ምዕራፍ 10- መንፈሳዊ ውጊያ

ይህንን ማወቅ ለምን ያስፈልጋል?

‹‹የባሕሩን ነፋሻማ አየር እያጣጣምን በዚህ መርከብ ላይ የምናሳልፈው መልካም የሽርሽር ጊዜ ጊዜ ይታየኛል፣›› አለ ማርቲን ለሚስቱ አብረው የሚያሳልፍቱን ጊዜ በአይነ ህሊናው እየሳለ፡፡

‹‹እውነት ብለሃል፣›› ስትል ሚስቱ ማውዴ መለሰች፡፡ እኔ ደግሞ የናፈቀኝ ያ ምቾት በተላበሰው የመርከቡ ላይ ድግስ መገኘት ነው! መቼም የመርከቡ ካፒቴን በአንዱ የምግብ ሥነ ስርአት ላይ ከእርሱ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ላይ እንድንመገብ ይጋብዘናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡››

‹‹በእርግጥ ይጋብዘናል እንጂ፣›› ሲል ማርቲን ለባለቤቱ መለሰላት፡፡ ‹‹ከእራት በኋላ ደግሞ በምሽቱ ጨረቃ ማራኪ የዳንስ ጊዜ ማሳለፍ፣ አይደል?››

‹‹ማርቲን፣ አንተ የፍቅር ሰው! ምን አይነት ወርቃማ ጊዜ እንደምናሳልፍ ይታየኛል፣›› አለች በረጅሙ ተንፍሳ፡፡

ከተወሰኑ ቀናት በኃላ የመርከቡን ካፒቴን በዋናው የመርከቡ አዳራሽ ውስጥ አገኙት፡፡ ማርቲን ካፒቴኑን ሰላም ካለው በኋላ ‹‹ካፒቴን፣ ላነጋግርህ እችላለሁ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ‹‹እንዴታ፣ ስለምን ጉዳይ ነው? ረጅም ጊዜ የማይፈጅ መሆን አለበት፡፡ እንደምታውቁት ሥራ የሚበዛብኝ ሰው ነኝ፡፡››

‹‹እንዳውም ልናነጋግርህ የፈለግንህ ለዚሁ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መርከብ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች በሙሉ ሥራ የበዛባቸው ይመስላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፍላጎቶቻችን ለማሟላት እስካይችሉ ድረስ በስራ የተጠመዱ ይሆናሉ፡፡ እኛ በማናውቀው አንድ ሌላ ጉዳይ የተጠመዱ ናቸው፡፡ እንዳውም አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ፊት አያሳዩንም!››

ካፒቴኑ በመገረም ከተመለከተው በኋላ፣ ‹‹ምን እያልክ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም —›› ማውዴ በተራዋ፣ ‹‹ካፒቴን፣ በዚህ መርከብ ላይ ለመውጣት ስንፈርም ከዚህ የተሻለ ምቾት፣ ከዚህ የተሻለ እንክብካቤ ጠብቀን ነበር፡፡ ምቾት የተላበሰው ድግስ ቀርቶ እየተመገብን ያለነው ወጥ ቤቶህ የሚያቀርቡልንን ተራ ምግብ ነው! በመርከቡ ላይ ያቀረብክልን ምቹና ለስላሳ ወንበሮች ሳይሆኑ በአሸዋ የተሞሉ ጆንያዎች ናቸው! ፈፅሞ የገመትነው ነገር አይደለም!››

በርቲን ደግሞ በተራው፣ ‹‹በመርከቡ ላይ የጠበቅነው መዝናኛ የለም። ይህ አልበቃ ብሎ ሰዎችህ መሳሪያዎች እየፈታን እንድንገጥም ሲያደርጉን ነበር፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ጊዜያት ምንም አይልም ነበር፡፡ ከ 20 ቀናት በኋላ ግን ደጋግሞ ያንኑ ነገር ማድረግ አሰልቺ ነገር ሆኖብናል።›››

ማዉዴ ብሶቷን ማሰማቷን ቀጥላለች፣ ‹‹ስለጉዞአችን ከእኛ አወንታዊ ሪፖርት የምትጠብቅ ከሆነ ቢያንስ በአከባቢያችን አንድ ፍንዳታ በተሰማ ቁጥር ተከትለው የሚሰሙትን እነዚያን የማስጠንቀቂያ ደውሎችና ፉሽካዎች ዝም ማሰኘት ይኖብሃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰዎችህ ቀንና ለሊት ሳይለዩ ያለማቋረጥ የሚተኩሷቸውን መድፎች ዝም ልታሰኝልን ብትችል እንደትልቅ እርዳታ እንቆጥረዋለን።››

‹‹እነዚያ የካሚካዝ የጦር አውሮፕላኖችስ?›› አለ ማሪቲን በመሃል ጥልቅ ብሎ፡፡ ‹‹ስልችት ብለውኛል፡፡ እነዚያ ጤና የጎደላቸው አብራሪዎች ሰው ሊጎዱ ይችላሉ እኮ!››

በመጨረሻ፣ ካፒቴኑ ችግሩ ምን እንደሆነ ተረዳ፡፡ ‹‹እናንተ ሰዎች፣ እንዴት ወደዚህ መርከብ ላይ ልትወጡ እንደቻላችሁ ወይም ይህ መርከብ ተራ የመጓጓዣ መርከብ እንደሆነ ልታስቡ እንዴት እንደቻላችሁ አላውቅም፡፡ ይህ መርከብ የጦር መርከብ ነው፣ እኛም በጦነት ውስጥ ነን!››

በርካታ ክርስቲያኖች ልክ እንደ እነዚህ ሰዎች ስላሉበት ቦታ የተሳሳተ መረዳት አላቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የተትረፈረፈ ሕይወት ሊሰጥህ እንደመጣ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ አማኝ ሊዘነጋው የማይገባው ሌላ ነገር ቢኖር አሁን የሚኖረው ጦርነት በታወጀበት ቀጠና ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ ያ የተትረፈረፈ ሕይወት በዚህ የጦርነት አውድ ውስጥ መታየት ይኖርበታል፡፡ የገባንበት ጦርነት ስለ መሬት ወይም ስለ ፖለቲካ ሳይሆን ዘላለማዊ ስለሆነችው የሰው ነፍስ ነው፡፡ ሃሳብህ፣ አነሳሽ ምክንያቶችህ፣ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ነገሮች፣ ንብረትህ፣ ታማኝነትህ እና ሰውነትህ የጦነቱ ሜዳዎች ናቸው፡፡

ራሳችንን ከጠላታችን እንዴት መከላከል እንዳለብን የምናውቅ ከሆነ በደህንነት መኖር እንችላለን፡፡ እንዴት ማጥቃት እንዳለብን የምናውቅ ከሆነ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግስት እናሰፋለን፣ የጠላትንም ተፅእና እንገፋለን፡፡

ጸሎት፡- ‹‹አባት ሆይ የእኔ ፍላጎት በሁሉም ነገር አንተን ማክበር ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ምኞቴን የሚጋፋ ጠላት አለኝ፡፡ አላማው እኔን ማጥፋት ነው፡፡ የአንተ ሃይል ከእርሱ ሃይል በማይቆጠር መጠን እንደሚበልጥ አውቃለሁ! የጨለማውን መንግስት እንድዋጋና ራሴን እንድመክት እንዴት ጦርነት ማድረግ እንደምችል አስተምረኝ፡፡ አሜን፡፡››

“በግዑዙ አለም ላይ ባሉ ሁኔታዎች እየተገለጠ ስላለው መንፈሳዊ ጦርነት ያለን ግንዛቤ ደካማ መሆኑን እኔ በበኩሌ ልቀበል እፈልጋለሁ፡፡ በግልጹ እየታየ ያለው ነገር፣ ክፉ መንፈሳዊያን ሠራዊቶች የክርስቶስን መንግስት ለማጥፋት የሚያደርጉት ጦርነት መሆኑን ልናውቅ ይገባል” – ጀምስ ስቴዎርት፣ ስኮትላንዳዊ የሥነ መለኮት ምሁር።

ጠላታችን ምን ይመስላል?

በ2ቆሮንቶ 2፡11 ሰይጣን፣ ‹‹—በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱ ሃሳብ አንስተውምና፡፡›› ሲል ጳውሎስ ስለ ሰይጣን ይናገራል፡፡ ጳውሎስ የሰይጣንን ሃሳብ እንዳይስት አነበብን፣ ነገር ግን የበሰሉ ክርስቲያኖች ጨምሮ በርካታዎቻችን ይህንን እውነት ሳንገነዘብ እንኖራለን፡፡ የዚህ ጥናት አላማ ጠላትህን እንድትገነዘብ ማድረግና በሴራው ላይ እንድትነቃ መርዳት ነው፡፡

የሰይጣን አጀማመር

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሕዝቅኤል 28፡12-19 አንብብ፡፡ ሰይጣን በፍጥረቱ መጀመሪያ ላይ ምን ይመስል ነበር? [ቁጥር 12-15፣17 ተመልከት፡፡] ቁጥር 15 ‹‹—በደል እስኪገኝብህ ድረስ—›› ይላል፡፡ ከዛ በኃላ ምን ይመስላል? [ቁጥር 16-18 ተመልከት፡፡]

ስለ ሰይጣን ኃጢአትና አመፅ የበለጠ ለመረዳት በብሉይ ኪዳን የሚገኘውን የኢሳይያስ መጽሐፍ 14፡12-17 ተመልከት፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር በሌላ ነቢይ (ኢሳይያስ) አማካኝነት ለሌላ ንጉስ (ለባቢሎን ንጉስ) ተመሳሳይ ጭብጥ ያለው ሃሳብ ያስተላልፋል፡-

 1. ቁጥር 12 በትዕቢቱ ምክንያት ሰይጣን ላይ የደረሰውን ፍርድ ያመለክታል፡፡ አንድ ወቀት ሰይጣን ‹‹አጥቢያ ኮከብ፣›› እና ‹‹የንጋት ልጅ፣›› ነበር፡፡ ቅጣቱ ምንድን ነበር?
 2. ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ትዕይንት የአይን ምስክር ነበር፡፡ ሉቃስ 10፡18 አንብብና ኢየሱስ ምን እንደተመለከተ ግለጽ፡፡
 3. ተመሳሳይ ትዕይንት በራዕይ 12፡9 ላይ ተገልጿል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ‹‹ታላቁ ዘንዶ›› ወደ ምድር እንደተጣለ እናነባለን፡፡ ከእርሱ ጋር ማን አብሮ ተጣለ?
 4. በኤፌሶን 6፡12 መሠረት ልንጋደለው የሚገባ እውነተኛ ጠላታችን ማን ነው?

ተጨማሪ ምልከታ፡- እግዚአብሔር ሰይጣንና ሌሎች መላዕክቶችን ሁሉ ህጸጽ አልባ አድርጎ ፈጥሯቸው ነበር፡፡ ክፋትን እግዚአብሔር አልፈጠረም፡፡ ሰይጣን የገዛ ነፃ ፈቃዱን በመጠቀም በአመጸ ጊዜ ክክብሩ ተጣለ። ሰዎችንም አሳተ። እግዚአብሔር ግን ገና ከመነሻው ይህን የሰይጣንን አሻጥር በጸጋ፣ በምህረት፣ በእምነት እና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስን መስዋዕትነት በመጠቀም እንዴት አድርጎ እንደሚገለብጥ አስቀድሞ አቅዶ ነበር፡፡››

ተጨማሪ ምልከታ፡- ሰይጣን፣ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑ መላዕክትን ከእርሱ አመፅ ጋር እንዲተባበሩ ለማድረግ ቢችልም የቀሩት ሁለት ሦስተኛ መላዕክት ግን ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆናቸውን ራዕይ 12፡4 ያስነብበናል፡ ያመጹት ጋኔን ሲባሉ የተቀሩት ግን መላዕክት ሆነው ቀሩ፡፡

የሰይጣን አላማዎችና ስልቶች

ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች ከተመለከትክ በኋላ የሰይጣንን አላማዎች ግለጽ፡፡

 1. ማቴዎስ 4፡1
 2. ማቴዎስ 4፡8-10
 3. ሉቃስ 8፡12
 4. ሉቃስ 13፡16
 5. ዮሐንስ 8፡44
 6. 2ቆሮንቶስ 11፡14-15
 7. 1ጴጥሮስ 5፡8
 8. ራዕይ 12፡9

ተጨማሪ ምልከታ፡- ሰይጣን እግዚአብሔር እንደሚገኝ፣ ‹‹በአንዴ በሁሉ ቦታ›› መገኘት አይችልም፡፡ ውሱን የሆነ ፍጥረት ቢሆንም እርስ በእርሳቸው ስኬታማ በሆነ መንገድ በመረጃ መረብ የተቆራኙ ናቸው፡፡ እንደአማኝ ከሰይጣን የበታቾች ጋር እንጂ ምናልባት በቀጥታ ከራሱ ከሰይጣን ጋር ላትገናኝ ትችላለህ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጥናት ውስጥ ቀለል ባለ መንገድ›› ለመጻፍ ይቻል ዘንድ ‹‹ከሰይጣናዊ መንግስቱ›› ጋር የሚኖርህን ግንኙነት ከራሱ ከሰይጣን ጋር እንደምታደርግ አድርገን እናቀርባለን፡፡

የሰይጣን ቀዳሚ ዘዴ – ደጆች እና እድል ፈንታዎች

ሰይጣን እንዴት ሰዎችን ለማጥፋት እንደሚያቅድ ለማወቅ ወደ ዘፍጥረት ተመልሰን መመልከት ይኖርብናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስህን ዘፍጥረት 4፡1-12 ላይ ከፍተህ አንብብ፡፡ ይህ ክፍል የአዳምና ሔዋን የመጀመሪያ ሁለት ልጆችን ማለትም የቃየን እና አቤል ታሪክን ያስነብበናል፡፡ ክፍሉ ከዚህ በተጨማሪ የአላማችንን የመጀመሪያ የግድያ ወንጀልም ያስነብበናል – ይህ በዋናው ገዳይ (ሰይጣን) የተቀነባበረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቃየን እና አቤል ለእግዚአብሔር መስዋዕት ቢያቀርቡም በሆነ ምክንያት የቃየን መስዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ለምን እንደሆነ ባናውቅም ምናልባት መስዋዕቱን የሚያቀርብበት የልብ ዝንባሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ቃየን በነገሩ በጣም ተበሳጨ፡፡ እግዚአብሔርም የቃየንን ልብ በመመልከት ጠቃሚ ምክር መከረው፡፡ ቃየን ግን ምክሩን ሊቀበል አልወደደም፡፡

 1. በቁጥር 7 ላይ መልካም የሆነውን ነገር ካላደረገ ኃጢአት በደጁ እንደምታደባ እግዚአብሔር ለቃየን ነገረው፡፡ ይህ ‹‹ደጅ›› ምን የሚያመለክት ይመስልሃል?
 2. ለምንድን ነው ኃጢአት በደጅ የሚያደባው? ምን ለማድረግ?
 3. እግዚአብሔር፣ ቃየን ምን እንዲያደርግ መከረው?

በ ኤፌሶን 4፡25-27 መሰረት፣ ቁጣ በራሱ ኃጢአት እንዳልሆነ እና በምንናደድበት ጊዜ የምናደርገው ነገር ኃጢአት ሊሆን እንደሚችል ወይም ቁጣችንን በጊዜ አንድ ነገር ካላደረግነው፣ ኃላ ላይ ኃጢአት ሊሆንብን እንደሚችል ይጠቁመናል፡፡ አሉታዊ ዝንባሌዎች ምላሽ ሳያገኙ በውስጣችን እንዲሰነብቱ ከፈቀድን፣ ለሰይጣን ‹‹ፈንታ›› የመስጠት አደጋ ውስጥ እንሆናለን፡፡

 1. ተራራ ወይም ዛፍ ለመውጣት እግር ለማስገቢያ የምትሆን ትንሽ ሽንቁር ያላትን ጠቀሜታ እላይ ከቀረበው ታሪክ አንጻር እንዴት ታየዋለህ?
 2. እግርህን ለመስቀል የምትረዳህን ሹንቁር ብታገኝ፣ ተራራውን ወይም ዛፉን መውጣት ‹‹ድል መንሳት›› መቻልህን እላይ ከቀረበው ታሪክ አንጻር እንዴት ታየዋለህ?

ሰይጣን በህይወትህ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር አይቆጣጠርም፡፡ ይህንን ማድረግ ፈፅሞ አይችልም፡፡ ነገር ግን ትንሽ ፈንታ ቢያገኝ፣ ማለትም ትንሿን የሕይወትህን ክፍል እንዲቆጣጠር ብትፈቅድለት፣ በሕይወትህ ትልልቅ ክፍሎች ላይ ድል ለመንሳት ይበልጥ ቅርብ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር፣ ለሰይጣን የመጀመሪያውን እግር ማስገቢያ እንዳትፈቅድለት ይመክርሃል! አንዴ ይህንን ቦታ ከሰጠኸው መልሰህ ለማግኘት ትቸገራለህና!

በ ሉቃስ 22፡31-34 ላይ ኢየሱስ በይሁዳ ተክዶ፣ ከመያዙና ለፍርድ ቀርቦ ከመሰቀሉ በፊት ባለችው ለሊት ከስምኦን ጋር ሲነጋገር እናነባለን፡፡ ሰይጣን በእግዚአብሔር ፊት ጀብደኛ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡

 1. ጥያቄው ምንድን ነበር?
 2. ይህ ምን ማለት ይመስልሃል?

በጴጥሮስ ሕይወት ውስጥ አንድ እክል ነበረ – ምናልባት ያ እክል ትዕቢቱ ሊሆን ይችላል። ይህም ሰይጣን በጴጥሮስ ሕይወት ውስጥ ሕጋዊ መብት እንዲያገኝና በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ የጴጥሮስን ሕይወት እንዲፈትን ፈቃድ ለማግኘት አስችሎታል፡፡ ጴጥሮስ የሰጠውን ደጅ ወይም ፈንታ በመጠቀምም ጥሎታል። ጴጥሮስ በፈተና ውስጥ በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር በሉአላዊ ስልጣኑ ይጠብቀው ነበር፡፡ ውድቀቱንም ለመልካም በመለወጥ ጴጥሮስ የተሻለ ሰው እንዲሆን ተጠቅሞበታል፡፡

የደጆች እና የእድል ፈንታ ሃሳብ ማጠቃለያ

በሕይወትህ ያለ ኃጢአት የሰይጣንን ትኩረት ይስባል፡፡ እርሱና አገልጋይ መናፍስቶቹ ያለማቋረጥ በህይወትህ ውስጥ አመቺ ሁኔታ ይፈልጋሉ፡፡ ምኞት ቢሆን፣ ትዕቢት ቢሆን፣ ቅንአት ቢሆን ወይም የመሳሰሉትን የሃጢአት ዝንባሌዎች ሲመለከት፣ ‹‹እዚህ ቦታ ላይ ዝንባሌ ይታየኛል፡፡ ይሄ ደካማ ጎኑ ነው፡፡ እስቲ ልጠቀምበት፡፡›› ይላል፡፡ ከዛም በበሩ ላይ በማድባት ደጁን ልትከፍትለት የሚያስችለውን አመቺ ሁኔታ ይጠብቃል፡፡ ሰይጣን ጥቃቅን እድሎችን በመጠቀም ሕይወትህን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ህልም አለው፡፡

ግልጽ መልዕክት አስተላልፈህለት በሩን በላዩ ላይ ልትዘጋ ወይም ክፍቱን ልትተውለት ትችላለህ፡፡ በርህን ክፍቱን ልትተው ስትፈቅድ እያልክ ያለኸው፣ ‹‹ሰይጣን ሆይ ሃሳብህን ለማስተናገድ ዝግጁ ነኝ፡፡ እንዴት ነው ፍላጎቶቼን የምታሟላው?›› ነው፡፡ እርሱ ደግሞ እቅዱን ያስረዳሃል፣ እናም ሞኝ ከሆንክ ታደምጠዋለህ ምክንያቱም እቅዶቹን አሳማኝ እንዲመስሉ አድርጎ ያቀርብልሃልና፡፡ ከዛም፣ የማታስተውል ከሆነ ያዘጋጀልህ ወጥመድ ውስጥ ትገባለህ፡፡

እግዚአብሔር ግን፣ ‹‹ገና ትንሽ ሳለ ንገስበት››፤ ልረዳህ የምትወድ ከሆነ እረዳሃለው፤ ነገር ግን መንፈሴ ወይም ሰይጣን ማን በሕይወትህ እድል ፈንታ ሊኖረው እንደምትወድ መወሰን ይኖርብሃል፡፡›› ሲል ይመክርሃል፡፡

‹‹በመንፈሳዊ ጦርነት ሙሉ ሙሉ ለመክተት፣ አስቀድመን ለሰይጣንና የእርሱ ለሆነው ሁሉ መራራ ጥላቻ ሊኖረን ይገባል፡፡ የሚያደርገውን መስፋፋት በቸልታ የምንመለከት ከሆነ በስንት ጥረት የተገኙ ግዛቶቹን መልሰን ልናጣቸው እንችላለን፡፡›› – ጎርዳን ቢ. ዋት

በመንፈሳዊ ውጊያ ያለን ስልጣን

ሰይጣንና ጋኔኖቹ እንዴት ያሉ ጨካኝ ጠላቶችህ እንደሆኑ ምናልባት አትረዳ ይሆናል፡፡ ሰይጣን ከዘመናት በፊት በሰው ልጅ ላይ ጦርነት አውጇል፡፡ ታላቅ ኃይል ስላለው በራሳችን ጉልበት ልንገጥመው ብንደፍር ሊያደቀን ይችላል፡፡

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ አገልጋዮች በመሆናችን ምክንያት ስለተሰጠን ስልጣን ይናገራል፡፡ ለዚህ ስልጣን የግሪኩ አቻ የሚከተለው ነው፡- Exousia: ‹‹መብት፣ ኃይል፣ ስልጣን፣ የመግዛት ስልጣን፣ ስልጣንን የተሸከመ፡፡››

 1. በቆላሲያስ 2፡9-10 መሠረት አለቅነትና ስልጣናትን ሁሉ የያዘው ማን ነው?
 2. በፊልጵስዮስ 2፡9-11 መሠረት የኢየሱስ ስም ከምን ያህል ሰዎች በላይ ነው?
 3. በዚህ ስም የትኞቹ ጉልበቶች ናቸው መንበርከክ ያለባቸው?

ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚበልጥ ስልጣን በዚህ አለም ላይ የለም፡፡ በእርሱ Exousia (ስልጣን) ፊት የትኛውም ንጉስ፣ ፕሬዝደንት፣ ጋኔን መልአክ፣ ሰይጣንን ጨምሮ ሊቆም አይችልም፡፡ እኛ ደግሞ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ከሰይጣን ጋር በሚኖረን ግንኙነት በዚሁ የስልጣን መጠን እንድንጠቀም ፈቃድ አግኝተናል፡፡ በኤፌሶን 2:6-7 መሠረት ከመንፈሳዊ ጠላቶቻችን አሻቅበን ህልቆ ሃይልና ስልጣን ባለበት በሰማይ በመንፈሳዊ ስፍራ በክርስቶስ ጋር ተቀምጠናል!

ነገር ግን በኃጢአትና ባለመታዘዝ ምክንያት ከዚህ መንፈሳዊ ሃይልና ሥልጣን ሸርተት ብንልና በጨለማው መንግስት ስር ራሳችንን ዳግመኛ ብናስገዛ፣ በዚህ መንግስት ላይ ጦርነት ለማወጅ አቅም በማጣት የተወሰነ የሽንፈት መጠን እንቀምሳለን፡፡ ይህ ሁኔታ ፈጥነን በመናዘዝ፣ ንስሃ በመግባትና ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስ በመሞላት ሊቀለበስ ይችላል (ምዕራፍ 3 ተመልከት)፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ያልተሞላህ ከሆነ መንፈሳዊ ጦነትን ለማድረግ አትሞክር!

ጠቃሚ ምክሮች

 1. ክርስቲያን መሆን ማለት ምንም ችግር አያጋጥምህም ማለት አይደለም፤ የአፅናፈ አለሙ ብልህ ችግር ፈቺ ባንተ ውስጥ አለ ማለት እንጂ፡፡
 • 1ጴጥሮስ 5፡7-9 አንብብ፡፡ ይህ መልዕክት ለአማኞች የተጻፈ ነው፡፡ ‹‹በመጠን ኑሩ፣ ንቁም›› ይላል፡፡ ለምን?
 • ክርስቲያኖችን በተመለከተ የጠላት የመጨረሻ ግቡ ምንድን ነው (ቁጥር 8)? ለዚህ ማስፈራሪያ ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል (ቁጥር 9) ?
 • የዮሐንስ 16፡33 ጥቅስ ክርስቲያኖችንና የሚገጥማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ በተመለከተ ሁለት ጥቅል ‹‹ተስፋዎችን›› ይናገራል፡- በዓለም ሳለን በእርግጥ ———— አለብን። ነገር ግን ልንፅናና ይገባል ምክንያቱም ————-
 • ለምንድን ነው ሁለቱም እነዚህ እውነታዎች ሊያበረታቱን የሚገባው?
 1. እንደ ክርስቲያን ስትኖር፣ ወደ ሕይወትህ የሚመጡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከዚህ በታች በተዘረዘሩ አራቱ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል –

ሀ. ሞኛ ሞኝ ወይም ኢ – ሞራላዊ የሆኑ ድርጊቶች ስታደርግ

በምስማሩ ፈንታ አውራ ጣትህን ብታስቀምጥ፣ ቅድመ ጥናት ሳታደርግ አክሳሪ በሆነ ካምፓኒ ውስጥ ሙአለ ንዋይን ብታፈስ፣ ሰካራም ብታገባ፣ ያለምንም ፓራሹት ከአስረኛ ፎቅ ላይ ብትዘል፣ የሚገጥምህ ነገር ምን እንደሆነ ብዙ መመራመር አያስፈልግም። በገላቲያ 6፡7 ላይ የተገጸው ሃሳብ ከእነዚህ ሃሳቦች ጋር ምን ግንኙነት አለው?

ለ. የሰይጣን ፈተናዎች

የሰይጣን የቀንና የሌሊት ጥረቱ በእግዚአብሔር ላይ እንድታምጽና የእርሱን መንገድ እንድትከተል ማድረግ ነው፡፡ 1ዮሐንስ 2፡15-16 የሰይጣንን ፈተናዎች ሶስት አቅጣጫዎች ያስነብበናል፡፡ እነዚህን ሦስት የፈተና አቅጣጫዎችን ጻፍና ምሳሌዎችን ፈልግላቸው፡፡

የምታሰላስለው ነጥብ፡- ሰይጣን የፈተና ስልቱን ለዘመናት አልቀየረም፡፡ በእርግጥም፣ መቀየር አላስፈላገውም አሁንም ድረስ ውጤታማ ናቸውና!

ሐ. በኃጢአት ውጤት ምክንያት እግዚአብሔር ሲቀጣን

እግዚአብሔር ልጆቹን ይወዳል፡፡ ማንኛውም ለልጁ ፍቅር ያለው አባት ልጁ ባልተገባ ስፍራ እንዲሆን አይፈቅድም፡፡ ይልቁንም ይህን ባሕሪ እንዲታረም ያደርጋል እንጂ፡፡ ይህን የሚያደርገው ልጁን ለመጉዳት ሳይሆን የተወሰደውን የተሳሳተ ምርጫ ለማረም እንጂ፡፡ የሰማዩ አባታችንም የሚያደርገው ይህንኑ ነው፡፡

ዕብራዉያን 12፡4-11 አንብብ፡፡ ይህ ክፍል እግዚአብሔር ለማረም ሲቀጣን በበጎ ፈቃድ እንድንቀበለው ይመክረናል፡፡ ለምን? (ቁጥር 10-11 ተመልከት)፡፡

መ. ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሳደግ በእግዚአብሔር ስንፈተን

አሰልጣኞች አትሌቶቻቸው ወደፊት ለሚገጥማቸው ታላቅ ውድድር ጥንካሬንና ጽናትን እንዲላበሱ በአስቸጋሪ ልምምድ ውስጥ እንዲያልፉ ያደርጓቸዋል፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹አትሌቶቹ›› በፊታቸው ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም እንዲችሉ፣ እዲበስሉና የበለጠ ጠቃሚ እንዲሆኑ ፈታኝ በሆነ ልምምድ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡

በ 1ጴጥሮስ 5፡10 መሠረት ፍፁማንና ብርቱ ከመሆናችን በፊት የምናልፍበት ነገር ምንድን ነው?

አትሌቶች በአስቸጋሪ ልምምድ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ሁሉ ለመታገስ እንዲችሉ በውድድሩ ግብ (ውጤት/መጨረሻ) ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ ክርስቲያኖች ከዚህ ምን ሊቀስሙ ይችላሉ?

 1. መዛራትና ማጨድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህ ነው። ያም ሆኖ ከላይ በተገለጹት አራት ምክንያቶች ወደ አማኙ ሕይወት ያሚመጡ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እግዚአብሔር ለመልካም ይለውጣቸዋል።
 • በዚህ ጥናት ውስጥ ገላቲያ 6፡7 አስቀድመን አይተናል (የመዝራትና የማጨድ ጥቅስ) ፤ አሁን ደግሞ ሮሜ 8፡25ን ተመልከት፡፡
 • ምን ያህል ነገሮች ናቸው እግዚአብሔርን ለሚወዱት ለበጎ የሚደረግላቸው?
 • ይህ ‹‹መጥፎ›› ነገሮችንም ጭምር እንደሚያጠቃልል ታስባለህ?
 • ይህ ጥቅስ እያንዳንዱ መንገድና እያንዳንዱ ሁኔታ መልካም እንደሆነ ይናገራል?
 • ይህ ጥቅስ በሕይወትህ ስለሚገጥሙህ አስቸጋሪ፣ የሚጎዱ፣ ፈታኝ፣ እና መጥፎ ሁኔታዎች ምን ይነግርሃል?

‹‹ክርስትና ከአለምና ከችግሮቿ አይለይህም፤ ጠቃሚ በሆነ ሁኔታና በድል በውስጧ እንድትኖር ያመቻችሀል እንጂ፡፡›› ቻርለስ ቴምናልተን

ማጨድ ሁል ጊዜ መዝራትን ይከተላል፡፡ ይህ አለማቀፋዊ መርህ ነው፡፡ እያንዳንዱ ምክንያት ውጤት አለው፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ቁሳዊም ሆኑ መንፈሳዊ ሕጎች የፈጠረው፣ ፍጥረት ያለ እንከን እንዲኖር ነበር፡፡ እነዚህ ሕጎች ለተወሰኑ ሰዎች የተበጁ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ማንም ሆንክ ምን ሕጎቹን ብትሰብር እነርሱ መልሰው ይሰብሩሃል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ሆንክም አልሆንክም ከ 10ኛ ፎቅ ላይ ራስህን ብትጥል፣ ፈጥነህ ወርደህ ትከሰከሳለህ፤ በርካታ አጥንቶችን ታደቃለህ አንተም ለከፍተኛ ሕመም ትዳረጋለህ ወይም ትሞታለህ፡፡ ይህ የምክንያትና ውጤት፣ የድርጊትና ምላሽ እውነታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን አሳዛኝ፣ የስቃይ ‹‹የመዝራትና የማጭድ›› ልምምድ በመውሰድ ለሚወዱትና ከእርሱ ጋር ተባብረው ለሚሰሩት ለመልካም ሊለዉጥላቸው ይችላል፡፡

ለገጠመን አስቸጋሪ ሁኔታም ሆነ ችግር መነሻ ምክንያቱ እግዚአብሔር ነው ብሎ ለመናገር ከባድ ነው፡፡ አንዳንዴ ሊሆን ይችላል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ላይሆን ይችላልና፡፡ በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ፣ ይኸውም – እግዚአብሔር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት እንደሚረዳህ፣ ከምትሸከመው በላይ እንዳይሆን እንደሚያደርግ (1ቆሮንቶስ 10፡13)፣ የሚረዳህን ጸጋ እንደሚሰጥህ እና ችግሩን ከፍጹም አላማው ጋር እንደሚያስማማው፡፡

 1. ክርስቲያኖች ከፈተና ሊሸሹና ዲያብሎስን ሊቃወሙት ይገባል፡፡

ክርስቲያኖች ይህን ሃሳብ ገልብጠው፣ ‹‹ከሰይጣን ልንሸሽ›› እና ‹‹ፈተናን ልንቃወም›› ይገባናል ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ተቃራኒ ነው!

 • 2ጢሞቴዎስ 2፡22 የሚመክረን፣ የጎልማሳ ምኞቶቻችንን ቆመን እንድንዋጋቸው ነው ወይስ ቦታችንንና አቅጣጫችንን ፈጥነን በመቀየር በሌሎች ነገሮች እንድንጠመድ?
 • ልክ እንደማይደፈሩ ጠላቶች ከእነዚህ ምኞቶች በመሮጥ ‹‹እንደፈሪ›› አይነት እርምጃ እንድንወስድ የታዘዝነው ለምን ይመስልሃል?

ሰይጣንን ደግሞ ልንሸሸው ሳይሆን ልንቃወመው ይገባል፡፡ ከእርሱ ወይም ከክፉ ስራዊቶቹ ፊት አንሸሽም፣ ጸንተን እንዋጋቸዋለን እንጂ፡፡ ያዕቆብ 4፡7 ልብ አድርገህ ተመልከት፣ የእኛ ድርሻ መቃወም ብቻ ነው፣ መምታት፣ መግረፍ፣ መደብደብ አይደለም፡፡ ይህን ስናደርግ በእግዚአብሔ ቃል ተስፋ መሠረት ከእኛ ይሸሻል!

ኤፌሶን 6፡10-18 አንብብ፡፡ የእግዚአብሔርን ጦር ዕቃ ሁሉ እንድንለብስ መታዘዛችንን ልብ በል፡፡ ለምንድን ነው ሰዎች የጦር መሣሪያን የሚታጠቁት?

‹‹እንድንለብስ›› የታዘዝነውን የጦር መሣሪያ ልብ በል፡፡ ከዛም እያንዳንዱ መሳሪያ ያለውን ጠቀሜታ ወይም ከምን እንደሚከላከለን ጻፍ፡፡

 • የእውነት መታጠቂያ
 • የጽድቅ ጡሩር
 • የሰላም ወንጌል ጫማ
 • የእምነት ጋሻ
 • የመዳን ራስ ቁር
 • የመንፈስ ሰይፍ – የእግዚአብሔር ቃል
 • ዘወትር መጸለይ

ሀ. ዲብሎስን ለመቃወም ጠቃሚ የሆነ አካሄድ

የ ያዕቆብ 4፡7-8 መልእክት፣ ሰይጣንን ለመቃወም ልንጠቀምበት የሚገባንን አካሄድ ያመለክተናል፡፡ ይህን ሃሳብ ንብረት ለመዝረፍ ወደ ቤትህ ከገባ ቤት ሰርሳሪ ጋር ለመጋፈጥ ከምታደርገው ሁኔታ ጋር አዛምደህ ተመልከተው፡፡ በዚህ መሠረት አራት እርምጃዎችን ትወስድ ይሆናል (መመርመር፣ መታጠቅ፣ ማጥመድ፣ መጠናከር)፡፡ እነዚህ አራት ደረጃዎች ጠላታችን በሆነው ዲያብሎስ ላይ የምንወስዳቸው እርምጃዎችም ጭምር ናቸው፡፡

የመጀመሪያ እርምጃ ፡ መመርመር። ‹‹በሰይጣን እንዳንታለል፣ የእርሱን ሃሳብ አንስተውምና፡፡›› -2ቆሮንቶስ 2፡11። ምሳሌ፦ ‹ሰይጣን ኃጢአት እንድሰራ እየፈተነኝ ሳይሆን አይቀርም!››

ሁለተኛ እርምጃ፡ መታጠቅ። ‹‹እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፡፡›› ያዕቆብ 4፡7። ሰይጣንን ለመዋጋት እግዚአብሔር እንዲረዳህ ጸልይ፡፡ በሰማያዊ ስፍራ በክርስቶስ ያለህን ስልጣን መያዝህን አትዘንጋ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ስለመሞላትህ እርግጠኛ ሁን፡፡

በፈተናዎችህ ወቅት የሚከተለውን አይነት ጸሎት መጸለይ ትችላልህ፡- ‹‹አባት ሆይ ባንተ ላይ ኃጢአትን እንድሰራ ሰይጣን እየፈተነኝ ነው፡፡ ስላለሁበት ሁኔታ እንድዋሽ ይፈልጋል፡፡ ልነግስበት እፈልጋለሁ፡፡ እባክህ በመንፈስህ ሙላኝ፡፡ ከስልጣናት፣ ከኃይላት፣ ከገዢቆችና ከክፉ ሃይላት በላይ የሚያደርገኝን በአንተ ቀኝ በመንፈሳዊ ስፍራ ከክርስቶስ ጋር የተቀመጥኩበትን ስፍራ እይዛለሁ፡፡ በአንተ በረከት፣ ጥበቃ እና ኃይል ጠላቴን እንድቃወምና እንዳሸንፈው እንድትረዳኝ እለምንሃለው፡፡››

ልትመክትበት የሚያስችልህ እንደ መሣሪያ ወይም ዱላ ወይም ሌላ ነገር በእጅህ ሳትይዝ ሠርሳሪን መጋፈጥ ሞኝነት እንደሆነ ሁሉ በራሳችን ሃይል የጨለማውን ሃይላት ለመጋፈጥ መሞከር በራስ ላይ ችግር መጋበዝ ነው፡፡

ሦስተኛ እርምጃ፡ ማጥመድ። ‹‹ዲያብሎስን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፡፡›› ያዕቆብ 4፡7። ዋነኛ የጦር መሳሪያህን ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል በመጠቀም ልክ ኢየሱስ በማቴዎስ 4፡1-11 ላይ እንዳደረገው ጠላትህን ፊት ለፊት ግጠመው፡፡

ፊት ለፊት ለመግጠም የምክር ሃሳብ፡- ‹‹አንተ ሰይጣን፣ የነገስታት ንጉስ የጌቶች ጌታ በሆነው እና በደሙ ገዝቶ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ባደረገኝ በኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን እመጣብሃለው፡፡ ኃጢአት እንድሰራ የምታደርገውን ተንኮል አውቄአለሁ፡፡ ይህን በማድረግህ በዘሌዋዊያን 19፡11 ላይ በተጻፈውና ‹‹አትስረቁ፣ አትካዱም፣ ከእናንተም እርስ በእርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ፡፡›› በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ላይ አፊዘሃል፡፡ እንድዋሽ እየሞከርክ በመሆኑ በእግዚአብሔር በተሰጠኝ ስልጣን በኔ ላይ ያነጣጠርከውን ስራ እንድታቆም፣ እንድትተወኝ እና ኢየሱስ ወዳዘዘህ ስፍራ እንድትሄድ አዝሀለው፡፡››

ኢየሱስ በምድረ በዳ ከሰይጣን ጋር ያደረገውን ታላቅ መጋፈጥ የሚተርከውን የማቴዎስ 4፡1-11 ክፍልን አንብብ፡፡ ኢየሱስ ዋነናኛ መሣሪያውን እንዴት እንደተጠቀመ ልብ በል፡፡ እያንዳንዱን የጠላት ፈተና ለመቃወም ሦስት ጊዜ የተጠቀመበት ሃረግ ነበር፡፡ ያ ሀረግ ምንድን ነው? (ቁጥር 4፣7፣10)

እላይ የተዘረዘሩትን መንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች ወደ ኃላ በመሄድ ተመልከት፡፡ ሰባት የተዘረዘሩ መሳሪያዎች ሲኖሩ ከነዚህ መካከል ስድስቱ የመከላከያ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ለማጥቂያ የሚውለው የቀረው አንዱ መሣሪያ ምንድን ነው?

‹‹የድልህ መሠረት የክርስቶስ ሞት ነው፡፡ ይህ ሞት ከኃጢአት ኩነኔ ለይቶ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝህ ሞት ብቻ ሳይሆን ከክፉው ድንገተኛ አደጋም ጭምር የሚሰውርህ ነው፡፡›› ጄለ ዱዋይት ፔንተኮስት

አራተኛ እርምጃ፡ መጠናከር። ‹‹ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል፡፡›› – ያዕቆብ 4፡8። ከጦርነት በኃላ፣ ጥቂት ቆይታ በጸሎት መውሰድ፣ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ማወደስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ፣ ድሉን በማተም ራስህን ማጠናከር ያስፈልጋል።

የቃል ጥናት ጥቅስ፡

‹‹እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።›› ያዕቆብ 4፡7-8

ማጠቃለያ፡

‹‹ከእኔ ጎን በመሆን ትዋጋለህ?›› ሲል ኢየሱስ ጥያቄ ያቀርብልሃል፡፡

ምዕራፍ 11ን ያጥኑ

2 thoughts on “ምዕራፍ 10- መንፈሳዊ ውጊያ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: