የኦሪት ዘኁልቁ መግቢያ

እስካሁን ድረስ ከፔንታቱክ መጻሕፍት መካከል የመጀመሪያዎቹ ሦስቱን ማለት ዘፍጥረት፥ ዘጸአትና ዘሌዋውያንን አጥንተናል። በዘፍጥረት እግዚአብሔር፥ አይሁድ የራሱ የተለዩ ሕዝብ እንዲሆኑና እንዲያገለግሉት እንዴት እንደመረጣቸው ተመልክተናል። በዘጸአት ደግሞ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባርነት እንዴት እንደተቤዣቸው አይተናል። ዘሌዋውያን የተዋጁ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ሆነው መኖር ይችሉ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ለአይሁድ ሕዝብ ስለሰጣቸው ሕግጋት ይናገራል። ዛሬ ደግሞ የእስራኤል ሕዝብ እምነትን በማጣቱ ምክንያት በእግዚአብሔር ተቀጥቶ በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት እንደተንከራተተ የሚናገረውን ኦሪት ዘኍልቁን እናጠናለን።

የውይይት ጥያቄ ሀ) የክርስቲያን ሕይወት እንደጉዞ የሚቆጠረው እንዴት ነው? ለ) የክርስቲያን የሕይወት ጉዞ ጅማሬ ምንድን ነው? ሐ) የጉዞው መጨረሻስ ምንድን ነው? መ) የራስህን ጉዞ የጀመርከው መቼ ነው?

የክርስቲያን መንፈሳዊ አካሄድ በጉዞ መልክ በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል። የክርስቲያን ሕይወት ዕድሜ ልክ የሚጠይቅ ረጅም ጉዞ ነው። አንዳንዶች ይህ ጉዞ «የመናኝ» ጉዞ ነው ይሉታል። ለክርስቲያኖች ይህ ጉዞ የተጀመረው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በዳኑበት ጊዜ ነው። ጉዞውንም የምናጠቃልለው መንግሥተ ሰማያት ስንደርስ ነው። በጣም አስፈላጊ ነገር የጉዞው መጀመሪያ ሳይሆን፥ መንግሥተ ሰማያት እስክንደርስ ድረስ ጉዞውን እንዴት እንደምንጓዝ ነው። የድልና የመንፈሳዊ እድገት መንገድ ልንጓዝ፥ እንችላለን። ወይም ደግሞ የመንፈሳዊ ሕይወት ሽንፈትና የእምነት ጉድለት ጉዞ ልንጓዝ እንችላለን። የእምነት ጉድለትና አለመታዘዝ የሚታይበት ሕይወት ለመኖር ከመረጥን በግል የምንከፍላቸው በርካታ ዕዳዎች ይኖራሉ።

እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ነጻ ካወጣቸው በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያደርጉትን ጉዞ ጀመሩ። ከሦስት ወራት በኋላ በሲና ተራራ ራሱን ከገለጠላቸውና የእርሱ ሕዝብ በመሆናቸው የተለዩ የሚያደርጋቸውን ግልጽ ትእዛዛት ከሰጣቸው ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኙ። በኦሪት ዘኁልቁ ወደ ከነዓን የሚደረገው ጉዞ ቀጥሉ እንመለከታለን። ከነዓን ለመድረስ ጥቂት ሳምንታት ብቻ ይፈጅ የነበረው ጉዞ 40 ዓመታት ወሰደ። ለምን? ምክንያቱም የእስራኤል ሕዝብ አለማመንና አለመታዘዝ ነበር። ኦሪት ዘኁልቁ በመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞአችን እንዴት መራመድ እንደሌለብን የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን፥ አለማመንና አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ክፉ ፍሬ ያሳየናል። ስለዚህ ከእነዚህ ትምህርቶች በመጠቀም በመንፈሳዊ ሕይወታችን እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝና ለታይታ ሳይሆን በእምነት ለመራመድ መወሰን አለብን።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ባለማመንና ባለመታዘዝ የተጓዝክባቸው ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? በዚያን ጊዜ ምን ሆነ? ለ) ለእግዚአብሔር በመታዘዝና በእርሱ በማመን የኖርክባቸው ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? ሐ) እምነትን በማጣት ከተራመድክባቸው ጊዜያት እነዚህ በምን ይለያሉ?

ኦሪት ዘኍልቁ ከኦሪት ዘጸአትና ዘሌዋውያን የሚቀጥል ታሪክ ነው። እስራኤላውያን ከሲና ተራራ ተነሥተው በከነዓን ምድር መግቢያ ድረስ ያደረጉትን ጉዞ ይገልጻል። በኦሪት ዘኁልቁ ታሪክ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በምድረ በዳ እንዴት እንደፈተናቸው በእግዚአብሔር ላይ ያለማቋረጥ እንዴት እንዳመፁ እንመለከታለን። ሕዝቡ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ እግዚአብሔር ከመፍቀዱ በፊት፥ እንዴት አንድ ትውልድ በሙሉ እንዲጠፋ እንዳደረገ እንመለከታለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኦሪት ዘኁልቁ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ሀ) የኦሪት ዘኁልቁ ዋና ታሪክ ምንድን ነው? ለ) በመዝገበ ቃላት ውስጥ የሚገኘውን የመጽሐፉን አስተዋጽኦ ገልብጥ። ሐ) «ዘኁልቁ» የሚለው ቃል በአማርኛ ምን ማለት ነው? ትርጉሙን የማታውቅ ከሆነ ግዕዝ የሚያውቅ ሰው ፈልገህ ትርጉሙን ለመረዳት ሞክር (የኦርቶዶክስ ቀሳውስት በዚህ ሊተባበሩህ ይችላሉ)።

የመጽሐፉ ርእስ

ከፔንታቱክ መጻሕፍት ውስጥ የአራተኛው መጽሐፍ ርእስ በአማርኛ «ዘኁልቁ» የሚል ሲሆን ትርጉሙም «መቁጠር» ማለት ነው። ይህ ርእስ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አይሁዳውያን ሁለት ጊዜ የመቆጠራቸውን ታሪክ ያመለክታል (ዘኁል.1 እና 26)። የዚህ ርእስ ምንጭ ሴፕቱዋጀንት የተባለው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። 

በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የዚህ መጽሐፍ ርእስ “በምድረ በዳ ውስጥ” የሚል ነው። ይህ ቃል የተገኘው በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኘው የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ከተወሰዱት ቃላት ነው። ይህ ርእስ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ርእሶች በብዙ ረገድ የተሻለ ነው። ምክንያቱም የኦሪት ዘኍልቁ ቃና ታሪክ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ባለማመናቸው ምክንያት ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ እንደተንከራተቱ ስለሚናገር ነው።

ጸሐፊው

እንደቀሩት የፔንታቱክ መጻሕፍት ሁሉ የዘኁልቁ ጸሐፊ ማንነት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የሚያከራክር ሀኖ ቆይቶአል። ክርስቲያኖችም ሆኑ አይሁድ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ሙሴ በመሆኑ ላይ አጥብቀው ይስማሉ። ስለዚህ ዋናው የዘኁልቁ ጸሐፊ ሙሴ መሆኑን ማመን የተሻለ ነው (ዘኁል. 33፡2)። ሙሴ በዘኁልቁ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ነገሮች በቀጥታ ከእግዚአብሔር ተቀብሏል። ዘኍልቁ የተፈጸሙትን አብዛኛዎቹን ነገሮች በግል ተለማምዶአቸዋል። በጊዜው የነበሩትንም ሌሎች መጻሕፍት ተጠቅሞባቸዋል። ለምሳሌ ሙሴ፥ ምሁራን «የበለዓም መዝሙራት» (ዘኁል. 22-24)፥ «የሐሴቦን መዝሙር» (ዘኁል. 21፡27-30) እና «የጌታ ጦርነት መጽሐፍ» ብለው የሚጠሯቸውን መጻሕፍት ኦሪት ዘኁልቁን ለመጻፍ ተጠቅሞባቸዋል (ዘኁል. 21፡14-18 ተመልከት)። በመጽሐፉ ውስጥ ሙሴ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው እንደ ሦስተኛ ሰው በመሆኑና (ዘኁል. 12፡3፤ 15፡22-23) እንዲሁም አንዳንድ የተጻፉ አስተያየቶችም መጽሐፉን በሌላ አቀናባሪ የተዘጋጀ ስለሚያስመስሉት (ምሳሌ፡- ዘኁል. 13፡11፤ 27፡14፤ 31፡53) ሙሴ ከጻፈው ከብዙ ዓመታት በኋላ፥ ሌላ ሰው አቀናብሮት ይሆናል። 

የኦሪት ዘኁልቁ ታሪካዊ ማጠቃለያ

የኦሪት ዘኁልቁ ታሪክ 38 ዓመታት ከ9 ወር የፈጀ ታሪክ ነው። · ይህ መጽሐፍ የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ስለመንከራተታቸው ይናገራል። ታሪኩ በሦስት ዋና ዋና ክፍለ-ጊዜያት ይከፈላል፡-

 1. በሲና ተራራ (ይህ የመገናኛው ድንኳን ተሠርቶ ካለቀበት ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር የክብር ደመና ሕዝቡን መምራት እስከ ጀመረበት ድረስ ያለው የ20 ቀናት ጊዜ ነው) (ዘኁል. 1-10፡11)። 
 2. በምድረ በዳ መንከራተት (ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፃቸው የተንከራተቱበት የ38 ዓመታት ጊዜ) (ዘኍል. 10፡11-20፡13)።
 3. ከቃዴስ እስከሞዓብ ምድር ድረስ የተደረገ ጉዞ (6 ወራት) (ዘኁል. 20፡14-36፡13)። 

የኦሪት ዘኁልቁ አስተዋጽኦ 

 1. እስራኤላውያን በሲና ተራራ (1፡1-10፡11) 
 2. ከሲና ተራራ እስከ ቃዴስ በርኔ የተደረገ ጉዞ (10፡11-13፡25)
 3. የእስራኤላውያን በቃዴስ መስፈርና ያ ትውልድ ሁሉ እስኪያልቅ ድረስ በምድረ በዳ መንከራተታቸው (13፡26-20፡21)። 
 4. ተተኪው የእስራኤል ትውልድ ከቃዴስ እስከሞዓብ ምድር ያደረገው ጉዞ (20፡22-21፡35) 
 5. የእስራኤላውያን በሞአብ ምድር መስፈር (22-36) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የኦሪት ዘኁልቁ መግቢያ”

 1. Evangelist Gebeyehu Yismaw

  እግዚአብሔር በእጅጉ ይባርካችሁ። በበኩሌ አዚህ ድረ ገጽ በሚላክልኝ መንፈሳዊ ትምህርት እየተማርኩ ነው። እንደ ባለ
  አደራ አገልጋይነቴ ለብዙሃን እያስተማርኩበት ነው።
  ተባርካችሁ ቅሩ!!!
  ገበየሁ ነኝ ከአዱስ አበባ, ኢትዮጵያ

  On Tue, Jan 28, 2020, 10:08 PM ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት wrote:

  > tsegaewnet posted: “እስካሁን ድረስ ከፔንታቱክ መጻሕፍት መካከል የመጀመሪያዎቹ ሦስቱን ማለት ዘፍጥረት፥
  > ዘጸአትና ዘሌዋውያንን አጥንተናል። በዘፍጥረት እግዚአብሔር፥ አይሁድ የራሱ የተለዩ ሕዝብ እንዲሆኑና እንዲያገለግሉት
  > እንዴት እንደመረጣቸው ተመልክተናል። በዘጸአት ደግሞ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባርነት እንዴት እንደተቤዣቸው አይተናል።
  > ዘሌዋውያን የተዋጁ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ሆነው መኖር ይችሉ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ለአ”
  >

Leave a Reply

%d bloggers like this: