በመንፈስ መመላለስ የሚገኝ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ (ገላ. 5፡16-6፡18)።

ከብሉይና አዲስ ኪዳን አስደናቂ ልዩነቶች አንዱ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚጫወተው ሚና ነው። በብሉይ ኪዳን፥ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የተወሰኑ መሪዎች የመሪነትና ጠላቶቻቸውን የማሸነፍ ተግባር እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው የእግዚአብሔር ኃይል ነበር። ስለሆነም፥ መንፈስ ቅዱስ ለጥቂት ሰዎች የሚሰጥ ሲሆን፥ አንዳንድ ጊዜ ከኃጢአት ወይም ከአገልግሎታቸው ፍጻሜ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ይለያቸው ነበር።

በአዲስ ኪዳን ግን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለልጆቹ በሙሉ ለመስጠት ቃል ገብቷል። ስለ መንፈስ ቅዱስ በምናስብበት ጊዜ በአብዛኛው አልፎ አልፎ ስለሚያከናውናቸው እንደ ልሳን ወይም ለአንዳንድ ሰዎች በሚሰጣቸው የተአምራት ስጦታዎች ስላመሳሰሉት አስደናቂ ነገሮች እናስባለን። አብዛኛው የአዲስ ኪዳን አስተምህሮ የሚያተኩረው ግን በመንፈስ ቅዱስ ሌሎች አገልግሎቶቹ ላይ ነው። ከመንፈስ ቅዱስ እጅግ ጠቃሚ አገልግሎቶች አንዱ ክርስቲያኖች የኃጢአት ባሕርያቸውን እንዲያሸንፉና እግዚአብሔርን በሚያስደስት መንገድ እንዲመላለሱ ማስቻል ነው።

ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚመራ የነጻነት ሕይወት በአኗኗራችን ላይ ለውጥን እንደሚያስከትል አስተምሯል። እንደ መንፈስ ቅዱስ ኃይል በምንኖርበት ጊዜ የኃጢአት ባሕርያችንን ሳይሆን እግዚአብሔርን ደስ እናሰኛለን። ጳውሎስ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት ተጻራሪ ኃይላት እንዳሉ ገልጾአል። የኃጢአት ተፈጥሮና መንፈስ ቅዱስ አሉ። ድነትን (ደኅንነትን) ባገኘን ጊዜ እግዚአብሔር የኃጢአት ተፈጥሯችንን አላስወገደም። የኃጢአት ፍላጎት አሁንም አብሮን አለ። ነገር ግን ከሕይወታችን የኃጢአት ተፈጥሮ የመቆጣጠር ኃይልን ሰብሮ ከእርሱ የበለጠ ኃይል ተሰጥቶናል። ይህም ኃይል በእያንዳንዱ ክርስቲያን ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ነው። እነዚህ ሁለት ኃይላት እኛን ለመቆጣጠርና በሕይወታችን ፍሬያቸውን ለማፍራት ይታገላሉ። [ማስታወሻ፡- ክርስቲያኖች ሰይጣን ወደ ኃጢአት እንደሚመራን በመግለጽ ወቀሳ መሰንዘራችን የተለመደ ነው። ምንም እንኳ ሰይጣን ኃጢአት እንድንፈጽም ሊፈትነንና የኃጢአት ተፈጥሯችንን ቢጠቀምም፥ ኃጢአትን የምንፈጽመው ሁልጊዜም በምርጫችን ነው። መውቀስ ያለብንም ራሳችንን ነው ያዕ. 1፡13-15 አንብብ]።

የኃጢአት ባሕርይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይከተል የግል እርካታንና ጥቅምን የሚያስገኙ ተግባራትን ለመፈጸምና የራስን ሕይወት ለመቆጣጠር የሚደረግ የእያንዳንዱ ሰው ኩሩ የማንነት ክፍል ነው። ይህ እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው አመለካከትና ተግባር ተቃራኒ ነው። ጳውሎስ ከእነዚህ የኃጢአት ባሕርያት «ተግባራት» ወይም «ፍሬዎች» አንዳንዶቹን ጠቃቅሷል። እነዚህም በሦስት የተለያዩ ምድቦች ሊቀርቡ ይችላሉ።

ሀ. ወሲባዊ ኃጢአቶች። ዝሙት (ከጋብቻ ውጭ የሚፈጸም የትኛውም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነት)፥ ርኩሰት፥ መዳራትና ዘፋኝነት። (ማስታወሻ፡- ዘፋኝነት የሚለው የአማርኛው ቃል ሙዚቃንና የሰውነት እንቅስቃሴን ያመለክታል። ነገር ግን ጳውሎስ ይህን ሲል ዘፋኝነት ሁሉ ኃጢአት ነው ማለቱ ሳይሆን፥ ሰዎችን ለወሲብ ለማነሣሣት የሚካሄድ ዳንስና ጭፈራ ኃጢአት እንደሆነ ማመልከቱ ነው።)

ለ. እንደ ጣዖት አምልኮና ጥንቆላ ያሉ ሐሰተኛ አምልኮዎችም አሉ።

ሐ. ራሳችንንና ሌሎችን ወደ ተሳሳቱ ተግባራት የሚመሩ የሚጎዱ የተሳሳቱ አመለካከቶች አሉ። እነዚህም ጥላቻ፥ መከፋፈል፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነትና ስካር ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ኃጢአቶች በቤተ ክርስቲያንህ ችግር የሚፈጥሩባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) እነዚህ ኃጢአቶች በሕይወትህ ችግር የሚፈጥሩባቸውን መንገዶች ግለጽ።

መንፈስ ቅዱስ ግን ከዚህ የሚቃረን ፍሬ ይሰጣል። ሰዎች እንዲለውጡ በሚፈልጋቸው ብዙ ውጫዊ ተግባራት (ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ነገሮች ወደ ሕግጋት ተመልሰው ሰዎችን በባርነት ይገዛሉ) ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ መንፈስ ቅዱስ ልባችንና አመለካከቶቻችንን ለመለወጥ ይፈልጋል። የአማኙ ልብና አመለካከቶች ከተስተካከሉ በኋላ፥ ተግባራቱም ይለወጣሉ። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በቀዳሚነት የኃጢአት ባሕርይ አመለካከቶች ተቃራኒ የሆኑ አመለካከቶች ናቸው። እነዚህም ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ ታማኝነት፥ የውኃትና ራስን መግዛት ናቸው። ጳውሎስ እንዲኖሩን የሚፈልጋቸውን አመለካከቶች ሁሉ ለመዘርዘር እየሞከረ አልነበረም። ነገር ግን በግንኙነት ዓይኖች የመንፈስ ቅዱስን ሥራዎች እየተመለከተ ነው። እምነታችንን የምንገልጽበት ዋነኛው መንገድ ፍቅር ከሆነ ለማፍቀር እንችል ዘንድ እነዚህ ባሕርያት በሕይወታችን ውስጥ ሊኖሩ ይገባል።

በኃጢአት ባሕሪያችንና በአዲሱ ባሕርያችን መካከል የሚካሄደው ጦርነት የተጧጧፈ ነው። ይህም ወደ መንግሥተ ሰማይ እስክንሄድ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል። ይህ ጦርነት ሳይካሄድ የሚውልበት ቀን ሊኖር አይችልም። እንግዲህ፥ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እንኖር ዘንድ ድልን የምንቀዳጀው እንዴት ነው? ጳውሎስ ማድረግ የሚገባንን ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ሰጥቶናል።

በመጀመሪያ፥ የኃጢአትን ተፈጥሮ መስቀል አለብን። በገላትያ 2፡20 ጳውሎስ ከክርስቶስ ሞት ጋር ስለመተባበራችንና በዚህ ውስጥ ስለተገለጠው የእግዚአብሔር ሥራ ገልጾአል። ይህ የክርስቶስ ስቅለት የኃጢአት ባሕርያችንን ቁጥጥር በማጥፋት ለእግዚአብሔር እንድንኖር አስችሎናል።

ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ልናደርገው ስለሚገባን ነገር ገልጾአል። ወደ ኃጢአት ለመምራት የሚያቀርበውን ፈተና ለመስማት ባለመፈለግ በየቀኑ የኃጢአት ተፈጥሯችንን መስቀል አለብን። ይህንን እንዴት ልናደርግ እንችላለን? አሮጌውን የኃጢአት ባሕርይ ላለመስማትና ፍላጎቶቹን ላለመፈጸም ከምንወስዳቸው እርምጃዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡- ሀ) እንደ መንፈስ ቅዱስ ምሪት መመላለሳችንን ለማረጋገጥ በየጊዜው ራሳችንን መመርመር። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳለብን ያሳያል። መንፈስ ቅዱስ የትኞቹ አሳቦችና አመለካከቶች ከክፉ ባሕርይ፥ የትኞቹ ደግሞ ከእግዚአብሔር እንደሆኑ የሚያሳየን በዚህ መንገድ ነው። ለ) የኃጢአት ተፈጥሮ መንገድ ትክክል እንዳልሆነና ኃጢአትን እንደፈጸምን በመገንዘብ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ንስሐ መግባት። ሐ) ወደ ኃጢአት ለመምራት የሚሞክረውን የአሮጌውን ባሕርይ ድምፅ ላለመስማት መምረጥና መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መኖር እንዳለብን ሲናገረን መስማት። መ) የኃጢአት ባሕርያችን ስበት ጠንካራ በሚሆንበት ጊዜ ይረዳን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ አለብን።

ሁለተኛ፥ በመንፈስ እንድንመላለስ ታዘናል። መንፈስ ቅዱስ የማያቋርጥ ወዳጃችን፥ መሪያችንና አጽናኛችን ነው። እርሱን መስማት መማር አለብን። በቃሉ ውስጥ የጻፈውን በማንበብ ድምፁን እንለያለን። መንፈስ ቅዱስ ወደ ንጹሕ ግንኙነት፥ የከበረ አምልኮ፥ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ወንጌሉን ወደ ማካፈል፥ ወደ የትኛውም ስፍራ በሚመራን ጊዜ በታዛዥነት እንከተለዋለን።

ጳውሎስ ለድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ ስናምን አዲስ ፍጥረት እንደምንሆን አስረድቷል (ገላ. 6፡15)። ይህም እግዚአብሔር ሁለንተናችንን ለመለወጥ እንደሚፈልግ ያሳያል። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ በምንመላለስበት ጊዜ የሚከሰቱትን የተወሰኑ ለውጦች ዘርዝሯል (ሮሜ 8፡9)።

ሀ. በመንፈስ መመላለስ፣ በኃጢአት የሚመላለሱ ሰዎች እግዚአብሔር ወደሚፈልገው መንገድ እንዲመለሱ መርዳትን ያካትታል። ፍቅር ለመርዳት ይሞክራል እንጂ ለኃጢአተኛ «በመጸለይ» ብቻ አያበቃም። ፍቅር ወደ ኃጢአተኛው በመሄድ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ ይማጸነዋል። ጳውሎስ ክርስቲያኑ ከኃጢአት መንገድ እንዲመለስ ለማድረግ በምንጥርበት ጊዜ እኛ ራሳችን እንዳንፈተን ያስጠነቅቀናል።

ለ. በመንፈስ መመላለስ የሌሎችን ሰዎች ሸክም ማገዝን ይጠይቃል። ይህ ግን በራስ ወዳድነት ሰዎች እንዲንከባከቡን መጠበቅ አይደለም። ስንችል የራሳችንን ሸክም መሸከም አለብን።

ሐ. በመንፈስ መመላለስ በትዕቢት ከሌሎች እንደምንበልጥ ማሰብ ወይም ራሳችንን እንደማንረባ መቁጠር አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች በመመርመር በተቻለን አቅም ለእግዚአብሔር ክብር ለመጠቀም መጣር አለብን።

መ. በመንፈስ መመላለስ የኃጢአት ባሕርያችንን የሚያጠናክር ተግባር አለመፍቀድም ነው። ጳውሎስ በሕይወታችን ውስጥ የሚሆነውን ሁኔታ ለማሳየት የመዝራትንና የማጨድን ምሳሌ ተጠቅሟል። መልካምና መንፈሳዊ ነገር (ጸሎት፥ አምልኮ፥ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፥ መልካም ጓደኝነትን የሚያንጽ ንግግር፥ የሚያንጽ ቪዲዮ ማየትን) ከዘራን፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መንፈሳዊ ዕድገትንና ዘላለማዊ ሽልማቶችን እናጭዳለን። ነገር ግን የኃጢአት ባሕርያችንን የሚያጠናክሩትን ነገሮች (መጥፎ ጓደኝነት፥ ሐሜት፥ መጥፎ መጻሕፍት ወይም መጥፎ ቪዲዮዎችን ማየት) ከዘራን፥ የኃጢአት ባሕርያችን ዘላለማዊ ጉዳት የሚያስከትሉትን ፍሬዎች እንድናጭድ ያደርገናል።

ሠ. በመንፈስ መመላለስ አሁን ጥቅም እያገኘንበት ባይመስልም እንኳን ለሰዎች መልካም ማድረግን ይጠይቃል።

እነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነትና ለእነርሱ የምናሳያቸውን ፍቅር የሚመለከቱ መሆናቸውን አጢን። ፍቅር መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ለማፍራት የሚፈልገው ዐቢይ ቁም ነገር ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– ሕይወትህን መርምር። ሀ) በመንፈስ መመላለስህን የምታሳይባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ለመንፈሳዊ ሕይወትህ የሚያግዙ ነገሮችን የምትዘራባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) ለኃጢአት ተፈጥሮህ የሚያግዙ ነገሮችን የምትዘራባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

መደምደሚያ (ገላ. 6፡11-18)

ጳውሎስ መልእክቱን ሲደመድም የሚከተሉትን ነገሮች ገልጾአል።

 1. በትላልቅ ፊደላት ጽፎአል። ይህን ያደረገበትን ምክንያት ባናውቅም፥ የመልእክቱን አስፈላጊነት ለማጉላት የፈለገ ይመስላል። ከዚህ በበለጠ ግን ሌላ ሰው ሳይሆን ራሱ እንደ ጻፈና ከዓይኑ ሕመም የተነሣ ትላልቅ ፊደላትን እንደ ተጠቀመ የሚያሳይ ይሆናል።
 2. አማኞች በትክክለኛ ነገሮች መመካታቸውን እንዲያረጋግጡ መከሯቸዋል። ስለ መገረዝ ጥቅም የሚሰብኩ ሰዎች በመገረዛቸው ይመኩ ነበር። እነዚህ ሰዎች ለክርስቶስ መስቀል ክብርን ሳይሰጡ መንፈሳዊነታችንን ያጎላሉ በሚሏቸውና ባከናወኗቸው ውጫዊ ተግባራት ይመኩ ነበር። ጳውሎስ በግርዛት ላይ የሚያተኩሩበት ብቸኛው ምክንያት አይሁዶች እንዳያሳድዷቸው በመፍራታቸው እንደሆነ ገልጾአል።

በአንጻሩ፥ ከክርስቶስ መስቀል በቀር ጳውሎስ በየትኛውም ውጫዊ ነገር ላለመመካት ይወስናል። ከክርስቶስ በስተቀር አይሁዳዊ ባሕሉ፥ ነገዱ፥ ወንድነቱ፥ ወይም ትምህርቱ እርባና-ቢስ እንደሆነ ገልጾአል። ጳውሎስ ዓለም እንደ ብርቅ ለምታያቸው ነገሮች ሞቷል። ጳውሎስ እንደ ትልቅ ነገር የሚቆጥረው አዲስ ፍጥረትነቱን ነበር። በሰውነቱ ላይ የሚታዩት የስደት ምልክቶች ጳውሎስ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንደሚመላለስ ያሳያሉ። ስለሆነም፥ ሌሎች አማኞች ሊንቁት አይገባም።

 1. ጳውሎስ እርሱንና የእግዚአብሔርን ቃል በእውነተኛ ሰላምና ምሕረት የሰሙትን የገላትያ ክርስቲያኖች ባረከ።

የውይይት ጥያቄ፡– ከገላትያ መልእክት ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያውቋቸው ይገባል የምትላቸውን እውነቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእምነት ሕይወት የንጽሕናና ሌሎችን የማገልገል ነጻነት ያመጣል (ገላ. 5፡1-15)

ዘነበ የዩኒቨርስቲ ክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት አባል ነበር። ከሳምንታዊ አምልኳቸው በአንዱ አንድ ግለሰብ በክርስቶስ ስለሚገኝ ነጻነት ሰበከ። ሰባኪው፥ «ከሕግ ነፃ ስለሆናችሁ የፈለጋችሁትን ሁሉ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ክርስቶስ ለኃጢአታችሁ እንደ ሞተ እስካመናችሁ ድረስ ምንም ዓይነት ሕግ መጠበቅ አያስፈልጋችሁም። ስለሆነም፥ ‹አትዋሽ፥ አትስረቅ፤ አታመንዝር የሚሉ የእግዚአብሔር ሕግጋት ከእንግዲህ በእኛ ላይ ተፈጻሚነት የላቸውም። እነዚህን ሕግጋት መጠበቅ አያስፈልገንም። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው በነፍሳችሁ እንጂ በሥጋችሁ አይደለም። ስለሆነም፥ እስከ ጸለያችሁ፥ በልሳን እስከ ተናገራችሁ፥ በመዝሙር እስካመለካችሁና ልባችሁ ንጹሕ መሆኑን እስካረጋገጣችሁ ድረስ፥ በሥጋችሁ የምታደርጉት ነገር አሳሳቢ አይሆንም» ሲል አብራራ። ዘነበ እግዚአብሔር እንዳሻው እንዲኖር የፈቀደለት መሆኑን በማመን ከኅብረቱ ሴት አባላት ጋር ማመንዘር ጀመረ። እግዚአብሔርን የሚገድደው ስላልመሰለው የፈተና መልሶችንም መስረቅ ጀመረ።

የውይይት ጥያቄ ሀ) ሰባኪው ለዘነበ ያስተማረው ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይመስልሃል? ለ) በሕግጋት ካልዳንን አማኞች ከሆንን በኋላ ሕግጋት በሕይወታችን ውስጥ ምን ዓይነት ሚና እንዳላቸው ግለጽ።

በገላትያ የመጀመሪያው ክፍል (ገላ. 1-4)፥ ጳውሎስ «ሰው ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?» ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል። የጳውሎስ ምላሽ፥ «ክርስቶስ ለኃጢአትህ እንደ ሞተ ብታምን እግዚአብሔር ድነትን እንደ ነፃ ስጦታ ይሰጥሃል። «ጥፋተኛ አይደለህም› ሲል ያውጃል። ድነትን ለማግኘት መፈጸም የሚኖርብህ ተግባር ወይም መጠበቅ የሚኖርብህ ሕግ የለም» የሚል ነው። በዚህ በሁለተኛው የገላትያ መልእክት ክፍል (ገላ. 5-6)፥ ጳውሎስ፦ «ክርስቲያን ከሆንሁ በኋላ እንደ እግዚአብሔር ልጅ እንዴት መመላለስ ይኖርብኛል?» ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል።

አንድ ሰው በሥራ ሳይሆን በጸጋ ከዳነ በኋላ የሚያደርገው ነገር አሳሳቢ አይደለም የሚለው አመለካከት በጳውሎስ ዘመን የተለመደ ነበር።

በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እየተስፋፋ መጥቷል። በክርስቶስ ነፃ ወጥተናል የሚለውን አሳብ ሰዎች እንደፈለግን ልንኖር እንችላለን ማለት ነው ብለው ይተረጉማሉ። ብዙውን ጊዜ የዚህ አመለካከት አራማጆች እግዚአብሔር ትኩረት የሚሰጠው ለመንፈሳችን፥ ከእርሱ ጋር ስላለን ግንኙነት ስለ አምልኳችንና ስለ ውዳሴያችን እንደሆነ ይናገራሉ። በሥጋችን ስለምናደርገው ነገር አያሳስበውም ይላሉ። ምንም እንኳ ብዙዎቻችን ይህን አሳብ በይፋ ባንናገርም፥ ራሳቸውን ክርስቲያኖች ብለው የሚጠሩና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሟሟቀ አምልኮ የሚያካሂዱ ሰዎች የዓመፅ ኃጢአት (ለምሳሌ፥ ዝሙት፥ ውሸትና የመሳሰሉትን) የሚፈጽሙት፥ ባይታዘዙትም እንኳ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ባለው ግንኙነት እንደሚረካ ስለሚያስቡ ነው። ይህ የተሳሳተ ትምህርት ነው። በክርስቶስ በማመን ብንድንም፥ የዳንነው በነፍሳችን፥ በሥጋችንና በሁለንተናችን እግዚአብሔርን ለማክበር ነው። ክርስቲያናዊ ነጻነት ማለት እግዚአብሔር እንዳሻን እንድንኖር ይፈቅድልናል ማለት አይደለም። ነገር ግን ክርስቲያናዊ ነጻነት ማለት ከሰይጣን ባርነት ነፃ ወጥተን እግዚአብሔርን የሚያስከብርና ክርስቶስን እንመስል ዘንድ ለተፈጠርንለት ዓላማ ለመኖር ነፃ መሆን ማለት ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ እኛም እንደ እርሱ ለመሆን ነፃ እንሆናለን።

ክርስቲያኖች፥ «በክርስቶስ በማመኔና በእግዚአብሔር ነፃ ማዳን ምክንያት እንደ ዳንሁ አውቃለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ቤተ ክርስቲያኔ የምትሰጠኝን ሕግና ትእዛዝ በመፈጸም እግዚአብሔርን ማስደሰት አለብኝ። መገረዝ፥ የተወሰነ የአለባበስ ስልት መከተል፥ ፀጉሬን በአግባቡ መያዝ፥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሄድ አለብኝ፥» ሊሉ ይችላሉ። አሕዝብ የነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች አይሁዳዊ ክርስቲያን አስተማሪዎቻቸውን ደስ ለማሰኘት በመፈለጋቸው ለመገረዝ እያሰቡ ነበር። የጳውሎስ ትምህርት አያሌ ዐበይት እውነቶችን ያካትታል።

ሀ. ጳውሎስ ውጫዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሕግጋት በመጠበቅ ሌሎችን ለማስደሰት ለተፈተኑት ክርስቲያኖች፥ «በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።» ብሏል (ገላ. 5፡1-12)። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የማይጠብቅባቸውን ሕግጋት ለመከተል በመሞከር ለባርነት እንዳይዳረጉ ያስጠነቅቃቸዋል። ጳውሎስ አሕዛብ የነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች እንዳይገረዙና በወግ አጥባቂነት የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት እንዳይከተሉ ያዛቸዋል። ለመገረዝ ከፈቀዱ ሁለት ነገሮች እንደሚከሰቱ ያስረዳል።

 1. የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ የሚወዷቸውን ሕግጋት ሊጠብቁና የማይወዷቸውን ሊተዉ አይችሉም ነበር። እነዚህን ሕግጋትና ደንቦች ለመጠበቅ በመሞከራቸው ለጠቅላላው ሕግ ባሪያዎች ይሆኑ ነበር።
 2. የክርስቶስ ሞት ጥቅም አይሰጣቸውም ነበር። መገረዝ ትንሽ ነገር ቢመስልም፥ የሚገረዙበትና ሕግን የሚጠብቁበት ምክንያት ጥልቅ አስከትሎቶችን ይመዝ ነበር። ይህም ለደኅንነታቸው በክርስቶስ ለማመን አለመፈለጋቸውንና እነዚህን ሕግጋት በመጠበቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅን ሊያገኙ እንደ ፈለጉ ያመለክት ነበር። የተወሰኑ ተግባራት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንደሚያስገኝላቸው ያስቡ ነበር።

በብሉይ ኪዳን ሦስት ዓይነት ዐበይት ሕግጋት ነበሩ። በመጀመሪያ፥ የግብረገብ ሕግጋት ነበሩ። እነዚህ ሕግጋት ሰዎች ከእግዚአብሔርና እርስ በርሳቸው የሚዛመዱባቸውን መንገዶች የሚደነግጉ ነበሩ። በዘጸአት 20፡1-17 የተገለጹት አሥርቱ ትእዛዛት ለእነዚህ ሕግጋት ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ይታዘዟቸው ዘንድ ተደግመው የተገለጹት ሕጋጋት እነዚህ ብቻ ናቸው። ሁለተኛ፥ ማኅበራዊ ሕግጋት ነበሩ። እነዚህ ሕግጋት እስራኤላውያን እንዴት አብረው እንደሚኖሩ፥ ምን እንደሚመገቡ፥ የሀብት ክርክሮችን እንዴት እንደሚያስተናግዱ፥ በሚታመሙበት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው፥ መሪዎች እንዴት እንደሚመረጡ፥ ወዘተ… የሚያሳዩ ነበሩ። ሦስተኛ፥ ሃይማኖታዊ ሕግጋትም ነበሩ። እነዚህ የአይሁዶችን አምልኮ፥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕቶችን እንዴት እንደሚያቀርቡ፥ ምን ዓይነት ሃይማኖታዊ በዓላትን እንደሚጠብቁ፥ ወዘተ… የሚያሳዩ ነበሩ። ከግብረገባዊ ሕግጋት ውጭ ያሉትን ሕግጋት ክርስቲያኖች መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ከእነዚህ ሕግጋት ውስጥ የምናወጣቸውና ለፍትሐዊ ማኅበራዊ ሕይወት የሚጠቅሙ መርሆች አሉ። በሌላ በኩል፥ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ብለን እስካልተጠቀምንባቸው ድረስ ብዙዎቹን ማኅበራዊ፥ ሃይማኖታዊና ቤተ ክርስቲያንህ የምትደነግጋቸውን ሕግጋት መጠበቁ ጉዳት የለውም። ይህ በታሪክ ሁሉ ብዙ ሰዎች የተሳሳተ አስተምህሮ እንዲከተሉ ያደረገ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።)

ለ. በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት መገረዝ ወይም አለመገረዝ ለውጥ የለውም። መገረዝን እንደ አስፈላጊ ባሕላዊ ተግባር ስለተመለከቱት በአይሁዶች ዘንድ ሥጋዊ ግርዛት ተቀባይነት ነበረው። አይሁዶቹ ይህን ልማድ ለማድረግ ነጻነት ነበራቸው። የአሕዛብ ክርስቲያኖች የራሳቸውን ባሕል ለመከተልና ልጆቻቸውን ላለማስገረዝ ሲፈልጉ፥ ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፡፡ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ፈጽሞ ከድነት (ደኅንነት) ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ነገር ግን አንድን ነገር የምናደርግበት ምክንያት የተሳሳተ ከሆነ፥ ተግባሩም የተሳሳተ ይሆናል። ለምሳሌ፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰት፥ ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት ወይም መንፈሳዊ ለመምሰል ብለን ለመገረዝ ብንፈልግ፥ የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ ተረድተናል ማለት ነው። እግዚአብሔር ለሁለት ነገሮች ትኩረት ይሰጣል።

1) በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እናገኝ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደ ሞተልን በፍጹም ልባችን ማመን። ጳውሎስ እምነት ድነት (ደኅንነት) ያገኘንበትን ሁኔታ የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የተስፋችን መሠረት እንደሆነ ያስረዳል። ክርስቶስን የምንመስልበትን፥ የጽድቅ ተግባራት የምንፈጽምበትንና ከእርሱ ጋር ለዘላለም የምኖርበትን የድነት (ደኅንነት) ሂደት ፍጻሜ ልንመለከት የምንችለው በእምነት ነው። ስለሆነም፥ በመንፈሳዊ ጉዟችን ለእግዚአብሔር በምናከናውናቸው ተግባራት ወይም በምንጠብቃቸው ሕግጋት ላይ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ለእኛ በፈጸመው ተግባር፥ በቅድስና እንድንመላለስና ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ የሚያስችሉንን ተግባራት እንድንፈጽም በረዳን እግዚአብሔር ላይ እናተኩራለን።

2) የእምነታችን እውነታ የሚገለጽበት ፍቅር። እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን፥ ነፍሳችን፥ ሥጋችንና አሳባችን እንድንወድ ታዘናል (ዘዳግ 6፡5፤ ማቴ. 22፡37)። ሌሎችንም እንድንወድ ታዘናል (ማቴ. 22፡37-40)።

በገላትያ ክርስቲያኖች መካከል ውዝግብን የሚፈጥር አንድ ቀንደኛ ሰው የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ ለዚህ ሰው ጠንካራ ቃላትን ሰንዝሯል። እግዚአብሔር ለሚያስፋፋው የሐሰት ትምህርት ይቀጣዋል።

ሐ. ክርስቲያናዊ ነጻነት ራሳችንን ለማስደሰት ወይም የኃጢአት ባሕርያችንን ለማስተናገድ ማመኻኛ አይሆንም (ገላ. 5፡13-15)። እግዚአብሔር ምን ይፈልጋል? ለእርሱ የሚሰጠው ቅድሚያ ምንድን ነው? እምነታችንን የምንገልጽበት ዐቢይ መንገድ ምንድን ነው? ይህ መንገድ አምልኮ ነው? ጸሎት ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ነው? ወይስ ትክክለኛ ልብሶችን መልበስ? እነዚህ ጠቃሚ ነገሮች ቢሆኑም እምነታችንን የምንገልጽባቸው ዐበይት መንገዶች አይደሉም። ጳውሎስ አንዳችን ሌላውን በፍቅር በማገልገል እምነታችንን ልንገልጽ እንደሚገባን አስረድቷል። እግዚአብሔር ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነት፥ «ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ» በሚል ቃል አጠቃልሎታል። በመጽሐፍ ቅዱስ፥ ፍቅር በቀዳሚነት ለሰዎች ያለን ስሜት ሳይሆን ተግባርና አመለካከት ነው። ሰዎችን ስንወድ እንቀበላቸዋለን፤ ሌሎችን ስንወድ በሰላም ለመኖር እንችል ዘንድ ለእነርሱ ትክክለኛ የሆነውን ነገር እናደርጋለን። ፍቅር ሁልጊዜም ዋጋ ያስከፍለናል። የተቸገሩትን ስንረዳ ወይም ለምስክርነት ስንወጣ ጊዜያችንን እንሠዋለን። ለድሆች ወይም ለወንጌል ስርጭት ገንዘባችንን ስንሰጥ ዋጋ እንከፍላለን። አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች ስንል የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለመተው እንገደዳለን። ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖች ፍቅርን አጥተው እርስ በርሳቸው እየተጣሉ በመሆናቸው እንዳይጠፉ አስጠንቅቋቸዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) ሕግጋትን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንደሚገኝ አብራራ (ገላ. 3፡1-4፡31)

የውይይት ጥያቄ፡- ገላ. 3-4 አንብብ። ድነት (ደኅንነት) በእምነት ብቻ መሆኑን እንዴት እንደምናውቅ ጳውሎስ ያቀረበውን ክርክር ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

ብዙውን ጊዜ በክርስቶስ አዳኝነት ላይ በሚደገፉና ሥራቸው ለደኅንነታቸው አስተዋጽዖ እንዳለው በሚተማመኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ሁለቱም የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ሊጠብቁ ይችላሉ። ሁለቱም መጠጥ ላይጠጡ፥ ተገቢ ልብሶችን ሊለብሱ፥ ግብረገባዊ ሕይወት ሊመሩ፥ ወዘተ… ይችላሉ። በሁለቱ መካከል ቀዳሚ ልዩነት የሚታየው ከመነሣሻ ምክንያታቸው ወይም ለድነት (ደኅንነት) በሚያምኑት ነገር ላይ ነው። በክርስቶስ ብቻና በነፃ የድነት (ደኅንነት) ስጦታ የሚያምነው ሰው በክርስቶስና በክርስቶስ የመስቀል ሞት ላይ ያተኩራል። ጳውሎስ «በፊታችሁ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር» ሲል ይህን ለማለት ነበር (ገላ. 3፡1)። በክርስቶስ ላይ በምናተኩርበት ጊዜ ኃጢአተኝነታችንና አዳኝ እንደሚያስፈልገን እንረዳለን። በምናከናውናቸው ተግባራት ድነትን (ደኅንነትን) ልናገኝ እንደማንችል እንገነዘባለን። እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ በመመሥረት ወደ ክርስቶስና ወደ ማዳኑ እንመለሳለን።

ነገር ግን ድነት (ደኅንነት) ክርስቶስን በማመንና በመልካም ሥራ አማካኝነት እንደሚገኝ ካመንን ትኩረታችን በሥራችን ላይ ይሆናል። ለምሳሌ፥ «ለመዳን በክርስቶስ ማመን አለብህ። እንዲሁም ቢራ መጠጣትህንና ጫት መቃምህን ልታቆምና ሁለተኛ ሚስትህን ልትፈታ ይገባል» በምንልበት ጊዜ የምንመሰክርላቸው ሰዎች አጽንኦት የሚሰጡት ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት በሚያሟሏቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ወይም ሥራዎች እንጂ በክርስቶስ ላይ አይሆንም። ስለሆነም በወንጌሉ ላይ ሌላ ነገር ጨምረናል ማለት ነው። አዳዲስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ይቀበላቸው ዘንድ በተወሰነ መንገድ እንዲለብሱ በምንናገርበት ጊዜ በክርስቶስ ከማመን ይልቅ በተግባሮቻችን ላይ ወደ ማመኑ ተመልሰናል ማለት ነው። ሰዎች ከልባቸው፥ የክርስቶስ ሞት ጠቃሚ ቢሆንም በቂ አይደለም፤ በትጋት እንደምከተለው ለማሳየትና ያድነኝ ዘንድ ድጋፉን ለማግኘት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አንድ ተግባር መፈጸም አለብኝ እንዲሉ እንገፋፋቸዋለን። ዓይኖቻችን ወደ ራሳችን ይመለሱና በክርስቶስ ላይ ማተኮራችን ይቀራል። ጳውሎስ ይህ አመለካከት ወንጌሉን እንደበረዘ ገልጾአል። ይህ የገላትያ ሰዎች ስውር የእምነት ለውጥ አንድ ጠንቋይ የደገመባቸው ይመስል ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ በሚጣል እምነት መሆኑን ለማብራራት የተለያዩ ማረጋገጫዎችን ይሰጣል።

ድነት (ደኅንነት) በእምነት እንደሚገኝ የሚያስረዳ የገላትያ ክርስቲያኖች የሕይወት ገጠመኝ ማረጋገጫ (ገላ. 3፡1-5)

ሀ. የገላትያ ክርስቲያኖች ድነትን ባገኙ ጊዜ የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሳይጠብቁ ነፃ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተቀብለዋል። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር እነርሱን ለመቀበልና ለማዳን የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዲጠብቁ እንዳልጠየቃቸው ግልጽ ነበር። ሕግጋትን ጠብቆ እግዚአብሔርን ለማስደሰት አሁን ከእምነት መመለሱ እግዚአብሔር ካዳናቸው መንገድ የሚቃረን ተግባር ነበር።

ለ. የገላትያ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ተአምራት የተለማመዱት በእግዚአብሔር ባመኑ ጊዜ እንጂ ሕግጋትን በጠበቁ ጊዜ አልነበረም። ስለሆነም፥ እነዚህ ተአምራት ሕግጋትን ሳይጠብቁ እግዚአብሔር እንደተቀበላቸው ያሳያሉ።

ሐ. ሕግጋትን ከመጠበቃቸው በፊት እውነተኛ ክርስቲያኖች ካልነበሩ፥ በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት የተቀበሏቸው ስደቶች ሁሉ ከንቱ ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዘፍጥ. 15፡1-6 እንብብ። እግዚአብሔር ለአብርሃም ምን ምን የተስፋ ቃሎችን ሰጠው? እግዚአብሔር ያከበረውና እንደ ጽድቅ የቆጠረው የአብርሃም ምላሽ ምን ነበር? አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ ለመታየት የሚያከናውናቸው የተግባር ዝርዝርች ነበሩ? ለ) ዘፍጥ. 12፡1-3 አንብብ። እግዚአብሔር ለአብርሃም ምን ምን የተስፋ ቃሉችን ሰጠ? ከእነዚህ የተስፋ ቃሎች ዛሬ አሕዛብ የሆንነውን ሰዎች የሚመለከቱት የትኞቹ ናቸው?

ድነት (ደኅንነት) በእምነት እንደሚገኝ የሚያስረዳ የብሉይ ኪዳን ማረጋገጫ (ገላ. 3፡6-4፡31)

ሀ. መጽሐፍ ቅዱስ የአይሁዶች አባት የሆነው አብርሃም እግዚአብሔርን በማመኑ እንደ ጸደቀ ወይም ተቀባይነትን እንዳገኘ ይናገራል (ገላ. 3፡6-9)። ይህ የሆነው ሕግ ከመሰጠቱና ከሙሴ በፊት ነበር። እግዚአብሔር አብርሃም ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ሕግጋትን እንዲጠብቅ አልጠየቀውም።

ጳውሎስ የአብርሃምን ምሳሌነት በመጠቀም ሁለት ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተላልፎአል። በመጀመሪያ፥ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ የሚለውን ትክክለኛ ግንኙነት የመሠረተው ለእግዚአብሔር አንድን ነገር በማድረግ ወይም የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት በመጠበቁ አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር የተስፋ ቃል ሰጠው። አብርሃም ያንን የተስፋ ቃል በማመኑ እግዚአብሔር እንደ ጽድቅ ቆጠረለት። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ በአዲስ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ላይ ተመሥረተን በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ የክርስቶስን ጽድቅ ተቀብለን ድነትን (ደኅንነትን) እናገኛለን። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው መልካምን ሥራ ሳይሆን በእምነት ምላሽ እንድንሰጥ ነው።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች በሥጋ ከአይሁድ እንደ ተወለዱ ሰዎች ሁሉ የአብርሃም ልጆች መሆናቸውን ለማስተማር ይፈልጋል። ለዚህም ምክንያቱ አብርሃም ከመገረዙ ወይም አይሁዳዊ ከመሆኑና በእግዚአብሔር ከመጠራቱ በፊት አሕዛብን ጨምሮ የሰው ልጆች በሙሉ በአብርሃም በኩል እንደሚባረኩ ቃል መግባቱ ነው። ስለሆነም፥ በክርስቶስ የሚያምኑ አሕዛብ የእግዚአብሔር በረከት ተቀባዮች ሲሆኑ፥ በክርስቶስ እንደሚያምኑ አይሁዶች ሁሉ የአብርሃም ልጆች ናቸው።

ለ. ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ሕግጋት በሙሉ የማይጠብቅ ሰው የተረገመ ነው ይላል (ገላ. 3፡10-14፤ በተጨማሪም ዘዳግ. 27፡26ን አንብብ)። የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ሊጠብቁ እንደማይችሉ አይሁዶች ራሳቸው ያምናሉ። ማንም ሰው የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ መጠበቅ ስለማይችል ማንም ሰው ሕግጋትን በመጠበቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም። ይልቁንም «የተረገሙ» በመሆናቸው ሌላ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ያስፈልጋቸዋል። ይህ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ደግሞ አንዱን በሌላ በመተካት የሚፈጸም ነው። (በብሉይ ኪዳን የይቅርታው መንገድ ለኃጢአተኛ ሰው ሕይወት የእንስሳት መሥዋዕት በመተካት ነበር።) ኃጢአት የሌለው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በእኛ ምትክ ሲሞት፥ ኃጢአታችንን ተሸክሞ «ተረግሟል»። የክርስቶስ መረገም በእንጨት ላይ የሚሞት ሰው ሁሉ እርጉም ነው ከሚለው የብሉይ ኪዳን ቃል ጋር የሚታይ ነው። በእንጨት ላይ መሞቱ ሌላ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ከፍቷል። ይህ አዲሱ መንገድ በመስቀል ላይ የተፈጸመ ሥራውን በማመን የሚገኝ ነው። በዚህ መሠረት እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባለት የተስፋ ቃሎች በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ሞት የእኛው ይሆናሉ። እግዚአብሔር ለሁሉም ክርስቲያን የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የዚህን የተስፋ ቃል ፍጻሜ ያሳያል። በዚህ እምነት ላይ አንዳች ተግባር መጨመር የክርስቶስን ሞት ትርጉም-አልባ ያደርገዋል። እግዚአብሔርን ለማስደሰት ሕግጋትን መጠበቅ የእምነት መንገድ ወይም እግዚአብሔርን ለድነት የማመን ተቃራኒ ነው። ማንም ሰው ለድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ እያመነ በተመሳሳይ ጊዜ ለደኅንነቱ ሊሠራ አይችልም። የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ ለመጠበቅ የቻለ አንድም ሰው ስለሌላ፥ ለድነት (ደኅንነት) ሕግጋትን መጠበቁ መረገም ነው።

ሐ. ጳውሎስ በእምነት የመዳንን መንገድ ከቃል ኪዳን ወይም ከኑዛዜ ጋር በማነጻጸር ያብራራል (ገላ. 3፡15-18) ምናልባትም ጳውሎስ አንድ አባት ለልጆቹ ሀብቱን ስለሚከፋፍልበት ሕጋዊ ኑዛዜ እያሰበ ይሆናል። አንድ ሰው ከመሞቱ በፊት ኑዛዜውን በፈለገ ጊዜ ሊለውጥ ይችላል። ከሞተ በኋላ ግን የመጨረሻ ኑዛዜው የጸና ይሆናል። ከዚያ በኋላ ማንም ሰው ኑዛዜውን አሻሽሎ ሊጽፍ አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር እንደገና በመደራደር የቃል ኪዳኑን ወይም የኑዛዜውን ቅድመ-ሁኔታዎች ሊለውጥ አይችልም። ስለሆነም፥ አብርሃም ከሞተ ከ430 ዓመታት በኋላ የተሰጠው ሕግ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን በእምነት የመዳን የተስፋ ቃል ሊለውጠው አይችልም። እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው የበረከት ተስፋ ቃል የአብርሃም «ዘር» ወደሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎአል። እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው የተስፋ ቃል ሙሉ ለሙሉ የሚፈጸመው በሕግ ሳይሆን በክርስቶስ ብቻ ነው።

መ. ጳውሎስ በእግዚአብሔር ዕቅዶች የሕግ ዓላማ ምን እንደነበረ ያብራራል (ገላ. 3፡19-25)

ጳውሎስ ቀደም ሲል ስለ ሕግ ያቀረባቸው አስተያየቶች በአይሁዶች ዘንድ ብዙ ጥያቄዎችን አስነሥቷል። «በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ማመን በቂ ከነበረ እግዚአብሔር ለምን ሕግን ሰጠ? ሕግ ጥቅም አልነበረውም ማለት ነው? ወይስ ሕጉ የእግዚአብሔር የእምነት መንገድ ተቃራኒ ነበር? ጳውሎስ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሕግን ጠቀሜታና እግዚአብሔር ሕግን የሰጠበትን ዓላማ አብራርቷል።

በመጀመሪያ፥ ሕጉ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው የተስፋ ቃል ፍጻሜ የሆነው «ዘር» ወይም ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ለሰው ልጆች የተሰጠ ጊዜያዊ ስጦታ ነበር (ገላ. 3፡19-20)። የተሰጠውም ከሰዎች መተላለፍ የተነሣ ነበር። ይህ ሐረግ ሁለት ፍችዎችን ሊሰጥ ይችላል። 1) ሕጉ የክፋትን መስፋፋት ለመገደብ እግዚአብሔር የተጠቀመበት መሣሪያ ነበር። ወይም 2) ሕጉ የተሰጠው ለክርስቶስ መምጣት በማዘጋጀት የሰዎችን ልብ ኃጢአተኝነትና ዓመፅ እንዲገልጥ ነበር።

ጳውሎስ ሕጉን ሰዎች የሰብአዊ ተፈጥሯቸውን ክፋት በሙሉ ተግባራዊ እንዳያደርጉ ከሚቆጣጠር የወኅኒ ጠባቂ ጋር ያነጻጽረዋል። እንዲሁም፥ በክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔርን ልጅነት ሙሉ መብቶች እስኪጎናጻፉ ድረስ የኃጢአት ተፈጥሯቸው የበለጠ ክፋትን እንዳይፈጽሙ ከምትከላከል የልጆች ሞግዚት ጋር ያመሳስለዋል። የሕግ ጠቀሜታ ክርስቶስ እስኪመጣና በመስቀል ላይ በመሞት የኃጢአትን ቅጣት እስኪከፍልና ሰዎችን ከኃጢአት ተፈጥሮ ቁጥጥር ነፃ እስኪያወጣቸው ድረስ የሚሠራ ጊዜያዊ ነበር። የብሉይ ኪዳን ሕግጋት የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለመግለጥ ቢረዱንም በክርስቶስ ካመንን በኋላ የበለጠ ክፋት ከመፈጸም በሞግዚትነት እንዲጠብቁን አንሻም። ብቁ የሚያደርገን መንፈስ ቅዱስ አለን።

ጳውሎስ በዚህ ስፍራ «ኃጢአት»ን ሳይሆን «መተላለፍ»ን የጠቀሰው ሆን ብሎ ነው። መተላለፍ የሚታወቀውን የእግዚአብሔር ትእዛዝ መጣስ ነው፥ ኃጢአት እግዚአብሔር የሰጠውን መመዘኛ ለማሟላት አለመቻል ነው። ይህም የተሳሳተ ተግባር በመፈጸም ወይም እግዚአብሔር የሚፈልገውን መልካም ተግባር ባለመፈጸም የሚገለጥ ነው (ለምሳሌ፥ ችግር የገጠመውን ሰው አለመርዳት)። በሮሜ 4፡15 ጳውሎስ ግልጽ ትእዛዝ እስኪመጣ ድረስ መተላለፍ እንዳልነበረ ገልጾአል። የእግዚአብሔርን ሕግጋት መተላለፋችንንና ከዚህም የተነሣ ኃጢአተኞች መሆናችንን ያወቅነው ሕግ በተሰጠ ጊዜ ነበር። እንዲያውም የእግዚአብሔርን ሕግጋት በምናውቅበት ጊዜ ሕግጋቱ ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር በመሥራት የበለጠ ኃጢአት እንድንፈጽም ያደርጉናል (ሮሜ 7፡7-18)። ስለሆነም በሲና ተራራ ላይ የተሰጠው ሕግ በጣም ጠቃሚ ዓላማ ነበረው። የሰው ልጅ ምን ያህል ኃጢአተኛና የእግዚአብሔር ጸጋና ይቅርታ የሚያሻው እንደሆነ አሳይቷል።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ፥ «ሕጉ የበለጠ ኃጢአት እንድፈጽም ካደረገኝ ክፉ አይደለምን?» ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል (ገላ. 3፡21-25)። ጳውሎስ ሕጉ መልካም እንደሆነ አበክሮ ይናገራል። አንድ ሰው ሕጉን መቶ በመቶ ለመፈጻም ቢችል ጽድቅን ሊያገኝ ይችል ነበር። ይህ በእርግጥ የማይቻል ነበር። ስለሆነም፥ መልካም የሆነው ሁለተኛው መንገድ ነበር። ይኸውም አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ የኃጢአት ባሕርያቸው እስረኞች በመሆናቸው የእግዚአብሔርን ድነት (ደኅንነት) በመልካም ሥራቸው ሊያገኙ የማይችሉ መሆናቸውን በማሳየት ሕጉ ሌላ የድነት (ደኅንነት) መንገድ እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል። በሥራቸው እግዚአብሔርን ለማስደሰት መጣራቸውን አቁመው በእምነት ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱና ብቸኛው የድነት ተስፋቸው በመሆን በመስቀል ላይ ያከናወነላቸውን ተግባር እንዲቀበሉ ረድቷቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለአማኞች ደንቦችንና ሕግጋትን ግልጽ ማድረግ በኃጢአት እንዳይወድቁ የሞግዚትነት ተግባር መፈጸምን የሚመስለው እንዴት ነው? ይህ አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ሰይጣን ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በተሳሳቱ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) ግልጽ ደንቦችን መስጠትን ያህል ቀላል ባይሆንም፥ ሰዎች ከውጫዊ ተግባራት ይልቅ ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ሰዎች ባላቸው ፍቅር ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ የበለጠ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? መ) ቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን ለእግዚአብሔርና ለእርስ በርሳቸው ልባዊ ፍቅር ከማሳየታቸው ይልቅ በውጫዊ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ የምታደርግ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። እንዲህ ከሆነ፥ ይህን ከውስጣዊ አመለካከቶች ይልቅ በውጫዊ ባሕርይ ላይ የማተኮር ሁኔታ ለመለወጥ ምን ሃሳብ ታቀርባለህ?

ሠ. ጳውሎስ የሕጉ ጊዜያዊ ሞግዚትነት እንዳበቃና በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች «የእግዚአብሔር ልጆች» እንደሆኑ ገልጾአል (ገላ. 3፡26-4፡7)

በገላትያ 3፡24፥ ጳውሎስ ሕጉ አንድ ልጅ አዋቂ እስኪሆን ድረስ የሚንከባከብ አገልጋይ እንደሆነ አስረድቷል። ይህንኑ አሳብ በገላትያ 4፡1-3 ይቀጥላል። ሕጻን ልጅ ወላጆቹ የደነገጉለት ዕድሜ እስኪደርስ ድረስ ሕጋዊ መብቶችና ውርስ የመቀበል ዕድል ስለሌለው ብዙም ከባሪያ አይሻልም።

ክርስቶስ መጥቶ ለኃጢአታችን ከሞተና እኛም ለደኅንነታችን በእርሱ ካመንን በኋላ ወደ ሙሉ አዋቂነት ደረጃ በመቀየር የእግዚአብሔርን በረከቶች ወርሰን ደስ እንሰኛለን። «ክርስቶስን ለብሰናል»፥ ይህም ክርስቶስ የሚያመጣቸውን የድነትና የአዲስ ባሕርይ በረከቶች እንዳገኘን ያመለክታል። ከዚህም የተነሣ አሁን እንደ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ደስ እንሰኛለን። አይሁዶች ወይም አሕዛብ፥ ወንዶች ወይም ሴቶች፥ ባሪያዎች ወይም ነፃ ሰዎች ይህንን ይቅርታ ሊያገኙ የሚችሉት በክርስቶስ በማመን ስለሆነ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የጎላ፥ የምጣኔ ሀብት ወይም የፆታ ልዩነት የለም። ሁሉም በእኩል ደረጃ የእግዚአብሔር ልጆች ሲሆኑ፥ ሁሉም የበሰሉና በእኩል ደረጃ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች የሚቀበሉ ይሆናሉ።

እንደ እግዚአብሔር ልጆች ከምንቀበላቸው ውርሶች አንደኛው መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ በማደር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይመሰክራል። ከእግዚአብሔር አብ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን ስለሚያደርግ፥ እግዚአብሔርን «አባ አባት» ብለን ልንጠራው እንችላለን። «አባ» የሚለው ቃል ልጆች አባታቸውን የሚጠሩበት የጥልቅ ፍቅርና ኅብረት ምልክት ነው።

ረ. ጳውሎስ ልጆች እንደ ባሪያዎች ሊኖሩ እንደማይችሉ ይገልጻል (ገላ. 4፡8-20)

የአሕዛብ ክርስቲያኖች በክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ከመሆናቸው በፊት የሐሰተኛ ጣዖታት ባሪያዎች ነበሩ። ይህም አይሁዶች የሕግ አጥባቂ ሃይማኖት ባሪያዎች እንደነበሩ ዓይነት ነው። ባመኑ ጊዜ ግን ነፃ ወጥተው የእግዚአብሔር ቤተሰብና ወራሾች ሆነዋል። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመለስና የተወሰኑ በዓላትንና ሌሎች የአይሁድ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን («ደካማ ሕጎችን») በመጠበቅ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት መሞከር ወደ ባርነት መመለስ ነበር።

ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖች መጀመሪያ ወንጌሉን በመሰከረላቸው ጊዜ እንዴት እንደ ወደዱት እንዲያስታውሱ ይለምናቸዋል። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ታሞ የነበረ ቢሆንም፥ የገላትያ ክርስቲያኖች ግን ይህ ሳይገድበው ወንጌሉን ስላመጣላቸው ይወዱትና ይሰሙት የነበረ ይመስላል። አንዳንድ ምሁራን “ዓይኖቻችሁን ለማውጣት ፈቃደኞች ነበራችሁ” የሚለውን አሳብ በመጠቀም ጳውሎስ የዓይን ሕመም እንደነበረበት ይናገራሉ። ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች የነበረውን ጥልቅ ፍቅር በመግለጽ፥ የወንጌሉን እውነቶች ለማካፈልና የአመለካከታቸውን ለውጥ ለማየት እንደሚመኝ ያስረዳል።

ሰ. ጳውሎስ የአጋርንና የሣራን የብሉይ ኪዳን ታሪኮች በመጠቀም ስለ ሕግና ጸጋ ያብራራል (ገላ. 4፡21-31)

ጳውሎስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ለማስደሰት የሕግን መንገድ እንደማይከተሉና የአብርሃምን አርአያነት እንደሚከተሉ በመግለጽ ክርክሩን ይቋጫል። ጳውሎስ ለዚህ ማብራሪያ የአይሁዶችን አተረጓጎም በመከተል የአጋርንና የእስማኤልን ባርነትና የሣራንና ይስሐቅን የተስፋ ቃል ልጅነት ያስረዳል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ያደረገውን ንጽጽር አጢን።

– አጋር፥ የሴት ባሪያ – ሣራ፥ ነፃ

– እስማኤል በተፈጥሯዊ መንገድ የተወለደ – ይስሐቅ በልዕለ ተፈጥሯዊ መንገድ ተወለደ

– አሮጌው ቃል ኪዳን – አዲሱ ቃል ኪዳን

– ምድራዊት ኢየሩሳሌም – ሰማያዊት ኢየሩሳሌም

– ይሁዳ – ክርስትና

አብርሃም ሁለት ዋነኛ ልጆችን ወልዷል። የመጀመሪያው እስማኤል የተወለደው ከባሪያይቱ አጋር ነበር፡፡ እስማኤል በአብርሃምና በአጋር መካከል በተደረገው ተፈጥሯዊ ግንኙነት የተወለደ በመሆኑ ልደቱ ተአምራዊ አልነበረም። አጋር ባሪያ ስለነበረች ከእርሷ የተወለደው እስማኤልም ባሪያ ነበር። አጋርና ልጁ ከአብርሃም ከተለዩ በኋላ ሕጉ በተሰጠበት በሲና ተራራ አካባቢ ኖረዋል። ሕጉ አሮጌ ኪዳን በመሆኑ እንደ አጋርና እስማኤል አይሁዶችን በባርነት ገዝቷል። ሕጉ ሰዎችን በባርነት የሚገዛውና በሥራ ላይ ያተኮረ የይሁዳ ሃይማኖት እንደሚገኝበት የኢየሩሳሌም ከተማ ነበር። ጳውሎስ አጋርና እስማኤል ሰዎች ሕግጋትን በመጠበቅ ለመዳን ያደረጉትን ጥረት እንደሚያሳዩ ገልጾአል። በሲና ተራራ የተሰጠውን የብሉይ ኪዳን ሕግ ይወክላሉ። እንዲሁም የእግዚአብሔርን ድነት (ደኅንነት) ለማግኘት ጥረት የሚደረግበትን ምድራዊ የሆነውን የአይሁዶች የአምልኮ ሥርዓት ያመለክታሉ።

ሁለተኛው ልጅ የሆነው ይስሐቅ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለሣራ በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት የተወለደ የተአምር ልጅ ነበር። ይስሐቅ ነፃና የአብርሃም ወራሽ ነበር። እንዲሁም አብርሃም የይስሐቅን መወለድ በእምነት እንደ ተቀበለ ሁሉ፥ አንድ ሰው ድነትን (ደኅንነትን) በእምነት የሚቀበልበት የአዲሱ ኪዳን ተምሳሌት ነበር። ይስሐቅ የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ተምሳሌት ነው። ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ተስፋ የሰጣት ስፍራ ነች።

ጳውሎስ በእነዚህ ሁለት ታሪኮች መካከል ክርስቶስን በእምነት በመቀበልና ሕግጋትን ለመጠበቅ በመሞከር መካከል ያሉትን ምስስሎች ተመልክቷል። ወደ ኋላ ተመልሶ ሕግን መከተል አብርሃም ከባሪያይቱ የወለደውን እስማኤልን እንደ መሆን ነበር። ይህ የበረከት ሳይሆን የባርነት ስፍራ ነበር። በክርስቶስ ማመን ቀን የነጻነት፥ የተስፋ፥ የተአምራዊ ልደትና የመንግሥተ ሰማይ ወራሽነት መንገድ ነበር። በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች የሣራ ልጆች ሲሆኑ፥ እንደ ይስሐቅ በተአምር የተወለዱ የድነትና የመንግሥተ ሰማይ የተስፋ ቃሎች ወራሾች ናቸው።

ለመሆኑ በተፈጥሯዊ መንገድ የተወለደው እስማኤል በልዕለ ተፈጥሯዊ መንገድ የተወለደውን ይስሐቅን ያስተናገደው እንዴት ነበር? እስማኤል ይስሐቅን የማሳደድና የመሳለቅ ተግባር ፈጽሞበታል። በተመሳሳይ ሁኔታ የሕግ ወይም የዓለማዊ ሥርዓቶች ባሪያ የሆኑት ሰዎች የገላትያን ክርስቲያኖች ያሳድዱ ነበር። የገላትያ ክርስቲያኖች አሮጌውን የሕግ ሥርዓት እንዲከተሉ የሚገፋፉአቸውን ሰዎች ምን ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር? አብርሃም እስማኤልን እንዳባረረው ሁሉ፥ እነርሱም እነዚህን ሰዎች ከክርስቲያኖች ኅብረት ማባረር ያስፈልጋቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች የእግዚእብሔርን ሞገስ፥ ይቅርታና ድነት (ደኅንነት) ለማግኘት የሚሞክሩባቸውን አንዳንድ መንገዶች ግለጽ። ለ) ይህ ባርነት የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) ፍርድ የሚገባቸው ኃጢአተኞች መሆናቸውን ተገንዝበው ወደ ክርስቶስ በሚመለሱና አንድን ተግባር በመፈጸም የእግዚአብሔርን ተቀባይነት ለማግኘት በሚሞክሩ ሰዎች መካከል ያለው የአመለካከት ልዩነት ምንድን ነው? መ) ይህ የነጻነት መንገድ የሚሆነው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጴጥሮስ በአንጾኪያ የወንጌሉን ግንዛቤ የሚያዛባ ተግባር በመፈጸሙ ጳውሎስ ተጋፈጠው (ገላ. 2፡11-21)።

ጳውሎስ ወደ ሶርያ አንጾኪያ ከተመለሰ በኋላ፥ ጴጥሮስ በዚያ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት ለመጎብኘት ወደዚያው ሄደ። በመጀመሪያ ካልተገረዙና «ከረከሱ» አሕዛብ ጋር መብላትን የሚከለክለውን የአይሁዶች ልማድ ጥሶ ጴጥሮስ በብሉይ ኪዳን ያልተፈቀደውን ምግብ በላ። ከዚያ በኋላ ግን አንዳንድ አጥባቂ የአይሁድ ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም መጥተው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንዳይረክሱ ከአሕዛብ ጋር ኅብረት እንዳያደርጉ አስተማሩ። ጴጥሮስም ጠቃሚ ሚና ከነበራቸው የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር ለመጋጨት ባለመፈለጉ ከአሕዛብ ጋር የሚያደርገውን ኅብረት አቆመ። አይሁዳዊ ልማዳቸውን ትተው ከአሕዛብ ጋር በግልጽ ኅብረት ማድረግ የጀመሩት እንደ በርናባስ ያሉ አንዳንድ አይሁዶችም ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ፈቀቅ ማለት ጀመሩ። ወዲያውም የአይሁድና የአሕዛብ ክርስቲያኖች በኅብረት ያመልኩባት በነበረችው የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን አይሁዶችና አሕዛብ ክርስቲያኖች ኅብረት የማያደርጉባት ሆነች። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በዘር ሐረጎች ተከፋፈለች።

ጳውሎስ ይህ ለአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለክርስትና የወደፊት ግሥጋዌ አደገኛ መሆኑን ተገነዘበ። አብያተ ክርስቲያናት አይሁዶችን በሚደግፉና አሕዛብን በሚደግፉ ወገኖች መከፋፈል ነበረባቸው? ወንጌሉ እነዚህን የመለያየት ግድግዳዎች አላፈረሰም? ይህ እግዚአብሔር አሕዛብን የሚቀበለው ባሕላቸውን ከለወጡ፥ ከተገረዙና የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ለመከተል ከፈለጉ ብቻ ነው ማለት ይሆን? እግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ሕዝብ ሰዎችን የሚቀበሉት ክርስቶስን በማመን ላይ በተመሠረተ አንድነት ሳይሆን በሥራ መመዘኛነት ነውን?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የተሳሳተ የወንጌል፥ የቤተ እምነቶች ወይም የዓለም አስተሳሰብ በማራመድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ክፍፍሎች ወደ አብያተ ክርስቲያኖቻችን እንዲገቡ የምናደርግባቸውን መንገዶች አብራራ። ለ) የተለያዩ ቤተ እምነቶች እርስ በርሳቸው ኅብረት ላለማድረግ ሲወስኑ ወይም የእነርሱ እምነት ከሌሉች እንደሚሻል ሲናገሩ ስለ ወንጌሉ ለዓለም የሚያስተላልፉት የተሳሳተ መልእክት ምንድን ነው? ሐ) አብያተ ክርስቲያናት በክርስቶስ የሚገኘውን አንድነት በማያሳዩበት ጊዜ የአማኞች ምስክርነት እንዴት እንደሚጠፋ ግለጽ።

ጳውሎስ በጠቅላላይቱ ቤተ ክርስቲያን ፊት ጴጥሮስን በመጋፈጥ ምላሽ ሰጥቷል። በርናባስን ወይም ሌሎች አይሁዶችን ሳይሆን ጴጥሮስን የተጋፈጠው ለምን ነበር? ጴጥሮስ ታላቅ መሪ በመሆኑ የእርሱ ግብዝነት (አጥባቂ አይሁዶች የሚሰነዝሩበትን ወቀሳ በመፍራት ተግባሩን መለወጡ) ሌሎች አይሁዶች እንዲሳሳቱ አድርጎ ነበር። ጴጥሮስ መሪ በመሆኑ በወንጌሉ እውነት የመመላለስ ኃላፊነት ነበረበት።

ጳውሎስ ከጴጥሮስ ጋር በአደባባይ ለምን ተፋጠጠ? የጴጥሮስ ተግባር ከጠቃሚ ሥነ መለኮታዊ ችግር የመነጨ ነበር። አሕዛብ በአይሁዶች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር? ይህ ጉዳይ ግልጽ መፍትሔ ካላገኘ የወንጌሉ ግንዛቤ መለወጥና ሰዎች አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትንና ድነትን (ደኅንነትን) ከማግኘታቸው በፊት ወደ አይሁድነት መለውጥ አለባቸው ብለው ማሰባቸው አይቀርም ነበር። የጴጥሮስ ተግባር የአይሁድ አማኞች ከአሕዛብ አማኞች እንዲለዩና የአሕዛብ አማኞች እምነት ድነትን ለማስገኘት ብቁ አይደለም ብለው በተግባራቸው እንዲናገሩ አድርጓቸዋል።

አንድ ኃጢአት የተፈጸመው በግለሰብ ደረጃ ከሆነ ማቴዎስ 18፡15-17ን በመጠቀም ንስሐንና ዕርቅን ለማምጣት መትጋት አለብን። ነገር ግን ኃጢአቱ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያካትት ከሆነ በአደባባይ መፍትሔ መሻት አለብን። ኃጢአቱ ይፋ ሊመጣ፥ ኑዛዜው በሰዎች ሁሉ ፊት ሊቀርብ፥ ሰዎች ሁሉ የሚመለከቱትና የሚረዱት ለውጥ ሊደረግ ይገባል። ጳውሎስ የተጋፈጠው ጴጥርስን ብቻ ቢሆን ኖር የመለየት ችግርና ድነት (ደኅንነት) በእምነት ብቻ የመገኘቱ ጉዳይ ለሌሎች ክርስቲያኖች ግልጽ አይሆንላቸውም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከጠቅላላው ቤተ ክርስቲያን ይልቅ በግል ልናስተካክላቸው የሚገቡ የኃጢአት ምሳሌዎችን ዘርዝር። ለ) በቤተ ክርስቲያን ፊት በይፋ ሊጋለጡና ሊወገዙ የሚገባቸው የኃጢአት ምሳሌዎችን ዘርዝር። ሐ) ኃጢአቶች በተለይም የመሪዎች ኃጢአቶች በይፋ ከመውጣት ይልቅ ከመእመናን በሚደበቁበት ጊዜ ሊከሰቱ የተመለከትሃቸውን አሉታዊ ነገሮች ግለጽ።

ጳውሎስ ጴጥሮስን የወቀሰው በሁለት ዐበይት ጉዳዮች ነበር። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ጴጥሮስን ስለ ግብዝነቱ ወቀሰው። ግብዝነት ሰዎችን ለማስደሰት ለንል ያልሆንነውን መስለን የምንቀርብበት ሁኔታ ነው። ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር እንዳይበላ የሚከለክለው ምንም ሥነ መለኮታዊ ምክንያት አልነበረውም። ቀደም ሲል ከአሕዛብ ጋር ይበላ ነበርና። ከአሕዛብ ጋር ኅብረት ማድረጉን ያቆመው ከኢየሩሳሌም የመጡትን የአይሁዳውያን ክርስቲያኖች ትችት በመፍራቱ ምክንያት ነበር። ሌሎችን በመፍራት ትክክለኛ የሆነውን ተግባር ከመፈጸም በምንቆጠብበት ጊዜ ሁሉ ግብዝነትን እናስተናግዳለን። እንዲሁም በሰዎች ፊት መንፈሳውያን መስለን ለመታየት ስንል አተገባበራችንን (ለምሳሌ፥ አዘማመራችንን፥ አጸለየያችንን፥ ሃሌ ሉያ ማለታችንን) የምንቀይር ከሆነ የግብዝነት ኃጢአት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ሌሎችን በመፍራት ወይም ለማስደነቅ የሚፈጽሟቸውንና በእግዚአብሔር ፊት የግብዝነት ኃጢአቶች የሚሆኑትን ነገሮች ዘርዝር።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ አሕዛብ የአይሁድን ልማዶች ይክተሉ ዘንድ ለማስገደድ ወንጌሉን ስለለወጠ ጴጥሮስን ወቀሰው። ጳውሎስ፥ «አንድ ሰው ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?» ብሎ ቢጠይቅ ኖሮ፥ ጴጥሮስ በክርስቶስ ማመን አለበት ብሎ ይመልስ እንደነበረ አይጠረጠርም፤ የሐዋ. 3፡19 አንብብ)። ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ጋር ኅብረት ለማድረግ በመፍቀዱ በተግባሩ የተለየ ስብከት እየሰበከ ነበር። ጴጥሮስ ለአሕዛብ፥ «እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆንን ከእኛ ጋር ኅብረት ለማድረግ ከፈለጋችሁ እንደኛ መሆን አለባችሁ። ልትገረዙና የሙሴን ሕግጋት ልትከተሉ ይገባል። ከእናንተ ጋር ኅብረት የምናደርገውና በእኩል ደረጃ የምንመለከታችሁ ያን ጊዜ ብቻ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን ድነትን ልታገኙ ብትችሉም ከእኛ ከአይሁዶቹ ዝቅ ያላችሁ “የሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች ናችሁ” እያለ ነበር። ይህም አሕዛብ እግዚአብሔርንና ሌሎች ክርስቲያኖችን ለማስደሰት ብለው ወደ አይሁድነት እንዲለወጡ ያደርግ ነበር። ይህ ደግሞ የሐሰት ወንጌል ነበር።

የውይይት ጥያቄ ዛሬ በተግባራችን የሐሰትን ወንጌል ልንሰብክ የምንችልባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለምሳሌ፥ በልሳንና ብልጽግናና ፈውስ፥ በመሳሰሉት ላይ የተጋነነ ትኩረት በመስጠት።)

ከገላትያ 2፡15-21 ውስጥ ጳውሎስ ለጴጥሮስና ለአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህሉን እንደተናገረና ምን ያህሉ ደግሞ የትምህርቱ ማጠቃለያ እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል። ነገር ግን ጳውሎስ ይህንን ከጴጥሮስ ጋር ያደረገውን የአደባባይ ፍጥጫ የተጠቀመው የወንጌሉን መሠረታዊ ምንነት ለመግለጽና ሰው በሥራ ሳይሆን በእምነት ብቻ እንደሚድን ለማሳየት ሳይሆን አይቀርም። የተቀረው የገላትያ መልእክት ክፍል ይህንኑ እውነት ያብራራል። የጳውሎስ አስተምህሮ የሚከተሉትን ነገሮች ያጠቃልላል።

ሀ. የአይሁድ ክርስቲያኖች ሕግጋትን በመጠበቅ ሊድኑ እንደማይችሉ ያውቃሉ። አለበለዚያ በክርስቶስ ማመን ለምን አስፈለጋቸው? ሌሎች አይሁዶች «የጸደቁት» በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናቸው እንጂ የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት በመጠበቃቸው አልነበረም። ይህ «ጽድቅ» የሚለው በጳውሎስ ጽሑፎች ውስጥ ዋነኛ ቁልፍ ቃል ነው። ይህም ዳኛው ተከሳሹን “ጥጥፋተኛ አይደለህም” ብሎ የሚያውጅበት የሕግ ቃል ነው። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በክርስቶስ የሚያምኑ አይሁዶች ዋናው ነገር በክርስቶስ ማመን እንጂ ሕግጋትን መጠበቅ እንዳልሆነ የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጾአል። እግዚአብሔርም ኃጢአተኛ አይደላችሁም በማለት የተቀበላቸውና ድነት ያጎናጸፋቸው በክርስቶስ ባመኑ ጊዜ ነበር። አንድ ሰው ሕግጋትን መጠበቅ ወይም መገረዝ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ያስገኝልኛል ብሎ ካሰበ በክርስቶስ ማመን አያስፈልገውም። ለዚህ ሰው ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነው። (ገላትያ 3-4 ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣል።)

ለ. ድነትን (ደኅንነትን) የሚያስገኘው በክርስቶስ ማመን እንጂ ሕግጋትን መጠበቅ ካልሆነ፥ ሰዎች በኃጢአታቸው በመቀጠል የእግዚአብሔርን ጸጋ አላግባብ አይጠቀሙም? ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) በእምነት ብቻ እንጂ በሥራ እንደማይገኝ ባስተማረ ጊዜ ሰዎችን ያሳሰባቸው ይሄ ነበር። ምንም እንኳን ሕግጋትን በመጠበቅ እግዚአብሔርን ለማስደሰት መሞከሩ ድነት (ደኅንነትን) ሊያስገኝ እንደማይችል ቢታወቅም፥ በክርስቶስ ባመንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን ሆነናል። አሁን የክርስቶስ የትንሣኤ ሕይወት የእኛ ነው። አሁን ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በውስጣችን ይኖራል። አመለካከታችን ሊለወጥና ባለማቋረጥ በክርስቶስ ታምነንና ተደግፈን ልንመላለስ ይገባል። እምነታችንን ተግባራዊ ስናደርግና በክርስቶስ ስናምን ክርስቶስ የአብን ፈቃድ ለመፈጸም አሁን በእኛ ውስጥ እንደሚኖር ሁሉ የተለየ ሕይወት እንኖራለን።

ጳውሎስ ከሚወዳቸው አገላለጾች አንዱ «በክርስቶስ ውስጥ» የሚል ነው። ጳውሎስ የክርስቲያኑን ሕይወትና ድነት (ደኅንነት) በሚያብራራበት ጊዜ፥ በድነት ግዜ ክርስቲያኑ በምሥጢራዊ መንገድ ከክርስቶስ ጋር ስለሚዋሃድ በክርስቶስ ላይ የደረሰው ሁሉ በክርስቲያኑም ላይ እንደሚደርስ ተዓነዘበ። (ለምሳሌ፥ ከእናቱ ጀርባ ላይ በአንቀልባ የታዘለ ሕጻን እርሷ ወደሄደችበት ስፍራ ሁሉ ይሄዳል።) ስለሆነም አዲስ ኪዳንን በምንመለከትበት ጊዜ ከክርስቶስ የመስቀል ሞት ጋር መተባበራችንን እንመለከታለን። ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር መሰቀሉንና መሞቱን ገልጾአል። (አሮጌ ተፈጥሮው ሞቷል ሕግን በመጠበቅ ከእግዚአብሔር ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርገው ሙከራ ከስሟል። በሕይወቱ ላይ ይነሣ የነበረው የኃጢአት ኃይል ሞቷል) ክርስቶስ ከሞት ሲነሣ ክርስቲያኑም አብሮት ይነሣል። የክርስቶስ ትንሣኤ ለአካላዊ ትንሣኤያችን ዋስትና ይሰጣል። እንዲሁም እንደ አዲስ ፍጥረት የምንመላለስበትን ዘላለማዊ ትንሣኤ ያስገኛል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ እኛም ወደ ሰማይ ዐርገን በመንፈሳዊ ሁኔታ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጠናል (ኤፌ. 26)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ድነትን የምናገኘው በክርስቶስ በማመናችን እንጂ በምናከናውነው ተግባር አይደለም የሚለው ትምህርት ምን ያህል የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እንደሚያስፈራ ግለጽ፡፡ የሚፈሩት ለምንድን ነው? ለ) ከክርስቶስ ጋር በመንፈስ ከተነሣን ምን ዓይነት ለውጥ ይጠበቅብናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ወንጌሉ ከእግዚአብሔር እንደ መጣና በሐዋርያት እንደ ጸደቀ ያሳያል (ገላ. 1፡11-2፡10)።

የሐሰት አስተማሪዎቹ ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ እንዳልሆነ፥ መልእክቱም አንድም ራሱ የፈጠረው አሊያም ወደ እርሱ በሚተላለፍበት ጊዜ እንደ ተበረዘ በመግለጽ ይከስሱት ነበር። ምናልባትም ደግሞ በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሐዋርያት በማይቀበሉት መንገድ እንደ ለወጠው ገልጸው ነበር። ጳውሎስ ንጹሑን ወንጌል የሚያስተምር እውነተኛ ሐዋርያ መሆኑን በመግለጽ ለዚህ ክስ ምላሽ ለመስጠት ፈለገ። ሐዋርያት እንኳን ትምህርቱን አጽድቀውለት ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ እግዚአብሔር ለሐዋርያነት ከጠራው ጊዜ አንሥቶ ለገላትያ ሰዎች እስከሚጽፍበት ጊዜ ድረስ ያሳለፈውን ሕይወት ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። የጳውሎስ ክርክር በሦስት ዐበይት ነጥቦች ላይ የተመሠረተ ነበር።

 1. ጳውሎስ የወንጌል መልእክቱን ከክርስቶስ በቀጥታ በመገለጥ ተቀብሏል (ገላ 1፡11-12)። ጳውሎስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ባይከተለውም በተአምራዊ መንገድ ከሞት ከተነሣው ክርስቶስ ጋር ተገናኝቶ የወንጌሉን መልእክት ተቀብሏል። ስለሆነም የሐሰት አስተማሪዎች ከሚሉት በተቃራኒ ጳውሎስ መልእክቱን አልፈጠረውም። ወይም የተበረዘ መልእክት አልተቀበለም።
 2. ጳውሎስ ወንጌሉን ከሐዋርያት ሊቀበል እንደማይችል ያብራራል (ገላ. 13-24)። ከክርስቶስ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ጳውሎስ እንደ ሐሰተኛ አስተማሪዎቹ ለብሉይ ኪዳን ቀናዒ ነበር። ለዚህም ነበር ቤተ ክርስቲያንን ያሳደደው፡፡ ስለዚህ፥ ጳውሎስ እንደ የሐሰት አስተማሪዎቹ ሁሉ ሕግጋትን ስለመከተል ጽኑ አቋም ይዞ ነበር ያደገው። ነገር ግን ጳውሎስ በእግዚአብሔር ተጠራ፤ ክርስቶስም ራሱን ገለጠለት። ጳውሎስ ይህን ሲል በደማስቆ መንገድ ከክርስቶስ ጋር ስለተገናኘበት ራእይ መናገሩ ነበር። ጳውሎስ ድነትን (ደኅንነትን) ካገኘ በኋላ የሐዋርያት ደቀ መዝሙር ለመሆን ወደ ኢየሩሳሌም አልሄደም። ነገር ግን ወደ ዓረቢያ ከሄደ በኋላ ወደ ደማስቆ በመመለስ ድነት (ደኅንነት) በእምነት ብቻ እንደሚገኝ የሚያስረጻውን ወንጌል ሰበከ። ጳውሎስ በመጨረሻው ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ከጴጥሮስና የክርስቶስ ወንድም ከሆነው ያዕቆብ ጋር ምሥጢራዊ ስብሰባ ያደረገው ደኅንነቱን ካገኘ ከሦስት ዓመታት በኋላ ነበር። ከዚያ ከየትኛቹም ሐዋርያት ርቆ ወደ ሶርያና ኪልቅያ አውራጃዎች ሄደ። ይህም ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን እንዳይታወቅ አድርጎታል። ስለ ተአምራዊ ለውጡ ከመስማታቸው በቀር ሌላ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይህም ጳውሎስ መልእክቱን ከሐዋርያት እንዳላገኘ ያሳያል።
 3. ጳውሎስ የኢየሩሳሌም ሐዋርያትን ድጋፍ አግኝቷል (ገላ. 2፡1-10)። ጳውሎስ ምናልባትም ድነትን (ደኅንነትን) ካገኘ ከ14 ዓመታት በኋላ ኢየሩሳሌምን እንደገና የጎበኘ ይመስላል። ምንም እንኳ አንዳንድ ምሁራን ይህ ጉብኝት በኢየሩሳሌም ጉባኤ ወቅት የተደረገ መሆኑን ቢናገሩም (የሐዋ. 15)፥ ጳውሎስ የሄደው በኢየሩሳሌም ረሃብ በተነሣ ጊዜ የርዳታ ገንዘብ ለማድረስ ይመስላል (የሐዋ. 11፡27-30)። ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ከሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ሐዋርያት ጋር በግል ተገናኘ፡፡ ቲቶንም ይዞ ነበር የመጣው። ቲቶ ያልተገረዘ አሕዛብ ክርስቲያን ነበር። ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) እንደ ግርዛት ባሉት ውጫዊ ነገሮች ሳይሆን በክርስቶስ ሞት በማመን ብቻ እንደሚገኝ ስለሚያስረዳው ትምህርቱ ለአይሁድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አብራርቷል። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጳውሎስ ልዩ የአሕዛብ ሐዋርያ መሆኑን ተገንዝበው እውቅና ሰጡት። ለመልእክቱ እውቅና በመስጠት ቲቶን እንዲገረዝ ሳያስገድዱ ቀሩ። የጠየቁት ነገር ቢኖር እምነታቸውን በሥራ ላይ የማያውሉትን እነዚህን ክርስቲያኖች ለችግረኞች በመስጠት ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያሳዩ ጳውሎስ እንዲያስተምራቸው ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት ሄዶ ወንጌሉን በሰበከ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና የኢየሩሳሌም ሐዋርያት የከለከሉትን ትምህርት አልነበረም ያስተማረው። ነገር ግን መሪዎቹና ሐዋርያቱ አሕዛብ ሳይገረዙ ወይም ብሉይ ኪዳንን ሳይጠብቁ በእምነት ሊድኑ እንደሚችሉ የሚያስረጻውን ትምህርት አጽድቀው ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መግቢያ (ገላ. 1፡1-10)

ጥላሁን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ታዋቂ ወጣቶች አንዱ ነበር፡ በሰንበት ትምህርት ቤት መምህርነትና የኳዩር ዝማሬን በመሳሰሉት የተለያዩ አገልግሎቶች ይሳተፍ ነበር። ጥላሁን ይህን ታዋቂነት ስለወደደ ሰዎች ያሚፈልጓቸውን ነገሮች ማድረጉን ቀጠለ። አብዛኞቹ ወጣቶች ስሜታዊ አምልኮን ስለሚወዱ ጥላሁን ፕሮግራም ስሚመራበት ጊዜ ሁሉ ምእመናኑ ጮክ ብሎ ስሜታዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ያበረታታል። አንዳንድ አባላት የፈውስ አገልግሎት በመፈለጋቸው ጥላሁን ይህንኑ አዘጋጀ። በሰዎች ዘንድ ማራኪና ተወዳጅ ሆኖ የነበረው ነገር ጥላሁን የሚያምንበትና የሚለማመደው ነገር ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ገላ. 1፡10 እንብብ። እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰዎችን ለማስደሰት ስለ መሞከር ጳውሎስ ምን ማለጠንቀቂያ ሰጠ? ሰዎችን ለማስደሰት በምንሞክርበት ጊዜ ማንን እናገለግላለን? ለ) እግዚአብሔርን ለማስደሰት መሞከር አንድን ሰው ታዋቂና ተወዳጅ ላያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? ሰዎችን ለማስደሰት መሞከር እግዚአብሔርን እንዴት ሊያስቆጣ እንደሚችል እንዳንድ ምሳሌዎችን ስጥ። ሐ) በተለይ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሰዎችን ከማስደሰት ይልቅ እግዚአብሔርን ለማስደሰት መሥራት ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? መ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የምእመናንን ፍላጎቶች ማዳመጥ አስፈላጊ የሚሆነው እንዴት ነው?

ብዙዎቻችን የጥላሁን ዓይነት ችግር አለብን። ሰዎችን ለማስደሰት እንፈልጋለን። ስለሆነም እግዚአብሔርን ማስደሰታችንን ሳናረጋግጥ ሰዎችን በማስደሰቱ ላይ አጽንኦት እንሰጣለን። ባሕላችን ስሕተት ቢሆንም እንኳ ኳየራችን የሚያደርገውን፥ ሌሎች ተማሪዎች በትምህርት ቤት የሚሆኑትን፥ ወዘተ… እንድንከተል ያስተምረናል። ተወዳጅነትን ለማትረፍና በቡድኑ ውስጥ ለመታቀፍ ስንል ይህንኑ እናደርጋለን። ሰዎች ክርስቶስን ለማስከበር ከልባቸው በሚጥሩበት ቡድን ውስጥ ካለን ይሄ ብዙም አሳሳቢ አይሆንም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የምእመኖቻቸውን ፍላጎቶችና ምርጫዎች ማወቃቸውም ጠቃሚ ነው። ታዋቂነት ወይም መንፈሳዊ ለመሆን መፈለግ እግዚአብሔር ከሚፈልገው ጎዳና የሚመልሰን ከሆነ፥ የክርስቶስ ሳይሆን የሰዎች ባሪያዎች ሆነናል ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ አብዛኛው ሕዝብ ትክክል እንዳልሆነ እንረዳለን። አብዛኛው ሕዝብ ትክክለኛ ያልሆኑ ምክንያቶች ስላሉት የተሳሳቱ ተግባራትን ይፈጽማል። አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔር ሰዎች እግዚአብሔርን ይታዘዙ ዘንድ ከአብዛኛው ሕዝብ መንገድ ተለይተው ብቻቸውን እንዲቆሙ ተጠርተዋል። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔር ባሪያዎች ነበሩ። ፊንሐስ ዘመዱን ገድሏል (ዘኁል. 25፡1-13)። ዳዊት ብቻውን ጎልያድን ተጋፍጧል። ኤልያስ ብቻውን የሕዝቡን ርኩሰት ተቃውሟል። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስትናን የሥራ ሃይማኖት ለማድረግ የተደረገውን ጥረት ተቃውሟል። እንዲያውም ጳውሎስ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ሐዋርያ የነበረ ጴጥሮስ ስሕተትን በፈጸመ ጊዜ ገሥጾታል። ጓደኛውና የወንጌሉ ሥራ ባልደረባ የነበረውን በርናባስንም ተገዳድሮታል። እግዚአብሔር ቀዳሚ ጉዳያችን «ሰው ምን ይለኛል» ሳይሆን፥ «እግዚአብሔር ምን ይለኛል» የሚል እንዲሆን ይፈልጋል።

ጳውሎስ የጥንቱን ዘመን የደብዳቤ አጻጻፍ በመከተል፥ የመልእክቱ ጸሐፊ መሆኑን ይናገራል። ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ ሌሎች ጸሐፊዎችን ስለሚጠቀም ጠቅላላውን መልእክት ስለ መጻፉ እርግጠኞች አይደለንም። (ለምሳሌ፥ ሮሜ 16፡22ን ተመልከት።) በገላትያ 6፡11 ጳውሎስ፦ «እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ» ብሏል። ይህ ፊርማውንና የመደምደሚያ ሃሳቡን ሊያመለክት ይችላል፤ ወይም ደግሞ ጳውሎስ የገላትያን መልእክት በገዛ እጁ መጻፉን ሊያሳይ ይችላል።

የጳውሎስ መግቢያ ብዙውን ጊዜ በመልእክቱ ውስጥ ሊያተኩር የፈለገውን አሳብ ያሳያል። ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክት መግቢያ ውስጥ በሐዋርያነት ምንጭ ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። በገላትያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚሠሩ የሐሰት አስተማሪዎች ጳውሎስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አብሮት ስላልነበረ እውነተኛ ሐዋርያ አይደለም ይሉ ነበር። ከሞት የተነሣውን ጌታ ካለማየቱም በላይ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያት ስላልመረጡትና ስላልላኩት ጳውሎስ ሐሰተኛ ነው ብለው የሐሰት አስተማሪዎቹ ተናገሩ። በገላትያ 1-2 በዚህ ክስ ላይ በማተኮር መልእክቱን በቀጥታ ከክርስቶስ እንደ ተቀበለና ከዚህም የተነሣ እውነተኛ እንደሆነ ያሳያቸዋል። ጳውሎስ ትምህርቱን በሚያስተዋውቅበት ጊዜ ሐዋርያ ነኝ የሚለው ሐዋርያነቱና መልእክቱ እንደ ጴጥሮስ ካሉ ዝነኛ ሰዎች ወይም እንደ ሐዋርያት ካሉ ቡድኖች ስለመነጨ አለመሆኑን ያስረዳል። የሐዋርያነት ጥሪው በቀጥታ ከክርስቶስ ነበር የመጣው።

መልእክቱ የተላከው በገላትያ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት» ነበር። አብዛኞቹ የጳውሎስ መልእክቶች የሚላኩት በከተማ ውስጥ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ወይም ግለሰቦች ነበር። ይህ መልእክት ግን በገላትያ አውራጃ ውስጥ ለሚገኙ አያሌ አብያተ ክርስቲያናት ሳይላክ አልቀረም።

ጳውሎስ ሰላምታውን ካቀረበ በኋላ በሰላምታው ውስጥ የወንጌሉን ቁም ነገር (አስኳል) ያብራራል። ክርስቲያኖች ጸጋና ሰላም የሚያገኙት ክርስቶስ ራሱን ለኃጢአታቸው መሥዋዕት አድርጎ ስለሰጣቸው ነው። የክርስቶስ ሞት መንፈሳዊ ድነትን (ደኅንነትን) ከማስገኘቱም በላይ «ከአሁኑ ክፉ ዘመንም» ያድነናል። ለእግዚአብሔር ቅዱሳን እንሆን ዘንድ ተለይተናል።

የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች፥ ታሪክ ሁለት ዘመናትን እንደሚያካትት ያስባሉ። አዳምና ሔዋን ኃጢአትን በፈጸሙ ጊዜ የተጀመረ «የአሁኑ ክፉ ዘመን» አለ። ይህ ዘመን ክርስቶስ ለመግዛት ሲመለስና ኃጢአትን ሲደመስስ ከፍጻሜ ይደርሳል። በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞትና በመንግሥቱ ጅማሬ የተጠነሰሰው «ወደፊት የሚመጣ ዘመን» አለ (ማቴ. 12፡32)። ክርስቶስ ወደ ምድር ተመልሶ በፍጹማዊ ሥልጣን በሚገዛበት ጊዜ ዘላለማዊ መንግሥቱ ይጀመራል። በዘላለሙ መንግሥት ኃጢአት ወይም በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ዓመፅ አይኖርም፡፡ አሁን ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ በሚገዛበት ጊዜ ይህንኑ መንግሥት «እንቀምሳለን»። ወደፊት በዘላለሙ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር በምንነግሥስት ጊዜ ይህንኑ ሊመጣ ያለውን ዘመን ሙሉ ለሙሉ እንቋደሰዋለን።

ከሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች በተቃራኒ፥ በገላትያ መልእክት ውስጥ አንድም የምስጋና ቃል አልተጠቀሰም። ነገር ግን ጳውሎስ ከመበሳጨቱ የተነሣ በገላትያ ክርስቲያኖች ላይ ቁጣና ንዴትን ወዲያውኑ ማሳየት ይጀምራል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከእውነተኛው ወንጌል ወደ ሌላ የሐሰት ወንጌል ተመልሰው ነበር። ወደ እግዚአብሔር መድረስ የሚቻለው በተለያዩ መንገዶች አማካኝነት ሳይሆን በአንድ እውነተኛ ወንጌል ብቻ ነው። በእውነተኛው ወንጌል ላይ የሚጨምር፥ የሚቀንስ ወይም የተለየ ወንጌል የሚያቀርብ ሁሉ ሰዎችን ሊያድን የማይችለውን ሐሰተኛ ወንጌል ያስተምራል። ጳውሎስ እጅግ የተቆጣው ሰዎች ለዘላለም ወደ መንግሥተ ሰማይ ወይም ሲኦል የሚሄዱበት ዕድል የሚወሰነው እውነተኛ ወይም ሐሰተኛ ወንጌል በማመናቸው ምክንያት በመሆኑ ነው። ስለሆነም መልአክ ከሰማይ ቢመጣና እርሱ ራሱም ቢለወጥ እንኳ ሌላ ወንጌል የሚሰብኩትን ሰዎች እንዳይሰሙ አስጠንቅቋቸዋል። ጳውሎስ የሐሰት ትምህርት የሚያስፋፉ ሰዎችን ሌሎችን ወደ ሲኦል እየሰደዱ በመሆኑ ራሳቸው ሲኦል ቢወርዱ እንደሚወድ በቁጣ ተናግሯል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ያሻቸውን እንዲያምኑ ዝም ብሎ ከመተው ይልቅ የወንጌሉን እውነት በጽኑ አቋም መከላከል የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) ይህን ማድረግ ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) የሐሰት ትምህርት እንዲስፋፋ አንከላከል ብንፈቅድ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ስለመሆናችን ወይም ለሰዎች ስላለን በጎ አስተሳሰብ ምን ያሳያል?

ጳውሎስ ቀላሉን መስመር ተከትሎ እንደ ሐሰት አስተማሪዎቹ ሰዎችን ለማስደሰት ሲል እምነቱን ወይም ወንጌሉን ለመለውጥ አልፈለገም። ሰዎችን ቢያስቆጣም እንኳ ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር ሐዋርያ ለማገልገል ቆርጧል። ከዚህ ውጭ የሆነ ምንም ዓይነት ምርጫ ሰዎች ወደ ሲኦል እንዲወርዱና እርሱም የሰዎች ባሪያ እንዲሆን ያደርገው ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የገላትያ መልእክት ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር፣ እና አስተዋጽኦ

 1. የገላትያ መልእክት ምናልባትም ጳውሎስ ከጻፋቸው እጅግ ጠንካራና ቁጡ ደብዳቤዎች ሁሉ ሳይልቅ አይቀርም። ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ወንጌሉን ለመመስከር ሲል በድንጋይ ከተወገረና ከሞት አፋፍ ላይ ከተረፈ በኋላ እውነተኛውን ወንጌል ትተው የሐሰት ትምህርቶችን በመከተል ላይ መሆናቸውን መስማቱ በጥልቀት አቆሰለው። ከሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች በተቃራኒ፥ በገላትያ መልእክት ውስጥ ምንም ዓይነት የማበረታቻና የምስጋና ቃላት አልተካተቱም። ጳውሎስ የመልእክቱ ጸሐፊ መሆኑን ከነገራቸው በኋላ በቀጥታ ወደ ተግሣጽ አምርቷል። ጳውሎስ እንደ «የማታስተውሉ» (ገላ. 3፡1)፥ «አዚም የተደረገባችሁ» (ገላ. 3፡1፥ «የተረገማችሁ» (ገላ. 1፡8-9)፥ «የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ» (ገላ. 5፡12)፥ ወዘተ… የሚሉ ጠንካራ አገላለጾችን ሰንዝሮባቸዋል። ለገላትያ ሰዎች የነበረው ፍቅርና መገደድ፥ እንዲሁም ለወንጌሉ እውነት የነበረው ጽኑ ስሜት ወደ ስሕተት ከሚነዳቸው ከማንኛውም ነገር ጋር እንዲታገል አድርጎታል።
 2. ይህ የጳውሎስ የመጀመሪያው መልእክት ነበር። ለረዣዥም መልእክቶች ቅድሚያ በመሰጠቱ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከገላትያ ቀደም ብለው ከሰፈሩት የሮሜና፥ የ1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ መልእክቶች በፊት ነበር የተጻፈው።
 3. ስለ ሰው ድነት (ደኅንነት) ወይም አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ስለሚመሠርትበት ሁኔታ የሚያስተምሩ በመሆናቸው የገላትያና የሮሜ መልእክቶች ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል። ነገር ግን የሮሜ መልእክት ነገረ መለኮታዊውን እውነት እንደ የክፍል ውስጥ ትምህርት ሲያቀርብ፥ ገላትያ በመጋቢነት ላይ በማተኮር ጠንካራ አገላለጾችን ይጠቀማል። ለዚህም ምክንያቱ የወንጌሉ ጠላቶች የእግዚአብሔርን መንጋ ማጥቃታቸውና ክርስቲያኖችን ለአደጋ ማጋለጣቸው ነበር።

የገላትያ መልእክት መዋቅር

አብዛኛዎቹ የጳውሎስ አጫጭር መልእክቶች ሁለት መሠረታዊ ክፍሎችን ያካትታሉ። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ቁልፍ ነገረ መለኮታዊ እውነቶችን የሚያቀርብባቸው ክፍሎች አሉ። ብዙዎቻችን ስለ እውነት አጥልቀን ለማሰብ አንፈልግም። አምልኮ ፥ ምስጋና ወይም አገልግሎት ደስ ያሰኘናል። ጳውሎስ ግን ሁልጊዜም ትክክለኛ አምልኮና ተግባራት በትክክለኛ እውቀት ላይ እንዲመሠረቱ አጥብቆ ይመክራል። የምናምነው አሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ልናመልክና ልናገለግል አንችልም። ገላትያ 1-4 በቀዳሚነት የመሠረተ እምነት ትምህርቶችን ያቀርባል። ጳውሎስ ሰዎች በሚያከናውኗቸው ተግባራት ሳይሆን በክርስቶስ በማመናቸው ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንደሚኖራቸው ያብራራል።

የውይይት ጥያቄ ሀ) ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሐሰት አስተማሪዎች የሚቃወሟቸውን አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች ዘርዝር። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ ማግኘት ለምን ያስፈልጋል? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች እውነትን ችላ እያሉ እንደ አምልኮ ባሉት ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩት ለምንድን ነው? ሐ) አምልኳቸውና ተግባራቸው እንደ እግዚአብሔር ቃልና ፈቃድ ይሆን ዘንድ ክርስቲያኖች ሁሉ በእውነት ላይ እንደ ተመሠረቱ መሪዎች በምን ሊያረጋግጡ ይችላሉ?

ሁለተኛው የጳውሎስ መልእክት ዓቢይ ክፍል በተግባራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ይህም እንደ ክርስቲያኖች እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው። ጳውሎስ በተግባር እስካልተገለጠ ድረስ እምነት ዋጋ እንደ ሌለው ያስረዳል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1 ላይ እንደ ገለጸው እውቀት ያስታብያል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እያውቁ ተግባራዊ አለማድረጉ ለክርስቲያኖች አደገኛ ነው። በዘመናችን ያሉት ክርስቲያኖች አምልኮን እየወደዱ በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተግባራዊ አያደርጉም። ገላትያ 5-6 እግዚአብሔርን በሚያስደስት መንገድ ስለ መመላለስ ተግባራዊ ጉዳዮችን ያነሣል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እውነትን በማወቅና በአምልኮ መሳተፍ ቀላል ሆኖ ሳለ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ማኅበረሰቡን በሚለውጥ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ከባድ የሚሆንባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ክርስቲያኖች በማኅበራዊ ሕይወታቸው፥ በሥራ፥ ከመንግሥት ወይም ከድሆች ጋር ባላቸው ዝምድና ተግባራዊ የማያደርጓቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) ሰዎች እምነታቸውን በኅብረተሰቡ ውስጥ በተግባር እንዲያሳዩ ለመርዳት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል?

የገላትያ መልእክት አስተዋጽኦ

 1. መግቢያ (ገላ. 1፡1-10)
 2. ጳውሎስ ወንጌሉ ከእግዚአብሔር እንደ መነጨና ሌሎችም ሐዋርያት እንዳጸደቁት ይናገራል (ገላ. 1፡1-2፡10)

ሀ. ጳውሎስ ወንጌሉን በመገለጥ በቀጥታ ከእግዚአብሔር ተቀበለ (ገላ. 1፡11-12)።

ለ. ጳውሎስ ወንጌሉን ከኢየሩሳሌም ሐዋርያት እንዳልተቀበለ ያስረዳል (ገላ. 1፡13-24)።

ሐ. የኢየሩሳሌም ሐዋርያት የጳውሎስን ወንጌል አጽድቀዋል (ገላ. 2፡1-10)።

 1. ጴጥሮስ በአንጾኪያ ስለ ወንጌሉ የተሳሳተ ግንዛቤ የሚፈጥር ተግባር በመፈጸሙ ጳውሎስ ተጋፈጠው (ገላ. 2፡11-21)።
 2. ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንደሚገኝ ገልጾአል (ገላ. 3-4)።

ሀ. ድነት (ደኅንነት) በእምነት እንደሚገኝ የሚያሳይ ከገላትያ ክርስቲያኖች ልምምድ የተወሰደ ማረጋገጫ (ገላ. 3፡1-5)።

ለ. ድነት (ደኅንነት) በእምነት እንደሚገኝ የሚያሳይ የብሉይ ኪዳን ማረጋገጥ (ገላ. 3፡6-4፡31)።

 1. ጳውሎስ የእምነት ሕይወት ምን እንደሚመስል ያብራራል (ገላ. 5፡1-6፡10)።

ሀ. የእምነት ሕይወት ለንጽሕናና ሌሎችን ለማገልገል የሚያስችል ነጻነት ያስገኛል (ገላ. 5፡1-15)።

ለ. የእምነት ሕይወት የኃጢአት ተፈጥሯችንን የሚያሸንፍና የመንፈስ ፍሬን የሚያፈራ መንፈስ ቅዱስን ያስገኛል (ገላ. 5፡16-6፡10)።

 1. መደምደሚያ (ገላ. 6፡11-18)

የገላትያ መልእክት ዓላማ

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) «ወንጌል» ማለት ምን ማለት እንደሆነ አብራራ። ለ) አንድ ሰው ለመዳን ሰምቶ ስለሚያምነው ወንጌል በምናብራራበት ጊዜ ልናካትታቸው የሚገቡን እውነቶች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) ስለ ወንጌሉ ምንነትና ሰዎች ሰምተው ይድኑ ዘንድ ስለሚቀርበው ምስክርነት አንድ ክርስቲያን ጥርት ያለ ግንዛቤ መጨበጥ የሚያስፈልገው ለምን ይመስልሃል?

የመጀመሪያው ዓላማ፡ ጳውሎስ ወንጌሉን በርዟል ለሚለው ክስ ምላሽ ለመስጠት። ጳውሎስ የእውነተኛ ወንጌልን ምንነት ለገላትያ ክርስቲያኖች አብራርቷል። እግዚአብሔር እንድን ሰው የሚቀበለው የተወሰኑ ውጫዊ ሕግጋትን ስለጠበቀ ሳይሆን፥ በክርስቶስ በማመኑ ነው። ጳውሎስ በመልእክቱ መልካሙ ዜና የሚያርፈው በክርስቶስ ሞትና ግለሰቡ ክርስቶስ ለኃጢአቱ እንደሞተ በሚያምንበት ጊዜ በሚሰጠው ጽድቅ (ከበደል መንጻት) ላይ እንዲሆነ ገልጾአል። በዚህ ቀላል እውነት ላይ በመጨመር፥ ሰዎች እንዲገረዙ ወይም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት እንዲጠብቁ መጠየቁ በወንጌል ላይ ሌላ ነገር መጨመር ይሆናል። ሰዎች በክርስቶስ እናምናለን ቢሉም እንኳ በእምነት መመዘኛ ላይ ሰብአዊ ተግባራት ከተጨመሩ መልካሙ የምሥራች ወንጌልነቱን ያጣል። ይህም እንደ ሌሎች የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ በሥራ ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት ይሆናል። አንድ ሰው ለድነት (ደኅንነት) በራሱ ሥራ ላይ በሚታመንበት ጊዜ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መንገድ በመምረጥ የክርስቶስ ሞት በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋርያት ሥራ 5፡1-35 አንብብ። ሀ) በኢየሩሳሌም የነበሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለምን በጉባኤ እንደ ተሰባሰቡ ግለጽ። ለ) በጊዜው የተነሣው መሠረታዊ የነገረ መለኮት ጥያቄ ምን ነበር? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለዚሁ ጉዳይ ምን ወሰኑ? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አሕዛብ እንዲጠብቁ የጠየቁት ምን ምን ሕግጋትን ነበር? እነዚህን ሕግጋት ለምን ሰጧቸው?

የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የታገለችው ከሁሉም የከበደ ጥያቄ፥ «አንድ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት?» የሚለው ሳይሆን አይቀርም። አይሁዶች ከ1000 ለሚልቁ ዓመታት እንደ ግርዛት፥ የቤተ መቅደስ አምልኮ፥ አመጋገብ ላሉት ጉዳዮች ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሏቸው ግልጽ መመሪያዎች ነበሯቸው። ከጳውሎስ በፊት በነበሩት 200 ዓመታት ውስጥ የአይሁድ መሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ለተጠቀሱት ሕግጋት ሌሎች በመቶዎች ሕግጋት ደንግገው ነበር። እነዚህ ተጨማሪ ሕግጋት እንድ መንፈሳዊ የሆነ አይሁዳዊ ሰው እንዴት ሊኖር፥ ምን ሊለብስና ምን ሊያደርግ እንደሚገባው ይዘረዝራሉ። የእነዚህ ተጨማሪ ሕግጋት ዓላማ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ማብራሪያ ማቅረብና በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት እንደሚተገበሩ ለማሳየት ነበር። ለምሳሌ ያህል፥ ብሉይ ኪዳን ሰዎች በሰንበት ቀን እንዳይሠሩ አዟል። ምንም እንኳ በዚህ ትእዛዝ ውስጥ በዕልተ ሰንበት ውስጥ ስለተፈቀደውና ስለተከለከለው ሥራ አንዳንድ መመሪያዎች ቢሰጡም፥ ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች ጥያቄዎችን ያስነሡ ነበር። ለምሳሌ፡ በሰንበት ቀን አንድ ሰው ስንት ኪሎ ሜትር እንዲሄድ ይፈቀድለታል? ስለሆነም የሃይማኖት መሪዎቹ በሰንበት አንድ ሰው ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንደሚችል ወሰኑ። ከዚያ ርቆ ከሄደ ተግባሩ እንደ ሥራ ይቆጠርና ኃጢአትን እንደሠራ ይታወቃል። የብሉይ ኪዳን ሕግጋትና እነዚህ ተጨማሪ ሕጎች የአይሁዶች ባሕል ሆነው አሁን ይሁዲነት የምንለውን ነገር መሠረቱ። አይሁዶች ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለመፍጠር ሕግጋቱን በሙሉ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስተምራሉ። አንድ አሕዛብ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ለመቀላቀል ሲፈልግ እንዲገረዝና እነዚህን ሁሉ ሕግጋት እንዲጠብቅ ይጠየቃል። ከዚያም ወደ እይሁድነት ይለወጣል። ብዙ አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለሚወዱ እርሱን በሚያስከብር መንገድ ለመኖር ቢፈልጉም ሳይገረዙና ወደ አይሁድነትም ሳይለወጡ ቀርተዋል። «እግዚአብሔርን የሚፈሩ» ሰዎች ተብለው ቢታወቁም አይሁዶቹ ግን በፍጹም ከልብ አልተቀበሏቸውም ነበር።

እግዚአብሔር ሐዋርያ ጳውሎስን የአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን እስከጠራው ጊዜ ድረስ፥ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የቤተ ክርስቲያን ምእመናን አይሁዶች ብቻ ነበሩ። አይሁዶች ድነትን (ደኅንነትን) በሚቀበሉበት ጊዜ ጥቂት ለውጦች ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር። ወደ ቤተ መቅደስ ሊሄዱ፥ መሥዋዕቶችን ሊሠዉ፥ ሊገረዙ፥ ባሕላዊ የአይሁዶችን ሥርዓቶች ሊፈጽሙ፥ ለሥርዓታዊ ጉዳዮች ብለው ከአሕዛብ ሊለዩ፥ ወዘተ… ይችላሉ። የቀድሞ ልምምዳቸውን ሳይተዉ ክርስቶስ ለኃጢአታቸው የሞተላቸው መሢሕ እንደሆነ ተቀብለው አመኑ። ጥቂት አሕዛብ ድነትን (ደኅንነትን) በተቀበሉበት ወቅት ለአይሁዶች የተሰጡትን የብሉይ ኪዳን ሕግጋት እንዲከተሉ ተጠየቁ። ስለሆነም፥ መገረዝ፥ ንጹሕ ያልሆኑትን ምግቦች አለመመገብ፥ ወዘተ ይጠበቅባቸው ጀመር።

ነገር ግን ጳውሎስ ወንጌልን ወደ ገላትያ በወሰደ ጊዜ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአይሁዶች የሚበልጡ አሕዛብ የሚገኙባቸውን ምእመናን ያስተናግዱ ጀመረ። እነዚህ አሕዛብ የራሳቸውን ባሕል የመከተል እንጂ ወደ አይሁድነት የመለወጥ ፍላጎት አልነበራቸውም። በግሪክ ባሕል ግርዛት ተገቢ አልነበረም። አይሁዶች የማይበሏቸው እንደ አሳማ ሥጋ ያሉት ነገሮች ለግሪኮች ተወዳጅ ምግቦች ነበሩ። አሕዛብ በክርስቶስ ለማመንና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ወደ አይሁድነት መለወጥ ያስፈልጋቸው ነበር? ወይስ ድነት (ደኅንነት) እግዚአብሔር የተወሰኑ ሕግጋትን ለጠበቁት ሳይሆን በክርስቶስ ላመኑት ሁሉ የሚሰጣቸው ነፃ ስጦታ ነበር? ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖችን በተለያዩ ደረጃዎች መመደብ ያስፈልጋት ነበር? ባሕላቸውን የለወጡ፥ የተገረዙና የአይሁዶችን ሕግጋት የሚታዘዙ «መንፈሳዊ» ክርስቲያኖችና በክርስቶስ እያመኑ የአይሁድን ባሕል ለመከተል የማይፈልጉ «ክርስቶስን የሚፈሩ» በማለት ክርስቲያኖችን በተለያዩ ደረጃዎች መመደብ ያስፈልጋቸው ነበር?

ጳውሎስ አሕዛብን ወደ አይሁድነት እንዲለወጡ ማስገደዱ በክርስቶስ እንዲያምኑ የሚከለክል የማሰናከያ ዓለት እንደሚሆን ተገንዝቦ ነበር። ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) የሰው ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ ያውቅ ነበር። አንድ ሰው ባህላቸውን መለወጥ አያስፈልገውም ነበር። አይሁዶችም እንኳ እንደ መገረዝ ያሉትን ሕግጋት በመጠበቅ ድነት (ደኅንነትን) ሊያገኙ ስለማይችሉ፥ በክርስቶስ ለማመን አንድ ሰው ባሕሉን መቀየር አያስፈልገውም ነበር። እግዚአብሔር የኃጢአትን ይቅርታ፥ የክርስቶስን ጽድቅ፥ የእግዚአብሔርን ልጅነት መብትና የዘላለም ሕይወት በስጦታ ለመስጠት አንድ ሰው በትሕትናና በእምነት ወደ እርሱ እንዲመለስ ይጠይቃል።

በኢየሩሳሌም የሚገኙ አንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ በተለይም ፈሪሳውያን ወይም ካህናት ሆነው በክርስቶስ ያመኑ አይሁዶች ይህን ትምህርት ለመቀበል ይቸገሩ ነበር (የሐዋ. 15፡5)። አንዳንዶቹ ጳውሎስን ተከትለው ወደ አሕዛብ አገሮች ሁሉ ይጓዙ ጀመሩ። ወደ ሶርያ፥ አንጾኪያና የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ አሕዛብ ድነትን (ደኅንነትን) እና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት በግርዛትና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመቀበል ወደ አይሁድነት መለወጥ እንዳለባቸው አስተማሩ።

ጳውሎስ ይህ አደገኛ ትምህርት አሕዛብ በክርስቶስ እንዳያምኑ ከማድረጉም በላይ የወንጌሉን ምንነት እንደሚለውጥ ተገነዘበ። ጳውሎስ ይህንን ከፋፋይ ጉዳይ ሐዋርያት ወደሚገኙባት የኢየሩሳሌም ከተማ ወሰደ። የሐዋርያት ሥራ 15 በዚህ ጉዳይ ላይ ስለተካሄደው ጉባኤ ያብራራል። ሐዋርያትና የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ «አንድ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? የሚለውን ሥነ መለኮታዊ ጥያቄ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መረመሩ።

ይህ የኢየሩሳሌሙ ጉባኤ በሁሉም ዘመናት የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሃሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮችን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው የሚያሳይ መልካም ምሳሌ ነው። ክፍፍሉ እንዲቀጥልና የኋላ ኋላ በራሱ ጊዜ እንዲጠፋ ዝም ብለው አልተዉትም። ሰዎቹ የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በሰላም እንዲኖሩ አላባበሏቸውም። ነገር ግን በፍጥነት ተሰብስበው የነገረ መለኮታዊ ጉዳዩን ሥር በመመርመር ውሳኔዎችንና ተግባራዊ እርምጃዎችን አድርገዋል። ከዚህ የመጀመሪያው ጉባኤ የምንማራቸው አንዳንድ ጠቃሚ መርሆዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

ሀ. ሁሉም ወገኖች አመለካከታቸውን እንዲገልጹ ዕድል ተሰጥቷቸዋል። አሕዛብ ሊገረዙና የሙሴን ሕግጋት መከተል አለባቸው የሚሉ አይሁዶች በአንድ በኩል፥ ጳውሎስና ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል አመለካከቶቻቸውን አብራርተዋል።

ለ. ከዚያም የተከበሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እግዚአብሔር ቀደም ሊል ምን እንዳስተማራቸው ተናገሩ። ጴጥሮስ ወንጌሉን ወደ ቆርኔሌዎስ ስላመጣበት ሁኔታና (የሐዋ 10) እግዚአብሔር ቆርኔሌዎስንና ሌሎች አሕዛብን ተቀብሎ ወደ አይሁድነት እንዲለወጡ ወይም የሙሴን ሕግጋት እንዲጠብቁ ሳይጠይቅ መንፈስ ቅዱስን ስለሰጠበት ክስተት ገለጻ አደረገ። አስፈላጊው ነገር እምነት ብቻ ነው።

ሐ. ጉባኤው የእነዚህ ሰዎች አቋም ያስከተለውን ፍሬ መረመረ። ጴጥሮስ አይሁዶች እንኳ የብሉይ ኪዳንን፥ ብሎም የተጨመሩትን ሕግጋት በመጠበቅ እግዚአብሔርን ሊያስደስቱና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ እንደማይችሉ ገለጸ። ይህም ሊሸከሙት የማይችሉት ቀንበር ነበር።

መ. መሪዎቹ የሰዎችን ምሥክርነት ይሰሙ ነበር። ጳውሎስ ወንጌል በገላትያ እንዴት እንዳስፋፋ ገለጸላቸው። ሳይገረዙ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ላይ ይወርድ ነበር። እግዚአብሔር ተአምራትን በመካከላቸው ከመሥራቱ የተነሣ፤ አሕዛብ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝና ለማፍቀር ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው።

ሠ. ጉባኤው መጽሐፍ ቅዱስን መረመረ። ያዕቆብ ስለ አሕዛብ መዳን የሚናገሩትን ቁልፍ የብሉይ ኪዳን ምንባቦች አብራራ።

ረ. መሪዎቹ ከጸሎትና ከውይይት በኋላ ውሳኔ ሰጡ። በውይይታቸው ወቅት ከነበረው አንድነታቸው በመነሣት መንፈስ ቅዱስ ውሳኔውን እንደሰጣቸው ተገነዘቡ። ቁልፍ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነና ለአሕዛብ የመዳንን መንገድ አስቸጋሪ ማድረግ እንደሌለባቸው ወሰኑ።

ሰ. የኢየሩሳሌሙ ጉባኤ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ወሳኔውን ተረድተው እንዲከተሉ በይፋ አስታወቀ። አይሁድና አሕዛብ ክርስቲያኖች ወደሚገኙባቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ውሳኔውን ገልጸው ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤውን እውቀት፥ መንፈሳዊነትና የማብራራትና ጥያቄዎችን የመመለስ ብቃት የነበራቸው ሰዎች ይዘው ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ዞሩ። ከተላኩት መሪዎች መካከል አንዳንዶቹ (ጳውሎስና በርናባስ) ሥነ መለኮታዊውን ጥያቄ ያነሡ ሲሆን፥ ሌሎቹ (ይሁዳና ሲላስ)፥ የዚህ ጉዳይ ተካፋዮች አልነበሩም። ይህም እንደኛው ወገን ነገሮችን ባለመረዳቱ ወይም በተሳሳተ መንገድ በመረዳቱ ሳቢያ የሚከሰት ወቀሳ እንዳይኖር አድርጓል።

ሸ. ጉባኤው በአይሁድና በአሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል ሊኖር ስለሚገባው አንድነት አንዳንድ ነገሮችን ለማመቻመች ተገደደ። እውነት ብቻ ሳይሆን ፍቅርና አንድነትም አስፈላጊዎች ናቸው። አብያተ ክርስቲያናቱ ሁለት የተለያዩ ባሕሎች ባሏቸው አይሁዶችና አሕዛብ የተገነቡ በመሆናቸው፥ አሕዛብ አይሁዶችን ሊያስቆጡ የሚችሉትን አንዳንድ ነገሮች ከመፈጸም እንዲታቀቡ ተጠየቁ። ያዕቆብ እንዳለው፥ እነዚህ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ላይ የተመሠረቱ ጥልቅ ግንዛቤዎች ነበሯቸው (ከጥንት ዘመን ጀምሮ የሙሴ ሕግ በሁሉም ከተማ የሚሰበክ ሲሆን በሰንበት ቀናት ደግሞ በምኩራቦች ይነበብ ነበር)።

የሚያሳዝነው ይህ በድነት (ደኅንነት)ና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቅ መካከል ስላለው ግንኙነት የሚያስረዳው ጠቃሚ ሥነ መለኮታዊ ጉዳይ በፍጥነት እልባት አላገኘም። አንዳንድ አይሁዶች ወደየቤተ ክርስቲያናቱ እየዞሩ አሕዛብ ለመዳን ወይም መንፈሳዊ ለመሆን የተወሰኑ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መጠበቅ እንዳለባቸው ማስተማራቸውን ቀጠሉ። ጳውሎስ በጻፋቸው በሁሉም መልእክቶች ማለት ይቻላል፥ ስለዚሁ የሕግና የክርስቲያናዊ ነጻነት ጉዳይ ጠቅሷል።

ይህ ድነት (ደኅንነት) በሥራ ሳይሆን በእምነት እንደሚገኝና አሕዛብ ወደ አይሁዳዊነት መለወጥ ሳያስፈልጋቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኙ የሚያስረዳው ትምህርት በጣም ከባድ በመሆኑ፥ እንደ ጴጥሮስና በርናባስ ያሉት መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ለጊዜው ግራ ተጋብተው ነበር። ጳውሎስ የአይሁድን ልማድ በመከተል በአንጾኪያ በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ክፍፍልን በመፍጠሩና ድነት (ደኅንነት) በእምነት የመገኘቱን እውነት በማመቻመቹ ጴጥሮስን እንደ ገሠጸው አመልክቷል።

ያዕቆብና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለአብያተ ክርስቲያናት በጻፉት ደብዳቤ ለአማኞች ሁለት ዓይነት ትእዛዛትን ሰጡ። የመጀመሪያዎቹ፥ ሁልጊዜም ለሰዎች ሁሉ የሚያገለግሉ ግልጽ ትእዛዛት ነበሩ። ስለሆነም፥ አሕዛብ አማኞች ዝሙትን እንዳይፈጽሙ ጠየቋቸው። የሁለተኛዎቹ፥ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ያልጠቀሳቸውና አይሁዶች ለመቀበል የሚቸገሩባቸው እንደ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ፥ የታነቀ እንስሳ ሥጋና ደም የመሳሰሉ ነገሮች ነበሩ። እነዚህ ነገሮች ለድነት (ደኅንነት) አስፈላጊ እንዳልሆኑና ነገር ግን በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ሰላምንና አንድነትን ለመፍጠር የተሰጡ ትእዛዛት መሆናቸውን መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ደብዳቤው አይሁዶቹ ጥንታዊ ባሕላቸውንና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን የመከተል መብት እንዳላቸው ያሳያል። አሕዛብ አይሁዶች እንዲለወጡ የማስገደድ መብት አልነበራቸውም። አይሁዶችም ቢሆኑ አሕዛብ ለመዳን ባሕላቸውን መለወጥ እንዳለባቸው የማስገደድ መብት አልነበራቸውም።

ይህ ነገረ መለኮታዊ ሃሳብ ቤተ ክርስቲያን ልትገነዘባቸው ከሚገቧት እጅግ መሠረታዊና ጠቃሚ እውነቶች አንዱ ነው። ሁሉም ሃይማኖቶችና የሰው ተፈጥሮ እግዚአብሔር በነፃ የሰጠውን ስጦታ በሥራ ወደሚገኝ ነገር የመለወጥ ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ለዚህ ነው ወንጌሉን በምንመሰክርበትና ሰዎች ክርስቲያኖች በሚሆኑበት ጊዜ ስለሚለውጧቸው ነገሮች ማብራራት አደገኛ የሚሆነው። በዚህ ጊዜ አዲስ የሚያምነው ግለሰብ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት በክርስቶስ ከማመኑ በተጨማሪ አንዳች ተግባር ማከናወን እንዳለበት ያስባል። ግለሰቡ ድነትን ካገኘና በእምነቱ ማደግ ከጀመረ በኋላ እግዚአብሔር እንዲለውጥ ስለሚፈልጋቸው ተግባራትና አመለካከቶች ልንነግረው እንችላለን። ነገር ግን በእነዚህ ነገሮች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ማብራሪያ ካልሰጠና የቤተ ክርስቲያናችንን ልማድ ብቻ የምናስተምር ከሆነ፥ ክርስትናን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የምንመላለስበት ሕይወት ሳይሆን የሕግጋት መጠበቂያ ሃይማኖት እንዳናደርገው መጠንቀቅ ይኖርብናል።

ከእኛ የተለየ ባሕል ወዳለው ጎሳ ወንጌሉን ይዘን በምንሄድበት ጊዜ ሁሉ ይህንን ተግባራዊ ጉዳይ ማስታወስ አለብን። ሁላችንም የእኛ መንገድ ከሁሉም የተሻለ መስሎ ይሰማናል። ባሕላችን የተወሰነ አለባበስ፥ የፀጉር አቆራረጥ፥ በግብርና ወይም በንግድ ሥራ ላይ መሰማራት ለሰዎች የእግዚአብሔር ፍላጎት እንደሆነ ያስተምራል። እግዚአብሔር ሰዎች «እንዲሠለጥኑ» ይፈልጋል ብለን እናስባለን። በዘላኖች መካከል የሚሠሩ አንዳንድ ወንጌላውያን ሕዝቡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የወንጌላውያኑን ባሕል እንዲቀበሉ ይጠይቃሉ። ፀጉራቸውን የሚቀቡበትን ጭቃ እንዲያስወግዱ፥ ከንፈሮቻቸውን በጥተው ወጭት እንዳያስቀምጡ፥ የብር አምባሮቻቸውን እንዲጥሉ፥ ልብስ እንዲለብሱ፥ የከብቶቻቸውን ወተትና ደም እንዳይጠጡ፥ ወዘተ… ይከለክላሉ። እነዚህ ሁሉ ባሕላዊ ጉዳዮች ናቸው። ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ወይም በቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት ለማግኘት ባሕላቸውን እንዲቀይሩ የማስገደድ መብት የለንም። ብዙ ወንጌላውያንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘላኖች ባሕላቸውን እንዲቀይሩ በመጠየቅ የማሰናከያ ዓለት እኑረውባቸዋል። የሁሉንም ባሕሎች አባላት የሚቀበል ወንጌል አይሰብኩም። ወንጌሉ ባሕሎች ሁሉ ከተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚቃረኑ ነገሮችን (ለምሳሌ፥ የጣዖት አምልኮ፥ የወሲብ ኃጢአት) እንዲተዉ ይጠይቃል። ነገር ግን ሌሎች የባሕላዊ ልምምዶችን የማስቀረት ምርጫ ለአማኙ መተው ይኖርበታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህ አማኞች በአሳብ የሚለያዩበትን አንድ ጉዳይ ምረጥ። ለ) ከላይ የተዘረዘሩትን ደረጃዎች በመጠቀም፥ መንፈስ ቅዱስ ይህንን ጉዳይ ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንድታስተካክል እንደሚፈልግ አብራራ። ሐ) በአሁኑ ሰዓት ይህ ጉዳይ የሚስተናገደው እንዴት ነው? ጉዳዩ እየተስተናገደ ያለበት ሁኔታ መልካም ይመስልሃል ወይስ ወደፊት ወደ ተጨማሪ ችግሮች የሚያመራ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ።

ሁሉም አሕዛብ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ አመስጋኞች መሆን ይገባቸዋል። ይህ ጉባኤ አሕዛብ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ወደ አይሁድነት መለወጥ እንዳለባቸው የሚያመለክት ውሳኔ ቢያስተላልፍ ኖሮ፥ ወንጌሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አሕዛብ አገሮች ሁሉ መድረሱ አጠራጣሪ ነበር። ወንጌሉ በአይሁዶች ብቻ ይገደብ ነበር።

ዛሬ አብያተ ክርስቲያናትን የሚከፋፍሉ ብዙ ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮች አሉ። እንደ ልሳን፥ ፈውስን የመሳሰሉ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ኢየሱስ ብቻ የሚሉና የይሖዋ ምስክሮች ትምህርቶች በዘመናችን አብያተ ክርስቲያናትን ሲከፋፍሉ ይታያል። አብያተ ክርስቲያኖቻችን ለእነዚህ ጉዳዮች በመግባባት ላይ የተመሠረተ ሁነኛ አቋም ካልወሰዱ በምእመናን መካከል ተጨማሪ ክፍፍል መፈጠሩ የማይቀር ነው። ምንም እንኳ በክርስቲያናዊ ፍቅር መንፈስ ላለመስማማት ብንስማማም ልዩነቶች እንዳሉ ተቀብሎ ችግሮችን ለመፍታት መጣሩ አይሻልምን? እውነት ለእግዚአብሔር አስፈላጊው ነገር ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በልጆቹ መካከል ፍቅርና አንድነት እንዲኖርም ይፈልጋል። እውነት ወይም ፍቅር ከጎደለብን እግዚአብሔርን እንደሚፈልገው ልናመልከው አንችልም።

ሁለተኛ ዓላማ፡ ጳውሎስ ሐዋርያ ሳይሆን የሐሰት አስተማሪ ነው ለሚለው ክስ ምላሽ ለመስጠት። የአይሁድ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ጳውሎስን ስለ ሁለት ነገሮች ከስሰውት ነበር። በመጀመሪያ፥ የሐሰት አስተማሪዎቹ ጳውሎስ የክርስቶስ ሐዋርያ መሆኑን አላመኑም ነበር። እንደ እነርሱው በኢየሩሳሌም ካሉት እውነተኛ ሐዋርያት ሥልጣን ሥር እንደማይሠራ በመግለጽ ኮነኑት። ሁለተኛ፥ የጳውሎስ መልእክት የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ የእውነተኛ ሐዋርያት ድጋፍ እንዳልተሰጠው ገለጹ። ጳውሎስ ወንጌሉ ሥራን ሳይጨምር በእምነት ብቻ ሰዎች የሚድኑበት እንደሆነ የመግለጽ ሥልጣኑ የመጣው በቀጥታ እግዚአብሔር ስለ ላከው እንደሆነ ማረጋገጥ ነበረበት። ጳውሎስ የሕይወት ምስክርነቱን በመስጠት ለእነዚህ ሁለት ክሶች ምላሽ ሰጥቷል። ከኢየሱስ ክርስቶስ መልእክት የተሰጠው እውነተኛ ሐዋርያ መሆኑን አመልክቷል። ጳውሎስ ወንጌሉን ከክርስቶስ ተቀበለው እንጂ ራሱ አልፈጠረውም። በኢየሩሳሌም ሐዋርያት ሳይላክ ወይም ባይመረጥም፥ ከእነርሱ አያንስም ነበር። መልእክቱም የመነጨው ከሐዋርያቱ ሳይሆን በቀጥታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሚሰብከው ወንጌል ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ የተበረዘ ወንጌል አልነበረም። በሌላ በኩል፥ ጳውሎስ የሚሰብከው ወንጌል ሌሎች ሐዋርያት ከሚያስተምሩት ጋር የሚስማማ እንጂ የሚጋጭ አልነበረም። ጳውሎስ ከሐዋርያቱ ጋር በተገናኘ ጊዜ እርሱነቱንና አገልግሎቱን ተቀብለውታል።

ሦስተኛ ዓላማ፡ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በእምነት ብቻ ነው የሚለው የጳውሎስ ትምህርት ወደ ኃጢአተኝነት አኗኗር የሚመራ ነው ለሚለው ምላሽ ለመስጠት። ምንም እንኳ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው አንድ ሰው ክርስቶስ ስለ እርሱ እንደ ሞተ አምኖ በሚቀበልበት ጊዜ እንደሆነ ቢታወቅም፥ እግዚአብሔር ሰዎች የተለወጠ ሕይወት እንዲኖሩ ይፈልጋል። እምነት በፍቅር አማካኝነት ራሱን መግለጽ አለበት (ገላ. 5፡6)። እግዚአብሔር የኃጢአተኛ ሥጋችንን ተግባራት ለመቀነስና የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ለመስጠት ሲል መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል (ገላ. 5፡22-23)።

የውይይት ጥያቄ፡- ለክርስቲያኖች በእነዚህ ሦስት የገላትያ መልእክት ዓላማዎች ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች መረዳት ለምን ይጠቅማል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የገላትያ መልእክት መግቢያ

በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፥ «ድነትn (ደኅንነት) ለማግኘትና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ከፈለግህ መገረዝ አለብህ፥ በክርስቶስ ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም» ይሉ ነበር። ዛሬም አንዳንድ ወንጌላውያን፥ «የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ከፈለግህ መጠጥ ማቆምና ሁለተኛ ሚስትህን ማባረር ይኖርብሃል፥ በክርስቶስ ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም» ይላሉ። ወንጌል ምንድን ነው? አንድ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርበታል? ከዳንን በኋላስ እምነታችን ከታዛዥነት ሕይወታችን ጋር እንዴት ይዛመዳል? እነዚህ ሰዎች በታሪክ ሁሉ ያነሷቸው ጥያቄዎች ናቸው። «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» የሚለው ጥያቄ እንድ ሰው ሊያነሣ የሚችለው እጅግ አስፈላጊ ጥያቄ ነው። ይህ ወደ መንግሥተ ሰማይ ወይም ወደ ሲኦል መግባታችንን የሚወስን ጥያቄ ነው። ጳውሎስ በወንጌሉ ላይ ብንጨምር ወይም ብንቀንስ የዘላለም ጥፋት ሊደርስብን እንደሚችል በመግለጽ ያስጠነቅቃል (ገላ. 1፡8-9)። ስለሆነም ለሁሉም ክርስቲያን ስለ ወንጌሉ ግልጽ ግንዛቤ ማግኘቱ አስፈላጊ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ የማይቀበላቸው ሚዛናቸውን ያዛቡ ሁለት ጫፎች (አክራሪ አቋሞች) አሉ። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት አንዳች በጎ ተግባር መፈጸም አለብን የሚል አክራሪ አቋም አለ። በጳውሎስ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ይህ ማለት መገረዝ ወይም የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መጠበቅ ነበር። ዛሬ ደግሞ፥ አለመጠጣት፥ የተወሰኑ ልብሶችን አለመልበስ፥ የመሳሰሉት በዝርዝሩ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ አመለካከቶች የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በክርስቶስ ማመንና ተጨማሪ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። ሰዎች በወንጌሉ ላይ ሌሎች ነገሮችን የመጨመር ዝንባሌ አላቸው። በገላትያ መልእክት ውስጥ በወንጌል ትምህርት ላይ የሚጨምረው ትምህርት ተዳሷል። ሁለተኛ፥ የተወሰኑ እውነቶችና በክርስቶስ ላይ እምነት እስካለን ድረስ እንዳሻን ልንኖር እንችላለን የሚል ሌላ አክራሪ አቋም አለ። እነዚህ ሰዎች፣ እምነት እንዳሻን እንድንኖር ነፃ በማውጣት ያድነናል ይላሉ። ጳውሎስ ግን በእውነት ከዳንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መመላለስ እንደሚገባን በአጽንዖት ያስገነዝባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ከእነዚህ የተራራቁ አቋሞች አንዱን ሰያስተምሩ የተመለከትኸው እንዴት ነው? ለ) ድነትን (ደኅንነትን) በተመለከተ የእምነትና የበጎ ተግባር ግንኙነት ምንድን ነው?

የገላትያ መጽሐፍ ሕግጋትን በመጠበቅና በድነት (ደኅንነት) መካከል ስላለው ግንኙነት መልስ ይሰጣል። ይህን በጣም ጠቃሚ መልእክት ሰምታነብበት ጊዜ ይህን ጥያቄ በአእምሮህ ያዝ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ገላትያ አንብብና ጸሐፊውን፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን፥ እንዲሁም መልእክቱን በተመለከተ የቀረቡትን አሳቦች ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን መዝገበ ቃላት በማንበብ ስለ አካባቢው፥ በዚያ ስለነበሩት ሰዎች፥ ስለ ሃይማኖታቸው፥ ወንጌሉ እዚያ እንዴት እንደደረሰ፥ ወዘተ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

 1. የገላትያ መልእክት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ገላ. 1፡1-2 አንብብ። ሀ) የዚህ መልእክት ጸሐፊ ማን ነው? ለ) ጸሐፊው እንዲህ ዓይነት መልእክት ለመጻፍ የነበረውን ሥልጣን እንዴት ገለጸ? ይህንን ከ2ኛ ቆሮ. 1፡1 ጋር በማነጻጸር ምን ዓይነት ተመሳሳይነቶችንና ልዩነቶችን እንደምትመለከት አስረዳ።

የጥንት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአዲስ ኪዳን መልእክቶችን ፈር በሚያስይዙበት ጊዜ የጳውሎስን መልእክቶች ሁሉ በአንድ አካባቢ አስቀምጠዋቸዋል። የጳውሎስን ረዣዥም መልእክቶች (ከሮሜ እስከ 2ኛ ቆሮንቶስ) መጀመሪያ ካስቀመጡ በኋላ አጫጭሮቹን አስከተሉ። በዚህ መሠረት አራተኛው መልእክት የገላትያ መልእክት ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ጳውሎስ የጻፈው የመጀመሪያው መልእክት ሊሆን ቢችልም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከቀረቡት ሌሎች ሦስት የጳውሎስ መልእክቶች አጠር ስለሚል ከ2ኛ ቆሮንቶስ ቀጥሎ ሰፍሯል።

በሁሉም መልእክቶቹ እንደሚያደርገው ጳውሎስ ራሱን «ሐዋርያ» ሲል ይጠራል። ጳውሎስ እንደ ሐዋርያ በልዩ ሁኔታ የተመረጠ የእግዚአብሔር ወኪል ሲሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን አማካኝነት ይሠራል። ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ በመልእክቶቹ ውስጥ ሐዋርያነቱን ብቻ ገልጾ ያልፋል። ለገላትያ በጻፈው መልእክቱ ግን ጳውሎስ ስለ ሐዋርያነቱ አንዳንድ ነገሮችን ይናገራል።

በመጀመሪያ፥ ሐዋርያነቱ ከሰዎች እንዳልመጣ፥ 12ቱ ሐዋርያትም ሆኑ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያ አድርጋ እንዳልመረጠችው ይናገራል።

ሁለተኛ፡ ጳውሎስ ሐዋርያነቱ ከ«ሰው» እንዳልመጣ ገልጾአል። ምናልባትም ጳውሎስ ይህን ሲል የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መሪ የነበረው ጴጥሮስ እንዳልሾመው መግለጹ ይሆናል። እንደ ዛሬው ዘመን ሁሉ፥ በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ከዝነኛ ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት መሠረት ግለሰቦችን የመቀበል ወይም ያለመቀበል ዝንባሌ ነበር። ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያልነበራቸውና የድጋፍ ደብዳቤ ያልያዙ ሰዎች ይጠረጠሩ ነበር። ጳውሎስ የድጋፍ ደብዳቤ ስላልነበረው አንዳንድ ሰዎች ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ይጠራጠሩ ነበር። ዛሬም ምንም እንኳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር መልካም የሥራ ግንኙነት መመሥረቱ ጠቃሚ ቢሆንም፥ የቤተ ክርስቲያን መሪነት ከምናውቃቸው ሰዎች ወይም ከምርጫ እንደማይመነጭ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። በሥልጣን ማገልገል ካለብን ምንም እንኳ ጥሪውን ለማጽደቅ በሰዎች ሊጠቀም ቢችልም፥ እግዚአብሔር እንደጠራን ማስታወስ አለብን።

ሦስተኛ፥ ጳውሎስ ሐዋርያነቱና የወንጌልን ምንነት የመወሰን ሥልጣኑ ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደመነጨ ገልጾአል። እግዚአብሔር አብና ወልድ ጳውሎስ ሐዋርያ እንዲሆን መርጠውታል። እግዚአብሔር ለአገልግሎት መጥራቱን ለማጽናት ሌሎች ሰዎችን ሊጠቀም ይችላል። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የተወሰነ ተግባር እንድንፈጽምላቸው ሊቀጥሩን ይችላሉ። ነገር ግን አንድን ተግባር ለማከናወን እግዚአብሔር በቀጥታ እንደጠራን ካላወቅን፥ እግዚአብሔር እንደሚፈልግብን አድርገን ልናገለግል አንችልም። ሰዎች ምን እንደሚናገሩና እንደሚያስቡ፥ ደመወዛችንን የተወሰኑ ግለሰቦች እንዴት እንደሚቆጣጠሩ በማሰብ ልንፈራ እንችላለን። የአገልግሎታችንን ሥልጣን ከሌሎች እንደተቀበልን ብናስብ እውነትን በመናገር ሌሎች ሰዎች ኃጢአትን በሚሠሩበት ጊዜ ለትክክለኛው ነገር ልንቆም አንችልም። ብዙውን ጊዜ በራስ ወዳድነትና በግል ጥቅም ላይ ተመሥርተን ልናገለግል እንችላለን። የኋላ ኋላም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወይም አገልግሎቱን ልንጎዳ እንችላለን። ነገር ግን እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ በእርግጠኝነት ካወቅን የእርሱን ብርሃን ተከትለን ትእዛዛቱን ልንጠብቅ እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞች (ወንጌላውያን፥ መጋቢያን፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ የወጣቶች መሪዎች) የሚያገለግሉት እግዚአብሔር በቀጥታ ጠርቶናል ብለው ስለሚያስቡ ነው ወይስ ሰዎች ስለመረጧቸው ወይም ሥራ ስለተሰጣቸው? ለ) አንድ ሰው እግዚአብሔር ጠርቶኛል በሚል እምነት የሚያበረክተው አገልግሎት፤ በመመረጡ፥ ሥራ በማግኘቱ ወይም ደመወዝ በመቀበሉ ምክንያት ከሚሰጠው አገልግሎት እንዴት ይለያል?

 1. ጳውሎስ የገላትያን መልእክት ለማን ጻፈ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በገላትያ 1፡2፥ የመልእክቱ ተቀባዮች እነማን ናቸው? ለ) የሐዋ. 13፡13-14፡25 አንብብ። በጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ አብያተ ክርስቲያናት የተመሠረቱባቸውን ከተሞች ዘርዝር።

ጳውሎስ የገላትያን መልእክት የጻፈው በገላትያ ለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ነበር። «ገላትያ» የሚለው ቃል ሁለት የተለያዩ ነገሮችን ሊያመለክት በመቻሉ ምክንያት ምሁራን በዚህ አሳብ ላይ ብዙ ይከራከራሉ። ቃሉ በሰሜን ማዕከላዊ ቱርክ የሚገኙትን የገላትያ ሰዎች ወይም በትንሹ እስያ ውስጥ የነበረችውን የሮም እውራጃ ሊያመለክት ይችላል።

ጳውሎስ ለሰሜን ገላትያ እንደጻፈ የሚያስቡ ምሁራን፤ ሉቃስ በግልጽ ባይጠቅስም ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት እንደመሠረተ ያስባሉ። በሐዋርያት ሥራ 16፡6 ላይ ሉቃስ፥ «በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ» ይላል። ምሁራኑ በዚህ ቃል ላይ በመመሥረት፥ ጳውሎስ የደቡብ ገላትያን አብያተ ክርስቲያናት ከጎበኘ በኋላ ወደ ሰሜን ገላትያ ተጉዞ ሌሎች ከተሞችን እንደ ጎበኘና አብያተ ክርስቲያናትን እንደ መሠረተ ይናገራሉ። እነዚህ ምሁራን ጳውሎስ በትንሹ እስያ ሰሜን ማዕከላዊ አካባቢ የሚገኙትን «የገላቲያ» ጎሳዎች ለማመልከት ሲል «ገላትያ» የሚለውን ቃል እንደ ተጠቀመ ያስባሉ።

ሌሎች ብዙ ምሁራን ደግሞ ጳውሎስ በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ለመሠረታቸው የደቡብ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደጻፈ ያስባሉ። እነዚህ ምሁራን በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን በመሠረተበት የሮም አውራጃ የሚገኘውን ስፍራ ለማመልከት ገላትያ የሚለውን ቃል እንደተጠቀመ ይናገራሉ። ሉቃስ በሰሜን ገላትያ አብያተ ክርስቲያናትን መመሥረታቸውን ስለማይጠቅስ ይህ ትክክለኛው ምርጫ ይመስላል።

ጳውሎስ መልእክቱን ከመጻፉ ከ400 ዓመታት በፊት ከጥቁር ባሕር በስተሰሜን (በከፊል የአሁኑ ሩሲያ አካባቢ) የሚገኝ አንድ ጎሳ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች መፍለስ ጀመረ። አብዛኞቹ ወደ አውሮፓ ሲሄዱ፥ ጥቂቶቹ ደግሞ ወደ ሰሜን ማዕከላዊ የትንሹ እስያ ክፍል አመሩ። ግሪኮች እነዚህን ሰዎች ገላታይ ይሏቸዋል። የሮም መንግሥት በትንሹ እስያ ሲስፋፋ፥ እነዚህ ሰዎች የሮሜዎቹ አጋሮች ሆኑ። በ25 ዓ.ም ሮማውያን ከዚሁ የትንሹ እስያ ክፍል የተወሰነውን አንድ ላይ አድርገው ገላትያ ሲሉ ሰየሙት። ከተለያዩ ዘሮች የተሰባሰቡት እነዚህ የገላትያ ሰዎች በብዙ አማልእክት የሚያምኑ ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ። ጳውሎስና በርናባስ በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዟቸው (47-49 ዓ.ም) ወደ ገላትያ አውራጃ ደረሱ። ምክንያቱን ባናውቅም በፍጥነት ወደ ሊሲያ፥ ጵንፍልያና ከገላትያ አውራጃ ዐበይት ከተሞች አንዱ ወደነበረችው ወደ ጲስድያ አንጾኪያ አመሩ። በዚህ ስፍራም የመጀመሪያይቱን ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ። ቤተ ክርስቲያኒቷ ሥራዋን ከጀመረች በኋላ ጳውሎስና በርናባስ በሮሜ በስተምሥራቅ የሚገኙትን ዋና መንገዶች በመያዝ በኢቆንዮንና በልስጥራን አብያተ ክርስቲያናትን ተከሉ። ከዚያ በመቀጠልም ጳውሎስ ያደገባትን የጠርሴስ ከተማ የምትገኝበትን የኪልቂ ክፍለ ሐገር በማቋረጥ በደርቤን ቤተ ክርስቲያንን መሠረቱ። በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጥቂት አይሁዶች ቢኖሩም፥ አብዛኛዎቹ አሕዛብ ነበሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አሕዛብ ከአይሁዶች በቁጥር ልቀው ተገኙ። የአይሁዶችና አሕዛብ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማምለክ ጳውሎስ በገላትያ መልእክት ውስጥ ያነሣቸውን ችግሮች አስከተለ።

ጳውሎስ አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ የአይሁድ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሐዋርያት ልከውናል ብለው መጡ። በእግዚአብሔር ዘንድ እውነተኛ ተቀባይነት ለማግኘት ግርዛትን ተቀብለው ወደ አይሁድነት በመለወጥ የሙሴን ሕግጋት ሊጠብቁ እንደሚገባ አስተማሩ። ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ብዙዎች ትምህርታቸውን መከተል ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ለመሠረታቸው የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመሪያ መልእክቱን ጻፈላቸው። ጳውሎስ ክርስቲያኖቹ ከእርሱ ከሰሙት ንጹሕ ወንጌል ወደ ሐሰተኛ ወንጌል እንዳይመለሱ ያስጠነቅቃቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ የገላትያ ክርስቲያኖች አዳዲስ ክርስቲያኖች ነበሩ። ሀ) አዳዲስ ክርስቲያኖች በቀላሉ ግራ ተጋብተው ወደ ሐሰተኛ ትምህርት የመግባታቸው ጉዳይ በአንተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ይታያል? ለ) አዳዲስ ክርስቲያኖች እምነታቸውን አውቀው በሐሰት ትምህርቶች ከመወሰድ እንዲጠበቁ ቤተ ክርስቲያንህ ምን ልታደርግ ትችላለች?

ጳውሎስ የገላትያን መልእክት የጻፈበት ዘመንና ስፍራ ጳውሎስ የጻፈው በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ለመሠረታቸው ሰሜናዊ የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት ከሆነ፥ መልእክቱ የተጻፈው ምናልባትም በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ወቅት ከኤፌሶን ከተማ ሊሆን ይችላል (53-57 ዓ.ም)።

ነገር ግን ጳውሎስ ከመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በኋላና ከሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በፊት ለደቡብ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የሚጽፍ ይመስላል። የገላትያ መልእክት የተጻፈው ከኢየሩሳሌሙ ጉባኤ በፊት (የሐዋ. 15) ከሆነ፥ ከ48-49 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተጽፎአል ማለት ነው። የተጻፈው ከኢየሩሳሌም ጉባዔ በኋላ ከሆነ ግን ምናልባት ከ49-51 ዓ.ም ተጽፎ ይሆናል። ይህም ከጳውሎስ ሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ትንሽ ቀደም ብሎ ማለት ነው። የገላትያ መልእክት የተጻፈው ከሶርያ አንኪያ ሲሆን፥ ጊዜውም ጠቃሚው የኢየሩሳሌም ጉባኤ ሊካሄድ በተቃረበበት በ49 ዓ.ም ይመስላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)