መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል

የተለየ ትኩረት ሳይሰጥ የሚያነብ አንባቢ እንኳን መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነብበት ጊዜ መጽሐፉ ፍጹም ልዩ መሆኑን ይገነዘባል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ የሚያጠቃልል ሲሆን ፥ ከአርባ በሚበልጡ በተለያዩ ዘመናትና፥ የኑሮ ሁኔታዎች ውስጥ ባለፉ ጸሐፊዎች የተጻፈ ነው። ይሁን እንጂ የማይገናኙ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ስብስብ ሳይሆን፥ አስደናቂ ተከታታይነትና ወጥነት ያለው፥ መጽሐፍ ነው። በአማርኛችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ድንቅ መጽሐፍ፥ በግሪክኛ “ቢብሉስ” በሚል ስያሜ ይታወቃል። እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች “ዘ ባይብል” የሚል ስያሜ የሰጡትም ከዚህ ቃል የተነሣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች የተጻፈ ቢሆንም በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ይህ ነው ልዩ ባሕርዩ። 

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚደግፉ ሁለት ማረጋገጫዎች አሉ። 1. አንዱ ውስጣዊው ማረጋገጫው ነው። ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመለከቱት እውነታዎች እና መጽሐፉ ራሱ ስለመለኮታዊነቱ የሚገልጠው ሲሆን፤ 2. ውጫዊው ማረጋገጫ ደግሞ፥ ልዕለ-ተፈጥሮ የሆነ ባሕርይውን የሚደግፉትና ውስጡ የተጠቀሱት እውነቶች ናቸው። 

ሀ. ውስጣዊ ማረጋገጫ 

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በመቶ በሚቆጠሩ የንባብ ክፍሎቹ ራሱ ገልጧል (ዘዳ. 6፡6-9፥ 17-18፤ ኢያሱ 1፡8፤ 8፡32-35፤ 2ኛ ሳሙ. 22፡31፤ መዝ. 1፡2፤ 12፡6፤ 19፡7-11፤ 93፤5፤ 119፡9፥ 11፥ 18፥ 89-93፥ 97-100፥ 104-105፥ 130፤ ምሳሌ 30፡5-6፤ ኢሳ. 55፡10-11፤ ኤር. 15፡ 16፤ 23፡29፤ ዳን. 10፡21፤ ማቴ. 5፡17-19፤ 22፡29፤ ማር. 13፡31፤ ሉቃስ 16፡17፤ ዮሐ. 2፡22፤ 5፡24፤ 10፡35፤ ሐዋ. 17፡ 11፤ ሮሜ 10፡17፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡13፤ ቆላ. 3፡ 16፤ 1ኛ ተሰ. 2፡13፤ 2ኛ ጢሞ. 2፡15፤ 3፡15-17፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡23-25፤ 2ኛ ጴጥ. 3፡15-16፤ ራእይ 1፡2፤ 22፡18)። ለማንም ግልጥ በሚሆን ሁኔታና በብዙ መንገዶች፥ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ገልጠዋል። የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ክርስቶስም ጭምር፥ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ገላጭነት የተጻፈ ቃል ነው ይላሉ። ለምሳሌ መዝሙር 19፡7-11 ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ተገልጦ፥ ፍጹምነትንና በአንጻሩ በቃሉ አማካይነት የተለወጡ ስድስት ሰብአዊ ባሕርዮች ተመልክተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስም ሕግ መፈጸም እንደነበረበት ገልጧል (ማቴ. 5፡17-18)። ዕብራውያን 1፡ 1-2 ውስጥም እግዚኣብሔር በብሉይ ኪዳን ለነቢያቱ፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ለልጁ የተናገረ መሆኑ ተረጋግጧል። ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን የእግዚአብሔር ቃልነት የማይቀበል የሚሆነው፥ መጽሐፉ የእግዚአብሔር ቃል ስለመሆኑ ራሱ የሚሰጠውን የተደጋገሙ መረጃዎች የማይቀበል ሲሆን ብቻ ነው። 

ለ. ውጫዊ ማረጋገጫ 

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በራሱ የሚያስረግጥ ብቻ ሳይሆን፥ ተጠራጣሪዎችን እንኳን ለማሳመን በሚችሉ ብዙ መረጃዎች የተሞላ ነው። 

1. የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታታይነት ወይም ወጥነት። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጡት እጅግ አስገራሚ እውነቶች አንዱ፥ ወደ 1600 ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ በኖሩና ከአርባ በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ሰዎች የተጻፈ መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፉ የስድሳ ስድስት መጻሕፍት ስብስብ ሳይሆን፥ አንድና ወጥ ነው። ጸሐፊዎቹ ከተለያየ ማኅበራዊ መሠረት የመጡ ናቸው፤ ነገሥታት፥ ጭሰኞች፥ ፈላስፋዎች፥ ዓሣ አጥማጆች፥ ሐኪሞች፥ የመንግሥት ባለሥልጣናት፥ ምሁራን፥ ባለቅኔዎች እና ገበሬዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በተላያዩ ባሕሎችና ልምዶች መኖር ብቻ ሳይሆን፥ የተላያዩ ባሕርያትም ነበሯቸው። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በግልጥ የሚታይ ተከታታይነትና ወጥነት አለው። 

የመጽሐፉ ተከታታይነት ከአሁኑ ዓለም አፈጣጠር እስከ አዲሱ ሰማይና ምድር መፈጠር ድረስ ባለው ታሪካዊ ቅደም ተከተል ሥርዓት ሊታይ ይችላል። ብሉይ ኪዳን ስለ እግዚኣብሔር ባሕርይ፥ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ድነት፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ስለ መላው ዓላም፥ ስለ እስራኤልና ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ዓላማና ዕቅድ ይገልጣል። መለኮታዊ ትምህርት ከዝቅተኛው፥ ማለት ቀለል ካለ መግቢያ ተነሥቶ እስከተወሳሰበ ትምህርትነት ደረጃ በደረጃ ይቀርባል። መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ አገላለጦችን በቀጥተኛ ትርጉማቸው፥ ትንቢቶችን ደግሞ በተወሰነ ጊዜ ክንውናቸው ያሳያል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ፥ በሰማይና በምድር እጅግ ስለከበረውና ፍጹም ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድሚያ መተንበይ፥ የትንቢቱን እውንነት ማመልከትና ኢየሱስን ከፍ ማድረግ ነው። ይህ አስደናቂ መጽሐፍ በሰዎች ተጻፈ ብሉ ከማመን ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ገላጭነት ተጻፈ የሚለውን መቀበሉ ይቀልላል። ስለሆነም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ሁሉ፥ የተለያዩት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች በተለያዩ ሰዎች የተጻፉ መሆናቸውን በመቀበል፥ የመልእክቶቹን አንድ ወጥነት በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና አነሳሽነት ይረዳሉ። 

2. የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ ጥልቅነት። እውነትን በመግለጥ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ተመርምሮ አያልቅም። ቴሌስኮፕ የሰማይን ከፍታ እንደሚያሳይ፥ መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔርን የእጅ ሥራዎች ከመነሻ እስከ ፍጻሜ፥ ከሰማያት ከፍታ፥ እስከ ሲኦል ጥልቀት ያመለክታል። ማይክሮስኮፕ ረቂቅ ነገሮችን እንደሚያሳይ ሁሉ፥ ረቂቁ የእግዚአብሔር ሥራ፥ ዕቅድና ዓላማው እንዲሁም የፍጥረቱ ፍጹምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት ብዙ መጻሕፍት የተጻፉት፥ ጸሐፊዎቹ ስለዘመናዊው ግኝት ግምት ባልነበራቸው ጊዜና በጥንታዊው የሰው ልጅ እውቀት ደረጃ ቢሆንም፥ በቅርቡ የተገኙት የሥነ-ምድር ምርምር ጥናቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች ከመቃረን ይልቅ ይደግፋሉ። ጥንታዊዎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚያስደንቅ አኳኋን ከዘመናዊው የሥነ-ምድር ምርምር ግኝቶች ጋር ይስማማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ዘላለማዊነት ያላቸውንና በእግዚአብሔር ብቻ የሚታወቁትን እውነቶች ስለሚገልጥ፥ ከሰው ምርምርና ግኝት በላይ የሆኑ እውነቶችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በሙላትና በረቂቅነት የሚያሳየንን ያህል የሚያሳይ ሌላ መጽሐፍ በዓለም የለም። 

3. የመጽሐፍ ቅዱስ የመለወጥ ኃይልና ኅትመቱ። በዓለማችን የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ለተለያዩ ሕዝቦችና ባሕሎች በተለያዩ ኣያሌ ቋንቋዎች የታተመ ሌላ መጽሐፍ የለም። የማተሚያ መኪና እንደተፈለሰፈም ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዓለም ታላላቅ ቋንቋዎች ሁሉ በብዙ ሚሊዮን ቅጂዎች ታትሟል። ጽሑፍ ያለው እያንዳንዱ ቋንቋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቢያንስ ጥቂት ክፍሎች የታተመ ነገር አለው። ምንም እንኳን እንደ ፈረንሳዊው ቮልቴር ያሉ ሃይማኖት የለሾች መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በኋላ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል ቢሉም፥ የሀያኛው ክፍለ-ዘመን ደራሲያንም መጽሐፉ ይረሳል ወይም ፈላጊ አይኖረውም ቢሉም፥ ካለፈው ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች በመታተም ላይ ነው። በተከታዮች ብዛት ከክርስትና የሚበልጡ ሌሎች ሃይማኖቶች፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሊወዳደር የሚችልና መገለጥ ያለው ጽሑፍ ሊያቀርቡ አልቻሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን የመለወጥ ኃይል በዘመናችንም ቀጥሏል። ላልዳነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ “የመንፈስ ሰይፍ” ነው (ኤፌ. 6፡17)፤ ለዳነው የሚያነጻ፥ የቅድስናና ድል አድራጊነት ኃይል ነው (ዮሐ. 17፡17፤ 2ኛ ቆሮ. 3፡ 17፥ 18፤ ኤፌ. 5፡25-26)። መጽሐፍ ቅዱስ የሕግና የሥነ-ምግባር ብቸኛው መለኮታዊ መሠረት እንደሆነ ይኖራል። 

4. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት። የመጽሐፍ ቅዱስ ከሰው እውቀት በላይ የሆነ ባሕርይ የሚታየው፥ ሊታወቅ የማይቻልን እውነት ግልጥና እንዲታወቅ አድርጎ ማቅረቡ ነው። ዘላለምን ማለት ሰው ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ተፈጥሮ ሳይቀር ይገልጣል። የእግዚኣብሔር ባሕርይና ሥራዎቹም ተገልጠውበታል፡፡ እግዚኣብሔር ለዓለም፥ ለእስራኤልና ቤተ ክርስቲያን ያለው አሳብና ዘላለማዊ ዕቅዱ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ውስጥ ተጠቃሏል። በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ገለጣ የመጨረሻ፥ ትክክልና ጊዜ የማይገድበው ነው። ሁለንተናዊ ባሕርይው ኣንባቢዎቹን ከጊዜና ከዘላለም ጋር በተዛመደ ነገር ብልሆች አድርጓቸዋል። 

5. መጽሐፍ ቅዱስ ስነ-ጽሑፍነቱ። በሥነ-ጽሑፍነቱ ሲታይ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ምጡቅ ነው። ታሪካዊ ዘገባዎችን ብቻ ሳይሆን፥ ዝርዝር ትንቢቶችን፥ ውብ የሆኑ ቅኔዎችን፥ ልዩ ውበት ያለው ተውኔትን፥ የፍቅርና የጦርነት ታሪኮችን፥ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ላይ የሚነሡ ፍልስፍናዎችን ያጠቃልላል። የጸሐፊዎቹ መለያየት ከያዛቸው ጉዳዮች ስብጥር ብዛት ጋር ይስማማል። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናት የኖሩትንና በሁሉም የእውቀት ደረጃ ላይ የነበሩትን ሰዎች የማረከ ጽሑፍ የለም። 

6. የማያዳላው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ለሰዎች እንዲያደላ አላደረገውም። ያለማመንታት የማንንም ኃጢአት እና ደካማነት ይገልጣል። ይህ ብቻ አይደለም፥ በራሳቸው በጎ ምግባር የሚታመኑ ፍጻሜያቸው ጥፋት መሆኑንም ያስገነዝባል። በሰዎች ብዕር ቢጻፍም፥ ከሰው ወደ ሰው ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ወደ ሰው የተላለፈ መልእክት ነው። ስለ ምድራዊ ነገሮችና ስለ ሰዎች ልምምድ ቢገልጥም፥ የሰማይና የምድርን፥ የሚታዩና የማይታዩ ነገሮችን፥ ስለ እግዚአብሔር የሚገልጡ እውነቶችን፥ ስለ መላእክት፥ ስለ ሰው፥ ስለ ጊዜና ዘላለም፥ ስለ ሞትና ሕይወት፥ ስለ ኃጢአትና ድነት፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትና ሲኦልም በግልጥነትና በሥልጣን ያብራራል። እንዲህ ያላን መጽሐፍ ሰው መጻፍ ቢፈልግ እንኳን፥ ያለመለኮታዊ ምሪት ሊጽፈው አይችልም ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ፥ ሰሰው ቢጻፍም፥ እግዚአብሔር ብቻ ከሚሰጠው እርግጠኛነት፥ ዋስትና እና ሠላም ጋር ከርሱ የተላከ ነው። 

7. የመጽሐፍ ቅዱስ ሉዓላዊ ባሕርይ። መጽሐፍ ቅዱስ፥ ከሁሉም ይልቅ እግዚአብሔር በልጁ በኩል እራሱን መግለጡን ያመለከተ፥ አካልነቱንና ክብሩን ያስገነዘበ ታላቅ መጽሐፍ ነው። እንደ ኢየሱስ ያለው ሰብእና የሟች ሰው ፈጠራ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ፍጹምነቱ ከሁሉ የላቀ እንዲሁም ቅድስናና ጥበብ ያለው በመሆኑ የዚህ ምድር ሰው የሚገነዘበው አልነበረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ባሕርይ የኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅ ታሪክ በመግለጥ ተረጋግጧል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተካተቱት ሰብአዊና ከሰብአዊነት በላይ በሆኑ ባሕርያት ኅብረት የተነሣ፥ የተጻፈ ቃል በሆነው መጽሐፍ ቅዱስና፥ ሕያው ቃል በሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ተመሳሳይነት ይታይ ይሆናል። ሁለቱም ከመሠረታቸው መለኮታዊ ናቸው። በመሆናቸውም የመለኮትንና የሰውን ምስጢራዊና ፍጹም ግንኙነት ይገልጣሉ። ሁለቱም በሚያምኑ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚሠራ የመለወጥ ኃይል ያላቸው ሲሆን፥ የማያምኑ ሰዎችን ደግሞ እንዳይቀበሷቸው በሚፈልግ ፈቃዳቸው እንዲቀጥሉ እግዚአብሔር ትቷቸዋል። በሁለቱም ውስጥ የማይበከለውና የማይሻረው መለኮታዊ ፍጹምነት አለ። የሚገልጿቸው እውነቶች የሕፃን አእምሮ በሚገነዘበው ደረጃ ቀላል ናቸው። ያንኑ ያህል፥ ፍጻሜ የሌለው የመለኮታዊው ጥበብ እንዲሁም እውቀት ሀብቶች ሲሆኑ፥ እንደፈጠራቸው እንደ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ናቸው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: