አማኞች ብዙውን ጊዜ ከኃጢአት ባሕርያቸው ጋር ይዋጋሉ። ለሽንፈትም ይዳረጋሉ (ሮሜ 7፡7-25)።

ጳውሎስ ሕጉ የገለጣቸው የኃጢአት ምኞቶች በሕይወታችን ውስጥ የሚታየው የኃጢአት ችግር አካላት መሆናቸውን ገልጾአል። የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ለሚያከብረው አይሁዳዊ ይህን መቀበሉ አስቸጋሪ ነበር። የእግዚአብሔር ሕግ መልካም ነው። መልካም የሆኑት የእግዚአብሔር ሕግጋት እንዴት የክፋት መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ? ጳውሎስ ችግሩ ያለው ከሕጉ ሳይሆን ከኃጢአት ባሕሪያችንና ለእግዚአብሔር ሕግጋት ከሚሰጠው ምላሽ እንደሆነ ገልጾአል። ለልጅ፥ «ድስቱ ይፈጅሃልና አትንካው» ብትለው፥ ምን ያደርጋል? እጁን ዘርግቶ ወዲያውኑ ወደ ድስቱ ሄዶ ይነካዋል። የሕግም ሁኔታ እንዲሁ ነው። ጳውሎስ የራሱን ገጠመኝ ጠቅሶ አሳቡን ያብራራል። ይህ ምናልባትም በ13 ዓመቱ መደበኛ የሕግ ትምህርት በሚከታተልበት ጊዜ የገጠመው ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ሕጉ እንደ እግዚአብሔር መልካም፥ ቅዱስና ጻድቅ ነው። ነገር ግን የኃጢአት ባሕሪያችን ስለ ሕግ በሚሰማበት ጊዜ፥ በመጀመሪያ ማድረግ የምንፈልገው ነገር ሕጉን መጣስ ነው፡፡ ሕይወትን ሊያመጣልን የተገባው ሕግም በተዘዋዋሪ መንገድ ግለሰቡ ኃጢአት ሠርቶ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲጋፈጥ ይገፋፋዋል። ችግሩ ያለው ከሕጉ ሳይሆን ከኃጢአተኛው ባሕሪያችን ነው። ስለሆነም፥ ሕጉ የዘላለምን ሕይወት ለማምጣት የሚያገለግል መሣሪያ ሳይሆን፥ የሰውን ልብ ኃጢአተኝነት በማሳየት የእግዚአብሔርን ጸጋና ጽድቅ እንዲሻ የሚያደርግ ነው።

ሮሜ 7፡14-25 በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ክርክር አስነሥቷል። ይህ የጳውሎስ ምስክርነት ነው ወይስ ምሳሌ ብቻ? ጳውሎስ የሚጽፈው ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ስለተከሰተው ሁኔታ ነው ወይስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት? ይህ ጳውሎስ ክርስቶስን አግኝቶ ከመፈወሱ በፊት ያጋጠመው ሁኔታ እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች የሚከተሉትን አሳቦች ይጠቅሳሉ። 1) የኃጢአት ባሪያ ለመሆን የተሸጥሁ፥ በእኔ ምንም መልካም የለም፥ ምንኛ ጎስቋላ ነኝ የሚሉ ዓይነት አገላለጾች ለክርስቲያኖች ያገለገሉ አይደሉም። 2) ጳውሎስ በሮሜ 8 ውስጥ ከሚያስተምረው አሳብ ጋር አይመሳሰልም። 3) እግዚአብሔር የሚሰጠን ድነት (ደኅንነት) ከኃጢአት ያወጣናል እንጂ በባርነት ውስጥ አያኖረንም። ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ያጋጠመውን ሁኔታ እየገለጸ ነው የሚሉት ደግሞ የሚከተለውን አሳብ ይሰነዝራሉ። 1) ጳውሎስ የተጠቀመባቸው የአሁኑ ጊዜ መግለጫ ግሦች የድሮውን ሳይሆን የአሁኑን ሕይወት ያሳያሉ። 2) በዓውደ ንባቡ ውስጥ ጳውሎስ የሚናገረው አንድ ሰው ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ሳይሆን ክርስቲያን ከሆነ በኋላ እንዴት የተቀደሰ ሕይወት እንደሚኖር ነው። 3) ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ሕግጋት መልካምነትና ለእግዚአብሔር ሕግጋት መልካምነት የሰጠው ምስክርነት ክርስቲያን ያልሆነ ሰው የሚያደርገው ነው።

24ኛ ጥያቄ ሀ) በሕይወትህ እንደ ጳውሎስ ከኃጢአት ጋር ታግለሃል? ትግሉ እንዴት እንደተካሄደ ግለጽ። ለ) ጳውሎስ የጠቀሰው ገጠመኝ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ወይስ በኋላ የተፈጸመ ይመስልሃል? ለምን?

ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቱ እያደገ በሚሄድበት ጊዜ ስለሚያጋጥመው ተከታታይ ጦርነት የሚናገር ይመስላል። አንድ ሰው ክርስቲያን ከሆነበት ጊዜ አንሥቶ፥ ከኃጢአተኛ ተፈጥሮው ጋር ለመታገል እንደሚገደድ ገላትያ 5፡16-26 ያስረዳል። እግዚአብሔርን ለማክበር የሚፈልገው አዲሱ መንፈሳዊ ባሕርዩ ባለማቋረጥ ከአሮጌው የኃጢአት ባሕርዩ ጋር ይዋጋል። ጳውሎስ ችግሩ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን አለማወቁ ሳይሆን ለመፈጸም አለመቻሉ እንደሆነ ገልጾአል። ንጹሕና ቅዱስ ለመሆን የሚደረገው ጦርነት ቀጣይነት ያለው ሲሆን፥ ብዙውን ጊዜ የኃጢአት ባሕርይ የሚያሸንፍ ይመስላል። ለመፈጸም የማንፈልጋቸውን ኃጢአቶች እንፈጽማለን።

(ማስታወሻ፡ «አሮጌ ተፈጥሮ» እና «ሥጋ» የሰውን ውጫዊ የሥጋ አካል የሚያመለክቱ አይደሉም። ነገር ግን በውስጣችን ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ለማመፅ የሚፈልገውንና ከመገዛት ይልቅ መግዛት የሚሻውን የኃጢአት ባሕርይ የሚያመለክቱ ናቸው። የተለያዩ የኃጢአት ውጤቶች የሚመጡት ከዚህ የኃጢአት ባሕርይ ነው።)

ሁኔታው ተስፋ የሌለው ነውን? ለዚህ የማያቋርጥ ውጊያ ምላሽ አለን? የእግዚአብሔርን ሕግ ለመታዘዝ እየፈለግሁ ብዙውን ጊዜ የምተላለፍ ከሆነ፥ እግዚአብሔር የሚመለከተኝ እንዴት ነው? ይኮንነኛል? መልሱ በሮሜ 8 ውስጥ ሰፍሯል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “አማኞች ብዙውን ጊዜ ከኃጢአት ባሕርያቸው ጋር ይዋጋሉ። ለሽንፈትም ይዳረጋሉ (ሮሜ 7፡7-25)።”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: