕርይ የሚያመለክት ሌላ መንገድ አለ። ብዙ ምሁራን ኦሪት ዘዳግምን የሚያዩት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ያለ ሰነድ ወይም ቃል ኪዳን አድርገው ነው።

ቀደም ሲል እንዳየነው እግዚአብሔር ሕግን በሲና ተራራ በሰጠበት ጊዜ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በሕዝቡ ባሕል መሠረት እንዴት እንዳደራጀው ተመልክተናል። «ሱዜረይም-ቫሳል» በመባል የሚታወቀውንና በ2ኛው ሺህ ዓ.ዓ. በኬጢያውያን መካከል በጣም ተለምዶ የነበረውን የስምምነት አሠራር ሲጠቀም እናያለን። ይህ ስምምነት አሸናፊ በሆነው ንጉሥ ወይም መሪዎችና ተገዢ በሆኑ ነገሥታት መካከል የሚፈጸም ነበር። በኦሪት ዘጸአት እግዚአብሔር ገዢ ንጉሥ ሆኖ፥ ቃል ኪዳኑን የዚህ ስምምነት እንደ ቫሳል (ሎሌ) ተቀባይ ከሆኑት ከእስራኤላውያን ጋር አድርጎ እናያለን። የሚከተለውን ባሕላዊ ያቃል ኪዳን ስምምነትን ኦሪት ዘዳግም እንዴት እንደሚመስሉ ተመልከት። እግዚአብሔር ንጉሥ (ሱዚረይም) መሆኑን እስራኤል ደግሞ ተገዢ (የስምምነቱ ውል ተቀባይ «ቫሳል» ወይም ሎሌ) መሆኗን አስታውስ።

 1. የተናጋሪው ወይም የቃል ኪዳኑ ሰጭ መግቢያ፡ በዘዳግ. 1፡1-5 ተንፀባርቋል፡፡ ምንም እንኳ ተናጋሪው ሙሴ ቢሆንም የሚናገረው ንጉሡን- እግዚአብሔርን ወክሎ ነው።
 2. የቃል ኪዳኑ ታሪካዊ አቀራረብ፡- ይህ በዘዳግ. 1፡6-3፡29 ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ደግም በሚናገርበት (በሚከልስበት) ጊዜ እግዚአብሔር እነርሱን እንዴት እንደመረጣቸው፥ ከግብፅ ባርነት ነፃ በማውጣት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዴት እንደመራቸው በሚያሳየው ክፍል ተንፀባርቋል።
 3. ስለ ቃል ኪዳኑ ከፍጻሜ መድረስ ይመሰክሩ ዘንድ ተገዢው ሊታዘዛቸው የሚገባ የቃል ኪዳኑ ቅድመ ሁኔታዎች፡- በማክበር ይጠብቁት ዘንድ እግዚአብሔር ለእስራኤል ትእዛዛቱን ሁሉ በሰጠበት በዘዳግም 4-26 ይታያል። 
 4. የቃል ኪዳኑ ሕጋዊ ሰነድ ምን ማድረግ እንደሚገባ የተሰጡ መመሪያዎች፡፡ በኦሪት ዘዳግም 27፡2-3 ሙሴ ሕጉ በድንጋይ ላይ እንዴት እንደሚጻፍና እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በገቡ ጊዘ አስታዋሽ ሆኖ እንደሚቀመጥ መመሪያ ሰጠ።
 5. ምስክሮች ተጠርተው ነበር (ዘዳግ. 31-32)፡- አሕዛብ ብዙውን ጊዜ ለምስክርነት የሚጠሩት ጣዖቶቻቸውን ነበር፤ ነገር ግን ሙሴ በመጀመሪያ ምስክር ይሆን ዘንድ መዝሙር ዘመረ (ዘዳ. 31፡19-22)። ቀጥሎም በዘላለማዊ አምላክና በሕዝቡ መካከል ምስክር ይሆን ዘንድ ሰማይና ምድርን ጠራ።
 6. ንጉሡ በረከትንና ርግማንን ወይም ለቃል ኪዳኑ በመታዘዝ የሚሰጥ ሽልማትንና ባለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣትን ዘረዘረ፡፡ በዘዳግ. 28 እግዚአብሔር እስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ቢታዘዙ የሚያገኙትን በረከት፥ ባይታዘዙ ደግሞ የሚጠብቃቸውን ቅጣት ወይም ርግማን የዘረዘሩበት ክፍል ነው።

ከዚህ የምንረዳው፥ኦሪት ዘዳግም በሲና ተራራ የተሰጠው የሕግ መደገም ብቻ ሳይሆን፥እስራኤላውያን አስቀድሞ በሲና ተራራ አባቶቻቸው ያደረጉትን ስምምነት ወይም ቃል ኪዳን ለሁለተኛ ጊዜ ማጽናታቸውን የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ መሆኑን ነው። በሲና ተራራ እንደነበረው ቃል ኪዳን፥ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ዘርዘር አድርጎ የሚያቀርብ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዘመናችን የዚሁ ተመሳሳይ የሆነ ግንኙነት በእግዚአብሔርና በክርስቲያኖች መካከል የሚኖረው እንዴት ነው? ለ) ተመሳሳይ ነው ወይስ የተለያየ? አብራራ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)