ሮሜ 5፡1-21

  1. ኃጢአተኛው በእግዚአብሔር ከጸደቀ በኋላ የሚቀበላቸው በረከቶች (ሮሜ 5፡1-11)

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 5፡1-11 አንብብ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሚያምኑ ሰዎች የሚሰጣቸውን የተለያዩ በረከቶች ዘርዝር።

አብርሃም በእምነቱ ምክንያት ተስፋ የተገባለትን ልጅ አግኝቷል። እኛስ ክርስቶስን ብቸኛ የድነት (የደኅንነት) መንገድ እንደሆነ ስናምን ምን እናገኛለን? ጳውሎስ ብዙ ልንደርስባቸው የምንችልባቸውን በረከቶችን ዘርዝሯል።

ሀ. ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ይኖረናል። ከእንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር እየተዋጋን ከፍርዱ ሥር የምንኖር ጠላቶቹ አንሆንም። የበረከትና የሰላም ግንኙነት እንመሠርታለን።

ለ. የእግዚአብሔር የክብር ተስፋ አለን። በአዲስ ኪዳን፥ ብዙውን ጊዜ «ተስፋ» የሚለው ቃል በመንግሥተ ሰማይ የኋላ ኋላ የድነት (ደኅንነት) ማረጋገጫ እንደሚጠብቀን ያሳያል። ጳውሎስ በእምነታችን መንግሥተ ሰማይ በምንደርስበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን እንደምናገኝ ያሳያል።

ሐ. ስደትና መከራ ቢያጋጥሙን እንኳን ድፍረት ይኖረናል። በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰተው መከራ የእግዚአብሔርን ቅጣት ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ ሊያከናውን የሚፈልገውን መልካም ነገር እንደሚያሳየን በእምነት እንረዳለን። መከራ እግዚአብሔር ለመንፈሳዊ ዕድገታችን ከሚጠቀምባቸው ዐበይት መሣሪያዎች አንዱ ነው።

መ. የእግዚአብሔርን ፍቅር ወደ ልባችን የሚያፈስ መንፈስ ቅዱስ ይሰጠናል። በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚወደን የሚያሳይ ምልክት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን እንድንወድ የሚያስችለን ነው።

ሠ. ጸድቀናል። በክርስቶስ ሞትና በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ ምክንያት «ጥፋተኞች አይደላችሁም» ተብለናል።

ረ በኃጢአተኞችና ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ከሚደርሰው የእግዚአብሔር የፍርድ ቁጣ ድነናል።

ሰ. በክርስቶስ ሕይወት ድነናል። ክርስቶስ ከሞት በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔር አብ ለኃጢአታችን ያቀረበውን መሥዋዕት ተቀብሎ አዲስ የድነት (የደኅንነት) መንገድ እንደከፈተ ያሳያል።

ሸ. ከፈጣሪ አምላካችን ጋር ታርቀናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ በረከቶች ሁሉ ለአንተ ጠቃሚዎች የሆኑባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር አብን፥ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ለአንተ ስላላቸው በረከትና ፍቅር አሁኑኑ አመስግናቸው።

  1. ኃጢአትንና ሞትን ወደ ዓለም ያመጣው የመጀመሪያው አዳም ሕይወትንና ጽድቅን ወደ ዓለም ካመጣው ሁለተኛው አዳም ጋር ሲነጻጸር (ሮሜ 5፡12-21)

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 5፡12-21 አንብብ። ሀ) በአዳምና በክርስቶስ መካከል የሚገኙት ልዩነቶችና ተመሳሳይነቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ክርስቶስ ከአዳም የሚበልጠው እንዴት ነው?

ጳውሎስ ክርስቶስ በእምነት የተቀበልነውን ድነት (ደኅንነት) በመስጠቱ ያከናወነውን ታላቅ ተግባር ለማሳየት ሲል ከአዳም ጋር አነጻጽሮታል። በጳውሎስ አእምሮ፥ በአዳምና በክርስቶስ መካከል አንድ ዐቢይ መመሳሰል አለ። ይኸውም ሁለቱም የሕዝብ ሐረግ ጅማሬዎች መሆናቸው ነው። አዳም የሰው ዘር ጅማሬ ነበር። ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሕዝብ ጅማሬ ነው። የሕይወታቸው ውጤት ግን በጣም ይለያያል። አዳም እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ ምክንያት ኃጢአትን ፈጸመ። ይህም ዘሮቹ የሰው ልጅ በሙሉ) ከእርሱ የኃጢአትን ተፈጥሮ እንዲያገኙና ይህም ኃጢአተኛ ተፈጥሮአቸው ወደ ሞት እንዲነዳቸው አድርጓቸዋል። እያንዳንዱ ልጅ የሚወለደው እግዚአብሔርን የሚያሳዝን የኃጢአት ተፈጥሮ ይዞ ነው። ከኃጢአት ዐበይት ውጤቶች አንዱ ሞት በመሆኑ፥ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሞት ከአዳም ወደ ዘሮቹ ተላልፎአል። የአንድ ሰው ኃጢአት በታሪክ ሁሉ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ኃጢአትን እንዲፈጽሙ አድርጓል።

«ስጦታው» ተብሎ የሚጠራው ወይም «ሁለተኛው አዳም» የተባለው ክርስቶስ ከመጀመሪያው አዳም ይበልጣል። የእግዚአብሔር መለኮታዊና ሰብአዊ ልጅ የሆነው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት በታሪክ ሁሉ ለኖሩ በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የኃጢአትን ዋጋ ከፍሏል። አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ በመሞቱ፥ ከአዳም ዘመን ጀምሮ እስከ ታሪክ ፍጻሜ ድረስ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ኃጢአቶች የሠሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በክርስቶስ በማመን በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት «ጥፋተኞች አይደላችሁም» ሊባሉና ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሊጀምሩ ይችላሉ።

ጳውሎስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ሰዎች ሁሉ ወዲያውኑ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኛሉ ማለቱ እንዳልሆነ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ሁለት አስፈላጊ ነገሮች ይከሰታሉ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ በመሞት በታሪክ ለኖሩ ሰዎች ሁሉ የሚሆን እምቅ ይቅርታ አስገኝቷል። ድነት (ደኅንነት) ሰው ሁሉ ሊያገኘው የሚችል ነገር ቢሆንም፥ ድነቱን የሚቀበሉት ግን በግላቸው ኢየሱስን በማመን ብቻ ነው። ሁለተኛ፥ አንድ ሰው ምንም ያህል ኃጢአት ቢሠራም በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት በማመን ጻድቅ ነህ ሊባልለት ይችላል። አሁን ሕይወት አለን። ይህም ሕይወት፥ ባመንን ጊዜ ከመቅጽበት የምናገኘውን መንፈሳዊ ሕይወትና አዳም ወደ ዓለም ያመጣውን ሞት የሚያሸንፍ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘትንም የሚያካትት ነው።

እንግዲህ የሕግ ዓላማ ምንድን ነው? አንደኛው ዓላማ ኃጢአት የመስራት አቅማችንን ግልጽ በማድረግ የሰውን ልጅ ኃጢአተኛ ልብ ማሳየት ነው። «በደል» የእግዚአብሔርን ሕግ መተላለፍን ያሳያል። ጳውሎስ ቀደም ሲል ሕግ በሌለበት የበደል ሕግ እንደሌለ ገልጾአል (ሮሜ 4፡15)። ሰዎች ኃጢአትን መሥራታቸው ባይቀርም ኃጢአተኝነታቸው እንደ አለመታዘዝ በግልጽ አይታይም። ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕግ በተገለጠ ጊዜ፥ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ባይሰጥም በእምነት የሚገኘውን የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ ይሹ ዘንድ ኃጢአተኝነታቸውን አሳይቷቸዋል። የጳውሎስ የኃጢአት ተፈጥሮ የተረጋገጠው ስላለመመኘት የሚናገረውን ሕግ በሰማ ጊዜ ነበር።

ሰዎች እያወቁ የእግዚአብሔርን ሕግ ከተላለፉ በኋላ አስከፊ ኃጢአተኝነታቸውን፥ በፈቃዳቸው እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ መፈለጋቸውን ይገነዘቡና ምሕረትን ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይላሉ። እግዚአብሔር አሁንም ስለሚወዳቸው በአስደናቂ ጸጋው ጽድቅን በማጎናጸፍ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል። ይህንንም የሚያደርገው ግን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያከናወነላቸውን ተግባር በእምነት ከተቀበሉ ብቻ ነው። ጥረትን የማይጠይቀውና እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰዎች በነፃ የሚሰጠው ጸጋ ሞትን ካመጣው ከሰዎች ኃጢአት በላያቸው ላይ ከነገሠው የበለጠ ነው። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንድናደርግና የዘላለምን ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ለአንድ ሃይማኖተኛ “ክርስቲያን” እየመሰከርህለት ሳለ የድነትን መንገድ በግልጽ ለማብራራት ትፈልጋለህ እንበል። ስለ እግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) መንገድ በሮሜ መልእክት ውስጥ ከተማርከው አሳብ በመነሣት የድነትን መንገድ እንዴት አድርገህ እንደምትገልጽ ጠቅለል አድርገህ አስረዳ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ሮሜ 5፡1-21”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading