ጳውሎስ አንድነትንና ለክርስቶስ መኖርን ማበረታታቱ እና አማኞች ስላበረከቱት ስጦታ ምስጋናውን ማቅረቡ (ፊልጵ. 4፡1-23)

፩. ጳውሎስ አንድነትንና ለክርስቶስ መኖርን ያበረታታል (ፊልጵ. 4፡1-9)

አንድን ሰው በምትወድበት ጊዜ ከሁሉም የሚሻለውን እንዲያገኝ ትፈልጋለህ። ከሁሉም የሚሻለው ሁልጊዜም እነርሱ ከሁሉም ይሻላል የሚሉት ሳይሆን በዘላለማዊ መንግሥት ብርሃን የላቀው ነው። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞችን ከልቡ ስለሚወድ የተባረከ ሕይወት ያገኙ ዘንድ ሊያከናውኗቸው የሚገቧቸውን ነገሮች ያስታውሳቸዋል።

ሀ. አንድ መሆን ይኖርባቸዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱን በደንብ ስለሚያውቅ፥ ጳውሎስ የሚጣሉትን ሁለት ሰዎች በማገዝ እንዲያስታርቋቸውና በሰላም እንዲኖሩ እንዲያግዟቸው ይጠይቃል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነትን መፍጠሩ የሁሉም ሰው ሥራ ስለሆነ፥ ከሐሜትና ቲፎዞነት ይልቅ እነዚህን ሴቶች ለማስማማት እንዲጥሩ ተጠይቀዋል።

ለ. የፊልጵስዩስ አማኞች ሁኔታቸውን አሸንፈው እንዲኖሩ ተበረታተዋል። ስደት በጳውሎስ ላይ እንደ ደረሰ ሁሉ በእነርሱም ላይ ይደርሳል። ሌሎች አሳዛኝ ነገሮችም ሊከሰቱ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ከማጉረምረምና እግዚአብሔርን ከመጠራጠር ወይም መራር ከመሆን ይልቅ መደሰት ይኖርባቸዋል። የምንደሰተው አስቸጋሪውን ሁኔታ ስለምንወደው ሳይሆን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆንና ፍጻሜው ማለትም ዘላለማዊው የመንግሥተ ሰማይ ሕይወት መልካም እንደሆነ ስለምናውቅ ነው። እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ስለሚቆጣጠርና ክርስቶስ ዳግም ስለሚመጣ፥ ሳንጨነቅ በልበ ሙሉነት እየተመላለስን በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ማጽናት ይኖርብናል። በምንጸልይበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር መልስ ከመስጠቱም በላይ ጥርጣሬያችንንና ጭንቀታችንን በማስወገድ በህልውናው እንድንተማመን ያደርገናል። ጳውሎስ በወታደሮች ተጠብቆ የሚኖር እሥረኛ ቢሆንም፥ በልቡ ውስጥ ትልቅ ነጻነት ነበር። በሚያስጨንቁን አስቸጋሪ ጊዜያት ወደ እግዚአብሔር ብንመለስ ደስታችንንና በእርሱ ላይ ያለንን መተማመን ይዘን እንጸና ዘንድ ልባችንንና አእምሯችንን የሚጠብቅ ወታደር ይልክልናል። ካለንበት ሁኔታ ባሻገር ዓለም የማይረዳው ሰላም ልባችንን ይሞላዋል።

ሐ. የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች አሳባቸውን እንዲቆጣጠሩ ተነግሯቸዋል። የምናስበው ተግባራችንን ከመወሰኑም በላይ፥ ስሜታችንንም ይመራዋል። ባለማቋረጥ ስለሚያሸንፉን አሳቦች የምናስብ ከሆነ፥ ብዙም ሳይቆይ በጭንቀት እንረታለን። ወይም ደግሞ ከእግዚአብሔር ስለሚያርቁን ነገሮች የምናስብ ከሆነ፥ አእምሮን የሚያልፍ ሰላም ሊኖረን አይችልም። እነዚህ እንደ ምኞት፥ ክፋት፥ ወይም ገንዘብ ያሉ አሳቦችም ወደ ኃጢአት ይመሩናል። ነገር ግን «እውነት፥ ጭምት፥ ጽድቅ፥ ንጹሕ፥ ፍቅር፥ መልካም፥ በጎነትንና ምስጋናን» የምናስብ ከሆነ፥ እግዚአብሔርን የሚያስከብር ተግባር በመፈጸም፥ በእምነታችን ልናድግና ልባዊ ደስታን ልናገኝ እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ያስጨነቁህን ነገሮች ዘርዝር። የተጨነቅኸው ለምን ነበር? ለ) የምናስባቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነትና ለሁኔታዎች ያለንን ስሜት የሚወስኑት እንዴት ነው? ሐ) ጸሎት ሁልጊዜም የምንፈልገውን ምላሽ ባያመጣም እንኳን ተገቢውን ሰላማዊ አመለካከት እንድንይዝ እንዴት እንደሚያግዘን ግለጽ።

፪. ጳውሎስ የፊልጵስዩስን አማኞች ለስጦታቸው ያመሰግናቸዋል (ፊልጵ. 4፡10-20)

የሙሉ ጊዜ ክርስቲያን አገልጋዮች ለመማር የሚቸገሩባቸው ነገሮች አንዱ ለገንዘብ መንፈሳዊ አመለካከትን ማዳበር ነው። አብዛኛው ክርስቲያን አገልጋዮች ብዙ ደመወዝ ስለማያገኙ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ይቸገራሉ። ከዚህም የተነሣ አንዳንዶች ገንዘብን የሚቀላውጡ «ለማኞች» ወይም ስጦታ ለመቀበል ሲሉ በየሰዉ ቤት የሚዞሩ ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ ኩሩዎች ስለሆኑ እግዚአብሔር የሚረዳቸውን ሰው ሲያመጣላቸው ስጦታውን ለመቀበል አይፈልጉም። የጳውሎስና የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት አገልጋዮች ለገንዘብ እንዴት ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያሳያል።

በሌላ በኩል ለአገልጋይ ከማሰቧ የተነሣ ሳትጠየቅ የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግ ቤተ ክርስቲያን ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው። የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ጊዜያቸውን ለአገልግሎት ለሚሰጡ ወገኖች የፍቅር እንክብካቤ በማድረጓ በአርአያነት የምትጠቀስ ነች። ጳውሎስ ሠርቶ ለመተዳደር በማይችልበት ሁኔታ ማንንም በማያውቅበት የባዕድ አገር መታሠሩን ሲሰሙ፥ ወዲያውኑ ገንዘብ ላኩለት። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ልገሳ ለእነርሱ አዲስ አልነበረም። ገና ወንጌሉን በተቀበሉ ጊዜ ጳውሎስና ሲላስ በፍጥነት ወደ ተሰሎንቄ ሄደው ወንጌልን መስበክ ነበረባቸው። በዚህም ጊዜ ለጳውሎስ የገንዘብ ዕርዳታ አድርገውለታል። ምንኛ ለጋስ ቤተ ክርስቲያን ነበረች! የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቻቸውን እንዲህ የሚንከባከቡ የፊልጵስዩስ ዓይነት ቤተ ክርስቲያኖች ቢበዙልን ምንኛ መልካም ነው።

ጳውሎስ ግን ሳይለምን ወይም ስጦታን ሳይጠይቅ አመለካከቱን በጥንቃቄ ጠብቋል። እግዚአብሔር ይረዱት ዘንድ ልባቸውን እንዲያነሣሣ ነበር የጠበቀው። በመሆኑም፥ ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱና ስለ መስጠት የተማራቸውን አራት ነገሮች ያጋራናል።

  1. እግዚአብሔር ልጆቹን የመንከባከብን ኃላፊነት ይወሰዳል። ስለሆነም፥ ልጆቹ ዓይኖቻቸውን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ከሌሎች መለመንን ማቆም አለባቸው። እግዚአብሔር ብዙ ገንዘብ በሚሰጠን ጊዜ በምስጋና ልንቀበለው ይገባል። ትንሽም ቢሰጠን በዚያው መርካት ይኖርብናል። በብዙም ሆነ በጥቂቱ ፍላጎታችንን በሚሞላው እምላክ ልንረካ ይገባል። እግዚአብሔር እንደ ድህነትና ረሃብ ያሉትን ሁኔታዎች ለማለፍ የሚያስችሉትን ልገሳዎች ያደርጋል። ተጨማሪ ገንዘብ ከመፈለግ ይልቅ እርሱ በሚሰጠን መርካት አለብን።
  2. ጳውሎስ መስጠት በሰዎች ልብ ውስጥ ክርስቲያናዊ ዕድገትን እንደሚያበረታታና ሽልማትን እንደሚያስገኝላቸው ተረድቶ ነበር።
  3. እግዚአብሔር ከሰጠን ነገር ላይ በልግስናና በደስታ መስጠት አንዱ እግዚአብሔርን የምናመልክበት መንገድ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን እንዲሰጡ አነሣሥቷቸው ኢየሱስን ሲታዘዙ ይሸልማቸዋል። ብዙውን ጊዜ፥ «ለእግዚአብሔር ምስጋናችንን እንጂ ምን እንሰጠዋለን?» ሲባል እንሰማለን። እግዚአብሔር ለሰጠን ሁሉ ወሮታ ልንከፍል እንደማንችል እውነት ነው። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን ልንሰጥ እንደምንችል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ለእግዚአብሔር ራሳችንን እንደ ቅዱስ መሥዋዕት ልንሰጥ እንችላለን (ሮሜ 12፡1-2)። ገንዘብ፥ ቁሳቁሶችንና ጊዜያችንን ለእግዚአብሔር ልንሰጥ እንችላለን። ይህም ራሱ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። አምልኮ መዝሙር መዘመር ብቻ አይደለም። የአምልኮ መሠረቱ ራሳችንን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው። ራሳችንን ለእግዚአብሔር ከሰጠን በኋላ ልንዘምርና እግዚአብሔር የሰጠንን ቁሳዊ በረከት ሌሎችን በመርዳት መልሰን ልንሰጠው እንችላለን።
  4. ገንዘባችንንም (ከብቶች፥ እህልና የመሳሰሉትን) ሆነ ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር በመስጠታችን ምክንያት አንደኸይም። እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። እግዚአብሔር ከበረከት ግምጃ ቤቱ (በክርስቶስ ያለ ባለጠግነት) ለእርሱ በልግስና የሚሰጡትን ይባርካል። ይህ በረከት ዛሬ ፍላጎታችንን ማሟላት ሊሆን ቢችልም፥ በተለይ በመንግሥተ ሰማይ በሚሰጠን ሽልማት የሚገለጥ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሁኔታዎች ሁሉ መርካት አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) መርካት ተስኖህ ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላህበትን ሁኔታ አስታውስ። ሐ) በችግር ውስጥ በመስጠትና በወንጌል ማኅበርተኝነት ለእግዚአብሔር መስጠት ክብር የሚሆነው እንዴት ነው?

፫. ማጠቃለያ (ፊልጵ. 4፡21-23)

ጳውሎስ አብረውት ከነበሩት ሰዎች ሰላምታ በመላክ ይህንን መልእክት ይደመድማል። እነዚህ ሰዎች እነማን መሆናቸውን አናውቅም። ምናልባትም ሉቃስና ጢሞቴዎስ አብረውት ይሆኑ ይሆናል። ነገር ግን ጳውሎስ የቄሣርን ቤተ ሰዎች ነጥሎ ጠቅሷል።

ምናልባት ይህ የቄሣርን ቤተሰብ አያመለክትም ይሆናል። ነገር ግን ወንጌል ቄሣር እስከሚያድርበት ቤት ድረስ መዝለቁን ያስረዳል። ጳውሎስ የቄሣር ሠራተኞች ለሆኑት ወታደሮች ወንጌሉን ለማካፈል ችሎ ነበር። ኔሮ የወንጌሉ ጠላት ሊሆን ቢችልም፥ ኃይልን የተሞላው ወንጌል እስከ ፊቱ ዘልቆ የጠላትን ግዛት ወሯል፡፡

ይህ የሆነው ጳውሎስ በመታሠሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛ በማንረዳው መንገድ የሚሠራ ምንኛ ድንቅ አምላክ ነው። በተለይም ወደ ሕይወታችን የሚመጣውን ሁኔታ ሁሉ በመቀበል ለመርካትና ለመደሰት በምንችልበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ተግባራትን ያከናውናል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: