የውይይት ጥያቄ፥ የሰው ልጅ ልብ በመሠረቱ መልካም ነው ወይስ ክፉ? ለምሳሌ፥ ሕግ እንዲሁም ሕግን የሚያስፈጽም የፖሊስ ኃይል ባይኖር ኖሮ የሰዎች ዝንባሌ መልካም ይሆን ነበር ወይስ ክፉ? መልስህን አብራራ።
የመጽሐፈ መሳፍንት የመጀመሪያ ዋና ክፍል (ከምዕ. 1-16 ያለው) በእነዚያ ዓመታት የነበሩ የአይሁዳውያን ዋና የፖለቲካ ችግሮችን ግልጽ በሆነ መንገድ ያሳየናል። ትኩረታቸውም ሕዝቡን ከውጭ ኃይል ወይም ከጠላት ቀንበር ነፃ ለማውጣት እግዚአብሔር ባስነሣቸው መሳፍንትነት አመራር ላይ ነው።
የመጽሐፈ መሳፍንት የመጨረሻው ክፍል (መሳፍንት 17-21) በመሳፍንት ዘመን የነበረውን ሃይማኖታዊና የሥነ-ምግባር ጉድለት የሚያንጸባርቅ ነው። የሰው ልብ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር እስካልሆነ ድረስ ሊኖር የሚችለውን ግልጽ ሥዕል ያሳያል። ሰው «በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን» (መሳ. 21፡25) ማድረግ ሲጀምር፥ ክፉ መሆኑ ወዲያውኑ ይረጋገጣል። ሕግ ወይም ሕግ አስፈጻሚ አካል በሌለበት ለሕገወጥነት መከሰት ጊዜ አይወስድበትም። ሕግና ሕግን የሚያስፈጽሙ የሕዝብ መሪዎች የሰው ኃጢአት በተወሰነ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ያደርጋሉ። እነዚህ ተከላካዮች ሲነሡ፥ የሰው ኃጢአተኝነት ወዲያውኑ ገሐድ ይወጣል።
የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) አንተስ ይህ ነገር ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ ስለ ሰው ክፉ ባሕርይ የሚያስተምርህ ምንድን ነው?
የውይይት ጥያቄ፡ መሳ. 17-21 አንብብ። በእነዚህ ምዕራፎች የሰው ልጅ ክፋት የታየው እንዴት ነው?
በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ. 17-21 የሚገኙት ታሪኮች የተፈጸሙበትን ጊዜ ማወቅ የማይቻል ነው። የዳን ነገዶች ገና ርስት በመፈለግ ላይ ስለሚገኙና የአሮን ልጅ ፊንሐስ ሊቀ ካህን በመሆኑ፥ ታሪኮቹ የተፈጸሙት በመጀመሪያዎቹ የመጽሐፈ መሳፍንት ዘመን ሳይሆን አይቀርም (መሳ. 18፡1፤ 20፡27-28)። የእነዚህ ታሪኮች ዓላማ በዘመነ መሳፍንት የነበረውን አጠቃላይ የሥነ-ምግባር መመሪያ መጥፋት ለማሳየት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሊያውቁና ሌሎችን ማስተማር ይገባቸው ለነበሩ ሌዋውያን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአል። ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ በላይ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ እንዲኖሩ የሚጠበቅባቸው ሌዋውያን ነበሩ። እነርሱም እንደቀረው ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አደረጉ። በኃጢአታቸውም ምክንያት የቀሩት ሕዝብ ወደ ክሕደትና ጣዖት አምልኮ ሄዱ። የእነርሱም ተግባር ሕዝቡን ወደ እርስ በርስ ጦርነት መራው።
- የሌዋውያን ካህናትና የዳን ነገድ ታሪክ (መሳ. 17-18)
የእግዚአብሔር ሕዝብን ኃጢአተኝነት የሚያመለክተው የመጀመሪያው ታሪክ፥ ስለ አይሁድ ሃይማኖት መበላሸት ይናገራል። ይህ ብልሽት የተጀመረው ከኤፍሬም ነገድ የሆነች አንዲት ሴትና ልጇ ከብር የተሠራ ምስል ሠርተው በቤታቸው ባስቀመጡ ጊዜ ነው።
ወደ ደቡብ ብዙ ኪሎ ሜትር ራቅ ብሉ አንድ ሌዋዊ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ ሌዋውያን የእስራኤላውያን ሃይማኖታዊ መሪዎች እንዲሆኑ በእግዚአብሔር የተመረጡ ነበሩ። ደግሞም ይኖሩባቸውም ዘንድ እግዚአብሔር 48 ከተሞችን ሰጥቷቸው እንደነበረ ታስታውሳለህ። ቤተልሔም ከእነዚህ አንዷ አልነበረችም። ይህም የሚያሳየው በሙሴና በኢያሱ ዘመን ተጀምሮ የነበረው የአኗኗር ዘይቤ እየተጣሰ መሆኑን ነው። ሌዋዊ ቤተልሔምን ትቶ ስለ መሄዱ የተነገረው እውነት፥ ጨርሶ ሊገኝባት የማይገባው ከተማ ስለነበረች፥ ሥራ አግኝቶ ወደሌላ ስፍራ መሄዱ ሊሆን ይችላል። ይህም እግዚአብሔር ያዋቀረው የአኗኗር ስልት እየተጣሰ መሆኑን ያሳያል። ሌዋውያን እስራኤላውያን ለጌታ ከሚሰጡት አሥራት በሚገኘው ገቢ ኑሮአቸውን መምራት ነበረባቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ሕዝቦች አሥራታቸውን በማይሰጡበት ጊዜ ይህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዴት ይጎዳል? ለ) ይህ የአንተ ቤተ ክርስቲያንም ችግር ነውን? ከሆነስ ለምን?
ሌዋዊው ሥራ ፍለጋ ወደ ሰሜን ተጓዘና ወደ ሚካ ቤት መጣ። ሚካም ላሠራው ጣዖት ካህን ሆኖ እንዲያገለግል ቀጠረው። ሚካ ቤቱን የአምልኮ ስፍራ ለማድረግ ፈልጎ ነበር። ይህንን ያደረገው ለእውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ በኃላፊነት ማገልገል የነበረበትን አንዱን ሌዋዊ በመቅጠር ነበር። ሌዋዊው ስለ ግል ሕይወቱ እንጂ ለእግዚአብሔር ስለሚደረግ አምልኮ ግድ ስላልነበረው የተሳሳተውን አምልኮ ለመምራት ፈቃደኛ ሆነ። እውነተኛ አምልኮን ሳይሆን ገንዘብን ብቻ ፈለገ።
ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ የዳን ነገድ አባሎች የሚኖሩበትን ስፍራ እየፈለጉ ወደዚህ ስፍራ ደረሱ። የዳን ነገዶች በሜዲትራኒያን ባሕረሠላጤ አጠገብ መሬት ተሰጥቶአቸው ነበር። መሬቱ በዚያ ስፍራ እጅግ ለም ቢሆንም፥ በከነዓናውያን ተይዞ ነበር፤ ስለዚህ የዳን ነገዶች ሌላ ስፍራ ይፈልጉ ዘንድ አምስት ወታደሮችን ላኩ። ወደ ሚካ ቤት በደረሱ ጊዜ ሌዋዊው ከደቡብ የእስራኤል ክፍል እንደመጣ ተገነዘቡ። በዚያ ስፍራ የሚካሄድ የጣዖት አምልኮ አለቃ መሆኑንም አወቁ። ከዚያ በኋላ አምስቱ ሰዎች ወደ ሰሜን 240 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ሌሳ ወደምትባል ስፍራ ደረሱ። የወደፊት ቤታቸውም በዚያ እንዲሆን ወሰኑ። የቀሩት የዳን ነገዶች ወደ ሌሳ መጥተው ምድሪቱን ሲወሩ፥ አምስቱ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት በመሄድ ሌዋዊውንና የሚካን ጣዖት ወደ ሌሳ ይዘው ሄዱ። ለብዙ ዓመታት ይህ ሌዋዊና ቤተሰቡ የዚህ ጣዖት ካህናት ሆነው ቀሩ። ሌሳ በኋላ «ዳን» ተብላ የተጠራች የእስራኤል የሩቅ ሰሜን ድንበር ናት።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ስለ እግዚአብሔር የነበራቸውን ደካማ አስተሳሰብ በሚመለከት ምን እንማራለን? ለ) የአይሁዳውያን ሃይማኖት በከነዓናውያን ሃይማኖት በፍጥነት የተበከለው ለምንድን ነው? ሐ) ሃይማኖታችን በዓለማዊ ልምምድ ስለመበከሉ አደገኛነት ምን እንማራለን?
ከዚህ ትምህርት የምናገኛቸው በርካታ እውነቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የከነዓናውያንን ባሕልና ሃይማኖት እንዴት በፍጥነት እንደለመዱ ማየት እንችላለን። ሁለተኛ፥ ሕዝቡ የእግዚአብሔር አምልኮ ከጣዖት አምልኮ ጋር ሊቀላቀል እንደሚችል እንዴት እንዳሰበ ማየት እንችላለን። እግዚአብሔር ወደ ጣዖት ሊለወጥና ለራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያና መጠቀሚያ ሊያደርጉት እንደሚችሉ አሰቡ። ሦስተኛ፥ የጣዖት አምልኮን ዋጋ ቢስነት እናያለን። ጣዖት ራሱን ከመሰረቅ ለማዳን አለመቻሉና፥ ኃይል እንደሌለው ያሳየናል።
- ሌዋዊውና ቁባቱ (መሳ. 19-21)
ከዘመነ መሳፍንት የምናገኘው ሁለተኛው ታሪክ የሕዝቡን የሥነ ምግባር ብልሹነት ያሳየናል። እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎቹ ድካምና ኃጢአት እንዳየለባቸው ለሁለተኛ ጊዜ እንመለከታለን። የመጀመሪያው ሌዋዊ ከቤተልሔም ተነሥቶ ወደ ኤፍሬም እንደሄደ፥ ሁለተኛው ሌዋዊ ደግሞ ወደ ቤተሰቦችዋ የተመለሰችውን ቁባቱን ፍለጋ ከኤፍሬም ወደ ቤተልሔም መጣ። ከቤተልሔም ቁባቱን ይዞ ወደ ኤፍሬም በሚመለስበት ጊዜ እግረ መንገዱን ጊብዓ በምትባል በብንያማውያን ከተማ መሸበትና አደረ። ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች፥ እስራኤላውያን እጅግ አስጸያፊ ተግባር ፈጸሙ። ለራሳቸው ሰዎች መስተንግዶ ማድረግ አልቻሉም። ግብረ ሰዶም ለመፈጸም ፈልገው ሰውዩውን ካደረበት ቤት ለማስወጣት ሞከሩ። ሌዋዊውን ያሳደረው ሰው ግን የገዛ ሴት ልጁንና የሌዋዊውን ቁባት አውጥቶ ሰጣቸው። ቁባቱም እስክትሞት ድረስ በመፈራረቅ ሌሊቱን ሙሉ አመነዘሩባት።
የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ታሪክ የሌዋዊንና የእስራኤልን ሕዝብ ሃይማኖታዊና ሥነ- ምግባራዊ ክፋት እንዴት ያሳየናል?
ሌዋዊው የቁባቱን ሬሳ 12 ቦታ ቆራረጠና ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንዳንዱን ቁራጭ ላከ። ይህም ነገር የ12ቱን ነገዶች ቁጣ ቀሰቀሰና ምን እንደተፈጸመ ለማየት መጡ። ታሪኩን በሰሙ ጊዜ፥ ይህንን ኃጢአት የፈጸሙትን ሰዎች አሳልፈው እንዲሰጧቸው የብንያም ነገዶችን ጠየቁ። ብንያማውያን ግን ስለተቃወሙ፥ የእርስ በእርስ ጦርነት ተነሣ። በጦርነቱም 40000 እስራኤላውያንና 25100 ብንያማውያን ሞቱ። የብንያማውያን ሴቶችና ልጆች በሙሉ ተገደሉ። ከብንያም ነገድ በሙሉ የተረፉት 600 ሰዎች ብቻ ነበሩ።
ሌሎች እስራኤላውያን፥ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው የብንያም ነገድ ሊጠፉ እንደሆነ ተገነዘቡ፤ ስለዚህ ለእነዚህ 600 ብንያማውያን 600 ሚስቶች የሚገኙበትን ዘዴ ፈጠሩ። በዚህም የብንያምን ነገድ ጨርሶ ከመጥፋት አዳኑት።
ሰዎች ራሳቸው የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ሲያደርጉ፥ ኃጢአታቸው አድጎ በርካታ ሰዎችን እንደሚነካና እንደሚያጠፋ አይገነዘቡም። የጊብዓ ሰዎች ኃጢአት በሺህ የሚቆጠሩ የበርካታ እስራኤላውያንን ሞትና የብንያም ነገድን ወደ ውድመት የሚያደርስ ጥፋት አስከትሉ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ቁጥሮች ኃጢአት ስለሚስፋፋበት መንገድና በምድሪቱ ስለ ሕግና ሥርዓት አስፈላጊነት ምን ያስተምሩናል? ለ) ከዚህ ታሪክ ለቤተ ክርስቲያኖቻችን የሚጠቅሙና ልናዛምዳቸው የምንችል አንዳንድ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)