በፔንታቱክ መጻሕፍት ጥናታችን፥ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን መሠረታቸው ከሆነው ከአብርሃም ጀምሮ፥ ታላቅ ሕዝብ ወደ መሆን እስከ ደረሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን ነገር ተመልክተናል። እግዚአብሔር በጸጋው ይህንን ታላቅ ሕዝብ በባርነትና በምድረ በዳም እያለ ተጠንቅቆ የመራበትን ኃይሉን መስከረናል። እግዚአብሔር ባመፁበት ሕዝብ ላይ የፈረደባቸው ቢሆንም፥ በምሕረቱ ለሕዝቡ እየተጠነቀቀ እስከ ተስፋይቱ ምድር ጫፍ ድረስ መርቶአቸዋል። ሙሴ የመጨረሻዎቹን ቃሎቹን ለአዲሱ የእስራኤላውያን ትውልድ የተናገረው በዚህ በተስፋይቱ ምድር ጫፍ ላይ ነበር። እነዚህ የመጨረሻዎቹ የሙሴ ቃሎች በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ይገኛሉ። ከዚያም ሙሴ የተስፋይቱን ምድር ከሩቅ አሻግሮ አይተ ሞተ።
የኦሪት ዘዳግም ርዕስ
በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ፥ ከፔንታቱክ መጻሕፍት መካከል የአምስተኛው መጽሐፍ ርዕስ ኦሪት ዘዳግም ይባላል። ይህ ስም ከሴፕቱዋጀንት የተገኝ ሲሆን ትርጉሙም «ሁለተኛ ሕግ» ወይም «የሕግ ድግግሞሽ» ማለት ነው። ይህ ስም የሚያንፀባርቀው የኦሪት ዘዳግም አብዛኛው ክፍል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በሲና ተራራ የሰጣቸው ሕግ የተደገመበትና ተስፋፍቶ የቀረበበት መሆኑን ነው።
አይሁድ ይህንን መጽሐፍ በኦሪት ዘዳግም መጀመሪያ ቁጥር ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን ቃላት በመውሰድ «ቃሉቹ እነዚህ ናቸው» የሚል ርዕስ ሰጥተውታል።
የኦሪት ዘዳግም ጸሐፊ
የውይይት ጥያቄ፥ የኦሪት ዘዳግም ጸሐፊ ማን እነደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት።
በዘመናት ሁሉ አይሁድም ሆኑ ክርስቲያኖች የኦሪት ዘዳግም ጸሐሪ ሙሴ እንደሆነ ይስማሙ ነበር። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን ሰዎች ይህንን በሁለት ምክንያቶች በመጠራጠር ጥያቄ ማንሣት ጀምረዋል። አንደኛ፥ ሙሴ በአንድ በተቀደሰ ስፍራ የማምለክን አስፈላጊነት በሚመለከት ትኩረት ሰጥቶ ይናገራል፤ ይህ ግን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እስከ ንጉሥ ኢዮስያስና ሕዝቅያስ ድረስ በተግባር አልታየም። ሁለተኛ ሙሴ በእስራኤል ንጉሥ ያለ ይመስል፥ ስለ ነገሥታት ይናገራል ስለዚህ ኦሪት ዘዳግም የተጻፈው ነገሥታት እስራኤልን መግዛት ከጀመሩ በኋላ መሆን አለበት ይላሉ።
ሆኖም ግን ኦሪት ዘዳግም እነርሱ እንደሚሉት ቆይቶ የተጻፈ መሆኑን ይህ አያረጋግጥም። ሙሴ በተለያዩ ስፍራዎች የሚደረግ አምልኮ የሚያመጣውን ችግርና እስራኤልም በዙሪያዋ እንዳሉ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ንጉሥ መፈለጓን አስቀድሞ በመገንዘብ ነገሥታቱን በሚመለከት መመሪያ መስጠቱንና በአንድ ስፍራ ማምለክን አስፈላጊነት መናገሩን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ዘዳግም ውስጥ ጸሐፊው ሙሴ እንደሆን የተጠቀሱ ነገሮች አሉ (ዘዳግ. 1፡5፤31፡9፥22፥24)። በቀሩት ቅዱሳት መጻሕፍት የኦሪት ዘዳግም ጸሐፊ ሙሴ መሆኑ ተናግሯል (ለምሳሌ ፡- 1ኛ ነገ. 2፡3፤ 8፡53)። ሆኖም ግን፥ አብዛኛውን የመጽሐፉን ክፍል ሙሴ ነው የጻፈው የሚለው አሳብ እንደተጠበቀው ሆኖ፥ መጽሐፉን ያቀነባበረው ሰው ከሙሴ ሞት በኋላ አንዳንዱን ነገር በመጨመር አጠናክሮት ሊሆን ይችላል (ዘዳ. 1-5፤ምዕራፍ 34)።
ኦሪት ዘዳግም የተጻፈው፥ አይሁድ በምድር በዳ መንከራተታቸው አብቅቶ ወደ ከነዓን ምድር ከመግባታቸው በፊት ነው፤ ይህም በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ መሆኑ ነው።
የኦሪት ዘዳግም አስተዋጽኦ
ኦሪት ዘዳግም ሁሉንም ዓይነት ሁኔታ የሚጨምሩ የተለያዩ በርካታ ሕግጋት ያሉት በመሆኑ መጽሐፉን በአስተዋጽኦው ከፋፍሎ ማቅረቡ አስቸጋሪ ነው። ቀላሉ መንገድ ኦሪት ዘዳግምን በሙሴ ሦስት ዋና ዋና ስብከቶች ዙሪያ ማደራጀት ነው።
- የሙሴ የመጀመሪያ ስብከት (ዘዳግም 1፡1-4፡43)
- የሙሴ ሁለተኛው ስብከት (ዘዳግ. 4፡44-28፡68)
- የሙሴ ሦስተኛው ስብከት (ዘዳግ. 29-33)
- የሙሴ ሞት (ዘዳግ. 34)
ሆኖም ኦሪት ዘዳግም ሊደራጅ የሚችልበት የመጽሐፉን ባሕርይ የሚያመለክት ሌላ መንገድ አለ። ብዙ ምሁራን ኦሪት ዘዳግምን የሚያዩት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ያለ ሰነድ ወይም ቃል ኪዳን አድርገው ነው።
ቀደም ሲል እንዳየነው እግዚአብሔር ሕግን በሲና ተራራ በሰጠበት ጊዜ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በሕዝቡ ባሕል መሠረት እንዴት እንዳደራጀው ተመልክተናል። «ሱዜረይም-ቫሳል» በመባል የሚታወቀውንና በ2ኛው ሺህ ዓ.ዓ. በኬጢያውያን መካከል በጣም ተለምዶ የነበረውን የስምምነት አሠራር ሲጠቀም እናያለን። ይህ ስምምነት አሸናፊ በሆነው ንጉሥ ወይም መሪዎችና ተገዢ በሆኑ ነገሥታት መካከል የሚፈጸም ነበር። በኦሪት ዘጸአት እግዚአብሔር ገዢ ንጉሥ ሆኖ፥ ቃል ኪዳኑን የዚህ ስምምነት እንደ ቫሳል (ሎሌ) ተቀባይ ከሆኑት ከእስራኤላውያን ጋር አድርጎ እናያለን። የሚከተለውን ባሕላዊ ያቃል ኪዳን ስምምነትን ኦሪት ዘዳግም እንዴት እንደሚመስሉ ተመልከት። እግዚአብሔር ንጉሥ (ሱዚረይም) መሆኑን እስራኤል ደግሞ ተገዢ (የስምምነቱ ውል ተቀባይ «ቫሳል» ወይም ሎሌ) መሆኗን አስታውስ።
- የተናጋሪው ወይም የቃል ኪዳኑ ሰጭ መግቢያ፡ በዘዳግ. 1፡1-5 ተንፀባርቋል፡፡ ምንም እንኳ ተናጋሪው ሙሴ ቢሆንም የሚናገረው ንጉሡን- እግዚአብሔርን ወክሎ ነው።
- የቃል ኪዳኑ ታሪካዊ አቀራረብ፡- ይህ በዘዳግ. 1፡6-3፡29 ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ደግም በሚናገርበት (በሚከልስበት) ጊዜ እግዚአብሔር እነርሱን እንዴት እንደመረጣቸው፥ ከግብፅ ባርነት ነፃ በማውጣት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዴት እንደመራቸው በሚያሳየው ክፍል ተንፀባርቋል።
- ስለ ቃል ኪዳኑ ከፍጻሜ መድረስ ይመሰክሩ ዘንድ ተገዢው ሊታዘዛቸው የሚገባ የቃል ኪዳኑ ቅድመ ሁኔታዎች፡- በማክበር ይጠብቁት ዘንድ እግዚአብሔር ለእስራኤል ትእዛዛቱን ሁሉ በሰጠበት በዘዳግም 4-26 ይታያል።
- የቃል ኪዳኑ ሕጋዊ ሰነድ ምን ማድረግ እንደሚገባ የተሰጡ መመሪያዎች፡፡ በኦሪት ዘዳግም 27፡2-3 ሙሴ ሕጉ በድንጋይ ላይ እንዴት እንደሚጻፍና እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በገቡ ጊዘ አስታዋሽ ሆኖ እንደሚቀመጥ መመሪያ ሰጠ።
- ምስክሮች ተጠርተው ነበር (ዘዳግ. 31-32)፡- አሕዛብ ብዙውን ጊዜ ለምስክርነት የሚጠሩት ጣዖቶቻቸውን ነበር፤ ነገር ግን ሙሴ በመጀመሪያ ምስክር ይሆን ዘንድ መዝሙር ዘመረ (ዘዳ. 31፡19-22)። ቀጥሎም በዘላለማዊ አምላክና በሕዝቡ መካከል ምስክር ይሆን ዘንድ ሰማይና ምድርን ጠራ።
- ንጉሡ በረከትንና ርግማንን ወይም ለቃል ኪዳኑ በመታዘዝ የሚሰጥ ሽልማትንና ባለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣትን ዘረዘረ፡፡ በዘዳግ. 28 እግዚአብሔር እስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ቢታዘዙ የሚያገኙትን በረከት፥ ባይታዘዙ ደግሞ የሚጠብቃቸውን ቅጣት ወይም ርግማን የዘረዘሩበት ክፍል ነው።
ከዚህ የምንረዳው፥ኦሪት ዘዳግም በሲና ተራራ የተሰጠው የሕግ መደገም ብቻ ሳይሆን፥እስራኤላውያን አስቀድሞ በሲና ተራራ አባቶቻቸው ያደረጉትን ስምምነት ወይም ቃል ኪዳን ለሁለተኛ ጊዜ ማጽናታቸውን የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ መሆኑን ነው። በሲና ተራራ እንደነበረው ቃል ኪዳን፥ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ዘርዘር አድርጎ የሚያቀርብ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዘመናችን የዚሁ ተመሳሳይ የሆነ ግንኙነት በእግዚአብሔርና በክርስቲያኖች መካከል የሚኖረው እንዴት ነው? ለ) ተመሳሳይ ነው ወይስ የተለያየ? አብራራ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)