የሕይወት እንጀራ

የጌታ እራት

ጌታን እራት ለሚያስፈጽሙ መሪዎች አስተያየት

This entry is part 178 of 8 in the series የጌታ እራት

የጌታን እራት መውሰድ አነስተኛ ግምት የሚሰጠው አላስፈላጊ የኢየሱስ ተከታዮች ድርጊት ከመሆን ይልቅ፥ ለእያንዳንዱ አማኝ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል። አባሎቻችን የመዘመር፥ የኳየር መዝሙር የማዳመጥ፥ ወይም ስብከት የማዳመጥን ያህል የጌታ እራትን መውሰድ ኢየሱስን የማምለክ አንዱ ክፍል መሆኑን እንዲያውቁ ማድረግ ይጠበቅብናል። ማንኛውም ያልተጠመቀ ሰው የጌታን እራት መውሰድ የለበትም ብላ ቤተ ክርስቲያናችን የምታስተምር ከሆነ፥ ሰዎች እንዲጠመቁና ከእኛ ጋር የጌታን እራት እንዲወስዱ ልናበረታታቸው ያስፈልጋል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ በቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ከተወሰደባቸው ምእመናን በስተቀር፥ አንድ ሰው ካመነ በኋላ የጌታን እራት ሳይወስድ ለረጅም ጊዜ የቆየበት ወቅት አልተሰማም። የጌታን እራት በአንድነት በመብላት የደኅንነታቸው መሠረት የኢየሱስ ሞት ብቻ መሆኑን አማኞች ሁሉ ቢያረጋግጡ ምንኛ መልካም ነበር? ስለ እኛ በመሞቱ ለኢየሱስ ምስጋናችንን የምንገልጽበት ቁልፍ መንገድ ይሆን ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን በአንዱ የክርስቶስ አካል ኅብረታችንን የምንገልጽበት ዋንኛ መንገድም ነው።  የሚከተሉትን አስተያየቶች በመጠቀም መሪዎች፥ አማኞች የጌታን እራት ሲወስዱ ከኢየሱስ ጋር የመገናኘት ልምምዳቸው ከፍ እንዲል ሊረዷቸው ይችላሉ።  1. አማኛች ሁሉ የጌታን እራት የአምልኮአቸው ተቀዳሚ ተግባር እንዲያደርጉ አበረታቱ። ወደ ቤት ቀድመው ከመሄድ ይልቅ መሳተፍ ያስፈልጋቸዋል።  2. አባላት ኢየሱስን ለመገናኘት ሰአዕምሮአቸው ተዘጋጅተው እንዲመጡ አበረታቷቸው (አደፋፍሯቸው)። አማኞች አኗኗራቸው በኢየሱስ ሞት ላይ ያላቸውን እምነት ማንጸባረቅ ያለማንጸባረቁን የጌታን እራት ሲወስዱ እንዲገልጹ፥ በሳምንቱ ውስጥ ሕይወታቸውን በመፈተሽ ሊቆዩ ያስፈልጋል። አብዛኛው የኀጢአት ኑዛዜ መደረግ የሚገባው ከአምልኮ ሥርዓቱ በፊት እንጂ፥ በሥርዓቱ ጊዜ አይደለም።  3. የጌታ እራትን የመውሰድ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት፥ ለምእመናን የጌታን እራት መቀበል ምሳሌነት አስታውሷቸው። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንደተመለከትነው፥ የጌታ እራት በተምሳሌት የበለጸገ ነው። የጌታን እራት ስንወስድ ስንበላና ስንጠጣ ምን እየገለጽን እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል።  4. አማኞች ያለአግባብ የጌታን እራት መብላታቸው አደጋ እንዳለው አስጠንቅቋቸው። እያንዳንዱ ምእመን እንደገና ልቡን መመርመርና ለጌታውና አዳኙ ኢየሱስ በትሕትና እየታዘዘ እየተራመደ እንደሆነ መፈተሽ ይገባዋል። ኃጢአታቸውንም እንዲናዘዙ አበረታቷቸው። በእውነት ከተናዘዙ የኢየሱስ ደም ከኃጢአታቸው ፍፁም ሊያነፃቸው እንደሚችል አስገንዝቧቸው። ነገር ግን የኑዛዜውን ጊዜ የሥርዓቱ ዋንኛ ክፍል እንዲሆን አታድርጉ፡፡  5. የኢየሱስ ሥጋና ደም ለእኛ ያደረገውን በማሰብ ሕዝቡ እግዚአብሔር አብንና ኢየሱስን እንዲያመሰግኑ የተለያዩ ነገሮችን አድርጉ። መዝሙር ዘምሩ፥ ደስ የሚያሰኙ የምስጋና ቃላትና ለጌታ መገዛትን በሚያሳዩ የማስተዋል ቃላት ተጠቀሙ። ሰዎች የኢየሱስ ሞት ያመጣላቸውን የሚያስደንቅ ነገር የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማንበብ እንዲገልጹት ፍቀዱላቸው። አጫጭር የምስጋና ጸሎቶችንም ይጸልዩ። የጌታን እራት መውሰድ ትኩረቱ ኢየሱስን ለማመስገንና በእርሱ መመካታችንን እንደገና ለማረጋገጥ ነው እንጂ፥ በኢየሱስ ሥቃይ ላይ መሆን የለበትም።  6. ይህን ምስጋና የሞላበትን የአምልኮ ጊዜ ኢየሱስ ባሳየን ወይም ጳውሎስ በገለጸው መሠረት ኅብስቱንና ጽዋውን በመውሰድ (1ኛ ቆሮ. 11፡23-26)። ሰዎች የጌታን እራት እየወሰዱ ያሉት በልምድ ብቻ ከሆነ፥ አወሳሰዱን መለወጥ ያስፈልግ ይሆናል። አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረታቸውን ለመግለጽ ሁሉም አማኝ እንዲቆይና አንድ ላይ እንዲበላ ያደርጋሉ።  7. ሰዎች ሁለት እውነቶችን እንዲያስታውሱ በማድረግ ፈጽሙ። አንደኛ፥ የጌታ እራት የጌታቸውን በቅርብ መመለስ እንደሚያመለክት አስታውሷቸው። ሁለተኛ፥ የጌታን እራት መውሰድ የጌታን ሞት የማወጃ አንዱ መንገድ እንደሆነ አስታውሷቸው። ነገር ግን እንደ ኢየሱስ ተከታዮች የጌታን ሞት እግዚአብሔር በአስቀመጠን ኅብረተሰብ ውስጥም ማወጅ ይገባናል። የጌታን እራት ስንበላ፥ ምሳሌ አድርገን የምናስተላልፈው ሁሉም የምንደሰትባቸው በረከቶች ከኢየሱስ ሞት የሚመጡ ናቸው ማለታችን ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ስንወጣ ይህን ተመሳሳይ እውነት ለማያምኑ ሰዎች ለማካፈል ፈቃደኞች መሆን ይገባናል፡፡ ያም ኢየሱስ ስለ እነርሱ መሞቱን በማመን እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ወደፈለገው ወደ ዘላለመአዊ በረከት ሊያደርሳቸው እንደሚችል ነው፡፡ ማጠቃለያ  ዛሬ ዛሬ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ጌታ እራት አስፈላጊነት ትኩረት (አጽንዖት) አይሰጡበትም። አብዛኛዎቹ ምእመናን ስላልተጠመቁ፥ የጌታን እራት አይወስዱም። የጌታን እራት መውሰድ የሚችሉት አባላትም ቢሆኑ የዚህ ክፍል አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ይወጣሉ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር የሚቃረን ነው። ምናልባትም በአምልኮ እጅግ አስፈላጊው ነገር ሊሆን የሚችለው የጌታን እራት መውሰድ ነው። እንዲያውም፥ ሁሉም አማኞች የጌታን እራት እንዲወስዱ ታዝዘዋል። ምናልባት ብዙዎቻችን በእምነታችን የምንታገልበት ምክንያት ብዙ ጊዜ የጌታን እራት ስለማንወስድ የጌታ እራት የሚያስተምረንን እውነት ስለምንረሳ ነው። በእምነታችን ሚዛን የምናጣበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ሕግጋትን እንደ ሕይወታችን መሠረት ለማድረግ በመመለስ ወይም በተአምራቶች ላይ ወይም በጊዜያዊ የምድራዊ በረከቶች ላይ በማተኮር የጌታ እራት ወደ ዘላለማዊ የበረከት እሴት የሚወስደን እርግጠኛው የኢየሱስ ሞት መሆኑን እንዲያስታውሰን ስለማንፈቅድለት ነው። የጌታ እራት በአንተ ሕይወት ውስጥ አስፈላጊ ነውን? ካልሆነ፥ ለምን አልሆነም? የኢየሱስ ሞት ምን ያህል ነገር እንዳደረገልህ ረስተሃልን? ወይስ ምናልባት እንደ ግል መድኀኒትህ አድርገህ ኢየሱስን ማመን እንዳለብህ አልተገነዘብክም? ካልተገነዘብክ ኢየሱስን አሁን እመን። ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ጋር በደስታ የኢየሱስን ሞት ሥርዓት (የጌታን እራት) እንድታከብር ምን ማድረግ እንዳለብህ ከቤተ ክርስቲያንህ ሽማግሌዎች ጋር ተነጋገር።  ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ጌታን እራት ለሚያስፈጽሙ መሪዎች አስተያየት Read More »

ክርስቲያኖች በጌታ እራት ላይ ያላቸው የግንዛቤ ልዩነት

This entry is part 177 of 8 in the series የጌታ እራት

ሁሉም ክርስቲያኖች የጌታ እራት አስፈላጊና ኢየሱስን በመታዘዝ ሊያደርጉት የሚገባ መሆኑን ያምናሉ። አብዛኞቹም «የጌታ እራት ምን ማለት ነው?» ለሚለው ጥያቄ የተሰጡትን አሥር ነጥቦች ያምኑባቸዋል። ይሁን እንጂ የጌታን እራት መረዳታችንና ልምምዳችን በቤተ እምነቶች መካከል ይለያያል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ይህ ልዩነት አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ወደሚጎዳ መከፋፈል ያደርሳል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ስለ ጌታ እራት ምን እንደሚያስተምር መረዳት አስፈላጊ ቢሆንም፥ ከእኛ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ማቃለል ግን ተገቢ አይደለም። እንዲያውም፥ ይህ አመለካከት «ሳይገባን» የጌታን እራት ወደ መብላት ይመራናል። በሚያለያየን ላይ ከማትኮር ይልቅ፥ በሚያስማማን ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል።  በክርስቲያን ቤተ እምነቶች መካከል ያሉ ዋና ዋናዎቹ ልዩነቶች ምንድን ናቸው?  ሥርዓቱ ሲካሄድ እንጀራውና ወይኑ ምን ይሆናል በሚለው ላይ የክርስቲያኖች እምነት ይለያያል። ኢየሱስ «ይህ ሥጋዬ ነው» እንዲሁም «ይህ ደሜ ነው» ሲል ምን ማለቱ ነበር?  በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እንደምናየው ሰዎች ይህን የኢየሱስ ዓረፍተ ነገር በአራት የተለያዩ መንገዶች ተረድተውታል።  ሀ) የሮማ ካቶሊክና የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ይህን የኢየሱስ ዓረፍተ ነገር የሚረዱት ቃል በቃል ነው። ስለዚህ ካህኑ ሲጸልይ ቁራሹ እንጀራና ወይኑ በተአምር ወደ ትክክለኛው የኢየሱስ ሥጋና ደም ይለወጣል ብለው ያስተምራሉ። ኅብስቱ የክርስቶስ ሥጋ ይሆናል። ወይኑም የኢየሱስ ደም ይሆናል። ይህን በሚበሉበት በእያንዳንዱ ወቅት ኢየሱስ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ይሞታል ማለት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች የጌታን እራት ማን መስጠት እንዳለበት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉትም ከዚህ የተነሣ ነው። ሕብስቱና ፅዋው የተዘጋጁባቸው ነገሮች እንዲለወጡ ለማድረግ ሥልጣን ያለው ካህኑ ብቻ ነው። ስለዚህም ነው የጌታን እራት መውሰድ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኛል የሚሉት። ምእመኑ በግሉ ሊያደርግ ስለሚገባው ዝግጅት ትኩረት አይሰጡም። ይልቁንም፥ ተቀባዩ ባይዘጋጅም እንኳን ሥጋውና ደሙ እማኙን የመለወጥ ኀይል አላቸው ይላሉ። የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ክርስቲያኖች የጌታን እራት በመውሰድ ጉዳይ ላይ የሚለያዩት ኅብስቱ እርሾ የሌለበት ይሁን ወይም እርሾ ያለበት ይሁን በሚለው ነው።  ለ) የመካነ ኢየሱስና የሉተራን ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ዓረፍተ ነገር የሚረዱት ቃል በቃል ነው። ይሁን እንጂ፥ አካላዊ ነገሩ እንደሚለወጥ ወይም ሁልጊዜ ሥጋ ወደሙ ሲበላ፥ ኢየሱስ ዴጋግሞ እንደሚሞት አያምኑም። ከዚህ ይልቅ፥ የኢየሱስ ሥጋና ደም ኅብስትና ወይኑን ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ይከብበዋል ይላሉ። በሆነ መንገድ የኢየሱስ ሥጋ ኅብስቱ ውስጥ ሲኖር፥ ደሙም ከወይኑ ውስጥ ይገኛል። ክርስቲያኖች ይህን ነገር ሲበሉ መንፈሳዊ ዝግጅት ካደረጉ በተለየ መንገድ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያደርጋሉ። ኃጢአታቸው ይቅር ይባላል፥ በኢየሱስ ላይ ያላቸው እምነትም እንደገና ይረጋገጣል። በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን በተገቢው መንገድ እንዲሰጥ የቄሱ መገኘት አስፈላጊ ነው።  ሐ) የፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን፥ በኢትዮጵያ ውስጥ የመካነ ኢየሱስ ክፍል የሆኑት (ቤቴል ሲኖድ) ሲሆኑ፥ የኢየሱስን ዓረፍተ ነገር በተለየ መንገድ ነው የሚረዱት። ሕብስቱና ፅዋው የተዘጋጀበት ነገር ትክክለኛው የኢየሱስ ሥጋና ደም መሆኑን አያምኑም። ሥጋና ደሙም በሆነ መንገድ ከሕብስቱና ፅዋው ጋር ይቀላቀላሉ ብለው አያምኑም። ይልቁንም፥ ክርስቲያኖች ሕብስቱንና ፅዋውን ሲወስዱ፥ ኢየሱስ በመንፈስ ሊገናኛቸው እንደሚመጣ ያስተምራሉ። መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ጋር እንዲተባበሩ ይረዳቸዋል። ተቀባዮቹ መንፈሳዊ ዝግጅት ካደረጉ፥ መንፈሳዊ እድገት እንዲያገኙ መንፈስ ቅዱስ ይረዳቸዋል። ከሌሉቹ ጊዜያት በበለጠ፥ በኢየሱስ ሞት ምክንያት ይቅር እንደተባሉ መንፈስ ቅዱስ ያረጋግጥላቸዋል። በእግዚአብሔር ፍቅር እንደታተሙ ሲያስገነዝባቸው፥ የኪዳኑ ቃል ወራሾች እንደመሆናቸውም መጠን፥ ኢየሱስ ቃል የገባላቸውንም በረከቶች ይቀበላሉ። አማኞችም ኢየሱስን ለመከተል በድጋሚ ራሳቸውን ሲያቀርቡ እንደ አዳኛቸውና ጌታቸው ሊታዘዙት ቃል ይገባሉ።  መ) በኢትዮጵያ አብዛኞቹ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት (ለምሳሌ፡- ቃለ ሕይወት የሕይወት ብርሃን፥ ሙሉ ወንጌል) የኢየሱስ ቃላት በምሳሌያዊነት መወሰድ እንዳለባቸው ያምናሉ። የተቆረሰው ኅብስት የተወጋውን የኢየሱስን አካል ይወክላል። ወይኑም የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም ይወክላል። ኢየሱስም እነዚህ ምሳሌዎችና ሥርዓት የሰጠን ስለ እኛ ብሎ መሞቱን እንድናስታውስ ነው። እምነታችን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ባደረገው ነገር ላይ መሆኑን እንድናስታውስ የሚረዳን የማስተማሪያ መሣሪያ ነው። እራሳችንን እንድንመረምርና ኢየሱስን ለመከተል እንደገና ራሳችንን እንድንሰጥ ያግዘናል። የጌታ እራት ሥርዓት ለእኛ ጥቅም እንዲሆን ካስፈለገ፥ መንፈሳዊ ዝግጅት ያስፈልገናል።  እንግዲህ ትክክለኛው አመለካከት የቱ ነው? ሁሉም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በጌታ እራት ከሮም ካቶሊክና ከኦርቶዶክስ እመለካከት ጋር በተለያየ ምክንያቶች አይስማሙም። አንደኛ፥ በየጊዜው የጌታ እራት ሥርዓት ሲከበር ኢየሱስ ለሕዝቡ ኃጢአት እንደገና ይሞታል በሚለው አይስማሙም። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት «ተፈጸመ» ብሎ ጮኾአል (ዮሐ 19፡30)። ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው መንገድ በቋሚነት ተከፍቷል። ኢየሱስ እንደገና ለመሥዋዕትነት መሞት የለበትም። ዕብ 9፡5-28 እና 10፡10-14 ኢየሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሞቱን ያስተምራል። ሁለተኛ፥ ሥጋ ወደሙ መብላት ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ አዲስ ኪዳን አያስተምርም። ይልቁንም ተቀባዩ ኢየሱስ በምትኩ እንደሞተ በግል እምነት ሊኖረው እንደሚያስፈልግ ያስተምራል። እያንዳንዱ ሰውም ለኃጢአቱ ይቅርታ ለማግኘትና በሕይወቱ እግዚአብሔርን እያስከበረ መኖር እንዲችል ለውጥ እንዲኖረው እግዚአብሔርን ሊጠይቅ እንደሚያስፈልግ ያስተምራል። ሦስተኛ፥ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት እንጀራውና ወይኑ ሥጋውና ደሙ መሆኑን ተናግሮ ነበር። «ይህ እንጀራና ወይን በቅርቡ (የወደፊት ጊዜ) ደኅንነታችሁን የሚያመጣ ሥጋዩና ደሜ ይሆናል» ብሎ አልተናገረም። የኢየሱስን ቃል እንዳለ መውሰድ ቢያስፈልግ ኖሮ ማለት የነበረበት ያንን ነበር። በምትኩ ግን፥ «ይህ ሥጋዩ ነው» እና «ይህ ደሜ ነው» (የአሁን ጊዜ) የሚሉትን ቃላት ነበር የተጠቀመው። ይህም ቃሉን እንዳለ ሳይሆን፥ በምሳሌያዊነቱ እንድንረዳው ያስገነዝበናል። አራተኛ፥ የኢየሱስን አባባል ቃል በቃል መረዳቱ የኢየሱስ ቃላት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካለው ከእግዚአብሔር ግልጽ ትእዛዛት ጋር እንዲቃረኑ ያደርጋል። በዚያም አይሁዶች ደም በጭራሽ እንዳይጠጡ ተነግሮአቸው ነበር (ዘሌዋ. 17፡10-16)።  የኢየሱስን አነጋገር አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደሚረዱት ከመረዳት ይልቅ፥ («ይህ ደሜ ነው») የሚለውን የኢየሱስን ቃል በምሳሌያዊነት መረዳት ይሻላል። ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ መንፈሳዊ እውነትን ለማስረዳት ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። እራሱን እንደ «ሕይወት እንጀራ»፥ ወይም «በር»፥ ወይም «ወይን»፥ ወይም «እረኛ» ሰይሟል (ዮሐ 6፡35፥ 19፡7-9፥ 10፡14 እና 6፡1)። እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ፥ የመንፈሳዊ ሕይወታችን ምንጭ፥ ለፍላጎታችን ሁሉ የሚጠነቀቅ እርሱ እንደሆነ እና ወደ እርሱ ስንቀርብ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚመግበን የሚያስገነዝቡ ናቸው። በተመሳሳይ መንገድ ኢየሱስ በጌታ እራት ጊዜ፥ ከፋሲካ ሥርዓት መብል ሁለት ተፈጥሮአዊ ነገሮችን ይኸውም ያልቦካ ኅብስት እና በዋንጫ ያለ ወይንን በተምሳሌትነት በመጠቀም ሞቱ ለአዲስ ኪዳን የቱን ያህል ማዕከላዊ እንደሆነ አስረድቷል። በእንጀራውና በወይኑ የተመሰለው ስለ እኛ መሞቱ፥ ከእግዚአብሔር ለምንቀበላቸው መንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ መሠረት ነው። ያለን ነገር ሁሉ ተጠብቆ በመንፈሳዊ ጤንነታችን የምንቆየው፥ ያለን ሁሉ በኢየሱስ ሞት ምክንያት ያገኘነው የእግዚአብሔር ጸጋ ውጤት እንደሆነ እውቀን ስንኖር ነው።  2. ኅብስቱና ወይኑን መቀበል ምን ሊፈጸም እንደሚችል ባለው አሳብ ላይ ክርስቲያኖች የተለያየ አቋም አላቸው። ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች የጌታን እራት ወሳጁ ከኢየሱስ ጋር ያለው መንፈሳዊ ግንኙነት የተስተካከለ ባይሆንም እንኳን፥ እንጀራውንና ወይኑን መውሰዱ ይቅርታ ያመጣለታል ብለው ያምናሉ። ነገር ግን 1ኛ ቆሮ. 11፡27-38 ግልጽ እንደሚያደርገው እንጀራውንና ወይኑን መብላት ብቻ ምንም ለውጥ አያመጣም። ራስ ወዳድ እና የተከፋፈሉት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አዘውትረው ይመገቡ ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይኖሩ ነበር። ይህ ምንባብ እንደሚያስተምረው፥ የጌታ እራት ትርጉም እንዲኖረው ልባችን መስተካከል ይኖርበታል። ሕይወታችንም እናምናለን ብለን የምንናገረውን ማንጸባረቅ አለበት። በአግባቡ ስንዘጋጅ፥ ይህን የመታሰቢያ እና የማወጂያ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን እውን (ግልጽ) ላማድረግና ወደ እርሱን ወደመምሰል እንድናድግ ለመርዳት ይጠቀምበታል።  3. የጌታን እራት ሥርዓት ማን መፈጸም እንዳለበትም ክርስቲያኖች አይስማሙም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጌታን እራት ለመስጠት ማን ሥልጣን እንዳለው መመሪያዎች የሉም። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፥ ኦርቶዶክስ እና መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት ለማካሄድ የሚያተኩሩት በቄሱ ሥልጣን ላይ ነው። ነገር ግን አዲስ ኪዳን ሁላችንም ስእግዚአብሔር ፊት ካህናት የመሆን መብት እንዳለን ይናገራል (1ኛ ጴጥ. 2፡9)። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ኢየሱስን የሚከተሉ ሁሉም አማኞች የጌታን እራት ለማካሄድ እንደተፈቀደላቸው የሚያስተምሩት ከዚህ በመነሣት ነው። በመሠረቱ የጌታ እራት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄደው በቤተ ክርስቲያን በተመረጡ ሰዎች ነው። እነዚህም መሪዎች በ1ኛ ጢሞ.

ክርስቲያኖች በጌታ እራት ላይ ያላቸው የግንዛቤ ልዩነት Read More »

አላግባብ የጌታን እራት ስለመውሰድ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች

This entry is part 176 of 8 in the series የጌታ እራት

በ1ኛ ቆሮ.11፡27-32 ጳውሎስ አማኞች «ሳይገባቸው» የጌታን እራት እንዳይወስዱ በጥብቅ ያስጠነቅቃል። «ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።» አላገባብ የጌታን እራት መውሰድ የሕመምን ቅጣት ወይም ሞትን በአማኞች ላይ ሊያመጣ እንደሚችል ተናግሯል። ጳውሎስ ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት አስፈላጊ ነው። በአማርኛ ‘ሳይገባው’ የሚለው ቃል ሦስት ነገሮችን ማለት ሊሆን ይችላል። አንደኛ፥ «አንድን ነገር አለመረዳት» ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንዳንዶች በስህተት እንደሚያስቡት ጳውሎስ በዚህ ክፍል የሚናገረው የጌታ እራትን ምሳሌነት ስለመረዳት ነው። የጌታ እራትን መውሰድ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው። ጳውሎስ ግን በደንብ ምንነቱን ሳይረዱ የጌታን እራት መውሰድ ፍርድን ያስከትላል ማለቱ አይደለም። ሁለተኛ፥ ወደ አንድ ቦታ ውስጥ ሳይገባ እንደ ማለት ሊሆን ይችላል። እንግዲህ ጳውሎስ እንደሚለው ችግሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ይሁን ወይም አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ሳይሆኑ የጌታን እራት መብላቱ ላይ አይደለም። ጳውሎስ ይህንንም ማለቱ አይደለም። ይልቁንም፥ ሦስተኛውን የዚህን ቃል ትርጉም ነው የወሰደው። ጳውሎስ ያለው የጌታን ሥጋና ደም ለመብላት ብቁ ሳንሆን ወይም የጌታን ሞት ምንነት በማያንፀባርቅ (በማይገልፅ) መልኩ ላለመውሰድ ጥንቃቄ የማድረግ ብቃትን ነው።  እንግዲህ ክርስቲያኖች ሳይገባቸው የጌታን እራት የሚበሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? በመሠረቱ ጳውሎስ እንደሚለው በማናቸውም ጊዜ የምንኖረው ኑሮ ስለ ኢየሱስ ሥጋና ደም ምሳሌነት ያለንን እምነት ካላንፀባረቀ፥ ሳይገባን የጌታን እራት ወስደናል ማለት ነው። ስቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በአማኞች መካክል መከፋፈል ነበረ። በሃብታምና በድኃ መካከል እኩልነት አልነበረም። ይህም የጌታን እራት በሚወስዱበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ይታይ ነበር። (ማስታወሻ፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ የጌታን እራት መውሰድ ትንሽ የእንጀራ (የኅብስት) ቁራሽ መብላት ወይም ትንሽ ወይን መጠጣት ብቻ አልነበረም። ይልቁንም፥ በአምልኮው ፕሮግራም መጨረሻ ላይ ከየቤታቸው ምግብ ያመጡት አማኞች ሁሉ ማዕዱን በአንድነት ይመገቡ ነበር። ይህንንም ምግብ ‘የፍቅር ግብዣ’ ብለውታል። በማዕዱ መጨረሻም፥ ቅዱስ ቁርባንን በጋራ ይወስዳሉ። የጌታ እራት በኢየሱስ ሞት የተመሠረተ የፍቅርና የአንድነት መግለጫ ነበር።) የዚህ ፍቅር መጓደል ስቆሮንቶስ አማኛች መካከል አንድነት የፈጠረውን የኢየሱስን ሞት እውነት የመስደብ ያህል ነበር። ምንም ዓይነት ዘር፥ ፆታ፥ ብሔር ወይም ነገድ ወይም ምንም ዓይነት ቤተ እምነት ይሁን ሰዎች ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንደሞተላቸው ካመኑ፥ የኢየሱስ አካል ክፍል ናቸው (1ኛ ቆሮ. 12፡18፥ ገላ. 3፡26-29)። ሁላችንም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞችና የዘላለም ሞት የሚገባን ነን። እያንዳንዳችን የዳንነው በተመሳሳይ መንገድ እምነታችንን ስለ እኛ ኃጢአት መሥዋዕት በሆነው በኢየሱስ ላይ ስማድረግ ነው። ሀብታምም ሆንን ድኃ፥ የተማርን ሆንን ያልተማርን፥ በከተማ የምንኖር ሆንን በገጠር፥ አማራ እንሁን ወይም ኦርሞ፥ ጥቁር ሆንን ነጭ፥ ወንድ ወይም ሴት፥ እኛ ሁላችንም አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ሁላችንም የአንዱ የኢየሱስ አካል ክፍል ነን። በቤተ ክርስቲያን አማኞች መካከል ያልተፈቱ ችግሮች እያሉ አማኞች የጌታን እራት ከወሰዱ፥ አማኞቹ ከቅዱስ ቁርባን ዓላማዎች ዋንኛውን አላሟሉም ማለት ነው። ይህም ዓላማ አማኞች ሁሉ በክርስቶስ ሞት አንድ መሆናችውን የሚገልጽ ነው። ስለዚህ ግብዝነት የእግዚአብሔርን ፍርድ አመጣባቸው። ይህም በዚህ ዘመን ለምንኖር ክርስቲያኖች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። በቤተ ክርስቲያናችንና በቤተ እምነቶች አብዛኛውን ጊዜ መከፋፈል አለ። በዚህ የፍቅር ጉድለት የጌታን እራት ስንወስድ የምናምነውን መዘበቻ እንደማድረግ ይቆጠራል። የጌታን እራት ያለ አግባብ በመውሰድ ከእግዚአብሔር ቅጣት ሥር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ይገባናል።  ደግሞ በሕይወታችን ምን ጊዜም ያልተናዘዝንበት የማያቋርጥ ኃጢአት ካለ፥ የጌታን እራት ሳይገባን ወሰድን ማለት ነው። በዝሙት ብንኖር እና ይህንንም የማንናዘዝና አኗኗራችንን የማንቀይር ከሆነ፥ የጌታን እራት ስንበላ የጌታን እራት ንቀነው፥ በማይገባ መልኩ እየወሰድን ነን። ወይም ገንዘብ ሰርቀን ካልተናዘዝንና ካልመለስን፥ ወይንም እግዚአብሔር አንድ ነገር እንድናደርግ ጠይቆን እምቢ ካልን የጌታን እራት ሳይገባን በላን ማለት ነው።  ጳውሎስ እምነታችንን የሚቃረኑ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ መኖር አለመኖራቸውን እራሳችንን እንድንመረምር የሚናገርበት ምክንያት ኃጢአታችንን ላንናዘዝና በመካከላችን ያለውን መከፋፈል ሳናስወግድ የጌታን እራት የምንወስድ ከሆነ፥ የጌታን ሞት ትርጉም ስለሚቃወም ነው። በሕይወታችን ጌታችን ኢየሱስ የሚፈልገውን ነገር ለመፈጸም ግድ የለንም እያልን ነው። ሕይወታችንን እርሱ በሚፈልገው መንገድ ሳይሆን፥ በእኛ ምርጫ እንመራለን ማለታችንም ነው። ሞቱን ስላስከተለው ኃጢአታችንም ቢሆን ምንም ግድ እንደሌለን መግለፃችን ነው። ኢየሱስ የሞተው እኛ ለፈጻምነው የዝሙት፥ የስርቆት፥ የሐሜት፥ የውሸት፥ የትዕቢት፥ የጥላቻ ኃጢአት ነው። ኃጢአታችንን የመናዘዝ ምንም ምልክት ሳናሳይ፥ በዚህ መንገድ ከኖርንና ለመለወጥም ፍላጎት ካላሳየን ለሞት ያደረሰው ኃጢአታችን መሆኑ ግድ አይለንም ማለት ነው።  ነገር ግን የሰዎችን ኃጢአት ከመጠን በላይ ላለማጋነን መጠንቀቅ አለብን። ጳውሎስ ይህን ትምህርት የሰጠው፥ ከጌታ እራት ሰዎችን ለማራቅ ሳይሆን፥ ትርጉም ባለው መልኩ በአንድነት (በኅብረት) ማክበ ር እንዲችሉና ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙ ለማበረታታት ነበር። ይልቁንም፥ በ1ኛ ዮሐ 1፡9 ያለውን ተስፋ ለአማኞች ማስታወስ አለብን። የጌታን እራት ሥርዓት ከመጀመራችን በፊት ባልተናዘዙበት ኃጢአት እራሳቸውን እንዲፈትኑ ለሕዝቡ ዕድል መስጠት አለብን። የኢየሱስ ደም እንዲያነፃቸው እነዚህን ኃጢአቶች እንዲናዘዙ መበረታታት ይገባቸዋል። እውነተኛ ኑዛዜ ሕይወታችንን እንዲለውጥ በዝሙት መኖርን ማቆም፥ የሰረቅነውን መመለስ፥ ወይንም ኅብረት ካቋረጥንበት ጋር ዕርቅ መሥርተን የምንኖርበት ቁርጠኝነት መሆኑን መገንዘብ ይገባቸዋል። ትክክለኛ ኑዛዜ ካለ፥ ግለሰቡ የጌታን እራት እንዲወስድ ሊፈቀድለት ይገባል። ይህ የኑዛዜ ጊዜ ከፍርድ ይልቅ፥ ይቅርታንና ከኀጢአት መንጻትን ወደሚያመጣው የኢየሱስን ሞትና ትንሣኤ ወደሚያደንቅ የመታደስ ሕይወት ሊመራ ይገባል።  ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

አላግባብ የጌታን እራት ስለመውሰድ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች Read More »

ቅዱስ ቁርባን (የጌታ እራት) ማለት ምን ማለት ነው?

This entry is part 175 of 8 in the series የጌታ እራት

የጌታን እራት ምንነት አለመገንዘብና ለህተት በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር ቀላል ነው። ሰቀላሉ የጌታ እራት ኢየሱስ በአቀደው መሠረት እንዲክበር፥ በዘመናት ሁሉ ውስጥ ለሚኖሩት ተከታዮቹ ኢየሱስ ለምን እንደሰጠ ልንገነዘብ ያስፈልጋል። ኢየሱስ የጌታን እራት አከባበር ሥርዓት ሲጀምር ምን ማለቱ እንደሆነ ከመግለፃችን በፊት፥ ቅዱስ ቁርባን ምን እንዳልሆነ በማብራራት እንጀምር።  ሀ. የጌታ እራት የሚከተሉትን ነገሮች ማለት አይደለም  1 የጌታን እራት መቀበል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ ሁሉም አይደለም። ኢየሱስን እንደ ግል መድኃኒታቸው አድርገው ያልተቀበሉ፥ ወይም በኢየሱስ ፊት የቅድስና ሕይወትን ለመኖር ፈቃደኛ ያልሆኑ የጌታን እራት መውሰድ የለባቸውም። ጳውሎስ እንዳለው ሕይወታቸውን በወንጌል ትምህርት ለመምራት የማይፈልጉ ሥጋውንና ደሙን ለመውሰድ ብቁ አይደሉም (1ኛ ቆሮ. 11፡27)።  2. የጌታ እራት ምስጢራዊ ስብሰባ እንዲሆን የታቀደ አይደለም። ምስጢራዊ የሆነ ነገር እንደምንሠራ ዓይነት ስሮችንና መስኮቶችን የምንዘጋበት ምክንያት የለም። ጳውሎስ እንደሚለው የጌታን እራት መውሰድ ወንጌልን የማብሰሪያ መንገድ ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡26)። ወንጌልን ለማያምኑ ሰዎች ወይም ላልገባቸው ልጆቻችን የምናውጅበት አንዱ መንገድ የጌታን እራት በምንወስድበትና ትርጉሙንም በምንገልጽበት ጊዜ እንዲገኙ (እንዲያዩ) ስመፍቀድ ነው።  3. የጌታ እራት እጅግ ቅዱሳን ሆነው ለሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ ኢየሱስ የመጀመሪያውን የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ሲፈጽም ከደቀ መዛሙርት ማናቸውም በጣም ቅዱስ አልነበሩም። ጴጥሮስና ሌሎችም ደቀ መዛሙርት ወዲያውኑ ኢየሱስን ክደውታል። ስለሆነም ኢየሱስ ተከታዮቹ የጌታን እራት ለመካፈል የሚያሟሉት የተለየ የቅድስና ቅድመ–ሁኔታን ትኩረቱ አላደረገም።  4. የጌታ እራት የአንድ ቤተ እምነት የአባልነት ምልክት እንዲሆን የሚሰጥ አይደለም። ይልቁንም፥ ለሁሉም እውነተኛ አማኞች የተሰጠ መብት ነው እንጂ። የጌታ እራት አማኞችን ከመከፋፈል ይልቅ፥ የሁሉም አማኞች የጋራ መሠረት መሆን አለበት። ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው፥ ሁሉም አማኛች ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱ የደኅንነታቸው መንገድ እንደሆነ ማመናቸውን ለሕዝብ በግልጽ (በይፋ) የሚመሰክሩበት ነው።  5. የጌታ እራት ለኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ የቅዳሴ ሥርዓት አይደለም። አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ሰው ከመሞቱ በፊት የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ከተካፈለ (ሥጋ-ወደሙ ከወሰደ) ይድናል ብለው የሚያስተምሩ አሉ። ነገር ግን አዲስ ኪዳን በግልጽ እንደሚያስተምረው የሚያድነን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን የግል እምነት እንጂ ቅዱስ ቁርባንን መውሰድ አይደለም (ኤፌ. 2፡8)።  6. የጌታን እራት ሥርዓት ስንፈጽም ማተኮር የሚገባን በኢየሱስ አካላዊ ሕመም ላይ አይደለም። አዎን፥ ኢየሱስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እጅግ በጣም ተሰቃይቷል። የመስቀል ላይ ሞት የጥንት ሰዎች የፈጠሩት አሰቃቂ ሞት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ አካላዊ ሕመም ላይ ትኩረት አያደርግም። ይልቁንም ትኩረቱ እግዚአብሔር አባት ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሣ ልጁ ኢየሱስ ስለ ኃጢአታችን መሥዋዕት እንዲሆን በመላኩ ላይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የሚያተኩረው ለኃጢአታችን ሊሞት በመጣውና የእግዚአብሔር ልጆች ባደረገን በኢየሱስ ጸጋና ምህረት ላይ ነው። እኛም የጌታን እራት ስንወስድ ያ ሞት የሚሰጠንን ጥቅም ሁሉ እንደገና ማስታወስ እንድንችል ነው።  7. ዋናው ስሜት የምስጋና እንጂ የኀዘን አይደለም። በሕይወታችን ስላለው ኃጢአት ለረጅም ጊዜ እንድናለቅስና እንድንፀፀት የሚያደርጉን አንዳንድ የፕሮግራም መሪዎች አሉ። ሕይወታችንን መመርመርና ኃጢአታችንንም መናዘዝ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ትኩረቱ በነፃነታችን እንጂ በኃጢአታችን ላይ አይደለም። የጌታን እራት ስንወስድ ልባችን ከእግዚአብሔርና ከኢየሱስ ፍቅር፥ ምህረትና ጸጋ የተነሣ በምሥጋና መሞላት ይገባዋል። ጊዜው የአምልኮና የውዳሴ ጊዜ ነው።  ለ. የጌታ እራት ምን ማለት እንደሆነ  ኢየሱስ የጌታን እራት ለምን ሰጠን? የጌታ እራት ምሳሌያዊ ሥርዓተ ቅዳሴ ነው። ውጪያዊው እንጀራውን የመብላትና ወይኑን የመጠጣት ተግባር ጥልቅ መንፈሳዊ እውነታዎችን ያመለክታሉ። የጌታን እራት ስንወስድ ተስናከብር/ ብዙ አስፈላጊ እውነቶችን ምሳሌያዊ እያደረግን ነው።  1. ኢየሱስ የቅዱስ ቁርባንን ሥርዓት የሰጠን የምንቀበላቸው በረከቶች ሁሉ ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመሞቱ ምክንያት የተገኙ መሆናቸውን ዘወትር እንዲያሳስበን ነው። በኑሮ ስመባከን ወይም በአንዳንድ አስተምህሮዎች በመሳት፥ የኢየሱስን ሞትና ምንነቱን እንዘነጋለን። የጌታን እራት ስንወስድ መዘንጋት የሌለብን የመንፈሳዊ ሕይወታችን መሠረት የሚያርፈው በምትካችን በሞተው ኢየሱስ ላይ መሆኑን ነው።  2. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የጌታን እራት የሰጠው በመታሰቢያነት እንዲያገለግል ነው። ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እንዲካፈሉ የሚጠበቅባቸው ወይም የሚፈቀድላቸው ሥርዐት አይደለም። ኢየሱስ የጌታን እራት ያስጀመረው ትክክለኛ ላልሆነ ዓላማ ይከተለው በነበረው ሕዝብ ሳይሆን፥ በቅርብ በተከተሉት ደቀ መዛሙርት ነበር። ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቢሆንም እንኳን ይሁዳ የጌታን እራት እንዲወስድ አልተፈቀደለትም። የወንጌል ታሪክ እንደሚያመለክተው የጌታ እራት ሥርዓት የተካሄደው የአስቆሮቱ ይሁዳ ከወጣ በኋላ ነበር። ይህ የሚያሳስበው የጌታን እራት መውሰድ የሚኖርባቸው ክርስቲያን ነን ብለው የሚናገሩ ላይሆኑ፥ ለኢየሱስ በመገዛትና በመታዘዝ የሚኖሩ መሆናቸውን ነው።  3. የጌታን እራት መውሰድ የኢየሱስን ሞት ምሳሌያዊነት ያመለከታል፡፡ እንጀራው ሲቆረስ፥ በመስቀል ላይ የሞተውን የኢየሱስን አካል በምሳሌያዊነት መቆረስ ያመለክታል። ጽዋው ሲቀዳም ኢየሱስ ደሙን ለእኛ እንዴት እንዳፈሰሰ ያመለክታል። የዚህ በዓል ምሳሌያዊነት ኢየሱስ ለእኛ መሞቱን ለሁሉም ሰዎች ማስተማር ነው።  4. የጌታን እራት ስንወስድ ወደ ኋላ መለስ ብለን የምንመለከተው፤ በምትካችን፥ የደኅንነታችንና የመንፈሳዊ በረከታችንም መሠረት ወደሆነው ወደ ኢየሱስ የምትክነት ሞት ነው። በመካከላችን ካለው የትንሣኤ ጌታ ጋር ዘላቂ ግንኙነት እንዳለን ስንገልጽ፥ የምናተኩረው በአሁኑ ሕይወታችን ላይ ነው። ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ወደፊት መመለስ ደግሞ በጉጉት ስንጠባበቅ፥ በማናየው መልኩ አዳኛችንን አንቀርበውም። ነገር ግን ፊት ለፊት ከእርሱ ጋር ኅብረት እናደርጋለን።  5. የጌታን እራት መውሰዳችን ምን እንደምናምን የሚገልጥ ነው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ ሁላችን መሞቱን ማመናችን በቤተ ክርስቲያን ባሉት ሁሉ ፊት የምንፈጽመው ግልጽ ምስክርነታችን ነው። ሌሎች ብዙ ኃይማኖቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ቤተሰቦቻችንና ጓደኛቻችን ኢየሱስ ስለ እነርሱ ብሎ በመስቀል ላይ መሞቱን ላያምኑ ይችላሉ። ነገር ግን እኛ የጌታ እራትን ልንወስድ ለደኅንነታችን ኢየሱስን በግላችን እንዳመንን መናገራችን ነው። ጳውሎስ ይህን «ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና» ይለዋል (1ኛ ቆሮ. 11፡26)። የጌታን እራት ስንወስድ፥ ምሳሌ የምናደርገው ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤታችንና ወደ ጎረቤቶቻችን ተመልሰን ክርስቶስ ባስቀመጠን ቦታ ሁሉ፥ ክርስቶስ ያደረገልንን በግልጽ መመስከርን ነው።  6. የጌታን እራት ስንበላ በግል ስኢየሱስ ሞት ውጤት ተካፋይ እንደሆንን ማሳየታችን ነው። እርሱ የሞተው ለዓለም ብቻ አይደለም። ይልቁንም፥ ኢየሱስ ለእኔ ኃጢአት ሞቷል እያልን ነው። በእርሱ ሞት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የማድረግ ዕድል አግኝቻለሁ። የጌታን እራት ስንወስድ፥ እኛ ኃጢአተኛና የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍርድ የሚገባን መሆኑን እያረጋገጥን ነው። ነገር ግን ስንበላ የዘላለም ሕይወትን ሊያመጣልን የሚችለው በእኛ ምትክ የሞተው ኢየሱስ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ መሆን አለበት። እርሱ ሲሞት፥ በኃጢአት ምክንያት ያለብኝን የሞት እዳ ከፍሎልኛል። አሁን እኔ በኢየሱስ ሞት ምህረት አግኝቼአለሁ፥ ድኛለሁ፥ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኛለሁ፥ በመንግሥተ ሰማይም የዘላለማዊነት ተስፋ ተገብቶልኛል።  7 ከሌሎች አማኞች ጋር በአንድነት መብላታችን በክርስቶስ አንድ አካል የመሆናችን ምሳሌ ነው። እኛ አንድ አካል፥ ያውም የክርስቶስ አካል ነን (1ኛ ቆሮ. 19፡7፥ 12፡12-13)። በአስተምህሮዎች ጉዳይ ላይ ጥቃቅን ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ። አንዳንዴም ላንስማማ እንችላለን። ነገር ግን የምንስማማበት አንድ ነገር አለ። የኢየሱስ በእኛ ምትክ መሞት በእምነታችን ውስጥ እጅግ አስፈላጊው እውነት ነው። በኢየሱስ ሞትም ያለን እምነት አንድ አካል እንድንሆን ያጣምረናል። የጌታን እራት ስንወስድ፥ የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት አንድ ሊያደርገን እንደሚገባ ኢየሱስ እየነገረን ነው። ልክ የመጀመሪዎቹ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ሁላቸውም ከእንጀራውና ከወይኑ እንዲበሉ እንደነገራቸው፥ እንዲሁ ሁሉም እውነተኛ አማኞች ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን አስወግደው ትኩረታቸውን አስፈላጊ በሆነው ጉዳይ ላይ እንዲያደርጉ ያስፈልጋል። እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ክብር የጎደለን ኃጢአተኞች እንደሆንን ማስታወስ አለብን። ነገር ግን እንደ አማኞች ይቅርታ ተደርጎልን እነዚያ ሰደሎች አይታሰቡብንም። ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ይህ ሁሉ የሆነው በእኛ ፈንታ በመስቀል ላይ ከሞተው ከኢየሱስ የተነሣ ነው።  8. የጌታ እራት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ መሞቱን የሚያንጸባርቅ እምነት እንዳለን በሚያሳይ መልኩ እየኖርን መሆኑን ለማረጋገጥ ሕይወታችንን ለመመርመር ተደጋጋሚ ዕድል ይሰጠናል። ጳውሎስ እንዳለው፥ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት፥ በዋጋ ገዝቶናል (1ኛ ቆሮ. 6፡20፥ 7፡23)። በሕይወታችን ላይ የፈለግነውን ለማድረግ ምንም መብት የለንም። ይልቁንም፥ የምንኖረው

ቅዱስ ቁርባን (የጌታ እራት) ማለት ምን ማለት ነው? Read More »

የጌታ እራት ሥረ መሠረት

This entry is part 174 of 8 in the series የጌታ እራት

ሁላችንም በሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማስታወስ እየታገልን ነው። የትኩረት አቅጣጫችን አስፈላጊነታቸው ዝቅተኛ ግምት በሚሰጣቸው እውነቶች ላይ ሲሆን፥ በጣም አስፈላጊ የሆነውን እንዘነጋለን። ለምሳሌ፥ በተአምራት ላይ በይበልጥ ለማተኮር ስኢየሱስ ላይ ያለን ትኩረት ይቀንሳል። ወይም ዓይናችንን በጥሩ ቤት ላይ፥ ብዙ ገንዘብ ስማግኘት ላይ፥ ወይም በትምህርት ላይ፥ ወዘተ… እናደርጋለን። ያለፈውን ታሪክና እግዚአብሔር ቀደም ሲል ያደረገልንን ለማስታወስ እንዳንችል በኑሮ ውጥረት ውስጥ ገብተን እንገኛለን። እንደዚያ እንደሆንን እግዚአብሔር ያውቃል፤ በመሆኑም እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕዝቡ ለእነርሱ ያደረገላቸውን እንዲያስታውሱ እንዴት ልዩ ቀን ወይም ልዩ ስፍራ እንደመሠረተላቸው እናነባለን። በኢያሱ 4፡15-24 ኢያሱ እንዴት 12 ድንጋዮችን ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ወስዶ የመታሰቢያ ሐውልት አድርጎ እንዳቆማቸው እናነባለን። በታሪክ ውስጥ የአይሁድ ሰዎች ሐውልቱን ሲመለከቱ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራና እንዴት ዮርዳኖስን አሻግሮ ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዳመጣቸው ያስታውሳቸዋል። ደግሞም የመታሰቢያ በዓላትም ነበሩ። ለምሳሌ፥ በማደሪያው ድንኳን ክብረ በዓል ጊዜ አይሁዶች ምቹ ቤቶቻቸውን እየተዉ፥ ለአንድ ሳምንት በጊዜያዊ ትንንሽ ድንኳኖች ይኖሩ ነበር። ይህንም ያደርጉ የነበሩት፥ በሙሴ ዘመን 40 ዓመት በምድረ በዳ በድንኳን የኖሩበትን ጊዜ ላለመርሳት ነው።  እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የብሉይ ኪዳን የመታሰቢያ ክብረ በዓላት አንዱ የፋሲካ በዓል ነበር። በዘጸአት 12 እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ በግብፅ ላይ የመጨረሻ መቅሰፍት (ቁጣ) በማምጣት የግብፃውያን ስኩር (የመጀመሪያ) ወንድ ልጆችን ሁሉ እንዴት እንደ ገደለ እናነባለን። ይህ መልአክ፥ አይሁድ ሁለት ነገሮችን ካደረጉ የእነርሱን በኩር ልጆች እንደማይገድል እግዚአብሔር ነግሮአቸዋል። አንደኛ፥ እርሾን ሁሉ ከቤታቸው አስወግደው እርሾ የሌለበትን ቂጣ ብቻ መብላት አለባቸው። በአዲስ ኪዳን እንደተነገረን ይህ እርሾን ከቤት የማራቅ ድርጊት ኃጢአትን ክሕይወታቸው ማራቃቸውን የሚያመለክት ምሳሌ ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡6–8)።  ሁለተኛ፥ አጥፊው መልእክ ከመምጣቱ በፊት በነበረው ሌሊት ጠቦትን እርደው፥ የተለየ ቅጠል ወስደው ሰጠቦቱ ደም ከነከሩ በኋላ ባበራቸው መቃንና በጉበኑ ላይ መቀባት ነበረባቸው። ከዚያም ጠበቱን ጠብሰው ቤተሰብ በሙሉ በአንድነት መብላት ነበረባቸው። በዚያች ሌሊት አጥፊው መልአክ በእስራኤላውያን መንደር ሲያልፍ፥ ሁሉም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽመው፥ ደሙንም በበሮቻቸው ላይ ቀብተው ስለነበር፥ መልአኩ የበኩር ልጆቻቸውን አልገደለም። ነገር ግን ደሙ በሌለበት ቤት የነበሩትን በኩር ወንድ ልጆች መልአኩ ገድሎአል። ይህ ኃይለኛ ቅጣት ነበር በስተመጨረሻ ፈርኦን አይሁድን እንዲለቅና ነፃ እንዲያወጣቸው ያስገደደው። እግዚአብሔርም ይህን የነፃነት ቀን በዘመናቸው ሁሉ እንዲያከብሩት ነግሮአቸዋል። ክብረ በዓሉም እግዚአብሔር ምን እንዳደረገላቸው ለማስታወስ ይረዳቸዋል። እግዚአብሔር የበኩር ወንድ ልጆቻቸውን አለመግደሉ ብቻ ሳይሆን፥ ሕዝቡንም ከባርነት ነፃ አውጥቶአቸዋል።  በአዲስ ኪዳን እንደተነገረን ኢየሱስ የፋሲካው በዓል ምሳሌነት ፍጻሜ ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡7)። እርሱ ደሙ በመቃኑና በጉበኑ ላይ እንደተቀባው እንደታረደው «ጠቦት» ዓይነት ነው። ኢየሱስ ደሙን በመስቀል ላይ በማፍሰሱና እኛም ስናምን ደሙ በእኛ ላይ ስለሚታይ እግዚአብሔር ያድነናል። እርሱ ከኃጢአት ባርነት ነፃ ያወጣናል። አሁን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ ነን።  ኢየሱስ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትን እንደ አዲስ የፋሲካ ክብረ በዓል ሰጥቶናል። ይህ ክብረ በዓልም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያደረገልንን በማስታወስና ከኃጢአት ነፃነታችንንና ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት በእርሱ ሞት ምክንያት መሆኑን ለሁሉም በግልጽ የምናውጅበት ነው። ዓላማው ኢየሱስ በመስቀል ላይ በምን ዓይነት ሥቃይ ውስጥ እንዳለፈ እንድናስታውስ እኛን መርዳት አይደለም። ይልቁንም፥ ትኩረቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞቱ በምናገኘው ጥቅም ላይ ነው። ማንኛውም እኛ ያገኘነው መንፈሳዊ በረከት የመጣው ኢየሱስ በመስቀል ላይ በፈፀመው ተግባር ነው።  ለእግዚአብሔር የሚያስፈልገው የመታሰቢያ ቀን ብቻ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ኅብረት ማድረግን ይወዳል። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ለዚህ ኅብረት ምሳሌው የእግዚአብሔር መገኘት ባለበት ሥፍራ አንድን ነገር በመብላት ነው። በዘጸአት 24፡9-11 እንዴት ሽማግሌዎች በሲና ተራራ ላይ በእግዚአብሔር ፊት እንደበሉ እናነባለን። እስራኤላውያን አስራታቸውን ወይም የድነት (የደኅንነት) መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ሲያመጡ፥ በእግዚአብሔር ሕልውና ፊት ይበሉ ነበር (ዘሌዋ. 11፡17-18፤ ዘዳግ. 14፡23፥ 26፤ 27፡7)። ኢየሱስ ተመልሶ ሊመጣ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደገና ከእግዚአብሔር ጋር የኅብረትን ምግብ እንደሚመገብ ተነግሮናል (ራእይ 19፡9)፡፡ የጌታ እራትም የኅብረት መግለጫ መብል ነው፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን ሆኖ ሁላችንም እንደ ክርስቶስ አካልነት (ማቴ. 18፡20)፥ ለኢየሱስ ክብር እንበላለን። ይህ ከኢየሱስ ጋርና እርስ በርሳችን ያለን ኅብረት የተቻለው በኢየሱስ ሞት ለተካፈለው የኃጢአታችን እዳ ነው። ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የጌታ እራት ሥረ መሠረት Read More »

ስለ ጌታ እራት ኢየሱስ የሰጣቸውን በርካታ መመሪያዎች መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

This entry is part 173 of 8 in the series የጌታ እራት

አንደኛ፥ የተሰጠው እንደ ትእዛዝ ነው። ሁሉም የእርሱ ተከታዮች የጌታን እራት ዘወትር እንዲወስዱ ተናግሯል። «ስትፈልጉ፥ የጌታን እራት ውሰዱ» አላለም። ወይም «ከፍተኛ መንፈሳዊነት ሲሰማችሁ፥ የጌታን ራት ብሉ» ወይም «ከተጠመቃችሁ በኋላ፥ የጌታን እራት ውሰዱ» ወይም «በቂ ጊዜ ሲኖራችሁ፥ የጌታን እራት ውሰዱ» አላለም። ይልቁንም፡ ሁሉም የእርሱ ተከታዮች የጌታን እራት በቋሚነት እንዲወስዱ ነው ያዘዘው። ክርስቲያኖች የጌታን እራት አዘውትረው ካልወሰዱ፥ የኢየሱስን ትእዛዝ እየጣሱ ነው። በብዙ መልኩ ይህ የሚያረጋግጠው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥ አንድ የሆነ ችግር እንዳለ ነው። ወይንም መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን እራት ሥርዓት ማክበር አስፈላጊያቸው እንደሆነ የሚያስተምረውን ትምህርት አልሰሙም ማለት ነው።  ሁለተኛ፥ የጌታን እራት የምንወስድበት ዋነኛው ዐላማ «ለመታሰቢያነት» ነው። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ የምናደርገው ሁሉ፥ እርሱን እንደሚያሳስብ ኢየሱስ ለተከታዮቹ በተደጋጋሚ ተናግሯል። ይህ ምሳሌያዊ ሥርዓት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት መሠረቱ ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ መሞቱን ማመናችን መሆኑን እንድናስታውስ የሚረዳን ነው።  ሦስተኛ፥ የጌታ እራት መሠረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለውን አዲሱን ኪዳን (ስምምነት) መጀመሩን መገንዘብ ነው። ወደፊት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡት በእስራኤልና በእግዚአብሔር መካከል በሲና ተራራ ላይ በተደረገው በአሮጌው ኪዳን መሠረት አይደለም። ይልቁንም ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነው።  ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ስለ ጌታ እራት ኢየሱስ የሰጣቸውን በርካታ መመሪያዎች መገንዘብ አስፈላጊ ነው። Read More »

የጌታ እራት ሥርዓት እንዴት እንደ ተጀመረ?

This entry is part 172 of 8 in the series የጌታ እራት

ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ ላይ የጌታን እራት ሥርዓት አስጀመረ። የጌታ እራት እንዴት እንደ ተጀመረ በአዲስ ኪዳን ሰአራት ዋና ዋና ምንባቦች ውስጥ ተጽፎ ይገኛል። ማቴ. 26፡17 30፤ ማር. 14፡17-26፤ ሉቃስ 22፡14-20 እና በ1ኛ ቆሮ. 1፡23-34። (እነዚህን ምንባቦች በዝግታ ለማንበብ ጊዜ ውሰድ።  ከመሰቀሉ በፊት በነበረችው ሌሊት ኢየሱስ የአይሁድን የቂጣ በዓል (ፋሲካን) ሊያከብር ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተሰበሰበ። የፋሲካ በዓል እግዚአብሔር በአስገራሚ ማዳኑ አይሁዶችን ከግብፅ ባርነት ነፃ ያወጣበትን ቀን በማሰብ የሚከበር ነበር (ዘጸአት 12፡1-30)። ኢየሱስም አዲስ ፋሲካ ሊጀምር የተቃረበበት ወቅት ነበር። በማግስቱ በመስቀል ላይ ሲሞት ለአይሁዶች ብቻ ሳይሆን፥ ለሚያምኑበት ሕዝብ ሁሉ ከኃጢአት ነፃ መሆንን አምጥቷል።  ደቀ መዛሙርት በዙሪያው እንዳሉ ኢየሱስ የጌታን እራት ሥርዓት ወሰነ። የእርሱ ተከታዮችም የጌታን እራት ሥርዓት በዘመናት ሁሉ እንዲፈጽሙ ተናግሯል። ይህ ሥርዓት ኢየሱስ ዘላለማዊ መንግሥቱን ለመመሥረት እስከሚመለስበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል። በፋሲካ በዓል መጨረሻም ኢየሱስ እንጀራን ያዘ። ሲቆርሰውም ይህ ስለ እነርሱ የሚቆረሰው አካሉ መሆኑን ነገራቸው። እንጀራውንም ሲበሉ ኢየሱስን ማስታወስ አለባቸው። ከዚያም ኢየሱስ ወይን ያለበትን ዋንጫ አንስቶ ደቀ መዛሙርት እንዲጠጡት ሰጣቸው። ወይኑም  ለኃጢአታቸው ይቅርታ የሚፈሰው ደሙ መሆኑን ነገራቸው። ደቀ መዛሙርት መጠጣት የነበረባቸው ኢየሱስን በማስታወስ ነው። በቀጣዩ ቀን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት ሥጋው ተቆረሰ፤ ደሙም ፈሰሰ። እርሱ ስለ እያንዳንዳችን ሲል ሞተ። የሥጋው መቆረስና የደሙ መፍሰስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የተደረገ የኃጢአት ይቅርታ ማስገኛ ኪዳን መሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል። ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የጌታ እራት ሥርዓት እንዴት እንደ ተጀመረ? Read More »

«ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት»

This entry is part 171 of 8 in the series የጌታ እራት

ተመስገን ለአንድ ዓመት ያህል አማኝ ነበር። ለሃያ ዓመታት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። ነገር ግን ተመስገን ግልጽ የወንጌል ስብከትን ሲሰማ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ መወለድ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ እንደማያደርገው ተገንዝቧል። ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ ማመን ፈለገ። ከስድስት ወራት ትምህርት በኋላ ተመስገን ተጠሙቀ። በተጠመቀበት ዕለት ከሌሎች አማኞች ጋር የጌታን እራት (ቅዱስ ቁርባን) ለመቀበል ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ። እየበላም ሳለ የአሁኑ የጌታ እራት ሥርዓት ቀድሞ ከነበረው የጌታ እራት ሥርዓት ጋር ትልቅ ልዩነት እንዳለው ተገነዘበ። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጌታን እራት መቀበል ማለትም ቅዱስ ቁርባንን መውሰድ፥ የአምልኮ ሥርዓት ማዕከል ሲሆን፥ አፈጻጸሙም በየሳምንቱ በሚደረግ ውስብስብ ሥርዐት ነበር። ሰዎቹም የጌታን እራት በሚወስዱበት ጊዜ የክርስቶስን ሥጋና ደም እንደተቀበሉ አድርገው ያምናሉ። የጌታን እራት መብላቱ የኃጢአት ስርየት እንደሚያመጣላቸው ያምናሉ፥ ጠንካራ ስሜትም ይፈጥርላቸዋል። ነገር ግን አሁን ተመስገን በሚሳተፍበት ቤተ ክርስቲያን በተነጻጻሪነት ሲታይ የጌታ እራት ብዙም ትኩረት የማይሰጠው የአምልኮ ክፍል ነው። የሚካሄደውም በወር አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹም የማኅበረ ምዕመናኑ ግማሽ ያህሉ ብቻ ነበሩ። ምንም እንኳን ሥርዓቱ ሞገስ ያለው ቢሆንም፥ አማኞቹ የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚበሉ አይመስልም። ነገር ግን ሥርዓቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሠራላቸውን ሥራ እንዲያስታውሱ ረድቷቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም የኢየሱስን ሞት ምሳሌያዊነት ብቻ የሚያመለክት መሆኑን ታስተምር ነበር።  ተመስገን ግራ ተጋባ። «የጌታ እራት ዓላማው ምንድን ነው»? እንጀራው (ሕብስቱና ወይኑ ትክክለኛው የኢየሱስ ደምና አካል ነው ተብሎ ሲወሰድ የተለየ ተአምራዊ ነገር ይፈጸማል ወይ? መቀበሉስ የኃጢአትን ይቅርታ ያሰጣል ወይ? ሁሉም ክርስቲያኖች የጌታን እራት መቀበል (መብላት) አለባቸው ወይስ የቤተ ክርስቲያን አባላት ብቻ? የሥርዓቱ ጊዜስ የሐዘን ነው? ወይስ የደስታ?» በማለት ተገረመ።  ብዙነሽ ያደገችው በወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ነበር። የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኗም ምእመናን በወር አንድ ጊዜ ከእሁድ የአምልኮ ሥርዓት በኋላ በመቅረት የጌታን እራት መቀበል/መውሰድ ልምዳቸው ነበር። ሥጋና ደሙን ከመውሰድ በፊት ያለው ጊዜም እጅግ የተከበረ ነበር። መሪዎችም በኢየሱስ ስቃይ ላይ ትኩረት በመስጠት ይናገራሉ። ሰዎችም ስለ ኃጢአታቸው እንዲያለቅሱ ያበረታታሉ። ብዙነሽም አብዛኛውን ጊዜ የጌታ እራት ዓላማው ምንድን ነው በማለት ትገረም ነበር።  አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች የጌታን እራት ቢወስዱም እንኳ፥ እንደ ተመስገንና ብዙነሽ ያሉ ሰዎች ሥርዓቱ ምን እንደሆነ አይገባቸውም። ይህች ጽሑፍ የጌታ እራት ትርጉም ምን መሆኑንና ሁሉም የእርሱ ተከታዮች በዚህ እንዲሳተፉበት ኢየሱስ ለምን እንደፈለገ ትገልፃለች። ስጽሑፍዋ መጨረሻም ክርስቲያኖች ስለ ጌታ እራት ዓላማ ያላቸውን የተለያየ አመለካከት እንቃኛለን።  በአዲስ ኪዳን ዘመን የጌታ እራት ለመጀመሪያቱ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ማዕከላዊ ነገር ነበር። በየሳምንቱ ምእመናን ሲሰበሰቡ አምልኮአቸውን በልዩ ምግብ ይደመድሙ ነበር (የሐዋ. 2፡42-46፤ 20፡7)። በኋላም አማኞች ይህን ምግብ «የፍቅር ግብዣ» ብለው ጠሩት፥ ምክንያቱም ይህ ግብዣ ለእያንዳንዳቸው ያላቸውን ፍቅርና በተለይም ስለ እነርሱ ለሞተው ጌታ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጽ ነበር። የኅብረተሰቡ ግብዣ ማዕከላዊው ክፍልም በእነርሱ ምትክ የሞተውን ጌታ ለማሰብ የሚደረግ ሕብስትን መቁረስና ወይንን መጠጣት ነበር። በተጨማሪም፥ ይህ ሥርዐት «የጌታ ማዕድ» (1ኛ ቆሮ. 10፡20፥ «ቁርባን»፥ «የበረከት ጽዋ» (1ኛ ቆሮ. 10፡16) እና «እንጀራን መቁረስ» (የሐዋ. 2፡42) ተብሏል። ከቤተ ክርስቲያን ጅማሬ አንስቶ የጌታን እራት መቀበል ለቤተ ክርስቲያን ዋንኛ የአምልኮ ተግባሯ ነበር። ጥምቀት እያንዳንዱ አማኝ ለክርስቶስ ያለውን ታማኝነት የአማኞችን ኅብረት እንደተቀላቀለ የሚያሳይበት መንገድ ነበር። ከትንሣኤው ጌታ ጋር ያላቸውን ቀጣይ ኅብረት ለማሳየት፥ አዘውትረው የጌታን እራት ይወስዱ ነበር። ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

«ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት» Read More »