ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መካከል ትንሹ አብድዩ ነው። ትንቢተ አብድዩ አንድ ምዕራፍ ብቻ ያለው ሆኖ ስለ ኤዶምና ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚመጣባት ፍርድ ይናገራል። በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ከሚያተኩሩ ሦስት የትንቢት መጻሕፍት መካከል አንዱ አብድዩ ነው። አብድዩ በኤዶም ላይ ሲተነብይ፥ ዮናስና ናሆም ደግሞ በአብዛኛው በአሦር መንገሥት ላይ ተንብየዋል።
የውይይት ጥያቄ፥ ስለ አብድዩ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ መጽሐፉ ያገኘሃቸውን ዐበይት እውነቶችን ዘርዝር።
የትንቢተ አብድዩ ጸሐፊ
መጽሐፈ አብድዩ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ራእይ የያዘ መጽሐፍ ስለመሆኑ በትንቢተ አብድዩ መጀመሪያ ቁጥር ላይ ተጠቅሷል። በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ ይህ «ራእይ» የተሰኘ ቃል መልእክቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በቀጥታ የመጣ መሆኑን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ይህም ሲባል፥ መልእክቱ የተገኘው ሌሊት በታየ ሕልም ወይም ራእይ አማካይነት ብቻ መሆኑን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል አይደለም።
ከስሙ በቀር ስለ አብድዩ የምናውቀው አንዳችም ነገር የለም። ኢየሩሳሌም በጠላቶችዋ ጥቃት በደረሰባት ጊዜ ኤዶም ላደረገችው ነገር ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ አብድዩ የኖረው በይሁዳ ሳይሆን አይቀርም። አብድዩ የሚለው ስም በጣም የተለመደ አይሁዳዊ ስም ቢሆንም፥ ይኸኛው አብድዩ ግን በመጽሐፈ ነገሥት፥ ዜና መዋዕል፥ ዕዝራና ህምያ የተጠቀሰው ሰው መሆኑ አጠራጣሪ ነው።
ትንቢተ አብድዩ ስለ ተጻፈበት ጊዜ ምሁራን የተለያየ አሳብ ይሰነዝራሉ። መጽሐፉ ከ850-400 ዓ.ዓ. ባሉት ጊዜያት መካከል በየትኛውም ወቅት ተጽፎ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ መካከል የበለጠ ድጋፍ ያላቸው ሁለት ጊዜያት አሉ። እነርሱም፡-
ሀ. በኢዮራም ዘመነ መንግሥት (853-841 ዓ.ዓ.)፡- ኢየሩሳሌም በፍልስጥኤማውያንና በዐረቦች በተጠቃች ጊዜ ነበር (2ኛ ነገሥት 8፡20-22)። አብድዩ የኖረው በዚህ ጊዜ ከሆነ፥ መልእክቶቻቸው በመጻሕፍት ከተያዙ ነቢያት መካከል የመጀመሪያው ይሆናል። የኖረውም በኤልሳዕ ዘመን ሊሆን ይችላል ማለት ነው።
ለ. ባቢሎን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ባደረሰች ጊዜ (606-586 ዓ.ዓ.)፡- ይህ ከሆነ ደግሞ አብድዩ የኖረው በኤርምያስ ዘመን ነበር ማለት ይሆናል። አብድዩ የተጻፈበት ጊዜ ይህ ሳይሆን አይቀርም።
ታሪካዊ ሥረ- መሠረት
የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኤዶም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ኤዶምና ይሁዳ ይህን ያህል ጠላትነት ለምን እንዳደረባቸው አብራራ።
ትንቢተ አብድዩን ለመረዳት፥ የኤዶምንና የይሁዳን ልዩ ልዩ ታሪኮች መመልከት አለብን። ይስሐቅ ሁለት ልጆች እንደነበሩት ታስታውሳለህ። ትልቁ ዔሳው ትንሹ ደግሞ ያዕቆብ ይባሉ ነበር። ያዕቆብ በማታለል የብኩርናን በረከት ከአባቱ ሲያገኝ፥ ከዔሳው ዘንድ ደግሞ ጥላቻን አተረፈ። ይህ ጥላቻ ወደ ዔሳውና ያዕቆብ የልጅ ልጆች ሁሉ ተላለፈ። የዔሳው ዝርያዎች ኤዶማውያን ሲሆኑ፥ የያዕቆብ ዝርያዎች ደግሞ ምርጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን ሆኑ። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጠችውን የተስፋ ምድር ወረሱ። ኤዶማውያን ደግሞ ከእስራኤል በስተደቡብ በሚገኘው በረሃ ኖሩ።
እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት ነፃ አውጥቶአቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚጓዙበት ጊዘ በኤዶም ምድር ለማለፍ ፈለጉ። ኤዶማውያን ግን ሊያሳልፏቸው ፈቃደኞች ስላልነበሩ፥ እስራኤላውያን በርካታ የሆኑ ተጨማሪ ብዙ ኪሎ ሜትሮች መጓዝ ነበረባቸው (ዘኁልቁ 20፡14-21፤ 21፡14)። አይሁዳውያን ኤዶማውያን ያደረጉባቸውን ነገር ሊረሱ በጭራሽ አልቻሉም ነበር።
በኋላም በዳዊትና በሰሎሞን አመራር እስራኤላውያን ኤዶምን ወርረው በመያዝ ተቆጣጠሯት። ይህ የበላይነት ኤዶማውያን ዓምፀው ነፃነታቸውን እስካገኙበት (2ኛ ነገሥት 8፡20-22) እስከ ኢዮራም ዘመነ መንግሥት ድረስ ቀጠለ (853-841 ዓ.ዓ.)። የተለያዩ የይሁዳ ነገሥታት ኤዶምን ደግመው ለመያዝ ቢሞክሩም የተቈጣጠሩዋት ለጊዜው ብቻ ነበር።
በ597 ዓ.ዓ. ባቢሎን ይሁዳን ተቆጣጠረች። በዚህ ጊዜ ኤዶማውያን መንግሥታቸውን በማስፋፋት ከይሁዳ ምድር የተወሰኑ ክፍሎችን ተቆጣጠሩ። ባቢሎን በ586 ዓ.ዓ. ይሁዳን በማጥቃት ስትደመስሳት፥ ኤዶማውያንም ከባቢሎን ጋር በማጥቃቱ ተባበሩ። አይሁድ ተማርከው ሲሄዱም ኤዶማውያን ከይሁዳ ምድር ተጨማሪ ግዛቶችን ያዙ። ይህም በትንቢተ አብድዩ ውስጥ የምናገኘው ጠንከር ያለ ትንቢት በኤዶም ላይ እንዲነገር አደረገ። አብድዩ የኤዶም አገር እንደገና ለማንሰራራት በማይችልበት ሁኔታ ፍጹም እንደሚደመሰስ ተነበየ።
የኤዶም አገር በሚልክያስ ዘመን እንዴት ጨርሶ እንደጠፋና መንግሥቱም እንደተደመሰሰ መናገር አስቸጋሪ ነው። (በ450 ዓ.ዓ.) የተለያዩ የዐረብ ነገዶች ኤዶምን በተደጋጋሚ አጥቅተው ሳያጠፏት አልቀሩም። በ312 ዓ.ዓ. የናባቲያን ዐረቦች ኤዶምንና ዋና ከተማዋን ጴጥራን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ። የኤዶም ሰዎች በኋላ ኤዶማውያን ሆኑ። በአይሁድ ተሸነፉና የእነርሱን ወግ ለመከተል ተገደዱ። (በመሠረቱ ታላቁ ሄሮድስ የኤዶም ሰው ወይም ኤዶማዊ ነበር)። ኤዶማውያን በ70 ዓ.ም. በሮም ላይ በተደረገው ዓመፃ ከእስራኤላውያን ጋር በመተባበራቸው ሙሉ በሙሉ ተደመሰሱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታሪክ ስለ እነርሱ ተወስቶ አናገኝም። ዋና ከተማቸው ጴጥራ በ636 ዓ.ም. በሙስሊሞች ተደመሰሰች። እግዚአብሔር አስቀድሞ በአብድዩ በኩል እንደተናገረው፥ ዛሬ የኤዶም ሰዎች ወይም የኤዶም መንግሥት የለችም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ለመፈጸም ብዙ ምእተ ዓመት ሊወስዱ ቢችሉም፥ እግዚአብሔር የተናገራቸው የተስፋ ቃሉችና ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ተስፋዎቹንና ትንቢቶቹን እንደሚፈጽም ከሚገልጸው እውነታ የምንመለከተው የእግዚአብሔር ባሕርይ ምንድነው? ለ) ይህ ባሕርይ መጽናኛ የሚሆነን ለምንድን ነው?
የትንቢተ አብድዩ አስተዋጽኦ
1. በኤዶም ላይ የሚመጣ ፍርድ (አብድዩ 1-14)
2. የጌታ ቀን (አብድዩ 15-21)
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡