የትንቢተ ኤርምያስ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ታላቅ ክርስቲያን፥ የተዋጣለት ወንጌላዊ ወይም ሰባኪ፥ በአገልግሎቱና በግል ሕይወቱ ሁልጊዜ የሚከናወንለት ይመስልሃልን?

መልስህን አብራራ። ለ) ክርስቲያኖች ከሆኑ ሕይወት እጅግ ቀላል እንደሚሆንላቸው፥ እግዚአብሔር ከበሽታ እንደሚጠብቃቸው፥ ሥራ እንደሚያገኙና ሀብታሞች እንደሚሆኑ አድርገው የሚያስቡ የምታውቃቸው ሰዎች አሉን? ይህ ነገር ሁልጊዜ እውን የሚሆን ይመስልሃል? ሐ) በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበሰለ ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም ወይም እግዚአብሔርን አይጠራጠርም ብለህ ታስባለህን? መልስህን አብራራ።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እጅግ በጣም ረጅሙ መጽሐፍ ትንቢተ ኤርምያስ ነው፤ ስለዚህ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት መጻሕፍት መካከል እንደ አንዱ አድርገው እንደሚቈጥሩት እናምናለን። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በመጽሐፉ ውስጥ ምን እንደሚያስተምር ለማየት ትንቢተ ኤርምያስን ሲያነቡ ወይም ሲያጠኑ አይታዩም። ትንቢተ ኤርምያስ ለብዙዎቻችን የተደበቀ መጽሐፍ ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር እንድናውቃቸው የሚፈልጋቸው በርካታ ጠቃሚ እውነቶች መጽሐፉን ባለማጥናታችን ተሰውረውብን ይኖራሉ።

በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥ የነቢዪ ኤርምያስን ታሪክና የተናገራቸውን ትንቢቶች እናገኛለን። በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ ነቢያት ሁሉ ስለ ሕይወቱ፥ ስላ አሳለፈው ትግል፥ ስለ ጥርጣሬውና ስለ ደረሰበት ስደት ይበልጥ በዝርዝር የተናገረ ኤርምያስ ነው። የኤርምያስን ሕይወት በምናጠናበት ጊዜ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚኖር ታላቅነትና በመንፈሳዊ ሕይወቱ ስለበሰለ ክርስቲያን ምንነት የሚኖሩን በርካታ አሳቦች ፈተና ይገጥማቸዋል። ኤርምያስ በእግዚአብሔር አመለካከት ታላቅ ሰው ነበር፤ ነገር ግን ብዙዎቻችን ኤርምያስ ጽኑ እምነት የሌለውና ታላቅ ሊባል የማይችል ሰው እንደሆነ ልናስብ እንችላለን፡- ታላላቅ ሊባሉ የሚችሉ ወንጌላውያንና ሰባኪዎች፥ ብዙ ነፍሳትን ለጌታ የሚማርኩና ሁልጊዜ ደስተኞች ሆነው እንዲሁም ሰምሮላቸው የሚኖሩ ሰዎች እንደሆኑ የማሰብ ዝንባሌ አለን። ይህ ግን ሁልጊዜ እውነት አይደለም። እግዚአብሔር ታላቅነታችንን የሚለካው ወደ ጌታ ባመጣናቸው በርካታ ሰዎች ምክንያት፥ ወይም ሰዎች በእኛ ደስ በመሰኘታቸው አይደለም። ታላቅነታችን የሚለካው እጅግ አስቸጋሪና አስጨናቂ በሆኑና እግዚአብሔርን ሳይቀር እንድንጠራጠር በሚጋብዙ ሁኔታዎች ውስጥ ለእግዚአብሔር በሚኖረን ታማኝነት ነው። የኤርምያስን ሕይወት በሚገባ ብንመለከት የሚከተሉትን ነገሮች ለማየት እንችላለን፡-

1. የኤርምያስ የስብከት አገልግሉት በሙሉ ከንቱ ይመስል ነበር። በሚያስተምረው ትምህርት የሚለወጡ ሰዎችን ማግኘት አልቻለም ነበር። ሕዝቡ ከክፋታቸው ተመልሰው በጽድቅ መንገድ ይመላለሱ ዘንድ ሊመራቸው አልቻለም። ይሁን እንጂ ኤርምያስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲናገር የሰጠውን መልእክት በታላቅ ብርታት ይናገር ነበር። መልእክቱ የማስጠንቀቂያና የፍርድ መልእክት ነበር። መልእክቱ ሰዎች ሊሰሙት የማይፈልጉት ዓይነት ቢሆንም እንኳ ኤርምያስ ለሕዝቡ ያመጣውን የእግዚአብሔርን መልእክት በታማኝነት ተናገረ። በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ያሰኘው ይህ ታማኝነቱ ነበር። 

2. የኤርምያስ ሕይወት በታላቅ መከራ፥ በስደትና በብቸኝነት የተሞላ ነበር። ኤርምያስ ሚስት ለማግባት የነበረው መብት በእግዚአብሔር ታግዶ ነበር። አብዛኛው የአገልግሎት ዘመኑ ሊያገለግላቸው በሞከረ ሰዎች በኩል በሚነሣበት ስደት የተሞላ ነበር። ይህ ነገር ኤርምያስን ብዙ ጊዜ በእጅጉ ተስፋ ያስቆርጠው ነበር። ስለ ሕዝቡ ኃጢአትና ዓመፅ ያውቅ ስለነበር በሕዝቡ ላይ ስለሚመጣው ጥፋት በማልቀሱ ምክንያት «አልቃሻው ነቢይ» ይባል ነበር (ለምሳሌ፡- ኤርምያስ 13፡17)። ኤርምያስ ብቸኝነት በእጅጉ ስላጠቃው ባይወለድ ይሻለው እንደነበር ሲመኝ እናገኘዋለን (ኤርምያስ 20፡13-18)። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔርን በመጠራጠር ይጠይቀው ነበር። ኤርምያስ ከእግዚአብሔር ዕቅድና ዓላማ ጋር ታግሏል፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ጥሪ ታማኝ ሆኖአል። እንዲሁም ታላቅ ስደትን ስላስከተለበትና ማንም ሰው ስለማይሰማው አገልግሎቱ ከንቱ የሆነ ቢመስልም የእግዚአብሔርን ቃል ተናግሯል።

3. ኤርምያስ በግል የነበረበት ትግል ከእግዚአብሒርና ከሌሎችም ጋር እውነተኛና ግልጽ ነበር። በሰዎች ፊት «ቅዱስ» በመምሰል፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያካሂደው የነበረውን ውስጣዊ ትግል ለመሰወር አልሞከረም። ይልቁንም በእግዚአብሔር ፊት ነበር። ታግሎ በሚጐዳበት ጊዜም ለእግዚአብሔር ይናገር ነበር። ያደረገውንም ትግል በመጽሐፉ ውስጥ መዝግቦታል። በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ ስላለው ትግል በእግዚአብሔርና በሌሎች ፊት ግልጽ መሆን የታላቅነት እንጂ የደካማነት ምልክት አይደለም። ቅዱስ የመምሰል ግብዝነትን ከማሳየት የመታቀብና ፍጹም ታማኝነትን የማሳየት ምልክት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ጊዜ ስለተዋጣለት የእግዚአብሔር ሰው ካለን አስተሳሰብ የኤርምያስ ሕይወት የሚለየው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ አገልግሎትህ ከንቱ እንደሆነ በማሰብ፥ የእግዚአብሔርን ዕቅድና ዓላማ በጥርጣሬ የጠየቅከበትን መንገድ ግለጽ። ሐ) ከኤርምያስ ሕይወት ስለ መሪነት ምን እንማራለን?

የትንቢተ ኤርምያስ ጸሐፊ

ትንቢተ ኤርምያስን የጻፈው የኬልቅያስ ልጅ ኤርምያስ ራሱ ነው። ኤርምያስ ያደገው የይሁዳ ዋና ከተማ ከሆነችው ከኢየሩሳሌም 5 ኪሎ ሜትር ያህል ወጣ ብላ በምትገኝ ዓናቶት በተባለች ትንሽ ከተማ ነበር። ወላጆቹ ከካህኑ ከአሮን የዘር ግንድ የመጡ ስለነበሩ ኤርምያስ ካህን ነበር። ኤርምያስ የተወለደው እግዚአብሔርን ይፈሩ ከነበሩ የአይሁድ ነገሥታት የመጨረሻው ኢዮስያስ በተወለደበት ዘመን ገደማ በ650 ዓ.ዓ. ነበር። ኢዮስያስ በይሁዳ ሁሉ የመንፈሳዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ከጀመረ (628 ዓ.ዓ.) ከአንድ ዓመት በኋላ (በ627 ዓ.ዓ.) ኤርምያስ የነቢይነት ጥሪውን ከእግዚአብሔር ተቀበለ። እግዚአብሔር መሪዎችን ወደ አገልግሎት ለመጥራት የሚጠቀምበት ዘዴ አንድ ዓይነት አይደለም፤ ነገር ግን ኤርምያስ ለሕዝቡ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ ሆኖ እንዲያገለግል በእግዚአብሔር መጠራቱን ያውቅ ነበር። ኤርምያስ ነቢይ ለመሆን ብቁ እንዳይደለ ቢሰማውም እንኳ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን መፍራት እንደሌለበት በመናገር፥ እግዚአብሔር ጥሪውን አረጋገጠለት። መልእክቱም የመልካም ተስፋ ቃል ኪዳን ያዘለ ሳይሆን የጥፋትና የፍርድ መልእክት እንደሆነ አስጠነቀቀው። ሕዝቡም መልእክቱን እንደማይሰሙና ኤርምያስን እንደሚቃወሙት በመንገር አስጠነቀቀው፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለሚሆን፥ ሕዝቡ ቢቃወሙትም እንደማያሸንፉት ተስፋ ሰጠው።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 1 አንብብ። ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሁሉ በኤርምያስ ጥሪ ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች ማስታወስና መታዘዝ የሚያስፈልጋቸው እንዴት ነው? ለ) ከእግዚአብሔር የተቀበልከው ምን ጥሪ አለህ? እግዚአብሔር በሕይወትህ እንድታከናውነው የሚፈልገው ምንድን ነው?

ንጉሥ ኢዮስያስ በይሁዳ ባካሄደው መንፈሳዊ ተሐድሶ ውስጥ የኤርምያስ ድርሻ ምን እንደነበር የምናውቀው ነገር የለም። ኤርምያስ የተቀረጹ ምስሎች ሁሉ እየተደመሰሱ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚካሄድ አምልኮ ሲታደስ በተመለከተ ጊዜ እጅግ እንደተደሰተ መገመት እንችላለን። ከዚያ በኋላ ግን ንጉሥ ኢዮስያስ በጦርነት በተገደለ ጊዜ ኤርምያስ እጅግ እንዳዘነ እንመለከታለን (2ኛ ዜና 35፡25 ተመልከት)። ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ መጥፋት የተነበየውና ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡ አጥብቆ መለመን የጀመረው ከኢዮስያስ ሞት በኋላ ነበር። ሕዝቡ አሻፈረኝ ብለው ወደ ጣዖት አምልኮ በተመለሱ ጊዜ ከእግዚአብሔር የሚመጣው ጥፋት የማይቀር መሆኑን ኤርምያስ አወቀ። ኤርምያስ ስለ ሕዝቡ እንዲጸልይ እንኳ እግዚአብሔር አልፈቀደም ነበር (ኤርምያስ 7፡16፤ 11፡14)። ኤርምያስ ሕዝቡ ሊጠፉ እንደቀረበ በመናገር መሪዎች እጃቸውን ለባቢሎናውያን እንዲሰጡ መጠየቅ ሲጀምር የተለያየ ጥቃትና ስደት ደረሰበት። የኤርምያስ የቅርብ ወዳጅ፥ መልእክቱን የጻፈለት ጸሐፊው ባሮክ ነበር። የትንቢቱን የመጀመሪያ ቅጅ ንጉሡ አቃጠለው (ኤርምያስ 36፡1-28)። ኤርምያስ ትንቢቶቹን እንደገና ጻፋቸው። ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰችና ሕዝቡ ተማርከው ከሄዱ በኋላ እንኳ አይሁድ በይሁዳ እንዲሰፍሩና ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ የሚመክራቸውን ኤርምያስን መስማት እምቢ አሉ። ይልቁንም ኤርምያስን አፍነው ወደ ግብፅ ወሰዱት። የአይሁድ አፈ ታሪክ እንደሚናገረው፥ ኤርምያስን በግብጽ ምድር በድንጋይ ወግረው የገደሉት አይሁድ ናቸው (ዕብራውያን 11፡37)። 

የኤርምያስ የነቢይነት አገልግሎት የተጀመረው በ626 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ የተጠቃለለው ደግሞ ከ586 ዓ.ዓ. በኋላ ነው። ይህ ማለት ኤርምያስ እግዚአብሔርን በታማኝነት ያገለገለው ከ40 ዓመታት በላይ ነው ማለት ነው።

የኤርምያስ ሕይወት በሁለት ዐበይት ባሕርያት ሊለይ ይችላል፤ የመጀመሪያው፥ ርኅራኄ ነው። የኤርምያስ መልእክት የጥፋት መልእክት የነበረ ቢሆንም፥ በደረሰበት ስደት ምክንያት መራር አልሆነም ወይም የሕዝቡን ሥቃይና መከራ አይቶ ርኅራኄ አልጐደለውም ነበር። ኤርምያስ አልቃሻው ነቢይ በመባል ይታወቅ እንደነበር ቀደም ሲል ጠቅሰናል፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ በመጽሐፉ ውስጥ በአጠቃላይ የሕዝቡን ኃጢአትና የሚደርስባቸውን ጥፋት በሚመለከት ስለ ውስጣዊ ሥቃዩና ኃዘኑ ማንበብ ስለሚቻል ነው። (ለምሳሌ፡- ኤርምያስ 8፡21-9፡1)። እንደ እውነቱ ከሆነ ከኢየሩሳሌም መደምሰስ በኋላ ኤርምያስ የጻፈው ሰቆቃወ ኤርምያስ ለሕዝቡ ያለቀሰው ልቅሶ ወይም ሙሾ የተመዘገበበት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች በመመልከት ኤርምያስ የተጋፈጣቸውን ችግሮች ዘርዝር፡- ኤርምያስ 16፡1-4፤ 20፡1-3፤ 26፡11-15፤ 28፡10-11፤ 36፡19፥ 26፤ 37፡11-15፤ 38፡5-6።

ሁለተኛ፥ ኤርምያስ በጣም ድፍረትና ብርታታ የነበረው ሰው ነበር። ብዙ ጊዜ ተስፋ የቆረጠ ቢሆንም፥ የነቢይነት አገልግሉቱን ግን አቋርጦ አያውቅም። ኤርምያስ ከሌሎቹ ነቢያት ሁሉ የላቀ ስደት የደረሰበት ነቢይ ነበር። በቤተ መቅደስ ተይዞ ለአንድ ምሽት በሰንሰለት ታስሮአል። ስለ ቤተ መቅደሱ መደምሰስ በተናገረ ጊዜ ካህናትና ሐሰተኞች ነቢያት ሊገድሉት ሞክረው ነበር። (ኦርዮ የተባለ ሌላ ነቢይ የተገደለው በዚህ ጊዜ ነበር (ኤርምያስ 26፡20-23])። ትምህርቱን ይቃወሙ በነበሩ ሐሰተኞች ነቢያት የማያቋርጥ ጥቃት ደርሶበታል። ኤርምያስ በተወለደበት ከተማ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ሳይቀሩ ተቃውመውት ሊገድሉት ዝተውበት ነበር (ኤርምያስ 11፡21-23)። የመጀመሪያው መጽሐፉ የተቃጠለ ሲሆን፥ ንጉሡም እርሱንና ጸሐፊውን ባሮክን ለመያዝ ሞክሮ ነበር። ከባቢሎን ጋር በተደረጉት የመጨረሻ ጦርነቶች በንጉሡ ላይ ዓመፅ አነሣሥተሃል ተብሎ ተከሶአል፤ ተገርፎአል፤ በእስር ቤትም ተጥሏል። በኋላ ደግሞ ንጉሥ ሴዴቅያስ በግዞት አስቀምጦታል። ሴዴቅያስ ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ብሎ ኤርምያስን የሚያሰጥም ጭቃ ባለበት ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል አድርጓል። በኋላ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አዳነውና እንደገና በግዞት እንዲቆይ አደረገው። ኤርምያስ የተራበ፥ ወደ እስር የተጣለ፥ የተገረፈና ብዙ ጊዜ ሕይወቱ ለሞት አደጋ የተጋለጠ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር የሰጠውን መልእክት በታማኝነት ከማስተላለፍ ወደኋላ አላለም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ርኅራኄና ድፍረት በዚህ ዘመን ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እጅግ አስፈላጊ ባሕርያት የሆኑት ለምንድን ነው? ለ) እነዚህ ባሕርያት በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብዙ ጊዜ ይታያሉን? ካልታዩስ ለምን? ሐ) እነዚህ ባሕርያት በሕይወትህ ይታያሉን? ሕይወትህን በመመርመር እነዚህን ባሕርያት በሕይወትህ እንዲጐለብቱልህ እግዚአብሔርን በጸሉት ለምነው።

በዚህ ጊዜ በይሁዳ የሚያገለግል ነቢይ ኤርምያስ ብቻ አልነበረም። ኤርምያስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ሶፎንያስ ያገለግል ነበር። ኤርምያስ ባገለገለበት ዘመን በይሁዳ ያገለግሉ የነበሩ ነቢያት ዕንባቆምና ምናልባት አብድዩ ነበሩ። በኤርምያስ ዘመን መጨረሻ ገደማ ሕዝቅኤልም ያገለግል ነበር፤ ነገር ግን የሚኖረው በባቢሎን በምርኮ ነበር። 

የኤርምያስ ታሪካዊ ሥረ መሠረት

ኤርምያስ የተወለደውና የመጀመሪያዎቹን የሕይወት ዘመኑን የኖረው የይሁዳ ሕዝብ የመጨረሻዎቹን የሰላም ዓመታት ባሳለፉበት ጊዜ ነበር። ኤርምያስ ከተወለደበት ከ650 ዓ.ዓ. ጀምሮ ኢዮስያስ እስከሞተበት እስከ 609 ዓ.ዓ. በይሁዳ ፖለቲካዊ ሰላምና ሃይማኖታዊ መነቃቃት ነበር። ንጉሥ ኢዮስያስ እግዚአብሔርን በመፍራት መንፈሳዊ ተሐድሶንና መነቃቃትን ወደ ይሁዳ ለማምጣት ሞክሯል። ከፖለቲካ አንጻር ጊዘው ሰላም የሰፈነበት ነበር። የይሁዳ ጠላት የነበረችው አሦር በሥልጣን እጅግ እያሽቁላቀለች የመጣችበትና ተከታይዋ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነችው ባቢሎን ደግሞ ገና ያልተጠናከረችበት ወቅት ነበር፤ ስለዚህ ይሁዳ ብቻዋን ቀርታ ነበር። ኤርምያስ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሁሉ ነቢይ ሆኖ ያገለገለ ቢሆንም፥ ስለ አገልግሎቱ ብዙ የምናውቀው ነገር የለም። 

በ612 ዓ.ዓ. ነገሮች ተለወጡ። አሦር የሚቀጥለው የዓለም ኃያል መንግሥት በሆነችው በባቢሎን ተሸነፈች። በ609 ዓ.ዓ. ግብፆች ከባቢሎን ጋር በተደረገ የመጨረሻ ጦርነት ከአሦር ጋር ለመተባበር በይሁዳ በኩል አለፉ። ንጉሥ ኢዮስያስ ግብፆች አገሩን እንደመተላለፊያ እንዲጠቀሙ ከመፍቀድ ይልቅ ከግብፆች ጋር ለመዋጋት ወጣ። ይህ ጦርነት እርሱን የሚመለከት ስላልነበረ የሞኝነት ሥራ ሠራ። በዚህ ጦርነት ንጉሥ ኢዮስያስ ተገደለ። በንጉሡ ሞት የይሁዳ ሕዝብና መንግሥት ወዲያውኑ ተብረከረኩ። ኢዮስያስ ከተገደለበት ከ609 ዓ.ዓ. ጀምሮ የይሁዳ ሕዝብ እስከተመቱበት እስከ 586 ዓ.ዓ. ድረስ የነበረው ወቅት በይሁዳ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስጨናቂ ጊዜ ነበር።

የኢዮስያስ ታላቅ ልጅ ኢዮአካዝ ጥቂት ወራት ብቻ ከነገሠ በኋላ (609 ዓ.ዓ.) በግብፅ ንጉሥ ተማርኮ ተወሰደ። ይህ ንጉሥ በምርኮ ከተወሰደበት ጊዜ ጀምሮ ኤርምያስ እንደወዳጅ የሆነ ንጉሥ ስላልገጠመው ስደት ይደርስበት ጀመር።

የኢዮስያስ ሁለተኛ ልጅ ኢዮአቄም የሚቀጥለው ንጉሥ በመሆን ከ609-598 ዓ.ዓ. ድረስ ገዛ። ኢዮአቄም እንደ አባቱ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ስላልነበረ ኢዮስያስ አስገኝቶ የነበረውን መንፈሳዊ ተሐድሶ በሙሉ ወዲያውኑ ደብዛው እንዲጠፋ አደረገ። የጣዖት አምልኮ በይሁዳ ሁሉ ተስፋፋ። አብዛኛው የኤርምያስ አገልግሉት የተካሄደው በዚህ ጊዜ ነበር። ኤርምያስ ሕዝቡ በፍጥነት ወደ ጣዖት አምልኮ መመለሳቸውን በማየቱ የይሁዳ ጥፋት በደጅ መሆኑን አውቆ ነበር። እነዚህን የጣዖት አምልኮ በግልጽ በመቃወሙ፥ ከኢዮአቄም ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻን አተረፈ። በ606 ዓ.ዓ. ኃያል የሆነው የባቢሎን መንግሥት ይሁዳን ማጥቃት ጀመረ። ጦርነቱ እጅግ ከፍተኛ እንኳ ባይሆንም፥ ኢዮአቄም የባቢሎን ተገዥ ሆነ። ዳንኤልና ሌሎች ንጉሣውያን ቤተሰቦች ተማርከው የሄዱት በዚህ ጊዜ ነበር። በ598 ዓ.ዓ. ኢዮአቄም በባቢሎን ላይ ለማመፅ ወሰነ። ባቢሎን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት ጥቃት አካሄደችና ይሁዳን ድል አደረገቻት፤ ኢዮአቄምም ሞተ። ንጉሥ ናቡከደነፆር የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው። እዚያም ቀሪውን የሕይወት ዘመኑን አሳለፈ። በተጨማሪ ከይሁዳ ታዋቂ ሰዎች አሥር ሺህ ያህሉን ማርኮ ወደ ባቢሎን አፈለሳቸው። በዚህ ምርኮ ከተወሰዱት መካከል ሕዝቅኤልም ይገኝበታል። በይሁዳ የቀሩት ያልተማሩና ድሀ ሰዎች ብቻ ነበሩ።

የመጨረሻው የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ የኢዮአቄም ወንድም ሴዴቅያስ ነበር። ይህ ንጉሥ ከኤርምያስ ጋር የነበረው ግንኙነት ተለዋዋጭ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ኤርምያስ የሚለውን ይሰማና ይረዳው ነበር፤ ዳሩ ግን የኤርምያስን ምክር ለመታዘዝ ፈቃደኛ አልነበረም። በሌላ ጊዜ ደግሞ በኤርምያስ ላይ ስደት እንዲነሣ አደረገ። በ586 ዓ.ዓ. በባቢሎን ላይ በማመፁ፥ ባቢሎናውያን በይሁዳ ላይ የነበራቸው ትዕግሥት ተሟጠጠ። የባቢሎን ጦር የሴዴቅያስን ልጆች ገደለ፤ ሴዴቅያስን አሳወረና ማረከው። የኢየሩሳሌምን ከተማ ቅጥሮች፥ ሕንጻዎችና ቤተ መቅደሱን አፈራረሰ። ኤርምያስ ይህንን ሁሉ ሞትና ጥፋት በጥልቅ ኃዘን ተመለከተ። ዳሩ ግን ከ70 ዓመታት በኋላ የይሁዳ ሕዝብ ከምርኮ በመመለስ ቤተ መቅደሱንና ቅጥሩን እንደገና እንደሚሠሩ እግዚአብሔር ተስፋ ሰጥቶ ስለነበር ይህ ነገር ጊዜያዊ መሆኑን ያውቅ ነበር (ኤርምያስ 25፡10-12፤ 29፡10)።

ማስታወሻ፡- ይህ የሰባ ዓመታት ምርኮ በተለያዩ መንገዶች ሊቀርብ ይችላል። የፖለቲካ ምርኮው የተጀመረው የመጀመሪያዎቹ ምርኮኞች ወደ ባቢሎን በተወሰዱበት በ605 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ የተፈጸመው ደግሞ አይሁድ ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ በተፈቀደላቸው በ538 ዓ.ዓ. ነበር። የሃይማኖት ምርኮው ደግሞ የተጀመረው ቤተ መቅደሱ በተደመሰሰበት በ586 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ የተጠቃለለው ደግሞ ቤተ መቅደሱ እንደገና በተሠራበት በ516 ዓ.ዓ. ነበር።

በኤርምያስ ሕይወት ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ዋና ዋና ዓመታት፡-

650 ዓ.ዓ. – ኤርምያስ ተወለደ፤

640 ዓ.ዓ. – ኢዮስያስ ነገሠ፤

628 ዓ.ዓ. – ኢዮስያስ መንፈሳዊ ተሐድሶ ጀመረ፤ 

627 ዓ.ዓ. – ኤርምያስ የነቢይነት ጥሪውን ከእግዚአብሔር ተቀበለ፤ 

612 ዓ.ዓ. – አሦር በባቢሎን እጅ ወደቀች፤ 

609 ዓ.ዓ. – ኢዮስያስ በጦርነት ተገደለ፤ 

605 ዓ.ዓ. – ባቢሎን ይሁዳን አስገበረች፤ ዳንኤል በምርኮ ተወሰደ፤ 

597 ዓ.ዓ. – ባቢሎን ኢየሩሳሌምን አሸነፈች፤ ሕዝቅኤልና አሥር ሺህ ሰዎች ተማረኩ፤

586 ዓ.ዓ. – ባቢሎን ኢየሩሳሌምን ደመሰሰች። 

ትንቢተ ኤርምያስ

ትንቢተ ኤርምያስ የተሰየመው በጸሐፊው በነቢዩ ኤርምያስ ስም ነው (ኤርምያስ 1፡1)። መጽሐፉ እንዴት እንደተጻፈ ኤርምያስ የተለያዩ ፍንጮችን ይሰጠናል። ከመጽሐፉ የተወሰኑ ክፍሎች የተጻፉት ኤርምያስ ለ20 ዓመታት ከተነበየ በኋላ፥ በ605 ዓ.ዓ. መሆኑን እናውቃለን። መጽሐፉን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ኤርምያስን አዘዘው (ኤርምያስ 36፡1-3 ተመልከት)። መጽሐፉን የጻፈው ኤርምያስ ራሱ አልነበረም። መጽሐፉን ለማስጻፍ ጸሐፊውን ባሮክን ተጠቀመበት (ኤርምያስ 36፡4)። ንጉሥ ኢዮአቄም የመጀመሪያውን ቅጅ ባነበበ ጊዜ አቃጠለው፤ ስለዚህ ኤርምያስ መጽሐፉን ለሁለተኛ ጊዜ ጻፈው። ይህ ትንቢት ዛሬ በእጃችን በሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ክፍል ሳይሆን አይቀርም (ኤርምያስ 36፡32)።

አንዳንድ ምሁራን ኤርምያስ የጻፈው የመጀመሪያ መጽሐፉ ከትንቢተ ኤርምያስ የመጀመሪያ ክፍል ማለት ከምዕራፍ 1-25 ጋር ተመሳሳይ ነው ይላሉ። ይህንንም የኤርምያስ የመጀመሪያ የትንቢት መጽሐፍ ብለው የሚጠሩት ሲሆን፥ በዚህ ክፍል ያለው አብዛኛው ንግግር ኤርምያስ ራሱ እንደተናገረው ተደርጎ የተጻፈ ነው። ቆይቶ ሌሎች ሁለት የትንቢተ ኤርምያስ ክፍሎች ተጨመሩ። ኤርምያስ 30-31 የኤርምያስ ሁለተኛ መጽሐፍ ተብሎ ሲጠራ፥ ኤርምያስ 46-51 ደግሞ ሦስተኛ መጽሐፍ ተብሎ ይጠራል። በኋላ በሌሎች ሦስት ክፍሎች ባሮክ ወይም ሌላ ሰው ስለ ኤርምያስ ሕይወት የሚናገሩ ታሪኮችን እንደጨመረ ይገመታል፤ እነርሱም፡- ኤርምያስ 26-29፤ 32-45 ና 51፡59-52፡34 ናቸው።

ትንቢተ ኤርምያስ የተጻፈው በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት ሳይሆን በተለየ መንገድ ነው። ቀጥሎ የትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፎች በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት ተገልጸዋል፡-

1. በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የተጻፉ ምዕራፎች፡- ኤርምያስ 1-7፡15፥ 

2. በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት የተጻፉ ምዕራፎች፡- ኤርምያስ 22፡10-12፥ 

3. በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተጻፉ ምዕራፎች፡- ኤርምያስ 26፤ 7፡16-20፡18፤ 25፤ ምዕራፍ 35 ና 36፤ 45-46፡12፤ ምዕራፍ 47-49፥ 

4. በኢኮንያን ዘመነ መንግሥት የተጻፉ ምዕራፎች፡- ኤርምያስ 22፡1-9፥ 13-20፤ 23፥

5. በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት የተጻፉ ምዕራፎች፡- ኤርምያስ 24፤ 27-34፤ 37-39፤ 46፡13-28፤ 50-51፥ 

6. ከኢየሩሳሌም መውደቅ በኋላ የተጻፉ ምዕራፎች፡- ኤርምያስ 40-44፤ 52 ናቸው። 

የማይመስል ቢሆንም እንኳ የብሉይ ኪዳን ረጅሙ መጽሐፍ ትንቢተ ኤርምያስ ነው። ኤርምያስ መልእክቱ ኃይል እንዲኖረው ለማድረግ ግጥምን ከስድ ንባብ ጋር አቀናጅቶ ያቀረበ፡ የሥነ-ጽሑፍ ጥበብ የነበረው ሰው ነበር። በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥ አራት ዓይነት ዐበይት ስብከቶችን እናገኛለን፡-

ሀ. የይሁዳን ኃጢአት የሚገልጹ ስብከቶች (ለምሳሌ፡- ኤርምያስ 5-9)፡- ኤርምያስ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ትተው ጣዖታትን ስላመለኩና በሲና ተራራ ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ስላፈረሱ ይገሥጻቸዋል። 

ለ. በይሁዳ ላይ የሚመጣውን ፍርድ የሚያመለክቱ ስብከቶች፡- ይህኛው ከሁሉም ዓይነት ስብከት ይልቅ የተለመደ የስብከት ዓይነት ነው። በኢየሩሳሌም ላይ ሊመጣ ስላለው ጥፋትና ስለ ሕዝቡ መማረክ ይናገራል። በቃል ኪዳኑ ውስጥ የነበሩት መርገሞች እንዴት እንደተፈጸሙ ያመለክታል (ዘዳግም 28:15-68ን ከኤርምያስ 11፡8 ጋር አወዳድር)። 

ሐ. ለሕዝቡ ትምህርት የሚሰጡ ስብከቶች፡- እነዚህ ሕዝቡ መንገዳቸውን እንዲለውጡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚለምኑ ወይም እግዚአብሔር በአሕዛብ አማልክትና ጣዖታት ላይ ያለውን ሥልጣንና ታላቅነት የሚያሳዩ ስብከቶች ናቸው። 

መ. የመጽናኛ ስብከቶች፡- እንደ ትንቢተ ኢሳይያስ በተለየ መንገድ ሕዝቡን የሚያጽናኑ ብዙ ስብከቶች አላቀፈም። ይሁን እንጂ ኤርምያስ ለእግዚአብሔር ባላቸው ታማኝነት ጸንተው የሚቆዩ ጥቂቶችን ያጽናናል። ኤርምያስ ከሰባ ዓመታት በኋላ ከምርኮ እንደሚመለሱ ለሕዝቡ ተናገረ። እንዲሁም አንድ ቀን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ስለሚያደርገው «አዲስ ቃል ኪዳን» ተናግሯል (ኤርምያስ 29፡10-11፤ 31፡31-34)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ አራት ዓይነት ስብከቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊሰበኩ የሚችሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) በብዛት የሚሰበከው የትኛው ስብከት ነው? ለምን? ሐ) ሁሉም ዓይነት ስብከት ይሰበክ ዘንድ ስብከቶቻችንን ሚዛናዊ አድርጎ ማቅረብ አስፈላጊ ነውን? ለምን?

እንደ ሕዝቅኤል ሁሉ ኤርምያስም መልእክቱን ለማጠናከር በርካታ ምሳሌያዊ ተግባራትን አከናውኖአል፡- ከተልባ እግር የተሠራች የተበላሸችውን መታጠቂያ (ኤርምያስ 13፡1-11)፥ የተሰባበረች ገንቦ (ኤርምያስ 19፡1-12)፥ የእስራት ቀንበርን (ኤርምያስ 27)፥ የተሸሸጉ ድንጋዮችን (ኤርምያስ 43፡8-13)፡ ሚስት ከማግባትና ልጆችን ከመውለድ መታቀብን (ኤርምያስ 16፡1-4፥ ቀብርና ሠርግ ወዳለበት ቤት አለመግባት (ኤርምያስ 16፡5-9)፥ በተወለደበት ከተማ መሬት መግዛትን (ኤርምያስ 32፡6-15) እና የሸክላ ሥራን (ኤርምያስ 18፡1-10) ተጠቅሞአል።

የትንቢተ ኤርምያስ አስተዋጽኦ

የትንቢተ ኤርምያስን አስተዋጽኦ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ነው። በአጠቃላይ በመጽሐፉ ውስጥ የሚታይ ግልጽ የሆነ ዐቢይ አሳብ የለም። እያንዳንዱ ምዕራፍ ከሌሎች ምዕራፎች የተለየ ትምህርት የሚሰጥ ይመስላል። የትንቢተ ኤርምያስን አስተዋጽኦ ማዘጋጀት አስቸጋሪ የሆነበት ሌላው ምክንያት በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አለመቅረቡ ነው።

ቀጥሉ አንድ የትንቢተ ኤርምያስ አስተዋጽኦ ቀርቧል፡-

1. የኤርምያስ ለነቢይነት መጠራት (ኤርምያስ 1)፥ 

2. ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያና ማበረታቻ (ኤርምያስ 2-35)፥ 

3. በኤርምያስ ላይ የደረሰው ስደትና መከራ (ኤምያስ 36-38)፥ 

4. የኢየሩሳሌም ውድቀትና ያስከተለው ውጤት (ኤርምያስ 39-45)፥ 

5. በአሕዛብ ላይ የተላለፉ የፍርድ ትንቢቶች (ኤርምያስ 46-51)፥ 

6. ታሪካዊ መደምደሚያ (ኤርምያስ 52)።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኤርምያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በዚያ ከተጠቀሱት እውነቶች መካከል እጅግ ጠቃሚ የሆኑትን ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: