የጌታ እራት

የተለያዩ ሰዎች ስለ ጌታ እራት የተለያየ ትርጉም አላቸው። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች፥ ህብስቱና ወይኑ መልካቸውን ባይለውጡም፣ በትክክል የክርስቶስ አካልና ደም ይሆናሉ ብለው ያምናሉ። ይህ አመለካከት [“ትራንስብስታንሺዬሽን” /Transubstantiation] የሚባል ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነም ነው። ምክንያቱም የክርስቶስ ደምና ሥጋ ይህ ሥርዓት በተፈጸመ ቁጥር መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒው የሚገልጠው የክርስቶስ ሞት ሙሉና በቂ፥ እንዲሁም ላንዴና ለሁልጊዜ የተፈጸመ መሆኑን ነው (ዕብ. 10፡101 9፡12)። ሉተራውያን ደግሞ ወይኑና ህብስቱ ለውጥ ባይኖራቸውም፥ ሰው ከቅዱስ ቁርባኑ በሚቋደስበት ጊዜ እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም ይሆናሉ ይላሉ። ይህም “ካንሰብስታንቪዬሽን” [Consubstantiationa] ይባላል። ሌሎች ደግሞ ይበልጥ ትክክል የሚመስል አመላካከት ያቀርባሉ፡- የጌታ እራት ሥርዓት የሚዘከረው ለመታሰቢያነት ብቻ ነው (1ኛ ቆር. 11፡24-25 “ለመታሰቢያዬ”) ህብስቱም ሆነ ወይኑ አይለወጡም፤ ክርስቶስ ግን በአገልግሉቱ ወቅት በመካከላችን ይገኛል፤ ያም ቢሆን ከህብስቱና ከወይኑ ውስጥ አይደለም ይላሉ። 

የጌታ እራት የተለያዩ ዓላማዎች አሉት፡-

1. የጌታችን ሕይወትና ሞት መታሰቢያ ነው። ህብስቱ ፍጹምና ቅዱስ ሕይወቱን ያመለክታል፤ ይህ ቅዱስ ሕይወት ለኃጢአት መሥዋዕትነት የበቃና ተቀባይነት ያለው ነው። ስለሆነም ህብስቱ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ የተሸከመውን የክርስቶስ አካል ያመለክታል (1ኛ ጴጥ. 2፡24)። ወይኑም ለኃጢአታችን ስርየት የፈሰሰውን ደም ይወክላል። ያ አካል ዳግመኛ ሲሰቀል ለማየትም ሆነ ደሙ ሲፈስ ለመመስከር ስለማንችል፥ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ለመታሰቢያነት ሲባል ብቻ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ አለብን። 

2. የጌታ እራት የወንጌልን እውነት የምናውጅበት ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡26)። 

3. የጌታን ዳግም ምጽአት በናፍቆት እንድንጠባበቅ ያሳስበናል፡፡ ይህን ሥርዓት የምናከብረው እስከዚያ ዕለት (ጌታ እስኪመጣ ድረስ ብቻ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 12፡26)። 

4. እራቱ በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለንን አንድነትና በዚህ አካል ውስጥ ካሉት አባላት ጋር ያለንን ኅብረት ያስታውሰናል(1ኛ ቆሮ. 10፡17)። 

መቼ መቼ ነው የጌታ እራት መከበር ያለበት? አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በየሦስት ወሩ ሲያደርጉ፥ በተለምዶ ሥርዓቱን ለመፈጸም ካሰቡበት እሁድ በፊት ዮዝግጅት አገልግሎቶችን ያከናውናሉ። አንዳንዶች በየወሩ ሲያደርጉ፥ በየእሁዱም መደረግ አለበት የሚሉ አሉ። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን እራት መከበሪያ ጊዜ ለይቶ አይነግረንም። ከበዓለ አምሳ ሰኋላ የነበሩት የመጀመሪያ አማኞች በየቀኑ ያደርጉት የነበረ ይመስላል። ይህ ግን በየቀኑ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ይከበር ነበር ማለት ሳይሆን፥ በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድ ማዕከል መፈጸሙን ለማመልከት ነው (ሐዋ. 2፡46)። በጢሮአዳ (ሐዋ. 20፡6) እሁድ ዕለት ተደርጎ ነበር። ታዲያ አንዳንዶች ከጥቅሱ በመነሳት በየእሁዱ ተደርጓል ቢሉም፥ በዚህ ሁኔታ ስለመዘከሩ በግልጥ የተጻፈ መረጃ አናገኝም። የቱንም ያህል ቢደጋገም፥ አንዳንድ ጊዜ በምሽት ቢከናወን ተመራጭ ሊሆን ይችላል። እራት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፥ ጠዋት ጠዋት መምጣት የማይችሉ ምእመናንም እንዲካፈሉ ለማድረግም ነው። ይህ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ከምታደርጋቸው ሌሎች ሥርዓቶች ይበልጥ ጠቃሚ ስለሆነ ሰፊ ጊዜ የሚሰጠው እንጂ፥ በችኮላ የሚከናወን ጕዳይ አይደለም።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: