የሕይወት እንጀራ አገልግሎት

የስህተት ትምሕርቶች

የቅዱሳንን እጅግ የተከበረ እምነት ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ከስህተት ትምህርቶች መለየት እጅግ ወሳኝ ነው (ይሁዳ 1:3)፡፡ በመጨረሻው ዘመን አንዳንዶች የሚያሳስቱ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ከእምነት እንደሚክዱ መንፈስ ቅዱስ በግልጽ ይናግሯል (1ኛ ጢሞ 4:1)፡፡ ስለዚህ ምዕመናን በነገረ መለኮት እውቀት እንዲጎለብቱና መናፍስትን ሁሉ እንዲመረምሩ የሚረዳ፣ በጥናት ላይ የተደገፈና በታላቅ ጥንቃቄ የተዘጋጀ ትምህርት እነሆ (1ኛ ዮሐ 4:1)፡፡ መጽሐፎቹን በፒ.ዲ.ኤፍ. ፋይል ለማውረድ ወይም እዚሁ (ኦንላይን) ለማንበብ በርእሶቹ ላይ ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡ መልካም ጥናት!

1. የይሆዋ ምሥክሮች የስህተት ትምህርትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ሳይሆን ከዘላለም የነበረ፣ ሁሉን የፈጠረና በባሕርዩ አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምረናል (ዮሐ 1:1-3)፡፡ በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራል (ቆላ 2:9)፡፡ ይህ በጥናት ላይ የተደገፈና በታላቅ ጥንቃቄ የተዘጋጀ ትምህርት፣ የይሆዋ ምሥክሮች የክርስቶስን ዘላለማዊ አምላክነት፣ የመንፈስ ቅዱስን አካላዊነትና የዘላለም ቅጣት ሕልውናን አስመልክቶ የሚያቀርቡትን የስህተት ትምህርት በጠራ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ የሚያጋልጥና ምዕመናን በእውነት ቃል ጸንተው እንዲቆሙ የሚያስታጥቅ ነው (ቲቶ 1:9)፡፡

2. የኢየሱስ ብቻ (Only Jesus / Oneness) የስህተት ትምህርትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ

እግዚአብሔር በአንድ መለኮታዊ ባሕርይ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሦስትነት የዘላለም ሕልውና ያለው አምላክ ነው (ማቴ 28:19)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ አብ ከሰማይ ሲናገር፣ ወልድ በውኃው ውስጥ ሲሆን፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሲወርድ የሥላሴን አብሮነትና አካላዊነት በግልጽ እናያለን (ማቴ 3:16-17)፡፡ ይህ ሥርዓተ ትምህርት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እንደሆኑ፣ ነገር ግን ሦስት የተለዩ ዘላለማዊ አካላት መሆናቸውን በመካድ የሚቀርበውን የ«ኢየሱስ ብቻ» (Modalism / Oneness) የስህተት ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ ጥልቅ አስተምህሮ የሚመረምርና የሚያቃና ነው (2ኛ ቆሮ 13:14)፡፡

3. የእስልምና አስተምህሮና ክርስቲያናዊ ምላሽ

መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም በቀር ሌላ የለም (የሐዋ 4:12)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የዓለም አዳኝ፣ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን የሞተውና ከሙታን የተነሳው ብቸኛው የሕይወትና የእውነት መንገድ እንደሆነ ቅዱስ ቃሉ ያለ ጥርጥር ያስተምረናል (ዮሐ 14:6)፡፡ ይህ በጥናት ላይ የተደገፈና በታላቅ ጥንቃቄ የተዘጋጀ ትምህርት፣ የእስልምና አስተምህሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝነት፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና የመስቀል ላይ ሞት፣ እንዲሁም ስለ መዳን መንገድ የሚያቀርባቸውን እሳቤዎች በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት የሚመረምር ነው (1ኛ ዮሐ 4:2-3)፡፡ ምዕመናን የክርስትናን መሠረታዊ እውነቶች በጥልቀት እንዲረዱ፣ እውነትን በፍቅር እንዲናገሩና ወንጌልን በበሰለና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲመሰክሩ የሚያስታጥቅ ሥርዓተ ትምህርት ነው (ኤፌ 4:15)፡፡

የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ መሪዎችና ምዕመናን እነዚህን የስህተት ትምህርቶች በጥልቀት በመረዳት የክርስቶስን መንጋ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ተኩላነት መጠበቅ አደራ አለባቸው (የሐዋ 20:28)፡፡ ሌሎች ተጨማሪ የስልጠና መጽሐፎችን ለማግኘት የሚሹ ከሆነ የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡- የመጽሐፎችና የስልጠና ማኑዋሎች ማህደር፡፡