የመጽሐፈ መሳፍንት ዋና ዋና ትምህርቶች

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት እንዳነበብነው በውስጡ የሚገኙ፥ ከሕይወትህና ከቤተ ክርስቲያንህ ጋር ልታዛምጻቸው የምትችለውን ዋና ዋና እውነቶች ናቸው ብለህ የምታስባቸውን ዘርዝር።

  1. መጽሐፈ መሳፍንት ለእግዚአብሔር በከፊል የመታዘዝ ውጤት ምን እንደሆነ ያሳየናል። እግዚአብሔር ከነዓናውያንን በሙሉ እንዲያጠፉ የሰጠውን ትእዛዝ አይሁድ በከፊል ብቻ ስለታዘዙት፥ ወደ ባሰ ኃጢአት የመውደቅን ሂደት ጀመሩ። ለእግዚአብሔር በከፊል መታዘዝ ብዙም ሳይቆይ፥ ለእርሱ በግልጽ ወዳለመታዘዝ ተለውጧል። የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር በክርስቲያን ሕይወትም ይፈጸማል። ማንም ሰው በድንገት በኃጢአት ፈጥኖ አይወድቅም። ይልቁንም ይህ በሂደት የሚፈጸም ነው። በመጀመሪያ መጠነኛ ጅማሬ ይኖረዋል። ይህ ጅማሬ በከፊል መታዘዝ ነው። በአብዛኛው የሕይወት ክፍላችን ለእግዚአብሔር እንታዘዛለን፤ ነገር ግን ያልተናዘዝናቸው ኃጢአቶች በሕይወታችን እንዲቆዩ እንፈቅዳለን። እነዚህ ኃጢአቶች፥ ኩራት፥ ትዕቢት፥ ቁጣ፥ ወይም ቅንዓት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ብዙ ሳይቆዩ እነዚህ ኃጢአቶች አድገው ሕይወታችንን በመቆጣጠር ለእግዚአብሔር በግልጽ ወዳለመታዘዝ ያደርሱናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህንን እውነት በራስህ ወይም በሌላው ክርስቲያን ሕይወት እንዴት አየኸው?

  1. መጽሐፈ መሳፍንት ዓለም በክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ያላትን ኃይልና እንዴት ወደ ኃጢአት እንደምትመራ ያሳየናል። በኢያሱ መሪነት እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለመከተልና እርሱን ብቻ ለማምለክ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጠላቶች የሆኑት ከነዓናውያን በመካከላቸው እንዲኖሩ ስለፈቀዱ፥ የከነዓናውያን ልምምድ ብዙም ሳይቆይ ችግር ያመጣባቸው ጀመር። ወዲያውኑ እንደከነዓናውያን ማሰብና ማምለክ ጀመሩ፤ በመጨረሻም እንደ ከነዓናውያን መኖር ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ከዓለምና ከልምምዷ እንድንለይ፥ እርሷንም ከመምሰል እንድንጠነቀቅ ያስተምረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ቆሮ. 6፡14-18 እና 1ኛ ዮሐ. 2፡15-17 አንብብ። ከዓለም ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት በዚህ ክፍል የተሰጠን ትእዛዝ ምንድን ነው?

ክርስቲያኖች ሁሉ ከዓለም ጋር ያለንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንድናቋርጥ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምረንም። ኢየሱስም የጸለየው፥ በዓለም እንድንኖር እንጂ፥ ከዓለም እንድንወጣ አይደለም (ዮሐ. 17፡14-19)። እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰዎችን ጓደኛ እንድናደርግ፥ ወንጌልን እንድናካፍላቸው፥ በሚያስፈልጋቸው ነገር እንድንረዳቸው፥ ከጎናቸው ሆነን እንድንሠራ፥ ወዘተ. ይፈልጋል። ኢየሱስ ራሱ «የኃጢአተኞች ወዳጅ» ተብሉአል (ማቴ. 11፡19)። ከማያምኑ ጋር ያለንን ማንኛውንም ኅብረት ማቆም አለብን የሚሉ ሰዎች ተሳስተዋል። ከእነርሱ ጋር ካልኖርን፣ ካላወቅናቸውና ፍቅርን ካላሳየናቸው በቀር፥ የዓለም ብርሃንና ጨው እንዴት መሆን እንችላለን? እንድንጠነቀቅ የተነገረን ነገር ቢኖር፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ዓለማዊ ተጽዕኖ እንዳይኖር ነው። እንደ እግዚአብሔር ልጆች የዓለም ፍልስፍና በሕይወታችን ላይ የማያስፈልግ ተጽዕኖ እንዳያደርግ መጠንቀቅ አለብን። ለምሳሌ፡ የገንዘብና የሥልጣን ፍቅር፥ ለራሳችን፥ ለቤተሰባችን ወይም ለጎሣችን በራስ ወዳድነት የተለየ ጥንቃቄ ለማድረግ መመኘት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን በዓለም ፍልስፍና ተጽዕኖ ሊደረግበት የሚችለው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች ጋር እየኖረ በዓለም ፍልስፍና ተጽዕኖ የማይደረግበት እንዴት ነው?

  1. እግዚአብሔር አማኞች ዓለምን እየመሰሉ ሲሄዱ፥ ያነጻቸው ዘንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ይጠቀማል። ይህ ማለት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ስለ ኃጢአት ፍርድ ናቸው ማለት አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ናቸው። አንዳንዶች በችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ኃጢአተኞች ስለሆኑ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ናቸው በማለት እንዳንፈርድ መጠንቀቅ አለብን። የእግዚአብሔር ሕዝብ በኃጢአት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፉ የሚያደርግበት መንፈሳዊ መመሪያ አለ። ይህም በሽታ፥ የወዳጅ ሞት፥ ወይም በአገር ላይ የሚመጣ ችግር ሊሆን ይችላል። በዚህ ዓይነት ጊዜ የሚመጣው ችግር ዓላማ ሕዝቡ ንስሐ ገብተው ከክፉ መንገዳቸው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ለማድረግ ነው። እውነተኛ ንስሐ ሰውን ጠባዩን እንዲለውጥ ያደርገዋል። እስራኤላውያን ግን በእውነት ንስሐ ገብተው እንደሆነ የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም። ከጠላቶቻቸው ነፃ እንደወጡ ብዙም ሳይቆዩ፥ ወደ ቀድሞ ክፉ ተግባራቸው ይመለሱ ነበር። የእግዚአብሔር ፍላጎት ግን ንስሐ እንድንገባና መንገዳችንን እንድንለውጥ ነው። ወደ በረከት ስፍራ የሚመልሰን በዚያን ጊዜ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በግል ሕይወትህና በቤተ ክርስቲያንህ እግዚአብሔር ከኃጢአት ያነጻችሁ ዘንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት እንደተጠቀመ ተጨባጭ ምሳሌዎችን ስጥ።

  1. የእግዚአብሔር ሕዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር ታላቅ መሪን በማስነሣት በእርሱ አማካይነት ነጻነትን ይሰጣቸዋል። እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው በሚጨቆኑበት ጊዜ፥ የሕዝቡን ጸሎት በመስማት መሳፍንትን አስነሣላቸው። በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ የምናያቸው መሳፍንት ተቀዳሚ ተግባራቸው ወታደራዊ መሪነት ሆኖ ሕዝቡን ከባርነት ነፃ አውጥተዋል። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች የመረጠው በመንፈሳዊነታቸው ለመሆኑ ምንም መረጃ የለንም። እንዲያውም አብዛኛዎቹ መሳፍንት በጣም መንፈሳዊ አልነበሩም። ሶምሶን ዘማዊ ነበር። ዮፍታሔ ልጁን ሠውቷል። ጌዴዎን ሕዝቡን ወደ ኤፉድ አምልኮ መርቷል። አብዛኛዎቹ መሳፍንት ልንከተለው የሚገባ መንፈሳዊ ምሳሌነት አልተዉልንም። ቢሆንም እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት ሰውን ከመንፈሳዊነቱ ውጭ እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል የእነርሱ ታሪክ ያሳየናል።

ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር የሚሠራው በተመሳሳይ መንገድ ነው። እግዚአሔር ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ለማውጣት መሠረታዊ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ሰው የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃውን ሳይመለከት ሊጠቀምበት ይችላል። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር፥ አማኝ ያልሆነን የፖለቲካ መሪን በማስነሣት፥ ለአማኞች እንዲራራና ከችግሮቻቸው ነፃ እንዲያወጣቸው ሊያደርግ ይችላል።

ነገር ግን እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ መሪዎች የተቀደሰ ሕይወት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። የእስራኤል ልጆች በተደጋጋሚ በኃጢአት የወደቁበት ምክንያት፥ ምናልባት እነዚህ መሳፍንት ለሕዝቡ መልካም መንፈሳዊ ምሳሌ ስላልሆኑ ይሆናል። የሰዎች ሥነ-ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት ብዙ ጊዜ የሚወሰነው በመሪዎቻቸው መንፈሳዊ ሕይወት ላይ መሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት መመሪያዎች አንዱ ነው። መሪዎች እግዚአብሔርን ሲወዱና በቅድስና ሲያገለግሉት፥ ሕዝቡም እንዲሁ ያደርጋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ እውነት ሲሆን ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምርጫ መመሥረት ያለበት፥ በትምህርት፥ በዘር፥ ወይም በቤተሰብ ውርስ፥ ወዘተ. ሳይሆን በመንፈሳዊ መመዘኛ መሆን እንዳለበት ይህ ምን ያስተምረናል?

  1. መጽሐፈ መሳፍንት የሚያተኩረው በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፡- መሳ. 3፡10፤ 6፡34፤ 11፡29፤ 14፡6፥ 19፤ 15፡14፤ 16፡20። ይህ በዚያን ዘመን ስለነበረው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምን ያስተምረናል?

ከመጽሐፈ መሳፍንት ልዩ ገጽታዎች መካከል አንዱ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የተደረገ ትኩረት ነው። ከዚህ መጽሐፍ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የተነገረው በጣም ጥቂት ነገር ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ግን የጌታ መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ከላይ የተሰጡትን ጥቅሶች በሚገባ ካጠናን የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን፡-

ሀ. አንድ የተለየ ተግባር ለመፈጸም በተጠሩ ውሱን መሪዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ነበር። የመንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ መውረድ የተለመደ ነገር አልነበረም፤ ሆኖም እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመምራት ወይም ነፃ ለማውጣት ይችሉ ዘንድ ለመረጣቸው ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው ነበር። በዚህ ዓይነት እነዚህ መሳፍንት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከባርነ ያወጡት በራሳቸው ኃይል ሳይሆን፥ እግዚአብሔር መንፈሱን ስለ ሰጣቸው እንደሆነ ግልጥ መሆን ነበረበት። እውነተኛው የእስራኤል ነፃ አውጭ እግዚአብሔር እንጂ መስፍኑ አልነበረም።

ለ. መንፈስ ቅዱስ ሰዎች የእርሱን ልዩ ኃይል በሚፈልጉበት ጊዜ በተደጋጋሚ ይመጣ ነበር። በመጀመሪያ አካባቢ ሶምሶን ከጠላቶቹ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ በላዩ ላይ ይወርድ ነበር።

ሐ. መንፈስ ቅዱስ በሰው ደስ በማይሰኝበት ጊዜ ከዚያ ሰው ተለይቶ ይሄድ ነበር። ይህን እውነት እግዚአብሔር ከሶምሶን ተለየ ከሚለው ቃል መመልከት እንችላለን። በንጉሥ ሳኦል ታሪክ መንፈስ ቅዱስ ተወው የሚል ቃል ስናነብ (1ኛ ሳሙ. 16፡14)፥ ይህ ነገር ግልጽ ይሆንልናል። ለጸሎቱ መልስን በመስጠት መንፈስ ቅዱስ ወደ ሶምሶን እንደተመለሰ ደግሞ የዳጎንን ቤተመቅደስ በመደርመሱ እንረዳለን፤ (መሳ. 16፡28-30)።

ልናስታውሰው የሚገባን አንድ በጣም አስፈላጊ እውነት አለ። እግዚአብሔር እውነቱን ሁሉ በአንድ ጊዜ አልገለጠም። ነገር ግን ስለ እርሱ የሚናገር ተጨማሪ እውነትን በየጊዜው በዘመናት ሁሉ በዝግታ ይገልጥ ነበር። ይህ «እየጨመረ የሚሄድ መገለጥ» በመባል ይታወቃል። አይሁድ እግዚአብሔር አምላክ አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ማለት ሥላሴ መሆኑን አያውቁም ነበር፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን መንፈስ የእግዚአብሔር ተቀጥያ፥ ወይም የእግዚአብሔር ኃይልና ሥልጣን፥ የመኖሩ ማረጋገጫ አድርገው ያስቡት ነበር። መንፈስ ቅዱስን ከሥላሴ አንዱ አድርገን የምንመለከተው በአዲስ ኪዳን ብቻ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ነው፥ ሆኖም ከእግዚአብሔር የተለየ ነው።

ይህም ማለት ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለንን መረዳት በብሉይ ኪዳን ላይ ብቻ ከመመሥረት መጠንቀቅ አለብን ማለት ነው። በኢዩኤል 2፡28 እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን መንፈሱን በሰዎች ሁሉ ላይ እንደሚያፈስ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። የዚህ ትንቢት ፍጻሜ የጀመረው በጰንጠቆስጤ ቀን ነው፤ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ በላይኛው ክፍል ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ላይ ወርዶባቸው ነበር (የሐዋ. 2)። በአዲስ ኪዳን በሚገኙ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች የሚከተሉት እውነቶች ግልጽ ናቸው።

ሀ. መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በጸጋው በሚያምኑበት ጊዜ ለልጆቹ በሙሉ የሚሰጠው እንጂ ለተወሰኑ የተመረጡ ሰዎች የሚሰጥ ብቻ አይደለም። በሮሜ 8፡9 ጳውሎስ ማንም መንፈስ ቅዱስ የሌለው የክርስቶስ አይደለም ይላል። በሌላ አነጋገር፥ ይህ ማለት አማኝ አይደለም ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ የመጣው ባመንበትና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በሆንበት ጊዜ ስለሆነ አሁን ወደ እኛ እንዲመጣ መጸለይ ስሕተት ነው፤ የእግዚአብሔርን መንፈስ ያለማቋረጥ እንድንሞላ መጸለይ ግን ተገቢ ነው፤ (ኤፌ. 5፡18)። መንፈስ ቅዱስን እንዳናጠፋው ኃጢአታችንን መናዘዝ አለብን (1ኛ ተሰ. 5፡19)።

ለ. እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ሕልውና ከልጆቹ ላይ አይወስድም። ክርስቲያኖች ኃጢአት በሚያደርጉበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሊወሰድባቸውና ደግሞ ተመልሶ ሊመጣ አይችልም። ኃጢአት የሚያደርግ ክርስቲያን እንኳ መንፈስ ቅዱስ አለው። እርስ በርሳቸው ይጋጩ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያኖች እንኳ መንፈስ ቅዱስ እንደነበራቸው ከ1ኛ ቆሮ. 1፡7 በግልጽ እንመለከታለን፤ ነገር ግን ኃጢአት በምናደርግበት ጊዜ በእኛ ውስጥ የሚሠራውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እናጣለን።

ሐ. የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያንን ያገለግሉበት ዘንድ እግዚአብሔር እንደፈለገ ለክርስቲያኖች ሁሉ ተሰጥተዋል (1ኛ ቆሮ. 12፡11)። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዓላማቸው ለግል ጥቅም፥ መንፈሳዊነታችንን ለመግለጥ አይደለም፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ብስለትና እግዚአብሔርን በማገልገል እንድታድግ እርስ በርሳችን ማገልገል እንድንችል ለማድረግ ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡26)።

መ. የአንድ ሰው መንፈሳዊነት የሚመዘነው፥ በመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች እንጂ (ገላ. 3፡22-23)፥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን በመቀበል አይደለም።

ይህ ትምህርት ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ከሚያስተምሩት የተለየ ቢሆንም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ሁሉ በጥንቃቄ በመመርመር ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩትን ነገር ማወቅ አስፈላጊ ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ወይም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በሚገኝ አንድ ክስተት ላይ የሥነ-መለኮት ትምህርት መሥርተን፥ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበት መንገድ ምን ጊዜም ይኸው ነው ልንል አንችልም። በመንፈስ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ከሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተገኘ እውነት እንጂ በእነዚህ ጥቂት ጥቅሶች ላይ ብቻ በተገኘ እውነት ላይ መመሥረት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከላይ የተመለከትናቸው ጥቅሶች አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ መንፈስ ቅዱስ ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር እንዴት ይጋጫሉ? ለ) ሕይወትህን መርምር። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሕይወትህ እንዳይሠራ የከለከሉህ ኃጢአቶች አሉን?

ሐ) የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወትህ እንዳሉ ማረጋገጫ የሚሆኑ ነገሮችን በምሳሌነት ጥቀስ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: