የሕይወት እንጀራ

ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች

መጽሐፍ ቅዱስ፦ እስትንፋሰ- እግዚአብሔር

This entry is part 2 of 52 in the series ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች

መጽሐፍ ቅዱስ፥ ጸሐፊዎቹ በእግዚአብሔር እየተመሩ የጻፉት ብቸኛ መጽሐፍ ነው። ይህ በእግዚአብሔር ምሪት መጽሐፍ ቅዱስን መጻፍ፥ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ይባላል። የእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ትርጉም እግዚኣብሔር ሰብአውያን ጸሐፊዎችን ተጠቅሞ ለሰው ዘር ያለውን ሙሉና ተከታታይነት ያለውን አሳቡን ማስጻፉ ነው። ይህን ሲያደርግ ጸሐፊዎቹ እነሱነታቸውን፥ የአጻጻፍ ስልታቸውን እና የግል ሁኔታቸውን ሳይተዉ እንዲጽፉ ፈቅዷል። ጽሑፉን በማዘጋጀት ረገድ እግዚአብሔር በሰዎች መገልገሉ እውነት ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጽፉትን ሁሉ ባይረዱም፥ በእግዚአብሔር እየተመሩ መጽሐፉን መጽሐፍ ቅዱስ ያሰኙትን ስድሳ ስድስት መጻሕፍት ጽፈዋል። እነዚህ መጻሕፍት አስገራሚ አንድነት ወይም ተያያዥነት ያላቸው ከመሆናቸውም ሌላ፥ የተጻፈው ቃል ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ መጻፉ ቋሚ ማስረጃዎች አሏቸው።  በዚህ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳን በሰው ብዕር ቢጻፍ፥ ሰው ለመሰሉ ሰው የጻፈው ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ለሰው ያስተላለፈው መልእክት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን እግዚአብሔር ቃል በቃል አጻፈውም አላጻፈው፥ የጥንት ዘገባዎች ግልባጭ ሆነም አልሆነ፥ የሰብአዊ ጻሐፊዎች የምርምር ውጤት፥ አሳብ፥ ምኞታቸው ወይም ፍርሃታቸው ሆነም አልሆነ፥ በማንኛውም መንገድ እግዚአብሔር እርሱ የሚፈልገውን ብቻ ይጽፉ ዘንድ ጸሐፊዎቹን መርቷቸዋል። ይህ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል የእግዚአብሔር ቃል ነው። ምንም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች በአቀራረባቸው ምናልባት የሚለያዩ ቢሆኑ፥ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ነው።  የእስትንፋሰ-እግዚአብሔር አስተምህሮ፥ ልዕለ ተፈጥሮ (supernatural) በመሆኑ፥ ለሰዎች ግንዛቤ አንዳንድ ችግሮች ያስከትል ይሆናል። እንዴት ነው አንድ ሰብአዊ ጻሐፊ በራሱ አሳብና እውቀት እየጻፈ፥ እግዚአብሔር እንዲመዘግብ የሚያዘውን ብቻ በትክክል ሊጽፍ የሚችለው? ይህን ከመሳሰሉ ጥያቄዎች የተነሣ፥ ሰብአዊው ጸሐፊው ምን ያህል በመለኮት ቁጥጥር ሥር ነበር? በሚለው ጥያቄ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። እነዚህ አስተያየቶች “እስትንፋሰ-እግዚአብሔርን አስመልክቶ የቀረቡ ንድፈ-አሳቦች” ተብለዋል። ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ፈቺዎች ሁሉ ከነዚህ ንድፈ-አሳቦች አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሆኑትን ንድፈ-አሳቦች ይከተላሉ። ተቀባይነት ያለው ንድፈ-አሳብ ለመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አፈታት ሁሉ መሠረት የሆነው ነው። ስለሆነም ስለ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ትክክለኛ የሆነውን ንድፈ-አሳብ በጥንቃቄ መለየት ይገባል።  ሀ. የእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ንድፈ-አሳቦች  1. “ቃል” እና “ምሉእ” እስትንፋሰ-እግዚአብሔር። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ትክክለኛው እስትንፋሰ-እግዚአብሔር የቃልና ምሉእ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ተብሎ ይገለጣል። “የቃል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” ትርጉሙ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በተጻፉበት ጊዜ ጸሐፊዎቹን በቃላት አመራረጥ ሳይቀር እግዚአብሔር መርቷቸዋል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰውን ጸሐፊነትም ያመለክታል። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጸሐፊዎቹን የግል ባሕርይ ሰአጻጻፍ ስልታቸውና በቃላት አመራረጣቸው የሚገልጡ ሲሆን፥ ማንነታቸውም ብዙውን ጊዜ በአስተሳሰባቸው፥ በአመለካከታቸውና በጸሎታቸው ወይም በፍርሃታቸው ይታወቃል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰብኣዊነት ቢኖርም፥ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር፣ የተመዘገቡት ቃላት ሁሉ ከእግዚአብሔር እንዲሆን ያደርጋል። ይህ “ምሉእ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ ትርጉሙም (“ምሉእ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” ማለት ነው። ይህ አሳብ፥ ለመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ግማሽ ነው የሚለውን አመለካከት ይቃወማል።  ትክክለኛውና መሠረታዊው የእምነት ትምህርት ምን እንደሆነ ግልጥ ለማድረግ ብዙ ጊዜ ተጨማሪ ገላጭ ቃላት ታክለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት የለሽና ትክክል መሆኑን ለመግለጥ፥ የማይሳሳት፥ የእውነት ቃል መሆኑን ለመግለጥ ደግሞ፥ ስሕተት ኣልባ ተብሏል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ኣንዳንድ ጊዜ እውነት ያልሆኑ ገለጣዎችን፥ ከዚያም አልፎ ዘፍጥረት 3፡4 ላይ እንደተመለከተው፥ የሰይጣንን የሐሰት ትምህርት ቢያቀርብም፥ እነዚህ ሁሉ ሰዎችን ወይም ሰይጣንን የሚያመለክቱ እንደሆኑ በግልጥ ተጠቅሷል። እግዚአብሔርም የእነዚህን ገለጣዎች እውነትነት አላረጋገጠም። መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ነው ብሎ መግለጥ፥ እንዲሁም እውነትን በመግለጥ ረገድ ስሕተት አልባና ሐቅ ነው ማለት፥ መጽሐፉ እንደ መለኮታዊ ቃልነቱ ተዓማኒ ይሆን ዘንድ ለእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ልዕለ-ተፈጥሮና ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ምሪት አለው ማለት ነው።  እስትንፋሰ-እግዚአብሔር በእርግጥ የሚመለከተው የመጀመሪያዎቹን ወይም ዋነኞቹን ጽሑፎች እንጂ፥ ቅጂዎችንና ትርጉሞችን አይደለም። የመጀመሪያው ዋና ጽሑፍ በአሁኑ ጊዜ የሌለ ከመሆኑ የተነሣ፥ ምሁራን አሁን ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ለማረጋገጥና ለመወሰን ብዙ ጥረዋል። እውነትን ለመማማር ላለን ዓላማ ግን፥ አሁን በእጃችን የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች፥ የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ትክክለኛ ብዢዎች መሆናቸውን ለመገመት ይቻላል። በይዘት ሳይሆን፥ በአገባብ ጥቃቅን፥ ልዩነቶች ቢኖሩም፥ የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮን እምብዛም የሚያዛንፉ አይደሉም። የተገኙት ተጨማሪ ጽሑፎችም ከላይ ከተጠቀሰው የግንዛቤ መደምደሚያ ጋር ይስማማሉ።  ለተግባራዊ ዓላማዎች ሲባል፥ በዕብራይስጥ የተጻፈው ብሉይ ኪዳንና በግሪክኛ የተጻፈው አዲስ ኪዳን በአንድነት፥ የእግዚአብሔር የራሱ ቃል መሆናቸውንና እርሱ ለሰው ሊያስተላልፍ የፈለጋቸው እውነቶች መሆናቸውን አምኖ ለመቀበል ይቻላል።  2. ሜካኒካዊ ወይም የቃል በቃል ንድፈ-አሳብ። ቀደም ሲል እንደተመለከተው፤ እውነተኛው እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ቃሉ በሚጻፍበት ጊዜ፥ በእግዚአብሔር አመራር ውስጥ የጸሐፊዎችን የመጻፍ ሰብእናና ነጻነት ይፈቅዳል የሚለው እውነተኛ አስተምህሮ ተገልጧል። የዚህ ተቃራኒ አመለካከት ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በሚጻፉበት ጊዜ፥ ሰዎች የራሳቸውን የአጻጻፍ ዘዴ ምንም ሳይጠቀሙ እግዚአብሔር እንደ ጽሕፈት መኪና ተጠቅሞባቸዋል ይላል። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን ቃል በቃል አጽፎት ሲሆን ኖሮ፥ የአጻጻፉ ስልትና ቃላቱ በአጠቃላይ አንድ ዓይነት በሆኑ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የግል ፍርሃታቸውን፥ ስሜታቸውን፥ የእግዚአብሔርን ማዳን እና ጸሎታቸውን በብዙ ሁኔታዎች ገልጠዋል። በመሆኑም በተዘዋዋሪ መንገዶች የራሳቸውን ማንነት በዚሁ መለኮታዊ ጽሑፍ ውስጥ አስገብተዋል። ለምሳሌ ሮሜ 9፡1-3 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለእስራኤል ያደረገው ጸሎት ቃል በቃል ከእግዚአብሔር የተሰጠ ቢሆን ኖሮ ትክክለኛ ትርጉሙን ያጣ ነበር።  በመሆኑም እስትንፋሰ-እግዚአብሔር እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የሚመለከት ቢሆንም፥ ማንነትን፥ የአጻጻፍ ስልትን ወይም የግል ፍላጎትን አያስቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ በአጻጻፍ ረገድ መለኮታዊውን ሥልጣን እንደሚቀበል ሁሉ፥ የጸሐፊውን ነጻነትም ያረጋግጣል። እግዚአብሔር ሰብአዊ ጸሐፊዎችን በመጠቀም ትክክለኛነትን አከናውኗል፤ ይህን ሲያደርግ ግን የቃል በቃል አጻጻፍን ተከትሎ አይደለም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር በቀጥታ እየተናገረ የተጻፉ መሆናቸው ተዘግቧል። አብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግን፥ ቀጥታ ቃል በቃል ለመጻፋቸው ምንም ማስረጃ ስለሌለ በሰብአዊ ጸሐፊዎች ነው የተመዘገቡት ለማለት ይቻላል።  3. ፅንሰ-ሐሳባዊ ንድፈ-አሳብ። አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም እስትንፋሰ እግዚአብሔርነት በማቃለል፥ እግዚአብሔር እስትንፋሱን የሰጠው በትክክለኛዎቹ ቃላት ሳይሆን፥ ፅንሰ-አሳብን ብቻ ነው በማለት የመጽሐፉን ደራሲነት ለሰብአዊ ጸሐፊዎቹ ለመስጠት ሞክረዋል። ይህ አመለካከት ችግሮች አሉት። ምክንያቱም ሰዎች በሚጽፉበት ጊዜ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን የተረዱት በከፊል ብቻ ቢሆንና ያን በራሳቸው ቃላት ቢያሰፍሩት ኑሮ በቀላሉ የማይገመት ችግር ያስከትሉ ነበር።  ለጸሐፊዎች የተሰጧቸው ንድፈ-አሳቦች ብቻ ናቸው የሚለውን አስተያየት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይቃወማል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በእግዚአብሔር መሪነት የተጻፈ መሆኑ ተደጋግሞ በአጽንኦት የተገለጠ እውነት ነው። የቃላት ጠቃሚነት በተደጋጋሚ ተጠቅሷል (ዘጸ. 20፡1፤ ዮሐ. 6፡63፤ 17፡8፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡13)። ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስ ቃላቱ ከእግዚአብሔር መሆናቸው በተደጋጋሚ ተረጋግጧል (ዮሐ. 10፡17፤ ገላ. 3፡16)። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ኤፌሶን 6፡17፤ ያዕቆብ 1፡21-23፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡2 ውስጥ በተደጋጋሚ ተመልክቷል። ከእግዚኣብሔር ቃል ላይ በሚቀንስ በማንኛውም ሰው ላይም ከባድ እርግማን ተላልፎበታል (ራእይ 22፡18-19)። ስለዚህም ይህ ንድፈ-አሳባዊ ትንታኔ፥ ቅዱሳት መጻሕፍት ራሳቸው በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፉ ስለመሆናቸው የሚያውጁትን እውነት በተመለከተ ከትክክለኛነት የራቀ ነው።  4. ከፊል እስትንፋሰ-እግዚኣብሔር። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰኑ ክፍሎች ብቻ ናቸው በእግዚአብሔር መሪነት የተጻፉ የሚሉ የተለያዩ ንድፈ-ሐሳቦች ተከሥተው ነበር። ለምሳሌ አንዳንዶች፥ ስለ መለኮታዊ እውነት መገለጥ የሚናገሩት የቃሉ ክፍሎች ትክክለኛ ቢሆኑም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ታሪካዊ፥ መልከዓ-ምድራዊ ወይም ሳይንሳዊ አባባሎችን በዚህ መልኩ ኣንቀበላቸውም ብለዋል። ከዚህ ጋር ተጓዳኝ የሆነው አመለካከት ደግሞ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ክፍሎች ይበልጥ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸው ስለሆኑ፥ የእውነትና የስሕተታቸው ሁኔታ የደረጃ ጉዳይ ነው የሚለው ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በሚጻፍበት ወቅት እግዚአብሔር ጻሐፊዎቹን በተለያዩ ደረጃዎች የረዳቸው ቢሆንም፥ ያለ ስሕተት ለመጻፍ የሚያስችላቸውን ክህሎት ግን አልሰጣቸውም የሚል ነው። በመሆኑም ከፊል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር በሁሉም አቀራረቡ የቃሉን የመጨረሻ ዳኝነት ለእያንዳንዱ አንባቢ ይተዋል። በመሆኑም በዚህ አካሄድ የቃሉ ሥልጣን፥ የአንባቢው ግለሰብ ሥልጣን ይሆንና፥ ሁለት አንባቢዎች በትክክል እውነት የሆነውና ያልሆነው የቱ ነው በሚለው እሳብ የማይስማሙበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።  5. አዲሱ ኦርቶዶክሲ (Neo-Orthodoxy) አስተሳሰብ ስለ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለው አመለካከት። በሀያኛው ምዕተ ዓመት ካርል ሳርት በሚባል ሰው አማካይነት አዲስ መለኮታዊ መገለጥ ማለት “እዲሱ ኦርቶዶክሲ” የተሰኘ አመለካከት ተከሠተ። ይህ አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ፦ እስትንፋሰ- እግዚአብሔር Read More »

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል

This entry is part 1 of 52 in the series ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች

የተለየ ትኩረት ሳይሰጥ የሚያነብ አንባቢ እንኳን መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነብበት ጊዜ መጽሐፉ ፍጹም ልዩ መሆኑን ይገነዘባል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ የሚያጠቃልል ሲሆን ፥ ከአርባ በሚበልጡ በተለያዩ ዘመናትና፥ የኑሮ ሁኔታዎች ውስጥ ባለፉ ጸሐፊዎች የተጻፈ ነው። ይሁን እንጂ የማይገናኙ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ስብስብ ሳይሆን፥ አስደናቂ ተከታታይነትና ወጥነት ያለው፥ መጽሐፍ ነው። በአማርኛችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ድንቅ መጽሐፍ፥ በግሪክኛ “ቢብሉስ” በሚል ስያሜ ይታወቃል። እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች “ዘ ባይብል” የሚል ስያሜ የሰጡትም ከዚህ ቃል የተነሣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች የተጻፈ ቢሆንም በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ይህ ነው ልዩ ባሕርዩ።  መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚደግፉ ሁለት ማረጋገጫዎች አሉ። 1. አንዱ ውስጣዊው ማረጋገጫው ነው። ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመለከቱት እውነታዎች እና መጽሐፉ ራሱ ስለመለኮታዊነቱ የሚገልጠው ሲሆን፤ 2. ውጫዊው ማረጋገጫ ደግሞ፥ ልዕለ-ተፈጥሮ የሆነ ባሕርይውን የሚደግፉትና ውስጡ የተጠቀሱት እውነቶች ናቸው።  ሀ. ውስጣዊ ማረጋገጫ  መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በመቶ በሚቆጠሩ የንባብ ክፍሎቹ ራሱ ገልጧል (ዘዳ. 6፡6-9፥ 17-18፤ ኢያሱ 1፡8፤ 8፡32-35፤ 2ኛ ሳሙ. 22፡31፤ መዝ. 1፡2፤ 12፡6፤ 19፡7-11፤ 93፤5፤ 119፡9፥ 11፥ 18፥ 89-93፥ 97-100፥ 104-105፥ 130፤ ምሳሌ 30፡5-6፤ ኢሳ. 55፡10-11፤ ኤር. 15፡ 16፤ 23፡29፤ ዳን. 10፡21፤ ማቴ. 5፡17-19፤ 22፡29፤ ማር. 13፡31፤ ሉቃስ 16፡17፤ ዮሐ. 2፡22፤ 5፡24፤ 10፡35፤ ሐዋ. 17፡ 11፤ ሮሜ 10፡17፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡13፤ ቆላ. 3፡ 16፤ 1ኛ ተሰ. 2፡13፤ 2ኛ ጢሞ. 2፡15፤ 3፡15-17፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡23-25፤ 2ኛ ጴጥ. 3፡15-16፤ ራእይ 1፡2፤ 22፡18)። ለማንም ግልጥ በሚሆን ሁኔታና በብዙ መንገዶች፥ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ገልጠዋል። የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ክርስቶስም ጭምር፥ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ገላጭነት የተጻፈ ቃል ነው ይላሉ። ለምሳሌ መዝሙር 19፡7-11 ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ተገልጦ፥ ፍጹምነትንና በአንጻሩ በቃሉ አማካይነት የተለወጡ ስድስት ሰብአዊ ባሕርዮች ተመልክተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስም ሕግ መፈጸም እንደነበረበት ገልጧል (ማቴ. 5፡17-18)። ዕብራውያን 1፡ 1-2 ውስጥም እግዚኣብሔር በብሉይ ኪዳን ለነቢያቱ፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ለልጁ የተናገረ መሆኑ ተረጋግጧል። ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን የእግዚአብሔር ቃልነት የማይቀበል የሚሆነው፥ መጽሐፉ የእግዚአብሔር ቃል ስለመሆኑ ራሱ የሚሰጠውን የተደጋገሙ መረጃዎች የማይቀበል ሲሆን ብቻ ነው።  ለ. ውጫዊ ማረጋገጫ  መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በራሱ የሚያስረግጥ ብቻ ሳይሆን፥ ተጠራጣሪዎችን እንኳን ለማሳመን በሚችሉ ብዙ መረጃዎች የተሞላ ነው።  1. የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታታይነት ወይም ወጥነት። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጡት እጅግ አስገራሚ እውነቶች አንዱ፥ ወደ 1600 ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ በኖሩና ከአርባ በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ሰዎች የተጻፈ መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፉ የስድሳ ስድስት መጻሕፍት ስብስብ ሳይሆን፥ አንድና ወጥ ነው። ጸሐፊዎቹ ከተለያየ ማኅበራዊ መሠረት የመጡ ናቸው፤ ነገሥታት፥ ጭሰኞች፥ ፈላስፋዎች፥ ዓሣ አጥማጆች፥ ሐኪሞች፥ የመንግሥት ባለሥልጣናት፥ ምሁራን፥ ባለቅኔዎች እና ገበሬዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በተላያዩ ባሕሎችና ልምዶች መኖር ብቻ ሳይሆን፥ የተላያዩ ባሕርያትም ነበሯቸው። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በግልጥ የሚታይ ተከታታይነትና ወጥነት አለው።  የመጽሐፉ ተከታታይነት ከአሁኑ ዓለም አፈጣጠር እስከ አዲሱ ሰማይና ምድር መፈጠር ድረስ ባለው ታሪካዊ ቅደም ተከተል ሥርዓት ሊታይ ይችላል። ብሉይ ኪዳን ስለ እግዚኣብሔር ባሕርይ፥ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ድነት፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ስለ መላው ዓላም፥ ስለ እስራኤልና ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ዓላማና ዕቅድ ይገልጣል። መለኮታዊ ትምህርት ከዝቅተኛው፥ ማለት ቀለል ካለ መግቢያ ተነሥቶ እስከተወሳሰበ ትምህርትነት ደረጃ በደረጃ ይቀርባል። መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ አገላለጦችን በቀጥተኛ ትርጉማቸው፥ ትንቢቶችን ደግሞ በተወሰነ ጊዜ ክንውናቸው ያሳያል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ፥ በሰማይና በምድር እጅግ ስለከበረውና ፍጹም ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድሚያ መተንበይ፥ የትንቢቱን እውንነት ማመልከትና ኢየሱስን ከፍ ማድረግ ነው። ይህ አስደናቂ መጽሐፍ በሰዎች ተጻፈ ብሉ ከማመን ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ገላጭነት ተጻፈ የሚለውን መቀበሉ ይቀልላል። ስለሆነም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ሁሉ፥ የተለያዩት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች በተለያዩ ሰዎች የተጻፉ መሆናቸውን በመቀበል፥ የመልእክቶቹን አንድ ወጥነት በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና አነሳሽነት ይረዳሉ።  2. የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ ጥልቅነት። እውነትን በመግለጥ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ተመርምሮ አያልቅም። ቴሌስኮፕ የሰማይን ከፍታ እንደሚያሳይ፥ መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔርን የእጅ ሥራዎች ከመነሻ እስከ ፍጻሜ፥ ከሰማያት ከፍታ፥ እስከ ሲኦል ጥልቀት ያመለክታል። ማይክሮስኮፕ ረቂቅ ነገሮችን እንደሚያሳይ ሁሉ፥ ረቂቁ የእግዚአብሔር ሥራ፥ ዕቅድና ዓላማው እንዲሁም የፍጥረቱ ፍጹምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት ብዙ መጻሕፍት የተጻፉት፥ ጸሐፊዎቹ ስለዘመናዊው ግኝት ግምት ባልነበራቸው ጊዜና በጥንታዊው የሰው ልጅ እውቀት ደረጃ ቢሆንም፥ በቅርቡ የተገኙት የሥነ-ምድር ምርምር ጥናቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች ከመቃረን ይልቅ ይደግፋሉ። ጥንታዊዎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚያስደንቅ አኳኋን ከዘመናዊው የሥነ-ምድር ምርምር ግኝቶች ጋር ይስማማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ዘላለማዊነት ያላቸውንና በእግዚአብሔር ብቻ የሚታወቁትን እውነቶች ስለሚገልጥ፥ ከሰው ምርምርና ግኝት በላይ የሆኑ እውነቶችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በሙላትና በረቂቅነት የሚያሳየንን ያህል የሚያሳይ ሌላ መጽሐፍ በዓለም የለም።  3. የመጽሐፍ ቅዱስ የመለወጥ ኃይልና ኅትመቱ። በዓለማችን የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ለተለያዩ ሕዝቦችና ባሕሎች በተለያዩ ኣያሌ ቋንቋዎች የታተመ ሌላ መጽሐፍ የለም። የማተሚያ መኪና እንደተፈለሰፈም ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዓለም ታላላቅ ቋንቋዎች ሁሉ በብዙ ሚሊዮን ቅጂዎች ታትሟል። ጽሑፍ ያለው እያንዳንዱ ቋንቋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቢያንስ ጥቂት ክፍሎች የታተመ ነገር አለው። ምንም እንኳን እንደ ፈረንሳዊው ቮልቴር ያሉ ሃይማኖት የለሾች መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በኋላ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል ቢሉም፥ የሀያኛው ክፍለ-ዘመን ደራሲያንም መጽሐፉ ይረሳል ወይም ፈላጊ አይኖረውም ቢሉም፥ ካለፈው ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች በመታተም ላይ ነው። በተከታዮች ብዛት ከክርስትና የሚበልጡ ሌሎች ሃይማኖቶች፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሊወዳደር የሚችልና መገለጥ ያለው ጽሑፍ ሊያቀርቡ አልቻሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን የመለወጥ ኃይል በዘመናችንም ቀጥሏል። ላልዳነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ “የመንፈስ ሰይፍ” ነው (ኤፌ. 6፡17)፤ ለዳነው የሚያነጻ፥ የቅድስናና ድል አድራጊነት ኃይል ነው (ዮሐ. 17፡17፤ 2ኛ ቆሮ. 3፡ 17፥ 18፤ ኤፌ. 5፡25-26)። መጽሐፍ ቅዱስ የሕግና የሥነ-ምግባር ብቸኛው መለኮታዊ መሠረት እንደሆነ ይኖራል።  4. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት። የመጽሐፍ ቅዱስ ከሰው እውቀት በላይ የሆነ ባሕርይ የሚታየው፥ ሊታወቅ የማይቻልን እውነት ግልጥና እንዲታወቅ አድርጎ ማቅረቡ ነው። ዘላለምን ማለት ሰው ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ተፈጥሮ ሳይቀር ይገልጣል። የእግዚኣብሔር ባሕርይና ሥራዎቹም ተገልጠውበታል፡፡ እግዚኣብሔር ለዓለም፥ ለእስራኤልና ቤተ ክርስቲያን ያለው አሳብና ዘላለማዊ ዕቅዱ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ውስጥ ተጠቃሏል። በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ገለጣ የመጨረሻ፥ ትክክልና ጊዜ የማይገድበው ነው። ሁለንተናዊ ባሕርይው ኣንባቢዎቹን ከጊዜና ከዘላለም ጋር በተዛመደ ነገር ብልሆች አድርጓቸዋል።  5. መጽሐፍ ቅዱስ ስነ-ጽሑፍነቱ። በሥነ-ጽሑፍነቱ ሲታይ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ምጡቅ ነው። ታሪካዊ ዘገባዎችን ብቻ ሳይሆን፥ ዝርዝር ትንቢቶችን፥ ውብ የሆኑ ቅኔዎችን፥ ልዩ ውበት ያለው ተውኔትን፥ የፍቅርና የጦርነት ታሪኮችን፥ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ላይ የሚነሡ ፍልስፍናዎችን ያጠቃልላል። የጸሐፊዎቹ መለያየት ከያዛቸው ጉዳዮች ስብጥር ብዛት ጋር ይስማማል። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናት የኖሩትንና በሁሉም የእውቀት ደረጃ ላይ የነበሩትን ሰዎች የማረከ ጽሑፍ የለም።  6. የማያዳላው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ለሰዎች እንዲያደላ አላደረገውም። ያለማመንታት የማንንም ኃጢአት እና ደካማነት ይገልጣል። ይህ ብቻ አይደለም፥ በራሳቸው በጎ ምግባር የሚታመኑ ፍጻሜያቸው ጥፋት መሆኑንም ያስገነዝባል። በሰዎች ብዕር ቢጻፍም፥ ከሰው ወደ ሰው ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ወደ ሰው የተላለፈ መልእክት ነው። ስለ ምድራዊ ነገሮችና ስለ ሰዎች ልምምድ ቢገልጥም፥ የሰማይና የምድርን፥ የሚታዩና የማይታዩ ነገሮችን፥ ስለ እግዚአብሔር የሚገልጡ እውነቶችን፥ ስለ መላእክት፥ ስለ ሰው፥ ስለ ጊዜና ዘላለም፥ ስለ ሞትና ሕይወት፥ ስለ ኃጢአትና ድነት፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትና ሲኦልም በግልጥነትና በሥልጣን ያብራራል። እንዲህ ያላን መጽሐፍ ሰው መጻፍ ቢፈልግ እንኳን፥ ያለመለኮታዊ ምሪት ሊጽፈው አይችልም ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ፥

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል Read More »