ምዕራፍ 4 – አሮጌውን ሰው ችላ ማለት

ጸሎት

‹‹አባት ሆይ፣ መታገል ሰልችቶኛል፡፡ በሁሉ ነገር አስደስትህ ዘንድ ታዛዥ ልጅህ ለመሆን እናፍቃለሁ፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እወድቃለሁ፡፡ እባክህ ከአንተ ጋር ባልተቋረጠ የድል ሕይወት መንገድ መጓዝን አስተምረኝ፡፡ አሜን፡፡››

አሮጌውን ሰው ችላ ማለት ያስፈልጋል?

በአንድ ሞቃት የበጋ ወር አንድ እድሜው በአስራዎቹ ውስጥ ያለ ወጣትና ወንድ አያቱ አሳ ያጠምዱ ነበር፡፡ አያትየው ከግማሽ ምዕት አመት በላይ ከጌታ ጋር ተጉዘዋል፤ ወጣቱ ግን ክርስቲያን ከሆነ ጥቂት አመታት ብቻ ናቸው፡፡

‹‹አያቴ፣›› አለ ይህ ወጣት አሣ በሚያጠምዱበት ቀን ማለዳ፣ ‹‹አንድ ችግር ገጥሞኛል፣ ትረዳኝ እንደሁ አላውቅም፡፡›› ሲል ጠየቀ፡፡

‹‹መልካም፣ ልረዳህ እሞክራለሁ፡፡ ምንድነው ነገሩ፣ ልጄ?››፣ አሉ አያትዬው የወጣቱን አይን አይን እያዩ።

‹‹ጥያቄዬ ክርስትናን የተመለከተ ነው፡፡ አሁን ከምኖረው የተሻለ ሕይወት መኖር እንዳለብኝ እና ለእግዚአብሔር የበለጠ መታዘዝ እንዳለብኝ አውቃለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይሳካልኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ልክ እንደ ብዙዎቹ ሌሎች ክርስቲያን እንዳልሆኑ ጓደኞቼ ስሆን ራሴን አጋኘዋለሁ፣ በረባ ባልረባው በእህቴ ላይ ስቆጣ፣ ስህተት እንደሆኑ የማውቃቸውን ነገሮች ሳደርግ፣ ወዘተ… ራሴን አገኘዋለሁ፡፡ ለምንድን ነው ሁል ጊዜ ጥሩ ሰው መሆን የማልችለው?››

አያትየው የማጥመጃ ገመዱን ወደ መሃል ወርውረው፣ ‹‹የምትለው ምን እንደሆነ ይገባኛል።›› ጥቂት ዝም ብለው የአሣ ማታለያዋ የት ቦታ ላይ እንዳለች ካጠኑ በኃላ፣ ‹‹አንድ ነገር ማወቅ ትፈልጋለህ? ታዲያ የምነግርህን ላገኘኸው ሁሉ የምትነግረው አይደልም። እናም ልጄ፣ እኔም ብሆን አንዳንድ ጊዜ የገለጽከው አይነት ችግር አለብኝ፡፡››

‹‹በእውነት?›› አለ ወጣቱ በመደነቅ፡፡ ‹‹አንተ፣ አያቴ! እንዴት ሊሆን ይችላል? ማለቴ፣ አንተም ጥሩ ሰው የመሆን ችግር ይኖርብሃል ብዬ ማመን ይከብደኛል፡፡››

አያትየው ፈገግ ብለው፣ ‹‹ማመን ይከብድሃል አይደል ልጄ? ቀድሞ በነበረው የመግዛት አቅሙ ባይሆንም አልፎ አልፎ በውስጤ መልካምና ክፉ የሆኑ ሁለት ውሾች እንዳሉ አሁንም ድረስ ይሰማኛል፡፡ እነዚህ ውሾች የሕይወቴ ‹ዋና ውሻ› ለመሆን ይታገላሉ፡፡

‹‹እንዴ! ልክ አሁን ሁለት ውሾች ሲታገሉ እንዳልከው አይነት ስሜት እኔም ይሰማኛል!… አያቴ፣ ግን ማን ነው በአንተ ውስጥ የሚያሸንፈው?›› ብሎ ጠየቀ ወጣቱ፡፡ ብልሁ ሽማግሌ በዚህ መሃል የማሰገሪያ ገመዱ ሲንቀሳቀስ አስተውለው ወጣቱን በአይን ጥቅሻ ካዩ በኋላ፣ ‹‹ይበልጥ የምመግበው ውሻ ነዋ፣ ልጄ›› ሲሉ መለሱለት፡፡

ትግሉ

ይህን ‹‹ትግል›› በሕይወትህ ታስተውላለህ? በርካታ ክርስቲያኖች ይህን ሕይወት ያውቁታ፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ሳይቀር በሮሜ 7፡18-19 በፃፈው መልዕክቱ በዚህ ትግል ውስጥ ማለፉን ገልጿል፡፡

‹‹በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፣ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።›› -ሮሜ 7፡18-19

የሕይወትህ አዳኝ እንዲሆን ክርስቶስን ወደ ሕይወትህ ጋብዘኸው ከሆነ፣ ‹‹አዲስ ፍጥረት›› (2ቆሮንቶስ 5፡17) መሆንህን አውቀሃል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ፣ ለምንድነው ታዲያ አሁን ድረስ ከብዙዎቹ ‹አሮጌ ባሕሪዎችህ›› ኃጢአቶች ጋር የምትታገለው?

በታሪኩ እንደተገለጸው ጉዳዩ የትኛውን ውሻ ትመግባለህ የሚለው ይሆናል፡፡ የትግሉን ምንጭና እንዴት ባለድል መሆን እንደሚቻል የበለጠ ለማወቅ ምንባብህን ቀጥል፡፡

አዲሱን ለብሰህ አሮጌውን አስወግደሀል?

ክርስቶስን በተቀበልክ ጊዜ ወዲያውኑ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ሆነሀል፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ እና በአካባቢህ ላሉ ሰዎችና ለራስህ ጭምር ጠቃሚ ሕይወት ለመኖር የሚያስችልህን ልኬት የሌለውን መለኮታዊ ጉልበት ተቀብለሃል ማለት ነው፡፡

ይህንን በምን ያህል መጠን እየተለማመድክ ነው?

ከ 1-10 ባለው የመለኪያ ስኬል አመልክት__________ 1= ማለት ፈፅም ሲሆን፣ 10= ማለት ደግሞ ሁል ጊዜ ማለት ነው።

በመልስ መስጫው ላይ ክፍተኛ ቁጥርን ፅፈህ ከሆነ እንኳን ደስ አለህ! የድል ሕይወት እና ፍሪያማ ሕይወት የመኖርን ምስጢር ካጣጣሙ ጥቂት ሰዎች ተርታ ነህና፡፡ በመለስ መስጫው ላይ ያመለከተክው ክፍተኛ ቁጥር ካልሆነ፣ እንደማንኛውም በርካታ በእድገት ውስጥ እንዳሉ ክርስቲያኖች ነህና ተጨማሪ እርዳታ ያሻሀል ማለት ነው፡፡

በመንፈስ የተሞላው፣ ክርስቶስን የሚወደው፣ እግዚአብሔርን በሕይወቱ ያከበረ ግን በሕይወቱ ትግሎች የነበሩበት ሐዋሪያው ጳውሎስ የጻፈውን ይህን መልዕክት አጥና፡-

‹‹እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?›› ሮሜ 7፡21-24

ቁልፍ የግንዛቤ ነጥብ፡-

በሮሜ 7 ላይ ከቀረቡት ሃሳቦች ልንወስድ ከሚገቡን ቁም ነገሮች መካከል ዋነኛው፣ ምንም እንኳን የተዋጁ ወንድ እና ሴት የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን መጠን ‹‹አዲስ ተፈጥሮ›› ቢኖረንም፣ ‹‹አሮጌው ሰው›› አሁንም ያለአንዳች ለውጥ በውስጣችን መኖሩን ነው፡፡ እናም እነዚህ ሁለቱ ተፈጥሮዎች በሕይወታችን ውስጥ የበላይነት ለማግኘት የማያቋርጥ ትግል ያደርጋሉ፡፡ እናስተውል፣ አዲሱን ትፍጥሮ ስንቀበል አሮጌው ማንነታችን ከሕይወታችን ጨርሶ አልወጣም (አልጠፋም)፡፡

በትምሕርቱ መግቢያ በቀረበው ታሪኩ ውስጥ የተገለፀው የመልካም እና ክፉ ውሻዎች ምሳሌ፣ ጳውሎስ በውስጡ ያሉትን ሁለት ‹‹ተፈጥሮዎች›› የገለጸበትን ሁኔት ይመስላል፡፡

  1. የጳውሎስ አዲስ ተፈጥሮ ምን ማድረግ ይወዳል?
  2. የጳውሎስ አሮጌ ተፈጥሮስ ምን ማድረግ ይወዳል?
  3. በጳውሎስ ትግል ውስጥ ራስህ አግኝተሃል?

መለወጥ እየፈለግን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝ እየፈለግን ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይህን ለማድረግ ጉልበት ሲያጥረን ይስተዋላል፡፡ በምዕራፍ 3 እንዳየነው የሃይላችን ምንጭ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱ በሕይወታችን ዙፋን ላይ ሲነግስ ሃይል፣ ድል እና የተትረፈረፈ ሕይወትን እንለማመዳለን፡፡ ነገር ግን፣ በየእለቱ ወይም በየደቂቃው፣ ‹‹እኔነት›› ከዙፋኑ ወርዶ ክርስቶስ በዙፋኑ ላይ እንዲቆይ የማድረግ ትግሉ ይቀጥላል፡፡

በእያንዳንዱ ፈተናዎቻችን ወቅት፣ አማራጭ አለን፡- በእግዚአብሔር መንገድ ወይም በሰይጣን መንገድ ለመሄድ፡፡ ወዴት እንደምንሄድ የምናውቅ ከሆነና እዛም መድረስ በእርግጥ የምንሻ ከሆነ፣ በጉዞአችን ላይ የሚያጋጥመን መንታ መንገድ የጎላ ችግር አይሆንብንም፡፡ ነገር ግን ለብዙዎቻችን ሰይጣን ያቀረበልንን አማራጭ፣ የዘወትር ልማድ (የሁል ጊዜ ልምምዳችን) እስኪሆንብን ድረስ መርጠናል፡፡ እግዚአብሔር ስላቀረበልን አማራጭ የማሰቢያ ጊዜ እንኳን ሳይኖረን ምክንያታዊ እና አርኪ ሊሆን ከማይችለውና ከማይረባው የሰይጣን አማራጭ ጋር መስማማት እንደ ልማድ ሆኖብናል፡፡

በእርሱ እንጂ በእግዚአብሔር መንገድ መጓዝ አርኪ ውጤት እንደሌለው እኛን ማሳመን የይጣን ዋነኛ ስልት ነው፡፡ ሰይጣን እንዲህ በማለት ያስተናል፣ ‹‹ፍላጎትህን እሞላለሁ፣ የምትሻውን ሁሉ እሰጥሃለው፣ ነፃ አወጣሃለሁ፤ ማንኛውንም ነገር አደርግልሀለው፣ ይህንንም ለማግኘት ምንም ወጪ አታወጣም፡፡›› ሰይጣን ማስመሰሉን በመቀጠል እንዲህ ይላል፣ ‹‹እግዚአብሔር የደስታህ እንቅፋት ነው፡፡ ሊያስርህ፣ ደስታህን ውስን ሊያደርግና ወደ ኋላ ሊያስቀርህ ነው የሚሻው፡፡ መንገዴን ምረጥ!›› ይልሃል፡፡ ይህን የሚያቀርብልህ ውብ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ከዛም አሣ ለማጥመድ ማጥመጃው ላይ የሚደረገውን ማታለያ ምግብ ስትቆነጥር፣ ወረንጦውን በሕይወትህ ላይ ይሰካዋል፡፡

የሁለቱ የውኃ ጉድጓዶች ተረት -ክፍል 1

1. ክርስቶስን ከመቀበላችን በፊት ያለን ሕይወት

ከእለታት አንድ ቀን በአንደ የእርሻ መሬት ላይ ተወልዶ በዛው መሬት ላይ ያደገ ገበሬ ነበር፡፡ የእርሻ ቦታውን ከቤተሰቡ ከወረሰም በኋላ የራሱን ቤተሰቦች በዛው የእርሻ መሬት አማካኝነት ያስተዳድር ነበር፡፡

ገበሬውና ቤተሰቡ ሁል ጊዜ ደካማና በሽተኞች ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት ከእርሻ ቤታቸው በቅርበት ያለው እና ለአስርተ አመታት እርሻቸውን ለማልማት የሚጠቀሙበት የውኃ ጉድጓድ የተበከለ ስለነበር ነው፡፡ እነሱ ግን ይህን አያውቁም ነበር፡፡ መርዛማ ከሆነ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጋር ተገናኝቶ በገበሬው የውኃ ጉድጓድ ውስጥ የሚገባ፣ መሬት ለመሬት የሚሄድ አነስተኛ ወንዝ ነበር፡፡ እናም ከዚህ ውኃ ለመጠጥነት በተጠቀሙ ቁጥር ቤተሰቡ በጤና መታወክ ይሰቃዩ ነበር፡፡ ገበሬውና ቤተሰቡ ለአስርት አመታት ከዚህ ጉድጓድ ውኃ ይጠጡ ስለነበረ የጤናቸው መታወክ ምክንያት ዉሃው እንደሆነ አያስቡም ነበር። ያሉበት የጤና ሁኔታ ውሃውንም ከመጠቀማቸው በፊት ያለ አድርገው ያስቡ ነበር፡፡ [ታሪኩ ይቀጥላል]

ክርስቶስን ከመቀበልህ በፊት የነበረህ ሕይወት በዚህ ታሪክ ውስጥ ባለው የእርሻ ቦታ ሊመሰል ይችላል፡፡ ገበሬው፣ ውሳኔ የሚሰጠውን አእምሮህን ይወክላል፡፡ በመሬት ስር ለስር የሚፈሰው ውሃ አሮጌ ሰውህን የሚወክል ሲሆን ብክለቱ ኃጢአተኛነትህን ይወክላል፡፡ የውኃ ጉድጓዱ፣ አሮጌው ሰው የሚያመነጨውን ዝንባሌአችንን እና ባሕሪያችንን ይወክላል፡፡

ገበሬው ሊቀዳበት የሚችለው አንድ የተበከለ የውኃ ጉድጓድ ብቻ እንደነበረውና የውኃውንም ብክለት እንዳላወቀ ሁሉ እኛም ጌታን ከማወቃችን በፊት ከእርሱ ልንቀዳበት የምንችለው የተበከለ ተፈጥሮ ብቻ ነበርን፡፡

ማርቆስ 7፡14-23 አንብብ፡፡ በሕይወታችን ያለው የኃጢአት ምንጭ ምንድን ነው ይላል?

‹‹አሮጌው የውኃ ጉድጓዳችን›› የሚያመነጨውን ዝንባሌ እና ባሕሪ አስተውል፡-

‹‹የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፣ ርኵሰት፣ ዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል ነው።›› -ገላቲያ 5፡19-21

‹‹በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፣ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፣ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፣ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፣ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።›› ኤፌሶን 2፡1-3

  1. በኤፌሶን 2፡1-3 መሠረት፣ ክርስቶስን ከማወቃቸው በፊት ምን ያህሉ ክርስቲያኖች ነበሩ ከዚህ ከተበከለው የኃጢአተኛ ተፈጥሮ፣ ዝንባሌያቸውንና ባሕሪያቸውን ይቀዱ የነበሩት?
  2. እነዚህ ዝንባሌዎችና ባሕሪያት፣ የተማርናቸው (ተምረን ያገኘናቸው) ናቸው ወይስ በተፈጥሮአችን ውስጥ ያሉ?

በአዳኛችን በኢየሱስ ከመቤዠታችን በፊትም ለሌሎች የምናዝን ሰዎች እንሆን ይሆናል፡፡ ብዙዎቻችን በጣም ክፉዎች ላንሆን እንችላለን፡፡ ብዙዎቻችን ነፍሰ ገዳዮች፣ ሴቶችን አስገድደን የምንደፍር ወይም የታጠቁ ዘራፊዎች አንሆን ይሆናል፡፡ ብዙዎቻችን ከመጥሮ ተግባሮቻችን ይልቅ መልካም ተግባሮቻችን የሚያመዝኑ እንሆን ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ብዙውን ጊዜ መልካም ነገር ለማድረግ እንጥራለን ማለት ነው፡፡ ይህ ጥረታችን በእግዚአብሔር ፊት ነጥብ ያስቆጥርልን ይሆን? ለምላሹ ኢሳይያስ 64፡6 አንብና ሃሳቡን በራስህ አባባል ከዚህ በታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ አስፍር፡፡

_____________________

2. ድነት!

ከዚህ በታች በገበሬው ሕይወት ውስጥ የምትመለከተው ትዕይንት የአንተን ድነት ይወክላል፡፡ አዳኝ እና አዲስ ‹‹የውኃ ምንጭ›› እንደሚያስፈልግህ አውቀህ እርምጃ የወሰድክበትን እለት ማለት ነው፡፡ በቀጣዩ ታሪክ ወስጥ የምታነበው በምድር ውስጥ ለውስጥ የሚፈሰው አዲሱ ወንዝ አዲሱ ተፈጥሮህን ይወክላል፣ በእዚህ አዲስ ወንዝ ውስጥ ምንም አይነት የተበከለ ኃጢአተኝነት የለም፡፡ አዲሱ የውኃ ጉድጓድ፣ አዲሱ ተፈጥሮህ የሚያመነጨውን አዲስ ዝንባሌዎችህንና ባሕሪያትህን ይወክላል፡፡

የሁለቱ የውኃ ጉድጓዶች ተረት -ክፍል 2

አንድ ቀን ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አንድ ሰው መጥቶ የገበሬውን የውኃ ጉድጓድ መረመረ፡፡ ከምርመራው በኋላ ገበሬው የውሃው ጉድጓድ መበከሉን አወቀ፣ እናም ከውሃው ጉድጓድ መጠቀም ወዲያውኑ አቆመ፡፡

ነገር ግን እንደሚታወቀው ሁሉ የእርሻ መሬቶች ለልማት፣ ገበሬዎችና የገበሬ ቤተሰዎች ደገሞ ለመኖር ውኃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የቁፋሮ ባለሞያዎቹ ከሌላ አቅጣጫ ወደ ገበሬው ይዞታ ውስጥ ለውስጥ የሚፈስ ሌላ ወንዝ መኖሩን ለገበሬው ነግረውት ስለነበር ስለጉዳዩ ከባለሙያዎች ጋር መማከር ጀመረ፡፡

ባለሙያዎቹ ባመለከቱት ቦታ ላይ ገበሬው አዲስ ጉድጓድ ቆፈረ፣ እናም ከጉድጓዱ የወጣው ውኃ ንፁህ ነበር፡፡ [ታሪኩ ይቀጥላል]

2ቆሮንቶስ 5፡17ን አንብብና ባዶ ቦታዎቹን አሟላ፡-

‹‹ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን_________________________________ፍጥረት ነው፡፡ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እሆን ሁሉም_________________ሆኖአል፡፡››

ገላቲያ 5፡22-23፣ ይህ አዲስ የውኃ ጉድጓድ ስለሚያመነጨው ዝንባሌና የባሕሪይ አይነት ያወራል፡፡

‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው።››

ክርስቲያን ከሆንክ በኋላ እነዚህ ፍሬዎች በሕይወትህ ሲትረፈረፉ ተመልክተሃል? ‹‹ፍሬ ማፍራትህ›› እየጨመረ እንዲሄድ ምን ማድረግ ያለብህ ይመስልሃል?

ከአዲሱ የውኃ ጉድጓድ የወጣው አዲስ ውኃ የገበሬውንና የቤተሰዎቹን ሕይወት ከተበከለው አሮጌ የውኃ ጉድጓድ በሽታና ሞት ታደገ፡፡ ሮሜ 8፡1-2 ነፃ ወጣን ይላል?

‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና።›› -ሮሜ 8፡1-2

ይህ ምን ማለት ነው?

የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ አዲሱ አማኝ እውነተኛ አዲስ ተፈጥሮ ይነግሩናል፡፡ በእያንዳንዱ ጥቅሶች ውስጥ አዲሱ አንተነትህን የሚገልፁ ስያሜዎችን ለይተህ አክብብ፡፡

  1. ‹‹አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና።›› -ዕብራዊያን 10፡14
  2. ‹‹በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል።›› -ዕብራዊያን 10፡10
  3. ‹‹ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፣ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።›› -ሮሜ 8፡29-30

አዲሱ የውኃ ጉድጓድ›› ‹‹አዲሱን አንተነትህን›› ይወክላል – እውነተኛ ማንነትህን፡፡ ከአሁን በኋላ፣ ‹‹ክህደትና ራስ ወዳድነት እኔነቶቼ አይደሉም፡፡ ምኞት ወይም ኩራት እኔነቶቼ አይደሉም፡፡ የእውነተኛ ማንነቴ መገለጫዎች ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ የውሃት እና ራስን መግዛት ናቸው!

የሁለቱ የውኃ ጉድጓዶች ተረት -ክፍል 3

ከተበከለው የውኃ ጉድጓድ መጠቀም አቁመው ከአዲሱ የውኃ ጉድጓድ ንፁሁ ውሃ መቅዳት ሲጀምሩ የገበሬውና የቤተሰዎቹ ጤንነት ቀስ በቀስ መሻሻል ጀመረ፡፡

ነገር ግን ችግራቸው ሙሉ በሙሉ አልተፈታም ነበር፡፡ አሮጌው የውኃ ጉድጓድ ከቤታቸው በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሲሆን አዲሱ ደግሞ ከቤታቸው እሩብ ማይል ያህል ይርቅ ነበር፡፡ ወደዚህ የውኃ ጉድጓድ ለመድረስ በቀጭን የእግር መንገድ ተጉዞ፣ አቀበት ውጥቶ ቁልቁለት ወርዶ፣ ዋሻ አቆራርጦ፣ ውኃው የሚገኝበት ትንሽ ቦታ ላይ መድረስ የግድ ነበር፡፡ ባንቧ ለመቀጠል ደግሞ አቅም አልነበራቸውም፡፡ እንዲሁም ከአዲሱ ጉድጓድ ውሃ ማውጣት አስቀድሞ ከተለመደው ጉድጓድ አንፃር አመቺ አልነበረም፡፡ [ታሪኩ ይቀጥላል]

“የእውነተኛ ማንነታችን መገለጫዎች ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ የውሃት እና ራስን መግዛት፣ ወዘተ ሊሆን ሲገባው፣ ለምን ችግሮችን በሕይወታችን እናያለን? አንዳንድ ጊዜ የፍቅር ሰዎች አንሆንም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደስታ የለሾች እንሆናለን፡፡ ይህ ‹‹አዲስ ተፈጥሮ›› እያለን እንዴት ነው አሁንም ድረስ ኃጢአት የምንሰራው?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የገበሬው የተበከለ የውኃ ጉድጓድ በቤቱ አቅራቢያ አሁንም ድረስ እንዳለ፣ በተመሳሳይ መንገድ አሮጌው ሰውም በእኛ ውስጥ አሁንም ድረስ አለ፡፡ ይህ ባህሪ በአቅራቢያችን የሚገኝ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ይቀርበናልም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለረጅም ዘመን ከእርሱ የመቅዳት ልምድ ስላዳበርን ነው፡፡ ጌታን እስካወቅንበት ጊዜ ድረስ ፍላጎታችንን ለማርካት የምንጓዘው ወደ እርሱ ብቻ ነበር፡፡ ገበሬው አሁንም ድረስ ከአዲሱ የውኃ ጉድጓድ ይልቅ ከአሮጌው የውኃ ጉድጓድ ሊቀዳ የሚችልበት ምን ምክንያት ያለው ይመስልሃል?

አሰላስል፡-

ከታች የቀረቡት ዝርዝሮች፣ ገበሬው የተበከለ መሆኑን እያወቀ ከተበከለው ጉድጓድ፣ ውሃ መጠጣት መቀጠሉን እንዴት ሊያብራሩ ይችላሉ? ክርስቲያኖች ዝንባሌዎቻቸውንና ባሕሪያቸውን ከአሮጌ ተፈጥሯቸው ለመቅዳት የሚያዘነብሉበትን ምክንያት እንዴት እነዚህ ነጥቦች ያብራራሉ?

  • ምክኒያታዊነት
  • ጥርጥር
  • እብሪተኝነት
  • ስንፍና
  • ልማድ

የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት

ከአዲሱ ውሃ በፊት፣ ገበሬው ውኃ ሲጠማው፣ የቤቱን በር ከፍቶ በመውጣት ወደ ግራ ይታጠፍና ወደ ጉድጓዱ የሚያመራውን አጭር መንገድ ይጓዝ ነበር፡፡ ይህ የሕይወት ዘመን ልምምዱ እንደነበር መዘንጋት የለብህም፡፡ የዘወትር ልማዱ ሆኗል። ተፈጥሯዊ ዝንባሌው ሆኗል። ይህን ልምዱን ልውጦ አሁን መሚጠማው ጊዜ ከቤቱ ወጥቶ፣ ወደግራ ከመታጠፍ ይልቅ ወደ ቀኝ ታጥፎ፣ ወደ አዲሱ የውኃ ጉድጓድ የሚያመራውን መንገድ ለመከተል ጊዜ የሚጠይቅ ልምምድ ማድረግ ይኖርበታል። ውሳኔው የዘወትር ልምዱ እስኪሆንና ተፈጥሯዊ እስኪሆን ድረስ የተወሰነ ጊዜ ይወስድበታል፡፡

መንፈስ ቅዱስ፣ ከገበሬው ቤት አጠገብ ተሰቅሎ ገበሬው ውኃ ለማግኘት ከቤቱ በወጣ ቁጥር “ወደቀኝ ታጠፍ!!!” በሚል ግዙፍ የማስጠንቀቂያ ምልክት ይመሰላል፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ አንዳንድ ጊዜ ገበሬው ይህን ምልክት ችላ ሊል ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንተም የመንፈስ ቅዱስን ማስጠንቀቂያ ችላ ልትል ትችላለህ፡፡ ለመጠጥነት የምትጠቀመውን ‹‹የውሃ ጉድጓድ›› መምረጥ የአንተ ድርሻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር እርዳታ ከጎንህ ቢሆንም፣ ምርጫ የማድረግ ሃላፊነት የራስህ ነው፡፡

‹‹ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፣ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።›› -ኤፌሶን 4፡22-24

በኤፌሶን 4፡22-24 መሠረት ምን አስወግደን ምን መልበስ አለብን?

ትክክለኛ የሚመስልህ አረፍተ ነገር ላይ አክብብ፡፡

  1. ‹‹አስወግዱ››፣ ‹‹ልበሱ›› የሚሉት ነገሮች፣ የእኔን ድርሻ መወጣት ሳይጠይቁ እንዲሁ በእኔ ሕይወት ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮች ናቸው፡፡
  2. ‹‹አስወግዱ››፣ ‹‹ልበሱ›› የሚሉት ነገሮች፣ የእኔን ፈቃድና የታሰበ ምርጫዬን የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የአሮጌው ተፈጥሮ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር አስተሳሰብ አንፃር፡-

‹‹አይቻልም›› – ሁሉ ነገር ይቻላል፡፡ -ሉቃስ 18፡27

‹‹ግራ ተጋብቻለሁ፡፡›› – መንገድህን እመራሃለው፡፡ -ምሳሌ 3፡5-6

‹‹አልችልም›› – እኔ እችላለሁ፡፡ -2ቆሮንቶስ 9፡8

‹‹ብርቱ አይደለሁም፡፡›› – አበረታሃለው፡፡ -ፊሊፕሲዮስ 4፡13

‹‹ኑሮን ልቋቋመው አልቻልኩም›› – በሚያስፈልግህ ሁሉ እሞላብሃለው፡፡ -ፊልፕሲዮስ 4፡19

‹‹ከምችለው በላይ ነው›› – ‹‹እረዳሃለው›› -ኢሳይያስ 41፡10

‹‹ሰግቻለሁ፡፡›› – ስጋትህን እኔ እወስደዋለሁ፡፡ -1ጴጥሮስ 5፡7

‹‹ከመጠን በላይ ደክሞኛል፡፡›› – አሳርፍሃለው፡፡ -ማቴዎስ 11፡28-30

‹‹ማንም አይወደኝም፡፡›› – ሁል ጊዜ እወድሃለው፡፡ -ሮሜ 8፡38-39

‹‹ፈርቻለሁ፡፡›› – ሰላሜን እሰጥሃለው፡፡ -ኢሳይያስ 26፡3

እንግዲህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ ለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። -ሮሜ 12፡1-2

ከላይ የቀረበው ጥቅስ ሦስት ትዕዛዞችን በውስጡ ይዟል፡፡ አንደኛው በቁጥር 1 ላይ የሚገኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቁጥር 2 ላይ ይገኛል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሶስት ትዕዛዞች ምንድን ናቸው?

  1. ________________________________________________
  2. ________________________________________________
  3. ________________________________________________
  4. ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በጻፈው በዚህ ክፍል ውስጥ ‹‹ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያው መስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ›› ሲል ምን ማለቱ ነው?
  5. ‹‹ይህን አለም መምሰል›› የምናቆመው እንዴት ነው?

አእምሮህን ማደስ

በሮሜ 12፡1-2 ላይ ከቀረቡት ትዕዛዞች መካከል አንዱ ‹‹የልባችንን (አእምራችንን) መታደስ›› ይመለከታል፡፡ አእምሮአችን፣ ከተበከለው የአሮጌ ተፈጥራችን ጉድጓድ ውኃ መቅዳት ትቶ መለኮታዊ ምንጭ ከሆነው አዲሱ ተፈጥራችን መቅዳት እንዲጀምር መማር (መሰልጠን) አለበት፡፡ ይህንን እንዴት ማድረግ እንችላለን? ሁለት ቁልፍ ስልቶች እነሆ፡-

  1. ያለማቋረጥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት 

መንፈስ ቅዱስ፣ የ ‹‹መታደስ›› ውጤትን በሕይወታችን ላይ እንደሚያመጣ በምዕራፍ 3 ላይ አይተናል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ውስጥ በመሆን ሃይል እየተሞሉ የመኖር አስፈላጊነትን በተመለከተ ቲቶ 3፡5 ምን ይለናል?

የሁለቱ የውኃ ጉድጓዶች ተረት -ክፍል 4

በመሆኑም፣ ምንም እንኳ አስቸጋሪ ቢሆንም ከአዲሱ የውኃ ጉድጓድ ብቻ ለመጠቀም አንዳቸው ሌላቸውን በማስታወስ ለመረዳዳት ገበሬውና ቤተሰዎቹ ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ ይህን ማድረግ ከጀመሩ ከረጅም ጊዜ በኋላ በሕይወታቸው ላይ ሦስት ነገሮችን ማስተዋል ቻሉ፡- (1) ወደ አዲሱ የውኃ ጉድጓድ የሚያደርጉት ጉዞ ቀሊል ስለሆነላቸው ደካማና ታማሚ መሆናቸው ቀረ፣ (2) ከአሮጌው የውኃ ጉድጓድ መጠቀም ካቆሙ ረጅም ጊዜ ስላለፋቸው ወደ ጉድጓዱ የሚወስደውን መንገድ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆነ፣ እና (3) ከቤታቸው ወጥተው ውኃ ለማግኘት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ግራውን መታጠፊያ ትተው ቀኙን መከተል አሁን ተፈጥራዊና፣ ሳያስቡት የሚያደርጉት ልማዳቸው መሆን ጀመረ፡፡

‹‹እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፣ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤›› -ቲቶ 3፡5

  1. ያለማቋረጥ የእግዚአብሔርን ቃል መመገብ 

የመታደስ ሂደት ሌላው ስያሜ ‹‹መቀደስ›› ነው፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ 17፡17 ላይ ስለ መቀደስ ሲፀልይ የተናገረውን አንብብ፡፡ ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።›› ዮሐንስ 17፡17

ተጨማሪ ምልከታ፡- ‹‹መቀደስ›› ማለት መንፃት፣ ለተቀደሰ አላማ መለየት ማለት ነው፡፡

አብ በቃሉ እንዲቀድሰን ኢየሱስ ወደ አባቱ ከፀለየልን፣መጽሐፍ ቅዱስን ባማቋረጥ ስለማጥናት ከዚህ ምን ረዳለህ?

የሁለቱ የውኃ ጉድጓዶች ተረት -ክፍል 5

ገበሬውና ቤተሰቡ ከተበከለው የውኃ ጉድጓድ መጠቀም ማቆም በእርግጥ ይሹ ነበር፡፡ ጊዜ በሄደ ቁጥር ወደ አዲሱ የውኃ ጉድጓድ ለመሄድ የሚያበረታታቸው መልካም ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ወደ አዲሱ የውኃ ጉድጓድ በሄዱ ቁጥር መንገዱ እየቀና ከበፊቱ ይልቅ አመቺ እየሆነ መምጣት ጀመረ፡፡ እናም ጉድጓዱን ለማግኘት እየቀለላቸው ሄደ፣ ከጉድጓዱም የመጠቀም ልማድ ማዳበር ጀመሩ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ወደ አሮጌው የውኃ ጉድጓድ የሚወስደው መንገድ ደግሞ ለመተላለፍ ከባድና ጉድጔዱንም ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጣ፡፡ በተቃራኒው፣ ይህን ትተው ወደ አሮጌው የውኃ ጉድጓድ መጓዝ በሚጀምሩበት ጊዜ ደግሞ ወደ ጉድጓዱ የሚያደርጉት ቀጣይ ጉዞ ቀላል እየሆነ የአዲሱ ጉድጓድ መንገድ ደግሞ አስቸጋሪ መሆን ይጀምር ነበር፡፡

ገበሬውና ቤተሰዎቹ ያለማቋረጥ ከአዲሱ የውኃ ጉድጓድ መጠቀም ሲጀምሩ መለማመድ የጀመሩትን ሦስት ጥቅሞች በራስህ አባባል ግለጽ።

  1. _________________
  2. _________________
  3. _________________

ክርስቲያን ያለማቋረጥ በመንፈስ መጓዝ ሲጀምርና የእግዚአብሔርን ቃል እያጠና በሕይወቱ ላይ ሲተገብር የሚለማመዳቸው ከላይኛው ሃሳብ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሶስት ጥቅሞችን ዘርዝር።

  1. _______________
  2. _______________
  3. _______________

በየጊዜው እግዚአብሔርን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት እና በሌሎችም ጉዳዮች መታዘዝ ስትጀምር፣ አእምሮህን (ልብህን) እያደስክ ነው፡፡ አእምሮህ አሮጌው ተፈጥሮህን ችላ እያለ ከአዲሱ ተፈጥሮ እንዲቀዳ እያሰለጠንከው ነው፡፡ ይህን በማድረግህም ‹‹አዲሱ ማንነትህን›› እያጠነከርክና እየቀደስክ ነው፡፡

  • መንፈስ ቅዱስ ሲወቅስህ ስትናዘዝና ንስሃ ስትገባ
  • መንፈስ ቅዱስ እንዲሞላህ ስትጠይቅ
  • መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና እና በሕይወትህ ላይ ተግባራዊ ስታደርግ
  • ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትሄድ (ከቅዱሳን ጋር ሕብረት ስታደርግ)
  • ስትጸልይ

የልብ ዝንባሌ አስፈላጊነት፡-

‹‹በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፣ ነገር ግን በፍጹም ልብ አይደለም።›› -2ዜና 25፡2

ንስሃ መግባት፡- ንስሃ ፊትን ከኃጢአት መልሶ ወደ እግዚአብሔር ዳግም መመለስን የሚጠይቅ የአስተሳሰብ ለውጥ ውጤት ነው፡፡

‹‹በመንፈስ ቅዱስን የተሞላና ጠቃሚ ሕይወት ለመኖር ቁልፉ ነገር ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዝ ነው፡፡ -ጆን ጂ. ሚሼል

እለት እለት መታደስህ፣ ከዚህ በታች እንደተዘረዘሩት አይነት አስቀያሚና፣ በሞትና በሕይወት መካከል ያሉ አማራጮች በሚገጥሙህ ጊዚያት፣ ምኞታቸውን ለመቋቋም ጠንካራ ትሆናለህ፣ ወደ ‹‹አሮጌው የውኃ ጉድጓድ›› የሚወስደውንም መንገድ ማግኘት አይሆንልህም፡፡ ወደ አእምሮህ የሚመጣው የመጀመሪያ ምላሽም ወደ አዲሱ የውኃ ጉድጓድ ጉዞ መጀመር ይሆናል፡፡

  • ዝሙት
  • አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀም
  • ስርቆት
  • ኢየሱስን መቃወም
  • ነፍስ ማጥፋት

በአጭሩ፡- እግዚአብሔርን በታዘዝከው ቁጥር፣ ለሚቀጥለው ጊዜ ለእርሱ ለመታዘዝ ቀላል እየሆነልህ ይመጣል፡፡ የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ዘላቂ የድል ሕይወት ይሰጥሃል!

ከሕይወትህ ጋር ማዛመድ፡-

  1. ልብህን ለመመርመር ጥቂት ጊዜ ውሰድ፡፡ እግዚአብሔር ልብህን መርምሮ በሕይወትህ ውስጥ ታዛዥ ያልሆንክባቸውን፣ ‹‹ከአሮጌው የውኃ ጉድጓድ›› የምትቀዳባቸውን፣ እና እርሱ በሕይወትህ ዙፋን ላይ እነዳይቀመጥ የተከለከለበትን የሕይወትህን ክፍሎች እንዲጠቁምህ ጠይቀው፡፡
  2.   እንድትናዘዘው፣ ንስሃ እንድትገባበት እና እንድታዝገዛለት የሚፈልገውን ነገር አሳይቶህ ከሆነ አሁኑኑ አድርገው!
  3. ‹‹ወደ አሮጌው ጉድጓድ›› ጉዞ በምትጀምርበት ወቅት ወዲያው መንቃት እንድትችል እና ፊትህን በተቃራኒው መንገድ እንድታዞር እንዲረዳህ ጌታን ጠይቀው፡፡
  4. ሁልጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እንዲኖርህና ታዛዥ እንድትሆን ይረዳህ ዘንድ ለምነው፡፡
  5.  በየእለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ጥቂት ጊዜ ለመውሰድና አምስት አስር ደቂቃም ትሁን በየእለቱ ለመጸለይ ውሳኔ አድርግ፡፡
  6. ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ሕብረት ለማድረግ ሁልጊዜ ወደ ቤተክርስቲን ለመሄድ ውሳኔ አድርግ፡፡
  7. እግዚአብሔር እድሉን ሲሰጥህ ለሌሎች ስለ ክርስቶስ ለመናገር ውሳኔ አድርግ፡፡

የቃል ጥናት ጥቅስ፡-

‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።›› -ሮሜ 12፡2

ማጠቃለያ

ኢየሱስ፣ ‹‹ልትታዘዘኝ ፈቃደኛ ነህ?›› ሲል ጥያቄ የቃርብልሃል፡፡

ምዕራፍ 5ትን ያጥኑ

Leave a Reply

%d bloggers like this: