ኢየሱስ ከሞት ተነሣ (ማር. 16:1-20)

ማርቆስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ያቀረበው ዘገባ ከሁሉም ወንጌላት አጠር ያለ ነው። ይህም በተለይ ብዙ ምሑራን እንደሚሉት፥ ምዕራፍ 16 ቁጥር 8 ላይ የሚያበቃ ከሆነ እውነት ነው ማለት ይቻላል። የክርስቶስን መቀበር የተመለከቱት ሦስት ሴቶች ወደ መቃብሩ ተመለሱ። በዚህ ጊዜ የተመለከቷቸው መላእክት ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣና ወደ ገሊላ እንደ ሄደ ነገሯቸው። ደቀ መዛሙርቱ በዚያ ከእርሱ ጋር ተገኝተዋል።

ማርቆስ ወንጌሉን የፈጸመው በሴቶቹ ፍርሃትና ግራ መጋባት ነው። ለምን እንዲህ መጽሐፉን ድንገት ጨረሰው? አንዳንድ ምሑራን ማርቆስ መጽሐፉን ቁጥር 8 ላይ የጨረሰው አንባቢያኑ ስለ ትንሣኤ እንዲያስቡ ለማድረግ እንደሆነ ያስባሉ። ክርስቲያኖች ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ማምለካቸው፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ገሊላ ሄደው ከክርስቶስ ጋር እንደ ተገናኙ ያረጋግጣል። በዚህ ጊዜ ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዚያ ነበር። ሰዎች በክርስቶስ የሕይወት ታሪክ ግራ ተጋብተው ለመኖር ወይም በክርስቶስ አምነው ግራ መጋባታችውን ለማስወገድ ምርጫ ነበራቸው።

ሌሎች ምሑራን የማርቆስ የመጀመሪያው መደምደሚያ እንደ ጠፋ ያለባሉ። ለዚህም ነው የቀድሞዎቹ ጸሐፊዎች አብዛኞቹ የማርቆስ ወንጌል የመጀመሪያ ቅጂ እካል አይደለም የሚሉትን ማርቆስ 16፡9-20 ላለመጨመር የተገደዱት፡፡

ማርቆስ 16፡9-20 በሌሎች ወንጌላትና የሐዋርያት ሥራ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ታሪኮች ጠቅለል አድርጎ ያቀርባል። የማቴዎስ ወንጌል ጋር በመስማማት፥ መግደላዊት ማርያም መጀመሪያ ክርስቶስን ያገኘችው እንደ ነበረች ያስረዳል። እንደ ሉቃስ፥ ሁለት ሰዎች በኤማሁስ መንገድ ከክርስቶስ ጋር እንደ ተገናኙ ያስረዳል። እንደ ዮሐንስ፡ ክርስቶስ ከአሥራ አንዱ ጋር እንደ ተገናኘና አንዳንዶች እንደ ቶማስ እንደተጠራጠሩት ይገልጻል።

ስለ ታላቁ ተልእኮ የሚናገረውም የማርቆስ ምንባብ በሌሎች ወንጌላት ውስጥ የተጠቀሱት እውነቶች ውህደት ይመስላል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በዓለም ሁሉ ወንጌልን እንዲሰብኩ አዝዟቸዋል። በክርስቶስ ያመኑ ደኅንነትን ሲያገኙ፥ ለማመን ያልፈለጉት ግን ተፈርዶባቸዋል።

ጸሐፊው በተጨማሪም ወንጌሉ በሚስፋፋበት ጊዜ ተአምራት (ምልክቶች) እንደሚታዩ ገልጾአል። (ማስታወሻ፡- ይህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ይህንን ሁሉ እንደሚያደርግ ሳይሆን፥ ምልክቶቹ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሚፈጸሙ የሚያሳይ መሆኑን አስተውል።)

ሀ. በክርስቶስ ስም አጋንንትን ማስወጣት

ሊ በአዲስ ልሳናት መናገር

ሐ እባቦችን መያዝ። (ምናልባትም ይህ ጳውሎስ እባብን ከያዘበት ታሪክ የተወሰደ ይሆናል። የሐዋ. 28፡)

መ መርዝ ጠጥቶ አለመሞት። ይህንን በተመለከተ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ምንም መረጃ የለም።

ሠ. በበሽተኞች ላይ እጅ በመጫን መፈወስ።

በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ብቻ ተመርኩዘን እምነታችንን እንዳንመሠርት መጠንቀቅ አለብን። ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ አብዛኞቹ በቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸሙ ሲሆን፥ ዛሬም እንኳ እየተፈጸሙ ነው። ነገር ግን ይህ ጥቅስ በራሱ ሁሉም ክርስቲያኖች በልሳን ይናገራሉ ብሎ ለማስተማር ጥቅም ላይ መዋል የለበትም፡፡ እባብን ስለመያዝና መርዝ ለለመጠጣት የቀረበው ትምህርት በሌላ ቦታ ስላልተደገመ፥ ክርስቲያኖች መንፈሳዊነታቸውን ለማሳየት መርዛማ እባቦችን እንዲይዙ ወይም መርዛማ መጠጥ እንዲጠጡ ማበረታታት ጥበብ የጎደለው ድርጊት ነው። በአገልግሎታቸው እነዚህን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ጥቂት ክርስቲያኖች አሉ፡ ከዚህም የተነሣ ብዙ ሰዎች ይሞታሉ።

ጸሐፊው ሌሎች የአዲስ ኪዳን ትምህርቶችንም እንደ ማጠቃለያ አድርጎ ያቀርባል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ፥ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ወዳለ ከፍ ያለ የክብርና የሥልጣን ስፍራ ሄደ። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚያሳየው፥ ሐዋርያት የኢየሱስን ታሪክ ለሌሎች ነገሩ፥ የኢየሱስንም አገልግሎት በሽተኞችን በመፈወስ፥ አጋንንትን በማውጣት፥ ወዘተ… ቀጠሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኢየሱስ መሰቀል፥ መሞትና መቀበር (ማር. 15፡21-47)

ክርስቶስ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት በመድከሙ፥ ሮማውያን ስምዖን መስቀሉን ተሸክሞ ክርስቶስ ከሁለት ወንበዴዎች ጋር ወደሚሰቀልበት ከከተማ ወጣ ያለ ስፍራ እንዲያደርስ አስገደዱት። ብዙውን ጊዜ ወንጀለኞች ወንጀላቸው የተዘረዘረበት ጨርቅ ከአንገታቸው ላይ ይደረግና መስቀሉን ተሸክመው ወደሚሰቀሉበት ስፍራ እንዲወሰዱ ይገደዱ ነበር። ማርቆስ መስቀሉን የተሸከመው ስምዖን፥ የአሌክለንድሮስና የሩፎስ አባት እንደነበር ገልጾአል። ጳውሎስም በሮሜ 18፡13 ሩፎስን ስለሚጠቅስ፥ እነዚህ ሰዎች ምናልባትም በሮም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሳይሆኑ አይቀሩም።

ስቅላት እጅግ አስከፊ የግድያ ዘዴ በመሆኑ፥ ባሮችና ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ወይም አማፅያን ብቻ በዚህ ዓይነት ይገደሉ ነበር። የአይሁድ መሪዎች ለክርስቶስ በነበራቸው ከፍተኛ ጥላቻ ምክንያት ለዚህ ቅጣት ዳረጉት። በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ምስማሮችን ቸነከሩባቸው። በዚህ ዓይነት ስቅላት የሚቀጡ ሰዎች ነፍሳቸው እስኪወጣ ድረስ በአብዛኛው ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ይሠቃዩ ነበር። የተሰቀለው ሰው ቶሎ እንዲሞት ለማድረግ፥ አንዳንድ ጊዜ ወታደርች ቅልጥሙን ይሰብሩ ነበር።

ክርስቶስን የሰቀሉት ወታደሮች የክርስቶስን ልብስ ተከፋፈሉ። ከሦስት ሰዓት ጀምሮ እስከሞተበት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ዋለ። ክርስቶስ ከሚቀበለው ሥጋዊ ሥቃይ በላይ ሰዎች በቃላት ይዘልፉት ነበር። ከሁሉም በላይ፥ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት በመሸከሙ ምክንያት እግዚአብሔር አብ ከእርሱ ጋር የነበረውን ኅብረት አቋረጠ። ክርስቶስ በታላቅ ድምፅ ጮኾ መሞቱ፥ ክርስቶስ ነፍሱን እንደ ሰጠ ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ የስቅላት ቅጣት የሚፈጽምባቸው ሰዎች እየተዳከሙ ሄደው ራሳቸውን ይስቱና በዚያው ያርፋሉ።

በዚህ ጊዜ ማርቆስ ስለ ክርስቶስ አንድ መልካም ቃል ብቻ ተናግሯል። ክርስቶስ በሚሞትበት ጊዜ አይሁዶች ምን እየሆነ እንዳለ ወይም ክርስቶስ የተለየ ሰው መሆኑን አልተገነዘቡም ነበር። ነገር ግን ቀደም ሲል ብዙ ሰዎች ሲሰቀሉ የተመለከተው የሮም ወታደር፥ ክርስቶስ የተለየና የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተገነዘበ።

የአርማቲያሱ ዮሴፍ ጲላጦስ የክርስቶስን አስከሬን እንዲሰጠው በጠየቀ ጊዜ፥ ጲላጦስ ክርስቶስ ቶሎ በመሞቱ ተደነቀ። የመቶ አለቃው ክርስቶስ መሞቱን ካረጋገጠ በኋላ፥ ዮሴፍ የክርስቶስን አስከሬን ለመውሰድ ፈቃድ አገኘና በራሱ መቃብር ውስጥ ወስዶ ቀበረው። በመጨረሻም፥ ከዮሴፍና ኒቆዲሞስ በተጨማሪ ለክርስቶስ ትኩረት ሰጥተው የቆዩ ሦስት ብቸኛ ሰዎች ነበሩ። እነርሱም ከክርስቶስ ጋር የኖሩ ሴቶች ሲሆኑ ክርስቶስ ሰባት አጋንንት ያወጣላት መግደላዊት ማርያም፥ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት የሆነችው ማርያም፥ የዮሐንስና ያዕቆብ እናት የሆነችው ሰሎሜ ከእርሱ ጋር ቆዩ። አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከሸሹ በኋላ፥ እነዚህ ሴቶች ጌታቸው ሊሞትና ሲቀበር ለማየት እዚያው ቆዩ።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙውን ጊዜ ወንዶች ከሴቶች በላይ ደፋሮች እንደሆኑ ይነገራል። በዚህ ጊዜ ግን ሴቶች ከወንዶች በላይ ደፍረው የተገኙት ለምን ይመስልሃል? ይህ እነዚህ ሦስት ሴቶች ለክርስቶስ ስለነበራቸው የእምነት ጥልቀት ምን ያስተምራል?

መጀመሪያ የማርቆስን ወንጌል ያነበቡ ብዙ ሰዎች ከፍተኛ ስደት ደርሶባቸዋል። አንዳንዶች በእንስሳት ቆዳ ተሸፍነው ለዱር አራዊት ተጥለዋል። ሌሎች ዘይት ተርከፍክፎባቸው በስታዲዮም እንደ ጧፍ እየነደዱ ብርሃን እንዲሰጡ ተደርገዋል። ከወታደሮች ወይም ከአናብስት ጋር ለመታገል የተገደዱም ነበሩ። አንዳንዶች እንደ ክርስቶስ ተሰቅለዋል። ነገር ግን ስደቱ ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም፥ ጌታቸው ክርስቶስ በስቅላት እንደ ሞተ በመገንዘብ ይጽናኑ ነበር። የእርሱ ሞት ለአሟሟታቸው አርአያ ነበር። ጳውሎስ በኋላ እንደገለጸው፥ ክርስቲያኖች መከራ በመቀበልና በመሠዋት ለቤተ ክርስቲያን የጎደለውን ይፈጽማሉ (ቆላ. 1፡24)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 14፡1-15:20

 1. ኢየሱስ ለመስቀሉ ተዘጋጀ (ማር. 14፡1-42)

ሀ. ኢየሱስ ለሞቱ በመዘጋጀት ሽቶ ተቀባ (ማር. 14፡1-11)። የክርስቶስ ሞት ድንገተኛ ነበር? አልነበረም። ክርስቶስ ላለፉት አያሌ ወራት ወደ ተወዳጇ ኢየሩሳሌም ሲደርስ፥ እንደሚገደልና ከሞት ግን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። ከመስቀሉ ሁለት ቀናት ቀደም ብላ አንዲት ሴት ውድ ሽቶ ቀባችው። ክርስቶስ ይህ ለቀብሩ መታሰቢያ እንደሚሆን ገለጸ። በወንጌላት አማካኝነት ከዚያም የዚህች ሴት ታላቅ ድርጊት ለዓለም ሁሉ እንደሚነገር አረጋገጠላቸው። ይህች ሴት ለክርስቶስ ያሳየችው ይህ ታላቅ ወሮታ ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል።

ይህች ሴት ለክርስቶስ ከገለጸችው መንፈሳዊ ፍቅር በተቃራኒ፥ ከክርስቶስ ጋር ለሦስት ዓመታት አብሮት የኖረው የአስቆሮቱ ይሁዳ፥ ክርስቶስን አሳልፎ ለመስጠት ከካህናት አለቆች ጋር ተስማማ። ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ በመሆኑ፥ ከክርስቶስ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ነበር። ለክርስቶስም ፍቅር ሊኖረው ይገባ ነበር።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካ ምግብ በላ (ማር. 14፡12-26)። ከሌሎች የሲኖፕቲክ ጸሐፊዎች በላይ ማርቆስ ስለ ክርስቶስ የመጨረሻው እራት ብዙ አሳቦችን ሰንዝሯል። ስለዚህም፥ ብዙ ምሑራን ይህ የመጨረሻው ምግብ በማርቆስ ቤት እንደ ተካሄደ ይገምታሉ። ማርቆስ ውኃ የተሸከመውን ሰውዩ ያውቅ ነበር። በአይሁድ ባሕል ውኃ መቅዳት የሴቶች ሥራ ነበር። ምናልባትም በቤታቸው ሴት ልጆች ባለመኖራቸውና መበለት እናቱ የፋሲካ ምግብ በማዘጋጀት ላይ ስለነበረች፥ ማርቆስ ውኃ ለመቅዳት ተገዶ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስ ውኃ የተሸከመውን ሰው በቀላሉ ሊለዩትና ሊከተሉት ችለዋል። ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካ በዓል ለመብላት ቀደም ብሎ ዝግጅት አድርጎ ስለነበር፥ እዚያ በደረሱ ጊዜ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶ ነበር። ክርስቶስ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው ማወቁን ለይሁዳ ጠቁሞታል። ክርስቶስ በሚፈስሰው ደሙ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚፈጸም ለደቀ መዛሙርቱ በመግለጽ፥ የጌታን እራት መሠረተ።

ኢየሱስ በመጭው የመስቀል ላይ ሞቱ ሳቢያ ታወከ (ማር. 14፡27-42)። ወደ ጌቴሰማኒ የአትክልት ስፍራ እየሄዱ ሳለ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚሸሹ ነገራቸው። በተጨማሪም፥ ከሞት ተነሥቶ በገሊላ ከእነርሱ ጋር እንደሚገናኝ አሳሰባቸው። ጴጥሮስ በፍጹም እንደማይክደው ሲናገር፥ ክርስቶስ ግን ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ገለጸለት። ክርስቶስ በቀጣዩ ሁለት ቀናት ውስጥ የሚፈጸሙትን ዝርዝር ጉዳዮች ያውቅ ስለነበር፥ ምንም ነገር ድንገተኛ አልሆነበትም። የመስቀል ላይ ሞቱ ድንገተኛ ክስተት አልነበረም። ይህ ክርስቶስ ሁልጊዜም የሚያመራበት አቅጣጫ እንጂ የሮም ወይም የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች በጣም ኃይለኞች በመሆናቸው ምክንያት የተከሰተ ጉዳይ አልነበረም።

ጌቴሴማኒ በደረሰ ጊዜ ክርስቶስ በኀዘን ታወከ። እጅግ የቅርብ ወዳጆቹ የነበሩት ጴጥሮስ፥ ዮሐንስና ያዕቆብ እንዲጸልዩለት ጠየቃቸው። ሦስት ጊዜ እግዚአብሔር የመስቀል ላይ ሞትን «ጽዋ» እና የዓለምን ኃጢአት መሸከምን እንዲያስወግድለት ጠየቀ። ክርስቶስ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ሊያደርግ እንደሚችል ያውቅ ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ በአባቱ ላይ ካለው እምነቱ ባሻገር፥ ለአብ ፈቃድ ራሱን ያስገዛ ነበር። እንቅልፍ የተጫጫናቸው ደቀ መዛሙርት በጸሎት ሊረዱት አልቻሉም ነበር። ብዙ ምሑራን በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር መቀራረቡን ይመለከታሉ። ጴጥሮስ በራሱ ላይ እየደረሰ ላለው ፈተና ባለመጸለዩ ክርስቶስ እንደ ገሠጸው (ማር. 14፡37-38) እና ጴጥሮስ ክርስቶስን ስለ ካደበት ሁኔታ ማርቆስ ተጨማሪ ዝርዝር አሳቦችን ማስፈሩ የምሑራኑን እሳብ የሚያጠናክር ይመስላል። (ማቴ. 26፡69-75ን ከማር. 14፡66-72 ጋር አነጻጽር።)

ጴጥሮስ፥ ዮሐንስና ያዕቆብ የእግዚአብሔርን ብርታት ሊጠይቁ በሚገባቸው የፈተና ሰዓት ማንቀላፋታቸውን ማርቆስ ሲገልጽ፥ ለሁላችንም ማስጠንቀቂያ እየሰጠን ነበር። ከሕይወታችን ኀጢአትን ለማስወገድ ከፈለግን፥ የሥጋን መንገድ ትተን እግዚአብሔር በሚፈልገው አቅጣጫ መጓዝ አለብን። እንዲሁም በስደትና በፈተና ጊዜ ለክርስቶስ ጸንተን ለመቆም ከፈለግን፥ የጸሎት ሰዎች ልንሆን ይገባል። ጸሎት መንፈሳዊ እንጂ ቀላል ወይም ተፈጥሯዊ ተግባር አይደለም። ብዙውን ጊዜ ጸሎት እጅግ በሚያስፈልገን ሰዓት ሥራ ይበዛብናል ወይም እንደክማለን። ነገር ግን ሥጋችንን ለፈቃዳችን አስገዝተን በጸሎት ልንተጋ ይገባል። ብርታትን የምናገኘው ከጸሎት ነው።

 1. የኢየሱስ መያዝና መመርመር (ማር. 14፡43–15፡20)።

ሀ. የኢየሱስ መያዝ (ማር. 14፡43-52)። ክርስቶስ በሮም ላይ የተነሣ አማጺ ነበር? የሞተው በዚህ ምክንያት ነበር? ሌሎች የአማፅያን መሪዎች ተከላካይ ሠራዊት ነበራቸው። ክርስቶስ ግን የተደራጀ ሠራዊት ስላልነበረው፥ በተያዘበት ወቅት ለመዋጋት አልሞከረም። አብረውት የነበሩት አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ትተውት ሸሽተዋል። ክርስቶስ ለሮም አስጊ ሰው እንዳልነበረ ግልጽ ነው።

ማርቆስ ከሌሎች ደቀ መዛሙርት በላይ ጠንካራ ስለነበረው ወጣት የጻፈው ታሪክ አስገራሚ ነበር። ከርቀት ክርስቶስን ለመከተል ሞከረ፤ ሊይዙት ባለበት ወቅት ልብሱን ትቶ ራቁቱን ሸሽ። ይህ ታሪክ የተጠቀሰው በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ብቻ በመሆኑ፥ ብዙ ምሑራን ራሱ ዮሐንስ ማርቆስ ሳይሆን እንደማይቀር ያስባሉ።

ኢየሱስ በሸንጎው ፊት ተመረመረ (ማር 14፡53-65)። ይህ ሸንጎ 71 የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች የተካተቱበት ነበር። በአይሁድ ሕግ ከፍተኛው የሥልጣን አካል ይሄ ሸንጎ ነበር። በክርስቶስ ላይ ግልጽ ክስ ለማቅረብ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡ ክርስቶስ የብሩክ አምላክ ልጅ የሆነ መሢሕ ስለመሆን አለመሆኑ እንዲነግራቸው በጠየቁት ጊዜ ብቻ፥ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ቀኝ የሚቀመጥ የሰው ልጅ መሆኑን በመናገሩ በእግዚአብሔር ላይ ተሳድቧል የሚል ክስ አግኝተዋል። አሁንም ቢሆን አይሁዶች በክርስቶስ ላይ ያግኙት ክስ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የማድረግ ሃይማኖታዊ ጉዳይ በመሆኑ፥ ክርስቶስ ለሮማውያን አስጊ ሰው አልነበረም። አይሁዶች በክርስቶስ ላይ በመትፋትና በመደብደብ፥ ክርስቶስ የተጠላና ያልተፈለገ ያህል መሆኑን አሳይተዋል (ዘኁል. 12፡14 ዘዳግ. 28፡9)። አይሁዶች እውነተኛ ነቢይ ነገሮችን በቅርቡ ለይቶ ያውቃል የሚል እምነት ስለ ነበራቸው፥ ዓይኖቹን ከሸፈኑ በኋላ ትንቢት እንዲናገር ጠየቁት።

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደ (ማር. 14፡66-72)። ብዙውን ጊዜ ኃጢአታችንን ለመደበቅ እንፈልጋለን። የጴጥሮስ ወዳጅ የነበረው ማርቆስ፥ ጴጥሮስ ክርስቶስን የካደበትን ኃጢአት ቢደብቅ አያስገርምም ነበር። ነገር ግን ማርቆስ፥ የክርስቶስን መሢሕነት በድፍረት የመሰከረው እጅግ ጠንካራውና ለክርስቶስ ለመሞት ቃል የገባው ብርቱው ደቀ መዝሙር፥ በሁለት ሴቶችና በጥቂት ቡድኖች ፊት ስለካደበት ሁኔታ ጽፎአል። እንደ ጴጥሮስ ማናችንም ክርስቶስን ልንክድ እንችላለን። ነገር ግን ክርስቶስ በቸርነቱ ጴጥሮስን ይቅር እንዳለው፥ እኛንም በምንክደው ጊዜ ይቅር ሊለን ይችላል።

ክርስቶስን በብዙ መንገዶች ልንክደው እንችላለን። ይህም በትምሕርት ቤት ውስጥ ስለ ክርስቶስና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምናውቀውን ለማካፈል በምንፈራበት ጊዜ፥ በሥራ ቦታ ለመመስከር ስንፈራ፥ እንዲሁም ጓደኞቻችን እንዳይሳለቁብን በመፍራት የስሕተታቸው ተካፋይ ስንሆን ክርስቶስን እንክዳለን። ማንም ሰው ክርስቶስን እንደማይከድና እጅግ ብርቱ ወይም በሳል እንደሆነ አድርጎ ሊያስብ አይገባም። መፍትሔው ደግሞ ኃጢአታችንን መደበቅ ላይሆን፥ መቀበል ነው። ማመኻኛ ላናቀርብ ኃጢአታችንን ልንናዘዝ ይገባል። ይህም የምንወደውን አምላካችንን በመካዳችን የተሰማንን ሕመም በመፈወስና ይቅርታን በማስገኘት ደስ ያሰኘናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስን በሆነ መንገድ የካድህበትን ጊዜ ግለጽ። ለ) ለምን? ሐ) በምንወድቅበት ጊዜ ስለምናገኘው ይቅርታ ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?

መ. ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት ተመረመረ (ማር. 15፡1-20)። በሮማውያን ሳይሾሙ ንጉሥ ነኝ ማለቱ በአብዛኛው በሮም ላይ እንደ ማመፅ ይቆጠር ነበር። ነገር ግን የሮም ገዥ የሆነው ጲላጦስ እንኳ ክርስቶስ ሮምን የሚያሰጋ የነገሥታት ንጉሥ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ክርስቶስን ብዙ ጊዜ «የአይሁድ ንጉሥ» ሲል ጠርቶታል። ነገር ግን ክርስቶስ እንዲፈታ ለማድረግ የሚችለውን ያህል ጥሯል። ምናልባትም ሮማውያን በደካማና ጥበብ በጎደለው አመራሩ ስለሚታወቀው ጲላጦስ ቀደም ሲል የሰሙት አደገኛ ነገር ላይኖር አይቀርም። ማርቆስ ወንጌሉን በሚጽፍበት ጊዜ ጲላጦስ ከመሪነቱ ሥልጣን ተነሥቶ ነበር። ስለዚህም ማርቆስ ለሮማውያን እንደራሴ የነበረው ጲላጦስ፥ ክርስቶስ ዓማፂ አለመሆኑን እንደሚያውቅ ገልጾአል። ነገር ግን ሕዝቡን በመፍራቱ ምክንያት ንጹሑ የነበረው ክርስቶስ እንዲሰቀል ተስማምቷል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማር. 12፡41-13:37

 1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ እውነተኛ አሰጣጥ አስተማረ (ማር. 12፡41-44)።

በተፈጥሯዊ መንገድ የአንድን ለጦታ ታላቅነት ከምንለካባቸው መንገዶች አንዱ የስጦታውን መጠን መመልከት ነው። አንድ መቶ ብር ወይም ከዚያ የበለጠ ገንዘብ የሚከፍሉትን ሰዎች እያደነቅን፥ ዐሥር ሣንቲም ብቻ የሚሰጡትን ቸል እንላለን። ብዙ የሚሰጡትን እያከበርን፥ ጥቂት ብቻ የሚሰጡንን እንንቃለን። ክርስቶስ ግን እግዚአብሔር አንድን ስጦታ የሚለካው፥ ሰጭውን ምን ያህል እንደሚጎዳው በማገናዘብ መሆኑን ገልጾአል። ዐሥር ብር ብቻ ያላት ድሀ ሴት አምስት ብር በምትሰጥበት ጊዜ፥ አሥር ሺህ ብር ኖሮት አንድ መቶ ብር ከሚሰጠው ነጋዴ የበለጠ ሰጥታለች ማለት ነው። በተማሩትና በሀብታሞች ተማርከን፥ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚመለከትበትን ሁኔታ እንዳንረሳ መጠንቀቅ አለብን።

የውይይት ጥያቀ:- ብዙ ገንዘብ የሚሰጡትን፥ የተማሩና ሀብታሞች የሚመስሉትን እያከበርን፥ ትንሽ ገንዘብ ብቻ የሚሰጡትን ድሆችና ያልተማሩ ሰዎች ቸል ልንል የምንችለው እንዴት ነው?

 1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ነገራቸው (ማር. 13)።

የክርስቶስን ምጽአት የሚያሳዩ ምልክቶችና፥ ክርስቲያኖችም እንዴት ለምጽአቱ መዘጋጀት እንዳለባቸው ብዙ ማብራሪያ ከሰጠው ማቴዎስ በተቃራኒ፥ ማርቆስ በምልክቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጓል። ከእነዚህ ምልክቶች አብዛኛዎቹ በማቴዎስ 24 ውስጥ ስለ ተጠቀሱ፥ በዚህ ክፍል ዝርዝራቸውን ከማቅረብ የበለጠ ተግባር አናከናውንም።

ሀ. ብዙ ሐሰተኛ መሲሖች ለሕዝቡ ችግሮች መፍትሔ እንደሚያመጡ ምርጥ የእግዚአብሔር መሪዎች አድርገው ራሳቸውን ያቀርባሉ። አንዳንዶች “ክርስቶስ” ተብለው በመጠራት ተአምራት ይሠራሉ።

ለ. ጦርነቶችና የጦርነት ወሬዎች ይሰማል።

ሐ. እንደ መሬት መንቀጥቀጥና ረሃብ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ይከሰታሉ፡፡

መ. በክርስቲያኖች ላይ ታላላቅ የስደት ጊዜያት ይደርሳሉ። የክርስቶስ ተከታዮች በአይሁድ ምኩራቦች)፥ እና በአሕዛብ (መንግሥታትና ነገሥታት) ፊት ቀርበው ለእምነታቸው መልስ ለመስጠት ይገደዳሉ። በዚህ ጊዜ ለመሪዎቹ ምላሽ ለመስጠት ከመፍራት ይልቅ፥ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩትን ቃል እንደሚሰጣቸው መተማመን ይኖርባቸዋል። እነዚህን ዕድሎች በመጠቀም ለመሪዎች መመስከር አለብን።

ሠ. ወንጌሉ በዓለም ሁሉ ለሁሉም የጎሳ ቡድኖች ይሰበካል።

ረ. ይህ ወንጌል በቤተሰቦች መካከል ከፍተኛ መለያየትን ስለሚያስከትል፥ የክርስቶስ ተከታዮች ይጠላሉ፤ ይሰደዳሉ። በዚህን ጊዜ ግን እኛ ለክርስቶስ ታማኞች ሆነን መጽናት አለብን።

ሰ. የጥፋት ርኩሰት ይከሰታል። (ማስታወሻ፡- ይህ ኢየሩሳሌም በሮማውያን መደምሰሷን ወይም በመጨረሻው ዘመን የሚከሰተውን ሌላ ድርጊት ስለ ማመልከቱ እርግጠኞች አይደለንም። ምናልባትም ሁለቱንም ያመለክት ይሆናል።) ዓለም ከዚህ በፊት አይታ የማታውቀው ከፍተኛና ፈጣን ጥፋት ይመጣል።

ሸ. ፀሐይን፥ ጨረቃንና ከዋክብቶችን የሚያጠቃ የህዋ አካላት ወይም ኮስሚክ (cosmic) ውድመት ይመጣል። (ይህ እግዚአብሔር በዓለም ላይ አስከፊ ፍርድ የሚያመጣበትን ሁኔታ የሚያሳይ የተለመደ አገላለጽ ነው። ኢሳ. 13፡10፥ ኢዩ 2፡10፥ 31፤ አሞጽ 8፡9)።

ቀ. ነገሮች እጅግ በሚከፉበት ሰዓት፥ ክርስቶስ ከመላእክቱ ጋር በመምጣት ልጆቹን (ምርጦቹን) ወደ ዘላለማዊ ፍርድ ከሚሄዱት ይለያቸዋል።

በ. ምንም እንኳ እነዚህ ምልክቶች የክርስቶስን ምጽአት ቢያሳዩም፡ (የበለስ ዛፍ የዓመቱን ወራት እንደምታሳይ ሁሉ)፥ ትክክለኛውን ቀን ወይም ዓመት ለይቶ ማወቅ አይቻልም።

ኀ. የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን ሰዎች ምጽአቱን እየተጠባበቅን፥ በታማኝነት መመላለስ አለብን፡፡ ከተሰጡት ምልክቶች ሁሉ ባሻገር፥ ክርስቶስ ባልተጠበቀ ሰዓት ይመጣል። ክርስቶስ ቶሎ አይመጣም ብለን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ሳንሰንፍ፥ ክርስቶስ ዛሬ ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ሕይወታችንን ማጥራት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ነገ እንደሚመጣ ብታውቅ ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ለ) እነዚህን ነገሮች አሁን የማታደርገው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በኢየሱስና የሃይማኖት መሪዎች መካከል የተካሄደ ክርክር (ማር. 11፡27-12፡40)

ማርቆስ፥ «ክርስቶስ በአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ለምን ተገደለ?» የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የክርስቶስን ሕይወት የመጨረሻ ቀናትና ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ያካሄዳቸውን ክርክሮች ገልጾአል። ልማዳቸውንና ሰንበትን ባለመጠበቁ ምክንያት፥ የተጠነሰሰው ጥላቻ እያደገ ሄዶ ወደ መስቀል ሞት አድርሶታል።

ሀ. በካህናት አለቆችና በሸንጎው አባላት የቀረበ ጥያቄ (ማር. 11፡27-12፡12)። የአይሁድ አለቆች ክርስቶስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱና ከቤተ መቅደስ ውስጥ ነጋዴዎችን ማባረሩ መሢሕነቱን እንደሚያመለክት ተገንዝበው ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ይህንን ለማድረግ ሥልጣን ከየት እንዳገኘ ገርሟቸዋል። እነርሱ ሥልጣናቸውን ከየት እንዳገኙ በሚገባ ያውቁ ነበር። ሥልጣናቸው የመጣው ከአሮን የዘር ሐረግ በመሆናቸው ወይም በእውቅ የሃይማኖት ሰውና የተማሩ በመሆናቸው ነበር። ክርስቶስ ግን ሥልጣኑ ከሰማይ እንደ መጣ የሚያስረዱ ተአምራትና ትምህርቶችን አቅርቧል። እግዚአብሔር አብ የነገረውን ብቻ እንደሚያደርግም ገልጾላቸዋል (ዮሐ 56)። ነገር ግን የማወቅ ፍላጎት ስላልነበራቸው፥ ክርስቶስ ጥያቄያቸውን ለመመለስ አልፈለገም። በዚህ ፈንታ፥ የመጥምቁ ዮሐንስ የነቢይነት ሥልጣን ከየት እንደ መጣ ጠየቃቸው። ይህንን ጥያቄ ከመለሱለት፥ እርሱም ጥያቄያቸውን ለመመለስ ተስማማ። ዮሐንስና ክርስቶስ ሥልጣናቸውን ያገኙት ከእግዚአብሔር ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ የክርስቶስን ጥያቄ ለመመለስ ባለመፈለጋቸው፥ እርሱም ጥያቄያቸውን ሳይመልስ ቀረ፡

ክርስቶስ የመሬት ባለቤቱንና የጪሰኞችን ታሪክ በመጠቀም፥ የሃይማኖት መሪዎችን ልብ ከፈተ። ክርስቶስ የሃይማኖት መሪዎች ምን ሊያደርጉበት እንደ ፈለጉና ፍጻሜውም ምን እንደሚሆን ለሕዝቡ ነገራቸው። እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ (ኢሳ 5- እስራኤል የእግዚአብሔር ወይን መሆናቸው ተገልጾአል) ለሃይማኖት መሪዎች አደራ ሰጥቷል። መሪዎቹ ቀን ሕዝቡን የእግዚአብሔር ሳይሆኑ የራሳቸው ንብረት በማድረግ እግዚአብሔርን አታለሉ። የእግዚአብሔር መልእክተኞች የነበሩትን ነቢያት የገደሉ ሲሆን፥ አሁን ልጁን ሊገድሉ ነበር። ከዚያስ? በመጀመሪያ፡ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ የመሪነት ሥልጣን የነበራቸውን ሰዎች ይገድላል። ይህም ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ወርረው አብዛኞቹን የሸንጎ አባላት በመግደላቸው ተፈጻሚነትን አግኝቷል። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ ሌሎች መሪዎችን ያስነሣል። እነርሱም የእግዚአብሔርን ሕዝብ በፍትሕ የሚመሩ ሐዋርያት ነበሩ። ሦስተኛ፥ ሊቀበሉ ያልፈለጉትና የገደሉት ክርስቶስ፥ የአዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሠረት ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ሰዱቃውያን ሊያስቡና ሊሠሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ለ) ይህ ክፍል የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለሥልጣናቸውና ለሥራቸው ሊኖራቸው ስለሚገባው አመለካከት ምን ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል?  

ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ የፖለቲካ ቡድን አካላት የቀረበ ጥያቄ (ማር. 12፡13-17)። ማርቆስ፥ ክርስቶስ በሮም መንግሥት ላይ የተነሣ አማፂ አለመሆኑን ለአንባቢዎቹ ያሳያል። ከአብዛኞቹ አይሁዶች በተቃራኒ፥ ክርስቶስ ሕዝቡ ታክስ ባለመክፈል የሮምን መንግሥት ከመደገፍ እንዲታቀብ እያስተማረ አልነበረም። በተጨማሪም፥ ማርቆስ ክርስቲያን ለሁለት መንግሥታት ታማኝነቱን መስጠት እንዳለበት ያብራራል። በመጀመሪያ፥ ምድራዊ የፖለቲካ መንግሥት ነበር። ክርስቶስ ሰዎች በጉልበታቸው ተጠቅመው አብዮትን እንዲያካሂዱ አልሰበከም። ነገር ግን ቀረጣቸውን ለሮም እንዲከፍሉ ነግሯቸዋል። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር የነገሠበት ምድራዊ መንግሥት አለ። ይህንንም መታዘዝ ያሻል። ሁለቱ መንግሥታት በሚጋጭበት ጊዜ፥ ክርስቲያኖች ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊውን ንጉሥ መታተዝ ይኖርባቸዋል። የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን ሁሉ እርሱ የሕይወታችን ንጉሥ እንደሆነ ማስታወስ አለብን። ከዚህ የተነሣ አምልኳችንን፥ ጊዜያችንንና ቁሳዊ ሀብቶቻችንን ጨምሮ፥ በሕይወታችን ሁሉ ላይ መብት እንዳለው መገንዘብ አለብን። ያለን ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው።

ከሰዱቃውያን የቀረበ ጥያቄ (ማር. 12፡18-27)። ሰዱቃውያን ጥቅም የሌለው ሥነ መለኮታዊ ክርክር ለመቆስቆስ በመፈለጋቸው፥ ሰባት ባሎችን ስላገባች ሴት ክርስቶስን ጠየቁት። እነዚህ ሰዱቃውያን በትንሣኤ የማያምኑ በመሆናቸው፥ ይህን ያሉት ክርክር ለመቀስቀስ ያህል ብቻ ነበር። ክርስቶስ ሰዱቃውያን ትንሣኤን በመካዳቸው ምን ያህል ከፍተኛ ሥነ መለኮታዊ ስሕተትን እንደ ፈጸሙ አስረድቷቸዋል። እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች እንደ አብርሃም፡ ይስሐቅና ያዕቆብ በሥጋ ሊሞቱ ቢችሉም፥ በመንፈስ ግን ሕያዋን ናቸው። ለዚህም ነው እግዚአብሔር የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ተብሎ የተጠራው። ስለዚህ፥ ሞትን መፍራት የለብንም። ሞት የህልውናችን ፍጻሜ አይደለም። ሞት መንፈሳችን ሕያው የሚሆንበትን ሌላ ዓይነት ህላዌ ይጀምራል።

መ. ከሃይማኖት ሊቅ የቀረበ ጥያቄ (ማር. 12፡28–34)። ከሕግ የሃይማኖት ሊቃውንት አንዱ የክርስቶስን ጥበብ በተመለከተ ጊዜ፥ ከትእዛዛት መካከል የትኛው እንደሚልቅ ጠየቀው። አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ውስጥ 618 መሠረታዊ ሕግጋት እንዳሉ ያምኑ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሕግጋት መካከል የትኞቹ «ከባድ» የትኛው ደግሞ «ቀላል» እንደሆነ ለማወቅ ይጥሩ ነበር። ስለዚህ ይህ ሰው ክርስቶስ ከሁሉም በላይ ከባዱ ሕግ የትኛው እንደሆነ እንዲነግረው መጠየቁ ነበር። ክርስቶስ እያንዳንዱ ሃይማኖት አጥባቂ አይሁዳዊ በየጠዋቱና በየማታዊ የሚደግመውን ዘዳግም 6፡4-5 በመጥቀስ መልስ ሰጠው። በዚህ ክፍል፥ ከሕጉ በስተ ጀርባ በእግዚአብሔር ማንነት ላይ ትክክለኛ እምነት አለ። ስለ እግዚአብሔር ያለን አመለካከት የተሳሳተ ከሆነ፥ አንድን ሕግ ለመጠበቅ መሞከሩ ዋጋ የለውም። በመጀመሪያ፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ክርስቶስ የሕግጋት ሁሉ መሠረቱ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እንደሆነ ተናግሯል። እግዚአብሔርን በሁለንተናችን ብንወደው በልባችን፥ በነፍሳችንና በጉልበታችንን እግዚአብሔርን የሚያስቀይም ተግባር ልንፈጽም አንችልም። ሁለተኛ፥ ከዘሌዋውያን 19፡18 በመጥቀስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ከመወደድ ጋር ሰውን መውደድም ግንኙነት ያለው መሆኑን ገልጾአል። እግዚአብሔር ከእርሱና ከሌሎች ሰዎች ጋር ስላለን ግንኙነት አጥብቆ ስለሚያስብ፥ የመጀመሪያውና ሁለተኛው ትእዛዝ ሊነጣጠሉ አይችሉም።

የውይይት ጥያቄ ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔርን ከመውደድ ሥር የተጠቀሱትን ሕግጋት ዘርዝር። ለ) ሌሎችን እንደ ራሳችን ከመውደድ ሥር የተጠቃለሉትን ሕግጋት ዘርዝር፡ ሐ) እነዚህ ሕግጋት ከአምልኳችን (ከሚቃጠል መሥዋዕት) በላይ አስፈላጊዎች ከሆኑ፥ ዕለተ እሑድ ወደ አምልኮ ስፍራ ከመሄዳችን በፊት ምን ልናደርግ ይገባል?

የሃይማኖት መሪዎች እነዚህ ሁለት ትእዛዛት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ግንኙነት መሠረት መሆናቸውን ወዲያውኑ ተገነዘቡ። እነዚህ ትእዛዛት እንደ መሥዋዕት፥ መዝሙር፥ ስብከት ወይም የገንዘብ ስጦታ ከመሳሰሉት ውጫዊ የአምልኮ ተግባራት በላይ አስፈላጊዎች ነበሩ። ብዙ ክርስቲያኖች እሑድ ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ሊዘምሩ፥ የመዘምራንን ዜማ ሊሰሙና ስብከት ሊከታተሉ ይወዳሉ። በአዘቦት ቀናት ግን እግዚአብሔርን ከማስከበርና ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር ከማንጸባረቅ ይታቀባሉ። ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቦቻቸውና ከሌሎችም ጋር ጤናማ ግንኙነት የላቸውም። ክርስቶስ አምልኮ ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ሰዎች ጋር ካለን ጤናም ግንኙነት እንደሚጀምር አስተምሯል። እያንዳንዱ የሕይወታችን አካል የእግዚአብሔርን ፈቃድ እስካልተከተለ፥ በፍቅር እስካልተሞላና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ሁሉ ከፍቅር ቁጥጥር ሥር እስካልዋለ ድረስ፥ የትኛውም የአምልኳችን ተግባር እግዚአብሔርን ሊያስደስት አይችልም።

ሠ. ኢየሱስ ለሃይማኖት መሪዎች ያቀረበው ጥያቄ (ማር. 12፡35-40)። የሃይማኖት መሪዎች ሊያጠምዱት ሲሞክሩ ከቆዩ በኋላ፥ ክርስቶስ የሚጠይቅበት ጊዜ ደረሰ። ክርስቶስ ምናልባትም ቀደም ሲል ያላስተዋሉትን ሥነ መለኮታዊ እውነት እንዲገነዘቡ ነበር የፈለገው። በጥያቄውም መሢሑ የዳዊት ልጅ ቢሆንም፥ አምላክ መሆኑን ዳዊት በመዝሙሩ ውስጥ ጌታ እንዳለው በመጥቀስ ገለጸላቸው [መዝ. (119)፡)]።

ክርስቶስ ሕዝቡ የሃይማኖት መሪዎችን ዓይነት አመለካከት እንዳይይዙ አስጠንቅቋል። በራስ እውቀት፥ ሃይማኖትና ክርስቶስን ለማመን ባለመፈለግ መኩራራት አደገኛ ነገር ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች የሰዎችን ሙገሳ ይፈልጉ ነበር። ለእነርሱ ሃይማኖት በሌሎች ዘንድ የመታወቂያ መሣሪያ ነበር። ሰዎች ወዲያውኑ እንዲለዩዋቸውና እንዲያከብሯቸው በማሰብ ለየት ያሉ ልብሶችን ይለብሳሉ። በሚያመልኩበት ጊዜ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፊተኛውን ስፍራ ይይዛሉ። እነዚህ መሪዎች በሰዎች ፊት ለመታየት ረዣዥም ጸሎቶችን ቢጸልዩም፥ ሌሎችን ሰዎች በተለይም ተስፋ የሌላቸውን መበለቶችና እንደ እነርሱ ዓይነቶችን ከመበደል አልተመለሱም።

የውይይት ጥያቄ ጥያቄ፡- ሀ) እኛም በአለባበሳችን፥ በአቀማመጣችን፥ በአዘማመራችን በአሰባስካችን ወይም በማስተማር ስልታችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተለይተን ለመታወቅ የምንጥርባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ለ) ክርስቶስ ዛሬ በመካከላችን ቢኖር፥ ስለ አመለካከቶቻችንና ኩራታችን የሚሰጠን ማስጠንቀቂያ ምን ይሆን ነበር?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 11፡1-26

 1. ኢየሱስ እንደ ሰላም ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም በድል ገባ (ማር.11፡1-11)።

አሁን ማርቆስ የክርስቶስን ታሪክ የሚናገርበት መንገድ ተቀይሯል። በፊት ማርቆስ የጊዜ ቅደም ተከተልን ጠቅሶ የዕለት ተዕለት ሁኔታዎችን ካስረዳ በኋላ፥ «ወዲያውኑ» በሚሉ ዓይነት ቃላት ታሪኩን በፍጥነት ይተርክ ነበር፡ አሁን ማርቆስ የዕለት ተዕለት ክስተቶችን ይዘረዝራል። አሁን ቀስበቀስ የታሪኩን ፍጻሜ (የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ) ይገልጻል። በተለይም በስቅለት ዕለት ማርቆስ ክስተቶችን ከሰዓት ሰዓት እየዘረዘረ የታሪኩን ፍጥነት ዝግ አድርጎታል። በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የተገለጹትን የነገሮች ቅደም ተከተል ከዚህ በታች ይመልከቱ፡

ሀ. እሑድ፡- ኢየሱስ በድል ወደ ኢየሩሳሌም ገባ (ማር 11፡1-11)።

ለ. ሰኞ፡- ኢየሱስ በለሷን ረገመ ቤተ መቅደሱን አነጻ (ማር 11፡12-19)።

ሐ. ማክሰኞ፡- ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተጋፈጠ፥ የተለያዩ ትምህርቶችን ሰጠ (ማር 11፡20-13-37)።

መ. ረቡዕ፡- ኢየሱስ ሽቶ ተቀባ፥ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ተስማማ (ማር. 14፡1-11)።

ሠ. ሐሙስ፡- ቅዱስ ቁርባንና የኢየሱስ መያዝ (ማር. 14፡12-72)።

ረ ዓረብ፦ ኢየሱስ በጲላጦስ ተመረመረ፥ ተሰቀለ፥ ሞተ፥ ተቀበረ (ማር. 15)።

ሰ. ቅዳሜ፦ ኢየሱስ ተቀበረ።

ሸ. እሑድ፡- ኢየሱስ ከመቃብር ተነሣ (ማር. 16፡1-8)።

ሮማውያን ትልቅ ጦርነት ካሸነፉ በኋላ፥ ለጦር ጄኔራሎቻቸው ከፍተኛ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት የማዘጋጀት ባሕል ነበራቸው። የሮም ጄኔራል በትልቅ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ፊት ፊት ሲሄድ፥ ወታደሮች ከኋላ ይከተሉታል። ምርኮኞችና ባሮች ደግሞ ከወታደሮቹ ኋላ ይከተላሉ። ክርስቶስ በድልነሺነቱ በሁሉም መንገድ የተለየ ነበር። ክርስቶስ የተቀመጠው በተናቀ የአህያ ውርንጭላ ላይ ሲሆን፥ ሰዎችም እርሱን ሳይሆን እግዚአብሔርን እያመሰኑ ይዘምሩ ነበር። ነገር ግን በዚህ ጊዜም ቢሆን አይሁዶች ስለ ንጉሣቸው የተሳሳተ አሳብ ይዘው ነበር፤ እርሱ የመጣው የዳዊትን መንግሥት ለመጀመር ሳይሆን ለመሞት ነበርና።

 1. ኢየሱስ ነጋዴዎችን ከቤተ መቅደስ አስወጣ (ማር. 11፡12-19)።

ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደሱ በደረሰ ጊዜ ወዲያውኑ በቁጣ ተሞላ። ሰዎች የአምልኮን ስፍራ ለሌላ ዓላማ ሲጠቀሙ በመመልከቱ፥ በአሕዛብ አደባባይ (አሕዛብ የሚያመልኩበት) እንስሳትን ይሸጡ የነበሩትን ነጋዴዎች አባረረ። ክርስቶስ ለምን ተቆጣ? ማቴዎስ የነጋዴዎችን ሌላ ምክንያት ጠቁሟል። በአሕዛብ አደባባይ ውስጥ መገበያየቱ አሕዛብን ከአምልኮ ማደናቀፍ ነበር። ኢሳይያስ 56፡7 አሕዛብ ከአይሁዶች ጎን እግዚአብሔርን ሊያመልኩ እንደሚችሉ ቢገልጽም አይሁዶች ግን ለአሕዛብ በነበራቸው ጥላቻ ምክንያት ወደ እግዚአብሔር እንዳይቀርቡ እየከለከሏቸው ነበር። ማርቆስ የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን ለመግደል ከፈለጉባቸው ምክንያቶች አንዱ ይሄ እንደሆነ ገልጾአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ኃጢአትን ሳይፈጽሙ ሊቆጡ የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የሚቆጡባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) ብዙውን ጊዜ የእኛ ቁጣ ከክርስቶስ ቁጣ የሚለየው እንዴት ነው?

 1. ኢየሱስ የበለስን ዛፍ ረገመ (ማር. 11፡12-14፥ 20-26)።

ቀደም ባለው ቀን ክርስቶስ ፍሬ ያላት የምትመስል (ነገር ግን የሌላታን) የበለስ ዛፍ አይቶ ነበር። ይህችን በለስ በፍርድ ረገማት። በቀጣዩ ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም በሚሄዱበት ጊዜ በለሲቱ ጠውልጋ በማየታቸው ደቀ መዛሙርቱ ተደነቁ። ክርስቶስ ይህንን የእምነት ትምህርት አድርጎ ተጠቅሟል። እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ስለሆነ፥ የሚነግረን ነገር ሁሉ ይፈጸማል። እንደ ተራራ የገዘፉ የሚመስሉ ነገሮች ሳይቀር በጸሎታችን ተግባራዊ ይሆናል። እምነት እንደ መክፈቻ ቁልፍ ነች። ቁልፉ በሚዘጋበት ጊዜ የእዚአብሔር ኃይል ወደ ሕይወታችን ሊፈስ አይችልም። እምነት በሚኖርበት ጊዜ ግን ቁልፉ ክፍት ስለሆነ፥ የእግዚአብሔር ኃይል በነጻነት እየፈሰሰ ተአምራትን ያደርጋል። ይህም አይሁዶች እግዚአብሔር የሚፈልግባቸውን የጽድቅ ፍሬ ባለማፍራታቸው ምክንያት ፍርድ እንደሚመጣባቸው የሚያሳይ ስውር ታሪክ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 10፡1-52

1. ኢየሱስ ስለ ጋብቻና ፍች አስተማረ (ማር. 10፡1-12)።

ፈሪሳውያን ክርስቶስን ለመፈተን በመፈለግ ስለ ፍች ጠየቁት። በዚህ ጊዜ እርሱም በፍች ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን አመለካከት ገልጾላቸዋል። ፍች ሁልጊዜም የኀጢአትና በእግዚአብሔር ዓላማ ላይ የማመፅ ምልክት ነው። እግዚአብሔር ጋብቻን የወጠነው ባልና ሚስት በጣም በመቀራረብ በአሳብና በተግባር እንዲጣመሩ ነው። ፍችን ማበረታታት በእግዚአብሔር ፍላጎት ላይ ማመፅ ነው። ፍች የሚፈቀድበት ብቸኛው ጊዜ ግንኙነቱ በዝሙት የተበላሸ እንደሆነ ብቻ ነበር። ከተፋታ ሰው ጋር መጋባቱም በዝሙት ከመኖር እኩል ነው።

በምዕራቡ ዓለም፥ ክርስቲያኖች በእነዚህ ጥብቅ የጋብቻ ትእዛዝ ላይ ዓምፀዋል። ከዚህም የተነሣ፥ ፍች የዓለማውያንን ያህል በዝቷል። ይህ የክርስቶስ ትምህርት ሁሉንም ሁኔታዎች ላያካትት ይችላል። ለምሳሌ፥ አካላዊ ጥቃት በሚኖርበት ጊዜ ምን ማድረግ ይገባል?) ለተጨማሪ የፍች ሁኔታ 1ኛ ቆሮ.7፡15ን ይመልከቱ።) ነገር ግን ይህን ትምህርት በከፍተኛ አክብሮት መቀበል አለብን። ችግሮቹ ምንም ያህል ከባድ ቢሆኑም፥ በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ክርስቲያኖች ሁሉንም አሸንፈው በአንድነት ሊኖሩ ይችላሉ።

ነገር ግን እግዚአብሔር ለጋብቻ የወጠነውን ፍጹማዊ ዕቅድ የምናፈርስበት ሌላ መንገድ አለ። ወንጌላውያንን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ከትዳር ጓደኞቻቸው ተለይተው ለወራት ይቀመጣሉ። ብዙውን ጊዜ ባልና ሚስት በብዙ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ይቀመጣሉ። ስሦስት ወር ወይም በዓመት አንድ ጊዜ ይገናኛሉ። ይሄ እግዚአብሔር ያጣመረውን የምንለይበት ሌላው መንገድ አይሆንም? የእግዚአብሔር ፍላጎት የባልና ሚስት አብሮ መኖር ከሆነ፥ ከዚያ ውጭ የሆነው ሁሉ ኃጢአት አይደለምን? ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ቤተሰባችንን መለያየቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ እርግጠኞች ነን? ወይስ የገንዘብ ፍቅር እግዚአብሔርን ወደማናስከብርበት አቅጣጫ እየመራን ይሆን? የቤተሰብና የአካባቢ ሁኔታ ወንጌላውያንን ከሚስቶቻቸው ቢለያቸው፥ ቤተሰባቸውን ክርስቶስን ከመታዘዝ አላስበለጡም ወይ? ቤተሰብ የቤተ ክርስቲያን እጅግ ጠቃሚ ክፍል ከሆነ፥ አነስተኛ ገቢና ተጨማሪ ችግሮች ቢገጥሙንም እንኳ ቤተሰብን ልንንከባከብ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች በባልና ሚስት መካከል ሰለሚኖረው ግንኙነትና ስለ ጋብቻ ያላቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች፥ እግዚአብሔር ለአእምር፥ ለልብና ለዓላማ አንድነት ያለውን ፍላጎት ሲያበላሹ የተመለከትህበትን ሁኔታ በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) ብዙ ክርስቲያኖች በሥራ ምክንያት ከትዳራቸው ሲርቁ የተመለከትህበትን ሁኔታ አብራራ። ይህ በቤተ ክርስቲያንና በቤተሰብ ላይ ያስከተላቸው አሉታዊ ውጤቶች ምንድን ናቸው?

2. የእግዚአብሔር መንግሥት የተገነባችው እንደ ልጆች ባሉ ሰዎች ነው (ማር. 10፡13-16)።

ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ባይቆጣም፥ አንዳንድ ጊዜ ግን ይህንኑ ሲያደርግ እንመለከታለን። ከእነዚህ ጥቂት ጊዜያት አንዱ፥ ልጆች አስቸጋሪዎች እንጂ በእግዚአብሔር ዓይኖች ብርቅ መሆናቸውን ያላጤኑት ደቀ መዛሙርት፥ ወደ ክርስቶስ እንዳይቀርቡ በተከላከሉበት ጊዜ የሰነዘረው ቁጣ ነበር። ክርስቶስ ቀን ለደቀ መዛሙርቱ ልጆች የእግዚአብሔር መንግሥት ሕይወት አርአያዎች እንደሆኑ ነገራቸው። ልጆች በወላጆቻቸው ላይ በፍጹም ልባቸው እንደሚተማመኑ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች በፍጹም ልባቸው ሊተማመኑበት ይገባል።

3. ደቀ መዝሙርነት ማለት ኢየሱስን ከምንም ነገር በላይ መውደድ ማለት ነው (ማር. 10፡17-31)።

ክርስቶስ ግብረገባዊ ሕይወት ይመራ ለነበረው ሀብታም ወጣት ሹም፥ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን ከፈለገ ገንዘቡን ሁሉ ለድሆች መስጠት እንዳለበት ሲናገር፥ ሹሙ ወደ ኋላ ተመለሰ። ለዓለም ነገሮች፥ በተለይም ለገንዘብ የነበረው ፍቅር ሁሉንም ነገር ትቶ ክርስቶስን የበለጠ መውደዱን እንዳያሳይ አገደው።

ደኅንነትና ክርስቶስን መከተል ቀላል አይደለም። እሑድ ቀን እጅን አንሥቶ ክርስቶስን እከተላለሁ ማለቱ ብቻ አይበቃም። ክርስቶስን መከተል ሕይወትን መስጠት ነው። ክርስቶስ በሕይወታችን ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝና ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር የሚያደናቅፍ ነገር ሁሉ ሊወገድ ይገባል። ለዚህ ሰው መሰናክል የሆነው ገንዘብ ሲሆን፥ ለሌሎች ደግሞ ትምህርት ወይም የቤተሰብ ፍቅር ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ ይህ ሰዎች በተፈጥሯዊ ብርታታቸው የሚያደርጉት ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ኀይል ለክርስቶስ ብለው ሁሉንም ነገር የሚተዉበት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ነገር ግን አንድ ሰው ሁሉንም ነገር ለክርስቶስ በሚሰጥበት ጊዜ የበለጠ ዋጋ ያገኛል። በዓለም ፊት ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዙ የሚፈልጉ ሀብታሞችና ዝነኞች፥ በዘላለሙ መንግሥት የመጨረሻውን ስፍራ ሲያገኙ ክርስቶስን በመከተላቸው ምክንያት ዓለም የናቀቻቸው በእግዚአብሔር መንግሥት ቀዳሚ ይሆናሉ።

4. ኢየሱስ እንደገና ስለ ሞቱ ተነበየ (ማር. 10፡32-34)።

ክርስቶስ የሚሞትበት ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ፥ ስለ ሞቱ በበለጠ መናገሩን ቀጠል። ክርስቶስ ስለዚሁ ጉዳይ ለአራተኛ ጊዜ ሲተነብይ፥ ሞቶ እንደሚነሣ ተናግሯል። ክርስቶስ ከስደት ለመሸሽ ያልፈለገው፥ ይህ በግልጽ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበር ነው። ተከታዮቹም ተመሳሳይ አመለካከት ይኖራቸው ነበር። 

5. መሪነት በኢየሱስ መንግሥት (ማር. 10፡35-45)

ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለምንድን ነው? በማርቆስ 10፡45 የተሰጠው ግልጽ ምሳሌ እንደሚያስረዳው ክርስቶስ የመጣው «ሰዎች እንዲያገለግሉት ሳይሆን፥ ሰዎችን ለማገልገልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ነበር»። ክርስቶስ የመጣው ሌሎችን እንጂ ራሱን ለማገልገል አልነበረም። የመሥዋዕቱ ጥልቀት ሰዎችን ከኀጢአታቸው ነፃ ለማውጣት መሞቱን ያረጋግጣል።

ይሁንና፥ ክርስቶስ ጠቃሚ ትምህርት ለማስተማር ወደ ምድር መምጣቱን የሚያሳይ ግልጽ ብያኔ ሰጥቷል። ያዕቆብና ዮሐንስ በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ሹመት ለማግኘት ፈልገው ነበር። ይህ የሌሎችንም ደቀ መዛሙርት ፍላጎት ያንጸባርቅ ስለነበር፥ የእነዮሐንስ አነጋገር ሌሎቹን አስቆጣቸው። ክርስቶስ ተከታዮቹ በተለይም መሪዎች ከዓለማውያን የተለየ የአመራር አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግሯል። አመራር ራስን ለማገልገል፥ ክብርን፥ ሥልጣንንና ኀይልን ለማግኘት ተብሎ የሚገባበት ሳይሆን፥ ሌሎችን ለማገልገል የራስን ሕይወት የሚጠይቅ ነው። ማርቆስ፥ መሪዎች ሲባሉ የሌሎች ሰዎች «አገልጋዮች» እንደሚሆኑ ገልጾአል። ሌሎችን ከማገልገል ውጭ የሆነው ምክንያት ከዓለም የሚመጣ በመሆኑ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ክርስቶስ በሚፈልገው መንገድ ከመምራት ይልቅ፥ ወደ ጥፋት የሚያደርስ ይሆናል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለመምራት ሕይወቱን ስለ ሰጠ፥ እኛም ለሌሎች ይህንኑ ልናደርግ ይገባል። 

6. ኢየሱስ ዓይነ ስውሩን በርጤሜዎስ ፈወሰ (ማር 10፡46-52)

ክርስቶስ ሌሎችን ካገለገለባቸው ምሳሌዎች መካከል፥ ለመሞት ወደ ኢየሩሳሌም በሚሄድበት ጊዜ የለማኙን ጩኸት ሰምቶ የፈወሰበት አንዱ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 9፡1-50

 1. ኢየሱስ ሰማያዊ ክብሩን ገለጸ (ማር. 9፡1-3)።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ከመሞታቸው በፊት ክብሩን እንደሚያዩ ከተናገረ በኋላ፥ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ወደ ተራራ ወጣ። በዚያም መለኮታዊ ክብሩን ገለጸ። በዚያም ሕግን የወከለው ሙሴና ነቢያትን የወከለው ኤልያስ ቀርበው ከኢየሱስ ጋር ተነጋገሩ። ለሁለተኛ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር የሚወደው ልዩ ልጁ እንደሆነ ሰሙ። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ምን ያህል እንደ ተደሰቱ አስቡ። ወዲያው ግን ኢየሱስ አምላክ ቢሆንም እንኳ፥ መከራን እንደሚቀበልና በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን እንደሚያጣ በመግለጽ ደቀ መዛሙርቱን አስደነገጠ። ያዩትን ሁሉ ለሌሎች አለመናገሩ ሳይከብዳቸው አልቀረም።

 1. ኢየሱስ ከአንድ ልጅ አጋንንትን አስወጣ (ማር. 9፡14-32)።

ደቀ መዛሙርቱ ከተራራው ሲወርዱም እንደገና ደነገጡ። ከልጁ አጋንንት ለማውጣት ባለመቻላቸው ወደ ተራራው ያልመጡት ደቀ መዛሙርት፥ ተጨንቀውና አፍረው ቆመው ነበር፡፡ ቀደም ሲል ክርስቶስ ለአገልግሎት በላካቸው ጊዜ ያከናወኑት አጋንንትን የማስወጣት ተግባር፥ ለምን እንደ ተሳናቸው ሊገባቸው አልቻለም ነበር።

ክርስቶስ ይህንን ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ እምነት ለማስተማር ተጠቀመበት፡፡ በመጀመሪያ፡ ለልጁ አባት፥ ለሚያምን ሁሉም እንደሚቻል ገለጸለት (ማር. 9፡23)። ስለ እምነት ልናስታውሳቸው የሚገቡን ሁለት ነገሮች አሉ። ታላላቅ ነገሮችን የሚሠራው ራሱ እምነታችን ሳይሆን፥ የምናምንበት አካል ነው። ስለሆነም በጣዖታት ላይ ከፍተኛ እምነት ያለው ሰው ታላላቅ ነገሮችን ሊያሳካ አይችልም። ነገር ግን በታላቁ አምላክ ላይ አነስተኛ እምነት ያለው ሰው እግዚአብሔር ታላላቅ ተአምራትን ሲሠራ ሊመለከት ይችላል። በተገላቢጦሹ እምነት በማይኖርበት ጊዜ ወይም ሰዎች ለማመን ሳይፈልጉ ሊቀሩ፣ እግዚአብሔር ተአምራትን ለመሥራት አለመቻሉ ሳይሆን፥ ነገር ግን ሰዎች እርሱን ወይም ችሉታውን በሚጠራጠሩበት ጊዜ ለመሥራት አለመምረጡ ነው።

ሁለተኛ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ሥራዎችን ለማከናወን በእምነት መጽናት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱን ያጋጠቸው ችግር ክርስቶስ በተአምር ለመፈወስ ኃይልን ማጣቱ አልነበረም። ክርስቶስ በአንድ የትእዛዝ ቃል ነበር አጋንንቱን ሁሉ ያስወጣው። ተግቶ የማይሠራ ሰው ጠንካራ ጡንቻ ሊኖረው አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ በጸሎት ጽኑ ትግል የማያደርግና በጾም በእግዚአብሔር ላይ ጥገኛ መሆኑን የማያሳይ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጡንቻ ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ቀደም ሲል እኛን ለመርዳት ቢሠራም እንኳ፥ ጥያቄዎቻችንን በፍጥነት የማይመልስባቸው ጊዜያት አሉ። እምነታችንን የሚፈታተን ሁኔታ ሁሉ አዲስ ሁኔታ ነው። በቀድሞው ስኬት ወይም ብርታት ላይ ሳንመሠረት፥ እንደገና በእግዚአብሔር ላይ ጥገኝነታችንን ማኖር አለብን።

የውይይት ጥያቄ- ሀ) ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ከተሳካልን በኋላ፥ በእግዚአብሔር ላይ መደገፋችንን የምናቋርጠው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር ለጸሎትህ ፈጣን ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት መንፈሳዊ ብርታትህ የጨመረባቸውን መንገዶች የሚያሳዩ ምሳሌያችን ስጥ።

ማርቆስ ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ስለ መጭው ሞቱ፥ ቀብሩና ትንሣኤው መግለጹን ዘግቧል።

 1. ኢየሱስ በመንግሥቱ ውስጥ አመራር ምን እንደሚመስል አስተማረ (ማር. 9፡33-50)

የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስወገዱ ቀላል አይደለም። እጅግ ከተሳሳቱ እመለካከቶች አንዱ ሥልጣንና የመሪነት ስፍራ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው። በዓለም ሁሉ ያለው ባሕል በራስ ጥቅም ላይ ያተኩራል። ሰዎች መሪ ከሚሆኑባቸው ዋንኛ ምክንያቶች አንዱ ሥልጣን፥ ሀብትና ኀይል ለማግኘት ነው። ይህ አመለካከት ካልተወገደ በስተቀር ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ መምራት አይቻልም። ይህ የኀይልና የክብር ፍላጎት ደቀ መዛሙርቱን ይፈታተናቸው ስለ ነበር፥ ክርስቶስ የመንግሥቱ አመራር በአምስት መንገዶች እንደሚለይ አስተምሯል።

ሀ. በክርስቶስ መንግሥት አመራር ከዓለም የተለየ ነው። ታላቅነት የሚለካው አንድ መሪ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከራስ ወዳድነት በጠራ መንፈስ ሌሎችን ለማገልገል በመቻሉ ነው፡፡ እንደ ትልልቅ ሰዎች በችሎታችንና በታላቅነታችን ከመመካት ይልቅ፥ እንደ ልጆች በእግዚአብሔር አብ ላይ ጥገኞች ልንሆን ይገባል።

ለ. በክርስቶስ መንግሥት አመራር የሚያከብረው ታላላቆች ናቸው የተባሉትን ሳይሆን፥ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ሰዎች ነው። ጠቃሚዎች ናቸው የምንላቸውን ሰዎች (ሀብታሞች፥ ነጋዴዎች፥ ምሁራን) እየወደድን፥ ጠቃሚዎች አይደሉም የምንላቸውን ሰዎች (ልጆች፥ ሴቶች፥ ድሆች፥ መሃይማንን) እንንቃለን። በክርስቶስ መንግሥት ለዓለም የማይጠቅሙ የሚመስሉ ሰዎች አስፈላጊዎች ናቸው።

ሐ የእግዚአብሔር መሪዎች ሌሎች ስኬታማ ሲሆኑና እግዚአብሔር ባልተጠበቁ መንገዶች ሲሠራ በሚመለከቱበት ጊዜ አይቀኑም። አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ሌላ አማኝ ክርስቶስን ሳያስፈቅድ አጋንንት ሊያወጣ በማየታቸው ቀንተው ክርስቶስ እንዲከለክለው ነገሩት። ክርስቶስ ግን የአመራር ሚና ሰዎችን ማበረታታት እንጂ መቆጣጠር እንዳልሆነ አስተማራቸው። ለእግዚአብሔር ክብርን የሚያመጣ ማንኛውም ነገር በሚከሰትበት ጊዜ መደሰት አለብን። ይህ የግድ «በእኛ» መሪዎች ወይም በምንጠብቃቸው ሰዎች መከናወን የለበትም። ምክንያቱም ለክርስቶስ ክብር የሚሠራ ሰው፥ ወዲያውኑ ተመልሶ የክርስቶስ ጠላት ሊሆን ስለማይችል ነው።

መ. አገልግሎት የሚለካው በምናከናውናቸው ተግባራት ታላቅነት ሳይሆን፥ በታማኝነትና በጥሩ አመለካከት በማገልገላችን ነው። የግድ ታላላቅ ሰባኪያን ወይም አስተማሪዎች መሆን የለብንም። የባሪያን በሚመስል አመለካከት የተሰጠ አንድ ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ዋጋ አለው።

ሠ. መሪዎችና በሌሎች ላይ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች፥ (ለምሳሌ፥ ወላጆች) በተግባራቸውና በአመለካከታቸው ትንንሽ ልጆችንና የቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ወደ ኀጢአት እንዳይገፉ መጠንቀቅ አለባቸው። ክርስቶስ ሌሎችን በኀጢአት ለማሰናከል የተጋነነ ቋንቋ በመጠቀም አንድን ሰው ከማሰናከል ይልቅ፥ የግል አካላዊ ጉዳትን መቀበል እንደሚሻል ተናግሯል። ሌሎችን የሚያሰናክሉ ሰዎች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ ዛሙርት ባለመሆናቸው፥ ከፍተኛ ቅጣት ይደርስባቸዋል። ተግባሮቻችንና አመለካከቶቻችን እንደ ብርሃን እያንጸባረቁ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መምራት ይኖርባቸዋል። መንፈሳዊ ባሕርይን በመላበስ (በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ)፥ እርስ በርሳችን በሰላም እንኖራለን።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ክርስቶስ ስለ መሪነት ያስተማረውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር እነጻጽር፡፡ ለ) አመራርን ይበልጥ ክርስቶስ ባየበት ዓይን ለመመመልከት፥ ከተግባራችንና ከእመለካከታችን ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

 

ማርቆስ 8፡1-38

 1. ኢየሱስ አራት ሺህ ሕዝብን መገበ (ማር. 8፡1-21)

ክርስቶስ ምንም ያህል ሥራ ቢበዛበትም ስለ ሰዎች ጥቅም የሚያስብ ሲሆን፤ ጉዳታቸው ልቡን ይሰማውና ይራራላቸው ነበር። በዚያን ጊዜ ለሰዎች መጎዳት የራራው ክርስቶስ፥ ዛሬም የሚያስፈልገንን ሁሉ በሚመለከትበት ጊዜ ይራራልናል።

ክርስቶስ አሁን አራት ሺህ ሕዝብ ለመመገብ ያነሣሣውን የርኅራኄ ምክንያት ቀደም ሲል አምስት ሺህ ሕዝብ በመገበበት ወቅት፥ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሮ የነበረውን ትምህርት አጠናክሯል። በዚህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን ሁሉ የሚያሟላ አምላክ መሆኑን አሳይቷል።

ፈሪሳውያን እንዲህ ያለ ታላቅ ተአምራት ቢመለከቱም እንኳ፥ በክርስቶስ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም። የአንድ ግለሰብ ልብ ከደነደነና በክርስቶስ ላለማመን ከወሰነ፥ ምንም ዓይነት ተአምራት ቢመለከት ሊያምን አይችልም። እግዚአብሔር ኀይሉን ለማሳየት በተአምራት ሊጠቀም ቢችልም፥ ሰዎች ሁልጊዜ በተአምራት ላይ ካተኮሩ፥ ይህ ፍላጎታቸው የእምነት እጥረት እንዳለባቸው ያሳያል። ፈሪሳውያን ክርስቶስ መሢሕነቱን ለማረጋገጥ ከዚያ የበለጡ ተአምራት እንዲሠራ ጠይቀውታል። ክርስቶስ ግን ተአምራት የማያምን ትውልድ ምልክቶች መሆናቸውን በመግለጽ፥ ለማመን ለማይፈልጉ ሰዎች ታምራትን እንደማያደርግላቸው ገልጾአል።

ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ራስን የማጽደቅ አመለካከት እንዳይይዙና ለማመን ተጨማሪ ተአምራትን እንዳይሹ አስጠንቅቋቸዋል። ራስን የማጽደቅ አመለካከት እንደ እርሾ መንፈሳዊነታቸውን በማጥፋት ወደ ሌሎችም ይዛመት ነበር።

12ቱ ደቀ መዛሙርት እንደ ብዙዎቻችን ከመንፈሳዊ እውነት ይልቅ በምድራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮራቸው፥ የክርስቶስን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ ተረጎሙ። የሚያስቡት ክርስቶስ ስለ ፈሪሳውያን ባስተማረው ጉዳይ ላይ ሳይሆን፥ ስለ ምግብ ነበር። ይህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን ሊያሟላ እንደሚችል አለማመናቸውን ያሳያል።

 1. ኢየሱስ ዓይነ ስውሩን ፈወሰ (ማር. 8፡22-26)

ይህ ተአምር በሁለት ደረጃዎች የተከናወነ በመሆኑ፥ በክርስቶስ አገልግሎት ውስጥ ለየት ያለ ነበር። ብዙውን ጊዜ የክርስቶስ ተአምራት በአንድ ጊዜ የተሳካ ውጠቶችን የሚያስገኙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ግን ክርስቶስ መጀመሪያ በታወሩት በሰውዬው ዓይኖች ላይ ምራቁን ቀባ። የግለሰቡ ዓይኖች በከፊል ስለ ተፈወሱለት፥ ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አየ። ነገር ግን ክርስቶስ እንደገና ሲዳስሰው ዓይነ ስውር የነበረው ግለሰብ አጥርቶ ለማየት ቻለ።

ይህ ምንን ያሳያል? ይህ አንዳንድ ጊዜ ተአምራት በከፊል ብቻ ውጤታማ እንደሚሆኑ ያሳያል? ዛሬ የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ ይላሉ። ነገር ግን በዚህ ግንዛቤና በክርስቶስ ፈውስ መካከል አንዳንድ ዐበይት ልዩነቶች አሉ። ክርስቶስ አንድም ሰው በከፊል ፈውሶ ብቻ አላሰናበተም። የፈውሱን እርግጠኝነት ተጠራጥሮ እንደገና የተሟላ ፈውስ የሰጠው ራሱ ክርስቶስ ነበር። ማንም ሰው ከክርስቶስ ዘንድ ከፊል ፈውስ አግኝቶ የሄደ የለም። ዛሬም እግዚአብሔር አንድን ሰው በተአምራዊ መንገድ ከፈወሰው፥ ከፊል ሳይሆን ሙሉ ፈውስ ነው።

ክርስቶስ ይህንን ባለ ሁለት ደረጃ ፈውስ ያካሄደው አንዳች መንፈሳዊ እውነት ለማስተማር ይሆን? የአንድን ሰው መንፈሳዊ ዓይኖች መክፈት ማለትም፥ መንፈሳዊ እውነትን መረዳት ብዙውን ጊዜ የሂደት አካል ነው። በአንድ ጊዜ መንፈሳዊ እውነቶችን ሙሉ በሙሉ ሊረዳ የሚችል ሰው የለም። ደቀ መዛሙርቱም አልተገነዘቡም ነበር። ለዚህም ነበር ስለ ክርስቶስ አገልግሎት ብዙ ነገሮችን ከትንሣኤው በፊት ለመረዳት ያልቻሉት። ጳውሎስም ሳይቀር ነገሮችን በድንግዝግዝ እንደሚያይ ለማመን ተገድዷል (1ኛ ቆሮ. 13፡12)። ይህን ስላለ ግን ተስፋ እንቆርጣለን ማለት አይደለም። ይህ ትሑት እንድንሆን ያስተምረናል። በተጨማሪም፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደጋችንን እንድንቀጥል ያስተምረናል።

 1. ጴጥሮስ የኢየሱስን መሢሕነት መሰከረ (ማር. 8፡27-30)

የማርቆስ ወንጌል የተመሠረተው በዚህ አጭር ምንባብ ላይ ነው። ማርቆስ ክርስቶስ መሢሑ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በብዙ የተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። በመጨረሻም፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ግል እምነታቸው የተጠየቁበት ጊዜ ደረሰ። ብዙውን ጊዜ ሌሎች ሰዎች ወይም ወላጆቻችን የሚያምኑትን ሃይማኖት መከተሉ ቀላል ነው። ነገር ግን ጠቅላላው ማንነታችን በእምነታችን ሊለወጥ በሚችልበት መልኩ በግላችን እውነትን ማመን አለብን። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በጠየቀበት ሰዓት፥ መጀመሪያ ስለ ሌሎች ከጠየቀ በኋላ፥ የራሳቸውን እምነት እንዲገልጹት አድርጓል።

 1. ኢየሱስ ስለ መጭው ሞቱና የደቀ መዝሙርነት መንገድ አስተማረ (ማር. 8፡31-38)።

ጴጥሮስና ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን መሢሕነት ከተገነዘቡ በኋላ፥ ጠቅላላው የኢየሱስ አገልግሎትና የማርቆስ ወንጌል ትኩረት ተለውጧል። በመጀመሪያ፥ ምን ዓይነት መሢሕ እንደሆነ የነበራቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማስተካከል ነበረበት። እርሱ መከራ የሚቀበልና የሚሞት እንጂ፥ ወረራ የሚያካሂድና የሚገዛ ንጉሥ አልነበረም። ሁለተኛ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱን መከተል መስቀልን እንደሚያስከትል ነግሯቸዋል። ይህም ክርስቶስን በሚከተሉበት ጊዜ በመንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወታቸው እንደሚሞቱ የሚያመለክት ነበር።

ከዚህ ጊዜ አንሥቶ፥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለሚመጣው ሞቱ ይናገር ጀመር። መጀመሪያ ይህ ደቀ መዛሙርቱን ስላስደነገጣቸው፥ ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነት የመሢሕነት እርምጃ አይድረስብህ አለው። ክርስቶስ ሰይጣን በጴጥሮስ ቃላት ተጠቅሞ ከመስቀል ሊመልሰው የመፈለጉን ፈተና ተገነዘበ። ክርስቶስ ይህን ሁኔታ ስለ ደቀ መዝሙርነትም ለማስተማር ተጠቅሞበታል። ክርስቶስ የሚሞትበትን መስቀል ተሸክሞ ወደ ጎልጎታ በመሄድ ለሰው ልጆች ደኅንነትን አስገኝቷል። ደቀ መዛሙርቱም እያንዳንዳቸው የሚሸከሙት መስቀል ነበራቸው። መስቀላችን መንፈሳዊ ነው። ራሳችን በሕይወታችን ላይ ላለን ቁጥጥር፥ ለዓለማዊ ብልጽግና መሞት አለብን። የደቀ መዝሙርነት መንገድ ማለት ሥጋዊ ሕይወታችንን ጨምሮ በዚህ ዓለም ጠቃሚዎች ናቸው የተባሉትን ነገሮች ሁሉ ማጣትን ያካትታል። ከዚያ በኋላ ለሰው ከሁሉም የበለጠ ዋጋ ያለውን የዘላለምን ሕይወት እናገኛለን። ነገር ግን ሕይወታችንን ብንታደግና በዓለም ጠቃሚዎች የሆኑትን ነገሮች ብንከተል፥ የዘላለም ሕይወታችንን እናጣለን። በስደት ጊዜ፥ በክርስቶስ አፍረን እርሱን ከመከተልና ቃሉን ከማስተማር ብንቆጠብ፥ ዘላለማዊ ጉዳት ይደርስብናል። በዘላለሙ መንግሥት፥ ክርስቶስ በአባቱ ፊት አያከብረንም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ጠቃሚዎች እንደሆኑ የሚያስቧቸውንና፥ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ ለመተው የሚቸገሩባቸውን ነገሮች ዝርዝር። ለ) ክርስቲያኖች በክርስቶስና በቃሉ ማፈራቸውን የሚያሳዩባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ሐ) የመስቀሉን መንገድ መከተል እንዴት እንደ ለወጠህ ግለጽ።

ከዚህ በኋላ፥ ክርስቶስ በሞቱ ላይ ስላተኮረ ታሪኩ ተለውጧል። እርሱም ቀስ በቀስ ወደሚሞትባት የኢየሩሳሌም ከተማ ተጓዘ፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ስለ ሞቱና ትንሣኤው በተደጋጋሚ ይነግራቸው ጀመር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 7፡1-37

 1. ክርስቶስ ሰውን ስለሚያረክስ ነገር አስተማረ (ማር. 7፡1-23)

በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ከቀረቡት ረዣዥም ታሪኮች አንዱ፥ ሰውን ስለሚያረከሱና ስለሚያነጹ ነገሮች የሚያስረዳው ነው። ይህ ቤተ ክርስቲያን ልትረዳው የሚገባት ጠቃሚ እውነት ነው። በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ይጠይቋቸው ከነበሩት ዐበይት ጥያቄዎች አንዱ፥ «ሃይማኖታዊ ንጽሕናችንን ለማሳየት ልንጠብቃቸው የሚገቡ ትውፊቶች አሉ ወይ?» የሚል ነበር። ለብዙ ምእተ ዓመታት አይሁዶች የተወሰኑ ነገሮችን በማድረግ ውስጣዊ ሕይወትን በንጽሕና መጠበቅ እንደሚቻል ተምረው ነበር። ለምሳሌ፥ ንጽሕናን በተመለከተ አንዱ መንገድ የተወሰኑ የሥጋ ምግቦችን አለመመገብ ወይም ደሞ እጅን በተወሰነ መንገድ መታጠብ። ይህ ሥርዓት የእግዚአብሔር ፈቃድና ጠቃሚ መሆኑን ሲማሩ የነበሩት አይሁዶች፥ በክርስቶስ ባመኑበት ጊዜ፥ ክርስቲያኖችም ይህንኑ ማድረግ አለባቸው ብለው ያስቡ ነበር። አይሁዶች ብቻ ሳይሆኑ የአሕዛብ ክርስቲያኖችም እነዚህኑ ሥርዓቶች እንዲፈጽሙ ተነግሯቸዋል። ላይ ላዩን ሲታይ የተወሰኑ ምግቦችን መመገቡ ወይም እጅን መታጠቡ ብዙ ለውጥ ስለማያመጣ፥ ለአሕዛብ የአይሁድን የአኗኗር መንገዶች መከተሉ ከባድ አልነበረም። ነገር ግን በውስጡ አደገኛ የሆነ ትምህርት እንደነበረ ግልጽ ነው። ይህም የተወሰኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በምንፈጽምበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ደስ እንደሚሰኝብን፥ እንዲሁም ለእኛ የተስማማን ነገር ሁሉ ለሁሉም ሰዎች መልካም እንደሆነ አድርገን እንደምንገምት የሚያሳይ ነው። ስለሆነም፥ የኃጢአት ሥር የሚኖርበትን የልባችንን አመለካከት ትተን በሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ እናተኩራለን።

የሃይማኖት መሪዎች፥ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰዎችን ንጹሕ ያደርጋሉ የሚሏቸውን አንዳንድ ሥርዓቶች አለመከተላቸውን በመግለጽ በወቀሱዋቸው ጊዜ፥ ክርስቶስ ሁለት ጠቃሚ ነገሮችን አስተማራቸው። በመጀመሪያ፥ በውጫዊ ልማዶችና ሥርዓቶች ላይ በማተኮር፥ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነውን ነገር ላለማየት የመታወር አደጋ መኖሩን ገለጸ። ፈሪሳውያን እግዚአብሔርን በአፋቸው እያከበሩ፥ በሕግጋት ላይ ቢያተኩሩም፥ ልባቸው ወደ እግዚአብሔር ስለመቅረቡ ግድ የላቸውም ነበር፡፡ ሕግጋቱን በቀላሉ ወደሚፈጽሙበት አቅጣጫ ጠምዝዘዋቸው ነበር። ይህም እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እየኖርን ነው ብለው እንዲከራሩ አደረጋቸው። ብዙውን ጊዜ ግን እግዚአብሔር በማይፈልገው መንገድ ይመላለሱ ነበር። ስለዚህ አመለካከታቸው ከእግዚአብሔር ትእዛዛት «መንፈስ» የራቀ ነበር።

ሁለተኛ፣ ጌታችን የትኛውም ሰው ሠራሽ ውጫዊ ተግባር አንድን ሰው ንጹሕ ወይም ርኩስ ሊያደርግ እንደማይችል አስተማረ። መንፈሳዊ ንጽሕና ወይም ርኩሰት የሚመጣው ከልብ ነው። የሰው አመለካከቶች፥ አሳቦችና ፍላጎቶች የሚኖሩት በልብ ውስጥ ነው። ልብ የመልካም ነገሮች (እግዚአብሔርንና ባልንጀራን መውደድ) እና የመጥፎ ነገርች (ጥላቻ፥ ምኞት፥ ቁጣ) ምንጭ ነው። የክርስቶስ ተከታዮች በእነዚህ ነገሮች ላይ ማተኮር አለባቸው፡ ተግባራችን መልካምና እግዚአብሔርን የሚያስከብር ይሆን ዘንድ ከርኩስ ነገሮች መራቅ አለብን። እውነተኛ ሃይማኖት ሰዎች የሚያዩት ሳይሆን፥ በአማኙ ልብ ውስጥ ያለው ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ክርስቲያንነታቸውን የሚያሳዩባቸው፥ ጠቃሚና መልካም ተደርገው የሚወሰዱትን አንዳንድ ክርስቲያናዊ ልምምዶች ለምሳሌ፥ ዓይንን ጨፍኖ መጸለይ፥ በጌጣጌጥ አለመዋብ የመሰሉትን ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ ባስተማረው መሠረት፥ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን ዓይነት ግንዛቤ ሊኖርህ ይገባል?

ክርስቶስ ፈሪሳውያን ወይም ደቀ መዛሙርት እነዚህን ሰው ሠራሽ ልምምዶች እንዲያቆሙ አልተናገረም። ነገር ግን ስለ ደንቦች ትክክለኛ ጭብጥ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስጠንቅቋቸዋል። ከጊዜ በኋላ ሁላችንም ትክክል ናቸው የምንላቸውን ውጫዊ ልምምዶች እናዳብራለን። ለምሳሌ፥ አልኮል አለመጠጣት ጥሩ ክርስቲያን መሆናችንን ያሳያል ብለን እናስባለን። (ማስታወሻ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ኃጢአት የተጠቀሰው መስከር ብቻ ነው)። ዓይኖቻችንን ጨፍነንና እጆቻችንን አጣጥፈን መጸለይ እንዳለብን እናስባለን፤ ስንዘምርም ዓይኖቻችንን ጨፍነን ራሳችንን ወደ ሰማይ እናቀናለን። በዕልልታ ሃሌ ሉያ እያልን እንጮኻለን። እነዚህ ድርጊቶች ስሕተት ባይሆኑም፥ እንድናደርጋቸው እግዚአብሔር ያዘዘን አይደሉም። መንፈሳዊ ሕይወታችን ምን እንደሚመስል እነዚህ ነገሮች አያሳዩም። ጫማ ሳያወልቁም ሆነ፥ አውልቆ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማምለክ ይቻላል። ዓይንን ጨፍኖ ወይም ሳይጨፍኑ መጸለይ ይቻላል። በዝማሬ ጊዜ ዓይንን መጨፈን ወይም አለመጨፈን እጅን ማንሳት ወይም ማውረድ፥ ማጨብጨብ ወይም አለማጨብጨብ ይቻላል። በአምልኮ ውስጥ እነዚህ ውጫዊ ተግባራት ትክክል ወይም ስሕተት የሚባሉ አይደሉም። ዋናው የልባችን ሁኔታ ነው።

 1. ታላቅ እምነት ያላት አሕዛብ (ማር 7፡24-30)

ክርስቶስ ጎሰኛ ነበር? የገዛ ወገኖቹ ለነበሩት ለአይሁዶች ብቻ ይጨነቅ ነበር? ወይስ ለአሕዛብም ያስብ ነበር? ለሮማውያን አንባቢዎች እነዚህ ጥያቄዎች አስፈላጊዎች ነበሩ። ስለሆነም፥ ማርቆስ ክርስቶስ ወደ ሶርያና ፊንቂ ተጉዞ አሕዛብ የነበረች ሴት እንዳገኘ አብራርቷል። ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት አይሁዶችን በመጀመሪያ ለማገልገል መጠራቱን ተናግሯል። ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች የነበሩትን አይሁዶች መግቦ ገና አልረካም ነበር። እግዚአብሔር፥ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሕዛብ እንዲሄዱ ገና አላዘዛቸውም ነበር። ይህን ማለት ግን ክርስቶስ ስለ አሕዛቡ ሕዝብ አያስብም ማለት አይደለም። ሴቲቱ ክርስቶስ አጋንንትን ለማውጣት እንደሚችል በመግለጽ እምነቷን ስታሳይና እግዚአብሔር በረከቶቹን ለአሕዛብ የማዳረስ ባሕርይ እንዳለው ስታመለክት፥ ክርስቶስ ልጇን ፈወሰላት፡፡ የሚገርመው የእግዚአብሔር ልጆች የነበሩት አይሁዶች፥ “ውሾች” ናቸው ከሚሏቸው ከአሕዛብ ያነሰ እምነት ነበራቸው።

 1. ኢየሱስ በአጋንንት የተያዘ ደንቆሮና ዲዳ ሰው ፈወሰ (ማር. 7፡31-37)

የክርስቶስ ፈውስ በአንድ መንገድ ብቻ አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ በቃሉ በመናገር፥ ሌላ ጊዜ በእጁ በመዳሰስ ሰዎችን ይፈውስ ነበር። በዚህ ስፍራ ክርስቶስ ሰውዬውን እንትፍ ብሎ በመዳሰስ ፈውሶታል። ይህም የደነቆሩትን ጆሮዎች ነካ፥ መናገር በተሳነው ምላስ ላይ እንትፍ አለ፥ ከዚያም በጸሎት ወደ ሰማይ ተመለከተ። እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ለጸሎት መልስ ስለሚሰጥ ሁልጊዜም አንድ ዓይነት ስልት ላይከተል ይችላል። ምሥጢሩና ኀይሉ የሚመጣው ከክርስቶስ ማንነት ነው። ሰዎች መንፈሳዊ ውጤት የሚያመጡት በተወሰነ መንገድ በመሄዳቸው፥ ወይም በመስበካቸው እንደሆነ በማሰብ እንዳንሳሳት መጠንቀቅ አለብን። ውጤቶችን የሚያመጣው የአሠራር መንገድ ሳይሆን፥ እዚአብሔር ራሱ የሚፈጽመው ተግባር ስለሆነ፥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከእውነት የራቀ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር አህያን ለማናገር ከቻለ (ዘኁል. 22፡28) ማንንም ሰው ሊያናገር ወይም የፈለገውን መንገድ ለክብሩ ሊጠቀም ይችላል።

ሰዎችን ያስደነቀው የክርስቶስ መፈወስ ብቻ ሳይሆን፥ ሁሉንም በሚገባ መፈጸሙ ነበር። ነገሮችን የምናከናውንበት መንገድ ነገሮችን ከማከናወን እኩል አስፈላጊ ነው። ያለ መልካም ዝግጅት የይድረስ ይድረስ ተግባር ብናከናውን ድርጊቱ ግምት ላይ ይጥለናል። ይህን ብናደርግ ለእግዚአብሔር ክብር ሳናስብ የራሳችንን ፍላጎት የምንፈጽም መሆናችንን ያሳያል። ዓለምን የፈጠረውና ሁሉም «መልካም ነው» ያለው እግዚአብሔር፥ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ እንድናከናውን ይፈልጋል። ከሥራ ላለመባረር፥ በትምህርት ቤት ከክፍል ወደ ክፍል ለማለፍ ወይም መንፈሳዊ ለመምሰል ላይ ላዩን ከመጣር ይልቅ፥ ፍሬ ያለው ሥራ ከልባችን ለመሥራት መትጋት አለብን፡፡

የውይይት ጥያቄ ሀ) በግማሽ ልብ የተሠሩ ነገሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ ከተሠሩት እንዴት ይነጻጸራሉ? ይህ ምን ልዩነት ያስከትላል? ) ሥራችን ባሕርያችንንና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሳየው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ትምህርት የማስተማርንና የስብከት አገልግሎታችንን እንዴት ሊለውጠው ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)