የመዳን መንገድ በሮሜ መልዕክት

የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎችን መሰርት በማድረግ የወንጌልን ጣፋጭ ዜና እነሆ። ከዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ሳንወጣ የምስራቹን ቃል ሙሉ ሃሳብ፣ ማለትም የሰውን መንፈሳዊ ሕመም፣ ከዚህ በሸታ የመዳንን አስፈላጊነት እና የፈውሱን የአሁንና የወደፊት ውጤት መመልከት እንችላለን።

ከሰው ልጅ መሰረታዊ ችግር ስንነሳ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 3:23 ላይ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” በማለት የሃጢአትን ዓለማቀፋዊነት እና ውጤት ይነግረናል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ሃጢአት ያለሰራ ሰው የለም። ይህን የሚጠራጠር አንባቢ ካለኝ፣ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ በከፊል የተዘረዘሩትን የሃጢአት አይነቶች እንዲያነብና ራሱን እዛውስጥ እንዲፈልግ ግብዣዬን አቀርባለሁ (ሮሜ 3፡10-18)። በሮሜ 3:23 መሰረት የሃጢአት በሽታ ውጤት ከእግዚአብሔር ክብር መጉደልን አስከትሏል። የእግዚአብሔርን ክብር ከሕይወታችን ላይ ያጎደለው ሃጢአት በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት በቀር በመጨረሻ ይዞን የሚሄድበት አድራሻም በሮሜ 6:23 ላይ በግጽ ተቀምጧል። “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው…”። ይህ ሞት አካላዊ ሞት ብቻ ቢሆን ምንኛ ቀላል በሆነ፣ ነገር ግን ሞቱ መንፈሳዊ ነው። ይህ ሞት ለዘላለም ከእግዚአብሔር ተነጥሎ በስቃይ የመኖር አደገኛ ፍርድ ነው።

ሁሉ እንዲድኑ እንጂ እንዳይጠፉ የሚፈልገው አምላካችን ችግሩን ነግሮን ብቻ ዝም አላለም። መፍትሄውንም አብሮ ጠቁሞናል እንጂ። በሽታችን ሃጢአት ይባላል፤ ውጤቱም የዘላለም ሞት ነው። ነገር ግን፣ “የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ…በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” (ሮሜ 6:23)። የሰው ልጅ በሽታው ሃጢአት፣ ውጤቱ ሞት ሲሆን መድሃኒቱ ደግሞ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ለዚህ አንድ በሽታ መድሃኒቱም አንድ ብቻ ነው። የስኳር በሽታ መድሃኒት ለልብ በሽተኛ መፍትሄ እንደማይሆነው ሁሉ ለሰው ልጅ የሃጢአት በሽታ መፍትሄው መድሃኒአለም (የአለም መድሃኒት ኢየሱስ) ብቻ ነው። እናም ሌላ መድሃኒት በመሞከር ጊዜዎን አያጥፉ ጤናዎንም አያውኩ።

የሮሜ አራተኛው ጥቅስ (ሮሜ 10፡9-10) ደግሞ ከዚህ የሃጢአት በሽታ ለመፈወስ የሰው ድርሻ ምን እንደሆነ ያስረዳናል። እግዚአብሔር፣ የችግራችን ሁሉ ምንጭ ሃጢአት እንደሆነ ነግሮናል። ከዚህ በሽታ ለመፈወስ ካልፈቀድን እጣ ፈንታችን የዘላለም ሞት እንደሚሆንም አስገንዝቦናል። የበሽታውንም መድሃኒት ማለትም ኢየሱስን እንዳው በጸጋው ብዛት በነጻ ሰጥቶናል። ቀሪው የእኛ ድርሻ ነው። እስቲ ጥቅሱ የሚለውን አብረን እንመልከት። “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።” በእጅህ ላይ ያስቀመጥከው መድሃኒት ምንም ያህል ፍቱን እንደሆነ በአለም የተመሰከረለት ቢሆንም እንኳ፣ ወደ ሰውነትህ እንዲገባ ካልፈቀድክ በቀር ምንም እንደማይጠቅምህ ሁሉ፣ ስለ ኢየሱስ ማንበብ፣ ማወቅ፣ መዘመር፣ ወይም ማጥናት በራሱ ካለብህ መንፈሳዊ ደዌ (በሽታ) አይፈውስህም። እውነተኛ መንፈሳዊ ፈውስ ኢየሱስን ከልብ በማመን እና ስለ እርሱ በመመስከር ይጀምራል። ይህም ማለት፣ ለመዋጥ በእጃችን ላይ የያዝነውን መድሃኒት ለህመማችን መፍትሄ እንደሆነ ሳንጠራጠር ወደሰውነታችን እንዲገባ እንደምንፈቅደው ሁሉ መድሃኒታችን ኢየሱስንም ለመንፈሳዊ በሽታችን መፍትሄ እንደሆነ በማመን ወደ ሕይወታችን እንዲገባና ማንነታችንን እንዲቆጣጠር ልንፈቅድለት ይገባል። እምነት ማለት ይኸው ነው። ይህን መድሃኒት የበላና የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። ከመንፈሳዊ ደዌውም ፈጽሞ ነጽቷል፤ ኩነኔም ከቶ የለበትም (ሮሜ 8:1)። ጌታን ማመን ማለት በሽተኛው እኔ ነኝ፣ መድሃኒቴም እርሱ ብቻ ነው ብሎ በእርሱ የማዳን ስራ ላይ ማረፍ ማለት ነው።

የሮሜ አምስተኛ ጥቅስ (ሮሜ 5:1-2) ደግሞ የፈውሳችንን ውጤት እና የማመናችንን ፍሬ ይነግረናል። በማመናችን ምክንያት፣ በሌላ አነጋገር፣ ከሚጠብቀን መንፈሳዊ ሞት ለማምለጥ መድሃኒአለም በሆነውን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነታችንን በመጣላችን ምክንያት ከእንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር ጠላቶች አይደለንም፤ ወዳጆቹ ነን እንጂ። እግዚአብሔር ያዘጋጀውን መድሃኒት በትዕቢት ስላልገፋንና መፍትሄ ሊሆኑን ከቶ የማይችሉትን የራሳችንን ሰው ሰራሽ መድሃኒቶች ለመቀመም አሻፈረኝ ስላላልን፣ ከእንግዲህ ከእርሱ ጋር ሰላም አለን። የሰጠንን መድሃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን በእምነት ወደ ሕይወታችን ስለጋበዝን፣ በዚህ እምነታችን ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት ጸድቀናል። “እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን። በእርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል” (ሮሜ 5:1-2)።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ መድሃኒት በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: