የማቴዎስ ወንጌል ጥናት መምሪያ እና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
ጌታ ኢየሱስ በተራራው ላይ የሰጠውን ታላቅ ትምህርት ሲያበቃ፣ ወደ ተራራው ግርጌ ወረደ። አሁን ደግሞ በትምህርቱ የገለጠውን መለኮታዊ ሥልጣን በተግባር የሚያሳይበት ምዕራፍ ተጀመረ። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ስምንት መጀመሪያ ላይ የምናገኛቸው ሦስት ተአምራት፣ ጌታ ኢየሱስ በበሽታ ላይ፣ በርቀት ላይና በሰው ልጅ ድካም ላይ ያለውን ፍጹም ሥልጣን የሚገልጡ ናቸው።
የሥጋና የነፍስ ንጽሕና፦ የለምጻሙ መፈወስ
ከመጀመሪያዎቹ ተአምራት አንዱ የአንድ ለምጻም መፈወስ ነው። በዚያ ዘመን ለምጽ ያለበት ሰው ከማኅበረሰቡ የተገለለና “ርኩስ” ተብሎ የሚጠራ ነበር። ይህ ሰው ግን በታላቅ እምነት ወደ ጌታ ቀርቦ “ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ሰገደለት። ጌታ ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው። ይህ ድርጊት እጅግ አስገራሚ ነው፤ ምክንያቱም በሕጉ መሠረት ለምጻምን የነካ ሰው ርኩስ ይሆናል። ነገር ግን የቅድስና ምንጭ የሆነው ጌታ ሲነካው ርኩሰቱ ወደ ጌታ አልተላለፈም፣ ይልቁንም የጌታ ንጽሕና ወደ ለምጻሙ ተላለፈና ወዲያውኑ ነጻ ሆነ። ይህም የሚያሳየን ጌታ እኛን ከኃጢአትና ከውርደት ለማንጻት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን ነው።
ታላቅ እምነትና ቃሉ ያለው ሥልጣን፦ የመቶ አለቃው ጸሎት
ሁለተኛው ተአምር ደግሞ በአንድ አሕዛብ በሆነ የመቶ አለቃ ቤት ውስጥ ተፈጸመ። ይህ መቶ አለቃ ስለ ታመመው ብላቴናው ወደ ጌታ መጣ። ጌታ “መጥቼ እፈውሰዋለሁ” ሲለው፣ የመቶ አለቃው ግን “ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ ሥር ልትገባ አይገባኝም፤ ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል” በማለት መለሰ። ይህ ሰው በሥልጣን ሥር ያለ ወታደር በመሆኑ፣ ጌታ በአካል ሳይገኝ በቃሉ ብቻ በሽታን ማዘዝ እንደሚችል ተረድቷል። ጌታም በእምነቱ ተደንቆ “በእስራኤል እንኳን እንዲህ ያለ ታላቅ እምነት አላገኘሁም” አለ። ጌታ ቃሉን ሲናገር በዚያው ሰዓት ብላቴናው ተፈወሰ። እምነት ማለት እግዚአብሔር በአካል ባለበት ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ ባለበት ቃል ላይ መታመን መሆኑን እንማራለን።
የድካማችን ተካፋይ፦ የጴጥሮስ አማት መፈወስና የትንቢቱ ፍጻሜ ጌታ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ የጴጥሮስ አማት በንዳድ ታማ ተኝታ አገኛት። እጅዋን ዳሰሳትና ንዳዱ ለቀቃት። ወዲያውኑም ተነስታ አገለገለቻቸው። ይህ ተአምር ጌታ በግል ቤታችንና በቅርብ ቤተሰባችን ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችንም እንደሚመለከት ያሳያል። በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አወጣ፣ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
ይህ ሁሉ የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስ “እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ” በማለት የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። ጌታ እኛን የሚፈውሰው ከሩቅ ሆኖ ሳይሆን፣ የእኛን ሕመም በመካፈልና በመሸከም ነው። የሰው ልጅ መከራና ሕመም ሁሉ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ውስጥ መፍትሔ አግኝቷል።
ለሕይወታችን የሚሆን ትምህርት
እነዚህ ተአምራት ዛሬም ለእኛ መልእክት አላቸው። በኃጢአት ለምጽ ተመቶ ለተሰበረ ሰው፣ ጌታ “እወዳለሁ ንጻ” የሚል አዳኝ ነው። በጭንቀት ውስጥ ሆኖ መፍትሔ ለሚፈልግ ሰው፣ ጌታ “በቃሉ ብቻ” ሁኔታዎችን የሚቀይር ባለሥልጣን ነው። በቤት ውስጥ በበሽታ ለሚሰቃዩት ደግሞ፣ ጌታ ወደ ቤታቸው ገብቶ እጃቸውን የሚዳስስ አጽናኝ ነው። ትልቁ ቁም ነገር ጌታን በታላቅ እምነት መጠጋትና በቃሉ ሥልጣን ላይ መታመን ነው።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ለምጻሙ “ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” ማለቱ ስለ ኢየሱስ ሥልጣን ያለውን እምነት እንዴት ይገልጻል?
👉ኢየሱስ ለምጻሙን በመንካቱ በአይሁድ ሃይማኖታዊ ንጽሕና ሕግ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ አመጣ?
👉የመቶ አለቃው “በቃለህ ብቻ ተናገር” ማለቱ ለምን ከእስራኤል እምነት በላይ ተባለ?
👉”ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ” የሚለው ቃል የወንጌልን ዓለም አቀፋዊነት እንዴት ያሳያል?
👉የጴጥሮስ አማት ከተፈወሰች በኋላ ወዲያውኑ ማገልገሏ ስለ ፈውስ ዓላማ ምን ያስተምራል?
👉ማቴዎስ በነዚህ ፈውሶች የኢሳይያስን ትንቢት የጠቀሰው ለምንድን ነው?
👉አጋንንት ያደሩባቸውን በቃሉ ብቻ ማስወጣቱ ስለ መለኮታዊ ሥልጣኑ ምን ይነግረናል?
👉የመቶ አለቃው ለሠራተኛው ያለው ርኅራኄ ምን ያስተምረናል?
👉ኢየሱስ ለምጻሙን ለካህን እንዲታይ ማዘዙ ሕጉን ለማክበሩ ማስረጃ ነውን?
👉ዛሬ እኛ “በቃለህ ብቻ ተናገር” የሚል እምነት አለን?
