አራት መቶ የጸጥታ ዓመታት

የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚደመደመው በመጽሐፈ ነህምያ ሲሆን፥ ትንቢታዊ መልእክቶች የሚጠቃለሉት ደግሞ በትንቢተ ሚልክያስ ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤላውያን የሚሰጠው መልእክት ተፈጸመ። እግዚአብሔር ኤልያስንና መሢሑን እንዲጠባበቁ ለእስራኤላውያን መልእክት ከሰጣቸው በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያክሉት ሌላ ተጨማሪ መልእክት አልሰጣቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ከሚልክያስ ዘመን ጀምሮ (400 ዓ.ዓ.) ኢየሱስ እስከ መጣበት (5 ዓ.ዓ.) ድረስ የነበረውን ጊዜ «400 የጸጥታ ዓመታት» ብለው የሚጠሩት ስለዚህ ነበር። አይሁድ የአዋልድ መጻሕፍት (አፖክሪፋ) በመባል የሚታወቁ ሌሎች ተጨማሪ መጻሕፍት የጻፉ ቢሆንም፥ እነዚህ መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን 39 መጻሕፍት ጋር እኩል እንዳይደሉ ተገንዝበው ነበር። 

እነዚህ አራት መቶ ዓመታት ለአይሁድ እጅግ ወሳኝ ስለነበሩ በእነዚህ ዓመታት ምን እንደተደረገ ማወቅ አስፈላጊ ነው። እነዚህን አራት መቶ ዓመታት የበለጠ በተረዳን ቁጥር፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተፈጸሙትን አንዳንድ ነገሮች በይበልጥ እንረዳለን። ከጊዜና ከቦታ እጥረት የተነሣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጥቂት አሳቦች ብቻ ተጠቃልለው ቀርበዋል።

1. የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች (539-331 ዓ.ዓ.)፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተደመደመበት ጊዜ፥ የፋርስ መንግሥት ነገሥታት አይሁድን ራቅ ብሎ እንደሚገኝ የግዛታቸው ክፍለ ሀገር ይዙዋቸው ነበር። በፖለቲካ ረገድ ከታላቁ የፋርስ የሥልጣን ማዕከል እጅግ ርቀው ይገኙ ስለነበር የፋርስ መንግሥት አይሁዳውያንን የራሳቸውን ጉዳይ እንዲያከናውኑ ትተዋቸው ነበር። ኢየሩሳሌም ከፍተኛ የንግድ ዕከልና የጳለስጢን ዋናዋ የፖለቲካ ሥልጣን ቁንጮ ነበረች። በፋርስ የንጉሠ ነገሥት ግዛት የሥልጣን ዘመን ውስጥ፥ የኋላ ኋላ በአዲስ ኪዳን ዘመን ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ብዙ ነገሮች ተፈጽመዋል። 

ሀ. አይሁድ በዓለም ዙሪያ ሁሉ መሠራጨታቸውን ቀጠሉ። አብዛኛዎቹ አይሁድ የሚኖሩት ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ውጭ ነበር። እንደ ሀገራችን የጉራጌ ብሔር አባሉች የተዋጣላቸው ነጋዴዎች በመሆን፥ በጥንቱ ዓለም በነበሩ በአብዛኛዎቹ ከተሞች ይገኙ ነበር። ይህ በየስፍራው ተበትኖ የመኖር ነገር በሚቀጥለው የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛትም እየጨመረ ሄዶ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን በግልጽ እንደሚታየው ጳውሎስ ወንጌልን ይዞ በተዘዋወረባቸው ስፍራዎች ሁሉ፥ በቅድሚያ ይሰብክ የነበረው የተበተኑት አይሁድ ወደሚሰበሰቡበት ምኩራብ በመሄድ ነበር።

ለ. የአይሁድ ዋና ቋንቋ ተለወጠ። አብዛኛዎቹ አይሁድ በእስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሳይቀሩ አራማይክ የተባለውን የንግድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። የብሉይ ኪዳን ቋንቋ የሆነውን ዕብራይስጥ ይጠቀሙ የነበሩት በአምልኮ ፕሮግራም ብቻ ነበር። ለምሳሌ የእግዚአብሔር ቃል በሚነበብበት ጊዜ ዕዝራ የተረጐመበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር (ነህምያ 8፡7-8)። ኢየሱስ አገልግሎቱን የሰጠው በአራማይክ ቋንቋ ነው። 

ሐ. የምኩራቦች አጀማመር፡- የአይሁድ ማኅበረሰብ ባሉበት ስፍራ ሁሉ፥ የማኅብረሰብ ማዕከልና ምኩራብ የተባለ የአምልኮ ስፍራ ይሠሩ ጀመር። በእነዚህ ምኩራቦች ውስጥ መሥዋዕት ባያቀርቡም እንኳ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ይሰበሰቡ ነበር። እነዚህ ምኩራቦች በኋላ የጣዖት አምልኮ የሰለቻቸው አሕዛብ ስለ እውነተኛው አምላክ ለመስማት የሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ሆኑ። ጳውሎስና ሌሎች አገልጋዮች ወንጌልን ለመስበክ ወደ እነዚህ ስፍራዎች እንደሄዱ እነዚህ አሕዛብ ፈጥነው በክርስቶስ በማመን ተለወጡ፡፡ 

መ. የካህናት ሥልጣን እየጨመረ መምጣት፡- ገና ከመጀመሪያው በኢየሩሳሌም የነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ አንድ የፖለቲካ (ለምሳሌ ዘሩባቤል)፥ ሌላ የሃይኖት (ለምሳሌ ታላቁ ካህን ኢያሱ) መሪ የነበረው ቢሆንም፥ ካህናቱ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪነቱን ጠቅልለው ለመያዝ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። ይህም ካህናቱ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ረገድ ከመምራት ይልቅ በፖለቲ ጉዳይ ላይ በማተኮር በሥልጣን እንዲባልጉ አደረጋቸው።

ሠ. “ጸሐፍት” የተባሉ አይሁድ ያሉብት መደብ ፈጠር፡- ጸሐፍት በሕግ እውቀትና ትርጓሜ ሥራ የተካኑ ነበሩ፡፡ እነርሱም የእስራኤል ቁልፍ የሕግ መምህራን ሆኑ፡፡ ሕዝቡ የብሉይ ኪዳንን ተዛዛት እንዳይጥሱ ለማረጋገጥ በመፈለጋቸው፣ ሕዝቡ ለተጻፉት ሕግጋት አንታዘዝም እንዳይሉ ለመጠበቅ ሲሉ እንደ “አጥር” የሚሆኑ ሌሎች ሕግጋትን ጨመሩ፡፡ በኋላ ለእነዚህ ሕግጋት ወግ ከመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕግ የበለጠ ስፍራ ይሰጣቸው ጀመር፡፡ ይህም ወዲያውኑ ይሑዲነትን ልባዊ ሳይሆን ሕጋዊነት ወደሚንጸባረቅበት “አድረግ፣ አታድርግ” የአይሁድ የሃይማኖት ሥርአት ለወጠው፡፡ ጸሕፍትም በተራቸው የፖለቲካ መሪዎች እስኪሆኑ ድረስ በስልጣን መጥቀው ሄዱ፡፡ በመጨረሻም ጸሐፍት፣ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች “ሸንጎ” የተባል ጉባኤ በማቋቋም የአይሁድን የአስተዳደር አካል መሠረቱ፡፡ 

ረ. የሳምራውያንና የአይሁድ ጥላቻ አጀማመር፡- እስራኤላውያን በአሦር እጅ በወደቁና በተማረኩ ጊዜ ከሌላ ስፍራ አሕዛብን ወደ እስራኤል በማምጣት ከቀሩት አይሁድ ጋር ለመቀላቀል እንደሞከሩ ታስታውሳለህ፡፡ አይሁድና አሕዛብ በመጋባታቸው ምክንያት የተወለዱት ልጆች ሳምራውያን ተባሉ፡፡ ከአይሁድ ወደባቢሎን ተወስደው የነበሩት አይሁድ ወደ እስራኤል በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል ሃይማኖት ከይሁዲነትና ከአሕዛብ የጣዖት አምልኮ ጋር ተደባልቆ ነበር። እነዚህ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር ተባብረው ቤተ መቅደሱን ለመሥራት በመጡ ጊዜ አይሁድ ተቃወሙ። አምልኮአቸው ንጹሕ ሆኖ እንዲቆይ ይፈልጉ ነበር። ይህም ሳምራውያንን አስቆጣቸውና የአይሁድ ጠላቶች እንዲሆኑ አደረጋቸው። ቆየት ብለው ሳምራውያን ከአይሁድ ተለዩ። ገረዚም በተባለ ተራራ ላይ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ ሠሩ። ከአይሁድ የአምልኮ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል የራሳቸው የአምልኮ መዋቅር አበጁ። በተቀዳሚ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት የያዙ የራሳቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ነበሯቸው። ይህም አይሁድን እጅግ አስቆጥቷቸው ስለነበር በነጻነታቸው ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሳምራውያንን ገደሉ። በአይሁድና በሳምራውያን መካከል የነበረው ይህ ጠላትነት፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ በሰማርያ ሲያልፍና በተለይ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ሲነጋገር ደቀ መዛሙርቱ አይተው በመደነቃቸው ይስተዋላል (ዮሐንስ 4)። 

ሰ. ምሁራን የአይሁድ መሠረታዊ ትምህርቶች በአንዳንድ መንገዶች የፋርስ ሃይማኖት ተጽዕኖ አድሮባቸዋል ብለው ያስባሉ። በፋርስ ዘመን የፋርስ ሰዎች ያደርጉት እንደነበረው አይሁዶች በመለኮታዊ ፍርድ፥ በሙታን ትንሣኤ፥ በአጋንንትና በመላእክት ሕልውና፥ ወዘተ. ላይ ያተኩሩ ነበር። 

2. የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት (331-142 ዓ.ዓ.)

የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት በታላቁ እስክንድር መሪነት፥ በዓለም ላይ እስከዚያ ዘመን ድረስ ተነሥተው ከነበሩ መንግሥታት ሁሉ በላቀ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። የፋርስን የንጉሠ ነገሥት ግዛት በሙሉ ከመጠቅለል አልፎ፥ ወደ ታች ወደ ግብፅና ሕንድ ድረስ ተስፋፋ። በጥንት ታሪክ ለመጀመሪያው ጊዜ አንድ የአውሮፓ አገር ግዛቱን እስከ ትንሹ እስያ ድረስ በማስፋፋት፥ በአንዳንድ ረገድ ከነበረው ተመሳሳይነት በስተቀር በወረራቸው ሕዝቦች ላይ በእጅጉ የተለየ ባህል አመጣ። ሆኖም ታላቁ እስክንድር የፋርስን መንግሥት መዋቅርንም ሆነ የክልል መንግሥታት አደረጃጀትን ለመደምሰስ አልሞከረም። ታላቁ እስክንድር በዘመኑ የታወቁ የዓለም ክፍሎችን በሙሉ ወርሮ ከያዘ በኋላ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ገና በወጣትነት ዘመኑ በ323 ዓ.ዓ. ሞተ።

በ301 ዓ.ዓ. የታላቁ እስክንድር ጦር ሜጀር ጄኔራሎች እያንዳንዳቸው አንዳንድ ከፍል በመያዛቸው መንግሥቱ ለአራት ተከፈለ። በይሁዳ ላይ ተጽዕኖ አሳድረው የነበሩት ሁለቱ መንግሥታት ግብፅንና ሊቢያን ይዞ የነበረው የፕቶሎሜካዊ ንጉሠ ነገሥት ግዛትና ሶርያና ፋርስን ተቆጣጥሮ የነበረው የሲሉሲድ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ነበሩ። በእነዚህ ሁለት የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች መካከል ወዳጅነት አልነበረም። እነዚህ ሁለት መንግሥታት ጳለስጢናን ለመቆጣጠር በመምከር ያለማቋረጥ ይዋጉ ነበር። ይህ ማለት አይሁድ ያለማቋረጥ እርስ በርሳቸው በሚጋጩና አብረዋቸው እንዲምቱ በሚጠይቋቸው ባዕዳን ሠራዊት ይጠቁ ነበር ማለት ነው።

ከ320-200 ዓ.ዓ. ፕቶሎሚዎች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። በይሁዳ ይኖሩ የነበሩትን አይሁድ እንደፈለጋቸው እንዲኖሩ ለቀቋቸው። በዚህ ጊዜ የአይሁድ ገዢዎች ካህናት ነበሩ።

ከ200-142 ዓ.ዓ. ሲሉሲዶች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። ከፍተኛው ትኩረታቸው አይሁድ የግሪክን ባህል እንዲለምዱ ማድረግ ነበር። ቀረጥ እንዲከፍሉ አይሁድን አስገደዷቸው። በጭካኔ ከሁሉ የከፋው መሪ፥ ከ175-164 ዓ.ዓ. የገዛው አንቲዩከስ 4ኛ ኤፒፋነስ የተባለው ነው። አይሁድ የጣዖት አምልኮ ያካትት የነበረውን የግሪኮችን ባህል እንዲለማመዱ ለማስገደድ ሞከረ። በኃላፊነት ላይ የነበረውን የአይሁድ ሊቀ ካህን አባርሮ የግሪክን ባህል ለመቀበል ይፈልግ የነበረውን የራሱን አይሁዳዊ ሊቀ ካህን በሕዝቡ ላይ ሾመ። ከግብፅ ጋር ይዋጋ ለነበረው ጦሩ ለመክፈል በቤተ መቅደስ የነበረውን ገንዘብ ሁሉ ወሰደ። ሮማውያን ግብጽን ወርሮ እንዳይዝ በከለከሉት ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። በቤተ መቅደስ ውስጥ ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት ሁሉ እንዲቆም በማድረግና በመሠዊያው ላይ አሳማ በመሠዋት መሠዊያውን አረከሰው። ዚዩስ ለተባለው የግሪክ ጣዖት መሥዋዕት ማቅረቢያ የሚሆን መሠዊያ በማሠራት ለዚዩስ መሥዋዕትን እንዲያቀርቡ አዘዘ። (በዳንኤል 11፡31-36 ስለዚህ ዘመን የተነገረውን ትንቢት ተመልከት)።

ከ167-164 ዓ.ዓ. ለሦስት ዓመታት በቤተ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ማንኛውም መሥዋዕት ቆመ፡፡ 

ይህ የአንቲዩከስ ተግባር አይሁድን ለዓመፅ አነሣማቸው፡፡ መቃብያን ተብለው ይጠሩ በነበሩ በአንድ ካህንና በሁለት ልጆቹ መሪነት አይሁድ በመካከላቸው የነበረውን የግሪክ ባህል መስፋፋት መቃወም ጀመሩ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በነበሩት ዓመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁድ ሕይወታቸውን አጡ። ዳሩ ግን በመጨረሻ በ162 ዓ.ዓ. ሴሉሲድስ የተባሉትን የሶርያ ግሪኮች በማሸንፍ በከፊል ነጻነታቸውን ለማግኘት ችለው ነበር። በ142 ዓ.ዓ. እስራኤል ሐስሞኒያንስ በሚባሉ ካህናት የምትመራ ነጻ መንግሥት ሆነች። አይሁድ ለ79 ዓመታት ከአሕዛብ ነጻ ሆነው ኖሩ።

ግሪኮች ይገዙ ከነበረበት ወቅት ቆይታ በአዲስ ኪዳን ዘመን ላይ ብዙ ተጽዕኖ ያሳደሩ በርካታ ነገሮች ተለውጠዋል። ከእነዚህም ዋናው የግሪክ ቋንቋ ሁሉም ስፍራ የሚነገር የንጉሠ ነገሥቱ ዋና ቋንቋ መሆኑ ነበር። በአይሁድ አፈታሪክ መሠረት በ250 ዓ.ዓ. 72 ምሁራን ብሉይ ኪዳንን በ72 ቀናት ውስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተረጐሙ። ይህም ሴፕቱዋጀንት በመባል የሚታወቀው የግሪክ ብሉይ ኪዳን፥ የዕብራይስጥ ወይም የአራማይክ ቋንቋ ለማይናገሩና ከጳለስጢና ውጭ ይኖሩ ለነበሩ አይሁድ ዋና መጽሐፍ ሆኖ ነበር። ደቀ መዛሙርት በሚገባ ያውቁትና በአምልኮአቸው ይጠቀሙበት የነበረው ይህንን ብሉይ ኪዳን ነበር፡፡ አዲስ ኪዳን በአጠቃላይ የተጻፈው በግሪክ ቋንቋ ነበር። ስለዚህ በግሪክ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሕዝቦች ሊረዱት የቻሉ ሲሆን፥ በኋላም በሮም የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ የወንጌል ሥራ በቀላሉ እንዲካሄድ ረድቶአል። 

3. በሐስሞኒያን ካህናት መሪነት ሥር የተገኘው ነፃነት (142-64 ዓ.ዓ.)

በመጨረሻ አይሁድ ነፃነታቸውን በተጎናጸፉ ጊዜ፥ ወዲያውኑ የአይሁድ ባህል እንቅስቃሴ ተጀመረ። የግሪክ ባህል የሚመስል ነገር ሁሉ ለጊዜው ተደመሰሰ፡፡ የሐሰት አምልኮ ይፈጽሙ የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሳምራውያን ተገደሉ። በእነዚህ ዓመታት ይሁዳ በጳለስጢና ውስጥ ከሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ ገናናዋ አገር ሆነች። እስከ ሶርያና ግብፅ ወደብ ድረስ የነበረውን ምድር ሁሉ አሸንፋ ያዘች። ይሁዳ፥ ሰማርያና ገሊላ በአይሁድ ቁጥጥር ሥር ሆኑ።

ዳሩ ግን ይህ ጊዜ የተለያዩ የአይሁድ ካህናት ለመሪነት የሚታገሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ሥልጣን ለመያዝ ወይም የበላይ ለመሆን ብሎ አንዱ መሪ ሌላውን ያስገድል ነበር፤ ወይም ሌላኛውን መሪ ለመዋጋት ጦር ያደራጅ ነበር፡፡ የሃይኖትና የፖለቲካ መሪዎችና ቡድኖች እርስ በርሳቸው ይዋጉ ነበር፡፡ የራሳቸውን ጥቅም ከማራመድ ሌላ ስለተራው አይሁዳዊ ምንም ግድ አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ ተራዎቹ አይሁዳውያን ከአሕዛብ አገሮች ነጻነታቸውን ያገኙ ቢሆኑ እንኳ እነዚህ ዓመታት ለእነርሱ የሰላም ዓመታት አልነበሩም፡፡ ሕዝቡ እነዚህን በሥነ-ምግባር የተበላሹና ሥልጣን የጠማቸውን መሪዎች በማየት የጽድቅና የሰላም መንግሥት የሚያመጣላቸውን የመሲሑን መምጣት እጅግ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር፡፡

በእነዚህ ዓመታት በሕዝቡና በአዲስ ኪዳን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሁለት የካህናት ቡድኖች መቋቋም ጀምረው ነበር፡፡ መጀመሪያ፥ የግሪክን ባህል በብዛት ያዛመዱ ካህናት የሚገኙበት ቡድን ነበር፡፡ እነዚህ ሀብታሞችና ዘመናውያን የነበሩት ካህናት የእስራኤልን የሊቀ ካህንነት ስፍራ ይዘው ነበር፡፡ ሀብታሞችና ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ቢሆኑም ብዙዎች አይሁድ ግን አያከብሯቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝቡን በኃይል መምራት ችለው ነበር፡ ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በስተቀር በየትኞቹም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና በሙታን ትንሳኤ አያምኑም ነበር፡፡ እዚህ ካህናት የፈሪሳውያን፥ የዮሐንስና ኢየሱስ ቀንደኛ ጠላቶች ነበሩ።

በሁለተኛ ደረጃ የፈሪሳውያንን ቡድን እናገኛለን። ፈሪሳውያን የዕዝራን፥ በኋላም የሃዚዲም የተባለውን ቡድን ባህልና ወግ የተከተሉ አክራሪ የአይሁድ ካህናት ነበሩ፡፡ ፈሪሳውያን የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ለመከላከል ወይም ለማስጠበቅ የሚቀኑ ወግ አጥባቂዎች ነበሩ፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው የብሉይ ኪዳን ሕግጋት እንዳይተላለፍና የእግዚአብሔርን ሕግጋት በመጠበቅ ጻድቅ ሆኖ ከፍርድ እንዲያመልጥ ይጠብቁታል ብለው ያመኑባቸውን በሺህ የሚቆጠሩ ሕግጋት አዘጋጅተው ነበር። የባዕድ የሆነውን ማንኛውንም ነገር ይቃወሙ ነበር። ፈሪሳውያን በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም እንኳ በጣም መንፈሳዊ ሰዎች ናቸው ብለው በሚያምኑባቸው መካከል እጅግ የተከበሩ ነበሩ። ባህላቸውን በመከተል ፈንታ፥ የአሕዛብን መንገዶች ስለተከተሉ ፈሪሳውያን ሰዱቃውያን ይጠሏቸው ነበር። እንደ ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ትኩረታቸው እነርሱ ወይም ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በማድረጋቸው ላይ ሳይሆን፥ ውጫዊ የሆኑ ሕግጋትን በመጠበቃቸው ላይ ነበር። በመሆኑም መንፈሳዊ ትዕቢት አድሮባቸው ነበር። መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ ውጫዊ የሃይማኖት መልካቸውን የሚቃወሙና ለእነርሱም ለመታዘዝ የማይፈልጉ ስለነበሩ ፈሪሳውያን ጠሉዋቸው። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል ሤራውን ያቀነባበሩት እነርሱ ነበሩ። 

4. ጳለስጢና በሮምና በታላቁ ሄሮድስ አገዛዝ ሥር (64-4 ዓ.ዓ.)

አይሁድ ለጥቂት ጊዜ አግኝተውት የነበረውን ነፃነት በ64 ዓ.ዓ. ተቀሙ። የሮም ሠራዊት ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት የይሁዳን ሕዝብና መንግሥት ተቋጣጠረ። ሮማውያን ወደ ቤተ መቅደሱ በመግባት ስላረከሱት በአይሁድ ዘንድ ጥላቻን አተረፉ። ሆኖም እነኝሁ ሮማውያን እስከ 70 ዓ.ም. ድረስ የፈለጉትን ጉዳይ እንዲፈጽሙ ለአይሁድ ሰፊ ነጻነት ሰጥተዋቸው ነበር። ሮማውያን ጳለስጢናን እንደ አንዲት ትንሽ ከፍለ ሀገር አድርገው ይቆጥሯት ነበር። አይሁድ ግን በሮማውያንም ሆነ በሌሎች አሕዛብ ቁጥጥር ሥር መሆናቸው አያስደስታቸውም ነበር። ነጻነትን ቀምሰው ነበር፡፡ ስለዚህ ሳይታክቱ ሮማውያንን አሽቀንጥረው ለመጣል ሞከሩ። ተቃወሚ የሆኑ ተዋጊዎች አብረዋቸው እንዲሰለፉ አይሁድን ለመሰብሰብ ጣሩ። በዚህም አይሁዳውያን ሕይወታቸውን አጡ። እንደነዚህ ካሉ የተቃዋሚ እንቅስቃሴዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የ«ቀናተኞች» ቡድን ሳይሆን አይቀርም። (ከደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ስምዖን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ቀናተኛ ነበር፤ ማቴዎስ 10፡4።)

ከይሁዳ በስተደቡብ በኩል ኤዶምያስ የሚባል ስፍራ ነበር። ኤዶማውያን በከፊል አይሁዳውያን በከፊል ደግሞ አሕዛብ (ዐረቦች ወይም ኤዶማውያን) ነበሩ፡፡ አንቲፓተር የተባለው መሪያቸው ከሮማውያን ጋር ወዳጅ ሆነና የአይሁድ ገዥ ሆኖ ተሾመ። ልጁ ታላቁ ሄሮድስ ባዘጋጀው የማታለል ዘዴ ሮማውያን «የአይሁዳውያን ንጉሥ» ብለው እንዲሰይሙት አደረገ። እርሱም ከ40 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከሞተበት እስከ 4 ዓ.ዓ. ድረስ ይሁዳን፥ ሰማርያንና ገሊላን ገዝቷል።

ሄሮድስ ብርቱ መሪ ነበር። በጳለስጢና ብዙ ከተሞችን በድጋሚ ሠርቶ ነበር። ይሁዳን ወደ ብርቱ አገር ለመለወጥ ታላቅ ጦር አደራጀ፡፡ በጳለስጢና ውስጥ ታላላቅ የመታሰቢያ ሐውልቶችን ሠራ። በዋናነት የሚጠቀሰው ሥራው ግን የሄሮድስ ቤተ መቅደስ የሚባለውን ሕንጻ መሥራቱ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሥራ የተጀመረው በ20 ዓ.ዓ. ነበር። ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የቤተ መቅደሱ ሥራ ተጠናቀቀ። ቤተ መቅደሱን የማስዋብ ሥራ ግን እስከ 63 ዓ.ም. ቀጠለ። አይሁድ ሄርድስን ቢጠሉትም፥ እርሱ የሠራውን ቤተ መቅደስ ግን በጣም ይወዱት ነበር። ሄሮድስ አይሁዳውያንና ሃይጎኖታቸው በመላው የሮም ንጉሠ ነገሥት ዝት ውስጥ የተከበሩ እንዲሆኑ አድርጎ ነበር። በዚያን ጊዜ በርካታ አሕዛብ የይሁዲነትን እምነት በመከተል እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሆኑ። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ላይ አሉታዊ የሆነ ንግግር ሲያደርግ አይሁድ የተቆጡት ስለዚህ ነበር (ዮሐንስ 2፡18-19፣ ማርቆስ 14፡57-58)። ይህ ቤተ መቅደስ ሲጓተት ቆይቶ በተጠናቀቀ በ7 ዓመቱ ማለትም በ70 ዓ.ም. በሮማውያን ተደመሰሰ እስከ ዛሬ ድረስም አልተሠራም።

ዳሩ ግን ሄሮድስ ጨካኝ ንጉሥ ነበር። የአመራር ሥልጣኑን ለመጨበጥ ባደረገው ትግል ከ45 በላይ የሆኑ ሰዱቃውያን ካህናትን ገድሏል። ሄሮድስ በዕድሜው እየገፋ ሲሄድ፥ አንድ ሰው ዙፋኔን ይወስድብኛል ብሎ መስጋት ጀመረ። ከዙፋኔ ያፈናቅሉኛል ብሎ ያሰባቸውን አብዛኛዎቹን ልጆቹንና ሚስቱን ገደለ። «የአይሁድ ንጉሥ» በቤተልሔም ተወልዷል የሚለውን ወሬ በሰማ ጊዜ በዚያች ከተማ ውስጥ የነበሩትን የአይሁድ ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ሄሮድስ በ4 ዓ.ዓ. ተገደለና ልጁ አርኬላዎስ ስፍራውን ወሰደ። ሄሮድስ የሞተው በ4 ዓ.ዓ. ስለሆነ ኢየሱስ የተወለደው ከዚህ በፊት መሆን አለበት። ምናልባትም ከ6-4 ዓ.ዓ. በነበረው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።

ማስታወሻ፡- ኢየሱስ የተወለደበት ጊዜ እኛ እንደምንጠብቀው 1 ዓ.ም. እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ያልሆነበት ምክንያት፥ የክርስቲያን ቀን አቆጣጠር እስከ 526 ዓ.ም. ድረስ ያልተጀመረ በመሆኑ ነው። ይኸውም ዛሬ አብዛኛው የዓለም ክፍል የሚጠቀምበትን የክርስቲያን የቀን አቁጣጠር የጀመረው መነኩሴ የቀን መቁጠሪያውን በሚወስንበት ጊዜ አምስት ዓመት ወደ ኋላ ሄዶ በመጀመሩ ነው።

በእነዚህ ዓመታት በአዲስ ኪዳን የተንጸባረቁ አንዳንድ ነገሮች ተፈጽመው ነበር፤ እነርሱም:-

1. አይሁድ መሢሑ እንዲመጣ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። የሚጠባበቁት ስለ ኃጢአታቸው መመሞት የመጣ ትሑት መሢሕ አልነበረም፡፡ እነርሱ የሚጠብቁት መሢሕ በጠላቶቻቸው በአሕዛብ ላይ ድልን በመንሣት ለምድራቸው ሰላም የሚያመጣውን ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ መሢሑ እንደተወለደና ቶሎ መግዛት እንደሚጀምር ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን ስለተጠቀመ ወዲያው ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ ዳሩ ግን  ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው ከተጠላው ከገሊላ ስለነበረና እንደ ድል አድራጊ ንጉሥም ሆኖ ስላልመጣ አልተቀበሉት፡፡ በእርሱ ላይ በመቆጣትም በመስቀል ላይ ቸነከሩት፡፡

አይሁድ ነጻ ለመውጣት በውስጣቸው ይቃጠል ነበረው ስሜት በመጨረሻ በ68 ዓ.ም. ፈነዳና በሮም ላይ አመጹ። እጅግ ከባድና አስቸጋሪ የሆነ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በ70 ዓ.. ኢሩሳሌምና ቤተመቅደሱ ተደመሰሱ፡፡ የይሁዳ መንግሥት ህልውና አከተመ። አዲሲቱ እስራኤል በ1948 ዓ.ም. እስከ ተመሠረተች ድረስ አይሁድ በዓለም ሁሉ ተበትነውና የጥቃት ኢላማ ሆነው ለብዙ አመታት ኖሩ፡፡

2. በሃይማኖት መሪዎች መካከል ያለማቋረጥ ይታይ የነበረው ልዩነት፡- የሰዱቃውያንና የፈሪሳውያን አጀማመር እንዴት እንደነበረና በመካከላቸው የነበረውን ጥላቻ ተመልክተናል፡፡ በአዲስ ኪዳን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ ኤሰነስ በመባል የሚጠራ ሌላ የሃይማኖት ቡድን ነበር። እነዚህም በአይሁድ ካህናትና ሕዝብ የፖለቲካና የሃይማኖት ሥነ-ምግባር የተሰላቹ ወገኖች ነበሩ፡፡ ስለዚህ በበረሃ የሚኖር አንድ አነስተኛ ማህበረሰብ አቋቁመው ነበር። ራሳቸውን እንደ እውነተኛ የእስራኤላ ቅሬታ በማየት በግል ቅድስና ላይ ያተኩሩ ነበር። መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ በብርሃን (መልካም) እና በጨለማ (ክፋት) መካከል ስለሚካሄድ ጦርነት ያስተምሩ ነበር። ይህ ቡድን በመጥምቁ ዮሐንስና በኢየሱስ አገልግሎት ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ ምሁራን የተለያየ አስተያየት አላቸው። አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ የዚህ እምነት ክፍል አባሎች ነበሩ ይላሉ፡፡ ይህ ግን የማይሆን ነው፡፡

3. የአዋልድ መጻሕፍት መጻፍ፡- አይሁድ በእነዚህ ዓመታት በአብዛኛው ወደሚመጣው መሢሕ የሚያመለክቱ የተለያዩ መጻሕፍትን ጽፈዋል። አብዛኛዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት ከ200 ዓ.ዓ.-100 ዓ.ም. ነበር። አይሁድ እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል ናቸው አላሉም። ነገር ግን መጻሕፍቱን ሰብስበው በአንድ ላይ ጠረዟቸው። በኋላም አይሁድ እነዚህን መጻሕፍት ወደ ግሪክ በተረጐሙ ጊዜ ከጳለስጢና ውጭ የሚኖሩ አይሁዶችና ክርስቲያኖች መጻሕፍቱን ስለወደዷቸው በብሉይ ኪዳን ትርጉሞች ውስጥ አካተቷቸው። ከዓመታት በኋላ የኦርቶዶክስና የሮማ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አድርገው ተቀበሏቸው። ፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ግን የቀድሞውን የአይሁድ (እንዲሁም የጥንት ክርስቲያኖች) አመለካከት በመያዝ፥ እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አይደሉም በሚለው አቋም ጸንተዋል። እነዚህን መጻሕፍት በሚመለከት በጥንቃቄ የሚደረግ ጥናት፥ ከቀረው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ጋር የማይስማሙ ትምህርቶች እንዳሉባቸው ያረጋግጣል። በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ከሚከሰቱ ልዩ ትምህርቶች የአብዛኛዎቹ ምንጮች እነዚህ መጻሕፍት ናቸው (ለምሳሌ፡- ዐፀደ ንስሐን የሚመለከተው ትምህርት)።

የውይይት ጥያቄ፥ በ400 ዓመታት የተፈጸሙትን ታሪኮች የሚናገረውን ይህንን ክፍል ከልስ። እነዚህ ታሪኮች በኢየሱስ ዘመን በነበሩት አይሁድ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: