የትንቢተ ሐጌ ዓላማ
እግዚአብሔር ሐጌን የጠራው ለአንድ ግልጽ ዓላማ ነበር። ይኸውም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ የተመለሱት አይሁድ ከ70 ዓመታት በፊት የተደመሰሰውን ቤተ መቅደስ በመሥራት ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር እንዲገልጡ ማበረታታት ነበር። ትንቢተ ሐጌ አይሁድ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ያላቸውን ዕድልና ያለባቸውን ኃላፊነት የሚያሳስቡ አራት መልእክቶችን ይዟል። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ሕዝብ በመሆናቸው የራሳቸውን አኗኗር ከማሻሻላቸው በፊት፥ እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚጠቀሙበትን ቤተ መቅደስ መሥራት ግዴታቸው ነበር።
እንዲሁም ሐጌ ለእስራኤል ሕዝብ ሙሉ በረከት ይዞ ስለሚመጣው መሢሕ ለአይሁድ አስታወሳቸው። አሁን ያሉበትን ሁኔታ ሳይሆን፥ የወደፊቱን የእግዚአብሔር ሥራ በማየት ሊበረታቱ ይገባ ነበር።
ትንቢተ ሐጌ መሪዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ማድረግ ስላለባቸው ነገሮች ስለሚያስተምር ዛሬም አስፈላጊነቱ የጐላ ነው። የሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት ሲበላሽና ሲጠፋ መልሶ ማስተካከል እንዴት እንደሚቻል ያስተምራል። በዚያን ጊዜ እንደነበሩ አይሁድ፥ እኛም በራሳችን የእግዚአብሔርን ነገሮች ከራሳችን ፍላጎትና ጥቅም ለማስቀደም መቻል አለብን። ምን ያህል ገንዘብ እንደምናገኝ፣ ምን ያህል ትምህርት እንዳለን፥ በምን ዓይነት ቤት ውስጥ እንደምንኖር ወዘተ. ከማሰብ ይልቅ፥ የበለጠ ሊገደን የሚያስፈልገው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነትና ለእርሱ ስላለን መታዘዝ መሆን አለበት።
የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ግድግዳዎች ሊደመሰሱና እንደገና ሊሠሩ የሚያስፈልግበትን ሁኔታ የሚገልጽ ምሳሌ ስጥ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ነገሮች ይልቅ ለግል ምቾቶቻቸው ማሰብ የሚቀልላቸው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ነገር ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህንን ለመዋጋት ምን ማድረግ ይችላሉ?
የትንቢተ ሐጌ አስተዋጽኦ
1. 1ኛ መልእክት፡- ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ መጠራታቸውና የሰጡት ምላሽ (ሐጌ 1)፥
2. 2ኛ መልእክት፡- ቤተ መቅደሱ በእግዚአብሔር ክብር እንደሚሞላ የተነገረ ትንቢት (ሐጌ 2፡1-9)፥
3. 3ኛ መልእክት፡- ሕዝቡ ከነጹና ቤተ መቅደሱን መሥራት ከቀጠሉ እግዚአብሔር ይባርካቸዋል (ሐጌ 2፡10-19)፡
4. 4ኛ መልእክት፡- እግዚአብሔር ዘሩባቤልን እንደ ራሱ ቀለበት ማተሚያ አድርጎ መረጠው (ሐጌ 2፡20-23)።
የትንቢተ ሐጌ ዐበይት ትምህርቶች
1. መታዘዝ በረከትን አለመታዘዝ ደግሞ ቅጣትን ያመጣል፡- ዛሬ ብዙዎቻችን እንደምናስበው ሁሉ አይሁዶችም፥ በሕይወታቸው ዘመን በሚፈልጉአቸው ነገሮች ላይ እስካተኲሩ ድረስ እንደሚያገኙአቸው ያምኑ ነበር። በሕይወት ውስጥ ከሁሉ የላቀውና ተፈላጊው ነገር ሊያገኙት የሚችሉት ሥጋዊ በረከት እንደሆነ ያምኑ ነበር። ስለዚህ ጠንክረው በመሥራት ቁሳዊ በረከቶችን አገኙ። ጥሩ ቤቶች፥ ጥሩ ሥራ፥ ወዘተ. ነበራቸው። ግን አንድ ነገር ደኅና አልነበረም፤ የእህል ምርታቸው የተጠበቀውን ያህል የሚያረካ አልነበረም፤ ድርቅ ከምድሪቱ በፍጹም የሚለቅ አይመስልም። ትንቢተ ሐጌ የሚያስተምረው፥ በሕይወት ውስጥ እውነተኛ በረከትን ለማግኘት፥ ማለትም ሥጋዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ በረከት ጨምሮ እንዲኖር፥ እግዚአብሔር እንድንሠራው የሚፈልገውን ነገር በተቀዳሚ የመሥራት ፍላጎት መኖር እንዳለበት ነው። እግዚአብሔርን መታዘዝ ያስፈልጋል። ከግል ፍላጎት በላይ ለእግዚአብሔር ጉዳይ ቅድሚያ የመስጠት ፍላጎት መኖር አለበት። ሐጌ የድርቁ ምክንያት ሕዝቡ እግዚአብሔርንና ጽድቁን አለመፈለጋቸው እንደነበር ይናገራል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፍጹም በረከት መቀበል ቢፈልጉ ኖሮ እግዚአብሔርን ማስቀደም ነበረባቸው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራትና ለእግዚአብሔር በንጽሕናና በመታዘዝ መኖር አስፈላጊያቸው ነበር። በእርግጥ እግዚአብሔር በቁሳዊ ነገሮች የሚባርካቸው በዚህ ጊዜ ነበር። እግዚአብሔር በሥጋዊ በረከቶች ሊባርካቸው ይችላል። ከዚህ የሚበልጠው ግን እግዚአብሔር በመካከላቸው በመኖር፥ ከእነርሱ ጋር ኅብረት በማድረግ፥ በመጠበቅ የልብ ሰላምና የሕይወት ደስታን በመስጠት ይባርካቸው ነበር።
ለክርስቲያኖች፥ እግዚአብሔርን ከታዘዝን ሥጋዊ በረከቶችን እንደምናገኝ የተገባልን ቃል ኪዳን የለም፡፡ ይህ ምድራዊ ሕይወት በሥቃይ፥ በስደትና በሞት የታጀበ እንደሆነ ተነግሮናል። ክርስቲያኖች የተገባልን ተስፋ ወይም ቃል ኪዳን ለእግዚአብሔርና ለክብሩ ከኖርን፥ እግዚአብሔርን ከታዘዝንና የእርሱን ነገር ካስቀደምን በሕይወታችን ከሁሉ የላቀውን በረከት እንደምናገኝ ነው። እግዚአብሔር በውስጣችን በመኖር ከእኛ ጋር ኅብረት ያደርጋል። ውጫዊ ሁኔታዎች ምንም ዓይነት ይሁኑ ሰላምና ደስታ ይኖረናል። እግዚአብሔር መጠጊያችን በመሆን በሕይወታችን ዘመን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ይሰጠናል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች እምነት ካላቸው፥ ሁልጊዜ ሥጋዊ በረከቶችን እንደሚያገኙ የሚመስላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ እውነት ነውን? ከሆነ ለምን? ካልሆነስ ለምን? ሐ) ከቁሳዊ በረከቶች ይልቅ መንፈሳዊ በረከቶች የበለጠ አስፈላጊ የሚሆኑት በምን መንገድ ነው? መ) ከላይ የተመለከትነው እውነት በሕይወትህ ሲረጋገጥ ያየኸው እንዴት ነው?
2. የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተ መቅደስ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ይናገራል። ሙሴ የመጨረሻ ቃሎቹን ለእስራኤላውያን በሚናገርበት ጊዜ አንድ ቀን እግዚአብሔር ስሙን የሚያጸናበት የአምልኮ ስፍራ እንደሚመሠርት ጠቁሟል (ዘዳግም 14፡23-25)። በኋላም እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንደገቡ በሴሎ የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ (ኢያሱ 18፡1)። ይህም ስፍራ በመጨረሻ ተደመሰሰ። ቀጥሎም ዳዊትና ሰሎሞን ቋሚ የሆነ እግዚአብሔር የሚመለክበት ቦታ ሠሩ። ታላቁ ቤተ መቅደስ ከሰባት ዓመታት በኋላ ተሠርቶ ሲያልቅ፥ በእግዚአብሔር ክብር ተሞላ (1ኛ ነገሥት 8)።
እግዚአብሔር ለአይሁዶች ያለው አሳብ የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ሥራ መጠናቀቅ በራሱ እንደ ተልዕኳቸው ማብቂያ እንዲታይ አልነበረም፤ ነገር ግን ሕንጻው እግዚአብሔር በመካከላቸው መኖሩን እንዲያውቁ የሚያሳይ ምልክት እንዲሆን ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው፥ ለቃል ኪዳኑ በመታዘዝ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩትና ሕያው የሆነውን እውነተኛውን አምላክ ከልባቸው እንዲያመልኩት ለማስታወስ ነበር።
ይሁን እንጂ በኤርምያስ ጊዜ አይሁድ ውጫዊውን ሕንጻ እንደ አንድ የአስማት ሐውልት ይመለከቱት ነበር። የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ከጠላቶቻቸው የሚጠብቃቸው ዋስትና አድርገው ይቆጥሩት ነበር። ለእግዚአብሔር ከሚሰጡት ትኩረት ይልቅ፥ ከውጭ ለሚታየው ሕንጻ የሚሰጡት ትኩረት የላቀ ነበር። በኋላም በሕዝቅኤል ራእይ የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ትቶ ሲሄድ ታየ፤ ይህም እግዚአብሔር በሕዝቡ ጣዖት አምላኪነትና አለመታዘዝ ማዘኑን የሚያሳይ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ከዚያ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ቢቆይም እንኳ እግዚአብሔር ግን በውስጡ አልነበረም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ለማጥፋት ወሰነ (ኤርምያስ 7፡1-15)። ሕዝቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምልኮ መፈጸማቸውን የቀጠሉ ቢሆንም፥ ይህን የሚያደርጉት በባዶ ሕንጻ ውስጥ ነበር። በመጨረሻ በ587 ዓ.ዓ. ናቡከደነፆር ባዶውን የቤተ መቅደስ ሕንጻ ደመሰሰው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ውጫዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የእግዚአብሔር በረከቶችን የማግኘት ዋስትና አድርገው የሚቆጥሩት እንዴት ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ለምንድን ነው? የእነዚህ ክርስቲያኖች ዝንባሌ በኤርምያስ ጊዜ ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር ተመሳሳይ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ሰባ ዓመት ያህል ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ይሠሩ ዘንድ ሕዝቡን አነቃቃቸው። ለእርሱ በመታዘዝ ከተመላለሱ ይሰጣቸው ዘንድ ቃል የገባላቸውን በረከት እንደ ገና እንደሚያፈስስላቸው ተስፋ ሰጠ። ቤተ መቅደሱ አሁንም ቢሆን ከሁሉ የላቀና የተሻለ ነገር አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንዳለና በመካከላቸው እንደሚኖር ያመለክት ነበር። ስለዚህ በእርሱ ፊት እንደ ቃል ኪዳን ሕዝብ መመላለስ ነበረባቸው። ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር በጣም አስፈላጊ የሆነውና አይሁድ እንዲሠሩት የታዘዙት ለምን ነበር? እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱ አይሁድ ሁሉ የሚያመልኩበት ስፍራ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። አይሁድ ቤተ መቅደሱን በተመለከቱና በዚያ አምልኮን ባቀረቡ ቁጥር እግዚአብሔር በመካከላቸው እንዳለ መገንዘብ አስፈላጊያቸው ነበር። ይህም የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንደሆኑና እንደ ቃል ኪዳን ሕዝቡም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መኖር እንዳለባቸው ያስታውሳቸው ነበር።
ነገር ግን የሚያሳዝነው አይሁድ ልክ እንደቀደሙት አባቶቻቸው ፈጥነው የቤተ መቅደሱን መኖር ለእግዚአብሔር በረከት መኖር ማረጋገጥ አድርገው ቆጠሩት። ለእውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ ወይም እግዚአብሔርን መታዘዝ ጉዳይ ብዙ ትኩረት አይሰጡም ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ አይሁድ ከእግዚአብሔር ይልቅ ቤተ መቅደሱን ያከብሩ ነበር። ኢየሱስም እንደ ኤርምያስ ስለ ቤተ መቅደሱ መደምሰስ ተነበየ (ሉቃስ 21፡5-6)። በዓይን የሚታየው ግዑዝ ሕንጻ አስፈላጊ እንዳልሆነ፥ ዳሩ ግን እግዚአብሔር በሰው ልብ ቅንነትና በልብ ውስጥ በሚፈጸም ንጹሕ አምልኮ እንደሚደሰት ለሳምራዊትዋ ሴት ተናግሯል። “በእውነትና በመንፈስ” እስከሆነ ድረስ ሰው የትም ቦታ እግዚአብሔርን ሊያመልከው ይችላል (ዮሐንስ 4፡21-24)።
በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በዓይን የምናየው ውጫዊ ሕንጻ እንዳልሆነ አስተምሯል። ይልቁንም ኢየሱስ የሚኖርበት የእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ቤተ መቅደስ ነው (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። በተጨማሪም እግዚአብሔር በመካከላቸው ስለሚኖር ማናቸውም ክርስቲያኖች የተሰበሰቡበት ቦታ ቤተ መቅደስ ነበር (1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16)። በዮሐንስ ራእይ ቤተ መቅደሱ ከሰማይ ሲወርድ እንመለከታለን። ነገር ግን ይህ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔርን ለዘላለም በሕዝቡ መካከል መኖር ተምሳሌት እንጂ ሕንጻ አይደለም (ራእይ 21፡1-4፥ 22)።
የአዲስ ኪዳን ትኩረት በጭራሽ በዓይን በሚታዩ ሕንጻዎች ላይ አይደለም። እንዲያውም የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ስለ መሥራታቸው የምናነብበው ነገር በጭራሽ የለም። ብዙ ጊዜ ለአምልኮ የሚገናኙት በአማኞች መኖሪያ ቤት ነበር። ሰዎች ለአምልኮ የሚያገለግሉ ሕንጻዎች መሥራት የጀመሩት በኋላ ነው። የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ብዙ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ብቻ ነው። የተለየ አትኩሮት ወይም ቅድስና የለውም። ክርስቲያኖች የአምልኮ ንጽሕናን ከመሻትና እግዚኣብሔርን ለመታዘዝ ከመትጋት በስተቀር በአካላዊ ሕንጻዎች ላይ ብዙም ትኩረት ከማድረግ መጠንቀቅ ኣለባቸው። እግዚአብሔር የሚፈልገው ያሸበረቀ ታላቅ ሕንጻን ሳይሆን እውነተኛ አምልኮን ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ለአምልኮ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የሚኖረው የተሳሳተ አመለካከት ለክርስቲያን ማሰናከያ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ያለው አምልኮ «በእውነትና በመንፈስ» እንዲሆን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?
የውይይት ጥያቄ፥ ሐጌ 1-2 አንብብ። የሐጌን አራት መልእክቶች አሳጥረህና አጠቃልለህ አቅርብ።
1ኛ መልእክት፡- የመጀመሪያው መልእክት የተሰጠው በነሐሴ ወር 520 ዓ.ዓ. ነበር። የዚህ መልእክት ዓላማ ቤተ መቅደሱ ፈርሶ ሳለ ሕዝቡ በራሳቸው ጉዳይ እንዴት እንደተጠመዱ ለማሳየት ነበር። በሕዝቡ ላይ የኢኮኖሚ ድቀት የደረሰበት ምክንያት እግዚአብሔርን ስላላከበሩና ለግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ብቻ በመገዛት መኖራቸው እንደነበር ሐጌ ይገልጣል። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ነገር ቢያስቀድሙና ቤተ መቅደሱን ቢሠሩ የእርሱን በረከት እንደሚያገኙ ያረጋግጥላቸዋል። የሐጌ መልእክት ሕዝቡ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲጀምሩ ያበረታታል። ሐጌ ይህን የመጀመሪያ መልእክት ካቀረበ ከሃያ አራት ቀናት በኋላ ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመሩ (ሐጌ 1፡1-11)።
የውይይት ጥያቄ፥ ዕዝራ 3፡10-13 አንብብ። የቤተ መቅደሱ ሥራ ቀደም ሲል ሲጀመር ሕዝቡ የሰጠው የተለያየ ምላሽ ምን ነበር?
2ኛ መልእክት፡- ሁለተኛው መልእክት የተሰጠው የቤተ መቅደሱ ሥራ ከተጀመረ ከአንድ ወር በኋላ በጥቅምት ወር 520 ዓ.ዓ. ነበር ሐጌ 2፡1-9)። በዚህ ወቅት ከነበሩት አይሁድ መካከል ሰሎሞን የሠራውን ቤተ መቅደስ ባቢሎናውያን ሳያጠፉት በፊት ያዩ ሰዎች ነበሩ። ከዚያኛው ጋር ሲነጻጸር አሁን የተሠራው ቤተ መቅደስ ትንሽ፥ ውበቱም መጠነኛ ነበር። በዚህም ጊዜ የቤተ መቅደሱ ሥራ ከሳምራውያን በኩል ተቃውሞ ገጠመው። ሕዝቡ ተስፋ መቁረጥ ጀመሩ። ሐጌ ሕዝቡ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቀጥሉ አበረታታቸው። እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበር። አንድ ቀን እነርሱ የሚሠሩት ቤተ መቅደስ ክብር ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ ክብር እንደሚበልጥ እግዚአብሔር ቃል ገባላቸው። እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ስለሚፈርድ አንድ ቀን በምድሪቱ ላይ ሰላም ይሆናል፡፡ ሐጌ «የሁሉም ሕዝቦች ፍላጎት» እንደሚፈጸም ይናገራል። ይህ ምናልባት ስለ ክርስቶስ መምጣት የሚናገር ትንቢት ሳይሆን አይቀርም።
3ኛ መልእክት፡- የተሰጠው በታኅሣሥ ወር 520 ዓ.ዓ. ነበር (ሐጌ 2፡10-19)። የሦስተኛው መልእክት ዓላማ እግዚአብሔር የእርሱን ነገር ባለማስቀደማቸው ነሥቶአቸው የነበረውን በረከት እንደገና እንደሚመልስላቸው በመናገር ሕዝቡን ማበረታታት ነበር። በተጨማሪ እግዚአብሔር ሕዝቡን፥ በተለይም መንፈሳዊ መሪዎችን ሕይወታቸው በዓለም እንዳይበላሽ እንዲጠነቀቁ ይልቁንም በእግዚአብሔር ፊት ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ ያስጠነቅቃቸዋል። ከካህናት ሕይወት ሁለት ምሳሌዎችን በመውሰድ፥ የአምልኮ ሥርዓት ቅድስና ወደ ሕዝቡ እንደማይተላለፍ ሁሉ የጥቂት ሰዎች መንፈሳዊ ቅድስናም ወደ ሌሎች እንደማይተላለፍ አስተምሯል። ቅድስና አንድ ሰው በግሉ በራሱ ምርጫ የሚፈጽመው ነው። ይሁን እንጂ የሥርዓተ አምልኮ ንጽሕና ጉድለት እንደሚተላለፍ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለ ኃጢአትም በእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ምክንያቱም ኃጢአት እንደ በሽታ ሌሎችን ማበላሸት ይችላልና።
የውይይት ጥያቄ፥ ይህን የቅድስናና የክፋት እውነታ በሕይወትህ ያየኸው እንዴት ነው?
4ኛ መልእክት፡- የሐጌ አራተኛ መልእክት የተሰጠው ሦስተኛው በተሰጠበት በታኅሣሥ ወር 520 ዓ.ዓ. ነበር (ሐጌ 2፡20-23)። የዚህ መልእክት ዓላማ እግዚአብሔር ዘሩባቤልን “የቀለበት ማኅተም” አድርጎ እንደመረጠው ለሕዝቡ መግለጽ ነበር። “የቀለበት ማኅተም” የንጉሥ ሥልጣን ምልክት ነበር። እግዚአብሔር ለብዙ ነገሮች ትኩረት ለመስጠት በዚህ ትንቢት ተጠቅሞአል።
ሀ) ይህ ትንቢት እግዚአብሔር ዘሩባቤልን እንደመረጠውና የመሪነትን መብት እንደሰጠው አጠናክሮ ይገልጻል። ለ) የፖለቲካ መሪ የሆነው ዘሩባቤል ምሳሌ የሆነለት መሢሕ ወደፊት እንደሚመጣ ለሕዝቡ ለማስታወስ ነበር። ሐ) አንዳንድ ምሁራን እግዚአብሔር በንጉሥ ኢዮአቄም የዘር ግንድ ላይ ያኖረውን መርገም ማንሣቱን ለማመልከት ነው ይላሉ (ኤርምያስ 22፡24-30)። መ) የትንቢቱ ዓላማ ሊሆን የሚችል ከሁሉም የተሻለው ምክንያት እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው የንጉሣዊ ዘር ግንድ እንዳልጠፋና እርሱ እንደሚፈጽመው ለማመልከት ነው። ስለ ዘሩባቤል የተተነበየው ትንቢት የዳዊት ልጅ የሆነው «የአይሁድ ንጉሥ» ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ተፈጸመ (ማቴዎስ 1፡11-12)።
ከኢየሩሳሌም መደምሰስ በኋላ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የነገሠ «ከዳዊት ዘር የወጣ ንጉሥ» የለም። ይሁዳና ኢየሩሳሌም ምን ጊዜም ቢሆን በአሕዛብ መንግሥታት ሥልጣን ሥር ነበሩ። ኢየሱስ «የአይሁድ ንጉሥ» ሆኖ በመጣ ጊዜ እንደ ዳዊት በሥጋ ለመግዛት ተዋጊና አሸናፊ ሆኖ አልመጣም። ይልቁንም ሕይወቱን ስለ ሕዝቡ የሚሰጥ ንጉሥ ሆኖ መጣ። አይሁድ ኢየሱስ ንጉሣቸው መሆኑን ሳይቀበሉ ቀሩና ገደሉት። ዳሩ ግን ይህ እግዚአብሔር በሐጌ በኩል ለዘሩባቤል የሰጣቸውን ተስፋዎች አላጠፋም። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነሥቷል። አንድ ቀን ከሰማይ ተመልሶ ይመጣልና «ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ» በመሆኑ ከዳዊት ዘር የወጣ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል (ራእይ 5፡5)። ኢየሱስ የዘሩባቤል ዘር ስለሆነ ትንቢተ ሐጌ የሚደመደመው ስለሚመጣው መሢሕ በመናገር ነው። አይሁድ የሚመጣውን ንጉሣቸውን በማሰብና እርሱን በመጠባበቅ መኖር ነበረባቸው። ይህ አሳብ በቅኝ አገዛዝ ሥር በነበሩባቸው ዓመታት ሁሉ መጽናኛ ሆኖአቸው ነበር፡፡
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ሐጌ የምንማራቸው መንፈሳዊ እውነቶች የትኞቹ ናቸው? ) እነዚህን መንፈሳዊ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ለሚገኙ ለሌሎች ለማስተማር ዐቅድ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡