ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ በታምር መያዛቸው እና ክርስቶስ ጴጥሮስን ይቅር ማለቱ (ዮሐ. 21፡1-25)

 1. ክርስቶስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙ ዓሣ ሰጠ (ዮሐ 21፡1-14)

ሐዋርያው ዮሐንስ መጽሐፉን የደመደመው በዮሐንስ 20፡30-31 ነው። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ታሪክ የጀመረውን ዘገባ ለመቋጨት ሌሎች ሁለት ታሪኮች ቀርተውት ነበር። የመጀመሪያው ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ዓሣን እንዴት በተአምር እንደ ሰጣቸው ነው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ አዝዟቸው ነበር (ማቴ. 28፡10)። በገሊላ ሳሉ ድንገት በዚያ የተገኘ ይመስላል። የሚያደርጉትን ነገር በማጣታቸው ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ዓሣ ለማጥመድ ሄዱ። ክርስቶስ መጀመሪያ ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት አብዛኞቹን የጠራው ሌሊቱን በሙሉ ሲጥሩ አድረው ምንም ሊያጠምዱ ባልቻሉበት ወቅት በተአምር ብዙ ዓሣ እንዲይዙ በማድረግ ነበር። (ሉቃስ 5፡1-11 እንብብ።) አሁንም ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር የነበረውን ጊዜ ሌላ ተአምር በማድረግ ይደመድማል። ምንም ሊያጠምዱ ባልቻሉበት ወቅት ክርስቶስ መረባቸውን ከጀልባይቱ በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲጥሉ አዘዛቸው። መረባቸው በዓሳዎች በተሞላ ጊዜ መጀመሪያ ዮሐንስ («ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር») በኋላም ሌሎች ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን ለይተው አወቁት። በመጀመሪያው የዓሣ ማጥመድ ተግባር ወቅት ጴጥሮስ የክርስቶስን ልዩ ኃይል ተመልከቶ እንደ ሰገደለት ሁሉ፥ አሁንም መጀመሪያ ጴጥሮስ ከጀልባይቱ ወርዶ ወደ ክርስቶስ እየዋኘ መጣ። ጴጥሮስ ይህንን ያደረገው ለምን ነበር? አንደኛው፥ ለክርስቶስ የነበረውን ታላቅ ፍቅር የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው፥ ጴጥሮስ ክርስቶስን በመክዳቱ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃይ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስን እንደሚወደው ለማሳየት ፈልጎ ነበር።

 1. ክርስቶስ ጴጥሮስን ይቅር አለው (ዮሐ. 21፡15-25)።

ጴጥሮስ ከዚህ በፊት በፈጸመው ስሕተት እንደሚያሠቃይ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። እርሱም ክርስቶስን እስከ ሞት ድረስ ለመከተል ቃል ቢገባም ከድቶታል። ክርስቶስ ይቅር ይለው ይሆን? ክርስቶስ ሌላ ዕድል ይሰጠው ይሆን? አሁንም በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ አገልግሎት ይኖረው ይሆን? ኢየሱስ በእርግጥ ይቅር እንዳለውና አሁንም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ለማረጋገጥ ሲል፥ ጴጥሮስን በግል አነጋግሮታል። በኢየሱስና በጴጥሮስ መካከል ከተደረገው ውይይት የምንመለከታቸው ጠቃሚ ነገሮች አሉ።

ሀ. ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ከድቶት ስለነበር፥ አሁን ኢየሱስ ፍቅሩን ሦስት ጊዜ እንዲገልጽለት ጠየቀው።

ለ. ክርስቶስ በጴጥሮስ ፍቅር ላይ ያተኩራል። በዮሐ 21፡15 ላይ «ከእዚህ» የሚለው ምንን እንደሚያመለክት አናውቅም። ጴጥሮስ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ስለሚያውቀው የዓሣ ማጥመድ ሥራ ይሆን? ክርስቶስ ጴጥሮስ ከቀድሞ ሕይወቱ ይበልጥ እርሱን ይወደው እንደሆነ መጠየቁ ይሆን? ወይስ «ከእነዚህ» የሚለው ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት የሚያመለክት ይሆን? ኢየሱስ ጴጥሮስን እየጠየቀ ያለው ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት ይበልጥ ትወደኛለህ እያለው ይሆን? ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ እየጠየቀው ያለው በሕይወቱ ከምንም ነገር ወይም ከማንም ሰው በላይ የሚወደው እርሱን መሆኑን ነው።

ሐ. ክርስቶስ በጥያቄዎቹ ውስጥ ስለ ፍቅር የሚገልጹትን ቃላት ይለውጣል። ኢየሱስ «ትወደኛለህ» እያለ ለሁለት ጊዜ ሲጠይቀው የተጠቀመበት ቃል «አጋፔ» የሚለውን መለኮታዊ ፍቅርን የሚገልጸውን ቃል ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ሲጠይቀው ደግሞ፥ «ፊሊዮ» የሚለውን ለወዳጆቹ ያለውን ፍቅር የሚገልጸውን ቃል ነው። ይህ ዮሐንስ ድግግሞሽን ለማስወገድ ሲል ያደረገው ወይም ክርስቶስ በሁለቱ መካከል እያነጻጸረ ስለመሆኑ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ምናልባት ዮሐንስ ሁለቱንም ቃላት የተጠቀመባቸው ተመሳሳይ አሳብ ለማስተላለፍ ሳይሆን አይቀርም።

መ. ኢየሱስ ጴጥሮስን ትሑት ሊያደርገው ተነሣ። ጳጥሮስ «ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ» በሚል የልበ ሙሉነት ዓረፍተ ነገር ቢጀምርም፥ መጨረሻ ላይ የተናገረው አሳብ ግን የለሰለሰ ነበር። «ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህም አንተ ታውቃለህ።» ጴጥሮስ ፍቅሩን ከሌሎች ጋር ለማነጻጸር አልሞከረም። ቀደም ሲል ሌሎች ደቀ መዛሙርት በሙሉ ቢለዩትም እንኳ፥ እርሱ ግን እስከ መጨረሻው እንደሚወደው በትምክሕት ተናግሮ ነበር (ማቴ. 26፡33)። አሁን ሊያደርግ የሚችለው ነገር ቢኖር ልቡን መርምሮ በሚችለው አቅም ክርስቶስን እንደሚወድ መግለጽ ብቻ ነበር። ይህ ከሌሎች መብለጡን ወይም ማነሱን አያውቅም። ለኢየሱስም ሊነግረው የፈለገው በሕይወቱ ከምንም በላይ እንደሚወደው ነበር።

ሠ. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ዐቢይ አገልግሎት ሰጠው። ይኸውም የኢየሱስ በጎች እረኛ እንዲሆን ነበር። በጎቹ የክርስቶስ እንጂ የጴጥሮስ አይደሉም። (መሪዎች ሁሉ ይህንን እጅግ ጠቃሚ እውነት መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የቤተ ክርስቲያን ምእመናን የራሳችን ወይም የቤተ እምነታችን ንብረቶች አይደሉም። የመሪዎችም አይደሉም። ንብረትነታቸው ለክርስቶስ ስለሆነ ለእርሱ ልንከባክባቸው ይገባል) መልካም እረኛ የሆነው ክርስቶስ በጎቹን እንዴት እንደሚመግብ ይገልጻል። ይህንን የሚያደርገው እንደ ጴጥሮስ ከምእመናኑ መካከል በሚያስነሣቸው መሪዎች አማካይነት ነው። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ኃይላቸውን በወንጌል ስርጭት ላይ ስለሚያውሉ፥ ምእመናንን መመገብ እንዳለባቸው ይዘነጋሉ። የታመመና የኮሰሰ በግ ለምን ይጠቅማል? ስለሆነም፥ ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን መንጋ መመገብ እንዳለበት ግልጽ ተደረገለት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስን በጎች መመገብ ለምን ያስፈልጋል? ለ) የጠፉትን በመፈለግና የኢየሱስን በጎች በመመገብ መካከል ሚዛናዊ ለመሆን አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ በጎችዋን የምትመግብባቸውን መንገዶች በምሳሌነት ጥቀስ። ጥሩ ተግባር እየተከናወነ ይመስልሃል? ለምን? መ) በጎቹን በተሻለ ሁኔታ ለመመገብ ምን ቢደረግ ይሻላል ትላለህ?

ክርስቶስ ለጴጥሮስ የሚነግረው አንድ ተጨማሪ አሳብ ነበረው። ለጴጥሮስ እንዴት እንደሚሞት ነገረው። ባረጀ ጊዜ ጴጥሮስ ሕይወቱን እንደ ልብ ማዘዝ አይችልም። ይልቁንም፥ እስረኛ ሆኖ በሌሎች ሰዎች ቁጥጥር ሥር ይውላል። ከዚያ በኋላ ጴጥሮስን ወደማይፈልገው ስፍራ ይወስዱታል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚለው፥ ጴጥሮስ በሮም በኔሮ ዘመን ታስሮ ነበር። የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ወደሚሰቀልበት ስፍራ ተወስዶ ተገድሏል። እንደ ክርስቶስ ራሱን ከፍ አድርጎና እጆቹን ዘርግቶ ለመሰቀል ስላልፈለገ፥ ወደ ታች ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት ለመናቸው። እንደ ጌታው ራሱን ወደ ላይ አድርጎ ለመሰቀል ብቁ ነኝ ብሎ አላሰበም ነበር።

ከክርስቶስና ከጴጥሮስ ኋላ ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር (ዮሐንስ) ነበር። ጴጥሮስ አሰቃቂ ሞት እንደሚጠብቀው ካወቀ በኋላ፥ የዮሐንስ አሟሟት እንዴት እንደሚሆን ክርስቶስን ጠየቀው። ጴጥሮስ ይህን ሲል፥ ኢየሱስ ማድላት የለብህም፤ እኔ እንደዚህ የምሠቃይ ከሆነ ሁሉንም በእኩል ማየት አለብህ። ስለሆነም፥ ዮሐንስም በተመሳሳይ መንገድ መሞት አለበት። አይደል? ማለቱ ነበር። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ለእግዚአብሔር ማቅረብ የለብንም። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ያለው ዕቅድ የተለየ ነው። አንዳንዶችን በቀላል ሌሎችን ደግሞ በከባድ ሁኔታ ይወስዳቸዋል። ክርስቶስ ጌታ ስለሆነ፥ እያንዳንዳችንን የሚወሰድበትን ሁኔታ የሚመርጠው እርሱ ነው። ከቶውንም ራሳችንንም ሆነ ሕይወታችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸር የለብንም። ይልቁንም፥ በታዛኝነትና ታማኝነት ክርስቶስን እየተከተልሁ ነኝ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።

ዮሐንስ ይህንን ታሪክ በመጽሐፉ ውስጥ ያካተተው ሌላም ምክንያት ስለነበረው ነው። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፥ ክርስቶስ ዮሐንስ ከመሞቱ በፊት ይመለሳል እየተባለ ይወራ ነበር። ዮሐንስ ይህን መጽሐፍ በሚጽፍበት ጊዜ ቢያንስ የ70 ዓመት አዛውንት ነበር። ስለሆነም፥ የሚሞትበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች በዚህ ጊዜ ክርስቶስ የሚመለስበት ጊዜ ተቃርቧል ብለው ያስቡ ነበር። ዮሐንስ ግን ክርስቶስ ዮሐንስ ከመሞቱ በፊት እመለሳለሁ እንዳላለና ዮሐንስ ከመሞቱ በፊት ቢመለስ ወይም ባይመለስ ይህ ጴጥሮስን ሊያሳስበው እንደማይገባ ገለጻለት።

የውይይት ጥያቁ፡- እግዚአብሔር እነርሱንና ሌሎችን የሚመለከትበትን ሁኔታ ከሌሎች ጋር ማነጻጸሩ ለብዙዎች ምን ያህል ቀላል እንደሆነ አብራራ። እንደዚህ ዓይነት ማነጻጸር የሚያስከትለው ውጤት ምንድን ነው?

ክርስቶስ ሁለት ጊዜ ጴጥሮስ እንዲከተለው ጠይቆታል። ወደ ሌሎች ሰዎች በምንመለከትበት ጊዜ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ቢክዱህ እንኳ እኔ አልክድህም ሲል እንደ ተናገረው ጴጥሮስ፥ ከሌሎች እንሻላለን ብለን እንኩራራ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሌላ ሰው ከእኔ በላይ እየተጠቀመ ነው ብለን በማስብ በቅንዓት ልንብሰለሰል እንችላለን። ይህም የዮሐንስ አሟሟት እንደ እኔ መሆን አለበት ሲል ጴጥሮስ እንደ ተከራከረው ዓይነት ነው። ዳሩ ግን ዓይኖቻችን በክርስቶስ ላይ ማረፍ አለባቸው። ልናነሣቸው የሚገቡን ጥያቄዎችም፥ «በእውነት ክርስቶስን እንደ ደቀ መዛሙርት እየተከተልን ነን? ክርስቶስን ከማንም ወይም ከምንም በላይ እንወደዋለንን? በታዛዥነት እየተመላለስን ክርስቶስ የሚጠይቀንን እናደርጋለን ወይ?» የሚሉ መሆን አለባቸው። በፍርድ ቀን በክርስቶስ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ፥ በትምህርት ቤቶች እንደሚደረገው በአማካይ ውጤት አይደለም ውጤት የሚሰጠን። እኛን ከሌሎች ጋር በማነጻጸር ፈንታ፥ እርሱ ከሚፈልገው ጋር ያነጻጽረናል።

ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ተጨማሪ አሳቦችን ለመናገር ይችል ነበር። እርሱ እንዳለው፥ አንድ ሰው የክርስቶስን ጠቅላላ ታሪክና የታሪኮቹን ቅደም ተከተል ለመዘርዝር ቢፈልግ፥ ዓለም የማይበቃቸው እጅግ ብዙ መጻሕፍት ሊጻፉ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ዮሐንስና መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንድናገኝ የፈለገውን እውቀት ሰጥተውናል። ይህም እውቀት በክርስቶስ ለማመንና ለመከተል በቂ ነው። ምንም እንኳ የበለጠ ለማወቅ ፍላጎቱ ቢኖረንም፥ የብዙዎቻችን ትልቁ ችግር የምናውቀውን ከሥራ ላይ ለማዋል አለመቻል ነው። እምነትህ ጠንካራ ነው? የክርስቶስ ተከታይ ነህ? ከእነዚህ በላይ ክርስቶስን ትወደዋለህ?

የውይይት ጥያቄ፡- ከማንኛውም ሰው ወይም ነገር በላይ ክርስቶስን ትወድ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስን በጸሎት ለመጠየቅ ጊዜ ይኑርህ። ሕይወትህን ለክርስቶስ እንደገና አሳልፈህ ስጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የክርስቶስ ስቅለት፣ ቀብር እና ትንሣኤ (ዮሐ. 19፡17-20:31)

 1. የክርስቶስ ስቅለት (ዮሐ 19፡17-37)

ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ሞት አያሌ አስገራሚ ዝርዝሮችን አቅርቧል።

ሀ. የሃይማኖት መሪዎች በክርስቶስ ላይ ያቀረቡትን ክስ ለመቀየር ፈለጉ። አንድ ሰው በወንጀል ተከስሶ ስቅላት በሚፈረድበት ጊዜ፥ ሮማውያን በአንገቱ ዙሪያ ወንጀሉን የሚገልጽ ጽሑፍ ያንጠለጥሉ ነበር። የክርስቶስ ክስ «የአይሁድ ንጉሥ» የሚል ነበር። የሃይማኖት መሪዎች ክሱ እንዲቀየር ቢጠይቁም፥ ጲላጦስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ለ. የክርስቶስን ልብስ መከፋፈላቸው፡- ዮሐንስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት እንደ ፈጸመ ካመለከትባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ይሄ አንደኛው ነው። ዮሐንስ የክርስቶስ ልብስ ላይ ዕጣ እንደ ተጣጣሉና ከወታደሮቹ አንዱ ዕጣውን አሸንፎ እንደ ወሰደ ገልጾአል። (ማስታወሻ፡- እያንዳንዱ ወታደር ከተሰቀለው ግለሰብ ልብስ መውሰዱ በሮም የተለመደ ድርጊት ነበር።)

ሐ. ክርስቶስ ለሚወደው ደቀ መዝሙር እናቱን በአደራ ሰጠ። ሉቃስ ብዙ ሴቶች በኀዘን ተሰብረው በክርስቶስ መስቀል አጠገብ መቆማቸውን ቢገልጽም፥ ዮሐንስ ግን ክርስቶስ እናቱን ለሌሎች ልጆቿ ሳይሆን፤ ለእርሱ ለራሱ አደራ ማለቱን ጠቅሷል።

መ. የሌቦቹ እግሮች መሰበርና የክርስቶስ ጎን መወጋት፡- ሰውን በስቅላት መግደል ረዥም ጊዜ ይወስዳል። አንዳንድ ጠንካራ ሰው ለመሞት እስከ ሁለት ቀን ሊፈጅበት ይችላል። ይህን ረዥም ጊዜ የሚወስድ አሟሟት ለማፋጠን ከሚደረጉት ነገሮች አንዱ በመስቀል ላይ የተሰቀሉትን ሰዎች እግሮች መስበር ነበር። ዮሐንስ አሁንም ክርስቶስ በሁለት መንገዶች የብሉይ ኪዳን ትንቢትን እንደ ፈጸመና የሁለቱ ሌቦች እግሮች እንደ ተሰበሩ አመልክቷል። እንደኛው፥ ቶሎ ስለ ሞተ እግሩን መስበር አላስፈለገም። ሁለተኛው፥ በጦር ተወግቷል። በጦር ሲወጋ ውኃና ደም መውጣቱ፥ ጦሩ የክርስቶስን ልብ እንደ ወጋ የሚያሳይ መሆኑን የሕክምና ሳይንስ ያስረዳል። ይህም የክርስቶስን መሞት ያሳያል። ይህን ታላቅ እውነት ዮሐንስ በዓይኑ እንደ ተመለከተ ገልጾአል። ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ሞት የሰጠው ምስክርነት እውነት ነበር። አንዳንድ ሙስሊሞች፥ ክርስቶስ ራሱን ስቶ የነቃው በመቃብር ውስጥ ነው፤ ነቅቶ ድኗል ማለታቸው የሚታመን አባባል አይደለም።

 1. የኢየሱስ መቀበር (ዮሐ 19፡38-42)። ሁሉም ወንጌላውያን በክርስቶስ ቀብር ወቅት የአርማትያሱ ዮሴፍ ስላደረገው መልካም ተግባር የገለጡ ሲሆኑ፥ ዮሐንስ ግን ኒቆዲሞስን ጠቅሷል። ኒቆዲሞስ የዘላለም ሕይወትን መንገድ ለማወቅ መጀመሪያ ወደ ክርስቶስ የመጣ የሃይማኖት መሪ ነበር (ዮሐ 3)። ከዚያ በኋላ ሕቡዕ ወይም አይሁዶች ያላወቁት አማኝ በመሆን በሃይማኖት መሪዎች ፊት ስለ ክርስቶስ ለመከራከር ሞክሯል (ዮሐ 7፡50-51)። እነዚህ ሁለት ሕቡዕ አማኞች ከኢየሱስ ሞት በኋላ በግልጽ ተከታዮቹ ሆኑ። የክርስቶስን አስከሬን ለመውሰድ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ወስደው በመቃብር ውስጥ አኖሩት። ቀደም ሲል ኒቆዲሞስ 25 ኪሎ ግራም የሚመዝን የከርቤና የእሬት ቅልቅል እንዳመጣ ዮሐንስ ገልጾአል። ይህም ኒቆዲሞስ ለክርስቶስ የነበረውን ፍቅርና አክብሮት ያሳያል። ነገሥታት በሚቀበሩበት ጊዜ ብዙ ዓይነት ቅመም ጥቅም ላይ ይውል ነበር። (2ኛ ዜና 16፡14)። ዮሐንስ የክርስቶስን ሥጋ በጥንቃቄ በተልባ እግር ልብስ መሸፈናቸውን መግለጹ፥ ሂደቱን ሲከታተል እንደ ነበረ ያስረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 20- አንብብ። ሀ) እነዚህ ምዕራፎች ስለ ክርስቶስ ምን ይነግሩናል? ለ) ክርስቶስን ስለ መከተል ምን እንማራለን?

 1. የኢየሱስ ትንሣኤ (ዮሐ. 20)።

ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሰጠውን ገለጻ ማንበብ፥ ፎቶግራፋዊ መረጃን እንደ መመልከት ይቆጠራል። ታሪኩ ያተኮረው የተለያዩ ሰዎች ስለ ትንሣኤው በሰጡት ምላሽ ላይ ነው።

ሀ. መግደላዊት ማርያም፡- ጌታችን ከሞት ሲነሣ በመጀመሪያ የተመለከተችው ይህቺው መግደላዊት ማርያም ነበረች። ይህም ለኢየሱስ ለነበራት ፍቅርና እርሱን ለማግኘት ስላሳየችው ቆራጥነት የተደረገላት አክብሮት ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄዳ የክርስቶስን ሥጋ እንዳጣችው ገልጾአል። ከዚያም ወደ ዮሐንስና ጴጥሮስ ፈጥና በመሄድ ነገረቻቸው። ወደ መቃብሩ በተመለሰች ጊዜ ግን ክርስቶስን አገኘችው። ክርስቶስ ገና ወደ አብ ስላላረገ ማርያም እንዳትነካው አስጠነቀቃት። (የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያተኩረው ክርስቶስን በመንካት ሳይሆን፥ ይዞ እንዳይሄድ በመከልከል ላይ ነው።) ክርስቶስ ይህን ያለው ለምንድን ነው? አንዳንዶች ክርስቶስ በቀጥታ ወደ ሰማይ ሄዶ ራሱን ለአብ ለማቅረብና ከዚያ በኋላ ወደ ምድር ለመመለስ ዐቅዶ ሳለ፥ ማርያም ይዛ ልታቆየው እንደ ፈለገች ያስረዳሉ። ትክክለኛው ትርጓሜ ግን፥ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት የተወሰነ ጊዜ እንዳለውና ማርያም ሌላ ጊዜ ስለምታገኘው ይዛው ለመቆየት ማሰብዋ አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚገልጸው ነው። ይልቁንም ማርያም ሄዳ ትንሣኤውን ለአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት እንድትናገር አሳሰባት። ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር አምላካቸውና አባታቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አሳይቷል። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳለውም ገልጾአል። ምክንያቱም እርሱ የክርስቶስ ልዩ አባትና አምላክ ሲሆን፥ ይህም ከደቀ መዛሙርቱ ግንኙነት ፍጹም የተለየ ነበር።

ለ. ጴጥሮስ፡- ማርያም መቃብሩ ባዶ እንደሆነ ስትናገር ሰምቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ። ወደ መቃብሩ ዘልቆ ሲገባም፥ ከከፈኑ ጨርቅ በስተቀር የኢየሱስን ሥጋ አላገኘም። መቃብሩ ባዶ መሆኑን ከተመለከተ በኋላ የሆነውን ነገር በቅጡ ሳይረዳ ተመለሰ።

ሐ. ዮሐንስ፥ «ሌላው ደቀ መዝሙር፡- ከጴጥሮስ ቀድሞ ቢሮጥም፥ ከመቃብሩ ውጭ ቆሞ ወደ ውስጥ ተመለከተ እንጂ፥ ወደ መቃብሩ ውስጥ አልገባም ነበር። ከዚያ በኋላ እርሱም ጴጥሮስን ተከትሎ ወደ መቃብሩ ውስጥ ገባ። ዮሐንስ የከፈኑን ጨርቅ ሲመለከት፥ በክርስቶስ ትንሣኤ አመነ።

መ. ቶማስ በሌለበት አሥሩ ደቀ መዛሙርት፡- በራቸውን ዘግተው ቁጭ ብለው ሳሉ ክርስቶስ በአምላካዊ ባሕሪው በደቀ መዛሙርቱ መካከል ተገኘ። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ሦስት ነገሮችን አድርጓል፡-

 1. ክርስቶስ ሐዋርያቱ (የተላኩ ማለት ነው) አድርጎ ሾማቸው። እግዚአብሔር እርሱን በላከበት ሁኔታና ሥልጣን፥ ክርስቶስ ለዓለም ወኪሎቹ አድርጎ ላካቸው።
 2. ከዚያም ክርስቶስ በእስትንፋስ መንፈስ ቅዱስን ሰጣቸው። ከዚያ በኋላ የምስክርነት ኃይላቸው ይመጣ የነበረው ከመንፈስ ቅዱስ ነበር። ይህ ክስተት ምን ትርጉም ይሰጣል? የመንፈስ ቅዱስ ሙሉ ህልውና በዚህ ጊዜ አለመኖሩን ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 እንመለከታለን። በመሆኑም፥ ሁለት አማራጮች ነበሩ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ከ50 ቀናት በኋላ በበዓለ ኀምሳ ቀን ስለሚሆነው ነገር እየተነበየ ነበር። የእርሱ እስትንፋስ ተስፋ በሰጠው መሠረት፥ መንፈስ ቅዱስ በቅርቡ እንደሚመጣላቸው የሚያሳይ ውጫዊ ተምሳሌት ነበር። ሁለተኛው፥ ክርስቶስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ ሙሉውና ዘላቂው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እስኪመጣላቸው ድረስ በእምነትና በታማኝነት እንዲቆዩ ለማድረግ ጊዚያዊ የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ሰጥቷቸዋል።
 3. ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ይኖራቸዋል። ይህ ጥቅስ በግሪኩ፥ «ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይቅርታን አግኝተዋል። ይቅር ያላላችኋቸው ይቅርታን አላገኙም» ይላል። ክርስቶስ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት ፍጹም ሥልጣን አልሰጣቸውም። ነገር ግን ይህ ምንባብ እንደሚያሳየው፥ በመንግሥተ ሰማይ የሚሆነውን ነገር እንዲያውጁ ብቻ ሥልጣን ሰጣቸው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ያመኑትን ይቅር ስላለ፥ ይቅርታ መስጠቱን ለማወጅ ሥልጣን ነበራቸው። ነገር ግን ሰዎች በክርስቶስ ካላመኑ፥ ይቅርታን እንዳላገኙ ለማወጅ ሥልጣን አላቸው ማለት እንጂ፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ሐዋርያ ንስሐ ያልገባ ሰው እንደሚድን ወይም ንስሐ የገባ ሰው እንደማይድን ያወጀበትን ሁኔታ አንመለከትም። ይቅርታን ለመስጠት ሥልጣኑ የእግዚአብሔር እንጂ የሰዎች አይደለም። ነገር ግን በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ተመሥርተን፥ በክርስቶስ ያመኑ ወገኖች ኃጢአት ይቅር እንደሚባል ለማሳወቅ፥ ያላመኑ ሰዎች ደግሞ ይቅርታን እንደማያገኙ ለማስጠንቀቅ እንችላለን።

ሠ. ኢየሱስ ቶማስ ባለበት ከአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ጋር ተገናኘ። ቶማስ ኢየሱስ ለአሥሩ ደቀ መዛሙርት በታየ ጊዜ አብሯቸው ስላልነበረ፥ በክርስቶስ ትንሣኤ ለማመን ተቸገረ። በክርስቶስ ጎንና በእግሮቹ ላይ የነበረውን ቁስል ዳስሶ ከተመለከተ በኋላ አመነ። ቶማስ ኢየሱስ በምድር ከነበረበት ጊዜ አንሥቶ በአማኞች ሁሉ ላይ ለሚታየው ነገር ተምሳሌት ሆኗል። አንደኛው፥ ክርስቶስን «ጌታዬና አምላኬ» ማለቱ ክርስቲያኖች ሁሉ ሊኖራቸው የሚገባው እምነት ነው። ክርስቶስ ተራ ሰው ሳይሆን፥ እንደ እግዚአብሔር አብ ያለ ፍጹም አምላክ ነው። ሁለተኛው፥ ቶማስ መሆን ለሌለብን ነገር ምሳሌ ነው። ቶማስ ክርስቶስን በዓይኖቹ እስከሚያይ ድረስ ለማመን ፈቃደኛ አልሆነም ነበር። ነገር ግን በዓይናቸው ሳያዩ ትንሣኤውን የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው። ማንኛችንም ብንሆን ድነትን (ደኅንነትን) አግኝተን ወደ መንግሥተ ሰማይ ከመሄዳችን በፊት፥ ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን በአካል ልናየው አንችልም። ወደ መንግሥተ ሰማያት ስንሄድ ግን እናየዋለን። እስከዚያው ግን በዚህች ምድር ላይ እንደ ኖረ፥ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ በእምነት ዓይናችን እናየዋለን። የዕብራውያን ጸሐፊ እንዳለው፥ «እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው» (ዕብ 11፡1)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኢየሱስ መታሰር፣ በሐናኒያና በጲላጢስ ፊት መቅረብ (ዮሐ. 18፡1-19፡16)

የወንጌል ማዕከል የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ካላተኮሩ የትኞቹም የወንጌል ታሪኮች ሙሉ ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም፥ እያንዳንዳቸው ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከራሳቸው ልዩ ገጽታ አንጻር ተርከዋል። ዮሐንስ ወይም ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር፥ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ይልቅ በእነዚያ የመጨረሻ ቀኖች ስለተፈጸሙት ድርጊቶች ብዙ ጽፎአል። ስለሆነም፥ ዮሐንስ በእነዚያ ጥቂት ሰዓታት በኢየሱስ ላይ ስለተፈጸሙት ነገሮች ከራሱ ዕይታ አንጻር የተለየ አመለካከት ያስጨብጠናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 18–19 አንብብ። ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ክርስቶስ ምንን እንማራለን? በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ውስጥ ስለ ክርስቶስ ያልተጠቀሱ ምን የተለዩ ነገሮች አሉ?

 1. የኢየሱስ መታሰር (ዮሐ 18፡1-11)

ዮሐንስ ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ጽዋው ከእርሱ ታልፍ ዘንድ ያቀረበውን የጭንቅ ጸሎት አልገለጸም። ዮሐንስ ክርስቶስ በዘመናት ሁሉ ለሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ ከጸለየው የሊቀ ክህነቱ ጸሎት በቀጥታ ወደ ሞቱ አምርቷል። ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ በመጨረሻ ሰዓታት ከሚያስተምራቸው ዐበይት እውነቶች አንዱ፥ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚችል መሆኑን ነው። በክርስቶስ የደረሰው ነገር ሁሉ ድንገተኛ አልነበረም። ክርስቶስ እንደሚታሰር ያውቅ ነበር። ቀደም ሲል ክርስቶስ ሰዎች ሊገድሉት ወይም ሊያስሩት በሚመጡበት ጊዜ ጥሎአቸው ዘወር ይል ነበር። አሁን ግን ይዘው ሊያስሩት ወደ መጡት ሰዎች ሄዷል። ክርስቶስ፥ ጴጥሮስ ሰይፉን ወደ ሰገባው እንዲመልስ ባዘዘው ጊዜ፥ «አብ የሰጠኝን ጽዋ ልጠጣ አይገባኝምን?» ብሏል። የመሞቻ ጊዜው ስለ ደረሰ ይህንኑ እያወቀ እንደ መሥዋዕት በግ ሞቱን ለመቀበል ሄደ።

ዮሐንስ በተጨማሪም በእነዚያ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት እንኳ ክርስቶስ ኃይልና ሥልጣን እንደ ነበረው አሳይቷል። ኃይልና ግርማው ታላቅ በመሆኑ ይዘው ሊያስሩት ወደ መጡት ሰዎች ሲሄድና ሲያዩት ሁሉም መሬት ላይ ወድቀዋል። በመጨረሻው ዘመን ዓለማውያን ያንን የክርስቶስን ቀን ለመቀበል እንደሚገደዱ ሁሉ፥ ሊይዙት የመጡ ወታደሮችም ከፊቱ ለመንበርከክ ተገድደዋል።

ለክርስቶስ ለመዋጋት ሰይፍ ያነሣው ስምዖን ጴጥሮስ መሆኑን የሚነግረን፥ የዮሐንስ ወንጌል ብቻ ነው። ዮሐንስ በተጨማሪም፥ ጆሮው የተቆረጠበት የሊቀ ካህናቱ ባሪያ ስሙ ማልኮስ ይባል እንደ ነበር ገልጾአል። ይህም ዮሐንስ ሁኔታውን በዓይኑ ያየ ሰው ብቻ ሳይሆን፥ ምናልባትም ማልኮስን ሳያውቀው እንደማይቀር ያሳያል።

 1. ኢየሱስ በሐናንያ ፊት ቀረበ (ዮሐ 18፡12-27)

የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ኢየሱስ በወቅቱ ሊቀ ካህናት በነበረው በቀያፋ ፊት መቅረቡን ሲናገሩ፥ የዮሐንስ ወንጌል ደግሞ በሐናንያ ፊት መቅረቡን ይናገራል። ሮማውያን ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት ሐናንያን ከሹመቱ አንሥተውት ነበር (15 ዓ.ም)። ነገር ግን አይሁዶች አሁንም እንደ ሊቀ ካህናት በመቁጠር ከሕጋዊው ሊቀ ካህናቱ በስተጀርባ ሆኖ ተሳትፎ እንዲኖረው ሳያደርጉ አልቀሩም። (ቀያፋ የሐናንያ አማች ነበር።)

በርካታ ምሑራን ለራሱና ለጴጥሮስ ወደ ሐናንያ ግቢ የመግቢያ ፈቃድ ያገኘውና ሁኔታውን ሲከታተል የነበረው፥ «ሌላው ደቀ መዝሙር» ዮሐንስ እንደ ሆነ ይናገራሉ። ዮሐንስ የሀብታም ቤተሰብ በመሆኑ፥ ሊቀ ካህናቱን ለማወቅ ዕድል ነበረው። ዮሐንስ ከሌሎቹ ወንጌላውያን ይልቅ ስለ ጴጥሮስ ክህደት ዝርዝር ጉዳዮችን ጠቃቅሷል። ዮሐንስ፥ ጴጥሮስ የክርስቶስ ተከታይ እንደሆነ በመግለጽ ከከሰሱት ሰዎች አንዳንዶቹን እንደሚያውቅ በመግለጽ፥ ክህደቱን በስፍራው ተገኝቶ እንደ ታዘበ አመልክቷል።

 1. ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት ቀረበ (ዮሐ 18፡28–19፡16)

ዮሐንስ ስለ ምርመራው ሊገልጽ፥ በክርስቶስና በጲላጦስ ንግግር ላይ ትኩረት ሰጥቷል። ዮሐንስ ስለ ኢየሱስና ስለ ጲላጦስ ምላሽ ሦስት እውነቶችን አብራርቷል።

ሀ. ጲላጦስ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ መሆን አለመሆኑን ሲጠይ፥ (ይህ ለሮም መንግሥት ክህደት ነበር)፤ ኢየሱስ የሰጠው መልስ ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር። አንደኛው፥ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ መሆኑን ለጲላጦስ ገለጸ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፥ መንግሥቱ ሰማያዊና መንፈሳዊ እንጂ ምድራዊ አለመሆኑን አስረዳ፥ የሮም መንግሥት በዚህ ስጋት ሊይዘው እንደማይገባ አመልክቷል።

ለ. ከዚያም ኢየሱስ ጥያቄውን በመንተራስ ጲላጦስን ተቋቋመው። ኢየሱስ ለእውነት፥ ለፍትሕ፥ ለጽድቅና እግዚአብሔርንም ደስ ለሚያሰኝ ነገር የቆሙት ሁሉ እንደሚሰሙት ገለጸ። ጲላጦስ ብዙ ሃይማኖቶች በተነሡበት አገር ስላደገ፥ የትኛው ሃይማኖት ትክክል እንደሆነ አያውቅም ነበር። በተጨማሪም፥ ተወልዶ ያደገው ስለ ሥልጣን እንጂ ስለ እውነት ምንም ግድ በሌለው ሕዝብ ዘንድ ነበር። ለእርሱ እውነት ምንም ማለት አልነበረም። ጲላጦስ ምንም እንኳ ክርስቶስን ከእስር ለመፍታት ቢፈልግም፥ እውነትን ለክብሩ ወይም ለስሙ ሲል በመለወጥ እንዲሰቀል ፈቅዷል። እርሱ ክርስቶስ እንዲሰቀል የተስማማው፥ «የቄሣር ወዳጅ» አይደለም ተብሎ እንዳይወቀስ በመፍራት ነበር። ይህም ሥራውን ከማሳጣት አልፎ ሞትን ሊያስከትልበት ይችል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ እውነትን ለሰላም፥ ከሰዎች ሞገስ ለማግኘት፥ ወይም ለግል ጥቅም ስንል እንደምንዘነጋ የሚገልጽ አንድ ምሳሌ ስጥ። ለ) በቤተ ክርስቲያንህ እውነትን ወደ ጎን ገፍተው፥ ሌላ ውሳኔ የሰጡበትን ሁኔታ አስረዳ። እውነትንና ፍትሕን ቢያከብሩ ኖሮ ምን ይመስኑ ነበር?

ሐ. ጲላጦስ ክርስቶስ ንጹሕ እንደሆነ በተደጋጋሚ ከገለጸ በኋላ፥ አይሁዶች ክርስቶስን ለመግደል የፈለጉበት ዋነኛው ምክንያት የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ በማለቱ እንደሆነ ተናገሩ። ይህም ጲላጦስን አስፈራው። ክርስቶስ መለኮት መሆኑን በግልጽ እንዲናገር ቢጠይቀውም፤ እርሱ ግን መልስ አልሰጠውም። ነገር ግን ጲላጦስ ሕይወቱን የማጥፋት ሥልጣን እንዳለው ሲናገር፥ ክርስቶስ ሥልጣኑን እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ገለጸ። ማንኛውም ፖለቲካዊ መሪ በራሱ ሥልጣን የለውም። በመጀመሪያ፥ ሥልጣን የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው (ዳን. 4፡17)። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ ስለሚቆጣጠር፥ መሪዎች የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ዕቅድ የሚለጥ ውሳኔ ሊያስተላልፉ አይችሉም።

አሕዛብ ሆኖ ሳለ የክርስቶስን ንጽሕና ለማወጅና በነፃ ለማሰናበት ጲላጦስ የተለያዩ መንገዶችን በሚሞክርበት ወቅት አይሁዶች፥ በተለይም መሪዎቹ ያደረጉት ታላቅ ክፋት በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ተገልጾአል። እነዚህ መሪዎች ለፍትሕ ግድ ስላልነበራቸው፥ ሕገወጥና በኃይል ላይ የተመሠረተ ምርመራ በክርስቶስ ላይ ፈጸሙ። አይሁዶች የሕግ ሰው (ጲላጦስ) የሰጠውን ውሳኔ በመጣስ ክርስቶስን ለመግደል ቆረጡ። ስለሆነም፥ ክርስቶስ በዚህ ጉዳይ እነርሱ ከጲላጦስ የከፉ መሆናቸውን ገልጾአል። አይሁዶች የሚያከብሩት ንጉሥ ቄሣር ብቻ መሆኑን በግልጽ ዐወጁ። ይህ ከብሉይ ኪዳን ትምህርት ጋር ፍጹም የማይስማማ አሳብ ነበር። አይሁዶች ሁል ጊዜም እግዚአብሔር ንጉሣቸው እንደሆነ ያምኑ ነበር (1ኛ ሳሙ. 8፡7)። ማንኛውም ምድራዊ ንጉሥ የሚወክለው ራሱን ብቻ ነው። በዚህ አሳባላቸው ግን የልባቸውን እውነተኛ ገጽታ አሳይተዋል። ሃይማኖተኞች ቢሆኑም እንኳ፥ እግዚአብሔር እንዲገዛቸው ከልባቸው አይፈቅዱም ነበር። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ንጉሣቸው አልነበረም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስ ንጉሥነት በሕይወትህ የታየባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ሌላ ነገር ወይም የራሳችን ፈቃድ ንጉሣችን እንዲሆን መፍቀድ ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው?

የክርስቶስ የሊቀ ካህንነት ጸሎት (ዮሐ. 17:1-26)

በዕብ 4፡14-16፤ 7፡25 ላይ ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን እንደሆነና እንደሚማልድልን ተገልጾአል። እርሱ የሚጸልየው ስለ ምንድን ነው? ለእርሱ አስፈላጊ ነገር ምንድን ነው? እርሱ የሚጸልየው ስለ ሥጋዊ ጤንነታችን፥ ከአደጋ ስለ መትረፋችን፥ ስለ ቁሳዊ በረከት ነው? በዮሐንስ 17 ላይ ክርስቶስ እንደ ሊቀ ካህናችን ስለምን እንደሚጸልይ የሚያሳይ ምሳሌ አለ። ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቶስ ልቡን ከፍቶ የጸለየበትን አጋጣሚ ተገንዝቦአል። የጸለየውም ለራሱ፥ አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፥ ለእናንተና ለእኔ ነው። ከከርስቶስ ጸሎት ምን እንማራለን?

ሀ. በጸሎታችን ሁሉ ቀዳሚው ጥያቄአችን መሆን ያለበት የእግዚአብሔር ክብር ነው። ሊያሳስበን የሚገባው የፍላጎታችን መሟላት መሆን የለበትም። ለእግዚአብሔር ክብርን ስለሚያመጣው ነገር ሳይሆን እኛ ለምንፈልጋቸው ነገሮች የምንጸልይ ከሆነ፥ እንደ ክርስቶስ ፈቃድ እየጸለይን አይደለም። ክርስቶስ እግዚአብሔርን በሚያከብርበት ጊዜ እግዚአብሔርም እርሱን እንደሚያከብረው በመገንዘብ፥ እግዚአብሔርን ለማክበር ፈለገ። ይህ ለእኛም እውነት ነው። በእግዚአብሔርና እርሱን በሚያስከብሩ ነገሮች ላይ ስናተኩር፥ እግዚአብሔርም እኛን ያከብረናል። ለመሆኑ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ያከበረው እንዴት ነው? ክርስቶስ እግዚአብሔርን ያከበረው እንዲያደርግ የነገረውን ነገር ሁሉ በማድረግ ነው። ክርስቶስ ሲያስተምር፥ ተአምራትን ሲሠራና ሞትን ሲቀበል፥ እግዚአብሔርን እያከበረ ነበር። እኛም እግዚአብሔርን የምናከብረው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ብቻ ሳይሆን፥ በዕለት ተዕለት እርምጃችን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ስናደርግ ብቻ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች እግዚአብሔርን እያከበሩ እንደሆነ ላያውቁ ይችላሉ። እግዚአብሔር ግን ያውቃል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔርን ሊያከብሩ ይችላሉ ብለህ ያቀረብሃቸው ጸሎቶች የትኞቹ ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ለእርሱ መገዛትህንና እርሱን ማክበርህን ታሳይ ዘንድ እንድታከናውናቸው የጠየቀህ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

የክርስቶስ ጸሎት ስለ ራሱ የነበረውን ቁልፍ ግንዛቤ ያንጸባርቃል። አንደኛው፥ ስለ ማንነቱ የነበረው ግንዛቤ ነው። እርሱ እግዚአብሔር ወልድ ነው፤ ለአብ የሚገዛ ነው፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ ነው።

ሁለተኛው፥ እርሱ በሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት ላይ ሥልጣን አለው። ክርስቶስ ከአብ የተቀበላቸውና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ያመኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን ያገኛሉ። ሦስተኛው፥ በዚህ ክፍል የዘላለም ሕይወት ተብሎ የተጠራው ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው ክርስቶስን ወደ ምድር በላከው በእግዚአብሔር አብና ለሰው ልጆች ኃጢአት በሞተው በክርስቶስ ነው።

ለ. ጸሎት ስለ ማንነታችን ባለን ግንዛቤ ላይ ይመሠርታል። ክርስቶስ ለአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጸልዮአል። እነዚህ እውነቶች ዛሬም ለእኛ ይጠቅማሉ። አንደኛው፥ ደቀ መዛሙርት የሚባሉት እግዚአብሔርን «ያዩ» ናቸው። ክርስቶስ እግዚአብሔርን ለአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መገለጡን እንደ ተናገረ ሁሉ፥ መንፈስ ቅዱስ እኛን ወደ ክርስቶስ በሚያመጣን ጊዜ እግዚአብሔር አብ ማን እንደሆነ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነና እኛም እንዴት ከእነርሱ ጋር ልንዛመድ እንደምንችል በመግለጥ ይጀምራል። ሁለተኛው፥ ደቀ መዛሙርት ከዓለም «ተጠርተው የወጡ» ወይም የተለዩ ናቸው። ዓለም ከምትከተለው ሕይወት ስለ ተለየን፥ በዓለም የሚኖሩ ሰዎች ከሚከተሉት የሕይወት ዘይቤ ተለይተን እንኖራለን። በቀዳሚነት ግን እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንንና ሌሎቹ ግን ስላልሆኑ፥ በዚህ ተለይተናል።

ሐ. ጸሎት የታዛዥነት ሕይወት ምልክት ነው። ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤታችን ብቻ የምንጸልየው ሳይሆን፥ ለዘለቄታው ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ግንኙነት ነው። ያ ግንኙነት ደግሞ የታዛዥነትን ሕይወት ይጠይቃል። አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከክርስቶስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለመጠበቅ መታዘዛቸው አስፈላጊ እንደ ነበረ ሁሉ፥ እኛም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ልንመጣ የምንችለው በመገዛትና በመታዘዝ የተመላለስን እንደሆነ ነው።

መ. ክርስቶስ በጸሎቱ ጊዜ በቀዳሚነት የጠየቀው በደቀ መዛሙርቱ መካከል አንድነትና ስምምነት እንዲኖር ነበር። ክርስቶስ እግዚአብሔር በስሙ ኃይል እንዲጠብቃቸው ጠይቋል። ነገር ግን ክርስቶስ የጠየቀው ለአካላዊ ጥበቃ ወይም ከሰይጣን ስለሚደርስባቸው ጥቃት አልነበረም። እግዚአብሔር ደቀ መዛሙርቱን ከስደት ነፃ እንዲያደርጋቸው ወይም ቁሳዊ ሀብት እንዲሰጣቸው አልጠየቃቸውም። ክርስቶስ የጠየቀው ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር አብና ወልድ ያላቸውን ዓይነት አንድነትና ስምምነት እንዲኖራቸው ነው። ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው በፍቅርና በአንድነት መመላለሳቸው ክርስቶስ ከሰማይ በእግዚአብሔር የተላከ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሆነ ገልጾአል። አንድነታችን የእግዚአብሔር አብን፥ የእግዚአብሔር ወልድንና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አንድነት ማንጸባረቅ አለበት።

ክርስቶስ እግዚአብሔርን የጠየቀው ሁለተኛው የጸሎት ጥያቄ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት በቅድስና እንዲጠብቃቸው ነበር። ከዓለም በመለየት፥ ወደ ገዳም በመግባት ወይም ክርስቲያኖች ብቻ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ በመኖርና ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ባለማድረግ፥ የቅድስናን ሕይወት መኖር አይቻልም። ቅድስና የሚመጣው ለክርስቶስ በመታዘዝ ነው። የመታዘዝ ሕይወት የሚገኘው ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት በማወቅ ነው። ከዓለም የምንለየው ክርስቲያን ካልሆኑት ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ባለማድረግ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት በመጠበቅ ብቻ ነው።

ሦስተኛው የጸሎት ጥያቄ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ፥ ሙሉ ክብሩን ወደምናይበት ሰማይ መሄድ እንድንችል ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእግዚአብሔር ጋር በታዛዥነት ሕይወት ለመኖር ልናውቃቸው የሚገቡን የቃሉ እውነቶች ምንድን ናቸው? ለ) ኢየሱስ ካቀረባቸው ሦስት ጸሎቶች መካከል እኛ ልናደርገው የሚከብደን የትኛው ነው? ለምን? ሐ) ክርስቶስ ስለ ብዙ ነገሮች ሊጸልይልን ሲችል፥ በእነዚህ ሦስቱ ብቻ የተወሰነው ለምን ይመስልሃል? መ) የክርስቶስን ጸሎት እኛ ዘወትር ከምንጸልይባቸው ርእሶች ጋር በማነጻጸር ተመሳሳይነታቸውንና ልዩነታቸውን አውጣ። ጸሎትህ የኢየሱስን ጸሎት እንዲመስል ምን ለውጥ ማድረግ አለብህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዮሐ. 16:1-33

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የመንፈስ ቅዱስ ትልቁ አገልግሎት ምን እንደ ሆነ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የሙሉ ወንጌል፥ የመካነ ኢየሱስና የቃለ ሕይወት ክርስቲያኖችን ጠይቅ። መልሶቻቸውን በወረቀት ላይ ጻፍ። ለ) የመንፈስ ቅዱስ ትልቁ አገልግሎት ምን ይመስልሃል? ሐ) ዮሐ 16፡5-16 አንብብ። በዚህ ክፍል ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱለ ትልቁ አገልግሎት ምንድን ነው አለ? መ) አብዛኛቹ ክርስቲያኖች የመንፈስ ቅዱስ ትልቁ አገልግሎት እንደ ሆነ የሚያስቡት ክርስቶስ የተናገረውን ነው ወይስ ሌላ ነገር? መልስህን አብራራ። አንዳንድ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ክርስቶስ ከተናገረው ውጭ እንደ ሆነ የሚያስቡት ለምንድን ነው?

እስካሁን ድረስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን የመጨረሻውን ዐቢይ ትምህርት ስናጠና ቆይተናል። በሞት ሊለይ ጥቂት ጊዜ ብቻ የቀረው አባት፥ ለልጆቹ ጠቃሚ ምክሮችን ለመስጠት እንደሚፈልግ ሁሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከመሞቱ በፊት እጅግ ዐበይት ከሆኑ እውነቶቹ መካከል፥ አንዳንዶቹን ለደቀ መዛሙርት አስተምሯል። ክርስቶስ ካስተማራቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት ነው። ስለ መንፈስ ቅዱስ ግልጽና ሚዛናዊ ግንዛቤ ለመጨበጥ ከፈለግን፤ ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ስለ መንፈስ ቅዱስ መሠረታዊ ዓላማ ያሰማውን ትምህርት መረዳት አለብን።

 1. ክርስቶስ እርሱን የሚከተሉ ሰዎች ስደትና ሞት እንደሚደርስባቸው ለደቀ መዛሙርቱ አስጠነቀቀ (ዮሐ 16፡1-4)።

አብዛኛውን ጊዜ ለአዲስ አማኞች የወንጌልን አዎንታዊ ጎኖች ብቻ ስለምንነግራቸው እንሳሳታለን። ስለ ድነት (ደኅንነት)፥ የዘላለም ሕይወት፣ ክርስቶስ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጣቸው፥ ከበሽታም እንደሚፈውሳቸው እንነግራቸዋለን። ይህ የበረከት ገጽታው ነው። ወንጌሉ ሌላም ገጽታ አለው፥ ፈተና፥ ቅጣትና ስደት በአማኞች ላይ ሊደርስ ይችላል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለቱንም የወንጌል ገጽታዎች ነበር የገለጸላቸው። ክርስቶስ በእርሱ ለሚያምኑ የዘላለም ሕይወትን፥ ሰላምንና ደስታን እንደሚሰጣቸው ተናግሯል። በተጨማሪም፥ ስደት እንደሚያጋጥማቸው ከመግለጽ አልተቆጠበም። ክርስቶስ እንደ ተጠላ ሁሉ እነርሱም ይጠላሉ።

ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከአይሁድ ምኩራብ እንደሚባረሩ ገልጾላቸዋል። አይሁዶች የክርስቶስን ተከታዮች በመግደላቸው፥ እግዚአብሔርን ያገለገሉ እየመሰላቸው ደቀ መዛሙርቱን በመግደልና በመጥላት አሳድደዋቸዋል። (እስጢፋኖስ እና ያዕቆብ ለዚህ ተስማሚ ምሳሌዎች ናቸው። የሐዋ. 7፡54-60፤ 12፡2-3)። አይሁዶች በዚህ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን እያስደሰቱ ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ኅብረት እንዳልነበራቸው የሚያመለክት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለአንድ ሰው በምንመሰክርበት ጊዜ ክርስቶስን መከተል የሚያስከፍለውን ዋጋ ጨምረን ብንገልጽለት፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የወንጌል ምስክርነት የሚለወጠው እንዴት ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን መከተል ስለሚጠይቀው ኃላፊነት የማንናገረው ለምንድን ነው?

 1. ክርስቶስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ስለሚመጣው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ አስተማረ (ዮሐ 16፡5-16)

ክርስቶስ ለተከታዩቹ ሁሉ ስለሚሰጣቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተጨማሪ ገለጻ ይሰጣል። ኢየሱስ በምድር ላይ ከሚቆይ ይልቅ ቢሄድ እንደሚሻል፥ ለደቀ መዛሙርቱ ገልጾአል። ለተከታዮቹ በሙሉ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው እርሱ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ብቻ ስለሆነ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ዐቢይ አገልግሎት ምን እንደሆነ ክርስቶስ የተናገረውን ልብ ብለህ አስብ።

ሀ. መንፈስ ቅዱስ ላላመኑ ሰዎች የሚሰጠው አገልግሎት አለው። አገልግሎቱም ኃጢአተኞች መሆናቸውን ማስገንዘብና አዳኝም እንደሚያስፈልጋቸው መግለጽ ነው። የማያምኑ ሰዎች የሚገሠጹበት ትልቁ ኃጢአት ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ መሆኑን አለማመናቸው ነው። በክርስቶስ በሚያምኑበት ጊዜ እንደማይኮንናቸው ያሳውቃቸዋል፥ ይህም ጻድቃን እንደሚሆኑ ያሳያል። በክርስቶስ ባለማመናቸው እግዚአብሔር ስለሚያወጣባቸው ፍርድ ያስጠነቅቃቸዋል። በተጨማሪም፥ የዓለም ገዥ የሆነው ሰይጣን እንደተሸነፈና ከእንግዲህ እርሱን መፍራትም ሆነ የሐሰት ትምህርቱን መከተል እንደሌለባቸው ያረጋግጥላቸዋል።

ምስክርነት የሁለት ወገኖች ተግባር ነው። በሰዎች ዘንድ እግዚአብሔር ለሚያምኑ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ፥ እንዲሁም በዚህም ስለሚሰጣቸው የዘላለም ሕይወት፥ ለማያምኑ ሰዎች ደግሞ ስለሚጠብቃቸው የዘላለም ሞት እንድንናገር አዝዞናል። ይሁንና ይህን ተግባር ሰዎች ብቻ የሚያከናውኑት ከሆነ ማንም ሰው ወደ እምነት አይመጣም። ሰዎች በመንፈሳቸው ሙት ናቸው። ሰይጣንም ሊበጥሱት በማይችሉት ሰንሰለት ተብትቦ አለሯቸዋል። ስለዚህ በሥራው ላይ እግዚአብሔርም መሳተፍ አለበት። መንፈስ ቅዱስ ለሰዎች በምናካፍላቸው ቃል አማካይነት መንፈሳዊ ዓይኖቻቸውንና አእምሯቸውን ይከፈታል። ይህም የተመሰከረላቸው ሰዎች ወንጌሉን እንዲረዱት ያደርጋል። በዚህ ጊዜ ዓለማዊው ሰው በክርስቶስ ያምናል።

ለ. መንፈስ ቅዱስ በአማኞችም መካከል ያገለግላል። ክርስቲያኖችን ያስተምራል፣ ወደ እውነትም ይመራቸዋል። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት የሚያገኘው ከየት ነው? መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረው ከኢየሱስ የተቀበለውን ብቻ እንደ ሆነ ራሱ ገልጾአል።

ሐ. መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን ያስከብራል። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ተግባር ነው። በሌላ አገላለጽ፥ መንፈስ ቅዱስ ዓለምን በኃጢአቱ በመውቀስ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ ሲያደርግና ክርስቲያኖች እውነትን እውቀው እንዲኖሩበት ሲመራቸው፥ በዚያን ጊዜ ክርስቶስ ከፍ ከፍ ይላል።

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ ሦስት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች ተግባራዊ ሲሆኑ ያየህባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር።

ክርስቶስ በብዙ የተለያዩ መንገዶች ይከብራል። በዕለተ ሰንበት ብቻ ሳይሆን በየቀኑ ለእርሱ እየተገዛን ስሙን ከፍ ስናደርግ፥ ትእዛዛቱን ስንጠብቅ፥ እርሱን ስንመስልና ለሌሎች ስለ እርሱ ስንመሰክር ይከብራል።

 1. ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱ ኀዘን ወደ ደስታ እንደሚለወጥ ተነበየ (ዮሐ. 16፡17-33)።

ዓላማ እንዳለንና የደስታም ቀን እንደሚመጣልን ስናውቅ፥ ይህ ችግሮችን ለመታገሥ ይረዳል። ነገር ግን ችግሮች ለምን እንደ ደረሱብን ካላወቅን ወይም የደስታ ቀን እንደሚመጣ እርግጠኞች ካልሆንን፥ በቀላሉ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። እርጉዝ የሆነች ሴት የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስ የሚያጋጥማትን የምጥ ችግር ታግሣ መቋቋም ይኖርባታል። ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ስለሚመጣው «ኅዘን»፥ እንዲሁም ስለሚያጋጥማቸው «ደስታ» አብራርቶ አስተምሯቸዋል።

ሀ. ኀዘን፡- በደቀ መዛሙርቱ ላይ የሚመጣው ኀዘን ሁለት ደረጃዎች ይኖሩታል። አንደኛው፥ ደቀ መዛሙርቱ ከፍተኛ ኀዘን የሚደርስባቸው ጌታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ወንጀለኛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ነው። በዚህ ጊዜ ተስፋቸው ሁሉ ይመነምናል። በአንጻሩ የክርስቶስ ጠላቶች እርሱ ለችግራቸው መፍትሔ ሆኖ ሲሞት በሚመለከቱበት ጊዜ እጅግ ደስ ይሰኛሉ። ሁለተኛው፥ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር አብ በሚመለስበት ጊዜ በመጠኑ ያዝናሉ። ይህን ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ከሚወዱት ከኢየሱስ በአካል ይለያሉ።

ለ ደስታ፡– ይህ ሦስት ደረጃዎች ይኖሩታል። አንደኛው፥ ክርስቶስ ከሞት ተነሥቶ በሕይወት ሲያገኙት ደስ ይላቸዋል። ሁለተኛው፥ በክርስቶስ አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ግንኙነት ስለሚኖራቸው ደስ ይላቸዋል። የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን፥ ጸሎታችንን ሰምቶ እንደሚመልስልን በመገንዘብ ወደ እርሱ የምንቀርብበት በር ተከፍቶልናል። ሦስተኛው፥ ክርስቶስ ዳግም በሚመለስበት ጊዜ ዘላቂ ደስታ ይኖረናል። ከክርስቶስ በአካል መለያየታችን ያበቃል። ችግሮቻችንና ስደቶቻችን አክትመው በታላቁ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር እንኖራለን። ጳውሎስ እንዳለው፥ «ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፥ የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው» (2ኛ ቆሮ. 4፡16-18)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሕይወትህ ያጋጠሙህን አንዳንድ ኅዘኖች ዘርዝር። ለ) በኀዘንህ ወቅት እግዚአብሔር ምን አስተማረህ? ሐ) በኀዘንህ ጊዜ ተስፋ ሳትቆርጥ እንድትኖር ያደረገህ ነገር ምንድን ነው? መ) በመከራ ጊዜ ዓይኖቻችንን በዘላለሙ ተስፋችን ላይ ማሳረፉ ለምን ይጠቅማል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የወይን ግንድና ቅርንጫፎቹ ምሳሌ እና ዓለም የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት መጥላት (ዮሐ. 15፡1-27)

 1. ክርስቶስ የወይን ግንድ ማለትም የተከታዮቹ መንፈሳዊ ሕይወትና ፍሬያማነት ምንጭ ነው (ዮሐ. 15፡1-17)

መንፈሳውያን ለመሆናችን ትልቁ መረጃው ምንድን ነው? በልሳን መናገራችን? ሌሎችን መፈወሳችን? ምስክርነት? ወይስ አምልኮ? መንፈሳውያን ለመሆናችን ትልቁ ምልከት ፍቅር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ገልጾአል። ይህን በሕይወታችን ለመፈጸም ከሁሉም የከበደ መሆኑ ግልጽ ነው። ልንዘምር፥ ልንመሰክር፥ በልሳን ልንናገር እንችላለን። ለሰዎች ሁሉ ከራስ ወዳድነት መንፈስ የጸዳ ፍቅር ከመስጠት ጋር ሲነጻጸር እነዚህ ሁሉ ቀላል ናቸው።

ነገር ግን ፍቅርን የሕይወታችን አካል ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? በዮሐንስ 15፡1-17 ላይ እንደምናነበው ፍቅር ከክርስቶስ ጋር ካለን ኅብረት የሚመነጭ ፍሬ ነው። በእስራኤል አገር በብዛት የሚገኘውን የወይን ተክል በምሳሌነት በመውሰድ፥ ክርስቶስ ምንም እንኳ በመካከላቸው በአካል ባይገኝም ደቀ መዛሙርቱ በፍቅሩ እንዲኖሩ አስተምሯቸዋል። በክርስቶስ መኖር አካላዊ ስፍራን የሚያመለክት ሳይሆን፥ ከእርሱ ጋር ሕያው የሆነ ኅብረት እንድናደርግ የሚያሳስበን ነው። ከክርስቶስ ጋር ሕያው የሆነ ኅብረት እስካለን ድረስ፥ ክርስቶስን መምሰላችን ተፈጥሯዊ ይሆናል። ክርስቶስ ፍቅር ስለሆነ፥ ሌሎችን በልዕለ ተፈጥሯዊ መንገድ እናፈቅራለን። የወይንን ተክል ምሳሌ አድርጎ በመውሰድ፥ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ተጣብቆ መኖር ምን እንደ ሆነ ገልጾአል።

ሀ. የወይኑ ባለቤትና ተካይ እግዚአብሔር አብ ነው። ወይን በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ስፍራዎች አይበቅልም። ወይን ከአንድ ግንድ ብዙ ቅርንጫፎች ያሉት ተክል ነው። ከሌሎች ተክሎች በተቃራኒ፥ ወይን በሚገባ የሚያድገው ሲገረዝ ነው። እንግዲህ ክርስቶስ በወይን ምሳሌ እግዚአብሔር አብ በሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል እንደሚሠራ እየነገረን ነው። ሕይወታችን ፍሬያማ እንዲሆን ስለሚፈልግ፥ ያለማቋረጥ ይንከባከበናል።

ለ. ክርስቶስ የወይን ግንድ ነው። ሰባተኛው የክርስቶስ «እኔ ነኝ» ዓረፍተ ነገር «እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ» የሚለው ነው (ዮሐ 15፡1)። ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ኅብረት እንዳላቸው የሚናገሩ ሌሎች ሃይማኖቶችና አስተማሪዎች አሉ። ነገር ግን የትኞቹም እውነተኛ ወይን አይደሉም። ቅርንጫፎቹ (የክርስቶስ ተከታዮች) ሁሉ ከእርሱ ጋር የተጣበቁ ናቸው። መንፈሳዊ ሕይወታችን የሚፈሰው ከእርሱ ነው። ቅርንጫፍ እንደ መሆናችን ፍሬ ልንሰጥ የምንችለው ከክርስቶስ ጋር እውነተኛ ኅብረት ሲኖረን ብቻ ነው።

ሐ. ክርስቲያኖች ሁሉ ልዩ ልዩ ቅርንጫፎች ናቸው። እንደ ቅርንጫፍ፥ ዓላማችን እንዲሁ መኖር ሳይሆን፥ ፍሬ ማፍራት ነው። ፍሬ ልንሰጥ የምንችለው ደግሞ መንፈሳዊ ሕይወታችን ጤናማ ከሆነና መንፈሳዊ ሕይወታችን ከክርስቶስ ጋር ካለን ኅብረት የተነሣ የሚፈስስ ሲሆን ብቻ ነው። ይህም የብርቱካን ተክል ሕይወት ከሥሩና ከግንዱ ወደ ቅርንጫፎች በማለፍ ፍሬ ከሚሰጥበት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው።

መ. እግዚአብሔር አብ (የተክሉ ባለቤትና ገበሬ) እኛን ፍሬያማ ለማድረግ የሚጠቀምባችው ሁለት ዐበይት መሣሪያዎች አሉት። ከእነዚህም፥ አንደኛው መግረዝ ነው። መግረዝ ማለት ዛፉ እንዲያድግና የተሻለ ፍሬ እንዲሰጥ ለማድረግ አንዳንድ አላስፈላጊ ነገሮችን ማስወገድ ነው። በተመሳሳይ መንገድ፥ እግዚአብሔር አብም መንፈሳዊ ፍሬ እንዳናፈራ የሚያደርጉንን ባሕርያት፥ ልማዶችና አመለካከቶችን ከእኛ ያስወግዳል። ይህ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ቅጣት ተብሎ ተጠቅሷል። የዕብራውያን ጸሐፊ እግዚአብሔር ልጆቹ ስለሆንን ይበልጥ ልጆቹን እንድንመስል እንደሚቀጣን ገልጾአል (ዕብ. 12፡4-10)። እርግጥ ነው ቅጣት ለጊዜው ያምማል፤ ዓላማው ግን ይበልጥ ፍሬያማ እንድንሆን ማድረግ ነው። ሁለተኛው፥ መቁረጥ ነው። እግዚአብሔር አብ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቆርጦ ያስወግደዋል። ከዚያም እግዚአብሔር አብ በፍርድ እንደሚያቃጥላቸው ገልጾአል። ምሑራን ይህን በተመለከተ አንድ ዓይነት አቋም የላቸውም። ይህ ክርስቶስን ያልተከተሉና እግዚአብሔርም በሕይወታቸው እንዲሠራ ያልፈቀዱ ሰዎች በዘላለማዊ ሞት እንደሚቀጡ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ክርስቶስን እንከተላለን እያሉ ነገር ግን ይህንኑ የማያደርጉትን እግዚአብሔር እንደሚያስወግዳቸው የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በሕይወታቸው የክርስቶስ ተከታዮች አለመሆናቸውን በማሳየታቸው እግዚአብሔር ፍርድን ያመጣባቸዋል። ወይም ደግሞ ክርስቶስ የሚናገረው ከኃጢአታቸው ንስሐ ለመግባት ያልፈለጉ ሰዎች በሥጋ የሚሞቱት ሞት ይሆናል (የሐዋ. 5፡1-11፤ 1ኛ ቆሮ. 11፡27-30)።

ሠ. እግዚአብሔር አብ የሚፈልገው ትልቁ ፍሬ ነገር ፍቅር ነው። እግዚአብሔርን ልንወድና ከእርሱ ጋር የቅርብ ኅብረት ልናደርግ ይገባል። (እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም አሳብህ፥ በፍጹም ሰውነትህ ውደድ። ማር. 12፡29-30)። እርስ በርሳችንም ልንዋደድ ይገባል። ኢየሱስ ወደ መስቀል ሞቱ ሊሄድ ሲል፥ በተደጋጋሚ የተናገረው ትልቁ ትእዛዝ ይህ ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆናችን ዋነኛው መረጃ ይሄ ነው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ይሞት ዘንድ ከሰማይ ወደ ምድር ያመጣው ፍቅር ነው። ማፍቀር ማለት ሌሎችን በትሕትና ማገልገልና ካስፈለገም ስለ እነርሱ መሞት ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያን ከሆንህበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ሕይወትህን ሲገርዝ (ሲያስተካከል) የቆየው እንዴት ነው? ለ) ከክርስቶስ ጋር ያለህ ግንኙነት በተግባር የሚታየው እንዴት ነው? ሐ) የአንድ ክርስቲያን ትልቁ መረጃ (መለያ) ፍቅር ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ፍቅር ለባልንጀሮቻቸውም ሆነ ለዓለም የማያላዩት ለምን ይመስልሃል? መ) ከሚስትህ፥ ከልጆችህ፥ ከቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን፥ በማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት መርምር። ሕይወትህን የሚመለከት ሰው በእነዚህ ሁሉ ላይ ፍቅርን እያሳየህ ነው ብሎ የሚመሰክርልህ ይመስልሃል? ካልሆነ ለምን? ሠ) የክርቶስን ፍቅር በእነዚህ የሕይወትህ ክፍሎች ሁሉ ልታሳይ የምትችልበትን መንገዶች በምሳሌ ዘርዝር።

 1. ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ (ዮሐ 15፡18-27)

ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀው ፍሬ ፍቅር ነው። ይህ ማለት ግን ሌሎች እኛን ይወዱናል ማለት አይደለም። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከማያምኑ ሰዎች ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስቧል። ኃጢአት የሌለበት የእግዚአብሔር ልጅ ከሰማይ ወደ ምድር የመጣው በፍቅር ምክንያት ነው። ነገር ግን ተጠላ፥ በመስቀልም ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ተደረገ። የእግዚአብሔር ልጆችም ተመሳሳይ ዕጣ ይጠብቃቸዋል። ለሌሎች ፍቅር ለማሳየት ብንፈልግም እንኳ፥ መጠላታችን የማይቀር ነው። በዓለም መጠላታችን ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ወይም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንደሌለው ያረጋግጣል። ክርስቶስ ወደ ዓለም ከመጣ፥ በሰዎች መካከል ከኖረና ወደ እግዚአብሔር አብ መድረስ የምንችልበትን መንገድ ካሳየን በኋላ፥ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር ላይ እንዳመጹ ለመኖር ምንም ማመኻኛ የላቸውም።

ነገር ግን በሚጠላን ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር አለብን? ምንስ ማድረግ አለብን? ዝም እንበል ወይስ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ እንመሥርት? እንዲህ ማድረግ አንችልም። ትልቁ ሥራችን ለዓለም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መመስከር ነው። ይህንን የምናደርገው ብቻችንን ነው? አይደለም። አጽናኝና የእውነት መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ይሆናል። መንፈስ ቅዱስ በምንመሰክርበት ጊዜ ኃይልን መስጠት ብቻ ሳይሆን፥ እርሱ ራሱም ለዓለም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክራል። መንፈስ ቅዱስ ከዳኑት ጋር ከመሥራቱም በተጨማሪ፥ ያልዳኑትን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማምጣት ስለ ኃጢአታቸው ይወቅሳል። መንፈስ ቅዱስ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ አይሰብም። ይልቁንም ትልቁ ዓላማው እንደ ብርሃን የሰዎችን ትኩረትን ወደ ክርስቶስ መሳብ ነው። ያላመኑት በክርስቶስ እንዲያምኑ፥ ያመኑት ደግሞ እርሱን እንዲመስሉና እንዲያመልኩ ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዓለም በክርስቲያኖች ላይ የምታደርሰውን በቃላት ሊገለጽ የማይቻል ጥላቻ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ስጥ። ለ) መንፈስ ቅዱስ፥ ሰው በክርስቶስ እንዲያምን ለማድረግ በልቡ ውስጥ ሲሠራ ያየኸው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን ለመስጠት ቃል ገባ (ዮሐ. 14፡15-31)

በዚህ ክፍል ስለ መንፈስ ቅዱስ ዓላማና አገልግሎት ግልጽ አሳብ የሚያስተላልፉ ትምህርቶች ይገኛሉ። ምንም እንኳ አንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳን መናገርን በመሳሰሉት አንዳንድ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ብቻ ደስ ቢሰኙም፥ የመንፈስ ቅዱስ መሠረታዊ ዓላማና አገልግሎት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ከፈለግን፥ እነዚህን በክርስቶስ የተነገሩትን እውነቶች መረዳት ይኖርብናል።

ሀ. መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አብ በክርስቶስ በኩል ይመጣል።

ለ. መንፈስ ቅዱስ «ሌላው» አጽናኝ ነው። በግሪክ ቋንቋ «ሌላ» የሚለውን ቃል ለመግለጽ የገቡ ሁለት ቃላት አሉ። እነዚህም «በዐይነቱ የተለየ»፤ ሌላው ደግሞ «በዐይነቱ ያው የሆነ» የሚሉ ናቸው። ዮሐንስ የመረጠው «በዐይነቱ ያው የሆነ» የሚለውን ነው። ይህም ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በአካልና በአገልግሎት ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ያመለከተበት ነው።

ሐ. መንፈስ ቅዱስ «አጽናኝ» ነው። «አጽናኝ» የሚለውን ለመግለጽ የገባው የግሪኩ ቃል ብዙ ፍችዎችን ይዟል። በግሪክ፥ ቃሉ ችሎትን የሚያመለክት ሕጋዊ ጽንሰ-አሳብን የያዘ ነው። «አጽናኝ» እንደ ጠበቃ በችሎት ፊት ከተከሳሹ ጎን ቆሞ በአግባቡ እንዲከራከር የሚረዳው ሰው ነው። ስለሆነም፥ የመንፈስ ቅዱስ መሠረታዊ አገልግሎት በችግራችን ጊዜ መጽናናትን መስጠት ብቻ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ፊት ባለን አገልግሎት ጸንተን እንድንቆም ማገዝ ነው።

መ. መንፈስ ቅዱስ «የእውነት መንፈስ» ነው። ከዚህ ስያሜ እንደምንረዳው፥ የመንፈስ ቅዱስ ዐቢይ አገልግሎት ተአምራትን ለማድረግ ኃይልን መስጠት ሳይሆን፥ ሰዎች እውነተኛውን ነገር ተረድተው እንዲኖሩበት መርዳት ነው።

ሠ. መንፈስ ቅዱስ «ለዘላለም» ከእነርሱ ጋር ይኖራል። የመጀመሪያው አጽናኝ የሆነው ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ፥ በፍልስጥኤም አገር ብቻ ኖሮ ወደ ሰማይ ተመልሶአል። መንፈስ ቅዱስ ግን መንፈስ በመሆኑ፥ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ ይገኛል። ስለሆነም፥ አንድ የክርስቶስ ተከታይ በዓለም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ቢገኝ መንፈስ ቅዱስ አብሮት ይሆናል። በተጨማሪም፥ መንፈስ ቅዱስ ከዳንንበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሰማይ እስከምንሄድበት ጊዜ ድረስ ሁልጊዜም አብሮን ይሆናል። መንፈስ ቅዱስ እንደ ክርስቶስ መጥቶ ተመልሶ የሚሄድ ላይሆን፥ ሁልጊዜም አብሮን ይኖራል።

ረ. መንፈስ ቅዱስ ለዓለም አይታይም። የክርስቶስ ተከታዮች ግን በውስጣቸው ስለሚኖር ያውቁታል። ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ውስጥ በቅርቡ ለውጥ እንዲሚኖር ገልጾአል። ክርስቶስን በሚከተሉባት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ከደቀ መዛሙርቱ «ጋር» ነበር። ከበዓለ ኀምሳ በኋላ ግን በደቀ መዛሙርቱ «ውስጥ» ይኖራል።

ሰ. መንፈስ ቅዱስ ያስተምራል። ክርስቶስን በሚያከብር መንገድ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ያስተምረናል። ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያስተማረውን እውነት ያሳስባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በመንፈስ ቅዱስ ከተነገሩት እውነታዎች በቤተ ክርስቲያንህ ትኩረት ያልተሰጠባቸው የትኞቹ ናቸው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ስለ መንፈስ ቅዱስ ትኩረት የተሰጠው ምንድን ነው? ከዚህ እንዴት ይለያል?

ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በሌሎች መንገዶችም አበረታቷል። አንደኛው፥ ምንም እንኳ ለጊዜው በሥጋዊ ዓይኖቻቸው ባያዩትም፥ በመንግሥተ ሰማይ እንደሚያገኙት ገልጾላቸዋል። ክርስቶስ ከእነርሱ የተለየው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አልነበረም።

ሁለተኛው፥ ክርስቶስ ስለ ሰጣቸው ዐቢይ ትእዛዝ እንደገና አስታውሷቸው ነበር። ለእርሱ በመታዘዝ ፍቅራቸውን እንዲያሳዩም አሳስቧቸዋል። እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ የጠየቀበትንና ክርስቶስ የሰጣቸውን ሌሎች ትእዛዛት መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስን እንደምንወደው ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ፥ ቃሉን መታዘዛችን ነው። ክርስቶስን የምንታዘዘው እንዲወደን ሳይሆን፥ ስለምንወደው ነው። እምነትና ፍቅር በሚኖረን ጊዜ፥ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር አብም ይወደናል።

ሦስተኛው፥ ክርስቶስ በሁኔታዎች የማይወሰን ሰላም እንደሚሰጣቸው ተናገረ። ለዓለም ሰላም ማለት ጦርነትን፥ በሽታን ወይም ሁከትን የመሳሰሉ ችግሮች አለመኖራቸው ማለት ነው። ስለሆነም መንፈስ ቅዱስ የሌለው ወይም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የማይመላለስ ሰው እነዚህ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ሰላም ያጣል። ክርስቶስ ግን ሰላምን የኅብረትና የአንድነት መኖር አድርጎ ያየዋል። መንፈስ ቅዱስ በችግሮቻችን ጊዜ ሁል ጊዜም ከእኛ ጋር ስለሚኖርና እግዚአብሔርም ችግሮቻችንን ሁሉ ስለሚከታተል፥ የእግዚአብሔር ተከታዮች በመከራ ውስጥ እንኳ የሰላምና የዋስትና ስሜት ይኖራቸዋል።

አራተኛው፥ ምንም እንኳ «የዓለም ገዥ » የሆነው ሰይጣን ሰዎች ክርስቶስን ወደ መስቀል እንዲወስዱት ለማነሣሣት በመዘጋጀት ላይ ቢሆንም፥ ክርስቶስ በነገሮች ላይ የነበረውን ሥልጣን አጥቷል ማለት አይደለም። የክርስቶስን ሕይወት የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር እንጂ ሰይጣን አይደለም። እግዚአብሔር ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንዲሞት ስለነገረው ከፍቅር የተነሣ ይህንኑ ተግባራዊ ማድረጉ የማይቀር ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ሰይጣን ዛሬም እኛን ይተናኮለናል። ነገር ግን በሕይወታችን ላይ የሚፈጸሙትን ነገሮች ለመቋቋም የሚያስችል ሥልጣን፥ በእኛ ላይ እንደሌለው መገንዘብ አለብን። ኃይል የክርስቶስ ነው። ሰይጣን ሊሠራ የሚችለው እግዚአብሔር እስከ ፈቀደለት ገደብ ድረስ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች ከሕይወታቸው ጋር ማዛመድ ያለባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ (ዮሐ. 14፡1-14)

ደምሴ ሥራ የሌለው ክርስቲያን ነው፤ እርሱና ቤተሰቡ በልተው የሚያድሩት ምግብ ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ የሚያገኘው አልፎ አልፎ ነው። የሚረዳው ዘመድ እንኳ አልነበረም። «ለነገ እንዳልጨነቅ እግዚአብሔር ለምን በቂ ገንዘብ አይሰጠኝም?» ሲል ያስባል። «ሥራ የማገኘው እንዴት ነው? ለኑሮ የሚያስፈልገንን ገንዘብ የማገኘው ከየት ነው?» ብታመም የምታክመው በምኔ ነው? በማለት ስለ ወደፊት ኑሮው እጅግ ይጨነቃል። «ብሞትስ፣ ባለቤቴንና ልጆቼን ማን ይንከባከባቸዋል?» እነዚህ አሳቦች ውስጡን ሰርስረው ለጭንቀት ዳረጉት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ፍርሃትና ጭንቀት አሳባችንን በቀላሉ የሚቆጣጠሩት ለምንድን ነው? ለ) ዮሐ 14፡1-4 እና ዕብ 11፡10፥ 16 አንብብ። እነዚህን ምንባቦች ከሕይወታችን ጋር ብናዛምድ ጭንቀትን እንድናሸንፍ እንዴት ይረዱናል?

ጭንቀት የሚመነጨው ካለማመን ነው። «ምግብና ልብስ ከየት እናገኝ ይሆን?» እያልን የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ነገር ለማሟላት የገባልንን ቃል ዘንግተናል ማለት ነው (ማቴ. 6፡25-34)። ስለወደፊቱ የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ «የነገ» ጌታ እንደ ሆነ ዘንግተናል ማለት ነው። ስለ ጤንነታችን የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ ታላቁ ሐኪም እንደ ሆነ ረስተናል ማለት ነው። እንዲሁም፥ ስለ ቤተሰቦቻችን የምንጨነቅ ከሆን፥ ክርስቶስ እኛ ከምንወዳቸው በላይ እንደሚወዳቸውና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ዘንግተናል ማለት ነው። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ተለይቷቸው እንደሚሄድ ባወቁ ጊዜ በጣም ተጨነቁ። ከሦስት ዓመት በላይ ከክርስቶስ ጋር ኖረዋል። ሥራቸውንም ትተው ነበር። በዚህ ላይ ድሆች ነበሩ። ወደፊት ምን ይገጥማቸዋል? ያለ ክርስቶስ የሕይወትን ማዕበል እንዴት ይቋቋሙታል? ስለሆነም፥ ክርስቶስ በአካል ከእነርሱ ጋር በማይኖርበት ጊዜ የወደፊት ሕይወታቸው እንዴት እንደሚሆን የተለያዩ እውነቶችን በመንገር ያጽናናቸዋል።

ዮሐንስ 14-17 ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እርሱ፥ ስለ መንፈስ ቅዱስና ስለ ደቀ መዝሙርነት ሕይወት እንዲነዘቡ የሚፈልጋቸውን አንዳንድ አጠቃላይና እጅግ ጠቃሚ እውነቶችን አካትቶ ይዟል።

 1. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ዘላለማዊ የመኖሪያ ስፍራ እንደሚያዘጋጅ ቃል ገባ (ዮሐ 14፡1-4)

ምን ጊዜም ቢሆን መለያየት ሥቃይ አለበት። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ተመልሶ መሄዱ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የመለየትን ሥቃይና ጥርጣሬ እንዳያስከትልባቸው በማሰብ የተለያዩ እውነቶችን አስተማራቸው። እነዚህ እውነቶች እያንዳንዱ ክርስቲያን ዛሬ ሊያውቃቸውና ከሕይወቱ ጋር ሊያዛምዳቸው የሚገቡ ናቸው። የክርስቶስ ተከታዮች በብርቱ መከራና ሥቃይ መካከል በተስፋ ሊኖሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለት ዐበይት እውነቶችን አስጨብጧል፡-

ሀ. ደቀ መዛሙርቱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት አጽንተው መያዝ አለባቸው። እምነት እንዴት እንደሚሠራ ባናውቅም፥ እግዚአብሔር በሰጠው ቃል ላይ ተመሥርቶ መኖር ነው። የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች በማወቅና በእነዚህ ቃሎች ላይ የተመሠረተ ሕይወት ለመምራት በመቁረጥ፥ ተስፋችንን አጽንተን እንይዛለን። ተስፋ ቆርጠን የምንጨነቀው ዓይኖቻችንን ከእግዚአብሔር ላይ ስናነሣ፥ የተስፋ ቃሎቹን ስንረሳና ፍጹም የተስፋ ቃሎቹን ከሕይወታችን ጋር ሳናዛምድ ስንቀር ነው።

ለ. የክርስቶስ ተከታዮች ዓይናቸውን በዘላለሙ ተስፋ ላይ ማድረግ አለባቸው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እንደማይተዋቸው፥ በሰማይም እነርሱ የሚኖሩበትን ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ስለሆነም፥ በእግዚአብሔር አብ መንፈሳዊ ቤት፥ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሁሉ የመኖሪያ ስፍራ ያዘጋጅላቸዋል። ሕዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ዘንድ ሲሄዱ በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ እንደማይታጎሩና በዘላለሙ ስፍራ እግዚአብሔር ለልጆቹ ለእያንዳንዳቸው የተለየ ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው ከክርስቶስ ትምህርት መገንዘብ ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዓይናችንን በዘላለሙ ተስፋ ላይ ማድረጋችን በእምነታችን ጸንተን እንድንቆም የሚረዳን እንዴት ነው?

 1. በኢየሱስ ማመን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ ነው (ዮሐ 14፡5-14)

መንገድ ወደምንፈልግበት ስፍራ እንድንደርስ ስለሚረዳን፥ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ነገር ግን ትክክለኛው መንገድ የትኛው እንደ ሆነ ማወቅ አለብን። ደቀ መዛሙርቱ ወደ እግዚአብሔር አብና በሰማይ ወደሚገኘው ወደ ዘላለማዊ ቤታቸው በሚያደርሰው ትክክለኛው መንገድ ላይ እየተጓዙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ፈልገው ነበር። ክርስቶስም ብርቱ በሆኑ ቃላት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷቸዋል፡-

ሀ. ኢየሱስ «እኔ መንገድ፥ እውነትና ሕይወት ነኝ፤’ በእኔ በቀር ማንም ወደ አብ ሊመጣ አይችልም» አላቸው (ዮሐ 14፡6)። ይህ ክርስቶስ የተናገረው ስድስተኛው «እኔ ነኝ» የሚለው ዐረፍተ ነገር ነው። በዚህ ንግግሩ ኢየሱስ ወሳኝ አሳቦችን ሰንዝሯል፤ ወደ ሰማይ እናደርሳለን የሚሉ ሰው ሠራሽ መንገዶች እንዳሉ ቢገልጽም፥ ሁሉም ግን እውነተኛ መንገዶች እንዳልሆኑ አመልክቷል። በራሳቸው መንገድ ወደ ሰማይ ለመድረስ የሚጥሩ ሰዎች፥ ካሰቡት ሊደርሱ አይችሉም። በመሐመድ፥ በቡድሃ ወይም በተከታዮቻቸው የሚያምኑ ሰዎች፥ መንግሥተ ሰማይ ሊገቡ አይችሉም። ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊደርስ የሚችለው በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። ምንም እንኳ ዛሬ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው መንገድ አንድ ብቻ ነው የሚለው አሳብ በዓለም ላይ ተወዳጅነት ባይኖረውም፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ግን ይህንን ሐቅ ነው። ይህ ክርስቲያኖች በራሳቸው ያመጡት አሳብ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ራሱ የተናገረው ነው። ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው ብቸኛው መንገድ እርሱ ራሱ እንደ ሆነ ተናግሯል። ክርስቶስ እውነትን ሁሉ የያዘ አምላክ በመሆኑ፥ እውነት የሆነውን አሳብ ማስተማር ብቻ ሳይሆን፥ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ እውነተኛ መንገድም ነው። እንዲሁም፥ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ሕይወትን የሚቆጣጠረው ክርስቶስ ነው። ስለሆነም፥ የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በክርስቶስ አማካይነት ብቻ ነው።

ለ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ትክክለኛ እንደራሴ ነው። ወደ ክርስቶስ መመልከት፥ ወደ እግዚአብሔር እንደ መመልከት ያህል ነው። ኃይላቸው፥ ባሕርያቸውና ዓላማቸውም አንድ ነው። ክርስቶስ ፈቃዱን ለአብ ስላስገዛ፥ አብ የነገረውን ብቻ ተግባራዊ ያደርጋል፤ ደግሞም ከእርሱ ጋር በፍጹም ስምምነት ስለሚሠራ፥ የአንዱ ሥራ የሌላውም ነው። (ማስታወሻ፡የሥላሴን ሕልውና የካዱና «ኢየሱስን ብቻ» እናመልካለን የሚሉ ተከታዮች እንደሚያስተምሩት በዚህ ክፍል ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ አካል መሆኑን እየገለጸ አይደለም። የተለያዩ አካላት መሆናቸው በዚህም ሆነ በሌሎች ክፍሎች ግልጽ ነው። ዮሐንስ የሚናገረው ግን በመካከላቸው ስላለው ፍጹም ስምምነትና የጋራ አንድነት ነው። እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ ድርጊቶችን ሁሉ በጋራ ተስማምተው ያከናውናሉ።)

ሐ. የክርስቶስ ተከታዮች ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት በማድረግ ደስ ይሰኛሉ። እነርሱም ክርስቶስ ካደረጋቸው ነገሮች የበለጠ እንደሚያደርጉ ገልጾአል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል እኔ ካደረግሁት ተአምር የበለጠ ታደርጋላችሁ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እርሱ ለማለት የፈለገው ግን፥ እኔ ካገለገልሁት ሕዝብ የበለጠ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ታገለግላላችሁ ማለቱ ነው። ክርስቶስ በሥጋዊ አካል ስለ ተወሰነ፥ በአንድ ጊዜ በብዙ ቦታዎች ላይ ለመገኘት አይችልም ነበር። ስለሆነም፥ የሚያገለግለው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ ተከታዮች በሕይወታቸው ውስጥ ካለው መንፈስ ቅዱስ የተነሣ ብዙ ሰዎችን ለመድረስ ይችላሉ። የክርስቶስ ተከታዮች በዓለም ሁሉ ሲሰራጩ፥ በክርስቶስ ኃይል ብዙ ተአምራትን ይሠራሉ። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሳይወሰኑ እስከ ምድር ዳርም ይደርሳሉ። ተአምራቱም አሁን ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው። ከሁሉም የሚልቀው ተአምር የክርስቶስ ተአምር ይሆናል። ይህም የክርስቶስ ተከታዮች የእግዚአብሔር መሣሪያዎች ሆነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ መንፈሳዊ ጎዳና መመለሳቸው ነው።

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያለውን ዓይነት የኃይል ምንጭ ሊኖራቸው ይችላል። በክርስቶስ አማካይነት ከእግዚአብሔር አብ ጋር ኅብረት ልናደርግ እንችላለን። ልጆቹ እንደ መሆናችን መጠን፥ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካለንና ክርስቶስ እንዳደረገው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ የምናስገዛ ከሆነ፥ እግዚአብሔር የምንጠይቀውን ሁሉ ለእኛና በእኛ አማካይነት ተግባራዊ ያደርጋል። ይህ እውነት የሚሆነው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ስናስገዛና የምንጸልይባቸው ነገሮች እግዚአብሔር እንዲከናወኑ የሚፈልጋቸው ሲሆኑ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንዳንድ ሰዎች ልመናችን ምንም ይሁን ምን፥ ትክክልም ይሁን ስሕተት፥ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሁሉ ለመመለስ ቃል ገብቶልናል ይላሉ። ይህ የተስፋ ቃል ምን ማለት ይመስልሃል? ለ) ጸሎቱ ላልተመለሰለት ሰው ምን ምላሽ ትሰጠዋለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካ ምግብ በላ (ዮሐ. 13:1-38)

ከዮሐንስ 13-17 በኋላ የወንጌሉ ትኩረት ይለወጣል። እስካሁን አጽንኦት የተሰጠው ለኢየሱስ ክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት፥ ላደረጋቸው ምልክቶችና ለሕዝብ ላቀረባቸው ትምህርቶች ነበር። ዮሐንስ በዚህ ይፋዊ አገልግሎት ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለሰጠው ቀጥተኛ ትምህርት ብዙም የገለጸው ነገር የለም። አሁን ግን ዮሐንስ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሳለ በመጨረሻው ምሽት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶች ላይ አተኩሯል። የመሞቻው ቀን የተቃረበ መሆኑን የተገነዘበ አባት ለልጆቹ የመጨረሻ ምክሩን እንደሚሰጥ ሁሉ፥ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ወሳኝ የአዲስ ኪዳን ትምህርቶችን አካፍሏቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ክርስቶስ አዲስ ኪዳንና የጌታ እራት ሥርዓትን መመሥረቱን አጉልተው ሲያሳዩ፥ ዮሐንስ ደግሞ ክርስቶስ ከሞቱ፥ ከትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላ ተከታዮቹ ሊኖሩት ስለሚገባ ሕይወት ገልጾአል።

ሀ. ክርስቶስ የትሕትና አገልግሎት የመንግሥቱ ምሳሌ እንደሆነ ገልጿል (ዮሐ 13፡1–17)። በአይሁድ ባሕል የአንድን ሰው እግር ማጠብ እጅግ ዝቅተኛ ሥራ ነው። ይህ አንድ የቤት አገልጋይ የሚያከናውነው ተግባር ነው። ቤተሰቡ አገልጋይ ከሌለው ሚስት ወይም ልጆች እንጂ አባወራው የእንግዳውን እግር አያጥብም። የሚደንቀው ነገር ታዲያ የዓለም ፈጣሪ የደቀ መዛሙርቱን እግሮች አጠበ። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ትሕትና ነው። ክርስቶስ ይህንን ያህል ራሱን ዝቅ ካደረገ፥ እኛም አርአያውን ተከትለን ራሳችንን በሌሎች ፊት ዝቅ ማድረግና ሌሎችን ማገልገል ይኖርብናል።

ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበው ለምንድን ነው? አንደኛው፥ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽበት መንገድ በመሆኑ ነው። በተጨማሪም በሞት ከመለየቱ በፊት እነርሱን የሚያገለግልበት የመጨረሻ ዕድል በመሆኑም ነው። ዮሐንስ ይህንን ተግባር «የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው» በማለት ገልጾአል። ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነበረውን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቶ ነበር። አሁን ግን ከቶ በማይረሱት መንገድ ነበር ፍቅሩን ያሳያቸው። ክርስቶስ እንደ ባሪያ እግራቸውን አጠበ። ፍቅር ሁልጊዜ ያገለግላል፥ ይሰጣልም። ፍቅር ከስሜት በላይ ነው። ፍቅር ሌሎችን ማገልገልና ሲያድጉ ማየት ነው። ፍቅር ሌሎችን ማገልገልን እንደ ዝቅተኛነት አይመለከትም።

ሁለተኛው፥ ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ማየት የሚፈልገውን ባሕርይ በምሳሌነት ለመግለጽ ነው። ዮሐንስ ክርስቶስ ሊደርስበት ያለውን ነገር ሁሉ ያውቅ እንደ ነበር ገልጾአል። የመጣበትን ስፍራ ያውቅ ነበር – ከሰማይ። የመጣበትንም ምክንያት ያውቅ ነበር። ለመሞት ተመልሶ የሚሄድበትንም ስፍራ ያውቅ ነበር – ወደ ሰማይ። እንዲሁም እግዚአብሔር አብ የሰጠውን ኃይልና ሥልጣን ሁሉ ያውቅ ነበር። ይህ ግን እንዲኩራራ ወይም ሌሎች እንዲያገለግሉት አላደረገውም። ክርስቶስ ተከታዮቹ ይህንኑ ባሕርይ እንዲይዙ ይፈልጋል። ሥልጣንና ኃይልን ከመፈለግና ሌሎች እንዲያገለግሉን ከመሻት ይልቅ ራሳችንን ዝቅ አድርገን አንዳችን ሌላውን ልናገለግል ይገባል።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ምሳሌውን እንድንከተል ያሳየንን ነገር በመውሰድ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግር መታጠብ አለብን ይላሉ። የክርስቶስ ምኞት ግን ከዚህ የላቀ ነው። እግርን ማጠብ ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ማገልገል አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ ጌታቸውና መምህራቸው እንደ ሆነ ያምኑ ነበር። ጌታቸው ራሱን ዝቅ አድርጎ ካገለገላቸው፥ እነርሱም እንዲሁ ከማድረግ መቆጠብ የለባቸውም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እርስ በርሳቸው አገልግሎት ሊሰጣጡ የሚችሉባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ። ለ) እነዚህ የጠቀስሃቸው ነገሮች ተግባራዊ እየሆኑ ናቸው? ከሆኑ ለምን? ካልሆኑስ ክርስቲያኖች ሁሉ ሌሎችን ዝቅ ብለው ቢያገለግሉ በቤተ ክርስቲያናችን ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣል?

ለ. ክርስቶስ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተነበየ (ዮሐ 13፡18-38)። ዮሐንስ ክርስቶስ በሕይወቱ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውም ነገር ለመቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በተደጋጋሚ ገልጾአል። ጊዜው ከመድረሱ በፊት ክርስቶስን ማንም ለማሰር አይችልም። ነገር ግን የተወሰነው የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስ ክርስቶስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ። ክርስቶስ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ለማሳየት ዮሐንስ ክርስቶስ ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው ብቻ ሳይሆን፥ ይህም ሰው ይሁዳ እንደ ሆነ መተንበዩን ጠቅሷል። በዮሐ 13፡23 ላይ ኢየሱስ «ይወደው ከነበረው ደቀ መዝሙር» ጋር እንተዋወቃለን። ከዚህ ምዕራፍ ጀምሮ እስከ መጽሐፉ መጨረሻ ድረስ ዮሐንስ ራሱን ለመጥቀስ ይህንን የተለየ ስም ይጠቀማል።

ይሁዳ ከክፍሉ ከወጣ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይበልጥ ነፃ ሆኖ ማስተማርና ወደፊት ሊኖሩት ስለሚገባቸው ሕይወት ያዘጋጃቸው ጀመር። ከእነርሱ ጋር የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር። ከ40 ቀናት በኋላ በአካል ከእነርሱ ጋር መኖሩ ያበቃል። እርሱ ወደ ሰማይ ስለሚሄድ እርሱ ወደሚሄድበት ሊከተሉት አይችሉም። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት እውነቶችን ገልጾላቸዋል፦

ሀ. ወንጀለኞች የሚሰቀሉበት ታላቁ የኀፍረት ስፍራ ወደ ክብር ስፍራ ይቀየራል። ክርስቶስ በታዛዥነት በመስቀል ላይ በመሞት እግዚአብሔርን ያከብር ነበር። እግዚአብሔርም የኀፍረቱን መስቀል ለውጦ ኢየሱስን ያከብረዋል፤ ለተከታዮቹም ሁሉ የመመኪያ ስፍራ ያደርግላቸው (1ኛ ቆሮ. 1፡18፤ ገላ. 6፡14)። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱና ከሞትም በመነሣቱ፥ ስሙ በታሪክ ሁሉ ከስሞች ሁሉ በላይ የላቀ ስም ለመሆን በቅቷል።

ይህ ለሰው ልጆች ፍጹም እንግዳ ነው፤ እግዚአብሔር ለሰዎች ኀፍረት የሆነውን ነገር ለውጦ ለራሱ ክብር እንደሚጠቀምበት በኢየሱስ ሕይወት በግልጽ ታይቷል። እግዚአብሔር የተጣለውን ድንጋይ (ኢየሱስን) የማዕዘን ራስ አድርጎታል (ማቴ. 21፡42-44)። ሽባዋን ሴት ተጠቅሞ ስለ ጸጋው እንድትመሰክር አድርጓል። የጳውሎስን የሥጋ መውጊያ ወስዶ የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ድካም እንደሚፈጸም አሳይቷል (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። በሕይወታችን የሚገጥመንን በሽታ፥ ሥቃይና ችግር በመጠቀም ክብሩን ይገልጻል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ኀፍረት የሚመስለውን ነገር በመጠቀም በሕይወትህ ክብሩን ሲገልጽ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ በሕይወታችን የሚከሰተውን ችግር ስለምንመለከትበት መንገድና በዚህም ጊዜ ስለምናደርገው ጸሎት ምን ዓይነት የአመለካከት ለውጥ እንዲኖረን ያደርጋል?

ለ. አዲሱና እጅግ ታላቁ የክርስቶስ ትእዛዝ “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚል ነው። በአንድ በኩል ይህ አዲስ ትእዛዝ አይደለም። ይህ አሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተሰወረ ሲሆን (ዘሌዋ. 19፡18 አንብብ)፥ ክርስቶስም ሁለቱ ታላላቅ ጠቃሚ ትእዛዛት እግዚአብሔርንና ባልንጀሮቻችንን መውደድ እንደሆነ ገልጾአል (ማቴ. 22፡37-40)። እንግዲህ ይህ ትእዛዝ «አዲስ» የሚሆነው እንዴት ነው? አዲስ ትእዛዝ የሚሆነው፡-

 1. አዲስ አጽንኦት አለው። ምንም እንኳ ብሉይ ኪዳን እርስ በርስ ስለመዋደድ በግልጽ ባይናገርም፥ በሌሎች ብዙ ትእዛዛት ላይ ግን ነገሩ ተወስቷል። አሁን ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ብዙ ሕግጋትና ደንቦች ሳይሆን በፍቅር ሕግ እንዲመሩ ገልጾአል።
 2. ሰዎች እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ውስጥ እግዚአብሔር ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚፈልጋቸው ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ፍቅር የትእዛዛት ሁሉ ፍጻሜ ሆኖ ተገልጾአል። ከውጫዊ ተግባራት ጋር የሚያያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕግጋትን ከሚደነግጉ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተቃራኒ፥ ኢየሱስ ከተከታዮቹ የሚፈልገው አዲስ ውስጣዊ አመለካከትን ነው፤ ይህም አንዱ ለሌላው የሚያሳየው ፍቅር ነው። እግዚአብሔርንና ሰዎችን ከወደድን ክርስቶስ የሚፈልጋቸውን ትእዛዛት መጠበቅ ተፈጥሯዊ ጉዳይ ይሆናል።
 3. የአንድ ክርስቲያን ምልክቱ ወይም መታወቂያው ነው። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ለመሆን ምልክቱ መገረዝና ውጫዊ ሕግጋትን መጠበቅ ነበር። አሁን ግን የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችን ምልክቱ እርስ በርስ ያለን ፍቅር እንደ ሆነ ተመልክቷል።
 4. በዓይነቱና በጥልቀቱ። ፍቅርን የሚገልጹ ሦስት የግሪክ ቃላት አሉ። ኤሮስ (Eros) ባል ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ያመለክታል። ፊሊዮ (Phileo) በጓደኛሞች መካከል የሚታየውን ፍቅር ያሳያል። አጋፔ (Agape) መለኮታዊ ማለትም ራሱን የሚገልጥ ፍቅር ነው። ክርስቶስ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት እርሱ እግራቸውን እንዳጠበና ስለ እነርሱም ሲል በመስቀል ላይ እንደ ሞተ ሁሉ የእርሱ የሆኑ ሁሉ ይህንኑ እንዲያደርጉ ነው። ለሌሎች መኖር እዲስ ትእዛዝ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የማያምኑ ሰዎች እንደ አንድ አማኝ ከእኛ የሚጠብቁብንን ነገሮች ዘርዝር። ፍቅር ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ነው? ለምን? ለ) ፍቅር የክርስቲያን መለያ መሆን አለበት፥ ዛሬ በክርስቲያኖች መካከል ፍቅር ጠፍቶ መከፋፈል የሰፈነው ለምን ይመስልሃል?

ሐ. ጴጥሮስ ለክርስቶስ ሲል ለመሞት እንዳሰበ ቢናገርም፥ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ኢየሱስ ተንብዮአል። ለክርስቶስ ለመኖር ወይም ለመሞት ቃል መግባት ቀላል ቢሆንም፥ ተግባራዊ ማድረጉ ግን ከባድ ነው። እጅግ ደፋር ደቀ መዝሙር የነበረው ጴጥሮስ ክርስቶስን ክዶታል። እኛም ከእርሱ ላንሻል እንችላለን። ነገር ግን ክርስቶስን በመታዘዝ እንድናድግ የሚያበረታቱን ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ጴጥሮስን ይቅር ብሎ እንደገና እንደ ተጠቀመበት ሁሉ እኛንም ይቅር እንደሚለን እናውቃለን። ሁለተኛው፥ ጸንተን እንድንቆም የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አለ። ስለ አንተ እሞታለሁ ብሎ ቃል የገባው ጴጥሮስ ሳይሳካለት ቀርቷል። በቃላችን እንድንጻጸና የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስ ስለ ሞቱ ትንቢት በተናገረ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች የሰጡት ምላሽ (ዮሐ.12፡20-50)

ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ የመጨረሻ ቀናት ሲናገር ስለ ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎት የጀመረውን ገለጻ የደመደመው በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የተለያዩ ሰዎች ለኢየሱስ የሰጡትን ምላሽ ምሳሌ አድርጎ በማቅረብ ነው። የእነዚህን ሰዎች ምላሽ የያዘው ልክ በሰርግ ላይ እንደ ተነሣ ፎቶ በዚያን ጊዜ የነበረውንና አሁንም ሰዎች ለኢየሱስ የሚሰጡትን ምላሽ ለማጤን ይረዳሉ።

ሀ. ግሪኮች፡- ዮሐንስ የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ግሪኮች እንደ ነበሩ ገልጾአል። ምናልባትም እነዚህ ግሪኮች እንደ ቆርኔሌዎስ የራሳቸውን ሃይማኖት ትተው የአይሁዶችን ሃይማኖት የተከተሉ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ የተነገረውን ዜና ሰምተው ሊያነጋግሩት ፈለጉ። ነገር ግን ምናልባትም ከሕዝቡ ብዛትና አሕዛብ ከመሆናቸው የተነሣ ከክርስቶስ ጋር ለመነጋገር ዕድል የማያገኙ ስለመሰላቸው ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ቀረቡ። ፊልጶስ የገሊላ ሰው በመሆኑ ምናልባት ከአሕዛብ ጋር ቅርበት ሳይኖረው አይቀርም።

ስሙ ወላጆቹ የአሕዛብን ባሕል እንደ ተቀበሉ ያሳያል። ስለዚህ ግሪኮች ፊልጶስ ከክርስቶስ ጋር ቀጠሮ ለመያዝ ሊረዳን ይችላል ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ፊልጶስ ወደ ጓደኛው ወደ እንድርያስ በመሄድ ተያይዘው ወደ ክርስቶስ መጡ። ኢየሱስ ከግሪኮቹ ሰዎች ጋር ስለ መነጋገሩ በዚህ ክፍል የተጠቀሰ ነገር የለም። ምናልባትም ዮሐንስ ይህንን ታሪክ የጠቀሰው ከክርስቶስ ሞት በፊት ወንጌል ወደ አሕዛብ መድረሱን ለማመልከት ይሆናል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ፥ የምሥራቹ ቃል ብዙ አሕዛብን ወደ ክርስቶስ ያመጣ ነበር።

ለ. ኢየሱስ፡- ኢየሱስ ሞቱ ያልጠበቀው ነበር? አልነበረም። ሞቱ እየቀረበ መምጣቱን ያውቅ ነበር። ይህ ማለት ግን ክርስቶስ ከሚጠብቀው ስቅለትና ከሚደርስበትም ነገር ጋር ግብግብ አልገጠመም ማለት አይደለም። እስካሁን ድረስ ዮሐንስ የክርስቶስ ጊዜ እንዳልቀረበ ሲገልጽ ነበር የቆየው። አሁን ግን ለስቅለቱ ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩ «ጊዜው እንደ ደረሰ» ገልጾአል። የስንዴ ቅንጣት ለመብዛትና ፍሬ ለመስጠት መሞት እንዳለባት ሁሉ፥ ክርስቶስም መሞት ነበረበት። ይህ መርሕ ታዲያ ክርስቶስን በሚከተሉት ሁሉ ላይ የሚሠራ ነው። ለግል ፍላጎታችን ካልሞትን፥ ለሕልማችን ካልሞትን፥ ለተደላደለ ኑሮ ካልሞትን፥ ለኃጢአት ካልሞትን ሕይወታችን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እርባና አይኖረውም። የሮም መንግሥት ባስከተለባቸው ስደት በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሲሞቱ የተመለከቱ አንድ የጥንት ጸሐፊ እንደ ገለጹት፥ “የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው።” ሞትን የመረጡት የዘላለም ሕይወትን አግኝተዋል። ነገር ግን ከሞት ለመሸሽ የሞከሩ ሰዎች ትልቁን ሕይወት ማለትም የዘላለም ሕይወትን አጥተዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስን በመከተልህ «የሞትህባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) «ሞትህ ያስከተለው ፍሬ ምንድን ነው? ሐ) ሰዎች ለመሞትና ክርስቶስን በሙሉ ልባቸው ለመከተል አለመፈለጋቸውን እንዴት እንደተመለከትኸው ግለጽ። የሕይወታቸው ዘላለማዊ ፍሬ ምንድን ነው?

ሐ. እግዚአብሔር አብ፡– ሰው እንደ መሆኑ ኢየሱስ ከመስቀል ሞቱ ለማፈግፈግ ፈልጎአል። ለመሆኑ እስከ መጨረሻ እንዲጸና ያደረገው ምንድን ነው? ሦስት ነገሮች አሉ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ዓላማውን በግልጽ ያውቃል። ወደ ዓለም የመጣውም ለመሞት እንደ ሆነ ያውቃል። ስለዚህ ለሌሎች ፍላጎቶች ላይገዛ ለእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ለመታዘዝ ቻለ። ሁለተኛው፥ ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔርን ለማክበር ቆርጦ ነበር። ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠት እንጂ ለሕይወቱ ትልቅ ግምት አልሰጠም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በሞቱ እንዲከብር ጠየቀ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሕይወትና በፈጸማቸው ተአምራት ደስ መሰኘቱን በሕዝቡ ሁሉ ፊት በይፋ ገለጸ። እግዚአብሔር በሞቱም ይከብር ነበር። ሦስተኛው፥ ክርስቶስ የሞቱን ውጤቶች ለመመልከት ችሎ ነበር። በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ለማስገኘት በመቻሉ ስሙ ከስሞች ሁሉ እንደሚልቅና አንድ ቀን ሰዎች ሁሉ እንደሚያከብሩት ተገነዘበ (ፊልጵ. 2፡9-11፤ ዕብ. 12፡2)።

በሕይወት ዘመናችን የምንፈጽመው ትልቁ ዓላማ ምንድን ነው? ትልቁ ዓላማችን በሕይወታችን፥ በድርጊታችንና በአሳባችን እግዚአብሔርን ማስከበር ሊሆን ይገባል። ዓላማችን ይህ ከሆነ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንደ ብርቱ ሕመም ድህነት፥ ስደት፥ ሞት የመሳሰሉ ነገሮችን ወደ ሕይወታችን ሊያመጣ ይችላል። መብቱም የእርሱ ነው። እግዚአብሔርን ለማክበር እስከፈለግን ድረስ፥ በሕይወታችን የሚከብርበትን መንገድ መምረጡ የእግዚአብሔር ድርሻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር በሕይወትህ እንዲከብር የምትፈልግባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በሕይወትህ የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራስህን መንገድ የምትከተልባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህን ነገሮች ተናዝዘህ እግዚአብሔር በሁሉም ነገር የእርሱን ክብር እንድትፈልግ እንዲረዳህ ለምነው። ሐ) ከራስህ በላይ የእግዚአብሔርን ክብር በመፈለግህ ሕይወትህን ዓላማህን፥ ሥራህን ቤተሰብህን፥ ወዘተ… እንዴት እንደ ለወጠ አብራራ።

ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ሰይጣን ድል ያደረገበት ወቅት ይመስል ነበር። ኢየሱስ ይህንን ጊዜ የጨለማ ጊዜ በማለት ጠርቶታል። ዳሩ ግን መስቀሉ ሦስት ነገሮችን አከናውኗል፡-

አንደኛው፥ በዓለም ላይ ፍርድን አምጥቷል። መስቀሉ የታሪክ መለያ መሥመር ነው። ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ያስገኘውን ድነት (ደኅንነት) የማይቀበሉ ሰዎች የዘላለምን ሞት ፍርድ ይቀበላሉ።

ሁለተኛው፣ የዚህን ዓለም አለቃ አሸንፎአል። ሰይጣን ክርስቶስ ተሰቅሎ እንዲሞት በማድረግ ያሸነፈ መስሎት ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ በሞቱ ሰይጣንን አሸነፈው። (ቆላ. 2፡15 አንብብ።) ሰይጣን በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጫና በመስቀሉ ላይ እንደ ተወገደ አዲስ ኪዳን ያስተምራል። ሰይጣን ሽንፈትን ከመከናነቡም በላይ ፍጻሜውም በደጅ ነው። ነገር ግን ሰይጣን ከእርሱ ጋር ወደ ሲኦል የሚወርዱ ሰዎችን ለማግኘት ትግሉን ቀጥሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ሰይጣን ለመጨረሻ ጊዜ ድል ይመታል፤ ወደ ሲኦልም ይጣላል (ራእይ 20፡10)።

ሦስተኛው፥ መስቀሉ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ይስባል። ይህም በሁለት መንገድ ይፈጸማል። በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ይቀበላሉ። ኢየሱስ የኃጢአት ዕዳችንን በከፈለበት ዓይናቸው በመስቀሉ ላይ ነውና። በኢየሱስ የማያምኑ ሰዎች ግን በፍርድ ቀን በፊቱ ሲቀርቡ የግዳቸውን እንዲያከብሩት ይደረጋሉ (ፊልጵ. 2፡9-10)።

መ. ሕዝቡ፡- ዮሐንስ የገለጸው ሦስተኛው ምላሽ ሕዝቡ ክርስቶስ ስለ ሞቱ የተናገራቸውን ነገሮች እንደ ተገነዘቡ ያሳያል። መሢሑ ለዘላለም ይገዛል ብለው ስላሰቡ፥ አይሁዶች ክርስቶስ ይህንን እንዲያብራራላቸው ጠየቁት። ክርስቶስ ጥያቄውን በቀጥታ ባይመልስም፥ እርሱ «ብርሃን» እንደ ሆነ በግልጽ ነገራቸው። በምድር ላይ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። ከዓለም በሚሄድበት ጊዜ ልዩ ብርሃኑ አብሮት ይሄዳል። ስለሆነም፥ ክርስቶስ በመካከላቸው ሳለ በእርሱ ማመን አለባቸው። ከዚያም አይሁዶች በክርስቶስ መንፈሳዊ ብርሃን ደስ ሊሰኙ ይችላሉ። ይህም «የብርሃን ልጆች» ማለትም «የእግዚአብሔር ልጆች» እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል (ዮሐ 1፡12)። ዮሐንስ ከክርስቶስ ተአምራዊ ምልክቶች ባሻገር በአይሁዶች መካክል የተከሰተውን አለማመን ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። አይሁዶች መሢሑን እንደማይቀበሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያውቅ ነበር።

ሠ. ጥቂት የሃይማኖት መሪዎች፡- ወንጌላት በሃይማኖት መሪዎቹ አለማመን፥ ለኢየሱስ ባላቸው ጥላቻና እርሱንም ለመግደል በሸረቡት ሴራ ላይ ትኩረት አድርገዋል። ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስና የአርማትያው ዮሴፍን የመሳሰሉ አንዳንድ መሪዎች በክርስቶስ ማመናቸውን ዮሐንስ ገልጾአል። ይህም ሆኖ ዮሐንስ እነዚህን ሰዎች የጠቀሰው ክርስቲያኖች እንደ እነርሱ መሆን እንደሌለባቸው ለመግለጽ ነው። ከምኩራብ እንዳይባረሩ ስለ ሠጉ በኢየሱስ ማመናቸውን ይፋ ለማድረግ ፈሩ፤ ምክንያቱም ከምኩራብ ከተባረሩ እንደ አይሁዶች ስለማይታዩ ነበር። ይህ ከሆነ ደግሞ የሰዎችን አክብሮት ከማጣታቸውም በላይ ሕይወታቸው በችግር የተሞላ ይሆናል። ዮሐንስ ግን ይህ እርምጃቸው ከእግዚአብሔር ይልቅ የሰውን ምስጋና መምረጣቸውን እንደሚያሳይ ገልጾአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ለመደበቅ የምንፈተነው እንዴት ነው? ለ) ይህንን የምናደርገው ለምንድን ነው? ሐ) የዮሐንስ አሳቦች በክርስቶስ ያለንን እምነት በግልጽ ለማሳየት ከመፍራታችን ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?

በዮሐንስ 12፡44-49 ላይ ኢየሱስ ለሕዝቡ የመጨረሻውን ቃሉን ተናግሯል። ማስጠንቀቂያዎቹ ግልጽና ጠንካራ ነበሩ። አንደኛው፥ እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ በፍጹም አንድነት ስለሚሠሩና በባሕርይም አንድ ስለሆኑ፥ ለደኅንነት ሁለቱንም መቀበል የግድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጾአል። አይሁዶች በእግዚአብሔር አብ እናምናለን እያሉ፥ እግዚአብሔር ወልድን አንቀበልም ማለት አይችሉም። ስለሆነም ክርስቶስ አምላክ በመሆኑ ከእግዚአብሔርም ተልኮ በመምጣቱና የተናገራቸውም ነገሮች በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል በመሆናቸው እርሱን መስማት ነበረባቸው። የዘላለም ሕይወት ሊገኝ የሚችለው አብ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ብቻ ነው። ሁለተኛው፥ ክርስቶስ እርሱን ባላመኑ ሰዎች ላይ ፍርድ እንደሚመጣ አስጠንቅቋል። ምንም እንኳ ፈራጁ እርሱ ራሱ ቢሆንም፥ ኢየሱስ ቆሞ መመስከር አያስፈልገውም። (ዮሐ 5፡27 አንብብ)። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት የድነትን (የደኅንነትን) መንገድ ከማሳየታቸውም በላይ ምስክርነቱ የማያምኑ ሰዎችን ይኮንናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች የማያምኑ ጓደኞቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው በክርስቶስ ካላመኑ ምንም ያህል ጥሩ ሰዎች ቢሆኑም፥ የዘላለም ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በገርነትና በግልጽ ማስጠንቀቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)