“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤” ምሳሌ 3:5
በራስ የመተማመን ዝንባሌ (predisposition toward independence) የሰው ልጆች ችግር ‹‹ሥር›› ከመሆኑ ባሻገር እኛ እና አለሙ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ለምናደርገው አመፅ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ሰይጣን እኛን ለማጥመድ ከሚጠቀምባቸው ዋነኛና ስኬታማ ማማለያዎቹ መካከል ይህ ዝንባሌያችን ቀዳሚውን ረድፍ ይይዛል ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም።
የሰይጣን ዋና የጦር ስልት፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ባሕሪ ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር እግዚአብሔር ሊታመን የማይችል አምላክ እንደሆነ ማሳመን እና በራሳቸው ማስተዋል ላይ እንዲደገፉ ማግባባት ነው፡፡ በዘፍጥረት 3፡1-5 ላይ ተመዝግቦ ባለው የአዳምና ሔዋን ታሪክ ውስጥ ሰይጣን፣ እግዚአብሔር ከአዳምና ሔዋን አንዳች የሚጠቅም ነገር የደበቀባቸው፣ የእነርሱን መልካም ነገር የማይሻ፣ እና ሊታመን የማይችል አምላክ መሆኑን በእጅ አዙር ነግሮና በውስጣቸው ጥርጥርን ዘርቶ እግዚአብሔርን ውሸታም ለማድረግ ያደረገውን ሴራ እናያለን፡፡
ዘፍ. 3፡1-5 እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ ነበረ፡፡ ሴቲቱንም፡- በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዟልን? አላት፡፡ ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፡- በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም፡፡ እባብም ለሴቲቱ አላት ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙን እና ክፉውን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡
አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ ጊዜ እንደሌሎቹ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ፣ እንከን የለሽ (perfect) ነበሩ፡፡ ሙሉ፣ ምንም ያልጎደላቸውና ፍፁም የረኩ (complete and totally satisfied beings) ነበሩ፡፡ ያደርጉት የነበረው ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ባሕሪ አንፃር የተጣጣመና የተዋሀደም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ሞት አልነበረም፡፡ ሞት ወደ አለም የገባው ከውድቀታቸው በኋላ መሆኑን የሚከተሉትን ሁለት ጥቅሶች መገንዘብ በቂ ነው – “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ አለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ …” ሮሜ. 5፡12። “ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ … ሁሉ በአዳም እንደ ሚሞቱ …” 1ቆሮ. 15፡21-22።
አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን መደገፍ ወደጎን በመተው፣ በራሳቸው ላይ በመተማመን፣ ሰይጣን በእግዚብሔር ባሕሪ ላይ የተናገረውን የውሸት ቃል አደመጡ፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪም በራሳቸው አይን እርካታን ለማግኘት ተራመዱ፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው መታመን ለመውጣት መወሰናቸውን የሚያመላክቱ ሦስት ማሳያዎች በጥቅሱ ውስጥ ተካትተው እናነባለን፡፡ (1) የሰው ማስተዋል/human understanding (ለጥበብ መልካም እንደሆነ አዩ)፣ (2) የሰውነት ፍላጎት/appetites of the body (ለመብላት ያማረ እንደሆነ አዩ)፣ እና (3) ገንዘብ ማድረግ ወይም የራስ ማድረግ/possessions (ለዓይን እንደ ሚያስጎመጅ አዩ)፡፡ ዛሬም ቢሆን የዘወትር ፈተናዎቻችን ከነዚህ በአንዱ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ‹‹በራስ የመተማመን ዝንባሌ›› (predisposition toward independence) የሰው ልጆች ችግር ‹‹ሥር›› ከመሆኑ ባሻገር እኛ እና አለሙ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ለምናደርገው አመፅ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
ዘፍ. 3፡6 ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች ከፍሬውም ወሰደችና በላች ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፡፡
በሰው ዘር ውስጥ የተወለደ ማንኛውም ግለሰብ፣ የአዳምን ኃጢአተኛ ባሕሪ ተካፍሏል፡፡ ማንኛውም ሰው ሲወለድ እግዚአብሔርን የመቃወም ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ይዞ ይወለዳል፡፡ ዘፍ. 5፡3 አዳምም ሁለት መቶ ሰላሳ አመት ኖረ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው፡፡ “እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” መዝ 51፡5። “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና” ኢዮ 15፡14። በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡- ኤር 17፡9 እና መክ 9፡3፣ ገላ. 5፡17፣ ኤፌ. 2፡2፣ ምሳ. 22፡15፣ ዘፍ. 8፡21፣ መዝ 14፡2-3። ይህ ዝንባሌው የስጋዊ ሕይወቱ ዋነኛ ጡንቻ ነው። ይህ ዝንባሌው የሃጢአታዊ ባሕሪው ጉልበት ብቻ ሳይሆን ምንጭም በመሆን ያገለግላል። ሃጢአቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ካለመታመን ይመነጫሉ። አባታችን አዳም በራሱ ማስተዋል ላይ ለመደገፍ በመወሰን ሞትን ወደ አለመ ጠራ። በመልኩ የተወለዱ ልጆቹም ፍጹም የሆነውን መዋጀታቸውን በተስፋ እየጠበቁ በእግዚአብሔር ላይ በመታመንና ባለመታመን ነፍሳዊ ትግል ውስጥ ላይና ታች ሲሉ ዘመናትን ቆጠሩ።
ጊዜው ሲደርስም፣ ለዚህ ጥያቄ ዘላለማዊ መልስ ይዞ ኢየሱስ በሰው የዘር ግንድ ውስጥ ተወለደ። በሰው ዘር ግንድ ውስጥ ይወለድ እንጂ እርሱ ሃጢአት አልነበረበትም፤ ኃጢአት ከሌለበት አባት ተወልዷልና፡፡ ኋለኛው አዳም (ኢየሱስ)፣ ከውድቀት በፊት እንደ ነበረው ፊተኛው ሰው አዳም ኃጢአት የለሽ ማንነትን ይዞ ተወለደ፡፡ ኢየሱስ በሕይወቱ ዘመን ያሳየው ቅዱስ ባሕሪ፣ እግዚአብሔር ለአዳም አስቀድሞ የወሰነለት ባሕሪ ነበር፡፡ “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተፅፋል ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም” ቆሮ. 15፡45-46። “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ፃድቃን ይሆናሉ” ሮሜ. 5፡19።
ልክ አዳም እንደ ተፈተነ ኢየሱስም በተመሳሳይ ሦስት አቅጣጫዎች ላይ ተፈተነ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሰይጣን ያቀረበለትን በራስ የመታመን ግብዣ ወደጎን በመተው ራሱን በእግዚአብሔር ጥበቃ ስር አሳልፎ በመስጠት ለመኖር ወሰነ (ማቴ. 4:1-10)፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ፈጽሞ በመደገፍ ሊኖር የሚችለውንም የድል ሕይወት ኖሮ አሳየን።
ዮሐ. 5፥30 እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።
ዮሐ. 6፥38 ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።
ዮሐ. 7፥16 ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤
ዮሐ. 8፥29 የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም አላቸው።
ዮሐ. 4፥34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።
ዮሐ. 17፥4 እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤
የውድቀታችን መሰረት በራሳችን ማሰተዋል ላይ ለመታመን ያደረግነው ቁርጠኝነት እንደሆነ ሁሉ የድላችን መሰረት ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ በፍጹም ልባችን መታመናችን ነው። “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤” ምሳሌ 3:5