የሕይወት እንጀራ

ትንቢተ አሞጽ

አሞጽ 1-9

የውይይት ጥያቄ፥ አሞጽ 1-9 አንብብ። ሀ) አሞጽ ትንቢት የተናገረባቸውን ሕዝቦች ዘርዝር። ኃጢአታቸው ምን ነበር? ለ) አሞጽ እስራኤልን የከሰሰባቸውን የተለያዩ ወንጀሎች ዘርዝር። ሐ) አሞጽ እስራኤል በኃጢአትዋ ምክንያት ምን ይደርስባታል አለ? መ) አሞጽ ስለ እስራኤል የወደፊት ሁኔታ የተናገራቸው የተስፋ ቃሎች ምን ነበሩ? 1. አሞጽ በአሕዛብ ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (አሞጽ 1፡1-2፡16)  አሞጽ ማንኛውም ጥሩ ሰባኪ እንደሚያደርገው እግዚአብሔር ያገለግለው ዘንድ ከላከው ሕዝብ በአንድ ጊዜ ራሱን ማግለል አልፈለገም። ስለዚህ መልእክቱን በአሕዛብ ላይ ስለሚመጡ ፍርዶች በመናገር ጀመረ። በዚህ መልእክት በእስራኤል ዙሪያ የሚገኙ ሕዝቦች በሙሉ ተጠቅሰዋል። ይኼኛው የትንቢተ አሞጽ ክፍል ሦስት ዐበይት ክፍሎች አሉት። በቅድሚያ አሞጽ ከአሕዛብ ይጀምራል። ይህ መልእክት አሕዛብን ይጠሉ በነበሩት በእስራኤላውያን ዘንድ በታላቅ ደስታ ተቀባይነት ማግኘቱ አይጠረጠርም። አሞጽ የአሕዛብን ኃጢአት ለማስተዋወቅ የሚጠቀምበት ልዩ አባባል ነበረው «ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት… ኃጢአት» የሚለው። የዚህ አባባል ትርጉም፥ ሕዝቡ የፈጸሟአቸው በርካታ ኃጢአቶች ቢኖሩም፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የሚፈርደው ግን በተለይ ስለ ሠሩትና ሊጠቀሱ ስለሚችሉት ሦስት ወይም አራት ኃጢአቶች ነው ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ የተጠቀሱት ስድስት የአሕዛብ አገሮች ደማስቆ (ሶርያ)፥ ጋዛ (ፍልስጥኤም)፥ ጢሮስ፥ ኤዶም፥ አሞንና ሞዓብ ነበሩ። በሁለተኛ ደረጃ፥ አሞጽ በደቡብ የይሁዳ መንግሥት ላይ ትንቢት ተናገረ። እስራኤላውያን ይህንንም ቢሆን የተቀበሉት በታላቅ ደስታ ሳይሆን አይቀርም። እስራኤልና ይሁዳ የቆዩ ጠላቶች ነበሩ። ምናልባትም እስራኤላውያን በሚያመልኩት ሐሰተኛ የጣዖት አምልኮ ምክንያት የይሁዳ ሰዎች የበታች አድርገው ይመለከቷቸው ስለነበር ይጠሏቸው ነበር። በሦስተኛ ደረጃ፥ አሞጽ በእስራኤል ላይ ትንቢት መናገር ጀመረ። ጻድቃንንና ድሆችን በመሸጣቸው ለተጨቆኑትም ፍትሕን በመከልከላቸው ሕዝቡን ይወቅሳቸዋል። እግዚአብሔር በቅርቡ እንደሚፈርድባቸው ይነግራቸዋል። አሞጽ በቀረው የመጽሐፉ ክፍል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በተናገረው ቃል ላይ ያተኩራል።  2. አሞጽ በእስራኤል ላይ የተናገረው የፍርድ ትንቢት (አሞጽ 3-6) እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ነበሩ፤ ከማንኛውም ሕዝብ የበለጠ እግዚአብሔር ሞገስ ሰጥቶአቸው ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ነበራቸው፤ የእግዚአብሔር ሕግጋት ነበራቸው፤ እግዚአብሔር ያስጠነቅቋቸው ዘንድ ነቢያትን ልኮላቸው ነበር። እነዚህን ንቀው እግዚአብሔርን ተዉ። ኅበራዊ ፍትሕ-አልበኝነታቸው ለእግዚአብሔር ሕግጋት የነበራቸውን ዝቅተኛ አመለካከት የሚያሳይ ነበር። ዳሩ ግን ብዙ በረከትና ልዩ መብት ሁልጊዜ ተጨማሪ ኃላፊነትን ይዞ የሚመጣ ነው። እስራኤል በነበራት እውቀት መሠረት ስላልኖረች እግዚአብሔር ታላቅ ፍርድ እንደሚያመጣባት ተናገረ። እግዚአብሔር ማንኛውም ጥፋት የሚመጣው በአጋጣሚ እንዳልሆነ፥ ነገር ግን የፍርድና የማስጠንቀቂያ ምልክት ሆኖ ከእርሱ ዘንድ እንደሚመጣ ያስታውሳቸዋል። ከዚህ ቀደም የገጠማቸው ድርቅ፥ መቅሠፍትና ወረርሽኝ ሁሉ እስራኤላውያን እንዲደነግጡና በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው እንዲድኑ የሚያነሣሣ የእግዚአብሔር ምሕረት ምልክት ነበር። ዳሩ ግን ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። ስለዚህ ዖሶች በመንጠቆ እንደሚጠመዱ፥ እስራኤሳውያንም እየተማረኩ ይሄዱ ነበር። እነርሱ በረከት ይዞ ይመጣል ብለው የሚያስቡት «የጌታ ቀን» የቅጣትና የጥፋት ቀን ሆነባቸው። ወደ እግዚአብሔር በንስሐ ከተመለሱ ግን እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው ተናግሮ ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ) ታላቅ በረከት ከፍ ያለ ኃላፊነትን ይዞ የመምጣቱ መወመሪያ ዛሬም ለእኛ ተመሳሳይ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? ለ) የእግዚአብሔርን ቃል የማወቅና የደኅንነትን እንዲሁም የሥጋዊ ሀብትን በረከት በቀላሉ ማየት እንደሌለብን ይህ ነገር ማስጠንቀቂያ ሊሆነን የሚገባው እንዴት ነው?  3. አሞጽ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣ ፍርድ አምስት ራእዮችን አየ (አሞጽ 7-9)  አሞጽ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ጥፋት የተናገረው በቀጥተኛ ትንቢት ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም፥ እግዚአብሔር የሚመጣውን ጥፋት የሚያሳዩ አምስት ራእዮችን ሰጥቶታል። ሀ. የምድሪቱን ሰብል የሚያጠፉ አንበጦች ራእይ፤ እዚህ አንበጦች በምድሪቱ ውስጥ የሚገኙትን ሰብሎች በሙሉ ያጠፉ ነበር። ነገር ግን በአሞጽ ጸሎት ምክንያት በእስራኤል ላይ ሊመጣ የነበረው ይህ ፍርድ ታገደ።  ለ. ምድርን የበላ እሳት ራእይ፡- ይህ እሳት ምድርን ሁሉ የሚያጠፋ ነበር፡- እንደገና አሞጽ ጸለየና እግዚአብሔር ይህንን ፍርድ እንደማይልክ ተናገረ።  ሐ. በቱንቢ የተሠራ ቅጽር ራእይ፡- ቱንቢ የሕንጻ ሥራ በሚሠራበት ጊዜ የግንቡ ማዕዘን በትክክል መጠበቁን ለማረጋገጥ የሚያገለግል መሣሪያ ነው። ይህ ቱንቢ እስራኤልን እንደ ቅጥር በመቁጠር ትክክለኛ መሆኗን ወይም አለመሆኗን ለማረጋገጥ በእግዚአብሔር መመዘኛ መሠረት እስራኤል በመንፈሳዊ በማኅበራዊና በሥነ-ምግባራዊ ይዘቷ ትክክለኛ ስላልነበረች እግዚአብሔር እስራኤልን በማጥፋት ሊቀጣት ወስኖ ነበር። ዳሩ ግን በዚህ ጊዜ ፍርዱ አልተገለጠም።  አሞጽ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ሲናገር፥ አሜስያስ የተባለው ካህን ስለዚህ ጉዳይ ለንጉሡ ገለጸ። እንዲሁም አሞጽን ተቃወመና በእስራኤል ወይም የጣዖት አምልኮ ማዕከል በነበረችው በቤቴል ላይ ትንቢት እንዳይናገር አዘዘው። አሞጽ ግን ትንቢት ከመናገር በቀር ሌላ ምርጫ እንደሌለው በመግለጽ መልስ ሰጠው። ነቢይ መሆንን አልመረጠም ነበር። ተራ ገበሬ ነበር። እግዚአብሔር ግን ለነቢይት እንደመረጠውና እንደላከው፥ በመሆኑም በእግዚአብሔር ስም መናገር እንዳለበት ገለጠ። አሞጽ አሜስያስን የእስራኤል ሁሉ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም፥ ስለሚመጣው ጦርነትና የእስራኤል መማረክ ግልጽ የሆነ ትንቢት ተናገረ። መ. የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ራእይ፡- አሞጽ የተለቀመ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበትን ዕንቅብ ተመለከተ። ልክ እንደዚሁ እስራኤል በአሦራውያን ተማርከው ሊሄዱ ተዘጋጅተው ነበር። የፍርድ ጊዜ ደርሶ ነበር። በምርኮአቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል የማወቅ ራብ በምድሪቱ ሁሉ ይስፋፋል፤ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ለማግኘት ወደየስፍራው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም።  ሠ. ጌታ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ የታየበት ራእይ፡- እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ፍርድን እንደሚያመጣ ሆኖ ተገልጾአል። ሕዝቡ እግዚአብሔር ሰላምና በረከት እንደሚሰጣቸው በሚያስቡበት በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔር የአምልኮ ስፍራዎችንና የእስራኤልን ከተሞች እንደሚያጠፋ ተናገረ።  4. አሞጽ ስለ ወደፊቱ የእስራኤል ተሐድሶ ተነበየ (አሞጽ 9፡11-15) ትንቢተ አሞጽ የሚጠቃለለው በመጽናናትና በተስፋ ቃል ነው። እግዚአብሔር የእስራኤልን ቅሬታ ወደ ምድሪቱ በመመለስ እንደሚመሠርታቸው ተናግሯል። ከዳዊት ዘር በሆነው (የወደቀችው የዳዊት ድንኳን ተብሎ በተጠራው) ንጉሥ በመሢሑ በኢየሱስ ይገዛሉ። የጠላታቸውን ምድር እንደገና በመውረስ፥ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ውስጥ የተሰጡትን በረከተች ያጭዳሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በትንቢተ አሞጽ ውስጥ የተመለከትሃቸውና የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች ሊያውቁአቸው የሚገቡ አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? ለ) ይህንን መጽሐፍና እነዚህን ትምህርቶች ለቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዐቅድ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

አሞጽ 1-9 Read More »

የትንቢተ አሞጽ ዓላማ እና ዐበይት የሥነ መለኮት ትምሕርቶች

የትንቢተ አሞጽ ዓላማ  ሰላምና ብልጽግና ሁልጊዜ በአንድ ሕዝብም ሆነ ግለሰብ ላይ የሚወርዱ የእግዚአብሔር በረከት ምልክቶች አይደሉም። አሞጽ በእስራኤል ላይ ትንቢት እንዲናገር በተጠራ ጊዜ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች የፖለቲካ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ብልጽግና ያገኙበት ወቅት ነበር። በመካከላቸው ታላቅ ኃጢአት ስለነበር፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ነበር። ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔር አሞጽን ከይሁዳ ወደ እስራኤል በመላክ የፍርድ ጊዜ መድረሱን እንዲነግራቸው አደረገ። ምድሪቱ በጣዖት አምልኮና በማኅበራዊ ኃጢአቶች ተሞልታ ነበር። መሪዎች ፍትሕ በጎደለው መንገድ ይገዙና ኃይላቸውን ለግል ጥቅም ማግኛ ይገለገሉበት ነበር። ነጋዴዎች እየጨመረ የሚሄድ ሀብታቸውን ድሆችን ያላግባባ ለመበዝበዝ፣ ባሪያ ለማድረግና ያላቸውን ጥቂት ሀብትና ንብረት ለመንጠቅ ይጠቀሙበት ነበር። እስራኤላውያን ለምን እንደሚፈረድባቸውና ወደ ምርኮ እንደሚወሰዱ እግዚአብሔር በአሞጽ በኩል የተናገረው በዚህ ወቅት ነበር። ንስሐ እንዲገቡ ለመናቸው ጠየቃቸው። እነርሱ ግን አሞጽን ወደ ይሁዳ አባርረው የኃጢአት መንገዶቻቸውን ስለቀጠሉ፥ የተሰጣቸውን ዕድል አልተጠቀሙም። በጥቂት ዓመታት ውስጥ አሦር ሰላምና ብልጽግናን ከእስራኤል ላይ ቀማች። በ722 ዓ.ዓ. ብሔረ እስራኤል ተደመሰሰ፤ ሕዝቡም በምርኮ ተጋዘ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሰላምና ብልጽግና የሞላበት ሕይወት መኖር ማለት እግዚአብሔር በእነርሱ ተደስቶአል ማለት እንደሆነ የሚመስላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ሁልጊዜ እውነት ነውን? መልስህን አብራራ። ሐ) ሰላምና ብልጽግና በክርስትና ሕይወት መንፈሳዊ ዕድገት ውስጥ ብዙ ጊዜ ወሳኝ የሚሆኑት ለምንድን ነው? በትንቢተ አሞጽ ውስጥ የሚገኙ ዐበይት የሥነ-መለኮት ትምህርቶች 1. እግዚአብሔር በድሆች ላይ የሚፈጸመውን ፍትሕ-አልበኝነትን ይጠላል። የውይይት ጥያቄ፥ አሞጽ 2፡6-7፤ 3፡10፤4፡1፤5፡7፥11-12፤ 6፡14፤8፡46 አንብብ። ሀ) አሞጽ እስራኤልን የሚከስባቸውን ማኅበረሰባዊ ኃጢአቶች ዘርዝር። ለ) ፍትሕን ያለ አግባብ በማዛባታቸው የተከሰሱትን ሰዎች ዘርዝር። አብዛኛዎቹ ነቢያት ያወገዙት የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንፈሳዊ ኃጢአት ቢሆንም፥ የአሞጽ መልእክት የሚያተኩረው በእስራኤላውያን ማኅበራዊና ሥነ-ምግባራዊ ኃጢአት ላይ ነበር። አሞጽ «ለማኅበራዊ ፍትሕ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ» ተብሉ ይጠራል። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት፥ እስራኤላውያንም ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን አምልኮ ከዕለታዊ ተግባራቸው ይለዩት ነበር። ውጫዊ የሆነውን ሥርዓት እስከፈጸሙ ድረስ፥ እግዚአብሔር እንደሚቀበላቸውና ደስ እንደሚሰኝባቸው ያስቡ ነበር። ስለዚህ በሃይማኖታዊ በዓላት ይገኙ፥ መሥዋዕቶችን ያቀርቡ፥ ይጾሙና ይጸልዩ ነበር። ሥርዓተ አምልኮ በማያካሂዱበት ጊዜ ግን እግዚአብሔርን ደስ በማያሰኝ ሁኔታ ይኖሩ ነበር። እግዚአብሔር አድልዎ የሌለበት መልካም ኅብረተሰብ ለመመሥረት ይረዳቸው ዘንድ ሕግን ቢሰጣቸውም፥ የእስራኤል ምድር ግን ፍትሕ ጐድሏት ነበር። ሀብታም የነበሩ አይሁዳውያን ድሆችንና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ይጨቁኑ ነበር። ይህን የሚያደርጉትም በሀብታቸው ላይ ሌላ ሀብት ለመጨመር ያገኙትን ይህን ተገቢ ያልሆነ ዕድል ለመጠቀም ነበር። ድሆችን ባሪያዎች አድርገው ይሸጡ ነበር። የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ለሀብታሞቹ የቆሙ በመሆናቸው፥ አድልዎ የሞላበት ፍርድ ይፈርዱ ነበር፤ ድሆች ደግሞ ከፍተኛ ቀረጥ እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር። የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ድሆችን በመርዳት ፈንታ፥ እነርሱን የሚጐዳ ነገር ያደርጉ ነበር። ኑሮአቸውን ለማሻሻል ዕድሉ ለሌላቸው፥ ለድሆች፥ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶችና ለሙት ልጆች ርኅራኄ የሚያሳይ ማንም አልነበረም። ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በትንቢተ ሆሴዕ እንደምንመለከተው ስለ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ስለ ማኅበራዊ ኃጢአታቸውም እንደሚቀጣቸውና ወደ ምርኮ እንደሚወሰዱ ተናገረ። መጽሐፍ ቅዱስ፥ የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን፥ እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን መውደድ እንዳለብን ይነግረናል (ማርቆስ 12:30-31 ተመልከት)። እግዚአብሔር በየእሑዱ ከምናደርገው ውጫዊ የአምልኮ ሥርዓታችን ይልቅ ከእርሱ ጋር ስላለን ውስጣዊ ግንኙነት ይገደዋል። ይህ ውስጣዊ ግንኙነት እውነተኛ እንዲሆን በዙሪያችን ከሚገኙ ሰዎች ጋር ትክክለኛ የሆነ ግንኙነት ሊኖረን ያስፈልጋል። ይህ ትክክለኛ ግንኙነት ከሰዎች ሁሉ ጋር በፍትሕ መኖርን፥ በተለይ ደግሞ በዙሪያችን የሚገኙትን ድሆችና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች መርዳትን ይጨምራል። ድሆችን የማንረዳ ከሆነ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ትክክል ይሆናል ማለት ያጠራጥራል። የውይይት ጥያቄ፥ ሉቃስ 10፡25-37 አንብብ። ሀ) እዚህ ጥቅሶች ሌሎችን ለመርዳት ስላለብን ኃላፊነት የሚያስተምሩን ምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህና ባለህበት ኅብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ድሆችና ኑሮ ያልተሳካላቸውን ሰዎች ዘርዝር። ሐ) አሞጽ ዛሬ በምድር ላይ የሚኖር ቢሆን ኖሮ፥ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በአገሪቱ መሪዎች ላይ ምን ዓይነት መልእክት የሚያቀርብ ይመስልሃል? መ) በዚህ ዘመን የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች በአሞጽ ዘመን የነበሩትን አይሁድ የሚመስሉባቸውን መንገዶች ጥቀስ። ሠ) ባለህበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለፍትሕ-አልበኝነት የተጋለጡትን ሰዎች ለመርዳት ቤተ ክርስቲያንህ ምን ማድረግ ያለባት ይመስልሃል? ረ) እግዚአብሔር ማኅበራዊ ፍትሕ-አልበኝነትን አጥብቆ የሚቃወመው ለምን ይመስልሃል? የሰዎች ሁሉ ፈጣሪ ለሆነው እግዚአብሔር፥ ሰዎች ሁሉ እኩል የመዳኘታቸው ጉዳይ አጥብቆ ይገደዋል። ክፋትንና ፍትሕ-አልበኝነትን ይጠላል። የእርሱ ፍላጎት «ጽድቅ እንደማይደርቅ ፈሳሽ» እንዲፈስ ነው (አሞጽ 5፡24)። ምንም እንኳ የምንኖረው አብዛኛው ሰው ጽድቅን በማይለማመድበትና ሰዎች ለድሆች በማያስቡበት ዓለም ቢሆንም፥ እኛ ግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ከዚህ የተለየን መሆን አለብን። እግዚአብሔር የመበለቶች፥ የሙት ልጆችና የድሆች አምላክ ነው። እግዚአብሔር ለእነርሱ የተለየ አትኩሮት አለው (መዝሙር (146)፡7-9)። እኛም የእርሱ ልጆች ከሆንን ይህ ዝንባሌ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በአካባቢያችን ስለሚኖሩ ሰዎች ችግር ግድየለሾች ከሆንን፥ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው አምልኮ ተቀባይነት ማግኘቱ ያጠራጥራል።  2. እግዚአብሔር የአሕዛብ ሁሉ አምላክ ነው። በትንቢተ አሞጽ ውስጥ እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይሆን፥ የአሕዛብ ሁሉ አምላክ እንደሆነ በተደጋጋሚ እንመለከታለን። የፈጠራቸው እርሱ ነው (አሞጽ 9፡7)፤ ስለሚያደርጉት ነገር በኃላፊነት የሚጠይቀው እነርሱን ነው (አሞጽ 1፡3-2፡3)። ብሔራዊ ኃጢአት በሚኖርበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ሕዝብ ላይ ፍርድን ያመጣል። እግዚአብሐር በሕዝቦች ላይ የሚፈርደው በሚፈጽሙት ኢ-ፍትሐዊ ወይም ፍትሕ-አልባ ድርጊትና በሕዝቦች ላይ በሚያደርሱት ግፍና በደል መሠረት ነው። እግዚአብሔርን የሚያከብሩና እርሱ በዝርዝር የደነገጋቸውን የጽድቅ ሕግጋት የሚጠብቁ ሕዝቦችን፥ እግዚአብሔር ያከብራቸዋል ይሸልማቸዋልም። ዳሩ ግን እግዚአብሔርን የማያከብሩ፥ በጭካኔና በፍትሕ-አልበኝነት የሚገዙ ይቀጣቸዋል። ትንቢተ አሞጽ የሚያስተምረን፥ እግዚአብሔር ለምንኖርበት አገር ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፥ ለሕዝቦች ሁሉ እኩል እንደሚገደው ነው። እግዚአብሔር ሶማሌን፥ ኬንያን፥ ሱዳንን፥ አሜሪካንን፥ እንግሊዝንና የቀሩትን አገሮች ሕዝቦች ሁሉ እኩል ይወዳቸዋል። ይህ እውነት እኛ ክርስቲያኖች ሌሎች ሕዝቦችን በአንዳንድ ቅድመ-ሁኔታዎች ላይ ተመሥርተን ፍትሕ በጐደለው ሁኔታ ወይም በጥላቻ ስሜት እንዳንመለከታቸው ሊረዳን ይገባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር የእኛን ሕዝብና አገር ብቻ ሳይሆን ሕቦችንና አገሮችን ሁሉ እኩል እንደሚወድ የምንረዳው በምን መንገዶች ነው? ለ) ፍትሕ በሌለበት አገር የሚኖር ክርስቲያን ፍትሕን ለማራመድ ያለው ኃላፊነት ምንድን ነው? ) በትንቢተ አሞጽ ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች ዛሬ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሊያውቁና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዱ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ አሞጽ ዓላማ እና ዐበይት የሥነ መለኮት ትምሕርቶች Read More »

የትንቢተ አሞጽ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ያዕቆብ 1፡27 አንብብ። ሀ) ሐዋርያው ያዕቆብ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕና ነውርም የሌለበት አምልኮ ምንድን ነው ይላል? ለ) ይህን ያለው ለምን ይመስልሃል? ይህን ጥቅስ በግል በምትወስደው ክርስቲያናዊ እርምጃህ ከሕይወትህ ጋር ለማዛመድ የፈለግኸው እንዴት ነው? መ) ቤተ ክርስቲያንህ ይህን ጥቅስ ለመፈጸም የምትጥረው እንዴት ነው? ትንቢተ አሞጽ ስለ እውነተኛ፥ ንጹሕና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ስላለው ሃይማኖት ይናገራል። ብዙዎቻችን እግዚአብሔር ጉዳይ ያለው ከልባችን ጋር ብቻ የሆነ ይመስለናል። በእግዚአብሔር ላይ ትክክለኛና ተገቢ የሆነ እምነት ካለን፥ ከኃጢአት ንጹሐን ሆነን ለመኖር ከጣርን፥ ለማያምኑ ሰዎች ከመሰከርን ብቻ እግዚአብሔር በእኛ ደስ የሚለው ይመስለናል። እነዚህ ሁሉ አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም፥ በእግዚአብሔር ፊት ግን እነዚህ ብቻ በቂ አይደሉም። መዘመር፥ መጸለይ፥ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ወይም መመስከር የመሳሰሉትን ተገቢ የሆኑ ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን ብንፈጽምም እንኳ ድሆችን፣ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና የሙት ልጆችን ለመሳሰሉ እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማድረግ ካልጣርን እውነተኛውን ሃይማኖት እየተከተልን አለመሆናችንን እንደ ያዕቆብ መልእክት ሁሉ ትንቢተ አሞጽም ያስተምረናል። በእግዚአብሔር አመላካከት እውነተኛ ሃይማኖት የሚጀምረው ከልብ በሚደረግ እምነትና አምልኮ ቢሆንም፥ ዳሩ ግን ይህን መሰሉ ልብ በችግር ውስጥ ስለሚገኙ ሰዎች ሁልጊዜ ግድ የሚለውና እነርሱንም ለመርዳት ፈጥኖ የሚደርስ መሆን አለበት። ብዙዎቻችን ግን እነዚህን ጥቅሶች በተግባር ላይ አናውላቸውም። በአሞጽ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ይህን አላደረጉም ነበር። ስለዚህ አሞጽ ራሳቸውን እንደ ጻድቃን የሚጥሩና ድሆችን በመናቅ ይጨቁኑ የነበሩትን መሪዎች ይከሳል። እግዚአብሔር ይበልጥ ደስ የሚሰኘው በሃይማኖታዊ አምልኮ (ለምሳሌ መሥዋዕቶችን በማቅረብ) ሳይሆን በፍርድ፥ በጽድቅ፥ በፍቅርና ለድሆች በሚደረግ ምሕረት ነው (አሞጽ 5፡21-24 ተመልከት)።  የትንቢተ አሞጽ ጸሐፊ  የትንቢተ አሞጽ ጸሐፊ አሞጽ የተባለው ሰው ነው። አመጣጡ ከደቡብ የይሁዳ መንግሥት ሲሆን፥ የተወለደባት ከተማ በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተ ልሔም 9 ኪ.ሜ. ያህል ርቃ በስተደቡብ የምትገኝ ቴቁሔ የምትባል ስፍራ ነበረች። በዘመኑ የነበሩት አብዛኛዎቹ ነቢያት የነቢይነትን አገልግሎት ያከናውኑ የነበረው ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ሲሆን፥ አሞጽ ግን እንደዚያ አልነበረም። ይህንን ስንል አሞጽ የነቢይነት አገልግሎት ሙያው አልነበረም ወይም ቤተሰቡ ከነቢያት ወገን አልነበረም ማለታችን ነው (አሞጽ 7፡14-15)። ይልቁንም አሞጽ ገበሬ ነበር። ላም ጠባቂና የሾላ ፍሪ ለቃሚ ሲሆን፥ አመጣጡ ከይሁዳ ድሀ ቤተሰብ ነበር። ይህ ሐቅ እግዚአብሔር ዕቅዱን ለመፈጸም የሚጠቀመው በተማሩት ሰዎች ብቻ እንዳይደለ ሊያስታውሰን ይገባል። ብዙዎቻችን እግዚአብሔር የሚጠቀመው በተማሩ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በሠለጠኑ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክብር ስፍራ ባላቸው ሰዎች ብቻ የሆነ ይመስለናል። ነገር ግን ይህ የሰይጣን ሽንገላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እግዚአብሔር ሞኞችን፥ ያልተማሩትንና የተጣሉትን ሰዎች ከፍተኛ ተግባር እንዲፈጽሙለት እንደሚመርጣቸው ነው። በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ጥበበኞችና ሀብታሞች የሆኑትን ሰዎች በማስገረም፥ በሥራው ውስጥ የሚታየውን ክብር ሁሉ ለራሱ ይወስዳል። የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡17-31 አንብብ። ሀ) አሞጽ እነዚህን ጥቅሶች የሚገልጠው እንዴት ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የእነዚህ ጥቅሶች እውነትነት ሲረጋገጥ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) በርካታ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አገልጋዮችን ለመምረጥ በትምህርት፥ በሀብትና፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሥልጠና ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው? እግዚአብሔር አሞጽን ጠርቶ ወደ ሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ላከው። አሞጽ ያገለገለው የእስራኤል የሃይማኖት ማዕከል በነበረችው በቤቴል ይመስላል። አሞጽ በእስራኤልና በይሁዳ ውስጥ የነበረውን ሥነ-ምግባራዊ ውድቀትና ማኅበረሰባዊ ብልሹነት እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በቅርቡ ከሚያመጣው ፍርድ ጋር በግልጽና በታማኝነት ያወጀው በዚህ ስፍራ ነበር። የአሞጽ መልእክት በሚገባ ተቀባይነት አላገኘም። ወደ ቤቱ እንዲሄድ በማስፈራራት ከነገረው ከአሜስያስ ጋር ተጋፍጧል (አሞጽ 7-12)። ለዳግማዊ ኢዮርብዓም ስለ አሞጽ ተነግሮት ነበር። በአሞጽ ላይ ምን እንደደረሰበት አናውቅም። ወደ ይሁዳ ተባርሮ ወይም ኢዮርብዓም አስሮት እንደሆነ አናውቅም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው አንዳችም ነገር የለም። ዳሩ ግን አሞጽ ለእስራኤላውያን ያስተላለፈውን መልእክት የያዘው መጽሐፍ በእጃችን አለ። የአሞጽ መልእክት አጭርና ቀጥተኛ ነው። አሞጽ በሕዝቡ ላይ ካቀረባቸው ወቀሳዎች አብዛኛዎቹ ዛሬም በእኛ ላይ ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው። ከትንቢተ አሞጽ መግቢያ (አሞጽ 1፡1) በመነሣት፥ ከ750-748 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ማለት ዳግማዊ ኢዮርብዓም እንደሞተ የአሞጽ አጭር አገልግሎት እንደተከናወነ መገመት እንችላለን። አሞጽ ይህንን ትንቢት የጻፈው በእስራኤል ያካሄደውን የስብከት አገልግሎት ጨርሶ እንደተመለሰ ሳይሆን አይቀርም። ትንቢቱ የተጻፈው ጳለስጢንን ከፍተኛ የመሬት መናውጥ ከመታት በኋላ ነበር። አሞጽ ይህን የመሬት መንቀጥቀጥ የትንቢቱ ፍጻሜና የእግዚአብሔርን ፍርድ ጅማሬ ከሚያሳዩ ምልክቶች አንዱ አድርጎ ቈጥሮት ነበር (አሞጽ 2፡13፤ 9፡1)። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ እጅግ ታላቅ ስለነበር ለብዙ ምእተ ዓመት ይወሳ ነበር (ዘካርያስ 14፡5)።  በዚህ ጊዜ በእስራኤልና በይሁዳ ይሠራ የነበረ ነቢይ አሞጽ ብቻ አልነበረም፡፡ ዮናስና ሆሴዕ በእስራኤል፥ በይሁዳ ደግሞ ሚክያስና ኢሳይያስ ያገለግሉ ነበር። አሞጽ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ሕዝቡን የሚያግባባ ከእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ውስጥ አንዱ ነበር። ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣባቸውን ፍርድ በመናገር ሕዝቡን ያስጠነቅቅ ነበር። የትንቢተ አሞጽ ታሪካዊ ሥረ መሠረት አሞጽ ትንቢቱን የጻፈበትን ዘመን የሚቆጥረው ከዳዊትና ከሰሎሞን አገዛዝ በኋላ ከተነሡት ሁለት ታላላቅ የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት ዘመነ መንግሥት ጋር በማያያዝ ነው። ነገሥታቱ የይሁዳው ዖዝያንና የእስራኤሉ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነበሩ። ሁለቱም ነገሥታት በሥልጣን ላይ የቆዩት ከ40 ዓመታት በላይ ነበር። ሁለቱም ይገዙ የነበረው ታላላቅ የአሕዛብ መንግሥታት ባልነበሩበት ዘመን ነበር። ስለዚህ ዖዝያንም ሆነ ዳግማዊ ኢዮርብዓም የአገራቸውን ድንበር በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን ተይዞ እስከነበረው ዳርቻ ድረስ ለማስፋት ችለው ነበር። በተጨማሪም ለሕዝባቸው የፖለቲካ መረጋጋትን፥ የጦር ኃይል ገናናነትንና የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማምጣት ችለው ነበር። ምናልባት ይህ በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ የሕዝቦች መደብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። የኢኮኖሚ ሁኔታው እጅግ መልካም ስለነበር ነጋዴዎች በሀብታቸው በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ በመሄድ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለመታውቅ በቁ። ደግሞም በባለጠጎችና ብዙውን ጊዜ ገበሬዎች በነበሩት ድሆች መካከል የነበረው የኢኮኖሚ ልዩነት እየሰፋ ሄደ። ነጋዴዎች መሪዎችን እንደፈለጉ በመጠምዘዝ ድሆችን እያጎሳቆሉ መሬታቸውንና ቤቶቻቸውን ቀሙ። በመሆኑም፥ እነዚህ ሀብታም መሪዎች ድሆችን መጨቆን ጀመሩ። ስለዚህ በእስራኤል ምድር የፖለቲካና የኢኮኖሚ መረጋጋት ቢኖርም እንኳ ሕዝቡ በመንፈሳዊ፥ በማኅበራዊና በሥነ-ምግባር ክፋት ተሞልተው ነበር። ከጠላቶቻቸው ደጋፊዎቻቸው ዋስትና እንዳላቸው ተሰማቸው። በመሆኑም የእግዚአብሔርን ጸጋና ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጠላቶቻቸው እንዴት እንዳዳናቸው ዘነጉ። የእስራኤል ብልጽግና ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ብልሹነተን አባባሰው። እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ እንደሚፈርድ የተናገረውን ቃል ዘነጋች። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት የሚያበቃበት ጊዜ ደረሰ። ከድሀው መደብና በሀብታሞች ይጨቆኑ ከነበሩት መካከል አንዱ የነበረው አሞጽ እነዚህን ክፉ ቀናት በመቃወም እንዲናገር በእግዚአብሔር ተመረጠ። ሁለቱም ብሔሮች ማለት እስራኤልና ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች እንደነበሩ፥ የፍርድ ጊዜም እንደደረሰ ተናገረ (አሞጽ 8፡1-2፤ 3፡9-15)። ከዚህም በኋላ፥ እስራኤል ተደምስሳ ሕዝቡ በምርኮ ወደ አሦር በመወሰዳቸው የአሞጽ ትንቢት በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በከፊል ተፈጸመ። የውይይት ጥያቄ፥ የዳግማዊ ኢዮርብዓምን ዘመን ከዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋር አወዳድር። ሀ) የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ለ) የሚለያዩትስ፣ ሐ) ከዚህ የእስራኤል ታሪክ፣ ሰላምና ብልጽግና ሊኖር የሕዝቡ ሥን ምግባራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ብዙውን ጊዜ ምን እንደሚደርስበት ልንማር እንችላለን?  የውይይት ጥያቄ፣ ስለ አሞጽ የተሰጠውን መረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በዚያ ስፍራ የተጠቀሱትን ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር።  የትንቢተ አሞጽ አስተዋጽኦ  1. አሞጽ በአሕዛብ ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (አሞጽ 1-2)፥ ሀ. በደማስቆና በሶርያ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡3-5)፥  ለ. በጋዛና በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡6-8)፥  ሐ. በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡9-10)፥  መ. በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡11-12)፥  ሠ. በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡13-15)፥  ረ. በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 2፡1-3)።  ሰ. በይሁዳ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 2፡4-5)፥  ሸ. በእስራኤል ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 2፡6-16) ናቸው።  2. በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ፍርድ አሞጽ የተናገራቸው ትንቢቶች (አሞጽ 3-6) ሀ. አሞጽ ለምን ፍርድ እንደሚገባቸው ይናገራል (አሞጽ 3)።  ለ. አሞጽ እስራኤላውያን ከዚህ ቀደም ከደረሰባቸው የእግዚአብሔር ቅጣት እንዳልተማሩ ለማሳየት

የትንቢተ አሞጽ መግቢያ Read More »