ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ (ዮሐ. 14፡1-14)

ደምሴ ሥራ የሌለው ክርስቲያን ነው፤ እርሱና ቤተሰቡ በልተው የሚያድሩት ምግብ ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ የሚያገኘው አልፎ አልፎ ነው። የሚረዳው ዘመድ እንኳ አልነበረም። «ለነገ እንዳልጨነቅ እግዚአብሔር ለምን በቂ ገንዘብ አይሰጠኝም?» ሲል ያስባል። «ሥራ የማገኘው እንዴት ነው? ለኑሮ የሚያስፈልገንን ገንዘብ የማገኘው ከየት ነው?» ብታመም የምታክመው በምኔ ነው? በማለት ስለ ወደፊት ኑሮው እጅግ ይጨነቃል። «ብሞትስ፣ ባለቤቴንና ልጆቼን ማን ይንከባከባቸዋል?» እነዚህ አሳቦች ውስጡን ሰርስረው ለጭንቀት ዳረጉት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ፍርሃትና ጭንቀት አሳባችንን በቀላሉ የሚቆጣጠሩት ለምንድን ነው? ለ) ዮሐ 14፡1-4 እና ዕብ 11፡10፥ 16 አንብብ። እነዚህን ምንባቦች ከሕይወታችን ጋር ብናዛምድ ጭንቀትን እንድናሸንፍ እንዴት ይረዱናል?

ጭንቀት የሚመነጨው ካለማመን ነው። «ምግብና ልብስ ከየት እናገኝ ይሆን?» እያልን የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ነገር ለማሟላት የገባልንን ቃል ዘንግተናል ማለት ነው (ማቴ. 6፡25-34)። ስለወደፊቱ የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ «የነገ» ጌታ እንደ ሆነ ዘንግተናል ማለት ነው። ስለ ጤንነታችን የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ ታላቁ ሐኪም እንደ ሆነ ረስተናል ማለት ነው። እንዲሁም፥ ስለ ቤተሰቦቻችን የምንጨነቅ ከሆን፥ ክርስቶስ እኛ ከምንወዳቸው በላይ እንደሚወዳቸውና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ዘንግተናል ማለት ነው። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ተለይቷቸው እንደሚሄድ ባወቁ ጊዜ በጣም ተጨነቁ። ከሦስት ዓመት በላይ ከክርስቶስ ጋር ኖረዋል። ሥራቸውንም ትተው ነበር። በዚህ ላይ ድሆች ነበሩ። ወደፊት ምን ይገጥማቸዋል? ያለ ክርስቶስ የሕይወትን ማዕበል እንዴት ይቋቋሙታል? ስለሆነም፥ ክርስቶስ በአካል ከእነርሱ ጋር በማይኖርበት ጊዜ የወደፊት ሕይወታቸው እንዴት እንደሚሆን የተለያዩ እውነቶችን በመንገር ያጽናናቸዋል።

ዮሐንስ 14-17 ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እርሱ፥ ስለ መንፈስ ቅዱስና ስለ ደቀ መዝሙርነት ሕይወት እንዲነዘቡ የሚፈልጋቸውን አንዳንድ አጠቃላይና እጅግ ጠቃሚ እውነቶችን አካትቶ ይዟል።

  1. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ዘላለማዊ የመኖሪያ ስፍራ እንደሚያዘጋጅ ቃል ገባ (ዮሐ 14፡1-4)

ምን ጊዜም ቢሆን መለያየት ሥቃይ አለበት። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ተመልሶ መሄዱ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የመለየትን ሥቃይና ጥርጣሬ እንዳያስከትልባቸው በማሰብ የተለያዩ እውነቶችን አስተማራቸው። እነዚህ እውነቶች እያንዳንዱ ክርስቲያን ዛሬ ሊያውቃቸውና ከሕይወቱ ጋር ሊያዛምዳቸው የሚገቡ ናቸው። የክርስቶስ ተከታዮች በብርቱ መከራና ሥቃይ መካከል በተስፋ ሊኖሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለት ዐበይት እውነቶችን አስጨብጧል፡-

ሀ. ደቀ መዛሙርቱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት አጽንተው መያዝ አለባቸው። እምነት እንዴት እንደሚሠራ ባናውቅም፥ እግዚአብሔር በሰጠው ቃል ላይ ተመሥርቶ መኖር ነው። የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች በማወቅና በእነዚህ ቃሎች ላይ የተመሠረተ ሕይወት ለመምራት በመቁረጥ፥ ተስፋችንን አጽንተን እንይዛለን። ተስፋ ቆርጠን የምንጨነቀው ዓይኖቻችንን ከእግዚአብሔር ላይ ስናነሣ፥ የተስፋ ቃሎቹን ስንረሳና ፍጹም የተስፋ ቃሎቹን ከሕይወታችን ጋር ሳናዛምድ ስንቀር ነው።

ለ. የክርስቶስ ተከታዮች ዓይናቸውን በዘላለሙ ተስፋ ላይ ማድረግ አለባቸው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እንደማይተዋቸው፥ በሰማይም እነርሱ የሚኖሩበትን ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ስለሆነም፥ በእግዚአብሔር አብ መንፈሳዊ ቤት፥ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሁሉ የመኖሪያ ስፍራ ያዘጋጅላቸዋል። ሕዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ዘንድ ሲሄዱ በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ እንደማይታጎሩና በዘላለሙ ስፍራ እግዚአብሔር ለልጆቹ ለእያንዳንዳቸው የተለየ ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው ከክርስቶስ ትምህርት መገንዘብ ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዓይናችንን በዘላለሙ ተስፋ ላይ ማድረጋችን በእምነታችን ጸንተን እንድንቆም የሚረዳን እንዴት ነው?

  1. በኢየሱስ ማመን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ ነው (ዮሐ 14፡5-14)

መንገድ ወደምንፈልግበት ስፍራ እንድንደርስ ስለሚረዳን፥ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ነገር ግን ትክክለኛው መንገድ የትኛው እንደ ሆነ ማወቅ አለብን። ደቀ መዛሙርቱ ወደ እግዚአብሔር አብና በሰማይ ወደሚገኘው ወደ ዘላለማዊ ቤታቸው በሚያደርሰው ትክክለኛው መንገድ ላይ እየተጓዙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ፈልገው ነበር። ክርስቶስም ብርቱ በሆኑ ቃላት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷቸዋል፡-

ሀ. ኢየሱስ «እኔ መንገድ፥ እውነትና ሕይወት ነኝ፤’ በእኔ በቀር ማንም ወደ አብ ሊመጣ አይችልም» አላቸው (ዮሐ 14፡6)። ይህ ክርስቶስ የተናገረው ስድስተኛው «እኔ ነኝ» የሚለው ዐረፍተ ነገር ነው። በዚህ ንግግሩ ኢየሱስ ወሳኝ አሳቦችን ሰንዝሯል፤ ወደ ሰማይ እናደርሳለን የሚሉ ሰው ሠራሽ መንገዶች እንዳሉ ቢገልጽም፥ ሁሉም ግን እውነተኛ መንገዶች እንዳልሆኑ አመልክቷል። በራሳቸው መንገድ ወደ ሰማይ ለመድረስ የሚጥሩ ሰዎች፥ ካሰቡት ሊደርሱ አይችሉም። በመሐመድ፥ በቡድሃ ወይም በተከታዮቻቸው የሚያምኑ ሰዎች፥ መንግሥተ ሰማይ ሊገቡ አይችሉም። ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊደርስ የሚችለው በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። ምንም እንኳ ዛሬ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው መንገድ አንድ ብቻ ነው የሚለው አሳብ በዓለም ላይ ተወዳጅነት ባይኖረውም፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ግን ይህንን ሐቅ ነው። ይህ ክርስቲያኖች በራሳቸው ያመጡት አሳብ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ራሱ የተናገረው ነው። ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው ብቸኛው መንገድ እርሱ ራሱ እንደ ሆነ ተናግሯል። ክርስቶስ እውነትን ሁሉ የያዘ አምላክ በመሆኑ፥ እውነት የሆነውን አሳብ ማስተማር ብቻ ሳይሆን፥ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ እውነተኛ መንገድም ነው። እንዲሁም፥ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ሕይወትን የሚቆጣጠረው ክርስቶስ ነው። ስለሆነም፥ የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በክርስቶስ አማካይነት ብቻ ነው።

ለ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ትክክለኛ እንደራሴ ነው። ወደ ክርስቶስ መመልከት፥ ወደ እግዚአብሔር እንደ መመልከት ያህል ነው። ኃይላቸው፥ ባሕርያቸውና ዓላማቸውም አንድ ነው። ክርስቶስ ፈቃዱን ለአብ ስላስገዛ፥ አብ የነገረውን ብቻ ተግባራዊ ያደርጋል፤ ደግሞም ከእርሱ ጋር በፍጹም ስምምነት ስለሚሠራ፥ የአንዱ ሥራ የሌላውም ነው። (ማስታወሻ፡የሥላሴን ሕልውና የካዱና «ኢየሱስን ብቻ» እናመልካለን የሚሉ ተከታዮች እንደሚያስተምሩት በዚህ ክፍል ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ አካል መሆኑን እየገለጸ አይደለም። የተለያዩ አካላት መሆናቸው በዚህም ሆነ በሌሎች ክፍሎች ግልጽ ነው። ዮሐንስ የሚናገረው ግን በመካከላቸው ስላለው ፍጹም ስምምነትና የጋራ አንድነት ነው። እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ ድርጊቶችን ሁሉ በጋራ ተስማምተው ያከናውናሉ።)

ሐ. የክርስቶስ ተከታዮች ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት በማድረግ ደስ ይሰኛሉ። እነርሱም ክርስቶስ ካደረጋቸው ነገሮች የበለጠ እንደሚያደርጉ ገልጾአል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል እኔ ካደረግሁት ተአምር የበለጠ ታደርጋላችሁ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እርሱ ለማለት የፈለገው ግን፥ እኔ ካገለገልሁት ሕዝብ የበለጠ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ታገለግላላችሁ ማለቱ ነው። ክርስቶስ በሥጋዊ አካል ስለ ተወሰነ፥ በአንድ ጊዜ በብዙ ቦታዎች ላይ ለመገኘት አይችልም ነበር። ስለሆነም፥ የሚያገለግለው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ ተከታዮች በሕይወታቸው ውስጥ ካለው መንፈስ ቅዱስ የተነሣ ብዙ ሰዎችን ለመድረስ ይችላሉ። የክርስቶስ ተከታዮች በዓለም ሁሉ ሲሰራጩ፥ በክርስቶስ ኃይል ብዙ ተአምራትን ይሠራሉ። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሳይወሰኑ እስከ ምድር ዳርም ይደርሳሉ። ተአምራቱም አሁን ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው። ከሁሉም የሚልቀው ተአምር የክርስቶስ ተአምር ይሆናል። ይህም የክርስቶስ ተከታዮች የእግዚአብሔር መሣሪያዎች ሆነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ መንፈሳዊ ጎዳና መመለሳቸው ነው።

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያለውን ዓይነት የኃይል ምንጭ ሊኖራቸው ይችላል። በክርስቶስ አማካይነት ከእግዚአብሔር አብ ጋር ኅብረት ልናደርግ እንችላለን። ልጆቹ እንደ መሆናችን መጠን፥ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካለንና ክርስቶስ እንዳደረገው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ የምናስገዛ ከሆነ፥ እግዚአብሔር የምንጠይቀውን ሁሉ ለእኛና በእኛ አማካይነት ተግባራዊ ያደርጋል። ይህ እውነት የሚሆነው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ስናስገዛና የምንጸልይባቸው ነገሮች እግዚአብሔር እንዲከናወኑ የሚፈልጋቸው ሲሆኑ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንዳንድ ሰዎች ልመናችን ምንም ይሁን ምን፥ ትክክልም ይሁን ስሕተት፥ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሁሉ ለመመለስ ቃል ገብቶልናል ይላሉ። ይህ የተስፋ ቃል ምን ማለት ይመስልሃል? ለ) ጸሎቱ ላልተመለሰለት ሰው ምን ምላሽ ትሰጠዋለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካ ምግብ በላ (ዮሐ. 13:1-38)

ከዮሐንስ 13-17 በኋላ የወንጌሉ ትኩረት ይለወጣል። እስካሁን አጽንኦት የተሰጠው ለኢየሱስ ክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት፥ ላደረጋቸው ምልክቶችና ለሕዝብ ላቀረባቸው ትምህርቶች ነበር። ዮሐንስ በዚህ ይፋዊ አገልግሎት ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለሰጠው ቀጥተኛ ትምህርት ብዙም የገለጸው ነገር የለም። አሁን ግን ዮሐንስ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሳለ በመጨረሻው ምሽት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶች ላይ አተኩሯል። የመሞቻው ቀን የተቃረበ መሆኑን የተገነዘበ አባት ለልጆቹ የመጨረሻ ምክሩን እንደሚሰጥ ሁሉ፥ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ወሳኝ የአዲስ ኪዳን ትምህርቶችን አካፍሏቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ክርስቶስ አዲስ ኪዳንና የጌታ እራት ሥርዓትን መመሥረቱን አጉልተው ሲያሳዩ፥ ዮሐንስ ደግሞ ክርስቶስ ከሞቱ፥ ከትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላ ተከታዮቹ ሊኖሩት ስለሚገባ ሕይወት ገልጾአል።

ሀ. ክርስቶስ የትሕትና አገልግሎት የመንግሥቱ ምሳሌ እንደሆነ ገልጿል (ዮሐ 13፡1–17)። በአይሁድ ባሕል የአንድን ሰው እግር ማጠብ እጅግ ዝቅተኛ ሥራ ነው። ይህ አንድ የቤት አገልጋይ የሚያከናውነው ተግባር ነው። ቤተሰቡ አገልጋይ ከሌለው ሚስት ወይም ልጆች እንጂ አባወራው የእንግዳውን እግር አያጥብም። የሚደንቀው ነገር ታዲያ የዓለም ፈጣሪ የደቀ መዛሙርቱን እግሮች አጠበ። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ትሕትና ነው። ክርስቶስ ይህንን ያህል ራሱን ዝቅ ካደረገ፥ እኛም አርአያውን ተከትለን ራሳችንን በሌሎች ፊት ዝቅ ማድረግና ሌሎችን ማገልገል ይኖርብናል።

ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበው ለምንድን ነው? አንደኛው፥ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽበት መንገድ በመሆኑ ነው። በተጨማሪም በሞት ከመለየቱ በፊት እነርሱን የሚያገለግልበት የመጨረሻ ዕድል በመሆኑም ነው። ዮሐንስ ይህንን ተግባር «የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው» በማለት ገልጾአል። ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነበረውን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቶ ነበር። አሁን ግን ከቶ በማይረሱት መንገድ ነበር ፍቅሩን ያሳያቸው። ክርስቶስ እንደ ባሪያ እግራቸውን አጠበ። ፍቅር ሁልጊዜ ያገለግላል፥ ይሰጣልም። ፍቅር ከስሜት በላይ ነው። ፍቅር ሌሎችን ማገልገልና ሲያድጉ ማየት ነው። ፍቅር ሌሎችን ማገልገልን እንደ ዝቅተኛነት አይመለከትም።

ሁለተኛው፥ ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ማየት የሚፈልገውን ባሕርይ በምሳሌነት ለመግለጽ ነው። ዮሐንስ ክርስቶስ ሊደርስበት ያለውን ነገር ሁሉ ያውቅ እንደ ነበር ገልጾአል። የመጣበትን ስፍራ ያውቅ ነበር – ከሰማይ። የመጣበትንም ምክንያት ያውቅ ነበር። ለመሞት ተመልሶ የሚሄድበትንም ስፍራ ያውቅ ነበር – ወደ ሰማይ። እንዲሁም እግዚአብሔር አብ የሰጠውን ኃይልና ሥልጣን ሁሉ ያውቅ ነበር። ይህ ግን እንዲኩራራ ወይም ሌሎች እንዲያገለግሉት አላደረገውም። ክርስቶስ ተከታዮቹ ይህንኑ ባሕርይ እንዲይዙ ይፈልጋል። ሥልጣንና ኃይልን ከመፈለግና ሌሎች እንዲያገለግሉን ከመሻት ይልቅ ራሳችንን ዝቅ አድርገን አንዳችን ሌላውን ልናገለግል ይገባል።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ምሳሌውን እንድንከተል ያሳየንን ነገር በመውሰድ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግር መታጠብ አለብን ይላሉ። የክርስቶስ ምኞት ግን ከዚህ የላቀ ነው። እግርን ማጠብ ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ማገልገል አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ ጌታቸውና መምህራቸው እንደ ሆነ ያምኑ ነበር። ጌታቸው ራሱን ዝቅ አድርጎ ካገለገላቸው፥ እነርሱም እንዲሁ ከማድረግ መቆጠብ የለባቸውም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እርስ በርሳቸው አገልግሎት ሊሰጣጡ የሚችሉባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ። ለ) እነዚህ የጠቀስሃቸው ነገሮች ተግባራዊ እየሆኑ ናቸው? ከሆኑ ለምን? ካልሆኑስ ክርስቲያኖች ሁሉ ሌሎችን ዝቅ ብለው ቢያገለግሉ በቤተ ክርስቲያናችን ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣል?

ለ. ክርስቶስ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተነበየ (ዮሐ 13፡18-38)። ዮሐንስ ክርስቶስ በሕይወቱ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውም ነገር ለመቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በተደጋጋሚ ገልጾአል። ጊዜው ከመድረሱ በፊት ክርስቶስን ማንም ለማሰር አይችልም። ነገር ግን የተወሰነው የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስ ክርስቶስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ። ክርስቶስ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ለማሳየት ዮሐንስ ክርስቶስ ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው ብቻ ሳይሆን፥ ይህም ሰው ይሁዳ እንደ ሆነ መተንበዩን ጠቅሷል። በዮሐ 13፡23 ላይ ኢየሱስ «ይወደው ከነበረው ደቀ መዝሙር» ጋር እንተዋወቃለን። ከዚህ ምዕራፍ ጀምሮ እስከ መጽሐፉ መጨረሻ ድረስ ዮሐንስ ራሱን ለመጥቀስ ይህንን የተለየ ስም ይጠቀማል።

ይሁዳ ከክፍሉ ከወጣ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይበልጥ ነፃ ሆኖ ማስተማርና ወደፊት ሊኖሩት ስለሚገባቸው ሕይወት ያዘጋጃቸው ጀመር። ከእነርሱ ጋር የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር። ከ40 ቀናት በኋላ በአካል ከእነርሱ ጋር መኖሩ ያበቃል። እርሱ ወደ ሰማይ ስለሚሄድ እርሱ ወደሚሄድበት ሊከተሉት አይችሉም። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት እውነቶችን ገልጾላቸዋል፦

ሀ. ወንጀለኞች የሚሰቀሉበት ታላቁ የኀፍረት ስፍራ ወደ ክብር ስፍራ ይቀየራል። ክርስቶስ በታዛዥነት በመስቀል ላይ በመሞት እግዚአብሔርን ያከብር ነበር። እግዚአብሔርም የኀፍረቱን መስቀል ለውጦ ኢየሱስን ያከብረዋል፤ ለተከታዮቹም ሁሉ የመመኪያ ስፍራ ያደርግላቸው (1ኛ ቆሮ. 1፡18፤ ገላ. 6፡14)። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱና ከሞትም በመነሣቱ፥ ስሙ በታሪክ ሁሉ ከስሞች ሁሉ በላይ የላቀ ስም ለመሆን በቅቷል።

ይህ ለሰው ልጆች ፍጹም እንግዳ ነው፤ እግዚአብሔር ለሰዎች ኀፍረት የሆነውን ነገር ለውጦ ለራሱ ክብር እንደሚጠቀምበት በኢየሱስ ሕይወት በግልጽ ታይቷል። እግዚአብሔር የተጣለውን ድንጋይ (ኢየሱስን) የማዕዘን ራስ አድርጎታል (ማቴ. 21፡42-44)። ሽባዋን ሴት ተጠቅሞ ስለ ጸጋው እንድትመሰክር አድርጓል። የጳውሎስን የሥጋ መውጊያ ወስዶ የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ድካም እንደሚፈጸም አሳይቷል (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። በሕይወታችን የሚገጥመንን በሽታ፥ ሥቃይና ችግር በመጠቀም ክብሩን ይገልጻል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ኀፍረት የሚመስለውን ነገር በመጠቀም በሕይወትህ ክብሩን ሲገልጽ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ በሕይወታችን የሚከሰተውን ችግር ስለምንመለከትበት መንገድና በዚህም ጊዜ ስለምናደርገው ጸሎት ምን ዓይነት የአመለካከት ለውጥ እንዲኖረን ያደርጋል?

ለ. አዲሱና እጅግ ታላቁ የክርስቶስ ትእዛዝ “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚል ነው። በአንድ በኩል ይህ አዲስ ትእዛዝ አይደለም። ይህ አሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተሰወረ ሲሆን (ዘሌዋ. 19፡18 አንብብ)፥ ክርስቶስም ሁለቱ ታላላቅ ጠቃሚ ትእዛዛት እግዚአብሔርንና ባልንጀሮቻችንን መውደድ እንደሆነ ገልጾአል (ማቴ. 22፡37-40)። እንግዲህ ይህ ትእዛዝ «አዲስ» የሚሆነው እንዴት ነው? አዲስ ትእዛዝ የሚሆነው፡-

  1. አዲስ አጽንኦት አለው። ምንም እንኳ ብሉይ ኪዳን እርስ በርስ ስለመዋደድ በግልጽ ባይናገርም፥ በሌሎች ብዙ ትእዛዛት ላይ ግን ነገሩ ተወስቷል። አሁን ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ብዙ ሕግጋትና ደንቦች ሳይሆን በፍቅር ሕግ እንዲመሩ ገልጾአል።
  2. ሰዎች እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ውስጥ እግዚአብሔር ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚፈልጋቸው ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ፍቅር የትእዛዛት ሁሉ ፍጻሜ ሆኖ ተገልጾአል። ከውጫዊ ተግባራት ጋር የሚያያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕግጋትን ከሚደነግጉ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተቃራኒ፥ ኢየሱስ ከተከታዮቹ የሚፈልገው አዲስ ውስጣዊ አመለካከትን ነው፤ ይህም አንዱ ለሌላው የሚያሳየው ፍቅር ነው። እግዚአብሔርንና ሰዎችን ከወደድን ክርስቶስ የሚፈልጋቸውን ትእዛዛት መጠበቅ ተፈጥሯዊ ጉዳይ ይሆናል።
  3. የአንድ ክርስቲያን ምልክቱ ወይም መታወቂያው ነው። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ለመሆን ምልክቱ መገረዝና ውጫዊ ሕግጋትን መጠበቅ ነበር። አሁን ግን የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችን ምልክቱ እርስ በርስ ያለን ፍቅር እንደ ሆነ ተመልክቷል።
  4. በዓይነቱና በጥልቀቱ። ፍቅርን የሚገልጹ ሦስት የግሪክ ቃላት አሉ። ኤሮስ (Eros) ባል ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ያመለክታል። ፊሊዮ (Phileo) በጓደኛሞች መካከል የሚታየውን ፍቅር ያሳያል። አጋፔ (Agape) መለኮታዊ ማለትም ራሱን የሚገልጥ ፍቅር ነው። ክርስቶስ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት እርሱ እግራቸውን እንዳጠበና ስለ እነርሱም ሲል በመስቀል ላይ እንደ ሞተ ሁሉ የእርሱ የሆኑ ሁሉ ይህንኑ እንዲያደርጉ ነው። ለሌሎች መኖር እዲስ ትእዛዝ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የማያምኑ ሰዎች እንደ አንድ አማኝ ከእኛ የሚጠብቁብንን ነገሮች ዘርዝር። ፍቅር ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ነው? ለምን? ለ) ፍቅር የክርስቲያን መለያ መሆን አለበት፥ ዛሬ በክርስቲያኖች መካከል ፍቅር ጠፍቶ መከፋፈል የሰፈነው ለምን ይመስልሃል?

ሐ. ጴጥሮስ ለክርስቶስ ሲል ለመሞት እንዳሰበ ቢናገርም፥ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ኢየሱስ ተንብዮአል። ለክርስቶስ ለመኖር ወይም ለመሞት ቃል መግባት ቀላል ቢሆንም፥ ተግባራዊ ማድረጉ ግን ከባድ ነው። እጅግ ደፋር ደቀ መዝሙር የነበረው ጴጥሮስ ክርስቶስን ክዶታል። እኛም ከእርሱ ላንሻል እንችላለን። ነገር ግን ክርስቶስን በመታዘዝ እንድናድግ የሚያበረታቱን ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ጴጥሮስን ይቅር ብሎ እንደገና እንደ ተጠቀመበት ሁሉ እኛንም ይቅር እንደሚለን እናውቃለን። ሁለተኛው፥ ጸንተን እንድንቆም የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አለ። ስለ አንተ እሞታለሁ ብሎ ቃል የገባው ጴጥሮስ ሳይሳካለት ቀርቷል። በቃላችን እንድንጻጸና የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስ ስለ ሞቱ ትንቢት በተናገረ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች የሰጡት ምላሽ (ዮሐ.12፡20-50)

ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ የመጨረሻ ቀናት ሲናገር ስለ ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎት የጀመረውን ገለጻ የደመደመው በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የተለያዩ ሰዎች ለኢየሱስ የሰጡትን ምላሽ ምሳሌ አድርጎ በማቅረብ ነው። የእነዚህን ሰዎች ምላሽ የያዘው ልክ በሰርግ ላይ እንደ ተነሣ ፎቶ በዚያን ጊዜ የነበረውንና አሁንም ሰዎች ለኢየሱስ የሚሰጡትን ምላሽ ለማጤን ይረዳሉ።

ሀ. ግሪኮች፡- ዮሐንስ የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ግሪኮች እንደ ነበሩ ገልጾአል። ምናልባትም እነዚህ ግሪኮች እንደ ቆርኔሌዎስ የራሳቸውን ሃይማኖት ትተው የአይሁዶችን ሃይማኖት የተከተሉ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ የተነገረውን ዜና ሰምተው ሊያነጋግሩት ፈለጉ። ነገር ግን ምናልባትም ከሕዝቡ ብዛትና አሕዛብ ከመሆናቸው የተነሣ ከክርስቶስ ጋር ለመነጋገር ዕድል የማያገኙ ስለመሰላቸው ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ቀረቡ። ፊልጶስ የገሊላ ሰው በመሆኑ ምናልባት ከአሕዛብ ጋር ቅርበት ሳይኖረው አይቀርም።

ስሙ ወላጆቹ የአሕዛብን ባሕል እንደ ተቀበሉ ያሳያል። ስለዚህ ግሪኮች ፊልጶስ ከክርስቶስ ጋር ቀጠሮ ለመያዝ ሊረዳን ይችላል ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ፊልጶስ ወደ ጓደኛው ወደ እንድርያስ በመሄድ ተያይዘው ወደ ክርስቶስ መጡ። ኢየሱስ ከግሪኮቹ ሰዎች ጋር ስለ መነጋገሩ በዚህ ክፍል የተጠቀሰ ነገር የለም። ምናልባትም ዮሐንስ ይህንን ታሪክ የጠቀሰው ከክርስቶስ ሞት በፊት ወንጌል ወደ አሕዛብ መድረሱን ለማመልከት ይሆናል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ፥ የምሥራቹ ቃል ብዙ አሕዛብን ወደ ክርስቶስ ያመጣ ነበር።

ለ. ኢየሱስ፡- ኢየሱስ ሞቱ ያልጠበቀው ነበር? አልነበረም። ሞቱ እየቀረበ መምጣቱን ያውቅ ነበር። ይህ ማለት ግን ክርስቶስ ከሚጠብቀው ስቅለትና ከሚደርስበትም ነገር ጋር ግብግብ አልገጠመም ማለት አይደለም። እስካሁን ድረስ ዮሐንስ የክርስቶስ ጊዜ እንዳልቀረበ ሲገልጽ ነበር የቆየው። አሁን ግን ለስቅለቱ ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩ «ጊዜው እንደ ደረሰ» ገልጾአል። የስንዴ ቅንጣት ለመብዛትና ፍሬ ለመስጠት መሞት እንዳለባት ሁሉ፥ ክርስቶስም መሞት ነበረበት። ይህ መርሕ ታዲያ ክርስቶስን በሚከተሉት ሁሉ ላይ የሚሠራ ነው። ለግል ፍላጎታችን ካልሞትን፥ ለሕልማችን ካልሞትን፥ ለተደላደለ ኑሮ ካልሞትን፥ ለኃጢአት ካልሞትን ሕይወታችን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እርባና አይኖረውም። የሮም መንግሥት ባስከተለባቸው ስደት በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሲሞቱ የተመለከቱ አንድ የጥንት ጸሐፊ እንደ ገለጹት፥ “የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው።” ሞትን የመረጡት የዘላለም ሕይወትን አግኝተዋል። ነገር ግን ከሞት ለመሸሽ የሞከሩ ሰዎች ትልቁን ሕይወት ማለትም የዘላለም ሕይወትን አጥተዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስን በመከተልህ «የሞትህባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) «ሞትህ ያስከተለው ፍሬ ምንድን ነው? ሐ) ሰዎች ለመሞትና ክርስቶስን በሙሉ ልባቸው ለመከተል አለመፈለጋቸውን እንዴት እንደተመለከትኸው ግለጽ። የሕይወታቸው ዘላለማዊ ፍሬ ምንድን ነው?

ሐ. እግዚአብሔር አብ፡– ሰው እንደ መሆኑ ኢየሱስ ከመስቀል ሞቱ ለማፈግፈግ ፈልጎአል። ለመሆኑ እስከ መጨረሻ እንዲጸና ያደረገው ምንድን ነው? ሦስት ነገሮች አሉ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ዓላማውን በግልጽ ያውቃል። ወደ ዓለም የመጣውም ለመሞት እንደ ሆነ ያውቃል። ስለዚህ ለሌሎች ፍላጎቶች ላይገዛ ለእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ለመታዘዝ ቻለ። ሁለተኛው፥ ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔርን ለማክበር ቆርጦ ነበር። ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠት እንጂ ለሕይወቱ ትልቅ ግምት አልሰጠም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በሞቱ እንዲከብር ጠየቀ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሕይወትና በፈጸማቸው ተአምራት ደስ መሰኘቱን በሕዝቡ ሁሉ ፊት በይፋ ገለጸ። እግዚአብሔር በሞቱም ይከብር ነበር። ሦስተኛው፥ ክርስቶስ የሞቱን ውጤቶች ለመመልከት ችሎ ነበር። በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ለማስገኘት በመቻሉ ስሙ ከስሞች ሁሉ እንደሚልቅና አንድ ቀን ሰዎች ሁሉ እንደሚያከብሩት ተገነዘበ (ፊልጵ. 2፡9-11፤ ዕብ. 12፡2)።

በሕይወት ዘመናችን የምንፈጽመው ትልቁ ዓላማ ምንድን ነው? ትልቁ ዓላማችን በሕይወታችን፥ በድርጊታችንና በአሳባችን እግዚአብሔርን ማስከበር ሊሆን ይገባል። ዓላማችን ይህ ከሆነ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንደ ብርቱ ሕመም ድህነት፥ ስደት፥ ሞት የመሳሰሉ ነገሮችን ወደ ሕይወታችን ሊያመጣ ይችላል። መብቱም የእርሱ ነው። እግዚአብሔርን ለማክበር እስከፈለግን ድረስ፥ በሕይወታችን የሚከብርበትን መንገድ መምረጡ የእግዚአብሔር ድርሻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር በሕይወትህ እንዲከብር የምትፈልግባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በሕይወትህ የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራስህን መንገድ የምትከተልባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህን ነገሮች ተናዝዘህ እግዚአብሔር በሁሉም ነገር የእርሱን ክብር እንድትፈልግ እንዲረዳህ ለምነው። ሐ) ከራስህ በላይ የእግዚአብሔርን ክብር በመፈለግህ ሕይወትህን ዓላማህን፥ ሥራህን ቤተሰብህን፥ ወዘተ… እንዴት እንደ ለወጠ አብራራ።

ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ሰይጣን ድል ያደረገበት ወቅት ይመስል ነበር። ኢየሱስ ይህንን ጊዜ የጨለማ ጊዜ በማለት ጠርቶታል። ዳሩ ግን መስቀሉ ሦስት ነገሮችን አከናውኗል፡-

አንደኛው፥ በዓለም ላይ ፍርድን አምጥቷል። መስቀሉ የታሪክ መለያ መሥመር ነው። ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ያስገኘውን ድነት (ደኅንነት) የማይቀበሉ ሰዎች የዘላለምን ሞት ፍርድ ይቀበላሉ።

ሁለተኛው፣ የዚህን ዓለም አለቃ አሸንፎአል። ሰይጣን ክርስቶስ ተሰቅሎ እንዲሞት በማድረግ ያሸነፈ መስሎት ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ በሞቱ ሰይጣንን አሸነፈው። (ቆላ. 2፡15 አንብብ።) ሰይጣን በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጫና በመስቀሉ ላይ እንደ ተወገደ አዲስ ኪዳን ያስተምራል። ሰይጣን ሽንፈትን ከመከናነቡም በላይ ፍጻሜውም በደጅ ነው። ነገር ግን ሰይጣን ከእርሱ ጋር ወደ ሲኦል የሚወርዱ ሰዎችን ለማግኘት ትግሉን ቀጥሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ሰይጣን ለመጨረሻ ጊዜ ድል ይመታል፤ ወደ ሲኦልም ይጣላል (ራእይ 20፡10)።

ሦስተኛው፥ መስቀሉ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ይስባል። ይህም በሁለት መንገድ ይፈጸማል። በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ይቀበላሉ። ኢየሱስ የኃጢአት ዕዳችንን በከፈለበት ዓይናቸው በመስቀሉ ላይ ነውና። በኢየሱስ የማያምኑ ሰዎች ግን በፍርድ ቀን በፊቱ ሲቀርቡ የግዳቸውን እንዲያከብሩት ይደረጋሉ (ፊልጵ. 2፡9-10)።

መ. ሕዝቡ፡- ዮሐንስ የገለጸው ሦስተኛው ምላሽ ሕዝቡ ክርስቶስ ስለ ሞቱ የተናገራቸውን ነገሮች እንደ ተገነዘቡ ያሳያል። መሢሑ ለዘላለም ይገዛል ብለው ስላሰቡ፥ አይሁዶች ክርስቶስ ይህንን እንዲያብራራላቸው ጠየቁት። ክርስቶስ ጥያቄውን በቀጥታ ባይመልስም፥ እርሱ «ብርሃን» እንደ ሆነ በግልጽ ነገራቸው። በምድር ላይ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። ከዓለም በሚሄድበት ጊዜ ልዩ ብርሃኑ አብሮት ይሄዳል። ስለሆነም፥ ክርስቶስ በመካከላቸው ሳለ በእርሱ ማመን አለባቸው። ከዚያም አይሁዶች በክርስቶስ መንፈሳዊ ብርሃን ደስ ሊሰኙ ይችላሉ። ይህም «የብርሃን ልጆች» ማለትም «የእግዚአብሔር ልጆች» እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል (ዮሐ 1፡12)። ዮሐንስ ከክርስቶስ ተአምራዊ ምልክቶች ባሻገር በአይሁዶች መካክል የተከሰተውን አለማመን ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። አይሁዶች መሢሑን እንደማይቀበሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያውቅ ነበር።

ሠ. ጥቂት የሃይማኖት መሪዎች፡- ወንጌላት በሃይማኖት መሪዎቹ አለማመን፥ ለኢየሱስ ባላቸው ጥላቻና እርሱንም ለመግደል በሸረቡት ሴራ ላይ ትኩረት አድርገዋል። ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስና የአርማትያው ዮሴፍን የመሳሰሉ አንዳንድ መሪዎች በክርስቶስ ማመናቸውን ዮሐንስ ገልጾአል። ይህም ሆኖ ዮሐንስ እነዚህን ሰዎች የጠቀሰው ክርስቲያኖች እንደ እነርሱ መሆን እንደሌለባቸው ለመግለጽ ነው። ከምኩራብ እንዳይባረሩ ስለ ሠጉ በኢየሱስ ማመናቸውን ይፋ ለማድረግ ፈሩ፤ ምክንያቱም ከምኩራብ ከተባረሩ እንደ አይሁዶች ስለማይታዩ ነበር። ይህ ከሆነ ደግሞ የሰዎችን አክብሮት ከማጣታቸውም በላይ ሕይወታቸው በችግር የተሞላ ይሆናል። ዮሐንስ ግን ይህ እርምጃቸው ከእግዚአብሔር ይልቅ የሰውን ምስጋና መምረጣቸውን እንደሚያሳይ ገልጾአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ለመደበቅ የምንፈተነው እንዴት ነው? ለ) ይህንን የምናደርገው ለምንድን ነው? ሐ) የዮሐንስ አሳቦች በክርስቶስ ያለንን እምነት በግልጽ ለማሳየት ከመፍራታችን ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?

በዮሐንስ 12፡44-49 ላይ ኢየሱስ ለሕዝቡ የመጨረሻውን ቃሉን ተናግሯል። ማስጠንቀቂያዎቹ ግልጽና ጠንካራ ነበሩ። አንደኛው፥ እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ በፍጹም አንድነት ስለሚሠሩና በባሕርይም አንድ ስለሆኑ፥ ለደኅንነት ሁለቱንም መቀበል የግድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጾአል። አይሁዶች በእግዚአብሔር አብ እናምናለን እያሉ፥ እግዚአብሔር ወልድን አንቀበልም ማለት አይችሉም። ስለሆነም ክርስቶስ አምላክ በመሆኑ ከእግዚአብሔርም ተልኮ በመምጣቱና የተናገራቸውም ነገሮች በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል በመሆናቸው እርሱን መስማት ነበረባቸው። የዘላለም ሕይወት ሊገኝ የሚችለው አብ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ብቻ ነው። ሁለተኛው፥ ክርስቶስ እርሱን ባላመኑ ሰዎች ላይ ፍርድ እንደሚመጣ አስጠንቅቋል። ምንም እንኳ ፈራጁ እርሱ ራሱ ቢሆንም፥ ኢየሱስ ቆሞ መመስከር አያስፈልገውም። (ዮሐ 5፡27 አንብብ)። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት የድነትን (የደኅንነትን) መንገድ ከማሳየታቸውም በላይ ምስክርነቱ የማያምኑ ሰዎችን ይኮንናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች የማያምኑ ጓደኞቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው በክርስቶስ ካላመኑ ምንም ያህል ጥሩ ሰዎች ቢሆኑም፥ የዘላለም ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በገርነትና በግልጽ ማስጠንቀቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርያም ኢየሱስን ሽቶ መቀባቷ እና ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በድል መግባቱ (ዮሐ. 12፡1-19)

  1. ማርያም ኢየሱስን ሽቶ ቀባችው (ዮሐ. 12፡1-11)

ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ደርሷል፤ የቀረው ስድስት ቀናት ብቻ ነው። ክርስቶስ ቢታንያ በሚገኘው የማርያም፥ የማርታና የአልዓዛር ቤት ተቀምጧል። ይህ ቤተሰብ ለክርስቶስ ያለው ፍቅር ጥልቅ በመሆኑ፥ ለክብሩ ትልቅ ግብዣ አዘጋጁለት። ሦስቱ የቤተሰቡ አባላት ፍቅራቸውን ለክርስቶስ ገለጹ። ምናልባትም ታላቅ እኅታቸው የነበረችው ማርታ ክርስቶስን ታስተናግድ ነበር። አልዓዛር ከክርስቶስ ጋር በማዕድ ተቀምጦ ይበላ ነበር። ማርያም የክርስቶስን እግር በውድ ሽቶ ትቀባ ነበር። የምታደርገው ነገር ሁሉ ለየት ያለ ነበር። ምንም ዓይነት የራስ ወዳድነት ስሜት ሳይታይባት ውድ ንብረቷን ሰጠችው። በሰው ፊት ጸጉሯን ፈትታ ለቀቀችው፤ ይህም የተከበሩ የአይሁድ ሴቶች የማያደርጉት ነገር ነው። ከዚያም እንደ አገልጋይ እግሩን አጠበች። (እግር ማጠብ የአገልጋዮች ተግባር ነበር።) ምናልባት ሽቶውን ያስቀመጠችው ለጋብቻዋ ቀን ይሆናል። ነገር ግን ለሌሎች ላናስብ ለእግዚአብሔር ያለንን የተለየ ፍቅር የምንገልጽበት ጊዜ ሊኖር ይገባል። ማርያም ፍቅሯን የገለጻችው በዚህ መንገድ ነበር።

ሌሎቹ ወንጌላት በሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ምላሾች ላይ ሲያተኩሩ፥ ዮሐንስ ግን በይሁዳ ላይ አተኩሯል። ይሁዳ የኢየሱስንና የቡድኑን ገንዘብ የሚይዝ ሰው እንደ ነበር ዮሐንስ ገልጾአል። ነገር ግን ሁልጊዜ ከሚይዘው ገንዘብ እየሰረቀ ይወስድ ነበር። ገንዘቡን የፈለገው ለራሱ እንጂ ለድሆች አልነበረም። ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ የሰጠው በድንገት አይደለም። ነገር ግን የገንዘብ ፍቅር በልቡ ውስጥ እንዲያድግ አድርጎ ነበር። ይህ የኃጢአት አረም በልቡ ውስጥ አደገ። ምንም እንኳ ክርስቶስ ስለ ገንዘብ ያስተማረውን ቢሰማም፥ ክርስቶስም ያደረጋቸውን ተአምራት ቢያይም፥ ይህ ኃጢአት በልቡ ውስጥ የሚያድገውን ክፋት እንዳያይ አሳወረው። በገንዘብ ረገድ ሰይጣን በሕይወቱ ውስጥ ስፍራ እንዲያገኝ ካደረገ፥ ሰይጣን በይሁዳ ሕይወት ውስጥ የፈለገውን ነገር ለመፈጸም ቀላል ይሆንለታል።

ይህ በሁላችንም ሕይወት ውስጥ እውነት ነው። ብዙ ጊዜ የሚያስቸግሩን ታላላቅ ኃጢአቶች አይደሉም። ትናንሽ የምንላቸው ኃጢአቶች ናቸው፥ ከምጽዋት የምትወሰደው ትንሿ ገንዘብና ትንሿ የዓይን አምሮት በጊዜ ካልተቀጩ፥ ሰይጣን ሕይወትህን ሊቆጣጠርና የኋላ ኋላም ሊያጠፋህ ይችላል።

ማንም ሰው ድንገት ዝሙት አይፈጽምም። የሚጀምረው በዚህ አሳብ ከተያዘ ሕሊና ነው። ግድያና ሌብነትም የሚጀምሩት ከክፉ ሃሳብና ቅናትና ምኞት ነው። አወዳደቃችን የይሁዳን ያህል የከፋ ላይሆን ይችላል፤ የማይታረሙ ትናንሽ ኃጢአቶች ወደ ትልቁ ያመራሉ፤ ይህም ሕይወታችንን፥ ምስክርነታችንን፥ ቤተሰባችንንና የኢየሱስን ስም የሚያጎድፍ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ ትልልቅ ኃጢአቶች ብቻ ሳይሆን ስለ ትንንሾቹም ማሰብ እንዳለብን ይህ ትምህርት የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ አሳሳቢ አይደሉም ብለህ የናቅሃቸውን ኃጢአቶች በምሳሌነት ጥቀስ። እነዚህ ኃጢአቶች አድገው ሕይወትህን ሊገዙ የሚችሉት እንዴት ነው? ሐ) አሁን ጊዜ ወስደህ ሕይወትህን በጸሎት መርምር። መንፈስ ቅዱስ እንደ አረም ወደ ሕይወትህ ሊዘልቁና ሊያጠፉህ ብቅ የሚሉትን ትናንሽ ኃጢአቶች እንዲያሳይህ ተማጠነው። በሕይወትህ ስለምታያቸው ኃጢአቶች ንስሐ ግባ። ከዚያም በክርስቶስ አማካይነት ስላገኘኸው ድል እግዚአብሔርን አመስግን።

  1. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በድል ገባ (ዮሐ 12፡12-19)

ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቶስ በ”ሆሳዕና” ዝማሬ ታጅቦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ፥ ታሪኩን በገለጸበት በዚህ ክፍል የተለያዩ ቡድኖች በሰጡት ምላሾች ላይ ትኩረት አድርጓል። ክርስቶስ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ ምን ትርጉም እንዳለው ሕዝቡ ባይገነዘብም፥ በሁኔታው ግን ደስ ሳይሰኙ አይቀሩም። በወቅቱ ለኢየሱስ በተደረገው ታላቅ አቀባበል የተደነቁት ደቀ መዛሙርትም እስከ ትንሣኤው ድረስ ክርስቶስ የአይሁድ የሰላም ንጉሥ ሆኖ መምጣቱን አልተገነዘቡም ነበር። ለሌሎች ክርስቶስ ተአምራትን በማድረግና በማስተማር አስደናቂ ትእይንት እንደሚያሳይ ሰው ነበር። የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ የተከታዮቹን ብዛት ሲመለከቱ ይበልጥ ቀኑበት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነሣው (ዮሐ. 11:1-57)

ሞት የሰው ልጆች ሁሉ ዋነኛ ጠላት ነው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ አንሥቶ ሥጋዊ ሞት የሰው ልጆች ሁሉ የመጨረሻው ጠላት ሆነ፡፡ ሁላችንም በሞት ተሸንፈናል። ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ችግሮች መልስ ይሆን ዘንድ፥ ለዚህ ዋነኛ ጠላት መፍትሔ ሰጥቷል። ይህ አልዓዛር ከሞት የተነሣበት ሰባተኛው «ምልክት» ክርስቶስ በሞት ላይ ፍጹም ሥልጣን እንዳለው ከማሳየቱም በላይ፥ ለሁላችንም ተስፋ የሚሰጥ ምልክት ነው። አልዓዛርን ከሞት ያስነሣው ይኸው ክርስቶስ እኛንም ከሞት ያስነሣናል። ነገር ግን በአልዓዛርና በእኛ ትንሣኤ መካከል ልዩነት አለ። አልዓዛር ከሞት ቢነሣም እንደገና ሞቷል። እኛ ግን ክርስቶስ ከሞት በሚያስነሣን ጊዜ ዳግም አንሞትም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሞት ከሁሉም የከፋ ጠላታችን የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ እኛንና የምንወዳቸውን ሰዎች ከሞት እንደሚያስነሣ የሚያመለክተው የተስፋ ቃል ታላቅ መጽናኛ የሚሆንልን ለምንድን ነው?

በዚህ ምድር ለኢየሱስ ቅርብ የሆነው ቤተሰብ የማርያም፥ የማርታና የአልዓዛር ቤተሰብ ሳይሆን አይቀርም። ክርስቶስ ብዙ ምሽቶችን በእነዚህ ወገኖች ቤት ያሳልፍ ነበር። ክርስቶስ የሕይወቱን የመጨረሻ ሳምንት ያሳለፈው በእነርሱ ቤት ነበር። ይህንንም ያደረገው ከኢየሩሳሌም ወደ ቢታንያ በየቀኑ 3 ኪሎ ሜትር ያህል እየተጓዘ ነበር። የሥጋ ወንድሞቹ በክርስቶስ ለማመን ባይፈልጉም፥ የዚህ ቤተሰብ አባላት ግን የክርስቶስ የቅርብ ወዳጆችና ደጋፊዎች ነበሩ።

የዮሐንስ ወንጌል በዚህ ስፍራ ትኩረቱን በመለወጥ ወደ ኢየሱስ ሞት እንድንመለከት አድርጓል። ክርስቶስ ከታላላቅ ተአምራቱ መካከል አንዱን በሚፈጽምበት ጊዜ እንኳ፥ በአይሁድ መሪዎች አስተባባሪነት የተቀሰቀሰው የአይሁዶች ቁጣና ጥላቻ ተጧጡፎ ቀጥሏል። ሕዝቡ እንዳይጠፋ ክርስቶስ መሞት እንዳለበት ለመሪዎቹ ግልጽ ነበር። (ዮሐ 11:50 አንብብ።)። ይህም ጥላቻ ክርስቶስን ለመስቀል ሞት ዳርጎታል። ነገር ግን የክርስቶስን ሞት የሚወስነው የአይሁድ መሪዎች ቁጣ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔር የጊዜ ሠሌዳ ነበር። ክርስቶስ ለዓለም ኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነው ጊዜው ሲደርስ ብቻ ነው።

ኢየሱስ የአልዓዛርን መታመም የሰማው በጲሪያ አካባቢ ሆኖ ነበር። አልዓዛርን ለመርዳት ከመፍጠን ይልቅ በዚያው ባለበት አያሌ ቀናት አሳለፈ። የእግዚአብሔር ዕቅድና የጊዜ ሠሌዳ ደቀ መዛሙርቱና ወዳጆቹ ከሚያስቡት የተለየ ነበር። (ማስታወሻ፡ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ልናውቃቸው ከሚገቡን ነገሮች አንዱ፥ የእርሱ የጊዜ ሠሌዳ ከእኛ እንደሚለይ ነው። እኛ ፈጣን ምላሽ በምንፈልግበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በአብዛኛው ይዘገያል። ቅጽበታዊ ፈውስን ስንሻ ለረዥም ጊዜ ከበሽታው ጋር እንድንኖር ወይም በታመምንበት በሽታ እንድንሞት ያደርጋል። በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር የጊዜ ሠሌዳ ጋር ከመታገል ይልቅ ለእርሱ መታዘዝን ልንማር ይገባል። ከእግዚአብሔር ዕቅድና የጊዜ ሠሌዳ ጋር በምንታገልበት ጊዜ በዋናነት ራሳችንን እንጎዳለን።)

ሁለት ቀናት አለፉ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አልዓዛር እንደ ሞተ ያውቅ ነበር። ቀደም ሲል ከአልዓዛር ፈውስ ይበልጥ ለእግዚአብሔር አብና ወልድ ታላቅ ክብር እንደሚሆን ለደቀ መዛሙርቱ ገልጾ ነበር። ለክርስቶስ የአልዓዛር ሞት ከእንቅልፍ ተቀስቅሶ የመነሣት ያህል ብቻ ነበር። እኛም በምንሞትበት ጊዜ ሰውነታችን ለጊዜው ያንቀላፋል። በመጨረሻው ቀን ግን ክርስቶስ ከሞት ያስነሣናል። ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን ግን ነፍሳችን አታንቀላፋም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፥ ምንም እንኳ አካላችን ወይም ሰውነታችን ቢያንቀላፋም ስንሞት የማንነታችን መለያ የሆነችው ነፍሳችን በክርስቶስ ፊት ትሆናለች (2ኛ ቆሮ. 5፡1-10)።

ደቀ መዛሙርቱ አይሁዶች ክርስቶስን ምን ያህሉ እንደሚጠሉትና ሊገድሉትም እንደሚፈልጉ ያውቁ ስለ ነበር፥ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ፈሩ። ሞት ቢጠብቃቸውም እንኳ ከእርሱ ጋር ለመሆን መወሰናቸው የእውነተኛ ፍቅርና ደቀ መዝሙርነት ምልክት ነበር።

ክርስቶስ ቢታኒያ ሲደርስ አልዓዛር ከሞተ ሦስት ቀን ሆኖት ነበር። በአይሁድ ባሕል አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ የአካባቢው ኅብረተሰብ በሚገኝበት የሦስት ቀን ኀዘን ይደረጋል፤ በአራተኛው ቀን የቅርብ ዘመዶች ብቻ ያለቅሳሉ። ከዚያ በኋላ ለተጨማሪ ሦስት ሳምንት በጣም የቅርብ ዘመዶች ብቻ ሲያለቅሱ ይቆያሉ። ዮሐንስ ስለ አልዓዛር ትንሣኤ በጻፈው ታሪክ የልዩ ልዩ ሰዎችና የክርስቶስ ምላሾች አጽንኦት ተሰጥቷቸዋል።

ሀ. ማርታ፡- ማርያም ከእግሩ ሥር በጸጥታ ቁጭ ብላ የክርስቶስን ትምህርት በምትከታተልበት ወቅት፥ ማርታ ክርስቶስን ለማስተናገድ ትጥር እንደ ነበር ታስታውሳለህ (ሉቃስ 10፡40-41)። ማርታ የክርስቶስን መምጣት እንደ ሰማች ልትቀበለው ወጣች። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ተአምር ሲሠራ ስላየች አልዓዛርንም ሊፈውሰው እንደሚችል አመነች። አልዓዛር በመጨረሻው ዘመን ከሞት እንደሚነሣ መናገሯ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንደ ነበራት ያሳያል። ክርስቶስ «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ» በማለት በሙታን ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና የዘላለምን ሕይወት ለመስጠት እንደሚችል ሲናገር አመነችው። (ይህ ኢየሱስ የተናገረው «እኔ ነኝ» የሚለው እምስተኛው ዓረፍተ ነገር ነው።) ማርታ ኢየሱስ 1) መሢሕና 2) የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሙሉ በሙሉ እምናለች። ለክርስቶስ የነበራት ፍቅርና እምነት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ምንም ነገር ቢነግራት አትጠራጠረውም ነበር። እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ሁሉ፥ ማርታም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክራለች።

ለ. ማርያም፡- ከማርታ ይልቅ ማርያም ዝግ ያለች ሴት ትመስላለች። ክርስቶስ እየመጣ መሆኑን ብትሰማም እንደ ማርታ ግን ወጥታ አልተቀበለችውም። በቤት ከለቀስተኞቹ ጋር ተቀምጣ ነበር። ነገር ግን ማርታ ክርስቶስ ሊያገኛት እንደሚፈልግ ስትነግራት ከለቀስተኞቹ ጋር እርሱ ወዳለበት እየሮጠች ሄደች። እንደ ማርታ ሁሉ ማርያምም ክርስቶስ የመፈወስ ችሎታ እንዳለው ማመኗን ገልጻለች።

ሐ. ኢየሱስ፡ ዮሐንስ፥ ኢየሱስ በሁኔታው ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ገልጾአል። ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሣው ያውቅ ነበር። ነገር ግን የማርያምንና የአይሁዶችን ኀዘን በተመለከተ ጊዜ በመንፈሱ እንደ ታወከና በነገሩም እንዳዘነ ተገልጾአል። ከዚያም አለቀሰ። ክርስቶስ ሊሆን ያለውን እያወቀ ለምን አለቀሰ? ክርስቶስ ያለቀሰው በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው፥ ያለቀሰው ኃጢአት በዓለም ውስጥ ስላስከተለው ሥቃይ ነው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ አንሥቶ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጅ ታሪክ የሞት ታሪክ ነበር። እንግዲህ ኢየሱስ ያለቀሰው ኃጢአት ፍጹሙን ፍጥረት በማጥፋቱ ነው። ሁለተኛው፥ ኀዘን ላደቀቃቸው ለአልዓዛር ወዳጆች ነበር ያለቀሰው። አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሣው ቢያውቅም፥ ሌሎች ግን ይህን ዕድል አላገኙም ነበር፡፡ የሌሎች ጉዳት የክርስቶስን ልብ አወከ፥ ስለ ኀዘናቸውም ከማርያምና ከማርታ ጋር አለቀሰ።

በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ማልቀስ ትክክል አይደለም የሚል አመለካከት በአማኞች መካከል ያለ ይመስላል። ለዚህም ጳውሎስ «አታልቅሱ» የሚል መልእክት ማስተላለፉን ይጠቅሳሉ (1ኛ ተሰ. 4፡13-14)። ይህ ግን ጳውሎስ የተናገረውን በቅጡ አለመረዳት ነው። ጳውሎስ በዚህ ምንባብ ላይ የሚናገረው ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳናዝን ነው። ይህን ሲል እንባችንን አውጥተን እንዳናለቅስ መከልከሉ አልነበረም፤ ተስፋ እንደሌላቸው እንዳንሆን እንጂ። ክርስቶስ እንኳ በሞት ምክንያት ስለመጣው ሥቃይ አልቅሷል። ዛሬም ቢሆን የምንወደውን ሰው በሞት ተነጥቀን በምናዝንበት ጊዜ አብሮን ያዝናል። ክርስቲያኖች ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች ማልቀስ ባይኖርባቸውም፥ በሞት ምክንያት ለተለዩአቸው ሰዎች ኀዘናቸውን በለቅሶ መግለጽ ይችላሉ። የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ማልቀሱ ክፋት የለውም። እንባ እግዚአብሔር ኀዘናችንን ለማጠብና ነፍሳችንን ለመፈወስ የሚጠቀምበት መንገድ ነውና። አንድ ሰው እንደ ልቡ እንዳያለቅስ በምንከለከልበት ጊዜ የነፍሱ ኀዘን በእንባ ታጥቦ ኑሮውን በደስታ እንዳይቀጥል ማድረጋችን ነው። ነገር ግን የምንወደውን ሰው ክርስቶስ እንደሚያስነሣውና ነፍሱ በሰማይ እንደምትሆን በመገንዘብ (ክርስቲያን ከሆነ)፥ በተስፋ ቢስነት ሳይሆን የመለየትን ሥቃይ ለመግለጽ ያህል ማልቀሳችን ተገቢ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የሚወዱት ሲሞት ወይም አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥማቸው ክርስቶስ ሰዎች እንዳያለቅሱ የሚከለክል ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) ማልቀስ ተቀባይነት ሊያገኝ ስለሚገባበትና ስለማይገባበት ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን ምን ልታስተምር ትችላለህ?

መ. አልዓዛር፡- ስለ አልዓዛርና በወቅቱ ስለነበረው ምላሽ እምብዛም የተነገረን ነገር የለም። ክርስቶስ በጠራው ጊዜ በከፈኑ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ ከመቃብሩ ወጣ።

ሠ. ጥቂት አይሁዶች፡- በኢየሱስ አመኑ። አእምሯቸው ክፍት ስለነበረ ተአምሩን አይተው ክርስቶስ መሢሕ እንደ ሆነ አመኑ። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ እውነተኛ እምነት ነበራቸው። የአንዳንዶቹ እምነት ግን ዘላቂ አልነበረም። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክርስቶስን ይክዱታል።

ረ. ጥቂት አይሁዶች በክርስቶስ አላመኑም። ይልቁንም ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ከሰሱት። እነርሱም ክርስቶስን ለማስገደል የበለጠ ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ። እውነትን ከመፈለግና የክርስቶስን ማንነት ከመገንዘብ ይልቅ የክብር ቦታቸውን ላለማጣት ሠጉ። ኢየሱስ ዐመፅን ቢያስነሣ፥ ሮም አይሁዶችን ትቀጣለች፥ የአይሁድ መሪዎችም ሥልጣናቸውን ያጣሉ። በ76 ዓ.ም. እንደ ሆነው የአይሁድ ሕዝብ ይመኩባቸው የነበሩ ነገሮች ወደሙ። የአይሁድ መሪዎች ክርስቶስን ለመግደል ወስነው ሊይዙት ፈለጉ።

ሰ. ቀያፋ፡- ቀያፋ ሊቀ ካህን ነበር። ይህ ሰው ሕዝቡ ክርስቶስን ተከትሎ በሮም መንግሥት ላይ ቢያምጽ ሊከሰት ስሚችለው አደጋ ሠጋ። «ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ቢሞት እንደሚሻል ገለጸ።» ይህ ሲል ክርስቶስ ቢሞት ዐመፁ እንደማይስፋፋና ሮምም ይሁዳን እንደማታጠፉ መግለጹ ነበር፡፡ ቀያፋ በዚህ ንግግሩ ሳያውቀው ትንቢት እየተናገረ ነበር። ኢየሱስ ለሰው ልጅ ኃጢአት በመስቀል ላይ ባቀረበው መሥዋዕት ሕዝቡን ከጥፋት አዳነ።

የውይይት ጥያቄ፡- እንደ እነዚህ የመሳሰሉትን ድርጊቶች ዛሬ የምናያቸው እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 12፡1-1 አንብብ። ሀ) ማርያም ለክርስቶስ ያላትን ታላቅ ፍቅር የገለጸችው እንዴት ነበር? ለ) ክርስቲያኖች እንደዚህ ያለ ጽኑ ፍቅር ሊገልጹ የሚችሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ሐ) ባለፈው ዓመት ለክርስቶስ ያለህን ፍቅር በተለየ መንገድ የገለጽኸው እንዴት ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ ከአይሁድ መሪዎች ጋር ተከራከረ (ዮሐ. 10፡22-42)

ከብዙ ጊዜ በኋላ የመታደስ በዓል ሲከበር ክርስቶስ አሁንም በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ነበር። ይህ የመታደስ በዓል የሚከበረው በታኅሣሥ 165 ዓ.ዓ ሲሆን፥ በአንቲኮስ ኤጲፋነስ የረከሰውን ቤተ መቅደስ ይሁጻ መቃብያን መልሶ አደሰው። በዓሉ አይሁዶች ለመጨረሻ ጊዜ የተቀዳጁትን ድል ያመለከታል።

ክርስቶስ በሃይማኖት መሪዎች ለሚመሩ አይሁዶች መሢሕነቱን ደጋግሞ ገልጾአል። የፈጸማቸው ተአምሮችና «ምልክቶች» መሢሕ መሆኑን ይመሰክራሉ። ይሁንና አይሁዶች እስከ አሁን ድረስ በመሢሕነቱ አያምኑም። ምክንያቱም ኢየሱስ አይሁድ ይጠብቁት የነበረው ፖለቲካዊ መሪ ስላልነበረ ነው። ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት አይሁዶችን ነፃ እንዳወጣው እንደ ይሁዳ መቃብያን አልነበረም። ክርስቶስ እነርሱን ደስ ለማሰኘት ተጨማሪ ተአምራትን ለማድረግ አልፈለገም። ቀደም ሲል ብዙ ምልክቶችን ሰጥቷቸዋል፤ ስለሆነም አይሁዶች አሁን ከውሳኔ ላይ መድረስ አለባቸው። ስለዚህ ኢየሱስ ለማያምኑት አይሁድ የሚከተለውን ተናገረ፡-

ሀ. ቀደም ሲል መሢሕ መሆኑንና ያደረጋቸውም ተአምራት ይህንኑ እንደሚያረጋግጡ ነገራቸው።

ለ. ጉዳዩ የተአምራት ሳይሆን የልብ ጉዳይ ነበር። በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች መሢሕ መሆኑን ቀደም ሲል ተረድተው ነበር። የእርሱም በጎች በመሆናቸው በጎቹ ድምፁን ያውቁታል። የክርስቶስ ተከታዮች የዘላለም ሕይወት አላቸው። ከዚህም በተጨማሪ ዋስትናም አላቸው፤ ምክንያቱም በእጁ መዳፍ ይጠብቃቸዋል። በምድር ብርቱ የሆነው እግዚአብሔር አብ ክርስቲያኖችን ለክርስቶስ ሰጥቷል። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ ስለሆነ (ይህ ማለት ግን የ«ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች እንደሚሉት አንድ አካል ማለት አይደለም)፤ ማንም የክርስቶስን በጎች ከእጁ ሊወስድ አይችልም። እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ የእግዚአብሔርን መንጋ ለመጠበቅ ከወሰኑ፥ ከክርስቶስ እጅ ፈልቅቆ ሊወስዳቸው የሚችለው ማን ነው? ማንም የለም።

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 8፡31–39 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ለልጆቹ የሚያደርገውን አስደናቂ ፍቅርና ጥበቃ በተመሳሳይ መንገድ የሚያሳዩት እንዴት ነው? ለ) በችግርህ ጊዜ እነዚህ ምንባቦች የሚያጽናኑህ እንዴት ነው?

የማያምኑት አይሁዶች ኢየሱስ ከሰው የተለየ መሆኑን በትክክል ተገንዝበዋል። እርሱ ሌላው «የእግዚአብሔር ልጅ» (son of god) ነኝ እያለ አለመሆኑን ተረድተዋል። እንዲህ ዓይነቱ የአይሁዶች አነጋገር እንደ ዳዊት ያሉ ሰዎችን የሚያመለክት ስያሜ ነበር (መዝ. 2)። ክርስቶስ ግን የእግዚአብሔር ልዩ ልጅ መሆኑን እየገለጸ ነበር – ከእግዚአብሔር አብ የተለየ ቢሆንም፥ ሙሉ በሙሉ አምላክ ነው። አይሁዶች ይህንን እንደ ስድብ በመቁጠር ክርስቶስን ለመግደል ፈለጉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንጋ መልካም እረኛ ነው (ዮሐ. 10፡1-21)

የውይይት ጥያቄ፡- መዝሙር 23 እና ሕዝቅኤል 34ን አንብብ። ሀ) ከእነዚህ ምንባቦች ስለ እግዚአብሔር ምን እንማራለን? ለ) ከእነዚህ ምንባቦች እግዚአብሔር ፍጹም እረኛን ስለመላኩ ምን እንማራለን? ሐ) ስለ እረኛ አንዳንድ አሳቦችን ለማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንብብ። የአይሁድ እረኞች ምን እንደሚመስሉና በኢትዮጵያ ከሚገኙ እረኞቹ እንዴት እንደሚለዩ ጠቅለል ያለ ማብራሪያ ጻፍ።

ውብ ከሆኑት ምሳሌዎች መካከል አንዱ፥ እግዚአብሔር እንደ እረኛ መመሰሉ ነው። ይህን ምሳሌ በትክክል ለመረዳት፥ የአይሁድ እረኞች ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ከምናያቸው እረኛች በጣም የተለዩ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። አብዛኞቹ በኢትዮጵያ የምናያቸው እረኛች ከደሀ ቤተሰብ የተወለዱና ያልተማሩ ሲሆኑ፥ ለበጎቻቸውም እምብዛም አይጨነቁም። በጎቻቸውን በድንጋይ ይወግራሉ፥ በበትር ይመታሉ፥ ወደ ቤታቸውም ሊወስዱ እያቻኮሉ ይወስዳሉ። አይሁዶች ግን ለእረኞቹ ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ፤ እረኞቻቸውም ለበጎቻቸው የላቀ ስፍራ ይሰጣሉ። የኢትዮጵያ እረኞች ቀኑ ሲመሽ በጎቻቸውን ይዘው ወደ ቤት ይመለሳሉ። የአይሁድ እረኞች ግን ቀኑ ከመሸ በዚያው ባሉበት ከበጎቻቸው ጋር ያድራሉ። ይህም ብዙ የከብት መንጋ ካላቸው የቦረናና ሌሎች የደቡብ ኢትዮጵያ ጎሳዎች ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። የአይሁድ እረኞች ለበጎቻቸው ምርጥ ሣርና ውኃ ለማግኘት ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ። አንዳንድ ጊዜ ሌሊት በጎቻቸውን ለመጠበቅ ሲሉ በረት ይሠራሉ። በረቱ መዝጊያ ስለማይኖረው እረኞቹ በበሩ ላይ ይተኛሉ። ይህም በጎቹ ከበረቱ ወጥተው በአራዊት እንዳይበሉ ይከላከላል። እረኛው ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር በጎቹን ከኋላ ሆኖ እየነዳ ሳይሆን ከፊት ሆኖ እየመራ ነው የሚሄደው። በስማቸው እየጠራ ወደ ለምለም ስፍራ ይመራቸዋል። ትናንሽ የበግ ግልገሎች በሚወለዱበት ጊዜ እረኛው በክንዶቹ አቅፎ ከቦታ ቦታ ያጓጉዛቸዋል። ይህም የአይሁድ እረኞች ከበጎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ መሆኑን ያሳየናል።

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለአይሁድ የእረኞች አለቃ መሆኑን ነግሮአቸው ነበር። ሕዝቡን የሚንከባከብ፥ የሚመራና የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ የሚያዘጋጅ እርሱ ነው። ሕዝቡን ለሚንከባከቡ ለሌሎች እረኞች ማለትም መሪዎች (ነገሥታት፥ ካህናትና ነቢያት) እንደሚሰጥ ተናግሯል። ነገር ግን እነዚህ እረኞች የእግዚአብሔርን መንጋ ስለበተኑ በሌላ እረኛ ማለትም በመሢሑ ተተኩ።

እንግዲህ ኢየሱስ መልካም እረኛ ነኝ ሲል አምላክ ነኝ ማለቱ ነበር። በተጨማሪም፥ የሕዝቅኤል ትንቢት በእኔ ተፈጸመ ማለቱ ነበር። ኢየሱስ ራሱን በእረኛ መስሎ ባቀረበው ተምሳሌት ውስጥ እያሌ እውነቶች ተካትተዋል።

ሀ. ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር መንጋ የሚወስድ በር ነው። ይህም ከርስቶስ «እኔ ነኝ» በማለት የተናገረው ሦስተኛው ዓረፍተ ነገር ነው። እርሱ መንገድ ነው። በክርስቶስ በኩል ሳይመጡ ከእግዚአብሔር መንጋ ጋር ለመቀላቀል የሚሞክሩ ሰዎች ምንም ያህል ቢጥሩ አይሳካላቸውም፤ መጨረሻቸውም የእግዚአብሔርን መንጋ መስረቅ ይሆናል።

ለ. የእግዚአብሔር መንጋ አካል መሆን አለመሆናችንን እንዴት እናውቃለን? የኢየሱስን ድምፅ ስለምናውቅ እንከተለዋለን። ከኢየሱስ ወገን የሆኑ በጎች ድምፁን ስለሚያውቁ በታዛዥነት ይከተሉታል።

ሐ. ሐሰተኛ እረኞች ከበጎቹ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ይመጣሉ። ክርስቶስ ግን ለበጎቹ ጥቅም ይሠራል። በደስታ የተሞላ ሕይወት ይሰጠናል ፍላጎታችንንም ይሞላል።

መ. ኢየሱስ መልካም እረኛ ነው። ይህ ኢየሱስ የተናገረው «እኔ ነኝ» የሚለው አራተኛው ዓረፍተ ነገር ነው። ክርስቶስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት በጎቹን የሚንከባከብ ፍጹም መሪ ነው። ከአራዊት በጎቹን ለመታደግ ከበሩ ላይ እንደሚተኛ የአይሁድ እረኛ፥ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር በጎች ራሱን አሳልፎ ከመስጠቱም በላይ፥ ለዓለም ሁሉ ኃጢአት በመስቀል ላይ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል።

ሠ. ኢየሱስ በሕይወቱ ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው። የአይሁድ መሪዎችም ሆኑ የሮም መንግሥት በክርስቶስ ሕይወት ላይ ሥልጣን የላቸውም። ሕይወቱ በራሱ እጅ በመሆኑ፥ በመስቀል ላይ ለመሞትና በትንሣኤ ሕይወት ለመነሣት ሥልጣን አለው።

ረ. ኢየሱስ ሌሎች በጎች አሉት። ክርስቶስ ይህን ሲል ምናልባትም ወደ ፊት በእርሱ ስለሚያምኑት አሕዛብ ሊሆን ይችላል። እነርሱም የክርስቶስን ድምፅ ለይተው ይከተሉታል። አንድ ቀን የአሕዛብና የአይሁድ አማኞች ቤተ ክርስቲያን ከተባለች አንዲት መንጋ ሥር ይተባበራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- የቤተ ክርስቲያን መሪዎች (ሽማግሌዎች) የእግዚአብሔር መንጋ እረኞች ናቸው። (1ኛ ጴጥ. 5፡1-4 አንብብ።) ከርስቶስ ስለ እረኝነቱ ሚና | ከተናገረው ነገር የእግዚአብሔርን መንጋ ስለመምራት እንማራለን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)