ስለ ጌታ እራት ኢየሱስ የሰጣቸውን በርካታ መመሪያዎች መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

አንደኛ፥ የተሰጠው እንደ ትእዛዝ ነው። ሁሉም የእርሱ ተከታዮች የጌታን እራት ዘወትር እንዲወስዱ ተናግሯል። «ስትፈልጉ፥ የጌታን እራት ውሰዱ» አላለም። ወይም «ከፍተኛ መንፈሳዊነት ሲሰማችሁ፥ የጌታን ራት ብሉ» ወይም «ከተጠመቃችሁ በኋላ፥ የጌታን እራት ውሰዱ» ወይም «በቂ ጊዜ ሲኖራችሁ፥ የጌታን እራት ውሰዱ» አላለም። ይልቁንም፡ ሁሉም የእርሱ ተከታዮች የጌታን እራት በቋሚነት እንዲወስዱ ነው ያዘዘው። ክርስቲያኖች የጌታን እራት አዘውትረው ካልወሰዱ፥ የኢየሱስን ትእዛዝ እየጣሱ ነው። በብዙ መልኩ ይህ የሚያረጋግጠው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥ አንድ የሆነ ችግር እንዳለ ነው። ወይንም መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን እራት ሥርዓት ማክበር አስፈላጊያቸው እንደሆነ የሚያስተምረውን ትምህርት አልሰሙም ማለት ነው። 

ሁለተኛ፥ የጌታን እራት የምንወስድበት ዋነኛው ዐላማ «ለመታሰቢያነት» ነው። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ የምናደርገው ሁሉ፥ እርሱን እንደሚያሳስብ ኢየሱስ ለተከታዮቹ በተደጋጋሚ ተናግሯል። ይህ ምሳሌያዊ ሥርዓት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት መሠረቱ ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ መሞቱን ማመናችን መሆኑን እንድናስታውስ የሚረዳን ነው። 

ሦስተኛ፥ የጌታ እራት መሠረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለውን አዲሱን ኪዳን (ስምምነት) መጀመሩን መገንዘብ ነው። ወደፊት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡት በእስራኤልና በእግዚአብሔር መካከል በሲና ተራራ ላይ በተደረገው በአሮጌው ኪዳን መሠረት አይደለም። ይልቁንም ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነው። 

ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading