ትንቢተ ሐጌ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ ማቴዎስ 6፡33 አንብብ። ሀ) ከሁሉ አብልጠን ልንፈልጋቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) «ይህም ሁሉ» ምንን ያመለክታል? ሐ) ይህን ጥቅስ በሕይወትህ የተጠቀምህበት እንዴት ነው?

ምናልባት በሕይወታችን እጅግ አስቸጋሪ የሆነውና ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ለይጣን ብዙ ጊዜ እኛን የሚያሸንፍበት መንገድ ለክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን ፍቅር በሌላ ፍቅር እንድንተካ ማድረጉ ነው። ይህም ሌላ ፍቅር ቤተሰባችን፥ ቁሳዊ ሀብታችን ወይም ንብረታችን፥ በሌሉች ዘንድ ያለን ታዋቂነት፥ ትምህርት፥ ወዘተ. ላይ ያተኩረ ሊሆን ይችላል። ሰዎችን ወይም የተለያዩ ነገሮችን ከእግዚአብሔር በላይ መውደድ ስንጀምር ሕይወታችንም መለወጥ ይጀምራል። ለእግዚአብሔር ነገሮች ያለን ጥልቅ ስሜት ይጠፋል። እግዚአብሔር የሚፈልጋቸውን ነገሮች ከመፈለግና ከማድረግ ይልቅ በራሳችን ፍላጎቶች ላይ የበለጠ ማተኮር እንጀምራለን።

ሐጌ በይሁዳ ባገለገለበት ጊዜ፥ የእስራኤል ሕዝብ ከምርኮ ተመልሰው በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ ይኖሩ ነበር። እግዚአብሔርን ይወዱት ነበርና መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱ ጊዜ በቅድሚያ ያደረጉት ነገር እግዚአብሔርን በማክበር እርሱን ማምላክ የሚችሉበትን ቤተ መቅደስ መሥራት መጀመር ነበር። ዳሩ ግን ይህ ብዙ አልቆየም። የገጠማቸው ተቃውሞና የራሳቸውን ኑሮ ለማሻሻል የነበራቸው ፍላጎት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራታቸውን እንዲያቆሙና ለራሳቸው ጥሩ ጥሩ ቤቶችን እንዲሠሩ አደረጋቸው። የራሳቸውን ነገር በማስቀደም የእግዚአብሔርን ነገር የመጨረሻ አደረጉ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አይሁድ የእርሱን በረከት የሚፈልጉ ከሆነ ከራሳቸው የግል ፍላጎት ይልቅ የእግዚአብሔርን ነገር ማስቀደም እንደነበረባቸው ያስታውሳቸው ዘንድ ነቢዩ ሐጌን ጠራው። ያንን ካደረጉና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ከሰሩ እግዚአብሔር ሊያከብራቸውና ሊባርካቸው ቃል ገብቶ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የራሳቸውን ፍላጎት ከእግዚአብሔር ፍላጎት የሚያስቀድሙባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ለእግዚአብሔር ነገር ቅድሚያ ሰጥተን የራሳችንን ፍላጎት የመጨረሻ ማድረግ ብዙ ጊዜ የሚከብደን ለምንድን ነው?

የትንቢተ ሐጌ ጸሐፊ

አይሁድ በ539 ዓ.ዓ. ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ በይሁዳ ካገለገሉት ሦስት ነቢያት (ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ መካከል አንዱ ሐጌ ነበር። ሐጌ ያገለገለው ዘካርያስ ባገለገለበት ዘመን ነበር።

በሐጌ 1፡1 የእግዚአብሔር ቃል በሐጌ በኩል እንደመጣ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎች ለነበሩት ለዘሩባበልና ለኢያሱ ተጽፏል። ስለዚህ ትንቢተ ሐጌን የጻፈው ሐጌ ነው ማለት ትክክል ነው።

ስለ ሐጌ የምናውቀው ተጨማሪ ነገር በጣም ጥቂት ነው። አንዳንዶች ሐጌ ቀድሞ በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ ያየ፥ አሁን እድሜው ከ70 ዓመት በላይ የሆነ ሽማግሌ ነው ይላሉ። ሐጌ በሽባዛር መሪነት መጀመሪያ ከምርኮ ከተመለሱት መካከል የነበረ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ በዕዝራ 1-2 ከተዘረዘሩት ከምርኮ ከተመለሱት ውስጥ አልተመዘገበም። አንዳንዶች ስለ ተቀደሰ የአምልኮ ሥርዓት ስለሚያስተምር (ሐጌ 2፡11-14) ካህን ነበር ብለው ያስባሉ።

ስለ ሐጌ የምናውቀው ጥቂት ቢሆንም እንኳ ትንቢት የተነበየው መቼ እንደነበር በትክል እናውቃለን። ሐጌ ትንቢቱን መቼ እንደተናገረ በጥንቃቄ መዝግቧል። አራቱም መልእክቶቹ የፋርሱ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በአራት ወራት የተሰጡ ነበሩ። የመጀመሪያው ትንቢት ነሐሴ 22 ቀን 520 ዓ.ዓ. የተነገረ ሲሆን፥ የመጨረሻው ደግሞ ታኅሣሥ 18 ቀን 520 ዓ.ዓ. ነበር። ሐጌ አገልግሎቱን የጀመረው ከዘካርያስ ሁለት ወር ቀድሞ ነው።

ትንቢተ ሐጌ የተጻፈው ወዲያውኑ ትንቢቱ እንደተነገረ መሆን አለበት። ምክንያቱም የቤተ መቅደሱ ሥራ ማለቁን የሚጠቁም ምንም ነገር በመልእክቱ ውስጥ አልተገኘም።

እግዚአብሔር ሐጌን የጠራው ለአንድ ግልጽ ዓላማ ነበር። አገልግሎቱ ረጅም ስላልነበረ ስለ ሕይወቱ ብዙ አናውቅም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሊጠራው ሐጌ በታማኝነትና በድፍረት የእግዚአብሔርን ቃል አስተምሯል። እግዚአብሔር ሕዝቡ እንዲነጹና የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲፈጽሙ ይፈልግ ስለነበር በሐጌ በኩል አነቃቃቸው። ሐጌ ተከናወነለት፤ ከአራት ወራት አገልግሎት በኋላ የነቢይነት ተግባሩ ተጠናቀቀ። ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ ሕዝቡን አነቃቃ። ሕዝቡም የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀምረው ከአምስት ዓመታት በኋላ ተጠናቀቀ።

እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ በሰዎች እንዴት እንደሚጠቀም ማስተዋል የሚያስገርም ነው። እግዚአብሔር አንዳንድ ሰዎችን ይጠራና የረጅም ጊዜ አገልግሎት ይሰጣቸዋል። ኤርምያስ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ሐጌ ላሉ ሌሎች ደግሞ አንድ የተለየ አገልግሎት ዐቅዶላቸው ነበር። እግዚአብሔር ሰዎችን ይጠራል እነርሱም የተጠሩበትን አገልግሉት ፈጽመው ወደ ቀድሞው ሥራቸው ይመለሳሉ። ይህ ነገር መሪዎችን ሁሉ የሚያስታውሰን አገልግሎታችን ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ የሚወስን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው። እንዴት እንደሚከናወንልንና በዘመናችን ሁሉ ጥቂት ፍሬ እያፈራን እንደምናገለግል ወይም ቤተ ክርስቲያንን በከፍተኛ ደረጃ የሚለውጥ አንድ ስብከት ብቻ እንደምናቀርብ የሚወስነው እርሱ ነው። መሪዎችን የሚጠራ፥ የአገልግሎታቸውን ዘመንና የስኬታማነታቸውን መጠን የሚወስን እግዚአብሔር እንደሆነ ልብ በል። የእኛ ኃላፊነት ለእግዚአብሔር ታማኞች መሆንና የቀረውን ነገር ለእርሱ ሉዓላዊ ሥልጣን መተው ነው። እግዚአብሔር ከእኛ ይልቅ ሌላውን ሰው የበለጠ በሚታይ መንገድ ቢጠቀምበት መቅናት ጨርሶ አይገባንም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሌላውን ሰው ሲጠራ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሥልጣናቸው መውረድ የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? ለ) እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ፥ ስለ አገልግሎት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? ) በርካታ መሪዎች ከእነርሱ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማና ታዋቂ በሆኑ ሌሎች መሪዎች የሚቀኑት ለምንድን ነው?

የትንቢተ ሐጌ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኤርምያስ 25፡1-14 አንብብ። ኤርምያስ የእስራኤል የምርኮ ዘመን ምን ያህል ይሆናል ብሎ ነበር? ለ) ዕዝራ 1፡1-8 አንብብ። ምርኮኞቹን የለቀቀው የፋርስ ንጉሥ ስም ማን ነበር? ሐ) የአይሁድን ሕዝብ ከምርኮ ይዞ የተመለሰው የመጀመሪያ መሪ ማን ነበር?

እግዚአብሔር ለበርካታ ዘመናት በይሁዳ የነበሩትን የአይሁድ ሕዝብ ንስሐ ካልገቡና እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን ካልታዘዙ ወደ ምርኮ እንደሚልካቸው በነቢያት መልእክት አስጠንቅቆአቸው ነበር። በመጨረሻም እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ለአይሁድ ቃል ኪዳን በሰጣቸው ጊዜ እንዳስጠነቀቃቸው (ዘዳግም 28)፥ በ586 ዓ.ዓ. ከ50 ዓመታት በላይ በስደት ወደቆዩበት ወደ ባቢሎን አስማረካቸው። (ማስታወሻ፡- በኤርምያስ የተተነበየው 70 ዓመት፥ አይሁድ መጀመሪያ ወደ ምርኮ ከሄዱበት ከ605 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከተመለሱበት እስከ 538 ዓ.ዓ. ድረስ የነበረው ጊዜ ነው። አንዳንዶች ይህን ምርኮ ቤተ መቅደሱ ከተደመሰሰበት ከ586 ዓ.ዓ. ድረስ እንደገና እስከተሠራበት እስከ 516 ዓ.ዓ. ያለውን ጊዜ የሚያካትት ነው ይላሉ)። አይሁድ የተማረኩት እንዲጠፉ ላይሆን፥ ከኃጢአታቸው እንዲነጹና ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ለቃል ኪዳኑ ታዛዦች እንዲሆኑ ለማበረታታት ነበር።

እግዚአብሔር ለሜዶንና ለፋርስ መንግሥት ሥልጣን ከሰጠ በኋላ አይሁድና ሌሎች ሕዝቦች ወደ ገዛ ምድራቸው እንዲመለሱ የሚደነግግ አዋጅ ያወጣ ዘንድ የንጉሥ ቂሮስን ልብ አነሣሣ። በ538 ዓ.ዓ. ቂሮስ ኣይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቀደ። የሚያስገርመው ግን ብዙዎቹ አይሁድ ወደ ጳለስጢና ለመመለስ ፈቃደኞች አለመሆናቸው ነው። ጥሩ ኑሮ በሚኖሩበት በባቢሎንና በሌሎች አሕዛብ አገሮች መኖርን መረጡ። በሽሽባደር መሪነት ቁጥራቸው ኀምሳ ሺህ የሚደርሱ አይሁድ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ሸሽባደር የይሁዳ መስፍንና የአይሁድ ማኅበረሰብ የመጀመሪያ ገዥ ነበር። ሰራያ የዘሩባቤል ሌላው ስሙ ሳይሆን አይቀርም።

አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ብዙ ወራት ከተጓዙ በኋላ ኢየሩሳሌም እንደደረሱ ወዲያውኑ ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመሩ። በታላቅ ደስታ የቤተ መቅደሱን መሠረት ጣሉ፡፡ ዳሩ ግን ወዲያውኑ ተቃውሞ ተነሳና የቤተ መቅደሱ ሥራ ቆመ። ከዚያ በኋላ አይሁድ የራሳቸውን ኑር ወደማሻሻል ዞር አሉ። ንግድና የእርሻ ሥራ ጀመሩ። አንዳንዶች በጣም ሀብታሞች በመሆን ያማሩ ቤቶችን ይሠሩ ጀመር። ወዲያውኑ ለለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው የማይገዳቸው ሆኑና ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የነበራቸው ፍላጎት ጠፋ። ድርቅና ራብ ወደ ይሁዳ መጣ። እነርሱ አሁንም በፋርስ ቁጥጥር ሥር ነበሩ፤ እንደ ኤርምያስና ሕዝቅኤል ባሉ ነቢያት አማካይነት የተሰጡ ተስፋዎች አልተፈጸሙም ነበር። ስለዚህ ሕዝቡ ተስፋ ቆረጡ። የቤተ መቅደሱ መሠረት ተጥሎ ምንም ሳይሠራ 18 ዓመት ያህል አለፈ።

የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በ529 ዓ.ዓ. ሞተ። ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥ ከፍተኛ ትግል ተካሂዶ ነበር፤ በመጨረሻ በ521 ዓ.ዓ. በትረ መንግሥቱን የጨበጠው ቀዳማዊ ዳርዮስ ከ521-486 ዓ.ዓ. በሥልጣን ላይ ቆየ። ዳርዮስ በመላው ግዛቱ ውስጥ በነበሩት ሃይማኖቶች ደስ ተሰኝቶ ነበር። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ማለት በ520 ዓ.ዓ. አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ ከፍጻሜ ያደርሱ ዘንድ ለማበረታታት የሚሆን መልእክት ያደርስ ዘንድ እዚአብሔር ነቢዩ ሐጌን ጠራው። በዚህ ጊዜ የሕዝቡ መሪዎች አዲሱ ገዥ ዘሩባቤል እና ካህኑ ኢያሱ ነበሩ። ከካርያስ ጋር በመሆን የቤተ መቅደሱን ሥራ ይጀምሩ ዘንድ አይሁድን ለማነቃቃት እግዚአብሔር ሐጌን ተጠቀመበት። ሕዝቡ በአራት አጫጭር መልእክቶች የቤተ መቅደሱን ሥራ ለመጀመር ተነቃቁ። የሐጌ ነቢይነት አገልግሎት ተፈጸመና ወደ ቀድሞ ሥራው ተመለሰ፡፡

የቤተ መቅደሱ ሥራ በ520 ዓ.ዓ. በተጀመረ ጊዜ፥ በይሁዳ የሚኖሩ ሳምራውያን አይሁድ ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመሥራት መነሳሳታቸውን ተቃወሙ። ዳርዮስ ቤተ መቅደሱ እንዲሠራ ንጉሥ ቂሮስ መጀመሪያ የፈቀደበትን መዝገብ ማገላበጥ ጀመረ። ያንን የመጀመሪያ ፈቃድ እንዳገኘ አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቀጥሉ ፈቀደላቸው። የቤተ መቅደሱ ሥራም ከ516/515 ዓ.ዓ. ተጠናቀቀ። ዳሩ ግን በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሁለት ነገሮች አልነበሩም። የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ ሞልቶ የነበረው “ሺክና” የእግዚአብሔር ክብር በቤተ መቅደሱ ውስጥ አልነበረም። የቃል ኪዳኑ ታቦትም አልነበረም። በኢትዮጵያ ውስጥ የሰሎሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ የቃል ኪዳኑን ታቦት ሰርቆ እንዳመጣ የሚናገር አፈ-ታሪክ ቢኖርም እንኳ ይህንን የሚደግፍ አጥጋቢ መረጃ አልተገኘም። አንዳንድ ምሁራን ኢየሩሳሌም ከመደምሰሷ ከብዙ ዓመታት በፊት የቃል ኪዳኑ ታቦት ከቤተ መቅደሱ ተወስዶ በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል ይላሉ። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ባቢሎናውያን ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ በ586 ዓ.ዓ. ሲደመስሱ ታቦቱ ጠፍቷል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። በሐጌና በኋላም በሄሮድስ ዘመን በተሠሩት ቤተ መቅደሶች ውስጥ ታቦት አልነበረም። ታቦቱ ይቀመጥበት የነበረው ቅድስተ ቅዱሳን የተባለው ስፍራ ምናልባት በዚያ ከነበረው መንበር በስተቀር አንዳችም ነገር አልነበረበትም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: