በዳዊትና በሳኦል መካከል የቀረበ ንጽጽር (1ኛ ሳሙ. 16-20)

ሀ. ዳዊት የእግዚአብሔርን መንፈስ ሲቀበል፥ ሳኦል ግን ክፉ መንፈስ ተቀበለ። እግዚአብሔር ሳኦልን ከናቀ በኋላ፥ የሚቀጥለው የእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን መረጠው። እግዚአብሔር ዳዊትን የመረጠው በውጫዊ መመዘኛ ሳይሆን በልቡ ስለነበረው ነገር ነው (1ኛ ሳሙ. 16፡7)። ዳዊት ትሑትና በእግዚአብሔር ላይ የሚታመን ሰው ነበር። በእጅጉ ኃጢአት ቢያደርግም እንኳ ለኃጢአት ሰበብ ከመስጠት ይልቅ ይቅርታ ለመጠየቅ ፈጣን ነበር። በእስራኤል ከነገሡት ነገሥታ ሁሉ ጨርሶ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ንጉሥ የሆነው ለእግዚአብሔር በነበረው ፍቅር፥ ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ በፍጹም ትሕትና በሰጠው አገልግሎትና ለእግዚአብሔር በነበረው መታዘዝ ነው።

የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ከተለየ በኋላ በዳዊት ላይ መጣ፡፡ በሳኦል ሕይወት ግን በእግዚአብሔር መንፈስ ፈንታ በቀሪው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ያሠቃየው ክፉ መንፈስ አደረበት። ሳኦል ለእግዚአብሔር መታዘዝን እምቢ ስላለ እግዚአብሔር የጥበቃ እጁን ከሳኦል ላይ አነሣ፤ ስለዚህ ሰይጣን በሳኦል ቀሪ የሕይወት ዘመን ሁሉ ወደ እርሱ እየመጣ ያሠቃየው ዘንድ ሙሉ ችሎታ አገኘ። ለሰይጣንና ለክፉ መናፍስት ተጽዕኖ ራሳችንን የምናጋልጠው ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ በምንኖርበት ጊዜ ነው። ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በምንኖርበት ጊዜ ግን ከሰይጣንና ከክፉ መናፍስት እንጠበቅና የእግዚአብሔር መንፈስ ይቆጣጠረናል። የሰይጣንን ሥራዎች የሚወስንና ከልካቸው እንዳያልፉ የሚያደርገው እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ሳይፈቅድለት ሰይጣን ጫፋችንን ሊነካ አይችልም። 

ለ. ዳዊት የሳኦልን መንፈስ ለማረጋጋት ይችል ዘንድ ወደ ቤተ መንግሥት መጣ። ዳዊት ሙዚቀኛ ስለነበር ሙዚቃው ሳኦልን ደስ ያሰኘው ነበር፤ ስለዚህ ሳኦል ከሚታመንባቸው ሰዎች አንዱ ሆኖ የሳኦል የጦር መሣሪያ ተሸካሚ (ጋሻ ጃግሬ) ሆነ። (** የእነዚህን ተግባራት አፈጻጸም ትክክለኛ ቅደም ተከተል መረዳት አስቸጋሪ ነው። በ1ኛ ሳሙ. 17 ያለው ታሪክ – የተፈጸመው በ1ኛ ሳሙ. 16 ላይ ከሚገኘው በፊት ሳይሆን አይቀርም።) ሳኦል ያገለግለው ዘንድ ወደ ቤተ መንግሥቱ የጋበዘው ሰው በእርሱ ምትክ ይነግሥ ዘንድ እግዚአብሔር የመረጠው ሰው መሆኑን መገንዘብ በጣም የሚገርም ነው። ዳዊት በዚህ መልክ ወደ ቤተ መንግሥቱ በመምጣት ያገኘው ልምምድ በእስራኤል ላይ መሪ በሆነ ጊዜ እንደ ጠቀመው አንዳችም ጥርጥር የለንም።

ሐ. ዳዊት በጎልያድና በፍልስጥኤም ሕዝብ ላይ ድልን ተቀዳጀ (1ኛ ሳሙ. 17)። ሳኦል በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ለመቀዳጀት በእግዚአብሔር አልታመነም። ዳዊት ግን ልጅ ቢሆንም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ ጥልቅ የሆነ እምነት ነበረው። ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ስም በመሳደባቸው በውስጡ በተፈጠረው ቁጣ ድልን እንደሚሰጠው በእግዚአብሔር ላይ ተደገፈ። እግዚአብሔርም በጎልያድ ላይ ድልን ሰጠውና እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን እንዲያሸንፉ አስቻላቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህ ታሪክ ለእግዚአብሔር ክብርን መስጠት የሚገባን መሆኑን በሚመለከት ትኩረት ስለመስጠት ምን ያስተምረናል? ለ) በእርሱ ከታመንን የእግዚአብሔር ኃይል ውጤታማ እንደሚያደርገን ምን ያስተምረናል?

መ. የሳኦል ቅንዓትና ዳዊትን ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ (1ኛ ሳሙኤ. 18-26)። የቀሩት የ1ኛ ሳሙኤል ታሪኮች በአብዛኛው የሚያሳዩን ሳኦል በቅንዓት የተነሣ ዳዊትን ለመግደል ያደረጋቸውን የተለያዩ ሙከራዎችን ነው። በተቃራኒው ግን ዳዊት ሳኦልን ለመግደል ልዩ ልዩ አመቺ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም እንኳ እምቢ በማለት ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን አስመሰከረ። ዳዊት በእስራኤል ውስጥ እጅግ ከታወቀ በኋላ ሳኦል በተለያዩ መንገዶች ዳዊትን ለመግደል ሞከረ። ዳዊት ሁለት ጊዜ ያህል የሳኦልን ልብ ለማረጋጋት የሙዚቃ መሣሪያውን በሚጫወትበት ጊዜ ሳኦል ሊገድለው ሞክሯል። በተጨማሪ በጦር ሜዳ እንዲገደል ለማድረግ ፍልስጥኤማውያንን በተለያየ መንገድ በመዋጋት ሁለት መቶ ሸለፈቶች እንደ እጅ መንሻ (ጥሉሽ) ይዞ እንዲመጣ አበረታታው። ዳዊትም ይህ ነገር ተሳካለትና በውጤቱ ሜልኮል የተባለችውን የሳኦልን ልጅ ከንጉሣዊ ቤተሰብ ለማግባት ቻለ። ዳዊት የተከናወነለት የሳኦል ጦር አዛዥ ሆነ። 

ሳኦል በዳዊት ላይ ከነበረው ቅንዓትና ጥላቻ በተቃራኒ፥ የሳኦል ልጅና የእስራኤል ዙፋን ወራሽ መሆን የነበረበት ዮናታን ለዳዊት የነበረው አመለካከት የፍቅር ነበር። በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረው የፍቅር ግንኙነት፥ በቅርብ ጓደኛሞች መካከል ሊኖር የሚገባ የፍቅር ምሳሌ ነው። ዮናታን ዳዊትን ጓደኛ አድርጎ ተቀበለው። እንደ ሳኦል አባባል፥ ዳዊት የሳኦልን መንግሥት የመገልበጥ አሳብ አለው የሚለውን ነገር ዮናታን ለማመን አልፈለገም። በመጀመሪያ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል እንደሚፈልግም አላመነም ነበር። ሳኦል እርሱን ለመግደል በሞከረ ጊዜ ግን፥ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል እንደሚፈልግ ዮናታን አመነ። ከዚያም ከሳኦል ፊት በመሸሽ እንዲሰወር ዳዊትን አስጠነቀቀው። ዮናታን ከዳዊት ጋር ከገባው ቃል ኪዳን በግልጥ እንደምንመለከተው (1ኛ ሳሙ. 20፡12-17)፣ የቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት መሆኑን ዮናታን ተረድቶ ነበር። በዳዊት ላይ ከመቅናት ይልቅ በእርሱና በዳዊት መካከል ያለውን ጓደኝነት እንዲቀጥልና ዳዊትም የእርሱን ዝርያዎች በርኅራኄ እንዲመለከት ብቻ ጠየቀ። ዳዊትም ይህንን ቃሉን በመጠበቅ ከሳኦልና ከዮናታን ሞት በኋላ ለቤተሰቦቻቸው መልካም አደረገ (2ኛ ሳሙ. 9)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሳኦል ለዳዊት የነበረውንና ዮናታን ለዳዊት የነበረውን አመለካከት አወዳድር። ዮናታን ከሳኦል ይልቅ መንፈሳዊ ብስለት የታየበት እንዴት ነው? ለ) በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረው ኅብረት፥ ለእኛም የቅርብ ጓደኝነት ኅብረት ስለማስፈለጉ ምን ያስተምረናል? ሐ) እግዚአብሔር አንድን ሰው መርጦ መሪ ይሆን ዘንድ ቢባርከው መቅናት እንደሌለብን ይህ ምን ያስተምረናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: