ዘፍጥረት 37-50 የዮሴፍ ታሪክ

የዚህ የኦሪት ዘፍጥረት የመጨረሻ ክፍል ዓላማ የእስራኤል ሕዝብ የከነዓንን ምድር ይወርሱ ዘንድ ቃል የተገባላቸው ሆነው ሳሉ፥ እንዴት ወደ ግብፅ እንደወረዱ ማሳየት ነው። ለኦሪት ዘጸአትም በመግቢያነት የሚያገለግል ነው። ምክንያቱም ኦሪት ዘጸአት እስራኤላውያን በግብፅ 400 ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመመለስ እንዴት እንደወጡ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። ታሪኩ የተፈጸመው በሙሴ ዘመን ገደማ ስለሆነ፥ ከሌሎቹ የእስራኤል አባቶች ታሪክ ይልቅ የዮሴፍን ታሪክ በዝርዝር ይነግረናል። በተጨማሪ ኃጢአታቸው የሚያስከትለውን ችግር ጨምሮ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሕይወት የሚመጣውን ነገር ሁሉ እየተቆጣጠረ እንዴት ያለማቋረጥ እንደመራቸው እንመለከታለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍጥ. 37-50 አንብብ። ሀ) ዮሴፍ ያያቸውንና የተረጎማቸውን ልዩ ልዩ ሕልሞች ዘርዝር። እያንዳንዳቸው እንዴት ተፈጸሙ? ለ) ዮሴፍ በምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው የሆነው እንዴት ነው? ሐ) በዮሴፍ ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ቁጥጥር የታየባቸውን መንገዶች ዘርዝር። መ) በስደት ውስጥ ይቅርታንና ትዕግሥትን ስለማሳየት ከዮሴፍ ሕይወት የምንማረው ነገር ምንድን ነው? 

ከብዙ ዓመታት በፊት፥ እግዚአብሔር በሌላ ምድር መጻተኞች ሆነው እንደሚኖሩና ለ400 ዓመታት በባርነት እንደሚገዙ ለአብርሃም ተናግሮት ነበር (ዘፍጥ. 15፡13)። በዮሴፍ ታሪክ ይህ ትንቢት መፈጸም ጀመረ። እግዚአብሔር የገባውን ቃል ኪዳንና የሰጠውን ተስፋ እኛ በምንፈልገው ፍጥነት ባይፈጽምም፥ ለሰጠው ተስፋና ቃል ኪዳን ግን ሁልጊዜ ታማኝ ነው።

 1. ዮሴፍ ወደ ግብፅ የሄደበት ምክንያት (ዘፍጥ. 37):- ከዘፍጥረት ምዕራፍ 37 ጀምሮ የእግዚአብሔርን እጅ በሥራ ላይ እናያለን። እግዚአብሔር አንድ ዓይነት ትርጉም ያላቸውን ሁለት ሕልሞች ለዮሴፍ ሰጠው። በመጀመሪያ፥ የወንድሞቹ ነዶዎች ለእርሱ ሲሰግዱ ያያል። በሁለተኛው ሕልም ደግሞ ፀሐይ፥ ጨረቃና አሥራ አንዱ ከዋክብት ለእርሱ ሲሰግዱለት አየ። ይህ ሕልም በወንድሞቹ ላይ ገዥ እንደሚሆንና እነርሱም እንደሚሰግዱለት ማለትም እንደ መሪያቸው ተቆጥሮ እንደሚያከብሩት የተሰጠ ትንቢት ነበር። ይህም ትንቢት ከብዙ ዓመታት በኋላ ዮሴፍ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ወንድሞቹ ምግብ ፍለጋ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ተፈጸመ።
 2. ትዕማር የይሁዳን ዘር አዳነች (ዘፍጥ. 38)፡- በዮሴፍ ታሪክ አጋማሽ ላይ በሌሉች ወንድሞቹ በተለይም በይሁዳ ሕይወት ኃጢአትና ክፋት መኖሩን የሚያሳይ አሳዛኝ ታሪክ እንመለከታለን። የይሁዳ ትልቁ ልጅ ዔር ትዕማር የምትባል ከነዓናዊት አገባ፤ ነገር ግን አንድም ልጅ ሳይወልድ ሞተ። በዚያ ዘመን በነበረው ወግ መሠረት ይሁዳ የሚቀጥለውን ልጁን አውናንን ከትዕማር ጋር ማጋባት ነበረበት። በባሕሉ መሠረት የሚወለደው የመጀመሪያ ልጅ የሟቹ ወንድም የዔር እንደሆነ ይቆጠር ነበር። የቀሩት ልጆች ደግሞ የአውናን ይሆኑ ነበር። የመጀመሪያው ልጅም የብኩርናን መብት ያገኝ ነበር። በሞተውም ልጅ ምትክ ከአያቱ ርስት ይወርስ ነበር። ይህ ማለት ይሁዳ ለበኩር ልጁ ያወርሰው የነበረው ነገር የመጀመሪያ ልጁ ከሞተ በኋላ የሚተላለፈው ለሁለተኛ ልጁ ሳይሆን ከትዕማር ለተወለደው ለልጅ ልጁ ይሆናል ማለት ነው። አውናን በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ስላደረገ እግዚአብሔር ቀሠፈው። ባሕሉን ለማክበርና ለወንድሙ ልጅ ለማሳደግ ያልፈለገ ይመስላል። ምናልባት ምንም ልጅ ሳይወልዱ በሞተው ወንድሙ ምትክ የብኩርናን መብት እንደሚወርስ ሳይገምት አልቀረም። አውናን ከሞተ በኋላ ይሁዳ በባሕሉ መሠረት ሦስተኛ ልጁን ለትዕማር ለመዳር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ግዴታውን ለእርሷና ለመጀመሪያ ልጁ ሳይፈጽም ቀረ፤ ስለዚህ እርሷና ልጆችዋ የብኩርና መብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሁዳን አታለለችው። ራሷን ሴተኛ አዳሪ አስመስላ በማቅረብ አማችዋ የሆነው ይሁዳ ከእርሱ ጋር እንዲተኛ አደረገችው። ከእርሱም ፋሬስና ዛራ ብላ የጠራቻቸውን መንታ ልጆች ወለደች። ይህን በማድረግዋ የይሁዳን ዘር ከመጥፋት አዳነች። የብኩርናን መብትም በቤተሰቧ በማስቀረት ልጇ ለይሁዳ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ወራሽ እንዲሆን አደረገች። የሚያስደንቀው ነገር ንጉሡ ዳዊትና የዳዊት ልጅ ተብሎ የሚጠራው የኢየሱስ ክርስቶስ ዘር የመጣው ከትዕማር ልጅ ከፋሬስ መሆኑ ነው(ማቴ. 1፡3)።
 3. እግዚአብሔር ዮሴፍን በግብፅ ጠብቆ አከበረው (ዘፍጥ. 38-40)።

ሀ. እግዚአብሔር ዮሴፍን በጲጥፋራ ቤት አከበረው፡- ዮሴፍ በዚህ ሰው ቤት ባሪያ ቢሆንም፥ ከእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝቦች አንዱ ነበር። እስራኤላውያንን ከራብ በማዳን የተሰጣቸው ቃል ኪዳን ከፍጻሜ እንዲደርስ ለማድረግ በእግዚአብሔር የተመረጠው ሰው ዮሴፍ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ዮሴፍን አከበረውና በግብፅ ውስጥ ባለውና መሪ በነበረው በጲጥፋራ ቤት አገልጋዮች ሁሉ አለቃ እንዲሆን አደረገ። ከጲጥፋራ ሚስት ጋር ዝሙት ፈጽሞ ሕይወቱ ሁሉ እንዲበላሽና እንዲጠፋ ለማድረግ ሰይጣን ሞከረ። ዮሴፍ ግን በዚህ መንገድ እግዚአብሔርንና ጲጥፋራን ላለመሳደብ ወስኖ የሰይጣንን ሙከራ ተቃወመ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለዮሴፍ ከጲጥፋራ ሚስት ጋር ዝሙት መፈጸም በጣም ቀላል የነበረው ለምንድን ነው? ለ) በዚህ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ኃጢአት የሚወድቁት ለምንድን ነው? ሐ) ይህንን ፈተና ስለማሸነፍ ከዮሴፍ ሕይወት የምንማረው ነገር ምንድን ነው?

ለ) እግዚአብሔር ዮሴፍን በወኅኒ ቤት አከበረው፡- ምንም ጥፋት ያልነበረበት ንጹሕ የነበረው ዮሴፍ ወደ ወኅኒ ቤት ከገባ በኋላ በዚያ ለብዙ ዓመታት ቆየ። እግዚአብሔር በዚያም ቢሆን ሞገስን ሰጠውና በወኅኒ ቤቱ የእስረኞች አለቃ አደረገው።

የወኅኒ ቤቱ የእስረኞች አለቃ ስለነበር እዚያ ታስረው ከነበሩት ከፈርዖን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጋር ለመገናኘት ቻለ። እነዚህ ሁለት ሰዎች በግብፅ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ነበሩ። ጠጅ አሳላፊው ንጉሡ ወይን ጠጅ ከመጠጣቱ በፊት የሚቀምስለት ሰው ነበር። ይህም ንጉሡን ማንም ሰው በመርዝ ሊገድለው እንዳይችል የተደረገ ዘዴ ነበር። ብዙውን ጊዜ የጠጅ አሳላፊው የንጉሡ ምሥጢረኛና የቅርብ ጓደኛ ነበር። የእንጀራ አበዛውም ንጉሡ ለሚበላቸው ነገሮች ሁሉ ኃላፊነት ስለ ነበረበት በጣም ከፍተኛ ስፍራ የነበረው ሰው ነው። እነዚህ ሁለት ሰዎች በእስር ቤት በነበሩ ጊዜ ዮሴፍ ሊተረጉምላቸው የቻለውን ሁለት ሕልሞች አዩ። የጠጅ አሳላፊው ሕልም ትርጓሜ ንጉሡን ያገለግልበት ወደነበረው ወደ ቀድሞ ሥፍራው መመለሱ ነበር። የእንጀራ አበዛው ሕልም ትርጓሜ ደግሞ የንጉሡን ምሥጢር ስላባከነ በስቅላት እንደሚገደል ነበር። እነዚህ ሕልሞች በኋላ የፈርዖንን ሕልም ለመተርጎም ወደ ቤተ መንግሥት እንዲጠራ ያደረጉት ስለነበሩ በጣም ጠቃሚ ሕልሞች ነበሩ።

 1. እግዚአብሔር ዮሴፍን በፈርዖን ፊት አከበረውና ጠቅላይ ሚኒስትር አደረገው (ዘፍጥ. 40-45)።

ዮስፍ የፈርዖንን ሕልም ከተረጐመ በኋላ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ እንደደረሰ ይታወቃል። እግዚአብሔር በዮሴፍ በኩል ለፈርዖን ሰባት የጥጋብና ሰባት የረሃብ ዓመታት እንደሚመጡ በሕልሙ አሳወቀው። ዮሴፍ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደመሆኑ መጠን ለረሀቡ ጊዜ የሚሆነውን እህል በጥጋቡ ጊዜ አዘጋጀ።

እግዚአብሔር ዮሴፍን ያን ወደ መሰለ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ያመጣው ለምንድን ነው? ሀ) የግብፅን ሕዝብ ከራብ ለማዳን፥ ለ) የተመረጠውን የእስራኤልን ሕዝብ ከራብ ለማዳንና፥ ሐ) ለአብርሃም የገባውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ይችል ዘንድ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ግብፅ ለማምጣት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ዕቅዱን ለመፈጸም ሲል ዮሴፍን በዚህ ዓይነት ካከበረው፥ ዛሬም ለእኛ እንዴት እንደሚሠራ ይህ ምን ያስተምረናል? ለ) እግዚአብሔር በዮሴፍ ሕይወት እንዳደረገው በአንተ ወይም በሌላው ክርስቲያን ሕይወት ያደረገውን ተመሳሳይ ነገር የሚገልጹ ምሳሌዎችን ዘርዝር።

ዮሴፍ ለባርነት የሸጡትን ወንድሞቹን ለመፈተን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ አደረጋቸው። እርሱን ለባርነት ስለሸጡበት ኃጢአት በእርግጥ መፀፀታቸውን ማየት ፈለገ። ይሁዳ ራሱን በብንያም ምትክ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑንና ወንድሞቹም እንደዚያ የተቀጡበት ምክንያት እግዚአብሔር ራሱ ስለቀጣቸው እንደሆነ መቀበላቸውን ሲያይ ከኃጢአታቸው በእርግጥ መመለሳቸውን አወቀ። ከዚያ በኋላ ራሱን ገለጠላቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዮሴፍ ወንድሞቹ እንደተለወጡና በእርግጥ ከኃጢአታቸው እንደተመለሱ ማወቅ ለምን አስፈለገው? ለ) ክርስቲያኖች በእውነት ከኃጢአታቸው መመለሳቸውን በምን እናውቃለን?

 1. የያዕቆብ ትውልድና ትንሹ የእስራኤል ጎሳ ወደ ግብፅ መውረድ (ዘፍጥ. 46-50)።

ዮሴፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ በኋላ ቤተሰቡ ወደ ግብፅ መጥተው እንዲኖሩ አደረገ። የእስራኤል ሕዝብ አባት የሆነው ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ። የዮሴፍን ልጆች ጨምሮ ወደ ግብፅ የመጡት እስራኤላውያን ጠቅላላ ቁጥር 70 ነበር። ከ400 ዓመታት በኋላ 70 የነበረው የእስራኤላውያን ቁጥር 2 ሚሊዮን ደርሶ ነበር።

ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት ለልጆቹ ለእያንዳንዳቸው በረከቱን አስተላለፈ። እነዚህ በረከቶች የትንቢት መልክ ሲኖራቸው የተሰጡትም በቀጥታ ከእግዚአብሔር እንደመጡ ተደርገው ነበር። የያዕቆብ በረከቶችና ትንቢት የእግዚአብሔር ቃል ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ፈጸማቸው።

ሀ) ያዕቆብ የዮሴፍን ሁለት ልጆች ኤፍሬምና ምናሴን ባረካቸው (ዘፍጥ. 48)። ይህንን በማድረግ ያዕቆብ የበኩር ልጅን መብት ለዮሴፍና ለልጆቹ ሰጠ። ደግሞም የብኩርናን መብት ከዮሴፍ ልጆች ለታናሹ ለኤፍሬም ሰጠ። እግዚአብሔር የርስቱን ዕጥፍ ለዮሴፍ ሁለት ልጆች ለኤፍሬምና ለምናሴ ስለሰጠ፥ በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ዮሴፍ የሚባል ነገድ አልነበረም። ይልቁንም በእርሱ ቦታ ኤፍሬምና ምናሴ የሚባሉ ሁለት ነገዶች ነበሩ። 

ለ) ለአሥራ ሁለቱ ልጆች የተሰጠ በረከት (ዘፍጥ. 49) 

ያዕቆብ ልጆቹን እያንዳንዳቸውን ባረካቸው፤ ትንቢትም ተናገረላቸው። ነገር ግን ሦስቱ ልጆቹ ለልዩ ቅጣት ተለዩ። እነዚህም በኩሩ ሮቤል፥ ስምዖንና ሌዊ ናቸው። ሦስቱም የብኩርና መብት አጡ። ሮቤል የአባቱን መኝታ ደፈረ። ይህም በጥንት ባሕል ታላቁ ልጅ የአባቱን ርስት ለመውሰድ መፈለጉን የሚያሳይ ነበር። (ሮቤል አባቱ እስኪሞት ድረስ መጠበቅ አቅቶት ቁባቶቹን ወስዶ ከእነርሱ ጋር በመተኛት የቤቱ ራስ መሆኑን አወጀ። ከዚህ የተነሣ ያዕቆብ ከሮቤል ላይ የበኩር መብት ወሰደበት። ስምዖንና ሌዊ ከነዓናውያን እኅታቸውን በመድፈራቸው የበቀል ሤራ ይወጥኑ ነበሩ። ይህ ዓመፅ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎች ለመሆን የነበራቸውን ዕድል አከሸፈባቸው። አብዛኛው በረከት የተላለፈው ለዮሴፍ ቢሆንም የብኩርና መብትና መሪነት ግን ለይሁዳ ተሰጠ። ይሁዳ አራተኛው ልጅ ሲሆን የነገሥታት አባት ሆነ። የያዕቆብ ሦስት ትላልቅ ልጆች እርግማንን እንጂ በረከትን አልተቀበሉም፤ ነገር ግን ዮሴፍና ይሁዳ በረከትን ከተቀበሉ ከያዕቆብ ልጆች ከፍተኛ ድርሻ ተቀብሉአል። በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ይህ አስፈላጊ ነበር፤ ምክንያቱም ቢባል በዮሴፍ ልጅ – በኤፍሬም ነገድና በይሁዳ ነገድ መካከል የእስራኤል ነገዶች መሪ ለመሆን ሲባል ብዙ ጊዜ ትግል ይካሄድ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ በመጨረሻ የኃጢአት ቅጣት የማይቀር ስለመሆኑ እነዚህ ታሪኮች ምን ያስተምሩናል? 

 1. ያዕቆብ በከነዓን ተቀበረ።

ይህ ዋጋ የሌለው ታሪክ ይምሰል እንጂ ሆኖም ግን የሚመስለው ግብፅ የአይሁድ ምድር እንዳልሆነች የሚያሳይ ስለሆነ በጣም አስፈላጊ ነው። በግብፅ መኖር የሚያስፈልጋቸው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር። በመጨረሻ የሚመለሱባት ከነዓን ምንጊዜም አገራቸው ነበረች። የያዕቆብ ሬሣ ለቀብር ወደ ከነዓን ተወሰደ። ቆየት ብሎ የዮሴፍ ሬሣም ለቀብር ወደ ከነዓን ተወሰደ፤ (ኢያ. 24፡32)።

አዲስ ኪዳን ይህንን ባይናገርም እንኳ ብዙ ምሁራን ዮሴፍን የክርስቶስ አምሳል አድርገው ያቀርቡታል። ሁለቱም ተሽጠዋል። ዮሴፍ ለባርነት ሲሸጥ፥ ኢየሱስ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ በአንዱ ተሸጠ (አልፎ ተሰጠ)። ስለ ዮሴፍ በግልጥ የተጠቀሰ ኃጢአት የለም። ኢየሱስም ያለ ኃጢአት ነበር። እግዚአብሔር ኢየሱስንም ዮሴፍንም ሌሎችን ለማዳን ተጠቀመባቸው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ለማዳን ዮሴፍን ተጠቀመበት። ኢየሱስን ደግሞ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ለማዳን ተጠቀመበት።

የውይይት ጥያቄ፥ ከኦሪት ዘፍጥረት ጥናት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ሰው ምን መማር ይቻላል?

በኦሪት ዘፍጥረት በግልጥ የተጠቀሱ የእምነት ትምህርቶች

 1. እግዚአብሔር፡-

በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ የእግዚአብሔርን ማንነት ለመረዳት የሚያስችሉን አምስት ዋና ዋና ሥዕላዊ መግለጫዎችን እናገኛለን። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን ለእኛ የሰጠበት አንዱ ዋና ምክንያት እርሱ ማን እንደሆነ ሊገልጥልንና ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ለማስረዳት መሆኑን ልብ በል። የእግዚአብሔርን ማንነት ለማወቅ የምንችለው፥ እርሱ ምን እንደሚመስል እኛ በምናስበው መንገድ ሳይሆን፥ እርሱ ከሚነግረን ነገር ነው።

ሀ. እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ታላቅ ፈጣሪ ነው። አንድ ቃል በመናገር ብቻ ፍጥረታትን ሁሉ እንዲሁም ሰውን ጨምሮ ፈጠረ። 

ለ. እግዚአብሔር ቃል ኪዳን አድራጊ አምላክ ነው። እግዚአብሔር ከእንግዲህ ምድርን በውኃ እንደማያጠፋት ከኖኅ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ተመልክተናል። በኋላም ከአብርሃምና ከዝርያዎቹ ጋር ቃል ኪዳን ገብቶአል። ይህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ከአይሁድ ጋር ላለው ልዩ ኅብረት መሠረት ነው። አሕዛብ የተባረኩት በዚህ ቃል ኪዳን መሠረት ነው። እግዚአብሔር ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለበትን ቃል ኪዳን አንድ ጊዜ ከገባ፥ ሕዝቡ ባይታዘዙትና ቢያምፁበትም እንኳ ያንን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ይተጋል።

ሐ. እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ይፈርዳል። እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ ነው፤ ስለዚህ ኃጢአትን ሳይቀጣ አይተውም። በአዳምና በሔዋን፥ በቃየን፥ በኖኅ ዘመን በነበሩ ሰዎች፥ የባቢሎንን ግንብ ለመሥራት በሞከሩ ሰዎች ላይ እንደፈረደ ሁሉ ዛሬም በኃጢአት ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ለመፍረድ ቃል ገብቷል። 

መ. እግዚአብሔር ኃጢአተኞችንም ይምራል፡- እግዚአብሔር ለኃጢአተኞች የሚገባቸውን ቅጣት በሙሉ ሰጥቶ አያውቅም። እርሱ መሐሪ ነው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ካደረጉ በኋላ እግዚአብሔር ፈለጋቸው። ብዙ ምሁራን እግዚአብሔር የእንስሳ ቆዳ ባለበሳቸው ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው የመጀመሪያውን መሥዋዕት እንዳቀረበ ያምናሉ። ከኤድን ገነትም ያስወጣቸው የሕይወትን ዛፍ እንዳይበሉና ለዘለዓለም በኃጢአተኝነት እንዳይኖሩ ብሉ ነው። ይህን የመሰለ ምሕረት የሚገባቸው ባይሆኑም እንኳ ሎጥን ከሰዶም፥ ያዕቆብን ከላባና ከዔሳው እጅ አዳነ። እግዚአብሔር ከአሕዛብ ሁሉ መካከል በመረጠው ጊዜ አብርሃም እንኳ ራሱ ጣዖት አምላኪ ነበር።

ሠ. እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሁሉ ይቆጣጠራል። ዓለምን የፈጠረው እርሱ ነው። እግዚአብሔር የጥፋትን ውኃ ላከ። ቋንቋቸውንም በመደበላለቅ ሰዎችን በምድር ላይ በተናቸው። የተመረጡት ሕዝቡን እንዳይጎዱ ወይም ዕቅዱን እንዳያበላሹ የነገሥታትን ሥራ ይቆጣጠራል። እግዚአብሔር ብልጥግናንና ድርቅን የመሳሰለውንም ነገር ወደ ምድር ይልካል።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ እነዚህን የእግዚአብሔር ባሕርያት በሕይወታችን የምናየው እንዴት ነው?

ሙሴ የእግዚአብሔርን ባሕርያት ከሚገልጽባቸው መንገዶች አንዱ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ በጠቀሳቸው በርካታ የእግዚአብሔር ስሞች ነው። አይሁድ ስለ እግዚአብሔር «ስም» በሚነጋገሩበት ጊዜ የሚያተኩሩት በእግዚአብሔር ውጫዊ ስም ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ባሕርይ ላይ ነበር። ስሙ እግዚአብሔር በእርግጥ ማን እንደሆነ ይገልጥ ነበር። ስለዚህ ሰዎች «የእግዚአብሔርን ስም እናመስግን» ሲሉ «እግዚአብሔርን እናመስግን» ማለታቸው ነበር።

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ይጠራባቸው ከነበሩት ስሞች አንዳንዶቹና ትርጉማቸው ቀጥሉ ቀርቦአል። 

 • ኤል (ዘፍ. 35፡7):- የእግዚአብሔር መሠረታዊ ስሙ ሲሆን በእግዚአብሔር ኃይል ላይ ያተኩራል 
 • ኤሎሂም (ዘፍ. 1፡1):- እግዚአብሔር ፈጣሪና ገዥ፥ ኃይልን የተሞላ ግርማዊ ነው። ኤሎሂም በብሉይ ኪዳን በጣም ከታወቁት የእግዚአብሔር ስት አንዱ ነው።
 • ኤል ኤልዩን (ፍ. 14፡18):- እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወይም ከማንም ጋር መወዳደር የማይችል በአማልክት ሁሉ ላይ አምላክ ነው። 
 • ኤል ሻዳይ (ዘፍ. 17፡1):- እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ፥ ሉዓላዊ ገዥ 
 • ኤልሮኢ (ዘፍ. 16፡13):- እግዚአብሔር ሁሉን ያያል ከእርሱ የተሰወረ ነገር የለም 
 • ያህዌ (ጆሆቫ) (ዘፍ. 2፡4):- ልዩና ከሁሉም የበለጠ የተከበረ አይሁዳዊ ስም፥ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ስም ሲሆን ፍፁም ታማኝነቱንና የቃል ኪዳን አምላክነቱን ያሳያል። የእግዚአብሔርን የምሕረት፣ የጸጋና የፍቅር ባሕርይ ያካትታል። በብሉይ ኪዳን ከሚታወቁት የእግዚአብሔር ስሞች አንዱ ነው። 
 • ያህዌ ይርኤ (ፍጥ. 22፡14):- በእግዚአብሐር ተራራ ይታያል ማለት እግዚአብሔር ያዘጋጃል።
 • አዶናይ (ፍጥ. 15፡2፣ 8):- እግዚአብሔርን በግል ለማምለክ የሚውል ስም፣ የእግዚአብሔር ጌትነት፥ ታላቅ ባለ ግርማ አምላክ። 
 • አቢር ይስራኤል (ዘፍጥ. 49፡24):- እግዚአብሐር፥ የእስራኤል ኃያል፡፡ 

የውይይት ጥያቄ፥ አምልኮ፥ እግዚአብሔር ስላደረገው ነገር ብቻ ሳይሆን፥ ስለ ማንነቱም ማመስገን ማለት ነው። ከላይ የተዘረዘሩትን ስሞች በመጠቀም ስለማንነቱ እግዚአብሔርን በጸሎት አመስግነው። 

 1. የሰው ልጅ፡

የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ፍጥረት ቁንጮ መሆኑን ኦሪት ዘፍጥረት ያሳየናል። የሰው ልጅ በመጨረሻ የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረም ነው። ይህ አምሳል የሰው ልጅ በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት እጅግ የተበላሸ ቢሆንም፥ ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም። አሁንም የተፈጠርነው በእግዚአብሔር አምሳል ነው፤ ስለዚህ ይህ የሚያሳየው የሰው ልጅ የማያምን እንኳ ቢሆን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ዋጋ እንዳለውና በእኛም ዘንድ ይህ መታወቅ ያለበት እንደሆነ ነው።

እግዚአብሔር ለሰው ትክክለኛ የሆነውንና ያልሆነውን (ማለት ኃጢአትን የማድረግ፣ ያለማድረግ መብት) የመምረጥ ፈቃድ ሰጥቶታል። ሰው የመሆን አንዱ ክፍል የመምረጥ መብት ነው። ስለዚህ ሰው እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ የመምረጥ ፈቃድ አለው። ሰው ምርጫውን መቆጣጠር ቢችልም ውሳኔው የሚያስከትላቸውን ነገሮች ግን መቆጣጠር አይችልም። ለእግዚአብሔር መታዘዝ በረከትን ያስገኛል፤ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ደግሞ ፍርድን ያስከትላል። የሰው ልጅ ብዙ ጊዜ የሚያሳየው ባሕርይ አለመታዘዝ እንደሆነ ኦሪት ዘፍጥረት ያሳያል። የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ፍጡር ቢሆንም፥ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያለውን የአገዛዝ መብት ግን አልተቀበለም። ለእግዚአብሔር ላለመታዘዝ የመረጡ ሰዎች፥ የውሳኔያቸው ውጤት የሆነውን የእግዚአብሔርን ቅጣት እንደሚቀበሉ የተረጋገጠ ነው። አንድ ሰው እግዚአብሔርን መታዘዝ ከመረጠ፥ እርሱ ያከብረዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ይህ ጉዳይ የታየው እንዴት ነው? ለ) ዛሬስ በሕይወታችን የምናየው እንዴት ነው?

ሰዎች ሁሉ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፥ በኢስያ ከሚኖሩት ጀምሮ በአውሮፓ እስካሉት። በጣም ከተማሩት ጀምሮ እጅግ ኋላቀር እስከሆኑት ድረስ ያሉት ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ናቸው። በዚህ መሠረት ነው ክርስቲያኖች በግልጽ ዘረኝነትን፥ ባርያ ፍንገላንና ፅንስ ማስወረድን ስሕተት ነው የሚሉት። የሰው ልጅ ሁሉ አንድ ነው። የሰው ልጆች መጀመሪያ ከአንድ ሰው ከአዳም፥ በኋላም ከኖኅ ተገኙ። የሰው ልጅ ከየትኛውም ዘር ይሁን፥ የትም ይኑር፥ ምንም ያህል ይማር፥ ጾታው ምንም ይሁን የእግዚአብሔር አምሳል ነው። ማንኛውም የጎሰኝነትና የዘረኝነት አመለካከታችን የትዕቢታችንና የኃጢአታችን ውጤት ሲሆን፥ ሁላችንም አንድ እንደሆንን የሚናገረውን የኦሪት ዘፍጥረትን ትምህርት የሚቃረን ነው።

የቤተ ክርስቲያናችን አባሎች ጎሰኝነትን የመቃወም አቋም እንዲኖራቸው ይህንን ትምህርት እንዴት እንጠቀምበታለን? በኢትዮጵያ ውስጥ በዘረኝነት ወይም በጎሰኝነት ላይ የተመሰረተ ጥላቻ እንዴት ይታያል? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይህንን ለመቃወም ምን ማድረግ አለብን? 

 1. ኃጢአት፡

ሰዎች ፈጣሪያቸው በሆነው በእግዚአብሔር ሕግ ላይ የማመፃቸው ውጤት ኃጢአት ነው። ይህም በመጨረሻ ሥጋዊ ሞትን ያመጣል። ደግሞም የነፍስ ግድያን፥ የቤተሰብ አባላት መለያየትን፥ ዘረፋን፥ ስርቆትን፥ ሴትን አስገድዶ መድፈርን ወዘተ. ያስከትላል። አዳምና ሔዋን የሠሩት የመጀመሪያው ኃጢአት እጅግ አጥፊ የሆኑ ውጤቶች ነበሩት። በእግዚአብሔርና በሰው፥ በባልና በሚስት መካከል ጠላትነትን አመጣ። ሴትና የመውለድ ችሉታዋ፥ ወንድና ለቤተሰቡ ምግብ የማቅረብ አስፈላጊነት ሁሉ በአሉታዊ ተጽዕኖ ሥር ወደቁ። የሰው ልጅ ሁልጊዜ ከኃጢአት ጋር ይታገል ዘንድ የአዳምና የሔዋን የኃጢአት ባሕርይ ለልጆቻቸው ሁሉ ተላለፈ።

 1. ቃል ኪዳን፡

በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የሚደረግ ስምምነት ቃል ኪዳን ይባላል። ከሰው ጋር ቃል ኪዳን ለማድረግ ጀማሪ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔር እንጂ ሰው ስላይደለ ቃል ኪዳን የእግዚአብሔር ጸጋ ምልክት ነው። አንዳንድ ጊዜ ከእርሱ ጋር የቃል ኪዳን ተካፋይ ለሆኑ ሰዎች መመዘኛ ቢያበጅም፥ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ቃል ኪዳን የሚያደርገው በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ሳይመሠረት ነው። በታማኝነቱ ላይ የተመሠረተው ተስፋው እርሱ የመረጣቸውን ሰዎች ይመለከታል፤ ስለዚህ የቃል ኪዳኑ አካል የሆኑትን ሁሉ ይቅር በማለት በሕይወታቸው ፈቃዱን ለመፈጸም ያተጋል።

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ አራቱም የሃይማኖት ትምህርቶች እያንዳንዳቸው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት ምን ያስተምሩናል?

በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ስለ ክርስቶስ የተነገሩ ትንቢቶችና ተምሳሌቶች፡- በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ስለ ጌታ ኢየሱስ የተነገሩ በርካታ ትንቢቶችና ተምሳሌቶች አሉ።

 1. አዳም፡- አዳም የመጀመሪያው ሰው እንደመሆኑ መጠን ከእርሱ ለመጡት የሰው ልጆች ሁሉ ራስና ተወካይ ነው። ኢየሱስም በእምነት የእግዚአብሔር ልጆች ለሆኑትና ለሚሆኑት ሁሉ ራስና ተወካይ ነው (ሮሜ 5፡12-19 ተመልከት)።
 2. ዘፍጥ. 3፡15፡- ይህ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ነው። በሰይጣንና «በሴቲቱ ዘር» መካከል ስለሚኖረው ጦርነት ይተነብያል። ያ ዘር ማን ነው? በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑትን እስራኤላውያንን ዛሬ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል (ሮሜ 16፡20)። ከሁሉም ይልቅ ከሴት (ከማርያም) የተወለደውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል። ሰይጣን «ሰኮናውን ይቀጠቅጣል»። ይህም ሰይጣን ያነሣሣውን የኢየሱስ ክርቶስን የመስቀል ሞት የሚያመለክት ነው፤ ነገር ግን ኢየሱስ ራሱን ይቀጠቅጠዋል። ይህም የሰይጣንን መሸነፍና ሙሉ በሙሉ መጥፋት የሚያመለክት ነው (ራእ. 20፡1-10 ተመልከት)።
 3. እግዚአብሔር እንስሳት ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆኑበትን ተግባር ጀመረ (ዘፍጥ. 3፡21)። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ ስለ ዓለም ኃጢአት ሊከፍለው ያለውን መሥዋዕትነት የሚያሳይ ነው፤ (ዕብ. 9፡27-28)። 

የኖኅ መርከብ፡- በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ሁሉ እግዚአብሔር በጥፋት ውኃ አማካይነት ካመጣው ፍርድ እንደዳኑ ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት ደግሞ በመጨረሻው ቀን ለማያምኑ ሰዎች ከተጠበቀው ፍርድ ይድናሉ (1ኛ ጴጥ. 3፡20-21)።

 1. መልከ ጸዴቅ፡- መልከ ጸዴቅ፥ ሊቀ ካህንና ንጉሥ እንደ ነበር ሁሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስም ሊቀ ካህንና ንጉሥ ነው፤ (ዘፍጥ. 14፡18-20፤ ዕብ. 6፡20፤ 7)። 
 2. ይስሐቅ፡- ይስሐቅ ብቸኛው (ልዩ) የአብርሃም ልጅ እንደሆነ ሁሉ፥ ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልዩ ልጁ ነው። አብርሃም ይስሐቅን እንደሠዋ ሁሉ እግዚአብሔርም ኢየሱስን የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ይስሐቅ በፍጹም ፈቃደኝነት ራሱን ለመሥዋዕት እንዳዘጋጀ ሁሉ ኢየሱስም ራሱን የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።
 3. ዮሴፍ፡- ልክ ዮሴፍ ወደ ባርነት እንደተሸጠና ወገኖቹን ከራብ ሁሉ እንዳዳነ ኢየሱስም ለመሠዋትና ሕዝቡን ለማዳን ተሰጠ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘፍጥረት 25-36 የይስሐቅና የያዕቆብ ታሪክ

እስካሁን ድረስ በኦሪት ዘፍጥረት ጥናታችን ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉ ተመልክተናል። በመጀመሪያ፥ ከአይሁድ ሕዝብ አጀማመር በፊት ያሉትን ጊዜያት በአጭሩ የሚያካትተውን – ከዘፍጥ. 1-11 ያለውን ክፍል፥ በሁለተኛ፥ ደረጃ ደግሞ የአይሁድ ሕዝብ ራስ የሆነውን የአብርሃምን ታሪክ የሚያሳየውን – ከዘፍጥ. 12-24 ተመልክተናል። በተጨማሪ ለአብርሃም በተአምራት የተወለደለትን ይስሐቅ የተባለውን ልጁን ታሪክ መመልከት ጀምረናል።

ዛሬ ደግሞ የአብርሃም ልጅና የልጅ ልጅ ስለሆኑት ስላ ይስሐቅና ስለ ያዕቆብ መመልከት እንጀምራለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ከዘፍጥረት 25-36 ያለውን ክፍል አንብብ። ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ይስሐቅ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ለ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ያዕቆብ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ቃል ኪዳኑን አደጋ ላይ ጥለውት የነበሩት ነገሮች ምንድን ናቸው? መ) በእነዚህ ምዕራፎች እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ያስተላለፈውና የጠበቃቸው እንዴት ነው? ሠ) የዚህ ክፍል ዋና ዋና ትምህርቶችን ዘርዝር። ረ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር የምንማራቸውን አንዳንድ ነገሮች ጥቀስ። ሰ) ከእነዚህ ምዕራፎች በእምነት ስለ መራመድ የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ኦሪት ዘፍጥረት የአብርሃም ልጅ ስለሆነው ስለ ይስሐቅ ብዙ ነገሮችን አይነግረንም። እጅግ በጣም ታዛዥ ልጅ እንደነበረ የምናውቀው አብርሃም ሊሠዋው በነበረ ጊዜ በፈቃደኝነት በአባቱ ላይ በመታመን ሲታዘዝ በማየታችን ነው። የይስሐቅ ታሪክ ለያዕቆብ ታሪክ እንደመግቢያ ሆኖ የሚያገለግለን ነው። ያዕቆብ የ12ቱ የእስራኤል ነገዶች አባት በመሆኑ፥ ለአይሁድ ሕዝብ በጣም አስፈላጊ ሰው ነበር። ሙሴ፥ የአብርሃምን ታሪክ በመንገር የእስራኤልን ሕዝብ እንዴት እንደነበር ካሳየን በኋላ አሁን ደግሞ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች እንዴት እንደተመሠረቱ ሊጠቁመን ይጀምራል። የፔንታቱክ ታሪክ እምብርት እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በራሱ አነሣሽነት የመሠረተው ቃል ኪዳን መሆኑን አስታውስ።

ይስሐቅ

ከዘፍጥረት 25-36 ድረስ ቃል ኪዳኑ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረባቸውን የሚከተሉትን ሁኔታዎች ተመልከት፡

 1. ሌሎቹ የአብርሃም ልጆች ለይስሐቅ መተላለፍ የነበረበትን ቃል ኪዳን አደጋ ላይ ጥለውት ነበር። ቃል ኪዳኑ መተላለፍ ያለበት በተአምራት ለተወለደው በተስፋው ልጅ፥ ለይስሐቅ እንጂ ለሌሎቹ አልነበረም (ዘፍጥ. 25፡1-18)። አብርሃም ሌሎች ልጆችም ነበሩት። የአብርሃምና የአጋር የመጀመሪያ ልጅ እስማኤል ነበር። ለይስሐቅ የተሰጡት የቃል ኪዳን ተስፋዎች ችግር እንዳይገጥማቸው አብርሃም እስማኤልን አስቀድሞ ከቤቱ አስወጥቶት ነበር (ዘፍጥ. 21፡8-21)። ሁለተኛ፥ ከሣራ ሞት በኋላ አብርሃም ካገባት ኬጡራ ከምትባል ሴት የወለዳቸው 6 ወንዶች ልጆች ነበሩት። አብርሃም፥ ከመሞቱ በፊት ስጦታ በመስጠት እነዚህን ስድስት ልጆቹን አሰናበታቸው። ይህም በርስት ጉዳይ ከይስሐቅ ጋር እንዳይጣሉ ታስቦ የተደረገ ነው። 
 2. የይስሐቅ ልጅን ያለ መውለድ አደጋ፡- ይስሐቅ ቃል ኪዳኑን የሚያስተላልፍለትና ርስቱን የሚወርሰው ልጅ እንደማይኖረው ያስመሰሉ ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። በመጀመሪያ፥ እንደ ሣራ ሁሉ ርብቃም መካን ነበረች፤ ነገር ግን በኋላ እግዚአብሔር ዔሳውና ያዕቆብ የተባሉ ሁለት ልጆችን ሰጣት። ሆኖም እነዚህ ልጆች በሚወለዱበት ጊዜ እንኳ ሲጣሉ የነበሩና በሕይወታቸው ዘመንም ሁሉ እየተጣሉ የሚኖሩ ሆኑ። ከመወለዳቸው አስቀድሞ እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን መስመር የሚቀጥለው ሰው ታናሹ (ያዕቆብ) እንጂ ታላቁ (ዔሳው) አይሆንም በማለት ተንብዮ ነበር። እግዚአብሔር አሁንም ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ ከሕዝቡ ባሕልና ከወላጆቻቸው ፍላጎት ተቃራኒ በሆነ መንገድ ተጓዘ (ዘፍጥ. 25፡ 19-23)።

ሁለተኛው አደጋ ደግሞ ርብቃ የሌላ ሰው ሚስት ልትሆን ነበር (ዘፍጥ. 26)። የዘፍጥረት 26 ታሪክ ከዘፍጥ. 25፡19-21 በፊት የተፈጸመ ሳይሆን አይቀርም። አብርሃምና ይስሐቅ ተመሳሳይ ድክመት ነበራቸው። ይስሐቅም በባዕድ አገር በተገኘ ጊዜ እግዚአብሔር ሕይወቱን ሊጠብቅለት እንደሚችል ማመንና በእግዚአብሔር መደገፍ አቃተው። ይስሐቅ በፍልስጥኤማውያን ምድር ለመኖር ሄደ። ልክ እንደ አብርሃም የሚስቱን ማንነት ላለመናገር ዋሸ። ሣራ፥ ታራ ከሌላ ሴት የወለዳት የአብርሃም ግማሽ እኅቱ ስለነበረች፥ እኅቴ ናት ብሎ በከፊል ዋሽቶ ነበር። ይስሐቅ ግን ርብቃ የአጎቱ የልጅ ልጅ ስለነበረች እኅቴ ናት ብሎ ሲናገር ሙሉ በሙሉ ዋሸ። ርብቃ የሌላ ሰው ሚስት ትሆን ዘንድ ተወስዳ ቢሆን ኖሮ ይስሐቅ ቃል ኪዳኑን ሊያስተላልፍለት የሚችል አንዳችም ልጅ አይኖረውም ነበር። እግዚአብሔር ግን በዚህ ድርጊት መካከል ጣልቃ ገባና ርብቃን የሌላ ሰው ሚስት ከመሆን አዳናት።

የውይይት ጥያቄ፥ ስሕተት ብንሠራም እንኳ እግዚአብሔር እንደሚረዳንና የተስፋ ቃሉንም እንደሚጠብቅልን መገንዘባችን በዚህ ዘመን ላለን ለእኛ ምን ያህል ማበረታቻ ይሆነናል?

ዘፍጥ. 26 እጅግ ጠቃሚ ክፍል የሆነበት ሌላ ምክንያት አለ። በዘፍጥ. 26 ሁለት ስፍራዎች ላይ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን የተስፋ ቃል በማረጋገጥ፥ እነዚያው ተመሳሳይ ተስፋዎች ለይስሐቅ እንደተላለፉለት ያሳየዋል (ዘፍጥ. 26፡3-5፥ 23-24)። 

 1. የተስፋው ወራሽ የሆነው ያዕቆብ በዔሳው የመገደል አደጋ (ዘፍጥ.25፡19-34፥27፡1-4)፡- ያዕቆብና ዔሳው በሚወለዱበት ጊዜ ባሕርያቸው ተወስኖ ነበር። ያዕቆብና ዔሳው ሲወለዱ እንኳ እየተጋፉ ነበር የተወለዱት። ያዕቆብ የኖረው ልክ እንደስሙ ትርጉም ነው። ያዕቆብ ማለት «አታላይ» ወይም «አደናቃፊ» ማለት ነው። ያዕቆብ በሚወለድበት ጊዜ እንኳ የወንድሙን ተረከዝ ይዞ በመውጣት ሊያደናቅፈው ሞክሮ ነበር። በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለወጣለት ስም በመኖር ዔሳውን ኋላም ላባን ሲያታልልና ሲያደናቅፍ ኖሯል።

በጊዜው በነበረው ባሕል መሠረት ታላቁ ልጅ ዔሳው የይስሐቅ ወራሽ መሆን ነበረበት። በእግዚአብሔር ዓላማ መሠረት ግን ያዕቆብ ወራሽ ሆኗል። ያዕቆብ ወራሽ መሆኑን ያውቅ እንደ ነበር አንዳችም ጥርጥር የለም፤ ነገር ግን ያዕቆብ እግዚአብሔር ይህንን በረከት እስኪሰጠው ድረስ እንደመታገሥ የዔሳውን ብኩርናን ለመስረቅ ዓቀደ። በመጀመሪያ፥ ያዕቆብ የዔሳውን ራብ ተጠቅሞ በጥቂት ምግብ ብኩርናውን ማለትም የይስሐቅ ወራሽ የመሆን መብት ገዛ። ሁለተኛ፥ ዔሳውን መስሉ አባቱን በመቅረብ ለወንድሙ የሚገባውን በረከት በመረከብ የማታለል ተግባር ፈጸመ፤ (ዘፍጥ. 27)። በረከቱ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባለትን ቃል ኪዳን ሁሉ የመውረስ መብትን ይጨምራል። በረከቱን ለያዕቆብ መስጠት የእግዚአብሔር ዕቅድ መሆኑን ይስሐቅና ርብቃ ቢያውቁም፥ እርሱን ከመታዘዝና ከመደገፍ ይልቅ ይስሐቅ የብኩርና መብትን ለሚወደው ልጁ ለዔሳው ለመስጠት ሞከረ። ርብቃ ደግሞ ባሏ የሚታለልበትን መንገድ በማዘጋጀት የብኩርናውን መብት እርሷ ለምትወደው ልጇ- ለያዕቆብ ለማድረግ ፈለገች። እግዚአብሔር ግን ሁኔታዎቹን ሁሉ በመቆጣጠር የራሱ ዕቅድ እንደተፈጸመ አየ። በረከቱና የቃል ኪዳኑ በረከቶች በሙሉ ለያዕቆብ ተላለፉ።

የውይይት ጥያቄ፥ የወላጆች አንድ ልጃቸውን ከሌላው አስበልጠው መውደድ በቤተሰብ ውስጥ ሊፈጥር ስለሚችለው አደጋ ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል?

ዔሳው መታለሉን በተገነዘበ ጊዜ፥ ያዕቆብን ለመግደል ወሰነ። ይህም ነገር ያዕቆብ ከከነዓን ወደ ካራን እንዲሸሽ አደረገው። ከ20 ዓመት በኋላ ያዕቆብ ወደ ከነዓን ሲመለስ፥ ዔሳው እርሱን የመግደል አሳቡን ለመፈጸም ጥሩ አጋጣሚ ሆነለት። እግዚአብሔር ግን የዔሳውን ልብ ለወጠና ያዕቆብን እንደ ወንድም ተቀበለው፤ (ዘፍጥ. 33)። 

 1. ያዕቆብ በካራን ምድር በነበረበት ጊዜ የገጠመው አደጋ፡- የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንዳይፈጸም ዕንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት ዋና ዋና አደጋዎች ያዕቆብን በካራን ምድር ገጥመውት ነበር። የመጀመሪያው፥ ያዕቆብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ- ከነዓን እንዳይመለስ የከለከለው አደጋ ነበር፤ (ዘፍጥ. 28-30)። በካራን ምድር ባለጸጋ ሆነ። ያዕቆብ ከከነዓን ወደ ካራን በሚጓዝበት ጊዜ እግዚአብሔር በቤቴል ተገናኘው። በሕልሙም እግዚአብሔር ሁለት ነገሮችን አሳውቆት ነበር፡- 
 2. i) እግዚአብሔር በረከቱን የሚፈጽምለት በተስፋይቱ ምድር እንደሚሆን አስታወሰው። 2) የቃል ኪዳኑን በረከት አስቀድሞ ለአብርሃምና ለይስሐቅ እንደሰጠ አሁን ለያዕቆብ አስተላለፈለት፤ (ዘፍጥ. 28፡12-15)። በባዕድ አገር በሚኖርበት ጊዜም ከእርሱ ጋር እንደሚሆን በመንገር አበረታታው።

ያዕቆብ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይመለስ ሊያደርገው የሚችለው አደጋ ካራን በደረሰ ጊዜ እየጨመረ መጣ። በመጀመሪያ ለሁለቱ ሚስቶቹ – ለልያና ለራሔል ሲል 14 ዓመታት ተገዛ። ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለአማቹ ለላባ ቁሳቁሳዊ የሆነ ሀብትና ንብረት ለማስገኘት ብሎ ተጨማሪ 6 ዓመታት ተገዛ።

እግዚአብሔር ግን አታላዩን ያዕቆብን መለወጥ የጀመረው በካራን ምድር ነበር። ያዕቆብ ከእርሱ የባሰ አታላይ የሆነ አጎት አጋጠመው፥ እርሱም ላባ ነበር። እግዚአብሔር ሌላውን ሰው ለማጭበርበርና ቁሳቁሳዊ በረከት ለማግኘት የራስን ጥበብና የማታለል ዘዴ መጠቀም ከንቱ ጥረት መሆኑን ለያዕቆብ ለማሳየት ሲል ላባን ተጠቀመበት።

ከ12ቱ የያዕቆብ ልጆች 11ዱ የተወለዱት በካራን ነበር። ብንያም ግን የተወለደው ቆይቶ በከነዓን ምድር ነበር።

ሀ. የልያ ልጆች፡- ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሉን 

ለ. የራሔል አገልጋይ የሆነችው የባላ ልጆች፡- ዳን፥ ንፍታሌም 

ሐ. የልያ አገልጋይ የሆነችው የዘለፋ ልጆች፡- ጋድ፥ አሴር 

መ. የራሔል ልጆች፡- ዮሴፍ፥ ብንያም ናቸው።

** ማስታወሻ ) ራሔልና ልያ ከአገልጋዮቻቸው ልጅ ለማግኘት በጊዜያቸው የነበረውን ባሕል ተጠቅመዋል። የአገልጋዮቻቸው ልጆች በሕግም አንፃር እንደ ራሳቸው ልጆች ይቆጠሩ ነበር።

 1. ii) የራሔል የመጨረሻ ልጅ ብንያም ወደ ከነዓን በገቡ ጊዜ ተወለደ። ዳሩ ግን ለራሔል ሞት ምክንያት ሆነ። ራሔል ብንያምን በምትወልድበት ጊዜ ሞተች።

iii) ብሉይ ኪዳን አንድ ሰው ሊኖረው የሚገባው አንድ ሚስት ብቻ እንደሆነ በቀጥታ አያስተምርም ነበር። ነገር ግን አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ብቻ የሚፈጽመው ጋብቻ በሁለት ምክንያት ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያስተምረናል። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥር የሰጠው አንዲት ሴትን እንጂ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አይደለም። ሁለተኛ፥ ከአንድ በላይ ሚስቶች በሚኖሩበት ቤተሰብ ውስጥ ብዙ ጊዜ በሚስቶቹና በልጆቻቸው መካከል በሚፈጠር ቅንአት ምክንያት የማያቋርጥ ችግር ይከሰታል። በአዲስ ኪዳን ግን እግዚአብሔር በግልጥ ሕዝቡ አንድ ሚስት ብቻ እንዲኖራቸው አስተምሯል (1ኛ ጢሞ. 3፡2፥12)።

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትን በቀጥታ በመቃወም ለምን አልተናገረም? ለዚህ ምክንያቱ «በየጊዜው የሚሆን መገለጥ» ወይም «የገለጣ እድገት» ተብሎ የሚጠራው ነገር ነው። እግዚአብሔር ስለ ማንነቱ ከሰዎችም ምን እንደሚፈልግ ሁሉንም ነገር – በአንድ ጊዜ አልሰጠም። ነገር ግን በዘመናት ሁሉ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ቀስ በቀስ እየጨመረና እያደገ በሚሄድ እውቀት በትዕግሥት ገልጧል። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ትኩረት ሰጥቶ ይገልጠው የነበረው፡- ሊመለክ የሚገባው ብቸኛውና እውነተኛው አምላክ እርሱ ብቻ እንደሆነና ሕዝቡ ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩ ነበር። ቆይቶ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር አስቀድሞ አንድ ወንድ ከአንዲት ሚስት ጋር ብቻ እንዲኖር ያወጣውን ዕቅድ ይበልጥ ግልጥ አደረገው (1ኛ ጢሞ. 3፡2፥12)።

የውይይት ጥያቄ፥ የአሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች ስም በቃልህ አጥና። ከያዕቆብ ታሪክ ልጆችን ስለማሳደግ የምንማረው ነገር ምንድን ነው?

ያዕቆብ በካራን እያለ የገጠመው ሁለተኛ አደጋ ከላባና ከቤተሰቡ ጋር የገጠመው ጠላትነት ነበር። እግዚአብሔር ያዕቆብን በቁሳቁሳዊ ነገር – ስለባረከው ሀብታም ሆነ። ያዕቆብ እጅግ የተሳካለት ሰው ስለሆነ የሚስቶቹ ቤተሰቦች ቀኑበት። ላባም በያዕቆብ ድካም በመጠቀም ሊያጭበረብረው ሞከረ። በውጤቱም ያዕቆብ ላባን አጭበረበረው፤ የበለጡ ከብቶችንም አገኘ። በመጨረሻም ያዕቆብ ሕይወቱን ለማዳን መሸሽ ነበረበት። ላባም ያዕቆብን ሊይዘውና ሊገድለው ፈለገ። ዳሩ ግን ሁለቱ ሰዎች ከመገናኘታቸው በፊት ያዕቆብን እንዳይነካው እግዚአብሔር ላባን አስጠነቀቀው፤ (ዘፍጥ. 30፡25-31፡55)።

 1. ያዕቆብና ቤተሰቡን ከሴኬማውያን በኩል አጋጥሞአቸው የነበረው አደጋ (ዘፍጥ. 34)፡- ያዕቆብ ወደ ከነዓን በተመለሰ ጊዜ ከከነዓን ወጣ ብላ በምትገኝ ሴኬም በምትባል ከተማ ይኖር ጀመር። የዚያች ከተማ መሪ የነበረው ሰው ልጅ የያዕቆብን ሴት ልጅ ደፈራት። በምላሹ የያዕቆብ ልጆች ሴኬማውያንን አታለሉአቸውና በከተማው ውስጥ ያሉትን ወንዶች በሙሉ ገደሏቸው። ይህም የቀሩትን ከነዓናውያንን ቁጣ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ያዕቆብን አደጋ ላይ ጣለው። በዚህ ጊዜ የእስራኤላውያን ቤተሰብ ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር።

በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አስፈላጊ እውነቶች፡-

 1. ያዕቆብ ከእግዚአብሔር መልአክ ጋር ታገለ፤ (ዘፍጥ. 32፡22-3)። ያዕቆብ ከካራን ተመልሶ ከዔሳው ጋር ሊገናኝ ሲል በድንገት ከእግዚአብሔር መልአክ ጋር ተገናኘና ታገለ። ይህ መልአክ ባለፈው ሳምንት ያጠናነው ልዩ የእግዚአብሔር መልአክ ይመስላል። ለመጀመሪያ ጊዜ ያዕቆብ ከሥጋዊ በረከት ይልቅ መንፈሳዊ በረከትን ፈለገ። ለመጀመሪያ ጊዜ የበረከቱ ምንጭ የእርሱ ጥበብና ችሎታ ሳይሆን እግዚአብሔር መሆኑን አመነ። ከእግዚአብሔር ጋር የጀመረውን ይህን ግንኙነቱን ለማመልከት ስሙ «እስራኤል» ተብሎ ተለወጠ። እስራኤል ማለት «ከእግዚአብሔር ጋር የሚታገል» ማለት ነው። ይህ አዲስ ስም ቆይቶ የአይሁዳውያን ሁሉ መጠሪያ ሆነና ሕዝቡ እስራኤላውያን ተባሉ። ይህ ስም ለአይሁድ ሕዝብም የሚስማማ ነው። ምክንያቱም በአሉታዊ መልኩ በታሪካቸው ሁሉ አይሁድ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታገሉ፥ እግዚአብሔርን ለመከተልና ለመታዘዝ የማይፈልጉ በመሆናቸው ነው።። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የያዕቆብ ሕይወት ከአንተ የእምነት እርምጃ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) ከያዕቆብ ታሪክ ስለመንፈሳዊ ነገሮች የምንማረው ምንድን ነው?

 1. በኦሪት ዘፍጥረት የአጻጻፍ ባሕርይ መሠረት፥ ሙሴ የተመረጠውን የአይሁድን ሕዝብ ታሪክ ከመቀጠሉ በፊት ያልተመረጡትን የሌሉቹን ሕዝቦች የትውልድ ታሪክ ይተነትናል። ሙሴ የይስሐቅን ታሪክ ከመናገሩ በፊት የእስማኤልን የትውልድ ታሪክ እንደሰጠ ቀደም ሲል ተመልክተናል፤ (ዘፍጥ. 25፡12-18)። በዘፍጥ. 36 ደግሞ የይስሐቅ ሌላው ልጅ የሆነውን – የዔሳውን የትውልድ ታሪክ ይተነትናል። ከዚያም ቀጥሉ የዮሴፍን ታሪክ ይነግረናል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የአብርሃም ታሪክ (ዘፍጥረት 12-24)

ዛሬ የኦሪት ዘፍጥረትን ሁለተኛ ዋና ክፍል ማጥናት እንጀምራለን። ዘፍጥረት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚመደብ መመልከታችንን ታስታውሳለህ። ዘፍ. 1-11 የሚያተኩረው ከእስራኤል አባቶች በፊት በነበረው ዘመን ላይ ሲሆን፥ ዘፍ. 12-50 ደግሞ አራቱን የእስራኤል ዋና ዋና አባቶች ታሪክ ያሳየናል። እነርሱም፡- አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብና ዮሴፍ ናቸው። በዛሬው ትምህርታችን የአይሁድ ሕዝብና በእግዚአብሔር ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ሁሉ አባት የሆነውን የአብርሃምን ታሪክ እንመለከታለን። በዓለም ታሪክ ውስጥ እንደ አብርሃም እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። አይሁድም ሆኑ ዐረቦች ሁለቱም በሥጋ አባታችን አብርሃም ነው ይላሉ። እንዲሁም ክርስቲያኖችም አብርሃም መንፈሳዊ አባታችን ነው ይላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 12-24 አንብብ። ሀ) ከዘፍ. 12፡1-3) እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ የሰጠውን ሰባት በረከቶች ዘርዝር። ለ) በዘፍ. 15 እና 17 ወዘተ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ተጨማሪ የተስፋ ቃላት ዘርዝር። ሐ) እነዚህ ቃል ኪዳኖች በብሉይ ወይም በአዲስ ኪዳን የተፈጸሙት እንዴት ነው? መ) አብርሃም በሕይወት ዘመኑ የሄደባቸውን ከተማዎች ወይም ቦታዎች ዘርዝር። ሠ) የአብርሃምን ሕይወት በአጭሩ አጠቃለህ አቅርብ። በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እንዴት እንደገለጸ አስረዳ። በእምነት ስላልተራመደባቸው ጊዜያት ግለጥ ወዘተ። ረ) አብርሃም በእምነት የመኖር ጥሩ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው? ሰ) የራስህን የእምነት ጉዞ ከአብርሃም ሕይወት የእምነት ጉዞ ጋር አወዳድረህ የሚመሳሰልባቸውንና የሚለያይባቸውን ነገሮች ጥቀስ።

ዘፍጥረት 11ን ባጠናንበት ጊዜ ከአብርሃም ቤተሰብ ጋር ተዋውቀናል። የአብርሃም ታሪክ የሚጀምረው በመስጴጦምያ በዑር ከተማ ነው። ዑር በመስጴጦምያ ከሚገኙ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ስትሆን፥ የከፍተኛ ሥልጣኔ ማዕከልም ነበረች። ደግሞም ዑር የጣዖት አምልኮ ማዕከል ነበረች፤ ምክንያቱም ሰዎቹ የጨረቃን አምላክ ያመልኩ ነበርና ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢያሱ 24፡2-3 አንብብ። በእነዚህ ቁጥሮች በዑር ስለ ነበረው የአብርሃም ቤተሰብ ሃይማኖታዊ ሕይወት የተጻፈው ምንድን ነው?

ስለ አብርሃም ቤተሰብ ምንም የተለየ ነገር አልነበረም። በዑር እንደነበሩ ሰዎች የአብርሃም አባት ታራና ቤተሰቡም የጨረቃና የከዋክብት አማልክትን የሚያመልኩ ይመስላል። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሉዓላዊ በሆነው ምርጫው የሥልጣኔና የሃይማኖት ብልሹነት ይታይባት የነበረችውን የዑር ከተማ ትቶ ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ ወደሚጀምርበት ምድር እንዲሄድ አብርሃምን ጠራው።

የአብርሃምን ሕይወት ለመረዳት የኦሪት ዘፍጥረትን የመጀመሪያ ክፍል ማስታወስ አለብን። እግዚአብሔር የአሠራር መንገዱን የለወጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ከሰዎች ሁሉ ጋር በእኩልነት ከመሥራት ይልቅ ከአንድ ሰውና ከአንድ ሕዝብ ጋር ለመሥራት ለምን መረጠ? መልሱ ያለው በዘፍጥረት የመጀመሪያ 11 ምዕራፎች ውስጥ ነው።

በአብርሃም ዘመን የዓለም ሁሉ መሠረታዊ ባሕርይ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ እንደነበር ታስታውሳለህ። እንዲከተሉት ለማድረግ እግዚአብሔር ለብዙ ዓመታት ከሰዎች ሁሉ ጋር ለመሥራት ሞክሯል። አሁንም በቀረው የብሉይ ኪዳን ክፍል እግዚአብሔር ዘዴውን ለወጠ። እግዚአብሔር አንድ ሰውና አንድ አነስተኛ ሕዝብ ለዓለም ብርሃን እንዲሆኑ ወሰነ። እግዚአብሔር ከሰዎች ሁሉ ጋር ሊኖረው የሚፈልገውን ግንኙነት በምሳሌነት እንዲያሳዩ የተመረጡ ነበሩ። ሌሎች ሕዝቦች እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ያለውን ልዩ ኅብረት እንዲመለከቱና ይህ ኅብረት በመንፈሳዊና በሥጋዊ መንገድ የሚያስገኘውን ሽልማት (በረከት) እንዲያዩ ዐቅዶ ነበር። እነዚህ ሕዝቦች ይህን ኅብረት አይተው ከእግዚአብሔር ጋር ወዳለው ልዩ ኅብረት እንዲመጡ የእግዚአብሔር አሳብ ነበር። እስራኤላውያን በዓለም ላይ የእግዚአብሔር ተወካዮች ነበሩ።

የሚያሳዝነው ግን የብሉይ ኪዳን ታሪክ እስራኤል ይህን ኃላፊነቷን መፈጸም አቅቷት መውደቋን የሚያሳይ መሆኑ ነው። በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀች። ከዓለም ከመለየት ይልቅ እንደ ዓለም ተመላለሰች። እግዚአብሔር ዓለምን ለእርሱ ትማርክለት ዘንድ ያሰበውን ዕቅድ ልታሟላ ስላልቻለች፥ ሥራውን ከቤተ ክርስቲያን ጋር በሚሠራበት በአዲስ ኪዳን ዘመን ለጊዜው ገለል ተደረገች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለእስራኤል የነበረው ዓላማ ዛሬ እግዚአብሔር እኛ እንድሆን ከሚፈልገው ነገር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) እስራኤል በወደቀችበት መንገድ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ የምትወድቀው እንዴት ነው? ሐ) አንተና ቤተ ክርስቲያንህ በኅብረተሰቡ ውስጥ ይህንን ዓላማ የምታሟሉት እንዴት ነው?

በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር የግንኙነት መስመር ተለውጦአል። ከዓለም ጋር በስፋት አልሠራም። ከአንድ ሕዝብም ጋር አልሠራም። ይልቁን ከተለያዩ ሕዝቦች መካከል ራሳቸውን ከዓለም ከለዩ ሰዎች ጋር መሥራት ጀመረ። ይህችም ቤተ ክርስቲያን ናት። ክርስቲያኖች የእርሱ ብርሃን እንዲሆኑና ለዓለም እንዲመሰክሩ ነበር። በሕይወታቸው በሚታየው ለውጥ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥትና ቤተሰብ ሊስቡ ያስፈልግ ነበር። የእርሱ ልጆች ነን ብለን ከምናስበው፥ ከእኛ እግዚአብሔር የሚፈልገው ይህንን ነው። ይህንን ዓላማ ለሕይወታችን እያሳካን ነውን?

ሀ) ከላይ የተጠቀሰውን የቤተ ክርስቲያን ዓላማ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ የምታሟሉባቸውን መንገዶች ጥቀስ። ለ) የተሻለ «የዓለም ብርሃንና ጨው» (ማቴ. 5፡13-16) ለመሆን እንድትችሉ አሁን ከምትሠሩበት መንገድ በተለየ ሁኔታ ልታከናውኑ የምትችሏቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝሩ።

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ዑርን እንዲለቅ የጠራው ታራን ይሁን ወይም አብርሃምን የምናውቀው ነገር የለም። ጥሪው የመጣው ግን ለአብርሃም ሳይሆን አይቀርም። አብርሃምም በዕድሜ የገፋ አባቱንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን ከራሱ ጋር ይዞ ወጣ። የአብርሃም ወንድም የሆነው ናኮር ለጊዜው በዑር የቆየ ቢሆንም በኋላ ግን ወደኖረበት ወደ ካራን ሄደ። አብርሃምና ሣራ፥ ታራና ሎጥ ወደ ከነዓን ለመሄድ 1000 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ ወደ ካራን ከተማ ደረሱ። ወደ ከነዓን በሚወስደው መንገድ ላይ የነበረችው የመጨረሻዋ ዋና ከተማ ካራን ነበረች። ከግብፅ በመነሣት በከነዓን በኩል ወደ መስጴጦምያ በሚወስደው መንገድ ላይ ነበረች። ደግሞም የጨረቃ አምላክ የሚመለክባት ከተማ ነበረች። ታራ ምናልባት በእድሜ ስለገፋ፥ ወይም የለመደውን ባሕልና ሃይማኖትን ትቶ ለመሄድ ባለመፈለጉ ከአብርሃም ጋር በካራን ሰፈረ። በዚህ ስፍራ የኖሩት ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ አይታወቅም፤ ነገር ግን ከታራ ሞት በኋላ አብርሃም የእግዚአብሔርን ጥሪ እንደገና ተቀበለና ወደ ከነዓን ሄደ። 

የአብርሃም መጠራት 

ዘፍጥ. 12፡1-3 በመጽሐፍ ቅዱሳችን ከሚገኙ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ክፍሎች አንዱ ነው። በብሉይና በአዲስ ኪዳን የነበረው የእግዚአብሔር ዕቅድ የተሠራበት መሠረት ነው። በእግዚአብሔርና በአብርሃም መካከል ለተደረገው ቃል ኪዳንም መሠረት ነው። አብርሃም በሕይወት እስከ ኖረበት ዘመን ድረስ እግዚአብሔር በመጀመሪያ በሰጠው የተስፋ ቃል ላይ በየጊዜው ይጨመርለት ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አብርሃምን መጀመሪያ ሲጣራው የሰጠው ሰባት ተስፋዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙ ተስፋዎች ሁሉ መሠረት ናቸው። 

ከዚህ በታች እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባውን ሰባት የተስፋ ቃሎች እንዴት እንደፈጸመ እናያለን። 

ለአብርሃም የተሰጡ ተስፋዎች              የተስፋዎቹ መፈጸም 

«ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።»              የእስራኤል ሕዝብ

(«እባርክሃለሁ።»                             አብርሃም ባለጠጋ ሆነ።

«ስምህን አከብረዋለሁ፡፡»                  አይሁድ፥ ዐረቦችና ክርስቲያኖች ሁሉም አብርሃምን እንደ

                                                 አባታቸው ያከብሩታል።

«በረከትም ትሆናለህ።»                    በአብርሃምና በዘሩ መጽሐፍ ቅዱስ ተጻፈ፤ ጌታ ኢየሱስ

                                                ተወለደ፥ ድነት ወደ ዓለም መጣ።

(«የሚባርኩህን እባርካለሁ፡፡»)          በዘመናት ሁሉ አይሁድን የሚባርኩ ሰዎችንና መንግሥታትን

                                                እግዚአብሔር ባርኮአቸዋል።

«የሚረግሙህን እረግማለሁ።»           በመናት ሁሉ አይሁድን የሚያሳድዱ ሰዎችንና መንግሥታትን

                                                እግዚአብሔር በተራው አጥፍቷቸዋል። (ምሳሌ፡- ባቢሎን፣ አሦር) 

«የምድር ነገዶች ሁሉ ባንተ ይባረካሉ።» በአብርሃምና በዘሩ ዓለም ሁሉ ተባርኳል። ይህ በተለይ እውን የሆነው እግዚአብሔር እራሱን ለዓለም የገለጠው በአይሁድ በኩል ስለሆነና የዓለም ሁሉ አዳኙ ክርስተስ አይሁዳዊ ስለሆነ ነው።

እግዚአብሔር አብርሃምን ሲጠራው ይጠብቃቸው ዘንድ ሦስት ትእዛዛትን ሰጥቶታል፡- 1) የሚኖርበትን ምድር ትቶ ይወጣ ዘንድ፥ 2) የአባቱን ቤተሰብ ትቶ ይወጣ ዘንድ፥ 3) እግዚአብሔር ወደሚያሳየው ምድር ይሄድ ዘንድ ነበሩ። አብርሃም የለመደውንና የሚያውቀውን ነገር ሁሉ ትቶ ወደማያውቀውና እንግዳ ወደሆነ ስፍራ ለመሄድ ትልቅ የእምነት እርምጃ ወሰደ። አብርሃም ግን ይህንን ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ አልጠበቀም። የአባቱን ቤተሰብ ሁሉ ትቶ እንደመሄድ የወንድሙ ልጅ የሆነውን ሎጥን ይዞ ወጣ። አብርሃም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በከፊል መጠበቁ በኋላ በሕይወቱ ላይ ትልቅ ችግር አስከተለበት። ይህም የወንድሙ ልጅ የሆነው ሎጥ ከሌሎች ነገሥታት ጋር ወደ ጦርነት እንዲሄድ ያደረገው የቤተሰብ ክፍፍል ማስከተሉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር በከፊል ብቻ እንዴት ልንታዘዘው እንደምንችል ምሳሌ ስጥ።

የአብርሃም ሕይወት በምድር ላይ ለሚኖረን የእምነት ጉዞ ጥሩ ምሳሌ ነው። ማንም ሰው እግዚአብሔርን ፍጹም በሆነ መንገድ መታዘዝ አይችልም። በሕይወታችን ዘመን እግዚአብሔርን የምንታዘዝባቸው ጊዜያት እንዳሉ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ የማንታመንባቸውና ለእርሱ የማንታዘዝባቸው ጊዜያትም አሉ። ስለ አብርሃም ሕይወት በዘፍጥረት የጥናት መጽሐፍ ውስጥ የበለጠ ማጥናት ትችላለህ። ቀጥሉ ግን ልናስታውሳቸው የሚገባን አጠቃላይ ነገሮች ብቻ ቀርበዋል። 

፩. እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም በሰጠው ተስፋ በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ቃል ኪዳን ገባለት። 

ሀ. እግዚአብሔር ከግብፅ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ለአብርሃምና ለዘሩ እንደሚሰጥ ቃል ገባለት፤ (ዘፍጥ. 15፡ 18)።

ለ. እግዚአብሔር አብርሃምን የብዙ ሕዝብ አባት፥ ሣራን ደግሞ የብዙ ሕዝብ እናት አደርጋችኋለሁ አላቸው፤ (ዘፍጥ. 17፡5፥ 15-16)። እግዚአብሔር፥ «ታላቅ አባት» የሚል ትርጉም የነበረውን አብራም የሚለውን የመጀመሪያ ስሙን «የብዙ ሕዝብ አባት» የሚል ትርጉም ወዳለው ወደ አብርሃም ቀየረው። የሚስቱንም ስም ከሦራ ወደ ሣራ ቀየረው። ትርጉሙም «ልዕልት» ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሰውን ስም ሲቀይር፥ ሰው ከእርሱ ጋር አዲስ ግንኙነት ጀመረ ማለት ነው። 

ሐ. እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ለማድረግ የተለመደውን ባሕላዊ መንገድ በመጠቀም ማረጋገጫ ሰጠ (ዘፍጥ. 15)። በጥንት ዘመን ሰዎች ሃይማኖታዊ በሆነ ወይም በሌላ ሥነ-ሥርዓት ቃል ኪዳን ወይም ስምምነት ሲያደርጉ አንድ እንስሳን በማረድ ሥጋውን በትክክል ሁለት ቦታ ቅርጫ ይከፍሉት ነበር። ከዚያ በኋላ ቃል ኪዳኑን የፈጸሙት ሁለት ወገኖች በተከፋፈሉት ቅርጫ መሃል ይራመዱ ነበር። ይህን የሚያደርጉትም የቃል ኪዳን ስምምነታቸውን ቢያጥፉ፥ እነርሱም እንዲገደሉ መስማማታቸውን ለመግለጽ ነበር። አብርሃም ያንን በግልጽ በማየት በእምነቱ ይበረታ ዘንድ፥ እግዚአብሔር የተለመደ ቃል ኪዳን ምልክት ሰጠው፤ ነገር ግን አንድን ነገር ማስተዋል አስፈላጊ ነው። በቃል ኪዳን ምልክት ማድረጊያው መካከል የተረማመደው እግዚአብሔር ብቻ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ይህ ቃል ኪዳን በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አልነበረምና ነው። ይህንን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ አብርሃም እንዲያደርገው የተጠየቀው አንዳችም ነገር አልነበረም። ይልቁንም የቃል ኪዳኑ መፈጸም የተመሠረተው እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ በመጠበቁ ላይ ነበር። 

መ. ነገሥታት ከአብርሃም ዝርያ እንደሚነሡ እግዚአብሔር ተስፋ ሰጥቶ ነበር፤ (ዘፍጥ. 17፡6)። ይህም የሚያመለክተው ዳዊትንና ልጆቹን በተለይ ደግሞ ለአብርሃም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነበር።

ሠ. እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለአይሁድ በአጠቃላይ ከእርሱ ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት የሚታይ ምልክት ሰጣቸው (ዘፍጥ. 17)። ይህ ምልክት የእያንዳንዱ ወንድ ልጅ መገረዝ ነበር። በሥጋ አይሁድ የሆነ ማንኛውም ሰው አልገረዝም ቢል በእግዚአብሔርና በአብርሃም ልጆች መካከል በተደረገው ቃል ኪዳን አይታቀፍም ማለት ነው፤ ስለዚህም የአብርሃም እምነት ስላልነበረው እውነተኛ አይሁዳዊ አልነበረም ማለት ነው። 

፪. አብርሃምን ያጋጠመው አደጋ የቃል ኪዳኑን መፈጸም ሊያሰናክለው የሚችል ነበር

ሀ. የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ የፈጠረው አደጋ። 

 1. የአብርሃም ብቸኛ ዘመድ የሆነው ሎጥ ወራሹ ነበር (ዘፍጥ. 13-14)፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ የአብርሃምን ርስት የራሱ ልጅ እንዲወርሰው ነበር። ቃል ኪዳኑ በሎጥ ምክንያት በሁለት መንገዶች አደጋ ላይ ወድቋል። በመጀመሪያ፥ ሎጥ የአብርሃም ወራሽ ነበር። የአብርሃም ርስት ልጁ ወዳልሆነው ወደ ሌላ ሰው ያልፋልን? አብርሃም ልጅ ቢኖረውም እንኳ ወራሹ ማን ይሆናል በሚለው ጥያቄ ውስጥ አከራካሪ ነገር ሊኖር ይችላልን? ነገር ግን ሎጥ የተስፋይቱን ምድር በተወ ጊዜ የአብርሃም ወራሽ የመሆኑ ነገር ቀረ። ሁለተኛው እግዚአብሔር እንደሚያወርሰው ለአብርሃም ተስፋ ሰጥቶት ነበር። ሎጥ የከነዓንን ምድር ለመውረስ ይመርጣልን? ሎጥ የፈለገው ምቹ የሆነ ምድርን ነበር። ከሁሉ የተሻለውን ምድር ለአጎቱ ለአብርሃም ሊለቅለት ሲገባ፥ እጅግ በጣም ጥሩ የመሰለውን ነገር ግን፥ እጅግ ክፉ የነበረውን የሰዶምን ምድር መረጠ። ስለዚህ ሎጥ የተስፋይቱን ምድር ከነዓንን ተወ። በራስ ወዳድነት ያደረገው ምርጫ ከእግዚአብሔር የበረከት ስፍራ ውጭ አደረገው። ለሁለተኛ ጊዜ እግዚአብሔር የከነዓንን ምድር ለአብርሃም ቃል ገባለት። ደግሞም ዝርያዎቹ ሊቆጠሩ እስከማይችሉ ድረስ እንደሚበዙ ተስፋ ሰጠው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሥጋዊ ክርስቲያን መላ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር አስገዝቶ አልኖርም በሚልበት ጊዜ የሚመርጠው ምርጫ ከሎጥ ምርጫ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? 

 1. ሎጥ በሰዶም ሲኖር ሳለ በሰሜን ነገሥታት ተማረከና ቃል ኪዳኑን አደጋ ላይ ጣለው። በአብርሃም ዘመን፥ በከነዓን ምድር በርካታ የከተማ መንግሥታት ነበሩ። ገናና የሆነችው ከተማም በአካባቢዋ ያለውን ምድር ሁሉ ትማርክና በማስገበር ትገዛ ነበር። የዚያች ከተማ መሪም ንጉሥ ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህ ታሪክ በተፈጸመ ጊዜ ሎጥ ወደ ሰዶም ምድር ተንቀሳቀሰ። በመሐሉ በሙት ባሕር በስተደቡብ መጨረሻ አካባቢ እንደ ነበሩ በሚገመቱ በሰዶምና ገሞራ ከተሞችና በኤላም፥ በጎኢምና እላሳር (በመስጴጦምያ የሚገኙ) ከተሞች መካከል በተደረገው ትግል ሎጥም ተማርኮ ተወሰደ። በዚህ ጊዜ ሰዶምና ገሞራ በሰሜን ነገሥታት እጅ የወደቁ ቢሆንም ዓምፀው ግብር አንከፍልም አሉ፤ ስለዚህ የሰሜን ነገሥታት የደቡብ ነገሥታትን ለመቅጣት መጡ። ደቡቦቹ ተሸነፉና ሎጥን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በምርኮ ተወሰዱ። አብርሃምም የወንድሙ ልጅ መማረኩን በሰማ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎችን በሙሉ (318 ወንዶች)፥ በከነዓን ምድር ከሚኖሩ አንዳንድ መሪዎች ጋር ይዞ ሄዶ የሰሜን ነገሥታትን በማጥቃት አሸነፋቸው። አብርሃም እነዚህን ነገሥታት ለመውጋት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጓዘ። ሎጥን ለማዳን ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ጣለ። ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም በኩል ሊጀምረው የነበረውን የተመረጠ ሕዝብን የማዘጋጀት ዕቅድ ሊያበላሽ ይችል ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አብርሃምን ጠብቆ ድልን አጎናጸፈው። 

የውይይት ጥያቄ ፥ ሎጥ ከአብርሃም ምርጥ የሆነውን መሬት ቢወሰድበትም አብርሃም ቸር ነበር። ከዚህ ምን እንማራለን?

ሙሴ ይህንን ታሪክ ለምን ጻፈው? የሎጥን የሞኝነት ምርጫ በማሳየት፥ ራስ ወዳድነት ክርስቲያንን እንዴት ችግር ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ለማሳየት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪ ወደ ከነዓን ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉትን እስራኤላውያንን ለማበረታታትም ሊሆን ይችላል። አብርሃም ከእርሱ ጋር የነበሩት ጥቂት ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለነበር ታላቅ ኃይልን ለማሸነፍ ቻለ። እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር ሊገቡ በተዘጋጁ ጊዜ ቁጥራቸው ከጠላቶቻቸው ቁጥር ያነሰ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለሆነ በቁጥር እጅግ ጥቂት ቢሆኑም እንኳ በርካታ የሆኑትን የእግዚአብሔር ጠላቶቻችን አሸንፈዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ በጠላቶቻቸው ብዛት የተዋጡት ክርስቲያኖች ይህ እንዴት ያበረታታቸዋል? 

 1. የሎጥ በሰዶምና ገሞራ ላይ ከመጣው ፍርድ ማምለጥ በቃል ኪዳኑ ላይ ትልቅ አደጋ ሊፈጥር የሚችል ነበር፤ (ዘፍጥ. 18-19)። ሎጥ የሰዶምን ኑሮ ስለወደደ ወደ ከተማይቱ ገባ። እግዚአብሔር በከተማይቱ ላይ በመፍረድ ሊያጠፋት ባሰበ ጊዜ ወደ ወዳጁ ወደ አብርሃም በመምጣት ዕቅዱን ገለጠለት (ዘፍጥ. 18)። አብርሃም ስለ ከተማይቱ እግዚአብሔርን አጥብቆ ለመነ፤ ነገር ግን አሥር ጻድቃን እንኳ ስላልተገኙባት እግዚአብሔር ከተማይቱን አጠፋት። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ለአብርሃም ብሉ ሎጥንና ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን አዳናቸው። ሎጥ ወደ ከነዓን ተመልሶ የአብርሃም ወራሽ ሆነን? የለም፤ ሎጥ ወደ ከነዓን ከመመለስ ይልቅ በዋሻ ውስጥ መኖርን መርጦ እምቢ አለ።

የሎጥ ታሪክ ለሥጋዊ ክርስቲያን ጥሩ ምሳሌ ነው። ሎጥ ከአብርሃም ጋር በሰላም ቢኖር ኖሮ ከአብርሃም ጋር የእግዚአብሔርን የበረከት ፍሬ በሙሉ በተካፈለ ነበር። በረከቶቹ ግን በአብርሃምና በሎጥ መካከል አለመስማማትን አስከተሉ። በረከቶቹ ወደ ራስ ወዳድነት መሩት። ሎጥ ለሥጋዊና ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ከምድሪቱ ምርጥ ነው ብሉ ያሰበውን ነገር መረጠ። ይህ ምርጫው በነገሥታት እንዲማረክ፥ በመጨረሻም ሚስቱን፥ ንብረቱንና ሀብቱን ሁሉ እንዲያጣ ምክንያት እንደሚሆን አልተገነዘበም። ከሴት ልጆቹ ጋር ኃጢአት በማድረግ የእግዚአብሔርና የእስራኤላውያን ጠላቶች የሆኑ ሕዝቦች የተገኙባቸውን ልጆች ወለደ። የሎጥ ልጆች የሆኑት ሞዓብና ዓሞን፥ ሞዓባውያንና ዓሞናውያን የተባሉ ሁለት ሕዝቦች ሲሆኑ እነርሱም በብሉይ ኪዳን ዘመን ከእስራኤላውያን ጋር ያለማቋረጥ ይዋጉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔርን ደስ እያሰኙ ከመኖር ይልቅ እራሳችንን ደስ እያሰኘን የመኖርን ውጤት ምንነት ከሎጥ ታሪክ ምን እንማራለን?

ለ. የአብርሃም ሎሌ ኤሊዔዘር በቃል ኪዳኑ ፍጻሜ ላይ የፈጠረው አደጋ፡- (ዘፍጥረት 15) 

በጥንት ዘመን አንድ ሰው ምንም ልጆች ከሌሉት ከሎሌዎቹ አንዱን ወራሽ አድርጎ ይሾመው ነበር። አብርሃም ለዚህ ጉዳይ የሾመው ተወዳጅ አገልጋዩ የነበረውን የደማስቆውን ሰው ኤሊዔዘርን ሳይሆን አይቀርም። የአብርሃም ፍላጎት ግን ከጉልበቱ የወጣው ልጁ እንዲወርሰው ነበር።

ከአብርሃም ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊው ክፍል ዘፍጥረት 15 ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን አደሰ። እጅግ ጠቃሚ በሆነው በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

 1. እግዚአብሔር ለአብርሃም በርካታ ተስፋዎችን በመስጠት ቃል ኪዳኑን ጀመረ።

ሀ. እግዚአብሔር ለአብርሃም ልጆቹ በሰማይ እንዳሉ ከዋክብት እንደሚበዙ የተስፋ ቃል ገባለት። 

ለ. ከግብፅ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለው የከነዓን ምድር በሙሉ ለአብርሃም ዝርያዎች ተሰጠ። 

 1. አብርሃም ለእግዚአብሔር በእምነት መልስ ሰጠ። ዘፍጥ. 15፡6 እንዲህ ይላል፡- «አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት።» አብርሃም የዳነው እንዴት ነበር? አንዳንድ ታላላቅ ነገሮችን ስላደረገ ነውን? ስለተገረዘ ነውን? አይደለም። እግዚአብሔር አብርሃምን የተቀበለውና ጻድቅ ብሎ የጠራው የገባውን የተስፋ ቃሉን ስላመነ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ለድነት (ደኅንነት) ከሚፈለግብን ነገር ጋር ይህ እንዴት ይመሳሰላል? (ሮሜ 4፡1-25 ተመልከት)።

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን የአብርሃምን እምነት በመውሰድ፥ እኛም የምንድነው ወይም ጻድቃን ተብለን የምንቆጠረው በምንሠራው መልካም ሥራ (ለድሆች በመስጠት፥ ባለመጠጣት፥ ዝሙትን ባለማድረግ ወዘተ) ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ብቻ እንደሆነ ለመግለጽ ተጠቅሞበታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትምህርት ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገባው በምንሠራችው መልካም ተግባራት፥ ማለትም በጥምቀት፥ ለድሆች በመስጠት፥ በመጾም ወዘተ ነው ብለው ከሚያስተምሩ ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው?

፫. እግዚአብሔር ስለ አብርሃም ዝርያዎች የወደፊት ጉዳይ ተንብዮአል።

እግዚአብሔር እስራኤላውያን ወደፊት መጻተኞች እንደሚሆኑ (በተስፋ የእነርሱ ብትሆንም እንኳ በከነዓን ውስጥ ምድር እንደማይኖራችው) እና ለ400 ዓመታት በባርነት እንደሚቆዩ ለአብርሃም ተናገረ። በሙሴ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ይህንን ትንቢት በማወቃቸው ይበረታቱ ነበር፤ ምክንያቱም 400 ዓመታት እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ቆጥረው ለመድረስ ይችሉ ነበር።

** (ማስታወሻ፡- እግዚአብሔር አሞራውያን የኃጢአታቸው ጽዋ ስላልሞላ በጸጋው የንስሐ ጊዜ እንደሰጣቸው ይናገር ነበር። አሞራውያን ከኃጢአታችው ይመለሱ ዘንድ እግዚአብሔር ለ400 ዓመታት በትዕግሥት ጠበቃቸው። አሞራውያን የከነዓናውያን ሌላ ስም ነው። እነርሱ ግን ከመመለስ ፈንታ በክፋታቸው እጅግ እየባሱ ሄዱ። ስለዚህ በመጽሐፈ ኢያሱ የእግዚአብሔር ፍርድ በአሞራውያን ላይ ይፈጸም ዘንድ እስራኤላውያን መሣሪያ ሆኑ። ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፏቸውም ታዘዙ።)

ሐ. በቃል ኪዳኑ ፍጻሜ ላይ እስማኤል የፈጠረው አደጋ፡- (ዘፍጥ.16፤ 21፡8-21)

ከአብርሃምና ከባሪያይቱ ከአጋር የተወለደው እስማኤል እግዚአብሔር ከአብርሃምና ከሣራ ሊያስገኘው ያቀደውን ተአምራዊ ልጅ የመወለድ ዕቅድ ሊያበላሸው ነበር። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ የሚሠራ መሆኑን በማመን ፈንታ አብርሃም በራሱ መንገድ የራሱን ልጅ በማዘጋጀት እግዚአብሔርን ሊረዳው ሞከረ። በዚያን ዘመን ሰው ከገዛ ሚስቱ ልጅ ማግኘት ካልቻለ ባሪያውን በመገናኘት ልጅ ይወልድ ነበር። በዚህ ዓይነት የተገኘውም ልጅ የልጅነት ሙሉ መብት በማግኘት ወራሽ ይሆን ነበር። አብርሃም ይህ ድርጊቱ የሚያስከትልበትን ኃዘን አልተገነዘበም ነበር። በቤቱ ውስጥ በሣራና በአጋር መካከል ጠብን ፈጠረ። ይህም ማለት የሚወደውን ልጁን እስማኤልን ከቤት ማባረር ነበረበት ማለት ነው። በኋላም በታሪክ እንደምናገኘው፥ የእስማኤል ዝርያዎች የሆኑት ዐረቦች፥ የአብርሃም ልጅ፥ የይስሐቅ ዝርያዎች የሆኑት የአይሁድ ክፉ ጠላቶች ሆኑ።

የውይይት ጥያቄ፥ የራሳችንን አሳብ ወይም መንገድ በመጠቀምና አንድ ነገር በማድረግ እግዚአብሔርን ለመርዳት ስለመሞከር ይህ ምን ያስተምረናል?

መ. አብርሃም እግዚአብሔር ሕይወቱን ለመጠበቅ እንደሚችል አላምንም በማለቱ በቃል ኪዳኑ ላይ የተፈጠረ አደጋ፡-

አብርሃም ታላቅ የእምነት ሰው ቢሆንም፥ ሊወጣው ያልቻለው ደካማ ነጥብ በሕይወቱ ነበር። ይህም ደካማ ነጥብ እግዚአብሔር ሕይወቱን እንደሚጠብቅ ሊታመንበት አለመቻሉ ነበር። በመጀመሪያ አብርሃምና ሣራ ወደ ግብፅ በወረዱ ጊዜ የተፈጸመ ታሪክ ነው (ዘፍጥ. 12፡ 10-20)። አብርሃም ወደ ግብፅ ይወርድ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለመጠየቁ ምንም ማረጋገጫ የለንም። በእግዚአብሔር ላይ እምነት በማጣቱ ሕይወቱን ለመጠበቅ በከፊል ሲዋሽ እናየዋለን። ሣራን ለማግባት ሲሉ ይገድሉኛል ብሎ ስለፈራ ለግብፃውያን እኅቱ እንደሆነች ነገራቸው። ሣራ የአብርሃም አባት ከሌላ ሚስት የወለዳት ስለ ነበረች (ዘፍ. 20፡12) ይህ ማለቱ በከፊል እውነት ነው። ሣራ ሚስት እንድትሆነው ወደ ፈርዖን ቤት ተወሰደች። ይህ የሚያሳየው አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ እምነት ማጣቱን ብቻ ሳይሆን፥ ቃል ኪዳኑን አደጋ ላይ እንደጣለው ነው። ፈርዖን ሣራን በሚስትነት ቢያስቀራት ኖሮ ለአብርሃም ከሣራ የሚገኝ ልጅና ሕዝብ ሊኖር አይችልም ነበር። እግዚአብሔር በዚህ መካከል ጣልቃ ሊገባና ሣራን ከፈርዖን እጅ ሊያድናት ይገባ ነበር። ይህም አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ እምነት ያልጣለበት የመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

ከብዙ ዓመታት በኋላ፥ አብርሃም በጌራራ ንጉሥ በአቤሜሌክ ፊት ይህንኑ ስሕተት ደገመው (ዘፍጥ. 20)። አብርሃም ስሕተቱን የሠራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሣራ ልጅ እንደሚያገኝ እግዚአብሔር ቃል ከገባለት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነበር። ይስሐቅ ከመወለዱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሰይጣን ወደ አብርሃም ያመጣው ፈተና ነበር። ወደ ጌራራ ንጉሥ ዘንድ በሄደ ጊዜ ሣራ እኅቱ መሆንዋን ለሰዎቹ ነገራቸው። ይህም ንጉሡ ሣራን ሚስቱ አድርጎ ሊወስዳት ፈለገ። እግዚአብሔር ሣራ የአብርሃም ሚስት መሆንዋን ለንጉሡ በመንገርና በማስጠንቀቅ ቃል ኪዳኑን ከአደጋ ጠበቀው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬስ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን በእርሱ በማመን ፈንታ፥ የራሳችንን ሕይወት ወይም ፍላጎታችንን ለመጠበቅ በመሞከር እነዚህን የመሰሉ ተመሳሳይ ፈተናዎች እንዴት እንጋፈጣቸዋለን?

ሠ. ለወራሹ፥ ለይስሐቅ ተገቢ የሆነች ሚስት ያለማግኘት አደጋ፥ (ዘፍጥ. 24) የአብርሃም የዘር ሐረግ እንዲቀጥል ይስሐቅ ሊያገባና ልጆችን ሊወልድ ይገባው ነበር፤ ነገር ግን ከአብርሃም አጠገብ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ሁሉ በአንዱ እውነተኛ አምላክ የማያምኑ ከነዓናውያን ነበሩ፤ ስለዚህ ይስሐቅ በካራን ካሉ ዘመዶቹ ዘንድ ማግኘት ነበረበት። ምናልባት ይስሐቅ የካራንን ምድር ወዶ ሊቀር ይችላል የሚል ፍርሃት ስለ ነበረው አብርሃም ይስሐቅን ወደዚያ መላክ አልፈለገም። በሌላ በኩል ደግሞ በሰለጠነ ከተማ (በካራ) የኖረች ሴት፥ የነበረችበትን አገር ትታ የማታውቀውን ሰው ለማግባት በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዛ ትመጣለች ብሎ ማሰብም የሚያጠራጥር ነበር፤ ነገር ግን አብርሃም እግዚአብሔር ለልጁ ለይስሐቅ ትክክለኛዋን ሚስት ሊሰጠው እንደሚችል አመነ። አብርሃም አገልጋዩን ላከ፤ እግዚአብሔር ሥራውን ስለ ሠራ ርብቃ ወደ ከነዓን ለመምጣትና የይስሐቅ ሚስት ለመሆን ተስማማች።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይስሐቅ የማታምን ሴት እንዳያገባ አብርሃም ያደረገው ጥንቃቄ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) የገዛ ሚስቶቻችንንም ሆነ የልጆቻችንን ሚስቶች በጥንቃቄ ስለመምረጥ ይህ ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው? ሐ) የማይቻል በሚመስል ሁኔታ ውስጥ እንኳ እግዚአብሔር ትክክለኛ የትዳር ጓደኛ ሊሰጠን ስለመቻሉ ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል?

በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች በርካታ ታሪኮችም አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌት የሆኑ ሁለት ታሪኮች አሉ፡-

 1. አብርሃም፥ የወንድሙን ልጅ ሎጥን ማርከው ወስደው የነበሩትን የሰሜን ነገሥታት አሸንፎ በሚመለስበት ጊዜ ከአንድ ልዩ ሰው ጋር ተገናኝቶ ነበር። ይህ ሰው በኋላ ኢየሩሳሌም የተባለችው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ ነበር። አብርሃም ከጦርነቱ ምርኮ ከሆነው ሁሉ አንድ አሥረኛውን (አሥራት) ለዚህ ንጉሥ ሰጠው። ንጉሡም አብርሃምን ባረከው አከበረውም፤ (ዘፍጥ. 14፡17-24)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 6፡20-7፡24 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች መልከ ጼዴቅን ይመስላል የተባለለት ማን ነው? ለ) ከመልከ ጼዴቅ ጋር የሚመሳሰለው በምንድን ነው? 

ስለ መልከ ጼዴቅ የምናውቀው ብዙ ነግር ባይኖርም፥ ወደ ዕብራውያን ሰዎች የተላከው መልእክት እርሱ የክርስቶስ ተምሳሌት ነው ይላል። «ተምሳሌት» በመጽሐፍ ቅዱሳችን የሚሰጠው ትርጉም አንድ የተለየ ድርጊት ወይም ሰው ወደፊት ስለሚመጣ ሰው ወይም ስለሚፈጸም ድርጊት ግልጽ የሆነ ምሳሌነት የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ፡- የእስራኤል ሕዝብ ከግብፅ ነፃ የመውጣት ታሪክ ከኃጢአት ነፃ የመውጣት ምሳሌ ነው። አዳም የሁለተኛው አዳም፥ የክርስቶስ ምሳሌ ነው (ሮሜ 5፡14)። በዚሁ ዓይነት፥ መልከ ጼዴቅም የሊቀ ካህናችን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌት ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መልከ ጸዴቅ ንጉሥም ሊቀ ካህንም ነው። መልከ ጼዴቅ ልክ እንደማንኛችንም ሰው በመሆኑ፥ የተወለደና የሞተ ቢሆንም፥ መቼ እንደተወለደና መቼ እንደሞተ ኦሪት ዘፍጥረት የሚያመለክተው አንዳችም ነገር የለም። ኢየሱስ ክርስቶስም፥ እንደ እግዚአብሔር ልጅ መጀመሪያና መጨረሻ የለውም። እርሱና የሊቀ ካህንነቱ ሥራ ዘላለማዊ ነው።

 1. ይስሐቅ የ15 ዓመት ወጣት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር አብርሃምን ከእርሱና ከልጁ የላቀ ማንን እንደሚወድ ለማረጋገጥ ፈተነው። አንድ ልጁን ይዞ በሞርያም ተራራ እንዲሠዋለት እግዚአብሔር አብርሃምን አዘዘው (ዘፍ. 22) 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለአብርሃም ይህንን ፈተና የሰጠው ለምን ይመስልሃል? ለ) ዛሬም ለእኛ ሊሰጠን የሚችለውን ተመሳሳይ የፈተና ዓይነት ጥቀስ።

አብርሃም ይህን ፈተና አልፎአል። ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጉዞ ወደ ሞርያም ተራራ በደረሰና ልጁን ለመሠዋት ቢላውን ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር በይስሐቅ ምትክ የሚሠዋ በግ ሰጠው።

ይህ በብዙ መንገድ የክርስቶስ ኢየሱስ ተምሳሌት ነው። ይስሐቅ የአብርሃም ብቸኛ ወይም ልዩ ልጅ እንደሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ ነው፤ (ዮሐ. 3፡16)። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ይሠዋ ዘንድ እንደሰጠ፥ እግዚአብሔር አብም ልጁን ኢየሱስን ለዓለም ኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ። ይህም ቢሆን እንኳ በሁለቱ ታሪኮች መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። እግዚአብሔር አብርሃምን፥ ልጁን እንዲሠዋ የከለከለው ሲሆን፥ የገዛ ልጁ በመስቀል ላይ እንዲሞት ግን ፈቅዷል። አብርሃም ልጁን ለመሠዋት የወሰደው ወደ ሞርያም ማለትም ወደ ጽዮን ተራራ ሲሆን፥ ኢየሱስ ለኃጢአታችን የሞተውም በሞርያም ወይም በጽዮን ተራራ ነው። ይስሐቅ ወጣት ልጅ እንደመሆኑ መጠን አባቱ መሥዋዕት አድርጎ እንዳያቀርበው መከላከል እና እምቢ ማለት ሲችል፥ በጸጥታ በመታዘዝ ለመሠዋት እንደፈቀደ ሁሉ፥ ኢየሱስም እግዚአብሔር አብ ይሠዋ ዘንድ ለወሰነው ውሳኔ በፈቃደኝነት ታዘዘ። በገዛ ፈቃዱ ሕይወቱን ሰጠ።

 1. «የእግዚአብሔር መልአክ» መታየት። በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችን፥ በብሉይ ኪዳን፡- «የጌታ መልአክ» ተብሎ የተጠራ ልዩ የሆነ መልአክ መኖሩን መለየት አስቸጋሪ ነው። ይህ መልአክ በዘፍጥረት፥ በዘጸአት፥ በዘኁልቁ፥ በ1ኛና በ2ኛ ሳሙኤል፥ በ1ኛና በ2ኛ ነገሥት እንዲሁም በ1ኛና በ2ኛ ዜና መዋዕል ውስጥ ተጠቅሷል። በኦሪት ዘፍጥረት ይህ መልአክ ከአጋር (ዘፍጥ. 16፡7-14፤ 21፡16-20)። ከአብርሃም (ዘፍጥ. 18፤ 22፡ 10-18) እና ከያዕቆብ (ዘፍጥ. 31፡11-13) እንደተገናኘ ተጠቅሷል። ይህ ልዩ የጌታ መልአክ ማን ነው? ስለዚህ መልአክ የተጠቀሱትን የተለያዩ ጥቅሶች ስንመረምር ወደሚከተሉት እውነቶች እንደርሳለን፡ –

ሀ. የጌታ መልአክ ከእግዚአብሔር የተለየ ነው። ይህን ስንል የጌታ መልአክ ስለ እግዚአብሔር ስለሚናገር እርሱ ከእግዚአብሔር የተለየ ሰብዕና አለው ማለታችን ነው።

ለ. የጌታ መልአክ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ተጠቅሷል። ለምሳሌ፣ አጋር ከጌታ መልአክ ጋር ከተነጋገረች በኋላ እግዚአብሔርን አየሁት አለች፤ (ዘፍጥ. 16፡10)።

ሐ. ይህ የጌታ መልአክ ይታያል ደግሞም ወዲያውኑ ይሰወራል። ግለሰቦች ወይም የእስራኤል ሕዝብ የእርሱ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው በተወሰኑ ጊዜያት ይታይና ተግባሩን ከፈጸመ በኋላ ይሄዳል። 

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፥ ይህ መልአክ በእግዚአብሔር ተልኮ የአንዳንድ ሰዎችን ወይም የእስራኤልን ሕዝብ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ የሚረዳ አንድ ልዩ መልአክ ነው ብለው ያስባሉ። እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራውም እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛ ሆኖ የሚመጣና የእግዚአብሔር ተወካይ መሆኑ የታወቀ ስለሆነ ነው ይላሉ። ሌሉች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ደግሞ ይህ መልአክ እግዚአብሔር ነው፤ እንዲያውም በአዲስ ኪዳን ሥጋ ከመልበሱ በፊት በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል ይላሉ። ዘላለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን በሥራ ላይ እንደነበረና በምድር ላይ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ለሰዎች እየተገለጠ ይሰወር እንደነበር የሚያመለክት ይመስላል።

የአብርሃም ሕይወት የጊዜ ቅደም ተከተል 

በአብርሃም ሕይወት በጣም ዋና ዋና የሆኑ ታሪካዊ ድርጊቶች 

 1. አብርሃም በ2166 ዓ.ዓ. አካባቢ ተወለደ 
 2. አብርሃም ካራንን ትቶ ወደ ከነዓን ተጓዘ – 75 ዓመት 
 3. የእስማኤል መወለድ – 86 ዓመት 
 4. እግዚአብሔር የግዝረትን ቃል ኪዳንና የይስሐቅን መወለድ ተስፋ ሰጠው – 99ዓመት 
 5. የይስሐቅ መወለድ – 100 ዓመት 
 6. የአብርሃም ይስሐቅን ለመሠዋት ማቅረብ – በግምት ወደ 115 ዓመት ይሆናል 
 7. አብርሃም በ1991 ዓ.ዓ. አካባቢ ሞተ – 175 ዓመት

ከአብርሃም ጋር የተገባው ቃል ኪዳን ለብሉይ ኪዳን ታሪክ ያለው አስፈላጊነት፡

የአብርሃምን ሕይወት ጠቃሚነትና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ደጋግመን ብንገልጠውም አጥጋቢ አይሆንም። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ብሉይ ኪዳንን የምንረዳበትና የእስራኤልን ሕዝብ አስፈላጊነት የምንመዝንበት መሠረት ነው። ትንቢትን የምንረዳበት መሠረትም ነው። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር ከአብርሃም በኋላም ከእስራኤል ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ነው ብለን ካመንን፥ ወደ ፊት ለእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኖቹን ያከብራል። ቃል ኪዳኖቹ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ እንደተመሠረቱ አድርገን ወይም የሚፈጸሙት በመንፈሳዊ ትርጓሜ በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው ብለን ካመንን እስራኤል ከእንግዲህ ወዲህ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ስፍራ የላትም ማለታችን ነው።

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረጋቸው እነዚህ የተስፋ ቃላት የብሉይ ኪዳኖች ታሪኮች የተመሠረቱባቸው መሠረቶች ናቸው። የአብርሃምን ሕይወት ለማጥናት በርከት ያለ ጊዜ የወሰድነው ለዚህ ነው። 

የብሉይ ኪዳን ታሪክ የተመሠረተው ከአብርሃም ጋር በተደረገ ቃል ኪዳን ላይ ነው። በቃል ኪዳኑ ውስጥ የብሉይ ኪዳንን ታሪክ እንደምሶሶ ሆነው የሚደግፉ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ነበሩ። የመጀመሪያው፥ አይሁድ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ መሆናቸው ነው። ከሌላው ሕዝብ ጋር ካለው ከየትኛውም ዓይነት ቃል ኪዳን በተለየ ሁኔታ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን አለው። ሁለተኛው፥ የከነዓን ምድር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአይሁድ እንደተሰጣቸው የተገባ ተስፋ መኖሩ ነው። ሦስተኛው፥ ደግሞ ከአብርሃም ዘር ነገሥታት እንደሚነሡ የተሰጠው ተስፋ ነው። በኋላ እንደምናየው፥ እነዚህ ነገሥታት የሚመጡት ከይሁዳ ዘር በተለይ ደግሞ ከዳዊት ዝርያ ነው። 

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ልንመለከታቸው የሚገቡ ሌሎች ሁለት እውነቶች አሉ። 1) እግዚአብሔር አሕዛብ በሙሉ በዘሩ እንደሚባረኩ ለአብርሃም ተስፋ ሰጥቶት ነበር። ይህ በረከት በተለያየ መልክ መጣ። እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ ለመግለጥ አይሁድን ተጠቀመ። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ የተጻፈው በአይሁድ ስለሆነ ነው። የሚያምኑትን ሁሉ የሚያድነው ጌታ ኢየሱስ በትውልዱ አይሁዳዊ ነው። 2) አብርሃም የእውነተኛ አማኞች ሁሉ አባት ነው። እንደ አብርሃም በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሁሉ እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ ይቀበላቸዋል። ከዚያም የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጅ የሆንከው መቼ ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘፍጥረት 4-11 የኃጢአት በመላው ዓለም መሠራጨት

ከዘፍጥረት 4-11 ባለው ክፍል ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ክንዋኔዎች አሉ። አንደኛ፥ አዳምና ሔዋን የመጀመሪያውን ክፋትና ኃጢአት ከሠሩበት ሰዓት ጀምሮ መስፋፋቱንና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡትን ዝርያዎቻቸውን በሙሉ ማጥፋቱን ቀጠለ። ሁለተኛ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ አብርሃም ድረስ ያለውን የድነት (ደኅንነት) መስመር ማሳየት ነው። ሦስተኛው፥ እንደ ዓለም ፈቃድ መኖርን ትተው በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ የኖሩ የተለያዩ ሰዎችን ማሳየት ነው። 

፩. ኃጢአትና ፍርድ በሰው ዘር ላይ እንዴት እንደመጣ ተጠቅሶ እናገኛለን።

በእነዚህ ምዕራፎች ሁሉ የኃጢአትና የሞት ዋና አሳብ እንዴት እንደተጠቀሰ አስተውል።

ሀ. በዘፍ. 4 ቃየን በተገቢው መንገድ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ማቅረብ እንዴት እምቢ እንዳለ እናነባለን። አንዳንዶች እግዚአብሔር ያልተቀበለው ደም የሌለበት ስለ ነበረ ነው ይላሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለበት መሠረታዊ ምክንያት እርሱን የማምለኪያ ትክክለኛ መንገድ ስላልነበረው ነው። እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አምልኮውን አላቀርብም አለ። ይህም የመጀመሪያውን ነፍስ ግድያ አስከተለ። ቃየን ወንድሙ አቤልን ገደለ።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ እግዚአብሔርን በተሳሳተ ዝንባሌ ወይም ውስጣዊ አሳብ ማምለክ እንዴት ይቻላል?

ለ. የቃየንን ዝርያዎች የማያቋርጥ ዓመፅ እንመለከታለን። የቃየን ዝርያዎች ለሥልጣኔ ለእድገትና ለበርካታ ከተሞች መቆርቆር ምክንያት የሆኑ ቢሆንም፥ ብዙ ሚስቶችን ማግባት ጀመሩ። እንዲያውም ላሜሕ አንድ ወጣት ሰው በመግደሉ ጉራውን ነዛ (ዘፍ. 4፡23-24)።

** ማስታወሻ፡- (ብዙ ሰዎች ቃየን እና ሴት ከየት ሚስት እንዳገኙ በማሰብ ይደነቃሉ። የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ብዙ ጊዜ ትኩረት የሚያደርገው በወንዶች ልጆች እንጂ በሴቶች ልጆች ላይ በደረሰው አይደለም፡፡ ከዘፍ. 5፡4 እንደምንረዳው አዳምና ሔዋን ወንዶች ልጆች ብቻ ሳይሆኑ፥ ሴቶች ልጆችም ነበሯቸው፤ ስለዚህ ቃየንና ሴት የራሳችውን እኅቶች እንዳገቡ መገመቱ ትክክል ነው። ይህ ነገር ከብዙ ዓመታት በኋላ ከግብፅ እስከ ወጡበት ጊዜ ድረስ በእግዚአብሔር የተከለከለ አልነበረም [ዘሌ. 18])።

ሐ. ከአዳም እስከ ኖኅ ያለው የትውልዶች ታሪክ በተተነተነበት በዘፍ. 5 በተደጋጋሚ የሚነገር አንድ ቃል አለ። ይህም ቃል «ሞት» የሚል ነው። ለበርካታ ዓመታት ቢኖርም እንኳ የሰው ልጅ መጨረሻው ያው ሞት ነው።

መ. በዘፍጥረት 6 የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች በማግባት ኃጢአት እንደሠሩ እንመለከታለን። ይህ ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፤ ስለዚህ ጉዳይ ምንነት የሚቀርቡ በርካታ አሳቦች አሉ፡-

1) «የእግዚአብሔር ልጆች» የሚለው ቃል ተፈጥሮአዊ ደረጃቸውን ትተው የሰውን ሴቶች ልጆች ስለ አገቡ መላእክት የሚናገር ሊሆን ይችላል። ይህንን አመለካከት ለመቀበል በጣም አስቸጋሪ የሚያደርገው መላእክት እንደማያገቡ ኢየሱስ ማስተማሩ ነው (ማር. 12፡25)። ሥጋዊ አካል የሌላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት ስለሆኑ ሴቶችን እንዴት ሊያገቡ ይችላሉ?

«የእግዚአብሔር ልጆች» የሚለው ቃል የፖለቲካ መሪዎችን ያመለክታል የሚሉም አሉ። (የጥንት ሰዎች መሪዎቻቸውን «አምላክ» ብለው ይጠሩ ነበር።) ኃጢአቱም፡- እነዚህ መሪዎች ከሴቶች ጋር የፍትወተ ሥጋ ፍላጎታቸውን ለመፈፀም የጋብቻን ቅድስና በመተላለፍ ብዙ ሴቶችን ማግባት መጀመራቸው ነው። በዚህም የሕዝቡን የሥነ- ምግባር መሠረት አበላሹት።

3) «የእግዚአብሔር ልጆች» ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያላቸው፥ የተለዩና ሴት የተባለው ሰው ዘሮች ነበሩ። «የሰዎች ሴቶች ልጆች» የቃየን ዝርያዎች ነበሩ። ኃጢአቱ፡- ዛሬ ክርስቲያኖች የማያምኑትን እንዳያገቡ እንደተነገራቸው ሁሉ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እግዚአብሔርን ከማይፈሩት ጋር ጋብቻ መመሥረታቸው ነበር (1ኛ ቆሮ. 7፡39፤ 2ኛ ቆሮ. 6፡14)። ይህ ነገር የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የሆኑ ሰዎች ምግባረ ብልሹ እንዲሆኑና ብዙ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው እምነት እንዲርቁ መንገድ ከፍቷል።

ከእነዚህ አመለካከቶች የትኛው እንደሚሻል ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከሁሉ የሚሻለው ምርጫ 1ኛው ወይም 3ኛው አመለካከት ይመስላል። እያንዳንዱ አመለካከት የራሱ ችግር አለው። ዛሬም ቢሆን ከኃጢአታቸው በስተኋላ ያለው አሳብ ግልጥ ነው። እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሚያገቡአቸው ሴቶች መንፈሳዊ መመዘኛን ከመፈለግ ይልቅ፥ ስለ አካላዊ ውበትና ስለ ፍትወተ ሥጋ ፍላጎት ብቻ ያስባሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ሰዎች የትዳር ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ ያላቸው ተመሳሳይ አመለካከት ምንድን ነው? ለ) አንድ ክርስቲያን የሚያገባው በመልክ ቁንጅናና ከጥሩ ቤተሰብ በመገኘት ብቻ ከሆነ ስሕተት የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) የትዳር ጓደኛን የመምረጫ እጅግ ጠቃሚ መመዘኛዎች የትኞቹ ናቸው?

በኦሪት ዘፍጥረት 6 የሚገኘው ታሪክ በተፈጸመ ጊዜ ክፋትና ኃጢአት እጅግ ተስፋፍቶ ስለ ነበር እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ። ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት ይኖር የነበረ አንድ ሰው ኖኅ ብቻ ነበር፤ ስለዚህ ከዘፍ. 6-9 ባለው ክፍል እግዚአብሔር የሰውን ዘር ለማጥፋት ስለተጠቀመበት የጥፋት ውኃ እናነባለን። የጥፋት ውኃ ዓላማ በክፉው የሰው ልጅ ላይ ለመፍረድና የእግዚአብሔር ሰው የሆነው ኖኅ በአዲስ መልክ እንዲጀምር ለማድረግ ነበር። ልክ እንደ አዳም ኖኅ የሰው ዘር ሁሉ ራስ ሆነ። ዛሬ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች በሙሉ የተገኙት ከኖኅ ነው።

ሠ. ከዘፍ. 10-11 ክፍል ክፋት በጥፋት ውኃ ሊጠፋ እንዴት እንዳልቻለ እናያለን። ኖኅ የእግዚአብሔር ሰው ቢሆንም፥ እርሱና ቤተሰቡ የክፋት ባሕርይ ነበረባቸው። በመጀመሪያ፥ ኖኅ ጠጥቶ ሰከረና ጨዋነት በጎደለው መንገድ እራቁቱን ሆነ። ከዚያም የኖኅ ልጆች ከነበሩት አንዱ የሆነው ካም የአባቱን እርቃነ-ሥጋ አየ። ከዚህ የተነሣ የካም ልጅ የነበረውና የእስራኤል ሕዝብ ጠላት የሆኑት የከነዓናውያን አባት ከነዓን በኖኅ ተረገመ። 

** (ማስታወሻ፡- አንዳንድ ሰዎች የተረገመው ከነዓን እንጂ ካም ስላልሆነ ከነዓንም በኖኅ ላይ ኃጢአት ሠርቷል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። በምንም ሁኔታ ይሁን ኖኅ በነቢይነት የከነዓን ዘር የሴምና የያፌት ዘሮች ባሪያ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናገረ፤ ነገር ግን ይህን ታሪክ ነጮች ጥቁሮችን ለመግዛት ሊጠቀሙበት አይገባም)።

ሁለተኛ፡- የኖኅ ዝርያዎች በሙሉ ብዙ ሳይቆዩ በኃጢአት ውስጥ ተዘፈቁ። በትዕቢታቸውና ሐሰተኞች አማልክትን ለማምለክ በመፈለጋቸው የባቢሎንን ግንብ ለመሥራት ተነሡ። ይህም ምድርን እንዲሞሉ ያዘዛቸውን እግዚአብሔር በተዘዋዋሪ መንገድ አንታዘዝም ማለት ነበር፤ ዳሩ ግን ለመበታተን አልፈለጉም ነበር (ዘፍ. 9፡7፤ 11፡4 ተመልከት)። አሁን ደግሞ እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ደባልቆ እንዲበተኑ በማድረግ በሰው ልጆች ላይ ፈረደባቸው። በዘፍ. 10 በምድር የሚገኙ የሰው ዝርያዎች ሁሉ ከየት እንደመጡ ተጽፏል። ነጮችና የምሥራቅ ሰዎች የመጡት ከያፌት ዘር ነው። ዓረቦችና አይሁድ የመጡት ከሴም ዘር ነው። አፍሪካውያን ደግሞ የመጡት ከካም ዘር ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኃጢአት በኖኅና በቤተሰቦቹ የመቀጠሉ እውነታ ኃጢአት ከትውልድ ወደ ትውልድ ስለ መተላለፉ ምን ይነግረናል? ለ) ዛሬ የኃጢአት ባሕርይ ከወላጆች ወደ ልጆች የመተላለፉን እውነታ እንዴት እናየዋለን? 

፪. ከአዳም እስከ አብርሃም ያለው እግዚአብሔርን የሚፈራው ትውልድ። 

የእነዚህ ምዕራፎች ሁለተኛ ዓላማ ደግሞ የአብርሃምን የዘር ሐረግ ወደ ኋላ በመመለስ እስከ መጀመሪያው ሰው እስከ አዳም ድረስ ማሳየት ነው። በዘፍጥረት 5 ሙሴ አሥር ትውልዶችን በመዘርዘር ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ያለውን የትውልድ አመጣጥ አሳይቷል። በዘፍ. 11፡10-32 ደግሞ ሙሴ የአዳምን የዘር ሐረግ የኖኅ ልጅ እስከሆነው እስከ ሴም ከዚያም እስከ አብርሃም ድረስ ያሳያል። እርሱም የተመረጡና እሥራኤል ተብሎ የተጠራው የእግዚአብሔር ሕዝብ ራስ ነው። «አባት» የሚለው የዕብራይስጥ ቃል አያትን ወይም ቅድመ አያትን የሚያሳይ ስለሆነ እነዚህ ቁጥሮች አሥር ትውልዶችን ይሁን ወይም አንዱ የሌላው ዘር መሆኑን ብቻ የሚያሳዩ ይሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ከስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።

፫. የዓለምን መንገድ ለመከተል እምቢ ያሉና ጻድቃን የሆኑ ሰዎች ምሳሌ፡፡

አብዛኛው የዚህ ክፍል ታሪክ ትኩረት በዓለም ላይ ኃጢአት እየተስፋፋ ስለመምጣቱ ቢሆንም፥ ስለ ኃጢአትና ፍርድ በሚናገሩ ታሪኮች ውስጥ የተለዩ ሕዝቦች ታሪኮች ተሰውረው እናገኛለን። እነዚህም ሦስት የተለያዩ ሰዎች በብዙኃኑ ሕዝብ መካከል ያለውን ኃጢአት ተቋቁመው በእግዚአብሔርም ፊት የጽድቅን ሕይወት የኖሩ ናቸው።

የመጀመሪያው ሄኖክ ነበር። ስለ ሄኖክ ሕይወት የተጻፈልንና የምናውቀው ነገር «አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረጉ» ነው፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ሞትን ሳያይ ወደ ሰማይ ወሰደው። እርሱም ሞትን ሳያይ ወደ መንግሥተ ሰማያት የተወሰደ የመጀመሪያ ሰው ነው።

ሁለተኛ፥ ኖኅን እናገኛለን። ስለ ኖኅ «በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበር» ተብሎላታል (ዘፍ. 6፡9)። ስለሆነም ቀሪውን የሰውን ዘር በሙሉ ካጠፋው ውኃ እግዚአብሔር እርሱንና ቤተሰቡን አድኖአል። የጥፋት ውኃንና እግዚአብሔር ኖኅን እንዴት እንደጠበቀው የሚናገረውን ታሪክ ከዘፍጥረት 6-9 ባለው ክፍል እናገኛለን። በታሪኩ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

 1. የኖኅ መርከብ መጠን 140 ሜትር ርዝመት 23 ሜትር ስፋትና 13.5 ሜትር ከፍታ ያለው ነበር። ይህም ማለት ርዝመቱ ከእግር ኳስ ሜዳ ከፍታውም ሦስት ፎቅ ካለው ሕንጻ የሚበልጥ ነበር። ሦስት ወለሉች ወይም ፎቆች ነበሩት። መርከቡ አንድ በርና አንድ መስኮት ብቻ ነበረው። እስከ 1900 ዓ.ም. ድረስ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ትልቅ መርከብ መሥራት አለመጀመራቸውን ማወቅ የሚያስገርም ነው። በአሁኑ ጊዜ በውቅያኖስ ላይ ዕቃ ጫኝ ተሽከርካሪዎችን የሚሸከሙ መርከቦች መጠናቸው ከዚያ የሚተካከል ነው። ኖኅ መርከቡን ለመሥራት 120 ዓመታት ፈጅቶበታል። ኖኅ ምንም ዝናብ ባያይና በሐይቅ (በባሕር) አካባቢ ካለመኖሩ የተነሣ ብዙ ውኃ ምን እንደሚመስል ባያውቅም እንኳ እግዚአብሔር እንዲሠራ ያዘዘውን ነገር በታማኝነት በመፈጸም መርከቡን ሠራ። 

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር አንድን ነገር እንድናደርግ የጠየቀን ለምን እንደሆነ ባልተረዳንበት ሰዓት እንኳ እርሱን በመፍራት ልንታዘዘው እንደሚገባ የኖኅ ተግባር እንዴት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል?

 1. የመርከቡ መሠራት ዓላማ በጥፋት ውኃ ጊዜ የኖኅን ቤተሰብና (8 ሰዎች) በምድር ላይ ከነበሩ እንስሳት በሙሉ አንድ አንድ ለማዳን ነበር። ሳይንቲስቶች ዛሬ በምድር ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ አንድ አንድ ቢገቡ መርከቡ ሊይዛቸው እንደሚችል አረጋግጠዋል። በአዲስ ኪዳን መርከቡ እግዚአብሔር ልጆቹን የመቤዠቱ ምሳሌ ነው (ዕብ. 11፡7፤ 2ኛ ጴጥ. 2፡5)። ደግሞም የጥምቀት ምሳሌ ነው (1ኛ ጴጥ. 3፡20-2)። 
 2. ኖኅና ቤተሰቡ በመርከቡ ውስጥ ለ377 ቀናት ቆዩ። (ከአንድ ዓመት በላይ ማለት ነው)። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት እግዚአብሔር ለእርሱና ለእንስሳቱ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ይሰጣቸው ነበር። 
 3. ውኃው ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች የጥፋት ውኃው በመስጴጦምያ አካባቢ ብቻ በመሆን በዚያን ጊዜ በታወቀው ዓለም የነበሩትን ነገሮች ብቻ እንዳጠፋ አድርገው ቢያስቡም እንኳ ውኃው የሸፈነው ምድርን በሙሉ እንደሆነ ከታሪኩ በግልጥ እንመለከታለን። በጥንት ዘመን በሁሉም አህጉር ታላቅ ጥፋትን ያስከተለ ውኃ እንደነበር የሚያሳዩ ምልክቶች መገኘታቸው የሚያስገርምና የዚህን ታሪክ እውነተኛነት የሚያረጋግጥ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ባያውቁም እንኳ በዓለም ላይ የሚገኙ በርካታ ሕዝቦች በባሕላቸው፥ ዓለም እንዴት በውኃ እንደጠፋች የሚናገር ታሪክ አላቸው። 
 4. በጥፋት ውኃው መጨረሻ ላይ እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ቃል ኪዳኑን ከመስጠቱ በፊት አንዳንድ ትእዛዛትን ሰጠው (ዘፍ. 9፡ 17)። 

ሀ. ምድርን ለመሙላት መባዛት ነበረባቸው፤ 

ለ. እንስሳት ሁሉ ለሰው ልጅ ለምግብነት ተሰጡት፤ 

ሐ. ኖኅ ደም እንዳይበላ ታዘዘ፤ 

መ. የሌላውን ሰው ነፍስ በግድየለሽነት የሚያጠፉ ሁሉ ይገደሉ ነበር።

ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰው ልጆችም ጋር ተስፋንና ቃል ኪዳንን አድርጓል። ያም ቃል ኪዳን እግዚአብሔር እንደገና ምድርን በጥፋት ውኃ እንደማያጠፋ የሚናገር ነበር። ቀስተ ደመና እግዚአብሔር ከዚህ በኋላ ምድርን በውኃ ላለማጥፋት የገባውን ቃል ኪዳን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ ምልክት ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ጴጥ. 3፡3-7 አንብብ። ምድር ወደፊት የምትጠፋው እንዴት ነው?

ማስታወሻ፡- አንዳንድ ሰዎች የኖኅን መርከብ በቱርክና በሩሲያ ድንበር ላይ በአራራት ተራራ ጫፍ አግኝተናል ቢሉም እስካሁን ድረስ ግን እውነትነቱ አልተረጋገጠም።

ሦስተኛ፥ የምናገኘው ሰው አብርሃም ነው። እርሱም በመስጴጦምያ ይኖር በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር እርሱ ወደሚያሳየው ምድር ይወጣ ዘንድ ያዘዘው ሰው ነበር። ዘፍ. 12-25 በዚህ ልዩ የእግዚአብሔር ሰው ላይ ያተኩራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ሰዎች ሕይወት በክፋት ዓለም ውስጥ ስለመኖር ምን የምንማረው ነገር አለ? ለ) በእኛስ ፊት ይኸው ምርጫ እንዴት ነው? ሐ) ለእኛም የተዘጋጀው ተመሳሳይ ሽልማት ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የአዳምና የሔዋን ኃጢአት (ከዘፍ. 3)

የውይይት ጥያቄ፥ ከዘፍ. 3 በሰው መጀመሪያ ኃጢአት በተሳተፉት ላይ የደረሰባቸውን እርግማን ዘርዝር።

ዘፍ. 3 ስለ ሰው የመጀመሪያ ኃጢአት ይናገራል። ይህም በእግዚአብሔር ላይ የፈጸመው የመጀመሪያው ዓመፅ ነበር። እግዚአብሔር በመጀመሪያ አዳምና ሔዋንን ሲፈጥር፥ በሥነ- ምግባር ፍጹም ነበሩ። የኃጢአት ተፈጥሮ ስለሌላባቸው ኃጢአት ሊያደርጉ የሚችሉበት ምክንያት አልነበረም። ምሁራን ይህንን «የንጽሕና ደረጃ» ብለው ይጠሩታል፤ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ምን እንደሆነ እንኳ አያውቁም ነበር። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን በዔደን ገነት ባኖረ ጊዜ ከፍሬው እንዳይበሉ የከለከላቸው አንድ ዛፍ ነበር። ይህ ፍሬ «መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቅ ዛፍ» የሚገኝ ነበር።

ሰይጣን በእግዚአብሔር ላይ ያመፀው አስቀድሞ ነበር። አዳምና ሔዋንም በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምፁ በማድረግ ፍጥረታትን ሁሉ ሊያበላሽ ቆረጠ፤ ስለዚህ ሰይጣን ወደ ሔዋን ቀረበ። ስለ እግዚአብሔር ትእዛዝ የተምታታ አሳብ እንዲኖራት አደረገ። ከዚህም በኋላ ሔዋንን ትእዛዙን በሰጣት በእግዚአብሔር ዓላማና ባህርይ ላይ እንድትጠራጠር አደረጋት። አዳምና ሔዋን ሁለቱም የተከለከለውን ፍሬ በሉ። በመጀመሪያ የተታለለችውና በኃጢአት በመውደቅ ለእግዚአብሔር ያልታዘዘችው ሔዋን ብትሆንም አዳምም በኃጢአት የወደቀው እያወቀ ነው። እግዚአብሔርን በመታዘዝ ፈንታ ሔዋንን መከተል መረጠ። አንዳንድ ምሁራን፡ – ሔዋን በተታለለች ጊዜ አዳም አብሮአት ነበር፤ ሆኖም ከስሕተት እንድትርቅ ሊያደርጋት አልፈለገም ይላሉ።

የውይይት ጥያቄ ፥ ኃጢአት በምናደርግበት ጊዜ አዳምና ሔዋን ከሠሩት ኃጢአት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

የመጀመሪያው የሰው ልጅ ኃጢአት ፈጣሪ በሆነው እግዚአብሔር ላይ ማመፅ ነበር። ፈጣሪያቸው የሆነው ጌታ ፍሬውን እንዳይበሉ የመከልከል ሙሉ መብት ነበረው፤ ነገር ግን የራሳቸውን ፍላጎት ለማድረግ ስለፈለጉ ዓመፁ። በእያንዳንዱ ኃጢአት ውስጥ ያለው ተመሳሳይ ዝንባሌ ይህ ነው። እያንዳንዱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ዓመፅ ነው። ለእግዚአብሔር ራስን ባለመስጠት ለትእዛዙ አልገዛም ማለት ነው። ፈጣሪያችን ለሆነው ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ራሳችንን ከማስገዛት ይልቅ በራሳችን ሕይወት ላይ ለመሠልጠን የምናደርገው ጥረት ነው። 

የመጀመሪያው የአዳምና ሔዋን ኃጢአት ለብዙዎች የሚደርሱ አስጨናቂ ውጤቶችን አስከተለ።

 1. አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ወዲያውኑ አቋርጦ ከእግዚአብሔር እንዲደበቁ አደረገ። 
 2. በአራት ነገሮች ላይ ቅጽበታዊ ፍርድ አመጣ፡-

ሀ. በእባቡ ላይ አካላዊና ተምሳሌታዊ ፍርድን አመጣ። እባብ ተፈጥሮው ተለውጦ በሆዱ የሚሳብ እንስሳ ሆነ። በእባብ ተመስሎ የቀረበው ሰይጣን ተፈርዶበት የመጨረሻ ሽንፈቱ ተነገረ። 

ለ. ሔዋንና ሴቶች ሁሉ ተፈረደባቸው። ከዚህ የተነሣ ልጅ መውለድ አስጨናቂ ሂደት ሆነ። ሴቶች ከባሎቻቸው ጋር የነበራቸው የእኩልነት ግንኙነት ተለውጦ ለባሎቻቸው የሚገዙ ሆኑ። 

ሐ. አዳምና ወንዶች ሁሉ ተፈረደባቸው። ሥራቸው ቀላልና የሚያስደስት መሆኑ ቀረና የቤተሰቦቻቸውን ሁሉ ፍላጎት ለማርካት በማያቋርጥ ፍልሚያ ውስጥ ገቡ። 

መ. ፍጥረት ተረገመ። የሰው ልጅ ወዳጅ መሆኑ ቀረና ጠላት ሆነ። ለእሾህ፥ አሜከላ፥ ራብ፥ የመሬት መንቀጥቀጥና ሌሎች አጥፊ ነገሮች መከሰቻ ሆነ። 

 1. የመጀመሪያውን እንስሳ መገደልና በመጨረሻም የሰዎች ሁሉ ሞትን አስከተለ። አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር «ደም ሳይፈስ ስርየት የለም» (ዕብ. 9፡22) የሚለው መንፈሳዊ መመሪያ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው ይላሉ። እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን ራቁትነታቸውን ለመሸፈን ቁርበት ማልበስ ብቻ ሳይሆን፥ ለኃጢአታቸውም እንስሳን ሠዋ። በብሉይ ኪዳን ለጊዜውም ቢሆን ኃጢአቱን ይሸፍን የነበረው የእንስሳ ደም ነበር። በአዲስ ኪዳን ግን ኢየሱስ ለኃጢአት የሚሆን የመጨረሻ መሥዋዕት ሆነ (ዕብ. 9፡22፥ 26-27 ተመልከት)።
 2. ከእነርሱ በኋላ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አስከተለ። አዳምና ሔዋን ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱ ሰዎች በሙሉ ራስ በመሆናቸው በሰው ልጆች ላይ ፍርድን አመጡ። ይህ ፍርድ የሰዎችን ሕይወት በምድር ላይ አስቸጋሪ ከማድረጉ ሌላ ሥጋዊ ሞት የሰው ልጆች ሁሉ የመጨረሻ ዕጣ መሆኑን እርግጠኛ አደረገው። ይህም ማለት ልጆቻቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ያለማቋረጥ ወደማመፅ የሚወስዳቸውን የኃጢአት ባሕርይ ጭምር ወረሱ ማለት ነው።
 3. አዳምና ሔዋንን ከዔደን ገነት እንዲባረሩ አደረጋቸው። ይህ እርምጃ የጸጋም የፍርድም እርምጃ ነው። ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ወስደው በመብላት በኃጢአት ለዘላለም እንዳይኖሩ እግዚአብሔር በጸጋና በፍርድ ከዔደን ገነት አባረራቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ የእነዚህ ኃጢአቶች ውጤት ዛሬ በሕይወትህ እንዴት ይታያል?

በአዲስ ኪዳን፥ ክርስቶስ ኃጢአት ያመጣቸውን ነገሮች ማስወገድ ጀምሮ እናያለን። በባልና በሚስት መካከል የነበረው ግንኙነት መስተካከል ነበረበት። በመጨረሻም ዘላለማዊ መንግሥቱ ሲጀመር ይህንን እርግማን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚያስወግድ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ እንመለከታለን (ራእ. 21-22)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘፍጥረት 1-2 የዓለም አፈጣጠር

መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ ወይም የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንስንም ሆነ ታሪክን የሚመለከት መረጃ የያዘ ቢሆንም ዓላማው ግን ይህ አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለሰው ልጅ መግለጥ ነው። እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን ለሰው ልጆች የሚናገርበት ዋናው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መረጃ ሳይንስንና ታሪክን የሚመለከት ጉዳይ ቢኖረውም፥ ሳይንስና ታሪክ መርምረው ያገኙት አብዛኛው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ አልተካተተም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የገለጠው ነገር ሁሉ በሳይንቲስቶችና በታሪክ አዋቂዎች ዛሬ ባይታመን እንኳ፥ ሊታመንና ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ከሰዎች አስተሳሰብና አመለካከት ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል መምረጥ አለብን። 

እንደምናውቀው ዘፍጥረት 1፡1 እንደ ዮሐ. 1፡1 ወደ ጊዜና ወደ ታሪክ መጀመሪያ ይመልሰናል። ይህ የእግዚአብሔር መጀመሪያ ሳይሆን፥ የተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ነው። እግዚአብሔር ዘላለማዊ ስለሆነ መጀመሪያ የለውም። 

ዘፍጥረት 1-2 የፍጥረታት ታሪክ አጠር ባለ መልክ አጠቃልሉ ያቀርበዋል። ዘፍጥረት 1 ፍጥረትን ሁሉ በመገምገምና በእያንዳንዱ ቀን የተፈጠረውን ነገር በመናገር የፍጥረታትን ታሪክ ያሳየናል። ከፍጥረታት ሁሉ በመጨረሻ የተፈጠረው የሰው ልጅ ምን ያህል ከሁሉ የላቀ ፍጡር መሆኑንም ያመለክታል። ዘፍጥረት 2 የሚያተኩረው ወንድና ሴት ሆኖ በተፈጠረው በሰው ልጅ ላይ ሲሆን፥ ይኖርበት ዘንድ ስለተዘጋጀለት ዔደን ተብሎ ስለሚጠራው ስፍራም ይናገራል።

በዘፍጥረት 1 እግዚአብሔር ነገሮች ሁሉ እንዴት እንደተፈጠሩ ለማሳየት አይፈልግም። ለምሳሌ መላእክት ወይም ሰይጣን የተፈጠሩት እንዴትና መቼ እንደሆነ የሚናገር ነገር የለም። ይልቁንም በቀላል ቋንቋ እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪ እንደሆነ ተገልጧል። ስለዚህ የተፈጠሩ ነገሮች በሙሉ የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔር ንብረት ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ስለሆነ ስለ እርሱ ሊኖረን የሚገባ አመለካከት ምን ዓይነት ነው? ለ) እግዚአብሔር ፈጣሪያችንን ልናከብር የምንችልባቸውን መንገዶች ግለጥ። 

በዓለም ላይ የምናያቸው ነገሮች በሙሉ ስለተገኙባቸው መንገዶች የሚናገሩ አምስት የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የማይቀበሉ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች አመለካከቶች ናቸው።

ክርስቲያን ባልሆኑ ሰዎች የሚንፀባረቁ ሁለት አመለካከቶች 

 1. የተፈጠሩ ነገሮች በሙሉ ፈጣሪዎቻቸው የሆኑ የተለያዩ አማልክት የሥራ ውጤቶች ናቸው። ይህ አመለካከት እውነተኛውን አምላክ የማያውቁ የጥንት ሰዎች የሚያንፀባርቁት ነው። ለምሳሌ፡- በብዙ አማልክት የሚያምኑ አንዳንድ ጣዖት አምላኪዎች፡- ምድር የፀሐይ አምላክና የሴት ጨረቃ አምላክ ልጅ ነው ብለው ያምኑ ነበር። በተጨማሪም የሰው ልጅ ከአማልክት መካከል የአንዱ ዝርያ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ይህም የቀድሞዎቹ ባቢሎናውያን፥ ግሪኮች፥ ሮማውያንና ከነዓናውያን አመለካከት ነበር። ዛሬም የብዙ አፍሪካውያን አመለካከት ሲሆን ሂንዱይዝም በተባለው በምሥራቃውያን እምነት ውስጥም የሚታይ ነው።

እግዚአብሔር የፍጥረታትን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገበት አንዱ ምክንያት እርሱ ብቻ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እንደሆነ ለማሳየት ነው። ዛሬ እግዚአብሔር እስራኤላውያንንና እኛን አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ እንዳለ ሊያስተምረን ይፈልጋል። እግዚአብሔር «በምድርና በሰማይ ያሉ» ነገሮች ሁሉ ፈጣሪ ነው። ለሰው ልጅ ትክክለኛ ቦታው ራሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ በመስጠት ፈጣሪውና ጌታው መሆኑን ተረድቶ እርሱን በማክበር መኖር ነው። 

 1. የተፈጠሩ ነገሮች በሙሉ የተፈጥሮ «አዝጋሚ ለውጥ» (ኢቮሉሽን) ውጤቶች ናቸው። ይህ ፅንሰ አሳብ ብዙዎቻችን በመንግሥት ትምህርት ቤት የተማርነው ነው። አዝጋሚ ለውጥ እንዴት እንደተፈጸመ የሚያስረዱ በርካታ የተለያዩ ንድፈ አሳቦች ቢኖሩም፥ ይህ አመለካከት የሚያስተምረው ከብዙ ቢሊዮን ዓመታት በፊት አንድ ታላቅ ፍንዳታ ተፈጽሞ ፀሐይ፥ ከዋክብት፥ ሌሉች ፕላኔቶች፥ ወዘተ. ተፈጠሩ። በአንድ ባልታወቀ ምክንያት ሕይወት መጀመሪያ ከተፈጠረው ፕላኔት ይወጣ ጀመር። ከዚያም በመጀመሪያ ዕፀዋት፥ ቀጥሉም እንደ አሜባ ያሉ በጣም ጥቃቅን እንስሳት ተገኙ። እነርሱም ቀስ በቀስ እንቁራሪት ወደ መሳሰሉ እንስሳት ተለወጡ። እነዚያ ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ ጡት አጥቢ እንስሳት ተለወጡ በማለት ነው፤ ስለዚህ በቀላል አማርኛ ሰው ከፍተኛው የአዝጋሚ ሂደት ለውጥ ውጤት ነው። ይህ አመለካከት ለእግዚአብሔርና እርሱ ለፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ምንም ቦታ አይሰጥም።

ሕዝ. 28፡11-17። በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በተደረገው ጦርነት የመጀመሪያዋ ምድር ወደ ባዶነትና ጨለማ ተለወጠች በማለት ግምታዊ አስተሳሰባቸውን ይሰጣሉ።

ስለዚህ ይህ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድን ምርኩዝ በማድረግ እግዚአብሔር ዓለምን እንደገና ጠግኖአል ወይም አድሶአል በማለት ያስተምራሉ።

ይህ አመለካከት ሙሉ በሙሉ እንደማይሆን አድርጎ ለመቃወም ባይቻልም ሁለት ዓለማት ስለ መፈጠራቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማስረጃ የለም። 

 1. ዘፍጥረት 1 የሚናገረው እግዚአብሔር ዛሬ በዓለም ላይ የሚገኙትን ነገሮች ሁሉ እንዴት እንደፈጠረ ነው። ቁሳዊ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ እግዚአብሔር በስድስት ቀናት ውስጥ የፈጠራቸው ናቸው። የተፈጠሩትም ከምንም ነው (ዕብ. 11፡3 ተመልከት)። ይህ አመለካከት በዘመናት ሁሉ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ያመኑበት ሲሆን ከሌሎች ሁሉ በተሻለ ሁኔታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚስማማ ነው።

ማንም ሰው እነዚህን አመለካከቶች «ማረጋገጥ» አይችልም። ይልቁንም ክርስቲያኖችም ሆኑ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የሚከተሉአቸው እነዚህ አመለካከቶች እምነትን ወይም ሊያዩ የማይችሉትን ነገር መቀበልን ይጠይቃል። የማያምኑ ሰዎችን ሁሉ ማርካት በሚቻልበት መንገድ ክርስቲያኖች ሊገልጹዋቸው የማይችሉዋቸው አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩም፥ በዕብ. 11፡3 እንደምናነበው እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪ መሆኑን የምንቀበለው «በእምነት» ነው። ይህ ማለት እኛ የእርሱ ፍጥረት ነን። እርሱ ፈጣሪ በመሆኑ በእኛ ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው። እኛም ለእርሱ በመገዛት መኖር አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕይወታችንን በሙሉ ለእግዚአብሔር ለመስጠትና እርሱን ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ የምንቸገረው ለምንድን ነው?

እስካሁን ባለን እውቀት አንጻር እግዚአብሔር ዓለምን በስድስት ቀናት እንደፈጠረ ማመን ከሁሉም የሚሻል ነገር ይመስላል። እግዚአብሔር እንደሌለና ነገሮች ሁሉ የአዝጋሚ ለውጥ ውጤቶች እንደሆኑ የሚያምኑ ሰዎችን አጥብቀን መቃወም ያለብን ቢሆንም፥ እኛ ስለ ፍጥረታት አፈጣጠር ካለን አመለካከት ለየት ያለ እምነት ያላቸውን ክርስቲያኖች መቀበል አለብን። ደኅንነታችን የተመሠረተው ስለ ፍጥረታት ባለን ትክክለኛ አመለካከት ሳይሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ታሪክ እኛ ለማወቅ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ የሚያብራራ ሳይንሳዊ ዘገባ አይደለም። የፍጥረት ታሪክ የተገለጠበት ዓላማ እግዚአብሔር ፈጣሪ እንደሆነና እኛ የእርሱ ልዩ ፍጥረቶች እንደሆንን በግልጥ ለማስተማር ነው።

ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛነት በምንም ዓይነት ሁኔታ ከመጠራጠር መጠንቀቅ አለብን። የእግዚአብሔርን ቃል ከለወጥንና እርሱ በግልጽ ከሚያስተምረን ነገር የተለየ አመለካከት ካለን፥ መሠረታችንን አጣን ማለት ነው። ስለ ፍጥረት አፈጣጠር መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ትምህርት የተሳሳተ ከሆነ ስለ እግዚአብሔር ማንነት፥ ስለ ኢየሱስ ማንነትና እኛን እንዴት እንዳዳነን፥ ወዘተ. የሚሰጠው ትምህርትም የተሳሳተ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። እኛም ሆንን ሌሉች ክርስቲያኖች የምንከተለው ማንኛውም አመለካከት በእግዚአብሔር ቃል ላይ በሚገባ የተመሠረተ መሆን አለበት።

ዘፍ. 1፡1-2 የፍጥረት ታሪክ መግቢያ ነው። በመግቢያው ውስጥ እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ምንጭ እንደሆነ ይገልጻል። የቀረው የፍጥረት ሥራም እንዴት እንደተከናወነ የሚገልጽ አስተዋጽኦ ይሰጣል። እግዚአብሔር ምንም ቅርፅ የሌላትን ዓለም ወስዶ ቅርፅ ሰጣት። እንዲሁም ባዶና አንዳች ያልነበረባትን ዓለም ወስዶ በተለያዩ ነገሮች ሞላት። 

ከዘፍጥረት ታሪክ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡. አንደኛ፥ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረባቸው ስድስት ቀናት ነበሩ። ሁለተኛ፥ የፍጥረትን ሥራ የሚመለከቱ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉ። የመጀመሪያው ክፍል እግዚአብሔር ለምድር ቅርፅን እንደሰጠ የሚናገር ሲሆን፥ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ እግዚአብሔር የፈጠረውን ነገር በተለያዩ ነገሮች እንደሞላ ይናገራል። ሦስተኛው፥ የሁለቱ ክፍሎች እያንዳንዱ ቀን የተያያዘ ነው። ለምሳሌ፡- 1ኛና 4ኛ ቀናት በሰማይ ስላሉ ብርሃናት መፈጠር ይናገራሉ። 2ኛና 5ኛ ቀናት እግዚአብሔር ባሕርንና ጠፈርን ሲያዘጋጃቸውና ሲሞላቸው እናያለን። 3ኛና 6ኛ ቀናት ደረቅ ምድርን የማዘጋጀትና የመሙላት ሥራ የተከናወነባቸው ቀናት ናቸው። ይህም ዓለምን የመፍጠር ሥራ ግልጥ የሆነ ቅንብር ተደርጎለት እንደ ነበር ያሳየናል።

እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረ ጊዜ ይህ ሥራ የሥላሴ ተግባር ነበር። በዘፍ. 1፡2 እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ሥራ አማካይነት የመፍጠርን ተግባር እንዳከናወነ እናነባለን። እግዚአብሔር «እንፍጠር» እያለ ራሱን በብዙ ቁጥር ሲጠራ እንመለከታለን (ዘፍ. 1፡26)። ይህንን በተለያዩ መንገዶች መረዳት ቢቻልም፥ እግዚአብሔር ሦስት አካላት አሉት። እነርሱም እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሲሆኑ፥ አዲስ ኪዳን በሚሰጠው በዚህ ትምህርት መሠረት ሥላሴ ፍጥረትን በሚመለከት አብረው እንደወሰኑና ሦስቱም በመፍጠር ሥራ ውስጥ እንደተሳተፉ እናያለን። 

የሰው ልጅ መፈጠር

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዘፍጥረት 1 ስለ ሰው ልጅ መፈጠር የሚናገሩ ስንት ቁጥሮችን ታገኛለህ? ለ) ስለ ሰው ልጅ አፈጣጠር እግዚአብሔር ይህን የመሰለ ሰፋ ያለ ገለጻ የሰጠው ለምን ይመስልሃል? ሐ) የሰውን ልጅ አፈጣጠር የሚናገረው ታሪክ ስለ ሌሎች አፈጣጠር ከተነገረው ታሪክ የሚለየው እንዴት ነው? መ) ሰው «በእግዚአብሔር አምሳል» ተፈጠረ ማለት ምን ማለት ይመስልሃል?

አብዛኛው የፍጥረት ታሪክ የሚያተኩረው አዳምና ሔዋን ተብለው በሚጠሩት በመጀመሪያዎቹ ሰዎች መፈጠር ላይ ነው። በዘፍ. 1 ሙሴ፥ እግዚአብሔር ወንድና ሴትን እንዴት እንደፈጠረ ባጭሩ ይገልጣል። ወንድና ሴት ሁለቱም የተፈጠሩት በእግዚአብሔር አምሳል ነው።

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነው ማለት ምን ማለት ነው? ከዚህ ዐረፍተ ነገር በርካታ ጠቃሚ እውነቶችን እንመለከታለን፡

 1. ሰው ከእንስሳት የተለየ ነው። በአንዳንድ በኩል ሲታይ ሰው በሥጋዊ አካሉ ከእንስሳት ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም፥ በእግዚአብሔር አምላል የተፈጠረ ስለሆነ ከእንስሳት የተለየ ነው። 
 2. ሰው እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ የተሻለ ነው። ከማናቸውም ፍጥረታት ሁሉ በጣም ተፈላጊ ነው። 
 3. ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ። እግዚአብሔር እንደ እኛ ዓይነት ሥጋዊ አካል ስለሌለው አካላዊ አለመሆኑ ግልጥ ነው። ይልቁንም አምሳልነቱ በሚከተሉት ነገሮች ነው፡-

ሀ. እግዚአብሔርም ሆነ ሰው ሁለቱም ስብዕና አላቸው። ይህም ማለት ያስባሉ፥ ያዝናሉ፥ ያቅዳሉ። 

ለ. እግዚአብሔርና ሰው ሁለቱም ክፉና ደጉን የመለየት የሥነ ምግባር እውቀት አላቸው። በመሆኑም ክፉውን ወይም ደጉን የመምረጥ ችሎታ አላቸው። 

ሐ. እግዚአብሔርና ሰው ሁለቱም ገዥዎች ናቸው። እግዚአብሔር በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ገዥ ነው። ሰውም የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ገዥ ነው።

መ.እግዚአብሔርና ሰው ሁለቱም «መንፈስ» አላቸው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው (ዮሐ. 4፡24 ተመልከት)። ሰውም ዘላለማዊ የሆነ መንፈስ አለው።

 1. ወንድና ሴት ሁለቱም እኩል የእግዚአብሔር አምሳልነት አላቸው። ወንድ ከሴት የተለየ የእግዚአብሔር አምሳልነት የለውም፤ የእግዚአብሔርን አምሳልነት በተመለከተ ሴትም ከወንድ ያነሰ የአፈጣጠር ልዩነት የላትም።

እኛ ሁላችንም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን ስለሆንን በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ክብር አለን?

ዘፍ.2 የሚያተኩረው በሰው ልጅ አፈጣጠር ላይ ነው። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት አዳምና ሔዋን ይኖሩበት ስለ ነበረው እጅግ ውብ ስፍራ ስለ ዔደን ገነት እናነባለን። እንደተገለጸው ከሆነ ዔደን ገነት መስጴጦምያ አካባቢ የነበረች ስፍራ ትመስላለች። እንዲሁም ሴት እንዴት ከወንድ ጎን እንደተሠራችም በዚህ ምዕራፍ ይናገራል።

በወንድና በሴት የአፈጣጠር ታሪክ እግዚአብሔር ለወንዶችና ለሴቶች ሁሉ በጋብቻ ውስጥ ያለው አሳብ ምን እንደሆነ እንመለከታለን። ሁለቱም በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠሩ፥ እኩልነት መኖር አለበት። አንድ ሥጋ ስለሚሆኑ፥ አንድነት መኖር አለበት። ሳይለያዩ እስከሞት ድረስ በአንድነት መቆየት አለባቸው። የቅርብ ጓደኛሞች መሆን አለባቸው። ቅርበታቸው ከተለመደው ቤተሰባዊ አቀራረብ ማለት አባትና እናት ከልጆቻቸው ጋር ካላቸው ግንኙነት እጅግ የበለጠ መሆን አለበት። ወንድ በመጀመሪያ ስለተፈጠረ ሚስት ለባሏ ታዛዥ መሆን ይገባታል።

ባልና ሚስት በኅብረታቸው ውስጥ አንዳችም የተሰወረ ነገር ሳይኖር ሙሉ በሙሉ ግልጥ መሆን አለባቸው። ይህም «ራቁታቸውን ነበሩ፤ አይተፋፈሩም ነበር» ከሚለው ቃል የሚታወቅ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዘፍጥረት 2 የተገለጸው የጋብቻ ሁኔታ ብዙ ሰዎች በጋብቻ ውስጥ የተለመደ ነው ብለው ከሚያስቡት ነገር በምን ይለያያል? ለ) የአንተ ወይም የወላጆችህ ጋብቻ በዘፍጥረት 2 ለትክክለኛ ጋብቻ ምሳሌነት ከቀረበው ከአዳምና ሔዋን ጋብቻ ጋር እንዴት የነጻጸራል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ቅደም ተከተልና አስተዋጽኦ፣ ልዩ ባሕሪያት እና ዓላማ

የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ቅደም ተከተልና አስተዋጽኦ

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት ዘፍ. 2፡4፤ 5፡1፤ 6፡9፣ 10፡1፤ 11፡10፤ 11፡27፤ 25፡12፤ 25፡19፤ 36፡1፥ 9፤ 37፡2። ሙሴ፡- «የ…..ታሪክ ይህ ነው» የሚላቸውን የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር።

ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን በሚጽፍበት ጊዜ ግልጽ የሆነ አስተዋጽኦ ነበረው። መጽሐፉን ያቀናበረው «የ…ይህ ነው» በሚሉት ቃላት ዙሪያ ነበር። ብዙ ምሁራን ይህንን አከፋፈል የኦሪት ዘፍጥረትን አስተዋጽኦ ለመንደፍ ይጠቀሙበታል።

 1. መግቢያ፡- የነገሮች ሁሉ አፈጣጠር (ዘፍጥ. 1፡1-2፡3) 
 2. ከአይሁድ አባቶች በፊት የነበረው ዘመን (ዘፍ. 2፡4-11፡26)

ሀ) የሰማይና የምድር መፈጠር ታሪክ (ዘፍ. 2፡4-4፡26) 

ለ) የአዳም ትውልድ እና የልጆቹ ታሪክ (ዘፍ. 5፡1-6፡8) 

ሐ) የኖኅ ታሪክ (ዘፍ. 6፡9-9፡29) 

መ) የሴም፥ የካምና የያፌት ታሪክ (ዘፍ. 10፡1-11፡9)

ሠ) የሴም ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 11፡10-26) 

 1. የአይሁድ አባቶች ዘመን (ዘፍ. 11፡27-50)

ሀ) የታራ ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 11፡27-25፡1) 

ለ) የእስማኤል ትውልድ (ዘፍ. 25፡12-18) 

ሐ) የይስሐቅ ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 25፡19-35፡29)

መ) የዔሳው ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 36፡1-37፡1) 

ሠ) የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 37፡2-50፡26)

ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን በዚህ ዓይነት ቢያቀናብረውም ለማስታወስ ቀላል የሆነ ሌላ የቅንብር መንገድ አለ። የሚከተለውን አስተዋጽኦ እየደጋገምህ አጥና ወይም በቃልህ ያዝ፡-

 1. ከአይሁድ አባቶች በፊት የነበረው ዘመን (ዘፍ. 1-11) 

ሀ. ፍጥረት (ዘፍ. 1-2) 

ለ. የሰው ልጅ በኃጢአት መውደቅ (ዘፍ. 3-5) 

ሐ. የጥፋት ውኃ በዓለም ላይ (ኖኅ) (ዘፍ. 6-9)

መ. የባቢሎን ግንብና የሰው ዘር መለያየት (ዘፍ. 10-11) 

 1. የአይሁድ የእምነት አባቶች ዘመን (ዘፍ. 12-50)

ሀ. አብርሃም (ዘፍ. 12-25) 

ለ. ይስሐቅ (ዘፍ. 24-26)

ሐ. ያዕቆብ (ዘፍ. 27-36) 

መ. ዮሴፍ (ዘፍ. 37-50)

ከዚህ በላይ ባለው አስተዋጽኦ ውስጥ ሁለት ነገሮችን ልብ በል፡- – በመጀመሪያ፥ ዘፍጥረት በሁለት ዓበይት ክፍሎች፥ ማለትም በዘፍጥረት 1-11 እንዲሁም በዘፍጥረት 12-50 እንደተከፈለ ልብ በል። የመጀመሪያው ክፍል የሚናገረው ስለ ጥንት ዘመን ሲሆን፥ ፍጥረታትን የመፍጠር ተግባር የተፈጸመው መቼ እንደሆነና ይህ ክፍለ ዘመን ምን ያህል ዓመታት እንደፈጀ ለማወቅ አንችልም። ዘፍ. 12-50 ደግሞ የሚናገረው ስለ አይሁድ ሕዝብ መመሥረትና ያንን ሕዝብ ስለ ጀመሩት አራቱ የእስራኤል አባቶች ታሪክ ነው።

ሁለተኛ፥ እያንዳንዱ ክፍል በአራት ንዑሳን ክፍሎች መከፈሉን ልብ ሰል። ከዘፍ. 1-11 ያለው የመጀመሪያው ክፍል ፍጥረትን፥ ውድቀትን፥ የጥፋት ውኃንና የባቢሎንን ግንብ የሚያጠቃልሉ አራት ክፍሎች አሉት። ከዘፍ. 12-50 ባለው ክፍል ደግሞ ትኩረት የተሰጣቸው አራት ዋና ዋና ሰዎች አሉ። ይህንን የዘፍጥረትን አስተዋጽኦ ብትከተል በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘውን ታሪክ ለማስታወስ ይረዳሃል። የኦሪት ዘፍጥረት ልዩ ባሕርያት በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ መጽሐፉን የበለጠ ለመረዳት ማዕከላዊ የሆኑና ሙሴ ያካተታቸው አንዳንድ ልዩ ነገሮች አሉ።

 1. ዘፍጥረት፥ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ዓላማውን ወደ ፍጻሜ ብዙ ጊዜ ለማድረስ ከተለመደው ባሕላዊ ሁኔታና ተግባር ተቃራኒ በሆነ አቅጣጫ እንደሚጓዝ ያሳያል። ይህ በተለይ የታየው እግዚአብሔር ከበኩሩ (ከመጀመሪያው ልጅ) ይልቅ ሁለተኛውን በመምረጡ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉት በርካታ ባሕሉች አይሁድ የመጀመሪያ ልጅ ልዩ እንደሆነ በማመን፥ ከአባቱ ንብረት የሚበዛውን ክፍል መውረስ እንዳለበት ይስማሙ ነበር። እግዚአብሔር ግን በዚህ ሰው ሠራሽ ባሕል ራሱን አልወሰነም። ለምሳሌ፡- በዘፍጥረት ውስጥ እግዚአብሔር ከቃየን ይልቅ ሴትን፥ ከያፌት ይልቅ ሴምን፥ ከእስማኤል ይልቅ ይስሐቅን፥ ከዔሳው ይልቅ ያዕቆብን፥ ከቀሩት ወንድሞቻቸው ይልቅ ይሁዳንና ዮሴፍን፥ ከምናሴ ይልቅ ኤፍሬምን ሲመርጥ እንመለከታለን። ይህ ሁሉ የሚያስተምረን እግዚአብሔር በእኛ ባሕላዊ ግንዛቤ መሠረት ብቻ ለመሥራት የሚወሰን አለመሆኑን ነው። ይልቁንም ከእኛ ጋር ባለው ግንኙነት ሉዓላዊ ነው። የተለያዩ ግለሰቦችን የሚመርጠውና በአንዳንዶቹ በኃይል የሚሠራው በሌሉቹ ደግሞ ያንኑ ያህል በኃይል የማይሠራው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይህም እግዚአብሔር በሕይወታችን ላይ ባለው ኃይልና የበላይ ተቆጣጣሪነት ከፍተኛ አድናቆትን እንድንሰጠው የሚያደርግ እንጂ በአእምሮአችን ውስጥ ቅንዓትን የሚፈጥር መሆን የለበትም። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሌሉች ክርስቲያኖች ባለጸጎች መሆናቸውን ወይም እግዚአብሔር ከእነርሱ ይልቅ በኃይል እየተጠቀመባቸው መሆኑን ሲገነዘቡ የሚቀኑት ለምንድን ነው? ለ) ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር ዕቅድ አሳልፎ ስለመስጠት የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው? ሐ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም አስፈላጊው ነገር፥ እግዚአብሔር ለሰጠን ስጦታዎችና ችሉታዎች ወይም ሥራዎች ታማኝ መሆን ነው፥ ወይስ በሰዎች ላይ ታላቅ መሪ መሆን? መልስህን አብራራ።

 1. በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ተምሳሌታዊ ትርጉም ያላቸው አንዳንድ ቁጥሮች ይገኛሉ። የሚከተሉትን ቁጥሮች ተመልከት፡- 

ሀ) አሥር – በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ አሥር ዋና ዋና ክፍሎች አሉ፤ (አሥር ጊዜ «የ … ይህ ነው» ታሪኮች) እንዲሁም በዘፍጥረት 5 ና 11 «አሥር» ትውልዶችን የሚጠቅሱ ትንተናዎች እናገኛለን»። ለአይሁድ አሥር የምሉዕነት ተምሳሌት ነው።

ለ) ሰባት – ሰባት የፍጥረታት ሥራ የተከናወኑባቸው ቀናት ከመኖራቸውም፥ በምዕራፍ 4 ውስጥ በሚገኘው የትውልዶች ታሪክ ውስጥ የሚገኙ ሰባት ስሞች፥ በጥፋት ውኃ ታሪክ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰባት ቁጥሮች፣ ለአብርሃም የተገቡ ሰባት ቃል ኪዳኖች፥ በግብፅ ውስጥ የደረሱ ሰባት የጥጋብና ሰባት የራብ ዓመታት እናገኛለን፡፡ እንዲሁም 70 (7 ጊዜ 10) የኖኅና የያዕቆብ ዝርያዎች ናቸው። ሰባት ብዙ ጊዜ የፍጹምነት ምሳሌ ነው።

ሐ) አሥራ ሁለት – የያዕቆብና የእስማኤል ነገዶች እያንዳንዳቸው አሥራ ሁለት ነገዶች ነበሩ (ዘፍ. 25፡16፤ 49፡28)። 

መ) አርባ፡- በጥፋት ውኃ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ የ40 ቁጥር ክፍፍሎች እናያለን (ዘፍ. 6-9)። በኋላም እስራኤላውያን 40 ዓመታት በምድረ በዳ እንደተንከራተቱ እናነባለን። አንድ ሰው ብሉይ ኪዳንን በሚያጠናበት ጊዜ እነዚህ ቁጥሮች ለአይሁድ የተለዩ እንደሆኑ ግልጽ እየሆነለት ይመጣል። ለምሳሌ 40 ቁጥር የፍርድና የፈተና ጊዜ ይመስላል (ለምሳሌ፡- ኢየሱስ በምድረ በዳ ለ40 ቀናት ተፈትኖአል)። ሰባት ማለት ደግሞ የተሟላ ወይም ፍጹም ማለት ነው፤ (ለምሳሌ፡- በዮሐንስ ራእይ መንፈስ ቅዱስ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ተብሎ ተጠርቷል)።

 1. በዮሐንስ ራእይ የመጨረሻ ምዕራፎች የሚገኙት በተለይም መንግሥተ ሰማያትን የሚገልጡት ሥዕላዊ መግለጫዎች ከኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያ ሦስት ምዕራፎች ስለ ዔደን ገነት ከተነገሩ መግለጫዎች የተወሰዱ መሆናቸው ትኩረትን የሚስብ ነው። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት በ1500 ዓመታት ልዩነት መካከል ቢሆንም ይህን የመሰለ ግንኙነት በመካከላቸው መታየቱ፥ እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ጸሐፊ መሆኑን የሚያሳይ ነው። 

የኦሪት ዘፍጥረት ዋና ዓላማ

የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ዓላማ ብንመለከት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን መግለጥ ነው ለማለት እንችላለን። እርሱ «የእግዚአብሔር ቃል» ነው ( ዮሐ. 1፡1-4፤ ዕብ. 1፡1-3)። «ኢየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ተሰውሮአል፤ በአዲስ ኪዳን ግን ተገልጦአል» የሚል አንድ አባባል አለ።

በሌላ አባባል የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በትንቢቶች አማካይነት የኢየሱስን መምጣት አሻግረው ተመለከቱ። እንዲሁም በሰዎች፥ በድርጊቶችና በነገሮች ሁሉ ውስጥ የመሢሑ መምጣት ሥዕላዊ መግለጫ ነበር። ስለሆነም ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ አጀማመር እናያለን። በዘፍጥረት ስለ ኢየሱስ የተነገሩ ትንቢቶችን አጀማመር እንመለከታለን። በአንዳንድ ታሪኮች ውስጥም የተደበቁ የኢየሱስ ተምሳሌቶች ወይም ሥዕላዊ መግለጫዎች አሉ። ብሉይ ኪዳንን ስናጠና እነዚህም ትንቢቶችና አምሳያዎች መፈለግ አለብን። ይህ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ የሚቀጥል «የድነት (ደኅንነት) መስመር» በመባል ይታወቃል።

ነገር ግን ሙሴ ፔንታቱክን የጻፈበት ዋና ዓላማ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገውን «ቃል ኪዳን» ለመግለጥ ነበር። ፔንታቱክና መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መሠረታዊ የሆነው አሳብ ይህ ቃል ኪዳን ነው፤ ስለዚህ የኦሪት ዘፍጥረት ማዕከላዊ እውነቶች የሚያተኩሩት ቃል ኪዳንን በሚመለከት አሳብ ላይ ነው። ዘፍጥረት 1-11 ከተለዩ ሕዝቦች ጋር ቃል ኪዳን ያስፈለገበትን ምክንያት ይናገራል። የሰው ልጅ በአጠቃላይ ፈጣሪውን ክዶ ኃጢአትን እንዴት እንደመረጠ ይናገራል። ዘፍ. 12-50 ደግሞ እግዚአብሔር ከአንድ ሰውና ከቤተሰቡ ጀምሮ አይሁድ ተብሎ የተጠራ አንድን የተለየ ሕዝብ እንዴት እንደመረጠ ይገልጻል። እግዚአብሔር ዓለምን ወደ ራሱ ለመመለስ የፈለገው በእነርሱ በኩል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው የቃል ኪዳን አሳብ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ወይም በአዲስ ኪዳን የሚታየው እንዴት ነው? ለ) የእስራኤል ሕዝብና የቤተ ክርስቲያን ዓላማ የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር አብርሃምን በመረጠው ጊዜ የነበረውን ዓላማ ዛሬ ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እየፈጸመችው ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘፍጥረት መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ «ዘፍጥረት» የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት። ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ተጻፈበት ዓላማና ስለ መጽሐፉ አስተዋጽኦ ያገኘኸው ነገር ምንድን ነው?

ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ልናጠናቸውና ልንረዳቸው ከሚገቡን እጅግ ጠቃሚ መጻሕፍት አንዱ ዘፍጥረት ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በዘፍጥረት ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ቢያውቁም እንኳ አብዛኛዎቹን ጥልቅ ትምህርቶች ግን አያጠኗቸውም። የዚህ መጽሐፍ ዓላማ ዘፍጥረትን በጥልቀት ማጥናት ባይሆንም፥ በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸውንና የተተኮረባቸውን ዋና ዋና የሥነ- መለኮት ትምህርቶች ለመመልከት እንሞክራለን። 

የኦሪት ዘፍጥረት ስያሜ 

ለኦሪት ዘፍጥረት የተሰጠው ስም የመጣው ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ቀደም ሲል አጥንተናል። ዘፍጥረት የሚለው ቃል በመጽሐፉ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች ላይ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ስለ መፍጠሩ በሚናገረው መሠረተ አሳብ ላይ ያተኩራል። እንደግሪኩ ስያሜ መጽሐፉ የሚያተኩረው በተለያዩ ነገሮች «አጀማመር» ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ከዚህ ቀደም ኦሪት ዘፍጥረትን በግል ካነበብከው በመነሣት አጀማመራቸው በመጽሐፉ የሆነ የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር።

በዘፍጥረት ውስጥ የቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍላችንን ለመረዳት በጣም ጠቃሚ የሆኑ የብዙ ነገሮችን አጀማመር እንመለከታለን። ለምሳሌ፡- የፍጥረታትን አጀማመር እንመለከታለን። እግዚአብሔር ፈጣሪ ስለሆነ እርሱ የፍጥረታት ሁሉ ባለቤትና ተቆጣጣሪ ነው። በዘፍጥረት ውስጥ የወንድና የሴትን፥ የጋብቻን፥ የኃጢአትን፥ ስለ ኃጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት፥ የተለያዩ ከተሞችን፥ የነፍስ ግድያን፥ የሥልጣኔ፥ የነገድና የጎሣዎችን፥ የተለያዩ ቋንቋዎችን አጀማመር፥ ወዘተ እናያለን። አብዛኛዎቹም በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ 11 ምዕራፎች ውስጥ ይገኛሉ።

ከብሉይ ኪዳን ታሪክ አንጻር ስናየው ግን በጣም አስፈላጊ ክስተት የሆነው የእስራኤል ሕዝብ አጀማመር ነው። የኦሪት ዘፍጥረት አብዛኛው ክፍል (ምዕራፍ 12-50) ስለ እስራኤል ሕዝብ አጀማመር የሚናገር ነው። ይህም ሕዝብ እግዚአብሔር የመረጠው ነው። 

የኦሪት ዘፍጥረት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡ሀ) የኦሪት ዘፍጥረት ጸሐፊ እንደሆነ በይበልጥ የሚገመተው ማን ነው? ለ) እንደ አንዳንድ ምሁራን አስተሳሰብ ዘፍጥረት የተጻፈው እንዴት ነው? ሐ) ሙሴ የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልክተህ ስለ ሕይወቱ በአጭሩ ጻፍ። መ) ኦሪት ዘፍጥረትን ለመጻፍ ሙሴ የተለየ ብቃት ያገኘው እንዴት ነው?

በዘመናት ሁሉ ሙሴ ዘፍጥረትን ጨምሮ የፔንታቱክ ጸሐፊ መሆኑ ይገመት እንደነበር ቀደም ሲል ተመልክተናል። ጸሐፊው ሙሴ እንደሆነ በዘፍጥረት ባይጠቀስም እንኳ የቀሩቱ የፔንታቱክ መጻሕፍት ግን ሙሴ እንደጻፈው ያሳያሉ። አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በሙሉ እንደ አንድ ክፍል ስለሚቆጠሩ፥ ዘፍጥረትንም የጻፈው ሙሴ መሆን አለበት። ሙሴ ዘፍጥረትን አልጻፈውም ብለን የምናምንበት አንዳችም ምክንያት የለም። ይልቁንም ሙሴ በዘፍጥረት ውስጥ የምናገኘውን ነገር ለመጻፍ በተለየ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ነበር።

ለአይሁድ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበሩ እጅግ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ሙሴ ነበር። ከግብፅ ባርነት አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸው ሙሴ ነበር። ለእስራኤል ሕዝብ ሕግን ለመስጠት እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ሙሴ ነበር። አይሁድ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዘወትር «የሙሴ ሕግ» ብለው የሚጠሩት ስለዚህ ነበር። ሙሴ ነቢይ፥ ካህን፥ ሕግ ሰጭ፥ ፈራጅ፥ አማላጅ፡ እረኛ፥ ተአምራት አድራጊና የአይሁድ ሕዝብ የፖለቲካ መሥራች ነበር።

ሙሴ የተወለደው ሌዊ ከተባለው የእስራኤል ነገድ እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ወላጆች ነበር። ነገር ግን የተወለደው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በግብፃውያን ባርነት ሥር ወድቆ፥ ግብፃውያንም እስራኤላውያን የሆኑ ወንዶች ልጆች ሁሉ በሚወለዱበት ጊዜ እንዲገደሉ ሕግ ያወጡበት ጊዜ ነበር። ግብፃውያን ይህንን ያደረጉበት ምክንያት እስራኤላውያን በቁጥር እጅግ ብዙ ይሆኑና ከዚህ ቀደም ሐይክሶሳውያን እንዳደረጉት ሊገለብጡን ይሆናል ብለው ፈርተው ስለ ነበር ነው። በእምነታቸው ጽናት የሙሴ ወላጆች ሊደብቁት እስከሚችሉበት ጊዜ ድረስ አሳደጉት። ሊደብቁት ከማይችሉበት ጊዜ ላይ ሲደርሱ ግን እግዚአብሔር እንደሚታደገው በመተማመን በዓባይ ወንዝ ዳር አስቀመጡት። የግብፅ መሪ የነበረው የፈርዖን ሴት ልጅ ባገኘችው ጊዜ ወደ ቤቷ ወስዳ እንደ ግብፃዊ አሳደገችው። የሙሴ ሕይወት እያንዳንዳቸው 40 ዓመታት በሆኑ ሦስት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

 1. 40 ዓመታት በግብፅ – በፈርዖን ቤት ውስጥ፡- በእነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ ሙሴ በሁለት የተለያዩ ባሕሎች ትምህርት አደገ። በመጀመሪያ፥ በአይሁድ ሃይማኖትና ከአባቶች በተወረሰ ትምህርት አደገ። ይህ የሆነው ለጊዜውም ቢሆን ያሳድጉት ዘንድ ኃላፊነቱ በተሰጣቸው በእኅቱ ማርያምና በእናቱ ነበር (ዘጸ. 2፡7-10)። ሁለተኛ፥ ሙሴ እንደፈርዖን ልጅ ሆኖ የማደግ ዕድል በማግኘቱ በዚያ ዘመን ሊኖር የሚችለውን ትምህርት ሁሉ ቀስሞ ነበር (የሐዋ. 7:22 ተመልከት)። ግብፅ በዚያን ዘመን እጅግ የሠለጠነች አገር ስለነበረች፥ ሙሴ እጅግ የተማረ ሰው ነበር ማለት ነው። እስጢፋኖስ ሙሴ «በቃልና በሥራው ሁሉ የበረታ ሆነ» ይላል።

ሙሴ ይህንን ሁሉ ትምህርት በመቅሰሙ፥እግዚአብሔር በኋላ ዘፍጥረትን ጨምሮ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዲጽፍ ተጠቀመበት። አይሁዳውያን ከነበሩት ወላጆች ስለ ወገኖቹ እንደሰማ ጥርጥር የለውም። ወደ ኋላ ተመልሶ እስከ አዳምና ሔዋን፥ ኖኅ፥ በተለይም አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብና ዮሴፍ ያለውን የሕዝቡን አፈ ታሪኮችን ያውቅ ነበር። በግብፅ ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት ስለአለፈው ጊዜ የሚናገሩ ታሪኮችን የማየት ዕድልም ገጥሞት ነበር። ይህ ታሪክ የዓለምን አፈጣጠር፥ በኖኅ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውኃ፥ የዓለምን መከፋፈል ወዘተ የሚጨምር ነው። ሙሴ ዘፍጥረትን ለመጻፍ በጣም ብቁ ሰው ነበር።

በእነዚህ 40 ዓመታት ሙሴ እስራኤላዊ እንጂ ግብፃዊ እንዳልሆነ አልዘነጋም ነበር። ካደገ በኋላ አንድ ውሳኔ ለማድረግ ተገደደ። ውሳኔውስ ዓለማዊ የሆነ ዕድል ባለበት በፈርዖን ቤት ለመቆየት? ወይስ እግዚአብሔር የተለዩ የቃል ኪዳን ሕዝቡ አድርጎ ከመረጣቸውና አሁን ባሮች ከሆኑት ሕዝብ ጋር ማበር ይሆን? 

የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 11፡24-26 አንብብ። ሀ) ሙሴ ያደረገው ምርጫ ምን ነበር? ለ) ዛሬ ይህንን ምርጫ ማድረግ ያለብን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

ሙሴ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት የተመረጠ መሪ እንደነበር ተረድቶ ነበር (የሐዋ. 7፡25)። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጊዜ ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ ኃይል ነፃ ሊያወጣቸው ሞከረ። ስለዚህ አንድን ሰው ከገደለ በኋላ የፈርዖንን ቤት ትቶ ከግብፅ መሸሽ ግድ ሆነበት።

 1. 40 ዓመታት በምድያም ምድረ በዳ፡- በሰው አመለካከት የሚቀጥሉት 40 ዓመታት የባከኑ ይመስላሉ። ሙሴ በጣም የተማረ ሰው ቢሆንም በግ ማገድ ጀመረ። በእግዚአብሔር አመለካከት ግን በሙሴ ሕይወት ይህ በጣም አስፈላጊ ጊዜ ነበር። ምድረ በዳውና በግ ማገዱ እግዚአብሔር ሙሴን የእስራኤል ሕዝብ መሪ ወይም እረኛ ለማድረግ የሚያስተምርበት ቦታና ሥራ ነበር። በምድረ በዳው እግዚአብሔር በትምህርቱና በችሎታው የነበረውን ትምክሕት በማስወገድ ሙሴን ትሑት አደረገው። ሙሴ ትሑት ከሆነና እግዚአብሔር በሕይወቱ እንዲሠራ በእርሱ ብቻ ከታመነ፥ ታላቅ ሥራን ይሠራ ዘንድ የእግዚአብሔር መገልገያ ለመሆን ተዘጋጅቷል ማለት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሙሴን በኃይል ይገለገልበት ዘንድ ትሑት ሊያደርገው ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? ለ) የእግዚአብሔርን ሕዝብ በምንመራበት ጊዜ በችሎታችንና በእውቀታችን ስለ መመካት ይህ ምን ያስተምረናል? ሐ) ከሙሴ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መኖር ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ምን ለመማር ትችላለህ?

 1. 40 ዓመታት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከግብፅ ወደ ከነዓን መምራት፡- አንድ ቀን እግዚአብሔር ሙሴን በሚቃጠል ቁጥቋጦ ውስጥ ተገናኘውና ወደ ግብፅ ተመልሶ እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ በማውጣት እንዲመራቸው ጠራው። ሙሴ ወደ ግብፅ ለመመለስ ቢፈራም፥ በመጨረሻ ከእግዚአብሔር ጋር ተስማማ። እግዚአብሔር ሙሴን በፈርዖን ፊት ስለ እርሱ ሆኖ ይናገር ዘንድ ተገለገለበት። ሙሴ ያደረገው በፈርዖን ቤተ መንግሥት በመሆኑ በፈርዖን ዘንድ እውቅናን ማትረፉ አያጠራጥርም። አሥር ታላላቅ ተአምራዊ መቅሠፍቶችን በግብፅ ላይ በማምጣት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ነፃ አውጥቶ በሙሴ አማካይነት 40 ዓመታት በምድረ በዳ መራቸው። በእነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ እግዚአብሔር ሙሴን ፊት ለፊት ተገናኘው። እግዚአብሔር ለሙሴ ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ድረስ የተጻፈውን ሕግ ሰጠው። ሙሴን ኦሪት ዘፍጥረትን፥ ዘጸአትን፥ ዘሌዋውያንን፥ ዘኁልቁንና ዘዳግምን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል። ይህ ሁሉ ቢሆንም እንኳ ሙሴ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዘ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ታገደ (ዘኍ. 20፡1-13)። ሕዝቡን እስከ ከነዓን ድንበር ድረስ አደረሳቸው። የተስፋይቱን ምድር በተራራ ጫፍ ላይ ሆኖ ከተመለከታት በኋላ ሞተ።

የውይይት ጥያቄ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር እንዴት ኃጢአትን አክብዶ እንደሚያየው ይህ ምን ያስተምረናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)