ትንቢተ ሕዝቅኤል በርካታ የሆኑ ልዩ ገጽታዎች እና አስተዋጽኦ

ትንቢተ ሕዝቅኤል በርካታ የሆኑ ልዩ ገጽታዎች አሉት፡-

1. ሕዝቅኤል ከማንኛውም የብሉይ ኪዳን ትንቢት መጻሕፍት በላቀ ሁኔታ (ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል 15 እና 16) በርካታ ምልክቶችንና ምሳሌዎችን ይጠቀማል። ለምሳሌ ሕዝቅኤል ብዙ አገሮችን በሕይወት እንዳሉ ፍጥረታት አድርጎ ያቀርባል። ኢየሩሳሌምና ሰማርያ በአመንዝራ ሴቶች፥ የዳዊት ንጉሣዊ የዘር ግንድ በአንበሳ ዋሻና በወይን ተክል፥ ግብፅ በአዞ፥ ባቢሎን ደግሞ በንሥር ተመስለው ቀርበዋል።

2. ሕዝቅኤል የነቢይነት መልእክቱን ለማስተላለፍ በአሁኑ ጊዜ በየአብያተ ክርስቲያናታችን እንደምናቀርባቸው ተውኔቶች (ድራማዎች) በተግባር በማሳየት ያቀርብ ነበር (ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል 3፡22-26፤ 4፡1-3)። እነዚህ በገቢር የሚታዩ ትዕይንቶች የፍርድን ቃል እየሰሙ ንስሐ እንዳይገቡ ልባቸውን ያጠነከሩትን አይሁድ ለማስደንገጥ የቀረቡ ነበሩ። 

3. ሕዝቅኤል ጠንከር ያለና የሚያስቈጣ ቋንቋ በመጠቀም፥ ሕዝቡን በእግዚአብሔር አመለካከት ኃጢአት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ ለማስገንዘብ ሊያስደነግጣቸው ይሞክር ነበር (ለምሳሌ፡- ኢየሩሳሌምን አመንዝራይቱ እያለ ይጠራታል)። 

4. አብዛኛዎቹ የትንቢት መጻሕፍት የተጻፉት በግጥምና ቅኔ የአጻጻፍ ስልት ሲሆን፥ የትንቢተ ሕዝቅኤል አብዛኛው ክፍል ግን የተጻፈው በስድ ንባብ አጻጻፍ ስልት ነው። 

5. ሕዝቅኤል መልእክቶቹን የተቀበለው በራእይ አማካይነት ነበር (ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል 1-3)። ከሕዝቅኤል በፊት ብዙ ነቢያት መልእክታቸውን በራእይ ሲቀበሉ አናይም። ራእይ ካላቸው ደግሞ ራእያቸው እንግዳ በሆኑ ተምሳሌቶች የተሞላ አልነበረም። ከሕዝቅኤል ጀምሮ ግን ነቢያት በብዙ ምልክቶች የተሞሉ ራእዮችን የመቀበል ዝንባሌያቸው ጨምሯል። የዚህ ዓይነቱ ትንቢት «አፓካሊፕቲክ» ትንቢት በመባል ይታወቃል። በዚህ ዓይነት ትንቢት ውስጥ ጨርሶ ያልተለመዱና በከፍተኛ ደረጃ ተምሳሌታዊ የሆኑ ራእዮች ይኖራሉ። በመንፈስ የሚደረጉ ጕዞዎች፥ የመላእክት ጐብኝት፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ፍርድ ወዘተ በተፈጥሮ ላይ ላለው የበላይ ተቁጣጣሪነት የሚሰጥ ትኩረት ይታያል። ከእንደነዚህ ዓይነት የትንቢት መጻሕፍት የሚመደቡት ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ዳንኤልና ዘካርያስ፥ ከአዲስ ኪዳን ደግሞ የዮሐንስ ራእይ ናቸው። 

የትንቢተ ሕዝቅኤል አስተዋጽኦ

1. የሕዝቅኤል ለነቢይነት መጠራት (ሕዝ. 1-3) 

2. በኢየሩሳለምና በይሁዳ ላይ የተነገሩ ትንቢቶች (ሕዝ. 4-24)፥ 

3. በተለያዩ የአሕዛብ መንግሥታት ላይ የተነገሩ ትንቢቶች (ሕዝ. 2532)፥ 

4. ስለ ወደፊቱ የእስራኤል መመለስ የተነገሩ ትንቢቶች (ሕዝ. 33-48)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: