የኦሪት ዘፍጥረት መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ «ዘፍጥረት» የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት። ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ተጻፈበት ዓላማና ስለ መጽሐፉ አስተዋጽኦ ያገኘኸው ነገር ምንድን ነው?

ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ልናጠናቸውና ልንረዳቸው ከሚገቡን እጅግ ጠቃሚ መጻሕፍት አንዱ ዘፍጥረት ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በዘፍጥረት ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ቢያውቁም እንኳ አብዛኛዎቹን ጥልቅ ትምህርቶች ግን አያጠኗቸውም። የዚህ መጽሐፍ ዓላማ ዘፍጥረትን በጥልቀት ማጥናት ባይሆንም፥ በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸውንና የተተኮረባቸውን ዋና ዋና የሥነ- መለኮት ትምህርቶች ለመመልከት እንሞክራለን። 

የኦሪት ዘፍጥረት ስያሜ 

ለኦሪት ዘፍጥረት የተሰጠው ስም የመጣው ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ቀደም ሲል አጥንተናል። ዘፍጥረት የሚለው ቃል በመጽሐፉ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች ላይ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ስለ መፍጠሩ በሚናገረው መሠረተ አሳብ ላይ ያተኩራል። እንደግሪኩ ስያሜ መጽሐፉ የሚያተኩረው በተለያዩ ነገሮች «አጀማመር» ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ከዚህ ቀደም ኦሪት ዘፍጥረትን በግል ካነበብከው በመነሣት አጀማመራቸው በመጽሐፉ የሆነ የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር።

በዘፍጥረት ውስጥ የቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍላችንን ለመረዳት በጣም ጠቃሚ የሆኑ የብዙ ነገሮችን አጀማመር እንመለከታለን። ለምሳሌ፡- የፍጥረታትን አጀማመር እንመለከታለን። እግዚአብሔር ፈጣሪ ስለሆነ እርሱ የፍጥረታት ሁሉ ባለቤትና ተቆጣጣሪ ነው። በዘፍጥረት ውስጥ የወንድና የሴትን፥ የጋብቻን፥ የኃጢአትን፥ ስለ ኃጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት፥ የተለያዩ ከተሞችን፥ የነፍስ ግድያን፥ የሥልጣኔ፥ የነገድና የጎሣዎችን፥ የተለያዩ ቋንቋዎችን አጀማመር፥ ወዘተ እናያለን። አብዛኛዎቹም በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ 11 ምዕራፎች ውስጥ ይገኛሉ።

ከብሉይ ኪዳን ታሪክ አንጻር ስናየው ግን በጣም አስፈላጊ ክስተት የሆነው የእስራኤል ሕዝብ አጀማመር ነው። የኦሪት ዘፍጥረት አብዛኛው ክፍል (ምዕራፍ 12-50) ስለ እስራኤል ሕዝብ አጀማመር የሚናገር ነው። ይህም ሕዝብ እግዚአብሔር የመረጠው ነው። 

የኦሪት ዘፍጥረት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡ሀ) የኦሪት ዘፍጥረት ጸሐፊ እንደሆነ በይበልጥ የሚገመተው ማን ነው? ለ) እንደ አንዳንድ ምሁራን አስተሳሰብ ዘፍጥረት የተጻፈው እንዴት ነው? ሐ) ሙሴ የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልክተህ ስለ ሕይወቱ በአጭሩ ጻፍ። መ) ኦሪት ዘፍጥረትን ለመጻፍ ሙሴ የተለየ ብቃት ያገኘው እንዴት ነው?

በዘመናት ሁሉ ሙሴ ዘፍጥረትን ጨምሮ የፔንታቱክ ጸሐፊ መሆኑ ይገመት እንደነበር ቀደም ሲል ተመልክተናል። ጸሐፊው ሙሴ እንደሆነ በዘፍጥረት ባይጠቀስም እንኳ የቀሩቱ የፔንታቱክ መጻሕፍት ግን ሙሴ እንደጻፈው ያሳያሉ። አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በሙሉ እንደ አንድ ክፍል ስለሚቆጠሩ፥ ዘፍጥረትንም የጻፈው ሙሴ መሆን አለበት። ሙሴ ዘፍጥረትን አልጻፈውም ብለን የምናምንበት አንዳችም ምክንያት የለም። ይልቁንም ሙሴ በዘፍጥረት ውስጥ የምናገኘውን ነገር ለመጻፍ በተለየ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ነበር።

ለአይሁድ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበሩ እጅግ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ሙሴ ነበር። ከግብፅ ባርነት አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸው ሙሴ ነበር። ለእስራኤል ሕዝብ ሕግን ለመስጠት እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ሙሴ ነበር። አይሁድ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዘወትር «የሙሴ ሕግ» ብለው የሚጠሩት ስለዚህ ነበር። ሙሴ ነቢይ፥ ካህን፥ ሕግ ሰጭ፥ ፈራጅ፥ አማላጅ፡ እረኛ፥ ተአምራት አድራጊና የአይሁድ ሕዝብ የፖለቲካ መሥራች ነበር።

ሙሴ የተወለደው ሌዊ ከተባለው የእስራኤል ነገድ እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ወላጆች ነበር። ነገር ግን የተወለደው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በግብፃውያን ባርነት ሥር ወድቆ፥ ግብፃውያንም እስራኤላውያን የሆኑ ወንዶች ልጆች ሁሉ በሚወለዱበት ጊዜ እንዲገደሉ ሕግ ያወጡበት ጊዜ ነበር። ግብፃውያን ይህንን ያደረጉበት ምክንያት እስራኤላውያን በቁጥር እጅግ ብዙ ይሆኑና ከዚህ ቀደም ሐይክሶሳውያን እንዳደረጉት ሊገለብጡን ይሆናል ብለው ፈርተው ስለ ነበር ነው። በእምነታቸው ጽናት የሙሴ ወላጆች ሊደብቁት እስከሚችሉበት ጊዜ ድረስ አሳደጉት። ሊደብቁት ከማይችሉበት ጊዜ ላይ ሲደርሱ ግን እግዚአብሔር እንደሚታደገው በመተማመን በዓባይ ወንዝ ዳር አስቀመጡት። የግብፅ መሪ የነበረው የፈርዖን ሴት ልጅ ባገኘችው ጊዜ ወደ ቤቷ ወስዳ እንደ ግብፃዊ አሳደገችው። የሙሴ ሕይወት እያንዳንዳቸው 40 ዓመታት በሆኑ ሦስት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

  1. 40 ዓመታት በግብፅ – በፈርዖን ቤት ውስጥ፡- በእነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ ሙሴ በሁለት የተለያዩ ባሕሎች ትምህርት አደገ። በመጀመሪያ፥ በአይሁድ ሃይማኖትና ከአባቶች በተወረሰ ትምህርት አደገ። ይህ የሆነው ለጊዜውም ቢሆን ያሳድጉት ዘንድ ኃላፊነቱ በተሰጣቸው በእኅቱ ማርያምና በእናቱ ነበር (ዘጸ. 2፡7-10)። ሁለተኛ፥ ሙሴ እንደፈርዖን ልጅ ሆኖ የማደግ ዕድል በማግኘቱ በዚያ ዘመን ሊኖር የሚችለውን ትምህርት ሁሉ ቀስሞ ነበር (የሐዋ. 7:22 ተመልከት)። ግብፅ በዚያን ዘመን እጅግ የሠለጠነች አገር ስለነበረች፥ ሙሴ እጅግ የተማረ ሰው ነበር ማለት ነው። እስጢፋኖስ ሙሴ «በቃልና በሥራው ሁሉ የበረታ ሆነ» ይላል።

ሙሴ ይህንን ሁሉ ትምህርት በመቅሰሙ፥እግዚአብሔር በኋላ ዘፍጥረትን ጨምሮ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዲጽፍ ተጠቀመበት። አይሁዳውያን ከነበሩት ወላጆች ስለ ወገኖቹ እንደሰማ ጥርጥር የለውም። ወደ ኋላ ተመልሶ እስከ አዳምና ሔዋን፥ ኖኅ፥ በተለይም አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብና ዮሴፍ ያለውን የሕዝቡን አፈ ታሪኮችን ያውቅ ነበር። በግብፅ ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት ስለአለፈው ጊዜ የሚናገሩ ታሪኮችን የማየት ዕድልም ገጥሞት ነበር። ይህ ታሪክ የዓለምን አፈጣጠር፥ በኖኅ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውኃ፥ የዓለምን መከፋፈል ወዘተ የሚጨምር ነው። ሙሴ ዘፍጥረትን ለመጻፍ በጣም ብቁ ሰው ነበር።

በእነዚህ 40 ዓመታት ሙሴ እስራኤላዊ እንጂ ግብፃዊ እንዳልሆነ አልዘነጋም ነበር። ካደገ በኋላ አንድ ውሳኔ ለማድረግ ተገደደ። ውሳኔውስ ዓለማዊ የሆነ ዕድል ባለበት በፈርዖን ቤት ለመቆየት? ወይስ እግዚአብሔር የተለዩ የቃል ኪዳን ሕዝቡ አድርጎ ከመረጣቸውና አሁን ባሮች ከሆኑት ሕዝብ ጋር ማበር ይሆን? 

የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 11፡24-26 አንብብ። ሀ) ሙሴ ያደረገው ምርጫ ምን ነበር? ለ) ዛሬ ይህንን ምርጫ ማድረግ ያለብን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

ሙሴ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት የተመረጠ መሪ እንደነበር ተረድቶ ነበር (የሐዋ. 7፡25)። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጊዜ ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ ኃይል ነፃ ሊያወጣቸው ሞከረ። ስለዚህ አንድን ሰው ከገደለ በኋላ የፈርዖንን ቤት ትቶ ከግብፅ መሸሽ ግድ ሆነበት።

  1. 40 ዓመታት በምድያም ምድረ በዳ፡- በሰው አመለካከት የሚቀጥሉት 40 ዓመታት የባከኑ ይመስላሉ። ሙሴ በጣም የተማረ ሰው ቢሆንም በግ ማገድ ጀመረ። በእግዚአብሔር አመለካከት ግን በሙሴ ሕይወት ይህ በጣም አስፈላጊ ጊዜ ነበር። ምድረ በዳውና በግ ማገዱ እግዚአብሔር ሙሴን የእስራኤል ሕዝብ መሪ ወይም እረኛ ለማድረግ የሚያስተምርበት ቦታና ሥራ ነበር። በምድረ በዳው እግዚአብሔር በትምህርቱና በችሎታው የነበረውን ትምክሕት በማስወገድ ሙሴን ትሑት አደረገው። ሙሴ ትሑት ከሆነና እግዚአብሔር በሕይወቱ እንዲሠራ በእርሱ ብቻ ከታመነ፥ ታላቅ ሥራን ይሠራ ዘንድ የእግዚአብሔር መገልገያ ለመሆን ተዘጋጅቷል ማለት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሙሴን በኃይል ይገለገልበት ዘንድ ትሑት ሊያደርገው ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? ለ) የእግዚአብሔርን ሕዝብ በምንመራበት ጊዜ በችሎታችንና በእውቀታችን ስለ መመካት ይህ ምን ያስተምረናል? ሐ) ከሙሴ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መኖር ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ምን ለመማር ትችላለህ?

  1. 40 ዓመታት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከግብፅ ወደ ከነዓን መምራት፡- አንድ ቀን እግዚአብሔር ሙሴን በሚቃጠል ቁጥቋጦ ውስጥ ተገናኘውና ወደ ግብፅ ተመልሶ እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ በማውጣት እንዲመራቸው ጠራው። ሙሴ ወደ ግብፅ ለመመለስ ቢፈራም፥ በመጨረሻ ከእግዚአብሔር ጋር ተስማማ። እግዚአብሔር ሙሴን በፈርዖን ፊት ስለ እርሱ ሆኖ ይናገር ዘንድ ተገለገለበት። ሙሴ ያደረገው በፈርዖን ቤተ መንግሥት በመሆኑ በፈርዖን ዘንድ እውቅናን ማትረፉ አያጠራጥርም። አሥር ታላላቅ ተአምራዊ መቅሠፍቶችን በግብፅ ላይ በማምጣት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ነፃ አውጥቶ በሙሴ አማካይነት 40 ዓመታት በምድረ በዳ መራቸው። በእነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ እግዚአብሔር ሙሴን ፊት ለፊት ተገናኘው። እግዚአብሔር ለሙሴ ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ድረስ የተጻፈውን ሕግ ሰጠው። ሙሴን ኦሪት ዘፍጥረትን፥ ዘጸአትን፥ ዘሌዋውያንን፥ ዘኁልቁንና ዘዳግምን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል። ይህ ሁሉ ቢሆንም እንኳ ሙሴ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዘ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ታገደ (ዘኍ. 20፡1-13)። ሕዝቡን እስከ ከነዓን ድንበር ድረስ አደረሳቸው። የተስፋይቱን ምድር በተራራ ጫፍ ላይ ሆኖ ከተመለከታት በኋላ ሞተ።

የውይይት ጥያቄ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር እንዴት ኃጢአትን አክብዶ እንደሚያየው ይህ ምን ያስተምረናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: