በልጅነታቸው የሞቱ ሕጻናት እጣ ፈንታ ምንድን ነው? መንግስተ ሰማይ የነሱ ናትን?

በርካት የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን ሰው “የተጠያቂነት እድሜ” (age of accountability) ላይ እስኪደርስ ድረስ ለሃጢአቱ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ አይሆንም በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ። እናም፣ አንድ ሕጻን ተጠያቂ (accountable) የሚያደርገው እዚህ እድሜ ላይ ከመድረሱ በፊት ቢሞት፣ በእግዚአብሔር ጸጋና ምሕረት፣ መንግስተ ሰማይ ይገባል ብለው ያምናሉ። ለመሆኑ፣ “የተጠያቂነት እድሜ” ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? “የተጠያቂነት እድሜ” የሚባል ነገርስ አለ ወይ?

ሕጻናት የቱንም ያህል ሕጻን ቢሆኑና በተግባር ያደረጉት ሃጢአት (personal sins) ባይኖርም ከአዳም በወረሱት ሃጢአትን የማድረግ ዝንባሌ (የውርስ ሃጢአት) ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት ንጹሃን ሊሆኑ እንደማይችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የውርስ ሃጢአት፣ ከቤተሰቦቻችን የምንወርሰው የሃጢአተኝነት ባህሪይ (ሃጢአትን የማድረግ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ) ነው። ቅዱስ ዳዊት፣ ስለ ሃጢአተኛ ባህሪው ሲያወራ፣ “ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ። (መዝሙር 51:5 አ.መ.ት.)” ይላል። ቅዱስ ዳዊት ገና ከመወለዱ ጀምሮ ሃጢአተኛ እንደነበረ ባዚህ ክፍል ላይ ገልጿል። የአባታችን አዳም የመጀመሪያ ሃጢአት አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ሞት በሰው ዘር ሁሉ ላይ አምጥቷል። በዚህ ምክንያት፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ጎልማሳም ይሁን ሕጻን፣ ከእግዚአብሔር ክብር ጎድሏል፤ በእግዚአብሔርም ፊት በደለኛ ሆኗል። ሰዎች ለዚህ በደላቸው ይቅርታን ያሚያገኙበት ብቸኛ መንገድ ደግሞ ክርስቶስን በእምነት በመቀበል ነው (ዮሐ 14:6፣ ሐዋ. 4:12)።

እግዚአብሔር ለሰው ሃጢአት መድሃኒት አዘጋጅቷል። መዳኒቱም አንድ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ይባላል። እግዚአብሔር ያዘጋጀውን ይህን ነጻ መድሃኒት ተቀብሎ የራስ ማድረግ የሰው የግል ምርጫ ጉዳይ ነው። ይህንን የግል ምርጫ ወይም ውሳኔ ማድረግ ያማይችሉ ሕጻናት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው የሚለው ጥያቄ እዚህ ላይ አብሮ መልስ ሊያገኝ ይገባል። በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ “የተጠያቂነት እድሜ” (age of accountability) ሃሳብ ብቅ የሚለው። በዚህ ሃሳብ መሰረት ሕጻናት ይህን የግል ምርጫ ለማድረግ የሚችሉበት እድሜ ወይም ብስለት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ቢሞቱ በእግዚአብሔር ምህረትና ጸጋ ከእግዚአብሔር ፍርድ አምልጠው የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ምክንያቱም ሕጻናቱ ይህንን የታሰበበት ምርጫ ወይም ውሳኔ ማድረግ አይችሉምና። ሕጻናቱ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሰው ልጅ ያበረከተውን የመዳን ነጻ ስጦታ ተረድተው “እንቢ” ወይም “እሺ” ለማለት ያሚያስቸላቸው እድሜ (የተጠያቂነት እድሜ) ላይ እስኪደርሱ ድረስ ምንም እንኳ በውርስ ሃጢአት ምክንያት ሃጢአተኛ ቢሆኑም በእግዚአብሔር ልዩ አሰራር ከተጠያቂነት ነጻ ይሆናሉ። ይህን ሃሳብ የሚደግፍ ያሚመስል የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሮሜ 1:20 ላይ እናነባለን። “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ”። በዚህ ክፍል መሰረት፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ከፍርድ ላለማምለጥ ምክንያት የሌላቸው ስለእግዚአብሔር ሊያውቁ የሚገባቸውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ግልጽ አድርጎላቸው ሳለ እነርሱ ግን እግዚአብሄርን በእግዚአብሔርነቱ ላለማክበር ስላመጹ እነደሆነ እንረዳለን። ስለ እግዚአብሔር በግልጥ የሚታየውንና ያሚታወቀውን ነገር አይተውና አውቀው የሚቃወሙ ሁሉ በዚህ ጥቅስ መሰረት ከእግዚአብሄር ፍርድ አያመልጡም። ነገር ግን፣ ይህን እግዚአብሔር የገለጠውን ነገር ለማየትም ሆነ ለመረዳት የሚችሉበት እድሜ ላይ ያልደረሱ ሕጻናት ከተጠያቂነትም ሆነ ፍርድ ነጻ ይሆናሉ።

ሕጻናት ለተጠያቂነት የሚደርሱበትን የእድሜ ቁጥር በእርግጠኝነት ማስቀመጥ አዳጋች ነው። በአይሁድ ባህል፣ አንድ ሕጻን ወደ አዋቂነት የሚሸጋገርበት እድሜ 13 ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እድሜ አንድ ሕጻን ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚሸጋገርበት እድሜ እንደሆነ አይነግረንም። የእድሜውን ቁጥር ማስቀመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም አንድ ልጅ ክርስቶስን ለመቀበል ወይም ላለመቀበም የእምነት ውሳኔ ማድረግ ያሚችልበት እድሜ ላይ ከደረሰ እዚህ የተጠያቂነት እድሜ ላይ መድረሱን አመላካች ይሆናል።

ይህን “የተጠያቂነት እድሜ” (age of accountability) ሃሳብ የሚደግፍ ያሚመስለው ሌላኛው መጽሃፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ደግሞ በ 2ሳሙ 12:21-23 ላይ ይገኛል። የዚህ ክፍል ሃሳብ በአጭሩ እንዲህ ነው፦ ንጉስ ዳዊት ባለቤቱ ካልሆነች ቤርሳቤህ ከምትባል አንዲት ሴት ጋር ያመነዝርና ሴቲቱ ልጅ ትወልዳለች። እግዚአብሔር ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ልኮ፣ ዳዊት በሰራው ሃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር የዳዊትን ልጅ በሞት እንደሚወስደው ይነግረዋል። በምላሹ፣ ዳዊት ልጁ እንዳይሞት በእግዚአብሔር ፊት ያዝንና ይጾም ይጀምራል። ነገር ግን እግዚአብሔር ሕጻኑን እንደተናገረው በሞት ወሰደው። ዳዊትም ልጁ እንደሞተ ባየ ጊዜ ሃዘኑን ተወ፤ ጾሙኑም ገደፍ። ይህንን ያዩ የዳዊት አገልጋዮች፣ ዳዊትን፣ “ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፤ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት።” የዳዊትም መልሲ፣ “…ሕፃኑ ሕያው ሳለ፦ እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቅሰሁም። አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ።” በሌላ አነጋገር፣ ዳዊት አሁን ልጁን ከሞት ወደ ሕይወት ማምጣት ባይችልም፣ ዳዊት ሲሞት፣ ልጁን በእግዚአብሔር መንግስት ዳግምኛ እንደሚያየው ያሰበ ይመስላል።

እግዚአብሔር የተጠያቂነት እድሜ ላይ ያልደረሱ ሕጻናትን እና ከጢአን መጓደል የተነሳ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ ያማይችሉ በሽተኞችን ከፍቅሩና ርህራሄው የተነሳ በክርስቶስ ለሰው ልጆች ያደረገውን የቤዛነት ስራ ለእነርሱም ቆጥሮ በእምነት ጌታ ኢያሱስን ከተቀበሉ ሰዎች ጎራ ማለትም በመንግስተ ሰማይ እንደሚያኖራቸው ማመን አመክኗዊ ብሎም ስነ መልኮታዊ ህጸስ የሌለበት ቢመስልም ሃሳቡን እንደማንደራደርበት የበዶክትሪን አቋም ልንይዘው ግን አይገባም። ሆኖም፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ግን ተመሳሳይ አቋም ልንይዝ እንችላለን። ይህም እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ፤ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ትክክል እንደሆነ እና እግዚአብሔር እኛ ከምንወዳቸው በላይ ሕጻናትን እንደሚያፈቅር።

1 thought on “በልጅነታቸው የሞቱ ሕጻናት እጣ ፈንታ ምንድን ነው? መንግስተ ሰማይ የነሱ ናትን?”

  1. ዕይታችንን እንድናሰፋ እና መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ልምድ ከፍ እንድናደርግ የምረዳ ማብራሪያ ነው፣ በፀጋው ጌታ ይደግፍህ።

Leave a Reply

%d bloggers like this: