የጌታ እራት ሥረ መሠረት

ሁላችንም በሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማስታወስ እየታገልን ነው። የትኩረት አቅጣጫችን አስፈላጊነታቸው ዝቅተኛ ግምት በሚሰጣቸው እውነቶች ላይ ሲሆን፥ በጣም አስፈላጊ የሆነውን እንዘነጋለን። ለምሳሌ፥ በተአምራት ላይ በይበልጥ ለማተኮር ስኢየሱስ ላይ ያለን ትኩረት ይቀንሳል። ወይም ዓይናችንን በጥሩ ቤት ላይ፥ ብዙ ገንዘብ ስማግኘት ላይ፥ ወይም በትምህርት ላይ፥ ወዘተ… እናደርጋለን። ያለፈውን ታሪክና እግዚአብሔር ቀደም ሲል ያደረገልንን ለማስታወስ እንዳንችል በኑሮ ውጥረት ውስጥ ገብተን እንገኛለን። እንደዚያ እንደሆንን እግዚአብሔር ያውቃል፤ በመሆኑም እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕዝቡ ለእነርሱ ያደረገላቸውን እንዲያስታውሱ እንዴት ልዩ ቀን ወይም ልዩ ስፍራ እንደመሠረተላቸው እናነባለን። በኢያሱ 4፡15-24 ኢያሱ እንዴት 12 ድንጋዮችን ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ወስዶ የመታሰቢያ ሐውልት አድርጎ እንዳቆማቸው እናነባለን። በታሪክ ውስጥ የአይሁድ ሰዎች ሐውልቱን ሲመለከቱ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራና እንዴት ዮርዳኖስን አሻግሮ ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዳመጣቸው ያስታውሳቸዋል። ደግሞም የመታሰቢያ በዓላትም ነበሩ። ለምሳሌ፥ በማደሪያው ድንኳን ክብረ በዓል ጊዜ አይሁዶች ምቹ ቤቶቻቸውን እየተዉ፥ ለአንድ ሳምንት በጊዜያዊ ትንንሽ ድንኳኖች ይኖሩ ነበር። ይህንም ያደርጉ የነበሩት፥ በሙሴ ዘመን 40 ዓመት በምድረ በዳ በድንኳን የኖሩበትን ጊዜ ላለመርሳት ነው። 

እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የብሉይ ኪዳን የመታሰቢያ ክብረ በዓላት አንዱ የፋሲካ በዓል ነበር። በዘጸአት 12 እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ በግብፅ ላይ የመጨረሻ መቅሰፍት (ቁጣ) በማምጣት የግብፃውያን ስኩር (የመጀመሪያ) ወንድ ልጆችን ሁሉ እንዴት እንደ ገደለ እናነባለን። ይህ መልአክ፥ አይሁድ ሁለት ነገሮችን ካደረጉ የእነርሱን በኩር ልጆች እንደማይገድል እግዚአብሔር ነግሮአቸዋል። አንደኛ፥ እርሾን ሁሉ ከቤታቸው አስወግደው እርሾ የሌለበትን ቂጣ ብቻ መብላት አለባቸው። በአዲስ ኪዳን እንደተነገረን ይህ እርሾን ከቤት የማራቅ ድርጊት ኃጢአትን ክሕይወታቸው ማራቃቸውን የሚያመለክት ምሳሌ ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡6–8)። 

ሁለተኛ፥ አጥፊው መልእክ ከመምጣቱ በፊት በነበረው ሌሊት ጠቦትን እርደው፥ የተለየ ቅጠል ወስደው ሰጠቦቱ ደም ከነከሩ በኋላ ባበራቸው መቃንና በጉበኑ ላይ መቀባት ነበረባቸው። ከዚያም ጠበቱን ጠብሰው ቤተሰብ በሙሉ በአንድነት መብላት ነበረባቸው። በዚያች ሌሊት አጥፊው መልአክ በእስራኤላውያን መንደር ሲያልፍ፥ ሁሉም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽመው፥ ደሙንም በበሮቻቸው ላይ ቀብተው ስለነበር፥ መልአኩ የበኩር ልጆቻቸውን አልገደለም። ነገር ግን ደሙ በሌለበት ቤት የነበሩትን በኩር ወንድ ልጆች መልአኩ ገድሎአል። ይህ ኃይለኛ ቅጣት ነበር በስተመጨረሻ ፈርኦን አይሁድን እንዲለቅና ነፃ እንዲያወጣቸው ያስገደደው። እግዚአብሔርም ይህን የነፃነት ቀን በዘመናቸው ሁሉ እንዲያከብሩት ነግሮአቸዋል። ክብረ በዓሉም እግዚአብሔር ምን እንዳደረገላቸው ለማስታወስ ይረዳቸዋል። እግዚአብሔር የበኩር ወንድ ልጆቻቸውን አለመግደሉ ብቻ ሳይሆን፥ ሕዝቡንም ከባርነት ነፃ አውጥቶአቸዋል። 

በአዲስ ኪዳን እንደተነገረን ኢየሱስ የፋሲካው በዓል ምሳሌነት ፍጻሜ ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡7)። እርሱ ደሙ በመቃኑና በጉበኑ ላይ እንደተቀባው እንደታረደው «ጠቦት» ዓይነት ነው። ኢየሱስ ደሙን በመስቀል ላይ በማፍሰሱና እኛም ስናምን ደሙ በእኛ ላይ ስለሚታይ እግዚአብሔር ያድነናል። እርሱ ከኃጢአት ባርነት ነፃ ያወጣናል። አሁን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ ነን። 

ኢየሱስ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትን እንደ አዲስ የፋሲካ ክብረ በዓል ሰጥቶናል። ይህ ክብረ በዓልም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያደረገልንን በማስታወስና ከኃጢአት ነፃነታችንንና ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት በእርሱ ሞት ምክንያት መሆኑን ለሁሉም በግልጽ የምናውጅበት ነው። ዓላማው ኢየሱስ በመስቀል ላይ በምን ዓይነት ሥቃይ ውስጥ እንዳለፈ እንድናስታውስ እኛን መርዳት አይደለም። ይልቁንም፥ ትኩረቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞቱ በምናገኘው ጥቅም ላይ ነው። ማንኛውም እኛ ያገኘነው መንፈሳዊ በረከት የመጣው ኢየሱስ በመስቀል ላይ በፈፀመው ተግባር ነው። 

ለእግዚአብሔር የሚያስፈልገው የመታሰቢያ ቀን ብቻ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ኅብረት ማድረግን ይወዳል። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ለዚህ ኅብረት ምሳሌው የእግዚአብሔር መገኘት ባለበት ሥፍራ አንድን ነገር በመብላት ነው። በዘጸአት 24፡9-11 እንዴት ሽማግሌዎች በሲና ተራራ ላይ በእግዚአብሔር ፊት እንደበሉ እናነባለን። እስራኤላውያን አስራታቸውን ወይም የድነት (የደኅንነት) መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ሲያመጡ፥ በእግዚአብሔር ሕልውና ፊት ይበሉ ነበር (ዘሌዋ. 11፡17-18፤ ዘዳግ. 14፡23፥ 26፤ 27፡7)። ኢየሱስ ተመልሶ ሊመጣ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደገና ከእግዚአብሔር ጋር የኅብረትን ምግብ እንደሚመገብ ተነግሮናል (ራእይ 19፡9)፡፡ የጌታ እራትም የኅብረት መግለጫ መብል ነው፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን ሆኖ ሁላችንም እንደ ክርስቶስ አካልነት (ማቴ. 18፡20)፥ ለኢየሱስ ክብር እንበላለን። ይህ ከኢየሱስ ጋርና እርስ በርሳችን ያለን ኅብረት የተቻለው በኢየሱስ ሞት ለተካፈለው የኃጢአታችን እዳ ነው።

ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading