የሕይወት እንጀራ

አስተምህሮ ክርስቶስ እና ደኅንነት

ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ነው 

This entry is part 5 of 95 in the series አስተምህሮ ክርስቶስ እና ደኅንነት

ጥያቄ፡- ሀ) መዝሙር 139፡1-4፥ 17-18፥22-23 እንብቡ። እግዚአብሔር ከሚያውቃቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ለ) ማርቆስ 2፡8፤ ዮሐንስ 1፡48} 6፡64፤ 16፡30፤ 21፡17 እንብቡ። ኢየሱስ የሚያውቃቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?  እግዚአብሔር ሁሉንም ያውቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ከሚወደዱ ክፍለ ምንባቦች ውስጥ መዝሙር 139 አንዱ ነው። ይህ ምዕራፍ እግዚአብሔር ከሚያውቃቸው ነገሮች መካከል ጥቂት ምሳሌዎችን (ናሙናዎችን) ይፈነጥቃል። ይህ መዝሙር እግዚአብሔር ስለ እኛ ሁሉንም እንደሚያውቅ ይነግረናል። እርሱ አሳባችንን፥ ሥራችንን፥ የምንናገራቸውን ቃላት ገና ሳንናገራቸው አስቀድሞ ያውቃል። እግዚአብሔር ስለ እኛ ያለው እውቀት ፍጹም ምሉዕ ነው።  ጌታ ኢየሱስ ይህን ስለ ሰዎች ያለውን ፍጹም እውቀት በምድር ላይ ላለ ገልጾታል። እርሱ ሽባውን ሰው ከመፈወሱ አስቀድሞ ፈሪሳውያን ምን እንደሚያስቡ ያውቅ ነበር። ናትናኤል ከእርሱ ጋር ከመገናኘቱ በፊት፥ የት እንደነበረ ያውቅ ነበር። እንደዚሁም ይሁዳ ራሱ ከማወቁ አስቀድሞ፥ አሳልፎ እንደሚሰጠው እርሱ ያውቅ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ ይገነዘቡ ነበር (ዮሐንስ 16፡30፤ 21፡17)። ኢየሱስ ሁሉን ነገር፥ በተለይም የሰዎችን አስተሳሰብ ማወቁ፥ እርሱ እግዚአብሔር ለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው።  ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ ስለ እናንተ ሙሉ በሙሉ ማወቁ እንዴት መጽናናትን ይሰጣችኋል? ቢያንስ በሁለት መንገዶች ለጹ። ለ) ኢየሱስ ስለ እናንተ ሙሉ በሙሉ ማወቁ የበደለኛነት ስሜት የሚያሳድርባችሁ ወይም የሚያስፈራችሁ እንዴት ነው? ቢያንስ በሁለት መንገዶች አስረዱ።  ኢየሱስ ስለ እኛ ያለው ፍጹም እውቀት ሊያጽናናንም የበደለኝነት ስሜት ሊያሳድርብንም ይችላል። የሚያጋጥመንን ሕመማችንና ሥቃያችንን ኢየሱስ የሚያውቅ መሆኑን መረዳታችን ያጽናናል። እንዲሁም ኢየሱስ ፍጹም በሆነ እውቀቱ፥ በተመሰቃቀለ ሕይወት ውስጥ የሚመራን መሆኑን ማወቃችን ያጽናናል። ኢየሱስ ለእኛ የሚበጀንን ማወቁ ያጽናናናል። ነገር ግን ኢየሱስ አሳባችንን፥ ስሜታችንንና የልባችንን እውነተኛ መነሣሣት ማወቁን መገንዘባችን የበደለኝነት ስሜት እንዲያድርብንም ያደርጋል። በአንድ ሰው ላይ ስንቆጣ፥ ወይም ስለ ማንነታችን በምስጢር ስንኮራ ወይም የሌላውን ሰው ስንመኝ ኢየሱስ የሚያውቅ መሆኑ ያሳስበናል። ስለሆነም የኢየሱስ ፍጹም እውቀት ያጽናናናል፤ ደግሞም ድርጊታችንን በመግለጥ ይወቅሰናል። ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ነው  Read More »

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ እና ሁሉን የሚገዛ ነው

This entry is part 4 of 95 in the series አስተምህሮ ክርስቶስ እና ደኅንነት

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ባሕርያት አሉት  ትናንትና ኢየሱስን በግልጽ «አምላክ» ብለው የጠሩትን ጥቅሶች ተመልክተን ነበር። ዛሬ ደግሞ ኢየሱስ፥ የእግዚአብሔር ባሕርያት እንዳሉትና እግዚአብሔር የሚፈጽማቸውን ተመሳሳይ ተግባራት እንደሚፈጽም የሚያስተምሩንን ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንመለከታለን።  ኢየሱስ ሁሉን ቻይ እና ሁሉን የሚገዛ ነው ጥያቄ፡- ሀ) መዝሙር 65፡7፤ 89፡9፤ ኤፌሶን 1፡11 እና ኢዮብ 42፡2 አንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ምንን ያስተምራሉ? ለ) ማቴዎስ 8፡26-27፤ 14፡19፤ 28፡18፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡22 አንብቡ። እነዚህስ ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ ምንን ያስተምራሉ? ሐህ ዮሐንስ 13፤ ቆላስይስ 3፡16-17 እና ዕብራውያን 1፡3 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እንደ ተገለጸው አንዳንዶቹ የኢየሱስ ሥራዎች ምንድን ናቸው?  እግዚአብሔር ሁሉን ቻይና ሁሉን ገዢ ነው። ይህ ታዲያ እግዚአብሔር ከባሕርያቱ ጋር የሚቃረኑ ተግባራትን ይፈጽማል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፥ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ ኃጢአትን ሊሠራ አይችልም። እግዚአብሔር ሁሉንም ሊያደርግ ይችላል በምንልበት ጊዜ ሥልጣን ሁሉ አለው፥ ዓለም ሁሉ በሥልጣኑ ሥር ነው፥ ለባሕርያቱ ተጻራሪ ያልሆኑትን ተግባራት ሁሉ ይፈጽማል ማለታችን ነው። መዝሙር 65፡7 እና መዝሙር 89፡9 በፍጥረቶቹ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና የዓለምን ሕዝቦችም በሥልጣኑ እንደሚያስተዳድር ይናገራሉ። በተለይ ኤፌሶን 1፡11 እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉትን ማንኛቸውንም ነገሮች በሥልጣኑ፥ እንደ ራሱ ፈቃድ እንደሚመራ ይገልጻል። በተጨማሪም ኢዮብ 42፡2 ስለ እግዚአብሔር የመፍጠር ችሎታ ይናገራል።  ኢየሱስም እግዚአብሔር መሆኑን የሚያረጋግጥ የማይወሰን ኃይልና ሥልጣን አለው። በመዝሙር 89፡9 ላይ፥ እግዚአብሔር በኃይለኛው የባሕር ማዕበል ላይ ሥልጣን አለኝ እንዳለው ሁሉ፥ ኢየሱስ በማቴዎስ 8፡26-27 ላይ አስደናቂ ምሳሌን አሳይቷል። ማቴዎስ 28፡18 ኢየሱስ በፍጥረታት ሁሉ ላይ ኃይልና ሥልጣን እንዳለው ይነግረናል። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡22 የኢየሱስ ሥልጣንና ኃይል ከመላእክትና ከሌሎችም ኃይላት በላይ መሆኑንና መንፈሳዊ ኃይላትም እንደ ተገዙለት ይገልጻል። ስለዚህ የኢየሱስ ችሎታ እርሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያረጋግጣል።  የኢየሱስ ኃይልና ሥልጣን፤ በአብዛኛው ሰማይና ምድርን በመፍጠር እና ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ በማድረግ ሥራው ውስጥ በግልጽ ይታያል። እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው። ይሁን እንጂ ዮሐንስ 1፡3 ቃል ማለትም ኢየሱስ ሁሉንም ነገር እንደ ፈጠረ በማያሻማ ሁኔታ ይናገራል። ቆላስይስ 3፡16-17 ይህንን የበለጠ አጉልቶ ይገልጸዋል። ኢየሱስ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጥሯል። ይህ መናፍስት የሆኑትንም ሁሉ ያጠቃልላል። ፈጣሪያቸው እንደ መሆኑ፥ እርሱ ከሁሉም ነገር በፊት ነበር። ሁሉንም ነገር በሥርዓት አድርጎ ደግፎ የያዘ እርሱ ነው (ዕብ 1፡3)። መጽሐፍ ቅዱስ ህልውና ያለውን ሁሉ ኢየሱስ ፈጠረ ሲል በግልጽ ይናገራል። እንግዲህ ይህ ሁሉ እርሱ እግዚአብሔር ለመሆኑ ምስክር ነው።  ጥያቄ፡– የኢየሱስ ታላቅ ኃይልና ሥልጣን እንዴት መጽናናትን ይሰጣችኋል? ቢያንስ ሁለት መንገዶችን ጻፉ።  የኢየሱስ ኃይልና ሥልጣን በብዙ መንገዶች ያጽናናናል። ኢየሱስ ወደ ሕይወታችን የሚመጣውን ነገር ሁሉ ይቆጣጠራል። ስለዚህ እርሱ ሳያውቅ በድንገት የሚደርስብን ነገር ሊኖር አይችልም። ኢየሱስ ለዓላማው ብሎ ካልፈቀደ በስተቀር፥ ሰብአዊም ሆነ አጋንንታዊ አደጋ ሊደርስብን ከቶ አይችልም። በእነዚህ አደጋዎች ላይም እርሱ ድልን እንድንቀዳጅ ይረዳናል። ኢየሱስ ለከበረ ዓላማው ካልፈቀደ በስተቀር፥ ምንም ዓይነት በሽታ እንደማያጠቃን እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። በሽታውንም እንድንቋቋም እርሱ ኃይልን ይሰጠናል። የኢየሱስ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር፥ ፈተናም ሊያጋጥመን አይችልም። በፈተናም ላይ ድልን እንድንቀዳጅ እርሱ ኃይልን ይሰጠናል (1ኛ ቆሮ. 10፡13)። ኢየሱስ ሕይወታችንን ፍጹም ወደሆነ ፈቃዱ እንደሚመራ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን (ምሳሌ 3፡5-6)። ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ እና ሁሉን የሚገዛ ነው Read More »

የክርስቶስ መለኮታዊነት 

This entry is part 3 of 95 in the series አስተምህሮ ክርስቶስ እና ደኅንነት

የመጀመሪያው ርእሳችን ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት የሚናገር ይሆናል። በዛሬው ትምህርታችን ውስጥ ኢየሱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ በግልጽ የሚያስተምሩን ስድስት ክፍለ ምንባቦችን እንመለከታለን። በተቀሩት ቀናት ደግሞ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የክርስቶስን መለኮታዊነት የሚገልጹ ሌሎች መንገዶችን እንመለከታለን።  አዲስ ኪዳን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ፤ ወደ ምድርም ከመጣ በኋላና ምድራዊ ሕይወቱ ከተፈጸመም በኋላ እርሱ አምላክ እንደነበረ ያስተምረናል። ይህን ነጥብ በጥናታችን ውስጥ መላልሰን እናነሣዋለን። ሆኖም ኢየሱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ በሚያስተምሩ ክፍለ ምንባቦች ብንጀምር መልካም ነው። የመጀመሪያዎቹ ክፍለ ምንባቦች ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት በግልጽ ሊገባን በሚቻል መንገድ የሚያቀርቡ ናቸው። ብዙ የሃይማኖት ዘርፎችና ክርስቲያን ያልሆኑ ሃይማኖቶች ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ይክዳሉ። ስለ ኢየሱስ መለኮትነት የሚያስተምሩ እነዚህ ምንባቦች ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ አምላክ አይደለም ብለው ለሚክዱት ወገኖች መልስ ለመስጠት ይረዷችኋል።  ዮሐንስ 1፡1  ጥያቄ፡- ዮሐንስ 1፡1 አንብቡ። ዮሐንስ ስለ ቃሉ ምን ይላል?  ዮሐንስ በወንጌሉ በምዕራፍ 1፡1 ላይ ኢየሱስ «ቃል» መሆኑን ይገልጻል። ወደ ኋላ ወደዚህ ክፍለ ምንባብ መለስ ብለን ዘርዘር ባለ ሁኔታ እናጠናዋለን። ለዛሬው ዮሐንስ ስለ ቃል የተናገረውን እጢኑ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። ዮሐንስ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ አምላክ የብሉይ ኪዳኑ አምላክ እንደሆነና በአንዳንድ ሁኔታም ከእግዚአብሔር እንደሚለይ ይመሰክራል። ምንም እንኳን ሰው እግዚአብሔር ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ ለመገንዘብ ቢያስቸግረንም። ይህ ጥቅል ግን ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በግልጽ ይናገራል።  አንዳንድ የእምነት ክፍሎች ዮሐንስ 1፡1 ኢየሱስ አንዱና እውነተኛው እግዚአብሔር መሆኑን አያስተምርም፥ ይልቅስ እርሱ የአምላክ ምሳሌ ነው፥ ይላሉ። እንደዚሁም በፅርዕ (በግሪክ) በተጻፈው የመጀመሪያው አዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ጥቅስ የሚያስተምረው፥ ኢየሱስ እግዚአብሔርን የሚመስል መለኮት መሆኑን እንጂ እርሱ አንዱና ብቸኛው እውነተኛው እግዚአብሔር መሆኑን አያስተምርም ይላሉ። እነዚህ መናፍቃን አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከሌላው ጋር ወዲያው ደግሞ ያንኑ ሰው መሆን በሥነ አመክንዮአዊ አይችልም። ስለዚህ ጥቅሱ ኢየሱስ አንዱና እውነተኛው ብቸኛው አምላክ ነው ብሎ አያስተምርም ሲሉ ይደመድማሉ።  በአንጻሩ ደግሞ ይህ ጥቅስ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን እንጂ እግዚአብሔርን ይመስላል ብሎ እንደማያስተምር የግሪክ ሊቃውንት ያረጋግጣሉ። ምንም እንኳን አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከሌላው ሰው ጋር ሆኖ፥ ያንኑ ሰው ሊሆን መቻሉ የሚታመን መስሎ ባይታይም፥ ጥቅሱ የሚናገረው ግን ይህንኑ ነው። ስለ ክርስቶስ ማንነት የሚኖረን ግንዛቤ ከመደበኛው የሰው ሥነ አመክንዮአዊ መረዳት ውጭ መሆኑን ማወቅ አለብን። ኢየሱስ በአንድ በኩል አንድና ብቸኛ እውነተኛው አምላክ ነው፤ እንዲሁም እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ነው። ደግሞም ከእግዚአብሔር የተለየ ነው። ዮሐንስ 1፡1 ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስረዳል።  ዮሐንስ 20፡28  ጥያቄ፡- ዮሐንስ 20፡24-29 አንብቡ። ሀ) የተቀሩት ደቀ መዛሙርት ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን ማየታቸውን ለቶማስ በነገሩት ጊዜ፣ ቶማስ በመጀመሪያ ምን ተሰማው? ) ቶማስ በመጀመሪያ ኢየሱስን ባየው ጊዜ፥ ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን ቶማስ እንዲያምን ለማድረግ ምን አደረገ? ሐህ ቶማስ ለኢየሱስ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?  ይህ በዮሐንስ 20፡24-29 የተጻፈ ታሪክ የተፈጸመው ኢየሱስ በፋሲካው እሑድ ጠዋት ከሞት ከተነሣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር። በፋሲካው እሑድ ማታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታይቶ ነበር (ዮሐ 20፡19) ይሁን እንጂ፥ ቶማስ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር ስላልነበረ በተገናኙ ጊዜ ኢየሱስን እንዳዩ ሲነግሩት ተጠራጠራቸው። ሞቶ የነበረ ሰው አሁን እንዴት ሕያው ይሆናል? በማለት ቶማስ ሊሞት ያየው ኢየሱስ ሕያው መሆኑን በእጆቹ ዳስሶ ካላረጋገጠ በስተቀር እንደማያምን ነገራቸው። ከሳምንት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ በዚያው ክፍል ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም አብሮአቸው ነበር። ከዚያም ኢየሱስ ገና እንደ ታያቸው ወዲያውኑ ወደ ቶማስ መለስ አለ። ቶማስ ከሳምንት በፊት የተናገረውን እንዳወቀ በሚገልጽ ሁኔታ ሞቶ የተነሣውና ሕያው የሆነው ያው የበፊቱ ኢየሱስ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ቶማስን ጠራው። የቶማስም ምላሽ «ጌታዬና አምላኬ» ማለት ነበር። «ጌታዬ» የሚለውን ቃል ብቻ ቢጠቀም ኖሮ፥ አክብሮትን ብቻ የሚገልጽ ስለሚመስል፥ ቶማስ «ጌታዬ» ብቻ ሳይሆን «አምላኬ» ማለቱንም ማስተዋል ያስፈልጋል። ቶማስ ከፊት ለፊቱ የቆመው ኢየሱስ፥ እግዚአብሔር መሆኑን ተገንዝቦአል። ጥያቄ፡– ዮሐንስ 20፡30-31 አንብቡ። ዮሐንስ ይህን ስለ ኢየሱስና ስለ ተማስ የሚያወሳ ታሪክ የነገረን ለምንድን ነው?  ዮሐንስ ይህን ታሪክ የነገረን አንድ ነገር ሊያስተምረን ነው። ይኸውም የኢየሱስን ማንነትና እርሱ አምላክ መሆኑን ሊያስተምረን ነው። ቶማስ ኢየሱስን አምላክ በማለቱ እንደ ተሳሳተ ዮሐንስ አይነግረንም። ይልቁንም ይህን ታሪክ ሲነግረን ዓላማው እኛም ኢየሱስን እንደ አምላክ አድርገን እንድንቀበለው ነው።  ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን የሚክዱ አንዳንድ መናፍቃን ቶማስ፥ «አምላኬ» ማለቱ ኢየሱስ ሕያው ሆኖ ስላየው መገረሙን በአንክሮ መግለጹ ነው እንጂ ሌላ ማለቱ አይደለም ይላሉ። ሆኖም ይህ አባባላቸው እውነት ላለመሆኑ ሦስት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፥ ቶማስ ይህን ቃል ለኢየሱስ መናገሩ በቁጥር 28 ላይ ተጽፎአል። ቶማስ ይህን ሲያደርግ ስሜቱን በአንክሮ መግለጹ ወይም እግዚአብሔር አብን መጥራቱ ብቻ አልነበረም። በልቡ ያመነበትን አውጥቶ ለኢየሱስ መናገሩ ነበረ እንጂ። ሁለተኛ፥ ቶማስ ኢየሱስን፤ «ጌታዬ » ብሎታል። እንደዚሁም «አምላኬ» ሲል ኢየሱስን ለማመልከት ነው። ሦስተኛ፥ ከቁጥር 30=31 ባለው ክፍል እንደተመለከትነው፥ ኢየሱስ ልጅም አምላክም መሆኑን እንድናውቅ ዮሐንስ ይህን ታሪክ መተረኩን ይገልጣል። እርሱም ቶማስ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አስቦ እንደ ተናገረ በመጥቀስ የእርሱን መግለጫ በመጠቀም ለእኛም ሊያሳየን ይፈልጋል።  ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በግልጽ የሚያስተምረን ሁለተኛው ክፍል ዮሐንስ 20፡28 ነው።  ዕብራውያን 1፡8-9  ጥያቄ፡- ዕብራውያን 1፡4-9 አንብቡ። ሀ. ልጁ ኢየሱስ ከመላእክት ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? ለ) ቁጥር 6 መላእክት ከኢየሱስ ጋር ለላላቸው ግንኙነት ምን ይላል? ሐ) በቁጥር 7 ላይ እግዚአብሔር መላእክትን ምን ብሎ ጠራቸው? መ) ከቁጥር 8-9 ስለ ልጁ ምን ተባለ?  በዕብራውያን 1፡4-14 ባለው ክፍል ውስጥ ጸሐፊው ኢየሱስ ከማንኛውም መልአክ በላይ መሆኑን ያመለክታል። በቁጥር 4 ላይም ጸሐፊው የእርሱ ነም ከሁሉ በላይ ስለሆነ፥ ኢየሱስ ከመላእክት ሁሉ በላይ ማረግ ያለው መሆኑን ይገልጻል። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። እንደዚሁም ልጁ ከአባቱ ጋር ስላለው ልዩ ግንኙነት ሊያስገነዝበን ስለፈለገ በቁጥር 5 ላይ ከብሉይ ኪዳን ሁለት ክፍሎችን ይጠቅሳል። እነርሱም መዝሙር 2፡7 እና 2ኛ ሳሙኤል 7፡14 ናቸው። በቁጥር 6 ላይ መላእክት ለልጁ እንደሚሰግዱለት ለመግለጽ ዘዳግም 32፡43 ይጠቅሳል። እንደዚሁም መላእክት አገልጋዮች መሆናቸውን ለማስረዳት በቁጥር 7 ሥር መዝሙር 104፡4ን ጠቅሷል። እነዚህ ጥቅሶች ሁሉ (ዕብራውያን 1፡4-7)። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት በላይ መሆኑን ያስረዳሉ። በመጨረሻውም ከቁጥር 8-9 ባለው ክፍል መዝሙር 45፡6-7 ያለውን ቃል ይጠቅሳል። በዚህ መዝሙር ውስጥ ልጁ ሁለት ጊዜ አምላክ ተብሎ ተጠርቷል። ልጁ አምላክ እንደ መሆኑ፥ ለዘላለም የጸና ዙፋን አለው። በዚሁ በዕብራውያን 1፡9 ውስጥ፥ ልጁ አምላክ ተብሎ ቢገለጽም የራሱ የተለየ ሕላዌ እንዳለው ማስተዋሉ ይጠቅማል። በዮሐንስ 1፡1 ውስጥ እንዳለው ትምህርት ይህ በሰብአዊ አስተሳሰብ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ማንነት ወይም ባሕርይ ያለን ግንዛቤ እነዚህ ጥቅሶች ከሚሰጡት ትምህርት ጋር ሊስማማ ይገባል። በዕብራውያን 1፡8-9 ያለው ክፍል ልጁ እግዚአብሔርም መሆኑን በግልጽ ሲያመለክት፥ ነገር ግን የተለየ የራሱ ሕላዌ ወይም ማንነት እንዳለውም ይናገራል።  ቲቶ 2፡12-13  ጥያቄ፡- ቲቶ 2፡12-13 አንብቡ። ሀ) የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ስንጠባበቅ የእግዚአብሔር ጸጋ እንዴት መኖር እንዲገባን ያስተምረናል? ለ) ቁጥር 13 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ ይመጣል ይላል። እርሱ በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንዴት ነው የተገለጸው?  ቲቶ 2፡12-18 ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት በግልጽ ያስተምራል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ ለማስተላለፍ የፈለገው ዋና መልእክት፥ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን ውስጥ ኃጢአትን ተቋቁመን የቅድስና ኑሮ እንዴት መኖር እንደሚያስችለን ነው። የክርስቶስን ዳግም መምጣት በተስፋ ስንጠባበቅ፥ ይህ የጸጋ ተግባር በቅድስና ለመኖር እንድንችል ይረዳናል። ይህ ዳግም ተመልሶ የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? ጳውሎስ «አምላካችንና መድኃኒታችን» ብሎ ይጠራዋል። በአማርኛው ጥቅስ ውስጥ «አምላክ» የሚለው ቃል ኢየሱስን ለመግለጽ ተጽፎአል። በመጀመሪያው፥ ግሪክ «እግዚአብሔር» ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ኢየሱስ መድኃኒታችንና አምላካችን (እግዚአብሔር) ነው። አንዳንድ የእምነት ክፍሎች ጳውሎስ ስለ ሁለት መገለጦች ይናገራል ይላሉ። ይህም ስለ እግዚአብሔር አብ መገለጥ

የክርስቶስ መለኮታዊነት  Read More »

የክርስቶስ አስተምህሮ አስፈላጊነትና ድነት (ደኅንነት) 

This entry is part 2 of 95 in the series አስተምህሮ ክርስቶስ እና ደኅንነት

በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ ከሆኑ መሪ አሳቦች መካከል አንዱ፥ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ርእሰ ጉዳይ ነው። ብዙ ሃይማኖቶች በእግዚአብሔር ያምናሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ለሰዎች የሚገልጥ፤ ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ የዘላለምን ሕይወት ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድና ሰውም አምላክም እንደሆነ የምታምነው። ስለዚህ የክርስቶስ አስተምህሮና እርሱ ለእኛ ያደረገው ነገር፥ ክርስትናን በዚህ ዓለም ካሉት ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ የተለየ ያደርገዋል።  1ኛ ጥያቄ፡- ዕብራውያን 1:1-2 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር ባለፉት ዘመናት ለሰዎች እንዴት ተናገረ? ለ) እግዚአብሔር ለእኛ በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ቀኖች እንዴት ተናገረን?  2ኛ ጥያቄ፡- ዕብራውያን አንብቡ። ወልድ አብን እንዴት ይገልጣል?  ዕብራውያን 1፡1-3 እግዚአብሔር ለሕዝቡ በብዙ መንገዶች እንደ ተናገራቸው ያስገነዝበናል። በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚናገርበት ዋነኛ መንገድ በነቢያት አማካይነት ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ከመጣ በኋላ እግዚአብሔር በአዲስና በተሻለ መንገድ ለሕዝቡ ተናገረ። በልጁ አማካይነት ተናገራቸው። ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለሰው እጅግ በላቀ መልኩ የገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። «እርሱ የክብሩ መነጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ . .» (ዕብ.1፡3)። ኢየሱስ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል በተለይም የእግዚአብሔርን ክብር ለሰዎች ያሳያል።  እግዚአብሔር ሰዎችን የፈጠረው እርሱን እንዲያውቁትና ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዲያደርጉ ነው (ኤር. 9፡23፤ ሆሴዕ 6፡6፤ ዮሐ 17፤ ፊልጵ. 3፡7-10)። እግዚአብሔርን ለማወቅ እጅግ በጣም ጠቃሚ ከሆኑት መንገዶች አንደኛውና ዋንኛው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው። እርሱን በበለጠ እየተገነዘብነውና እያወቅነው ስንሄድ፥ እግዚአብሔርንም በበለጠ ልናውቀው እንችላለን። ስለዚህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ደህና አድርጎ ማጥናት ማንኛውም ክርስቲያን ሊፈጽመው የሚገባ ጠቃሚ ተግባር ነው። እግዚአብሔር የሚፈልግበትን ጠቃሚ ተግባር የሚፈጽም ክርስቲያን ለመሆን ካሻችሁ፥ ጌታ ኢየሱስን ለማወቅ ጊዜ ውሰዱ። ይህ ትምህርት ኢየሱስንና የፈጸመልንን ተግባራት በተሻለ ሁኔታ እንድታውቁ ይረዳችኋል። ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

የክርስቶስ አስተምህሮ አስፈላጊነትና ድነት (ደኅንነት)  Read More »

አስተምህሮ ምንድን ነው? 

This entry is part 1 of 95 in the series አስተምህሮ ክርስቶስ እና ደኅንነት

በቀላል አነጋገር፥ «አስተምህሮ» የሚለው ቃል «ማስተማር» ማለት ነው። ክርስቲያኖችም ብዙ ጊዜ ስለ አስተምህሮ በሚናገሩበት ወቅት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝ በአንድ በተወሰነ ርእሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት ስለሚሰጥ ትምህርት መናገራቸው ነው። በዚህ በትምህርተ መለኮት ማስፋፋት ጥናት መርሐ ግብር ውስጥ የሚጠቀሱ መጻሕፍት አብዛኛዎቹ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያስነብቡ ናቸው። በዚህ አኳኋን መጽሐፍ ቅዱስን መጽሐፍ በመጽሐፍ ማጥናት የመጀመሪያውና በጣም ጠቃሚው መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠናበት መንገድ ነው። የእያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መልእክት አስቀድመን ሳንገነዘብ፥ መላውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፈጽሞ ልንረዳ እንችልም። ሆኖም ግን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ልናጠና የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ መሪ አሳቦችን በመለየትና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ርእሰ ጉዳዮቹ ከሚሰጠው ትምህርት ጋር በማስተያየት ልናጠና እንችላለን። በዚህ አኳኋን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እጅግ በጣም ጠቃሚ መሪ አሳቦችን በምናጠናበት ጊዜ፥ እነዚህን መሪ አሳቦች ከምንኖርበት ዓለም ሁኔታ ጋር አገናዝበን እንዴት እንደምንገልጻቸውና በተግባርም ላይ እንዴት እንደምናውላቸው ለማሰብ ምቹ ሁኔታ እናገኛለን። ይህ የአስተምህሮ (ዶክትሪን) ጥናት ይባላል። አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ርእሰ ጉዳዮችን ጠቅለል አድርጎ ማስተማርና የርእሰ ጉዳዮቹን መልእክቶች ከዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚገናዘብ መልኩ መግለጽ ማለት ነው።

አስተምህሮ ምንድን ነው?  Read More »